ጥበብ በታሪክ ገፅ

ጋዜጠኞችና የተደበቀው ርሃብ ትዝታ

‹‹ጋዜጠኞች የሕዝብ ዐይንና ጆሮ ናቸው›› የሚለው ብሂል አብሮን አድጎ አብሮን ያረጀ ነው:: ጋዜጠኞች ከማናቸውም የሕብረተሰብ ክፍል ቢመነጩ፤ ሙያዊ ግዴታቸውና ተልእኳቸው አንድ ያደርጋቸዋል:: የጋዜጠኛ ብእር የሕዝቡን የእለት ተእለት ሕይወት የሚያዘምር እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም:: ከዚህ ውጭ ብእሩ ቢሰነዘር አንድም ምንደኛ አንድም ሙያዊ ቀርነት ያለው ይሰኛል::እናም ተዘውትሮ ስለጋዜጠኛው ተልእኮና ግብር ሲዘከር፤ ለሕዝብ እውነታና ሃቅ የመሰለፍ ያለያም ያለመሰለፍ አቋሙ ይሰመርበታል:: በተለይም ባንድ አገር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ጋዜጠኛው ሲገዝጥ፤ ሚዛናዊነትን መጠበቁ የግድ ይለዋል:: ይህ ታልሆነ ሕዝብና ጋዜጠኛው ይለያያሉ:: ሕዝብ ሚዛናዊነት የጎደለውን ዘገባ ከመጥላት የበለጠ የሚጠላው የለውም:: ሕዝቡ ባይኑ እያየ ያለውን እውነታ ጋዜጠኛው ከሸፈጠው፤ እጅግ ይነወራል፣ ይጠላል:: የዚህ ጥላቻ መጨረሻውም ሕዝብን ከፊት ለፊቱ እየሄደ ይመራዋል የተሰኘው ጋዜጠኛ፤ እራሱ ተመሪ ይሆንና ከጫወታው ውጭ ይሆናል::

 የጋዜጠኝነት ሙያ በሃገራችን በሥራ ላይ መዋል የጀመረው፤ ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጋዜጣ ከ‹‹አእምሮ›› ልደት በኋላ ነው:: በዚያን ጊዜ ሙያው እጅግ ኋላ ቀር በሆነ ደረጃ ይከውን እንደነበር አንዳንድ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ:: በጽሕፈት መኪና አይጻፍም አይተየብም ነበር:: በእጅ ጽፎ እጅግ ኋላ ቀር በሆነው ዘዴ አባዝቶ ጋዜጣን በማደል ነበር ይሠራ የነበረው:: ባለሙያዎችም ቢሆኑ ሙያዊ ሥልጠናና ዘመናዊ የቀለም ትምህርት ያልነበራቸው ነበሩ:: ሆኖም ሥራቸውን ባላቸው አቅምና ችሎታ አድምተው የሚሠሩ ትጉሃን እንደነበሩ ሰነዶች ይመሰክሩላቸዋል:: ከዚያ ኋላ ቀር የጋዜጠኝነት ሙያ ትግበራ ዘመን በኋላ በየጊዜው ለውጦች ተካሂደዋል:: ባገር ውስጥና በውጭ አገር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ ሳይቀር ሙያዊ ሥልጠና ለጋዜጠኞች የሰጣል:: በሙያው መገልገያ መሣሪያ በኩል ደግሞ በተሻሻለ መተየቢያ፣ ዲጂታል ማተሚያ መሣሪያ፣ ዘመናዊ የፎቶግራፍና የፊልም ካሜራ (from Bolex to digital camera) ፣ ከሪል ወደ ሪል ቴፕ (Reel to Reel tape recorder) ወደ ዲጂታል ቴፕ ሪኮርድርና የእስቱዲዮ ዘመናዊ መሣሪያዎች ሽግግር ተደርጓል:: እነዚህ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የጋዜጠኝነት ትምህርትንና የመገልገያ መሣሪያዎችን እጅግ አዘምነዋል:: ጋዜጠኛው ይህንን የተሸሻለ እውቀትና መሣሪያ ይዞ ሕዝብን በቅንነት የሚያገለግልበት በጎ ተልእኮው ይጠበቃል::

 የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በሃገራችን ዘመን ጠገብ ታሪክ ውስጥ የኛው ጋዜጠኞች አቢይ በሆኑ አውዶች ላይ የተጫወቱትን ሚና በመጠኑ ለማሳየት ነው:: ጋዜጠኞች በጦር ግምባር፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ፣ በልማትና በመሳሰሉት አበይት ክንውኖች ወቅት ተሰልፈው ሙያዊ ግብራቸውን ፈጽመዋል:: ከነዚህ የጋዜጠኝነት ውሎ አውዶች አንዱ፣ በየካቲት 66ቱ ያብዮት ፍንዳታ ዋዜማ ላይ ተከስቶ የነበረውን፣ አሰቃቂውን የወሎና የትግራይ ርሃብ አገዛዘጥ ሚናቸውን ይመለከታል:: ምናልባትም ጋዜጠኞቻችን ይህን ሠራችሁ አልሠራችሁ ተብለው የተፈተኑበትም ትልቁ ጉዳይ ይህ ሳይሆን እንዳልቀረ ታሪክ ያስታውሰዋል:: ጋዜጠኝነትና ሙያዊ ተገብሮ ችሎት ላይ ለጥያቄ የቀረበበት ፈታኝ አጋጣሚ ያ ነበር ተብሎም ይጠቀሳል:: በወሎና በትግራይ ደርሶ የነበረው ክፉ የርሃብ እልቂት የያኔዎቹን ጋዜጠኞቻችንን ከበር በር ያተራመሰና ያናጋ ጉዳይ ነበር::

‹‹የተደበቀው ርሃብ›› እየተባለ የሚጠቀሰው ያ አስከፊ የርሃብ እልቂት፣ በወቅቱ ለሕዝብ እንዲታወቅ ጋዜጠኞቻችን የነበራቸው ሚና ምን ነበር? የውጪዎቹስ ጋዜጠኞች ጉዳዩን እንደምን ዘገቡት? የተደበቀን ሕዝባዊ ጉዳይ ከራሱ ከሕዝቡ ሰውሮ ለማቆየት በጃንሆይ መንግሥት በኩል የተደረገውን ያልተሳካ ሙከራ፤ ጋዜጠኞቻችንን እንደምን አስተናገዱት? እንደምንና እስከምን ድረስ ከእውነታው ጋር ግብ ግብ ገጠሙ? ያሸናፊነት ወይስ የተሸናፊነት ጋዜጠኝነትን ግብር ፈጸሙ? ባድርባይነት ሕሊናቸው ላይ ተኙ ወይስ በሃቀኝነት የድርቁን ሰቆቃ አጋለጡ? የሚሉ ዐቢይ ጥያቄዎችን እያነሳን፤ በ1967 ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረውን የመርማሪ ኮሚሽን የምርመራ መዝገብ እንፈትሻለን::

 ከጦር ኃይሎች ተውጣጥቶ ተቋቁሞ የነበረው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፤ በወቅቱ ዐበይት ትኩረት ሰጥቶባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የተደበቀው ርሃብ ጉዳይ አንዱ ነበር:: ደርግ ይህንን የተደበቀውን ርሃብ ከመነሻው እስከመድረሻው ተከታትሎ ለሕዝብ የሚያጋልጥ አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሟል:: ኮሚቴው ‹‹ምርመራ ኮሚሽን›› በሚባል መጠሪያ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከርሃቡም ባሻገር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት አስተዳደራዊ በደሎች ሁሉ የሚፈትሽ ተደርጎ ነበር የተዋቀረው:: ለዚህ መጣጥፋችን የትኩረት አጀንዳ አድርገን የወሰድነው ግን አንዱን የርሃቡንና የጋዜጠኞችን ጉዳይ በሚመለከት መርማሪ ኮሚሽኑ ያደገውን የማጣራት ተግባር ብቻ ነው::

 በመርማሪ ኮሚሽኑ ውስጥ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ተመርጠው በደርግ የተሰየሙ ብዙዎች ነበሩ:: ከነዚህም እውቅ ሰዎች ማካከል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም (ያኔ አቶ)፣ ዶክተር በረከተአብ ኃ/ሥላሴ፣ አቶ ሁሴን እስማኤል (በኋላ የትምህርት ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ የነበሩ)፣ ኮማንደር ለማ ጉተማ (በኋላ ያዲስ አበባ ኢሠፓ 1ኛ ጸሐፊ የነበሩ)፣ አቶ ባሮ ቱምሳ (የሕግ ባለሙያ)፣ ዶ/ር መኮንን ወ/አምላክ (ከአ.አ. ዩኒቨርስቲ) አቶ ጂሃድ አባቆያስ ከማእድን ሚኒስቴር፣ አቶ ጌታቸው ደስታ (ከጠቅላይ ኦዲት)፣ ኮሎኔል ነጋሽ ወ/ሚካዔል (ከፖሊስ ሠራዊት)፣ ሻምበል ሰላመ ሕሩይ (በኋላ ኮሎኔል ከብሄራዊ ጦር) አቶ መዋእል መብራህቱ (ከፓርላማ የኤርትራ እንደራሴ) እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል::

 መርማሪ ኮሚሽኑ ባደረገው እልክ አስጨራሽ የምርመራ ሥራ፣ ብዙ መቶ ገጾችን የፈጀ የምርመራ ውጤት በወሎና በትግራይ የርሃብ እልቂት ላይ አዘጋጅቷል:: በዘገባውም ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎች በርሃቡ ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳጡ አመልክቷል:: ድርቁ እያየለና እየከፋ መጥቶ ይህን ያህል ሕዝብ ሲፈጅ፤ ‹‹የዜና ማሰራጫዎች እንደምን ሳያሳውቁ ቆዩ? የንስር ዐይንና የቆቅ ጆሮ አላቸው የሚባሉት ጋዜጠኞችስ እንደምን ይህን ግዙፍ እልቂት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሳያጋልጡት ቀሩ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ትናንትም ዛሬም ተጠይቋል:: ‹‹የዜና ማሰራጫዎች ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ የችግሩን አስከፊነት በመሳወቅ ተገቢው እርዳታ በነፍስ አድንነት እንዲቀርብ ለምን አላደረጉም? የሥርዓቱ ጥቅምና ፍላጎት አስጠባቂና ገመና ሸፋኞች ሆነው በቸልተኝነት አለፉት ወይስ ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ያደረጉት ጥረት ነበር?›› ለሚሉትና ለሌሎችም መሪ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሲል መርማሪ ኮሚሽኑ የጋዜጠኞችን በር አንኳኩቶ ነበር:: ኮሚሽኑ ባደረጋቸው የምርመራና የማጣራት ሂደት ውስጥ፤ ጋዜጠኞችን በድርቁ ምክንያት ለጠፋው የሰው ሕይወትና ንብረት ከተጠያቂዎች አንደኞቹ አድርጎ ፈርጇቸዋል::

ኮሚሽኑ፣ በዚያን ጊዜ ከነበሩት ያገራችን ጋዜጠኞች መካከል፣ በአሥራ ሰባቱ ላይ ያደረገው ምርመራና የደረሰበት መደምደሚያ፤ ለዘመነ ደርጎቹም፣ ለዛሬዎቹም፣ ለነገዎቹም ጋዜጠኞቻችን ብርቱ ግንዛቤና ትምህርት የሚሰጥ ነወ:: ይህ የጋዜጠኞች የታሪክ አጋጣሚ ከተራው ጋዜጠኛ እስከ ሚኒስትሩ ድረስ፤ አንድም በምስክርነት አንድም በተጠያቂነት እንዲቀርቡ፣ እንዲፈተኑና እንዲፈተሹ ያደረገ ነበር:: መርማሪ ኮሚሽኑ በተለይ በጋዜጠኞች ላይ ባካሄደው ምርመራ ላይ ተንተርሶ የተጠናቀረው መጣጥፍ የሚከተለውን ይመስላል:: ከምስክሮችና ከተጠያቂዎች የተገኘ መረጃ በወሎ ስለደረሰው ርሃብና እልቂት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለሥልጣኖችንና ሠራተኞችን የሚመለከተውን ኃላፊነት በሚነኩ ጉዳዮች ዙሪያ ከዚህ ቀጥሎ ስሞቻቸው የተዘረዘሩት ሰዎች ለመርማሪ ኮሚሽን ቃላቸውን ሰጥተዋል::

• አቶ በዓሉ ግርማ ………………የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

• አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ….የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

• አቶ ተስፋዬ ሃብትህ ይመር…የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ዋናአዘጋጅ

• አቶ መስፍን ብርሃነ …….……የአዲስ ስዋር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

• አቶ እሸቱ ሸንቁጥ ……የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜና አስተካካይ

• አቶ ማዕረጉ በዛብህ ……………..በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት፣ የእንግሊዝኛ ክፍል ኃላፊ

• አቶ ሳሙዔል ፈረንጅ………… በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋናዳይሬክተር

• አቶ ኤልያስ ብሩ ……………. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፊልም አንሺ

• አቶ ተፈሪ ወሰን………………………… በማስታወቂያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ተጠባባቂ ኃላፊ

• አቶ አበበ አንዱ ዓለም………የዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ

• አቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም………………….በራዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም ክፍል ም/ ዋና ሥራ አስኪያጅ

• አቶ ሣህሉ አሰፋ…………………………በማስታወቂያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ረዳት

• ክቡር አቶ ንጉሤ ኃብተ ወልድ …….. በማስታወቂያ ሚኒስቴር ም/ ሚኒስትር የነበሩ

• ክቡር አቶ ተገኝ የተሻ ወርቅ…………. በማስታወቂያ ሚኒስቴር ም/ ሚኒስትር የነበሩ

• ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚ…………….. የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩ

• በኋላም ደግሞ እኒህ የሚከተሉት ኃላፊዎች ቃላቸውን እንደሰጡ ኮሚሽኑ በዘገባው ላይ አመልክቷል::

• አቶ አድማሱ ባድማ …………………………… የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር

• አቶ መርስዔ ሃዘን አበበ……………………………የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ም/ አዘጋጅ ከላይ ስማቸው ከተዘረዘሩት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መካከል አቶ በዓሉ ግርማ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ አቶ ተስፋዬ ሃብትህ ይመር የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና፣ አቶ መስፍን ብርሃነ የአዲስ ስዋር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፤ አራቱም በሰጡት ቃል፤ ስለ ወሎ ድርቅ በጋዜጣ አንዳችም ነገር እንዳይጻፍ በሚኒስትሩ በዶ/ር ተስፋዬ ገብረእግዚ ተከልክለው እንደነበር ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል:: የዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አበበ አንዱዓለም በበኩላቸው በሰጡት ቃል፤ በወሎ ስለደረሰው ድርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት ወደ ታህሳስና ጥር ገደማ በ1965 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጸዋል:: አቶ አበበ አያይዘውም፤ ‹‹ይሁን እንጂ ድርቅ ገብቷል ብለን እንዳንጽፍ ተከልክለናል›› ሲሉ መስክረዋል:: በተጨማሪም ይህ ትእዛዝ በቃል የተላለፈው ባጠቃላይ ስለ ድርቅ መግባት ማውሳት መንግሥትን ያስወቅሳል ከሚል እሳቤ ተነስቶ እንደሆን አቶ አበበ ለኮሚሽኑ ጠቁመዋል::

አቶ አበበ አንዱ ዓለም በተለይም የወሎውን ድርቅ በሚመለከት አለቃቸውን ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚን፤ ‹‹ በጥር ወር 1965 ዓ.ም. ወሎ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ስለደረሰው ድርቅ ሕዝብ አስተባብረን እርዳታ እንዲገኝ እናድርግ ብዬ ዶክተር ተስፋዬን ብጠይቃቸው ‹ቆይ› ብለውኛል›› ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል::

እኚሁ ተጠያቂ ቀጥለውም፤ ‹‹ዋናው የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ በሚያዝያ ወር ሲቋቋም መቀሌም ወሎም መዋጮ ተደርጓል:: ይህንኑ ገልጸን ሕዝብ እናስተባብር ብዬ ዶ/ር ተስፋዬን ብጠይቃቸው ‹ለኮሚቴው ሃሳቡን አቅርብ› አሉኝ:: እኔም ለክቡር አቶ ሙላቱ ደበበ (ለሊቀ መንበሩ) ይህንኑ ደግሜ ብነግራቸው ‹የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና የሶማሌ ችግሮች እያሉ ባሁኑ ጊዜ መግለጽ አያስፈልግም› የሚል መልስ ሰጡኝ ብለዋል:: ከዚሁ ጋር አያይዘውም አቶ አበበ በሰጡት ቃላቸው፤ ‹‹ከዋናው ኮሚቴ አባሎችም አቶ ታደሰ ሞገሴና አቶ ጸጋዬ ተወልደ ብርሃን ሃሳቤን በመደገፍ፤ ለሕዝብ ይገለጽ ብለው ነበር:: ነገር ግን ሌሎቹ የኮሚቴው አባሎች ስላልደገፉትና ይልቁንም ሊቀ መንበሩ በመንግሥቱ ላይ ችግር ያመጣል ስላሉ በዜና ማሰራጫዎች ሳይተላለፍ ቀረ::›› ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል:: የዜና አገልግሎቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ አንዱ ዓለም ይህንኑ ምስክርነታቸውን በመቀጠልም፤ ‹‹ ከዚያ በኋላ አቶ ለገሠ በዙ (የወሎ ክፍለ ሃገር እንደራሴ የነበሩት) በቴሌቪዥን መግለጫ ሰጡ:: ዶክተር ተስፋዬም አቶ ለገሠ ይሄን መግለጫ እንዲሰጡ ‹ከበላይ ታዝዣለሁ› ብለው ነግረውኝ ስለነበር፤ የአቶ ለገሠ መግለጫ በመንግሥት የታዘዘ ነው ብዬ ገመትሁ›› ካሉ በኋላ፤ ወሎ የተነሳውን ፊልም ከሚከተሉት ባለሥልጣኖች ጋር መመልከታቸውን ገልጸዋል:: አቶ አበበ አሰቃቂውን የወሎ ድርቅ ፊልም ከክቡራኖቹ ከአቶ ጌታሁን፣ ካቶ ሙላቱ ደበበ፣ ካቶ ተገኝ የተሻ ወርቅና ካቶ አሰፋ ይርጉ ጋር እንደተመለከቱት ለመርማሪ ኮሚሽኑ አስረድተዋል:: አያይዘውም፤ ‹‹ ፊልሙ አሰቃቂ ነው:: ፊልሙን ካዩት ሰዎች መካከል ክቡር አቶ ጌታሁን ለሕዝብ እንዲታይ ፈለገው ነበር:: ነገር ግን ለሕዝብ እንዲታይ ስለተከለከለ ሳይታይ ቀርቷል ሲሉ ለኮሚሽኑ የማጠቃለያ ቃላቸውን ሰጥተዋል::

 አቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም ስለ ወሎ ድርቅ ጉዳት የተሰጣቸው ልዩ መመሪያ አለመኖሩን ለመርማሪ ኮሚሽኑ ቢያሳውቁም፤ በነባር ጋዜጠኝነታቸው የማስታወቂያ ሚኒስቴርን አጠቃላይ የውስጥ አሠራር እንዲያስረዱ ተጠይቀው መግለጫ ሰጥተዋል:: በዚህም መገለጫቸው፤ ‹‹ መሥሪያ ቤቱ ከመሠረታቸው ሕግ ይልቅ እለት በእለት ከሚኒስትሩ በሚሰጠው መመሪያ የሚሠራ መሆኑንና መንግሥቱን ያሳጣል ወይም ሕዝቡን ያስቆጣል ብሎ የሚፈራው ነገር እንዳይገለጽ ሲከለከል ቆይቷል:: የረሃብና የድርቅ ነገር፣ የተላላፊ በሽታም ነገር እንደ ኮሌራ ያለ ጉዳይ እንዳይገለጽ የተከለከለበትን ጊዜ አውቃለሁ›› ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል::

ከንጉሠ ነገሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች መካከል የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ም/ ሚኒስትር አቶ ንጉሤ ኃብተ ወልድ (በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሠራተኞች ዲግ ታይገር – Dig Tyger እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት) ለመርማሪ ኮሚሽኑ ቃላቸውን ከሰጡት ሹማምንት መካከል አንዱ ነበሩ:: አቶ ንጉሤ ስለ ድርቁ የሰሙት በጥር ወር 1965 ዓ.ም. እንደነበር ለኮሚሽኑ ገልጸው፤ ማስተባበያ እንዲሰጥ በየካቲት ወር ላይ በሚኒስትሩ እንደታዘዘ መስክረዋል:: አያይዘውም፤ ‹‹ክቡር አቶ ለገሠ በዙ ማስተባበያ በቴሌቪዥን ከሰጡ በኋላ፣ ‹መግለጫው ልክ አይደልም፣ ችግር አለ› የሚል የሕዝብ ድምጽ ስለሰማሁ፤ ችግሩን አጥንተን የህዝብና የመንግሥትን እርዳታ በማስተባበበር ተጋድሎ እንዲደረግ ያስፈልጋል ስል አሰብኩ:: ይህም ጉዳይ በዜና ማሰራጫዎች እንዲገለጽ ስል ለሚኒስትሩ ሃሳብ ባቀርብ፤ ‹ይሄ ጉዳይ በኛ ደረጃ የሚወሰን አይደለም ብለው ከለከሉኝ:: ›› ሲሉ አስረድተዋል:: ክቡር አቶ ንጉሤ አያይዘውም፤ ‹‹ በመጀመሪያ የችግሩን መጠን እንግለጥ ብዬ ባሳስብ፣ ብሞክር፣ አልሆነልኝም ተከለከልኩ›› ብለዋል:: ቆይቶ ግን ችግሩ እየገፋ ሲመጣ፣ በመንግሥት በኩል የተደረገው እርዳታ በመገናኛ ብዙሃን እንዲገለጽ ሚኒስትሩ መፍቃዳቸውን እኚህ ባለሥልጣን መስክረዋል::

 ክቡር አቶ ንጉሤ እንደገለጹት የኋላ ኋላ በሚያዝያ ወር የወሎን ድርቅ የሚያሳየው አሰቃቂ ፊልም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፊልም አንሺው በኤልያስ ብሩ ተነስቶ መጣ:: ‹‹ ለሕዝቡ ይታይ አልን:: የለም ከሕዝብ ከመታየቱ በፊት በኮሚቴ ይታይ ተባለ:: አቶ ጌታሁንም ለሕዝብ ይታይ አሉ:: በሌሎች በኩል ድጋፍ ስላልተገኘ ሳይታይ ቀረ›› ሲሉም ክቡር አቶ ንጉሤ አክለዋል:: ‹‹ የረሃቡ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ስለሚያስረዳ፣ ፊልሙን ሚኒስተሮቹ በሙሉና ንጉሠ ነገሥቱም እንዲያዩትና ከዚያም ለሕዝብ እንዲታይ አሳሰብሁ፣ ግን ሰሚ አጣሁ::›› ብለዋል ም/ ሚኒስትሩ::

 መርማሪ ኮሚሽኑ ከክቡር አቶ ንጉሤ ኃብተ ወልድ የተቀበለው የምስክርነት ቃል ሰፊ ነው:: ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ከተደረገ በኋላ፣ ላለቃቸው ለዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚ ስለፊልሙ ይዘት እንደነገሯቸውና፣ ሚኒስተሩም ለጠቅላይ ሚኒስተሩ አሳውቀው ፊልሙ እንዲታይ እንደሚያሰፈቅዱ እንደገለጹላቸው አቶ ንጉሤ መስክረዋል:: ‹‹በመካከሉም ›› ይላሉ ክቡርነታቸው፤ ‹‹በመካከሉም ግንቦት ደረሰና የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ተጀመረና ጉዳዩ እንዳይገለጥ ሆነ:: ከስብሰባው በኋላ ቀስ በቀስ ሳይጎላ ትንሽ ትንሽ ዜናዎች ቀረቡ:: ባንዳንድ ቀበሌዎች ችግር ደርሷል በማለት መነገር ጀመረ:: ነገር ግን መግለጫው መንግሥት እርዳታ እያደረገ እንዳለ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር::›› ብለዋል:: ‹‹በዚህ ጊዜ›› ይላሉ አቶ ንጉሤ፤ ‹‹በዚህ ጊዜ ሚኒስትሩ ዶ/ር ተስፋዬ ከእህል እጥረት አስተባባሪው ኮሚቴ ከምታገኙት ዜና በስተቀር ስለ ወሎ ችግር አንዳችም መግለጫ እንዳታወጡ ብለው አዘውናል›› ሲሉ ለኮሚሽኑ ሙሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል::

 ክቡር አቶ ንጉሤ በመጨረሻው የምስክርነት ቃላቸው ላይ ስለ ፊልም አንሺው ኤልያስ ብሩ አንድ አስገራሚ ምስክርነት ሰጥተዋል:: ‹‹ ዶ/ር ተስፋዬ ወሎ ሄዶ ፊልሙን የሚያነሳውን ሰው (ኤልያስ ብሩን ማለታቸው ነው) የሚሰጠውን እርዳታ የሚያጋንን ፊልም እንዲያነሳ መመሪያ ሰጥተው ነበር:: እሱ ግን እልቂቱን የሚያሳይ ፊልም በብዛት አንስቶ መጣ:: ይህን በማድረጉም ወቅሼዋለሁ›› ካሉ በኋላ ለዚህ ምክንያታቸውን ሲገልጹ፤ ‹‹ምክንያቱም የመንግሥት እርዳታውን አሰጣጥ ጉዳይ እንዲያጋንን ታዞ የነበረውን ቢፈጽም ኖሮ፤ ሚኒስትሮቹ እንዲታይ ይፈቅዱ ነበር ብዬ ስላመንኩ ነው›› ብለዋል::

ቆራጡ ፊልም አንሺ አቶ ኤልያስ ብሩ መርማሪ ኮሚሽኑ ዘንድ ቀርቦ የእምነት የክህደት ቃሉን ሲጠየቅ፤ ቀደም ሲል ክቡር አቶ ንጉሤ ኃብተ ወልድ የሰጡትን ትክክለኛ ምስክርነት አረጋግጧል:: አቶ ኤልያስ በዚህ የምስክርነት ቃሉ፤ ‹‹የተሰጠኝ መመሪያ መንግሥት የሠራቸውን መጠለያ ጣቢያዎችና በጣቢያዎቹ ውስጥ የሚረዱትን ሰዎች በጠቅላላውም መንግሥት የሚያደርገውን እርዳታ አንሳ የሚል ነበር:: ወሎ ስሄድ ግን የርሃቡ ሁኔታ ካሰብሁትና ከገመትኩት በላይ አሰቃቂ ሆኖ ስላገኘሁት፤ ከመመሪያው ውጭ ያየሁትን በሙሉ የሚያሳይ ሁለት ሺህ ጫማ ፊልም አንስቼ መጣሁ›› ሲል የሃቀኛ ጋዜጠኝነትን ተግባር የፈጸመበትን ቃሉን ሰጥቷል::

 የዛሬው አቶ ኤልያስ ብሩ

 አቶ ኤልያስ ያንን ሁሉ አሰቃቃቂ ትርኢት ባይኑ እያየ ሳይዘግበው ማለፍን አልፈቀደም:: አድርባይነትንና ለሆድ ማደርን አሸቅንጥሮ ጥሎ፤ ለሕሊናው ሲል ይህንን አስደናቂ ሙያዊ ተግባር ፈጽሟል:: ዛሬ በጡረታ ሕይወት ላይ የሚገኘውን ይህንን ጀግና የፊልም ባለሙያ አፈላልጎ የሚሸልመውና ለተወጣው ሙያዊ ግዳጅ የሚያመሰግነው ተቋም ያስፈልጋል:: አርአያነቱ ዛሬም ሆነ ወደፊት በሙያው ላይ ለተሰማሩ ጋዜጠኞችና ፊልም አንሺዎች ማሳያ ነውና!

በሥራው ላይ ብርቱ ባለሙያነቱን የምናውቅለት አቶ ኤልያስ ብሩ፣ ይህንን አሰቃቂ የወሎ ድርቅ እልቂት ያጋለጠው ከዮናታን ዲምብልቢይ አንድ ዓመት አስቀድሞ ነው:: ኤልያስ በ1965 ዓ.ም. በካሜራው ቀርጾ ሲየቀርብና የጃንሆይን መንግሥት ሲያተረማምስ፣ ዮናታን ደግሞ የጉዳዩን ጭምጭምታ ሰምቶ ወደ ወሎ የተጓዘውና የቀረጸው በ1966 ዓ.ም. ነው:: ዮናታን ዲምቢልቢይ በሥራው ትልቅ እውቅናና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ሲያገኝ፣ የኛን ኤልያስ ብሩን እስከ ዛሬ ድረስ ያስታወሰው የመንግሥትም ይሁን የግል ድርጅት የለም::

 ቀጣዩ ተመርማሪ አቶ ሣህሉ አሰፋ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ረዳት ነበሩ:: አቶ ሣህሉ ዮናታን ዲምብልቢይ የተባለው ዝነኛው እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ በመስከረም 1966 ዓ.ም ቡድኑን ይዞ ወደ ወሎ ሲጓዝ አብረውት የተመደቡለት ባልደረባው ነበሩ:: ላቶ ሣህሉ የተሰጠው የሥራ መመሪያ፤ መንግሥትን የሚያስወቅስ ነገር በፊልም እንዳይነሳ እንዲከላከሉ ነበር:: እቦታው ደርሰው አሰቃቂውን ረሃብ ካዩ በኋላ ግን እምባቸውን አፍስሰው፤ ‹‹በኔ ላይ የመጣ ይምጣ እንጂ ይህንን አሰቃቂ ሁኔታ በፊልሙ ማንሳት አለበት›› ብለው ዮናታን መፍቀዳቸውን ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል:: ከወሎ እንደተመለሱም የችግሩን አስከፊነትና ጥልቀት ላለቃቸው ላቶ ተፈሪ ወሰን ማስረዳታቸውን በሰጡት ምስክርነት ላይ አስመዝግበዋል:: አቶ ተፈሪ ወሰንም ሲጠየቁ ይህ አቶ ሣህሉ የሰጡት ምስክርነት ትክክል መሆኑን ለመርማሪ ኮሚሽኑ አረጋግጠዋል:: በተጨማሪም አቶ ተፈሪ በሰጡት ምስክርነት፤ በዶ/ር ተስፋዬ ትእዛዝ ለንደን ድረስ ተጉዘው ዮናታን ዲምብልቢይ የቀረጸው ፊልም እንዳይሰራጭ እንዲከላከሉ ተመድበው እንደነበር ገልጸዋል:: ነገር ግን ለንደን ደረስ ተጉዘው ዲምብልቢይን እንዳያሰራጨው ቢጠይቁትም እሺ የሚል ሆኖ ስላላገኙት ያላንዳች ውጤት ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ለኮሚሽኑ አረጋግጠዋል:: የዮናታን ዲምብልቢይ አሰቃቂና አሳዛኝ ፊልም፤ በደርግ ትእዛዝ መስከረም 1 ቀን፣ 1967 ዓ.ም. ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲታይ ተደርጎ፤ ሕዝብን እምባ በእምባ አራጭቷል:: መስከረም ሁለትም የጃንሆይ ከዙፋናቸው መውረጃ ቀን ሁኗል::

 ዮናታን ዲምብልቢይ

 ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣኞች አንዱ የነበሩት አቶ ተገኝ የተሻወርቅ ለመርማሪ ኮሚሽኑ የበኩላቸውን ምስክርነት ከሰጡት ተጠያቂዎች አንዱ ነበሩ:: ‹‹ስለወሎ ርሃብና ስለ ጉዳዩም የተሰጠ ትእዛዝ መኖር አለመኖሩን አላውቅም›› ብለዋል አቶ ተገኝ:: አያይዘውም፤ ‹‹ በመጀመሪያ ጊዜ በወሎ ርሃብ እንደነበር በጥር ወር 1965 ዓ.ም. ተሰደው በመጡ ሰዎች ዜና ምክንያት መስማታቸውን ኋላም ፊልሙን ካዩት ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል:: አቶ ተገኝ ምስክርነታቸውን ሲያጠቃልሉም፤ ‹‹ ማናቸውም ዜና እንዲገለጽ ወይም እንዳይገለጽ የመወሰን ወይም ፖሊሲ የማውጣት ሥልጣን አልነበረኝም›› ብለዋል::

 የማስታወቂያ ሚኒስቴር የበላይ ባለሥልጣን የነበሩት ዶክተር ተስፋዬ ገብረ እግዚ ለመርማሪ ኮሚሽኑ የበኩላቸውን የተጠያቂነት ቃል ሰጥተዋል:: ሚኒስትሩ፤ ‹‹ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የተቋቋመበትን ሕግ አንብቤ አላውቅም›› ሲሉ ያስረዱ ሲሆን፤ አያይዘውም መሥሪያ ቤቱ በልማድ ሲያያዙ የመጡትን መመሪያዎች ይዞ ይሠራ እንደነበረና እርሳቸውም ያዘጋጇቸው ሦስት መመሪያዎች የቆየውን ልማድ የሚያጠቃልሉ መሆናቸውን ገልጸዋል:: ዶ/ር ተስፋዬ የመመሪያዎች ግልባጮች ቀርበውላቸው ከተመለከቷችው በኋላ፤ በውስጣቸው ሕዝቡንና የሕዝብን ጥቅም የሚነኩ ነገሮች በጋዜጣ፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን እንዳይወጡ የተደረገው ድርጊት መሥሪያ ቤቱ በሕግ ተገልጾ ለተቋቋመበት የማሳወቅና የማስተማር ዓላማ ጋር ተቃራኒ መሆኑን አምነው ቃላቸውን ለኮሚሽኑ ሰጥተዋል:: የወሎ ደርቅ ጉዳይም በዜና ማሰራጫዎች እንዳይገለጽ የተደረገው በዚሁ መመሪያ መሠረት መሆኑንም ገልጸዋል:: ዶ/ር ተስፋዬ የወሎ ድርቅ ክስተትን ማወቅ የቻሉት ከየካቲትና መጋቢት ወር ጀምሮ እንደሆነ ሲገልጹ፤ በሚያዝያ ወር አንድ ፊልም አንሺ (ኤልያስ ብሩ መሆኑ ነው) ወደ ሥፍራው ሄዶ የተሰጠውን እርዳታ እንዲያነሳ ማዘዛቸውን መስክረዋል::

 በግንቦት ወር 1965 ዓ.ም. የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት አሥረኛ ዓመት ክብረ በዓል ከመካሄዱ በፊት የወሎ ድርቅ፣ የሶማሊያና የተማሪዎች ጉዳይ በዜና ማሰራጫዎች እንዳይገለጽ በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ በቃል መታዘዛቸውን አሳውቀዋል:: በዓሉም ካለፈ በኋላ እስከ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ የወሎን ድርቅ የሚመለከት አንዳችም ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳልወጣ ሚኒስትሩ ለኮሚሽኑ ተናዘዋል:: አያይዘውም ‹‹ማናቸውም ማስታወቂያ (ፐብሊሲቲ) ንጉሠ ነገሥቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካወቁና ከፈቀዱ በኋላ ነበር የሚወጣው›› ሲሉም አሰምረውበታል::

እኚህ ሚኒስትር ቀደም ብለው እነ አቶ ተፈሪ ወሰን፣ አቶ ሣህሉ አሰፋ፣ አቶ ኤልያስ ብሩ የሰጡትን ምስክርነት በሙሉ በአዎንታ መቀበላቸውን ለኮሚሽኑ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል:: ‹‹ አቶ ተፈሪ ወሰን ለንደን ሂዶ የዲምብልቢይ ፊልም እንዳይታይ እንዲያደርግ… ፋክት ሺት የተባለውን የድርቅ ማስተባበያ ጽሑፍ እራሴ አዘጋጅቼ በየኤምባሲው የማስተባበል ሥራ እንዲሠራ አድርጌያለሁ›› ሲሉ የእምነት ቃላቸውን ሰጥተዋል:: ክብር ዶ/ር ተስፋዬ ለምን እንዲህ ያለ መመሪያና ትእዛዝ እንደሰጡ በኮሚሽን ሲጠየቁ፤ ‹‹…እኔ በጊዜው የታዘዝኩትን ፈጽሜያለሁ:: የማሳወቅ ጉዳይ መንግሥት ያዘዘውን ፖሊሲ ማሳወቅ ብቻ ነው:: ምክንያቱም የዜና ማሰራጫዎቹ የመንግሥት ስለሆኑ ነው›› ብለው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የንጉሡ ትእዛዝ አስፈጻሚ እንደሆኑ አሳውቀዋል::

ከዚህ ተደብቆ ከነበረው የወሎ ርሃብ የመርማሪ ኮሚሽን ዘገባ እንደምንረዳው፤ የወቅቱ ጋዜጠኞች ነጻ ሁነው ነጻ ሙያዊ ግዳቸውን ለመወጣት ችግር እንደነበረባቸው ነው:: ከዜና ማሰራጫና ከጋዜጠኝነት መራሄ ግቦች ውጭ ሥራዎች ይሠሩ እንደነበር ባለሙያዎቹና ኃላፊዎቹ ከሰጡት ቃል መረዳት ይቻላል:: የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት የበላዮቻቸውን ይሁንታና ፍቃድ ብቻ ጠብቀው የዜና ማሰራጫዎቹን ተቋማት ይመሩ እንደነበር አሳውቀዋል:: ጋዜጠኝነት ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ በዘፈቀደ በልምድና በስሜት ብቻ ይሠራ እንደነበርም አልሸሸጉንም:: የዚህ አይነቱ የዜና ማሰራጫዎች የበዘፈቀደ አስተዳደርና አመራር የነዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚእን የሕይወት ዋጋ እንዳስከፈለ ትናንትን ማስታወስ ይበቃል:: ዶ/ር ተስፋዬና አቶ ተገኝ የተሻወርቅ ከ60ዎቹ የጃንሆይ ባለሥልጣኖች ጋር በደርግ ሕይወታቸውን ያጡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቁንጮ ሰዎች ነበሩ:: ቀሪዎቹ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለሥልጣኖች ደግሞ ለዓመታት ለእስር ተዳርገው ነበር::

ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?›› በሚለው ድንቅ ግጥሙ፤ የረሃብተኞችን ጥኑን ሰቆቃ አድምቆ ገልጾታል:: ከግጥሙ አንድ አንጓን ወስደን እንመልከት::

‹‹የሆድ ነገር ስንት ያቆያል? ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?

ስንት መዕልት? ስንት ሌሊት?

 ስንት ሰዓት ነው ሰቆቃው?

ስንት ደቂቃ ነው ጭንቁ?

እስቲ እናንተ ተናገሩ ተርባችሁ የምታውቁ ስንት ያቆያል? ስንት ይዘልቃል?

 እውነት ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?››

 ሲል አጥብቆ በመጠየቅ፤ የረሃብን አስከፊነት ገልጾታል::

ይህ የሎሬት ጸጋዬ ግጥም ስሜት ተጠቂ የሆነው ስመ ጥሩው ጋዜጠኛ ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ ሚያዝያ 5 ቀን፣ 1967 ዓ.ም. ከወሎ ተፈናቅለው ፓርላማ አደባባይ ላይ ተከማችተው ለነበሩ ረሃብተኞች ታሪክ የማይረሳው ታላቅ ገድል ፈጽሟል:: ጋሼ ጳውሎስ ያዲስ አበባ ነዋሪዎችን በማስተባበር፣ እነሱ ባዋጡት ምግብ፣ መጠጥና ቁሳቁስ የፋሲካን በዓል አብረው እንዲፈስኩ ማድረጉ ነው:: ጋሽ ጳውሎስ በዚህ ሰብዓዊ አገልግሎቱ የታደጋቸው ወገኖቻችን ‹‹ለካስ እኛም ወገን ጠያቂ አለን›› ሲሉ የልብ እርካታቸውን ገልጸውበታል:: ጋዜጠኝነትን በብእሩም በግብሩም የተገበረው ታላቁ ጋዜጠኛ ጋሽ ጳውሎስ ብዙ ብዙ አርአያነትን አስተምሮን በክብር አልፏል::

ስመ ጥሩው ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ

 ‹‹ያልነቃ ጋዜጠኛ አደንቋሪ ጋጋኖ ነው›› የሚለው የቆየ ብሂል፤ ሁሌም ጋዜጠኛውን ከሕብረተሰቡ ቀድሞ፣ ነቅቶና አውቆ እንዲገኝ የሚያተጋ ነው:: ከጃንሆይ ዘመን ወዲህ ሁለት ስርዓቶችን አይተናል:: ትናንትም በደርግ ዛሬም በዘመነ ኢሕአዴግ ነቅተው ሙያቸውን አስከብረው እራሳቸውንም የሚያስከብሩ ብቁ ጋዜጠኞችን በብዛት ለማየት አልታደልንም:: ለሙያቸው ክብር ሲሉ እንደ ኤልያስ ብሩና እንደ ሣህሉ አሰፋ እውነትን ከነብጉራ ቀርጸው፣ አስቀርጸውና ዘግበው ለታሪክ ያቆዩ ጀግኖች ብዙ ያስፈልጉናል:: በኤርትራ ጦር ግምባሮች ለወራት የጦሩን ገድል ሲዘግቡ ከርመው ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ፤ ከሥራ የተባረሩትን እነጸጋዬ እንደሻውን የመሳሰሉ የቁርጥ ቀን ልጆች አርአያነት ማስታወስ ያስፈልጋል:: ጸጋዬ እንደሻው ለስድስት ወራት በኤርትራ በረሃዎች ተንከራቶ የጦሩን ውሎና ገድል የዘገበ ቆራጥ ጋዜጠኛ ነበር:: ጸጋዬ በፈንጂ ፍንጣሪ ተመቶ፣ ግዳጁን ጨርሶ ሲመለስ፣ የተገንጣዮቹ ባላ አደራ የነበረው አለቃው ገዳሙ አብርሃ ያላንዳች ይሉኝታና ድብቅ ምክንያት በማን አለብኝነት ነበር ከሥራው ያባረረው:: ያለቃው ድብቅ ምክንያት የኋላ ኋላ ሲገለጥ፤ የጀብሃንና የሻቢያን አከርካሪ በፕሮፓጋንዳ ሥራው ክፉኛ መምታቱ ነበር:: ልክ እንደ ጸጋዬ ሁሉ የዚህ ያለቃቸው የበቀል በትር ያረፈባቸው ዘማች ጋዜጠኞች ቁጥር ብዙዎች ነበሩ:: ሁሎቹም ይህንን ጸረ ኢትዮጵያዊነት በደል ታግለው ያንን እኩይ አለቃቸውን እያጋለጡ፤ ለተከበረው የጋዜጠኝነት ሙያቸውና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ክብር ቁመው ዘልቀዋል::

ዘማቹ ጋዜጠኛ ጸጋዬ እንደሻው

ታላቁ ጸሐፌ ተውኔት ሼክስፒር እንዳለው፤ ‹‹መሆን ወይ አለመሆን›› ችግሩ እዚያ ላይ ነውና፤ በስመ ጋዜጠኝነት ሙያውን የሚያለከሰክሱ መንገደኞችን መጥረግ ያስፈልጋል:: ባንዳንድ ኤፍ ኤም ራዲዮ ላይ ያየር ሰዓትን ለመሙላትና ሰወልዲ ለመሰብሰብ ብቻ ታጥቀው የተነሱ አጭበርባሪዎችን ከሙያው አምባ ማጥራት ያስፈልጋል:: ልክ በየፌስቡኩና በየዩትዩብ እንደምናያቸው በሬ ወለደ ዘማሪያን ሁሉ፣ ባንዳንድ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር የራቀ አጀብኛ ጋዜጠኝነትን (Yellow journalism) የሚተገብሩ ደካሞች አሉ:: አንዳንዶቹማ በጓደኝነት፣ በጥቅምና በእከከኝ ልከክህ ጸረ ጋዜጠኝነት በርኖስ ስር ተሸጉጠው አንዱን ባንዱ ሰው ሲያሰድቡ፣ ሲያሳሙ ለሰዓታት የሚደመጡ አሉ:: ዘገባዊ ፋይዳው ሲመዘን ያላንዳች ማስረጃና መጨበጫ አንዱ ጫፍ ላይ ቁመው ሌላው ጫፍ ላይ የቆመውን ሰው ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ማጋፈር ነው ሥራቸው:: በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ የተዘወተሩት የጠያቂና መርማሪ ጋዜጠኛ መሣሪያዎች እነ ‹‹ማን? የት? መቼ? ለምን? እንዴት?›› ጨርሶውኑ አይታወቁም:: ማይክሮፎንን እተናጋሪው አፍ ላይ ለጉሞ የልብህን ያህል ፎክር አቅራራ ማለት ነው የሚቀናቸው:: ባለ ቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን እንዲህ ያሉት ገልቱዎች ሲያስጠሉት፤ ‹‹መትፋት ያስነውራል›› ሲል በአጉራ ዘለል ከያኒያን ላይ ምሬቱን ገልጧል:: የገጠመው ማለፊያ ግጥም ለእንዲህ ዓይነቶቹ ረጋ ሠራሽ ጋዜጠኞች መምቻ መልካም ምግታር ነውና በጥቂቱ እነሆ…

 ‹‹መትፋት ያስነውራል››

 ‹‹እፍ አንቺ መብራት ጨልሚ

 እፍ አንቺ መብራት ክሰሚ

 ጥፊ፣ ጨልሚ፣ ውደሚ!…››

 አለ አሉ ሼክስፒር ቄሱ

 መቼም አያልቅበት እሱ…

 መድረክ ላይ ኩስ ከሚተፋ

 አዎን… ሕይወት እራሷ ትጥፋ…››

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top