ፍልስፍና

“የኢትዮጵያውያን ዓለም ሰዋዊ ዓለም ነው” (ሳምነር)

መግቢያ

ባለፈው ጽሑፌ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ክላውድ ሳምነር ባደረገው አበርክቶ ላይ ዳሰሳ አድርጌያለሁ። በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ በሚደረግ ውይይት ስሙ የማይታለፈው ክላውድ ሳምነር አንድ ሙግት አለው። ይኸውም የምዕራባውያኑ ዓለም ከሰው ልጅ የተለየ፣ ዳር ተቁሞ የሚጠና የነገሮች ስብስብ ሲሆን የኢትዮጵያውያን ዓለም ደግሞ ሰዎች ራሳቸው በጥብቅ የሚቆራኙበትና በሂደቱም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እና ድጋፍ የሚያደርጉበት ሰዋዊ ዓለም ነው የሚል ነው። ለውይይታችን መነሻ የሚሆነንም ይኸው በሰውና በሌላው ተፈጥሮ ያለው መስተጋብር ምን ይመስላል? የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው።

 በኢትዮጵያውያን የቃላዊ እና ጽሑፋዊ ትውፊቶች ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረገው ፈላስፋው ሳምነር የደረሰበት ድምዳሜ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የዘርዓ ያዕቆብን እና የወልደ ሕይወትን ሐተታዎች በተነተነበት የኢትዮጵያ ፍልስፍና ቅጽ 2 መጽሐፉ (ገጽ 62)፣ “The Western world is one of things, the Ethiopian world is one of persons” ይለናል። የዚህ ዓረፍተ ነገር አንድምታ እንዲሁም ተግባራዊ ነጸብራቅ ብዙ የሚያከራክር እና የሚያወያይ ነው። በዚህ አጭር ጽሑፍ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ በጥንታዊ የግእዝ ብራና ተጽፈው የሚገኙ ከውጭ ቋንቋ የተተረጎሙ እና በኢትዮጵያውያን የተጻፉ የፍልስፍና መጻሕፍት ውስጥ አምስቱን ሰብስቦ Classical Ethiopian Philosophy በሚል ርእስ እ.አ.አ በ1985 ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን እንደሚመስል በአጭሩ እንመለከታለን። የኢትዮጵያውያን ዓለም እንደምን ያለች ነች? ይህስ በቋንቋቸው እና በይትበሃላቸው፣ በሃይማኖታቸው እና በፍልስፍናቸው እንደምን ተንጸባርቋል? የሚሉ ጥያቄዎች መነሻችን ናቸው።

የኢትዮጵያ ዘመን አይሽሬ የፍልስፍና ድርሳናት  “Classical” የሚለው ቃል ለብዙ ነገሮች መግለጫነት ያገለግላል። ባንድ በኩል ከጥንታዊነት ጋር ሲያያዝ በሌላ በኩል ከውበት፣ ከጥራት፣ እንዲሁም በጥንቃቄ እና በልዩ ጥበብ የተሰራ የሚል አንድምታ ይይዛል። ሁለቱም አገላለጾች ስህተት የለባቸውም። የቋንቋ ባለሙያ ባልሆንም ቃሉ ለፍልስፍና ባይተዋር ስላልሆነ አጠቃቀሙ ላይ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል። በፍልስፍና ውስጥ Classic ከጥንታዊነት እና ከዘመን ተሻጋሪነት ጋር ይያያዛል። ባንድ በኩል በአስተሳሰቡ ጥልቀት እና በሙግቱ ጥንካሬ፣ እውነታን በገለጸበት መንገድ እና የሰው ልጆችን ነባራዊ ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ጥንት የተፈለሰፉና ዘመን የማይሽራቸው የፈላስፎችን አስተያየቶች የሚያመላክት ነው። በሌላ በኩል ዛሬ ካሉ የዘመናችን ሙግቶች በጥንካሬያቸው ጎልተው የወጡትን ምጡቅ አስተሳሰቦች የሚያጠቃልል ነው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ሐሳቦች የትም ቦታና በየትኛውም ሥርዓት “በከመ ይቤ፣ እከሌ እንዳለው” እየተባሉ የሚጠቀሱ ናቸው። ለምሳሌ ፕሌቶን ሲያደንቁት ፍልስፍናን ፕሌቶ ጨርሶታል፣ ከዚያ በኋላ ያለው The Republic (የፕሌቶ መጽሐፍ) የግርጌ ማስታወሻ ነው እስከማለት የደረሱም አሉ።

ሳምነር የስብስቡ ርእስ ላይ ለምን Classical የሚል ቃል እንደተጠቀመ ባይነግረንም ዘመን ተሻጋሪ፣ ድንቅ፣ ተጠቃሽ የሚሉትን ቃላት ለመግለጽ ይመስለኛል። ሐሳቡ ስህተት የለበትም። አድለር የተባለ አሜሪካዊ ፈላስፋ Great Ideas from Great Books በተሰኘው መጽሐፉ ታላላቅ መጻሕፍት ስለሚባሉት የሚነግረንም ይህንን ነው። አንዴ ተነበው የማይጣሉ፣ ባነሱት ሐሳብ ክብደት እና ባቀራረባቸው ውበት፣ ግልጽነት የሁሉንም ቀልብ እና ኅሊና ሰቅዘው በመያዝ አስተሳሰብን የሚያሰፉ፣ ሙግትን ውይይትን የሚከፍቱ፣ ተግባቦትን የሚያበለጽጉ ናቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ድርሳናት ናቸው በአንድ ዳጎስ ባለ መጽሐፍ ውስጥ በእንግሊዝኛ ተሰብስበው ከ34 ዓመታት በፊት የታተሙት። የተጻፉበት (የተተረጎሙበት እና የተደረሱበት) ዘመን ከ5ኛው እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን የ12 መቶዎች ዘመናት ሂደት ውጤቶች ናቸው።

ይዘታቸው ከግልጽ ሐይማኖታዊ እስከ የግል ሕይወት ታሪክ፤ ከእምነት እስከ ‘ክህደት’- ወሙግት፤ ከተምሳሌታዊ እስከ ቀጥታ ትኩረት፤ ከጥቅል ማህበራዊ ጥበብ እስከ ግላዊ ምክንያታዊነት የተዘረጉ ናቸው። በምንጫቸው ከውጭ ቋንቋ ለተተኳሪው ማኅበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ እንዲስማማ ተደርገው የተተረጎሙ እና በኢትዮጵያውያን በራሳቸው የተደረሱ ኦርጂናሌ ድርሳናትን የሚያካትት ነው። በትኩረታቸው ደግሞ፣ ባለፈው የዘርዓ ያዕቆብን እና የወልደ ሕይወትን ሐተታዎች በተመለከትንበት ጽሑፍ እንዳልነው፣ ከግል የእለት ተዕለት ኑሮ እስከ ማኅበራዊ መስተጋብር፤ ከግለሰቦች ግዴታና መብት እስከ መሪዎች የፖለቲካ እብለት፤ ከጥልቅ ሐተታ ተፈጥሮ እና ልዕለ ተፈጥሮ አካል እስከ ማኅበራዊ ትችት፤ ከረቂቅ ፍልስፍና እስከ ተግባራዊ ምክረ ሐሳብ የተሰናሰለ ነው። ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ዘመን አይሽሬነታቸው ሲሆን አንዳንዶቹ እንደዚህ ዓይነት ሐሳብ “ከአፍሪካውያን ኅሊና ሊፈልቅ አይችልም” ከሚለው እስከ “እንደዚህ ዓይነት ሐሳብማ በቅኔ ትምህርት ቤት ካለፉ እና የትርጓሜ ትምህርት ቤትን በር ካንኳኩ ልኂቃን አይጠበቅም” የሚለው የትችት አስተያየት ተሰንዝሮባቸዋል። ሌላው የሚያጋራቸው ዋና ንጥረ ነገር እና ባህላዊ ዳራ “የኢትዮጵያውያንን ሰዋዊ ርዕዮተ ዓለም” ማንጸባረቃቸው ነው። መነሻቸው እና መድረሻቸው ይኸው ሰዋዊ ዓለም (“the symbols that support it are deeply personalist [,…] the broader cultural background where the human element is both the base and the summit”) ነው።

 ይህ የጋራ ነፍሳቸው ነው በአንድ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ቤተሰብ ስር እንዲደመደቡ ያደረጋቸው። በተለይ የሴሜቲክ ኢትዮጵያውያን ዓለም ይኸው ሰዋዊ ዓለም ሲሆን ሁሉም የሚያንጸባርቁት ይህንኑ ነው የሚለን ሳምነር በቋንቋቸው ሳይቀር ጎልቶ ይታያል። ስለዚህ ጉዳይ ከታች የማብራራው ይሆናል። ይህ ሰዋዊ የሆነው የሴሜቲኮች ዓለም ከሌሎቹ የኢትዮጵያውያን ዓለም ጋር እንዴት ይታያል? የሚለው ጥያቄም በዚያው አስተያየት ይሰጥበታል። ከዚያ በፊት ግን የእያንዳንዳቸውን መጻሕፍት አጭር ዳሰሳ እናስቀድም:-

 ሀ. የመጀመሪያው ፊሳልጎስ (ፊስ አልጎስ) The Fisalgwos

ከጥንት የሲርያ ወይም የዓረብኛ ቋንቋ እንደተተረጎመ ይነገርለታል። በ2009 ዓ.ም በዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ወደ አማርኛ ተተርጉሟል። የሁለቱም ትርጉሞች በተመሳሳይ ወር ገበያ ላይ የዋለ ሲሆን መግቢያው እና አወቃቀሩ የተወሰነ ልዩነት አለው። መሰረታዊ ይዘቱ ሳምነር ወደ እንግሊዝኛ ከተረጎመው ጋር አንድ ነው። ፊሳልጎስ በሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ የእምነት ሰው የተጻፈ እንደሆነ ይነገርለታል። ይዘቱም እንስሳትን፣ እጽዋትን፣ ማዕድናትን እና የከበሩ ድንጋዮችን ባህርያት በመተንተን ሃይማኖታዊ ሁነቶችን ለማብራራት እና የሰዎችን ጠባያት ለማስተካከል ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብበት መጽሐፍ ነው። የአንድ እንስሳን ወይም እጽን ባህርይ በመተንተን “የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት፣ ትንሳኤ፣ ሰይጣንን ድል መንሳት እንዲሁ ነው፤ መጽሐፍም ይህንን ይላል” የሚል ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ሲደግፍበት በሌላ በኩል ደግሞ “በአስተሳሰብ እና በተፈጥሮ ካንተ በታች የሆኑ እንስሳት ይህንን ሲያደርጉ አንተስ ሰው ሆይ እንዴት ይህንን ማድረግ ይሳንሃል?” የሚል ተግሳጽ ወይም “አንተም የልቡናህ ፍቅር ወይም የኅሊናህ እውቀት በጠፋ ጊዜ እንደዚህ ታደርግ ዘንድ ይገባሃል” የሚል ምክር ይሰነዝራል። ይህም ሳምነር እንደሚለው አድማጩን ወይም ተማሪውን ወደ ተፈጥሮ የሚጋብዝ እና “ለአንክሮ ለተዘክሮ፣ ለማድነቅ እና ለማስታወስ” በተፈጠረው ዓለም ውስጥ ራሱን ተሳታፊ በማድረግ ራሱን እንዲያሳድግ ጥሪ ያቀርባል።

የኢትዮጵያውያን ዓለም ሰዋዊ ዓለም ነው ሲባል የተፈጥሮን ሁነት እና ድምጽ ሰምቶ ለጥያቄዋ መልስ የሚሰጥበት፣ ራሱን የተፈጥሮ አካል በማድረግ የለውጥ ሂደቱ፣ የጉዞው አጋዥ ነውና። በዋናነት ከተጠቀሱት እንስሳት ውስጥ ለምሳሌ እናታቸውን እና አባታቸውን የሚንከባከቡ የወፍ ዝርያዎች፣ በጉልበቱ እና በብልሃቱ የሚታወቀው አንበሳ፣ ራሱን በማደሱ እና ራሱን ከጠላት ለመከላከል እና ጠላቱን ለማጥቃት በሚጠቀምባቸው ብልሃቶች የሚታወቀው እባብ፣ ንስር አሞራ ደግሞ የሰውን ልጅ ሥነ ምግባር ስለማሳደግ፣ እናትና አባትን ስለመንከባከብ፣ ከድንቁርና ስለማውጣትና የጥበብን መንገድ ስለመምራት ተጠቅሰዋል። ለምሳሌ እንሺላሊት ባረጀች ጊዜ የዓይን ብርሃኗ ይቀንሳል። ከፍ ወዳለ ቦታ በመውጣት ከጸሐይ ሙቀት እየተቀበለች ብርሃኗን እንደምታገኝ ሁሉ ሰው ሆይ አንተም ድንቁርና ወይም የእውቀት ማነስ በገጠመህ ጊዜ በሰቂለ ኅሊና ከፍ ወዳለ የተመስጦ ወይም የጥበብ ምንጭ (እግዚአብሔር) በመቅረብ ራስህን ከድንቁርና ነጻ አውጣ የሚል ምክር ቀርቧል።

ለ. አንጋረ ፈላስፋ The Book of the Wise Philosophers:- ሊቀ መዘምራን ሞገስ እቁበ ጊዮርጊስ በ1953 ዓ.ም አንጋረ ፈላስፋ (የፈላስፋዎች አነጋገር) በሚል ርእስ የተረጎሙት ሲሆን የተርጓሚው መቅድም ስለ ሕልም አፈታት፣ የሕልም ዓይነቶችና ከሰው ተፈጥሮ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ጥሩ ጽሑፍ አቅርበውልናል። ስለ መጽሐፉ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ እውቀት የሚከተለውን መግለጫ ያስነብቡናል:-

 የመጽሐፉ ይዞታ ምክር መንፈሳዊ እና ጥበብ ሥጋዊን በሰፊው ከመስጠቱ በላይ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” እንደተባለው መደበኛውን ሃይማኖት ሳይለቅ በሰፊው አይገለጽና አይሰራበት እንጅ ጥንታዊ ሲሆን ዛሬ አዲስ ነገር መስሎ የሚታየውን የሳይንሱን አስተያየት በሰፊው ይገልጻል። የረቂቃኑን እና የግዙፋኑን ሥነፍጥረቶች አኳኋን አንድ በአንድ እየተነተነ ይናገራል (ገጽ ፪)።

አንጋረ ፈላስፋ ከስሙ እንደምንረዳው የፈላስፎች አባባሎች ስማቸውን በመጥቀስ ወይም ከፈላስፎች አንዱ እንዲህ አለ እያሉ የሰበሰቡት ጽሑፍ ነው። ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ እስከ 5ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የጥንት የግሪክ እና የሮማ ፈላስፎችን አባባሎች እና ሌሎች ተረቶችን ያካተተ ነው። ወደ ግዕዝ የመለሰው አካል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ተረቶች እየጨመረ ያበለጸገው ሲሆን በጊዜ ሂደት ውስጥ ተርጓሚዎች እና ጽሑፉን የገለበጡት አካላትም ሌሎች ማሻሻያዎችን አካተውባቸዋል ማለት ይቻላል። አንዳንድ ቦታ ላይ “የዚህ መጽሐፍ ጽሐፊ ይህንን ይላል” የሚለው ሐረግ ይህንን የሚያሳይ ነው። ሞገስ እቁበ ጊዮርጊስ ራሳቸው ከተለያዩ የብራና መጻሕፍት አመሳክረው የተረጎሙት እንደሆነ፣ በምዕራፍ እንደከፋፈሉት እና ከራሳቸው አስተያየት “ትንሽ ቃላቶች” እንደጨመሩበት ይነግሩናል። ከእነዚህ ቃላቶች ውስጥ “ማስተዋል የራቀን ለማቅረብ፣ የቀረበውን ለማራቅ የሚያገለግል የልብ መነጽር ነው” የሚል አስተያየት እና ሌሎች አባባሎች ይገኛሉ።

በሳምነር ስብስብ ውስጥ የሚገኘው የፈላስፎች መጽሐፍ ይኸው አንጋረ ፈላስፋ ሲሆን መጀመሪያ ላይ የጠቢቡን የሂቃር ታሪክ ያስነብበናል። በመጽሐፉ ውስጥ በስፋት የተነገረው የሥነ ምግባር ጉዳይ ሲሆን ስለ ጥበብ፣ ስለ ምርምር፣ ስለ ህብረት እና ስለ ሰላም፣ ስለ ፖለቲካዊ መሪነት ስለ ፈሪሃ እግዚአብሔር ወዘተ ይተነትናል። ለምሳሌ ስለ ፖለቲካ መሪነት ሲያትት “ንጉስ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ውክልና ነው። መኳንንቱ ደግሞ የርሱ የሕጉ ጠበቃዎች ናቸው። ነገሥታት እና መኳንንቱ ፍትሐውያን ከሆኑ ዜጎች ኢ-ፍትሐዊ ሊሆኑ አይችሉም።” (ገጽ 148)

 አንጋረ ፈላስፋ እንዲህ ዓይነት ከላይ ሲያዩዋቸው ቀላል የሚመስሉ አባባሎችንና ጥልቅ የፍልስፍና ክርክሮችን የያዘ መጽሐፍ ነው። ከላይ ሲታዩ “አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች፣ ስሜት ቆንጣጭ፣ ብያኔ እና መርሆ የሚያስቀምጡ አባባሎች ሲሆኑ ወደ ተረት፣ ታሪክ፣ እንቆቅልሽ፣ ዲስኩር እና ሙግት ያድጋሉ” (ገጽ 52) ነው የሚለን ሳምነር። ፍልስፍናዊ ይዘቱም በሚያነሱት ርእሰ ጉዳይ (ግዙፉና ረቂቁ ዓለም፣ ተፈጥሯዊ እና ማኅበራዊ ክስተት) እንዲሁም ከሚያቀርቡት መከራከሪያ ላይ ይመሰረታል።

ሐ. የእስክንድስ ሕይወት እና መርሆዎቹ The Life and Maxims of Skǝndǝs የእስክንድስ ታሪክ እና መርህ በመባል የሚታወቀው ይህ መጽሐፍ የአንድ የፍልስፍና ተመራማሪ የግል ገጠመኝ እና ስለ ተፈጥሮ እና የሰዎች ባህርይ ያተተበት መርሆዎቹ ስብስብ ነው። ሦስት ክፍል ያለው ሲሆን የመጀመሪያው የግል ሕይወቱ እና ገጠመኙን የያዘ ነው። ቀጣዮቹ ሁለት ክፍሎች ደግሞ ጥያቄዎች እና መልሶች ናቸው። በድምሩ 163 ጥያቄዎች የያዘ ሲሆን ስለ ፈጣሪ፣ ስለ ሰው ነፍስ፣ ኅሊና፣ ስለ መላእክት፣ ስለ ተፈጥሮ ክስተቶች፣ ስለ ጨረቃ፣ ጸሐይ እና ከዋክብቱ፣ ስለ ተፈጥሮ ክስተቶች (ዳመና፣ መብረቅ፣ ወጀብ)፣ ስለ መሬት፣ ሰማይ፣ ስለ ሰው ልጆች ሥራዎች እና አጠቃላይ ሕብረታቸው ወዘተ የሰጣቸውን ምላሾች ይዘዋል።

 የእስክንድስ ታሪክ ባጭሩ የባለጸጎች ልጅ ሲሆን ወላጆቹ ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ከፈላስፎች ጥበብ እንዲማር ወደ ሩቅ አገር ላኩት። በዚያው ትምህርቱን እየተማረ ወደ ጠቢብነት ደረጃ በደረሰ ጊዜ መጻሕፍትን ሲመረምር ከጠቢባን አንዱ “ሴቶች ሁሉ አመንዝራዎች ናቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ እንደደረሰ አነበበ። ይህንን አረፍተ ነገር ለማረጋገጥ መላ ዘየደ። ይኸውም ለ24 ዓመታት የተለያትን፣ አባቱ ስለሞተ ብቻዋን

የኢትዮጵያን ባህል እና ወግ ዘመን ተሻጋሪነት ሲያብራራ ኢትዮጵያውያን ባህላቸው እና ወጋቸውን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩት ከውጭ ንክኪ በመጠበቅ ሳይሆን ማንኛውንም ከውጭ የሚመጣን ሐሳብ ወደ ራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ የማዋሃድ ብልሃት እና ልምድ ስላላቸው ነው

የምትኖረውን እናቱን መፈተን ነበር። በርሱ እሳቤ የኔ እናት የተከበረች ንጹሕ ሴት ስለሆነች እንደዚህ ዓይነት ነገር አታደርግም የሚል ነበር። ወደ ትውልድ መንደሩ ሄዶ ማንም ስለማያውቀው የእናቱን አገልጋይ ያገኛታል። ስለ አባቱ፣ ስለራሱ፣ ስለ እናቱ ሲጠይቃት አባቱ ከሞተ ረጅም ዘመን እንደሆነው፣ ልጃቸው ለትምህርት ከወጣ ተመልሶ እንዳልመጣ፣ እናቱም ብቻዋን እየኖረች እንደሆነ ነገረችው። ለአንድ ሌሊት ከእመቤቷ ጋር እንዲያድር መልእክት እንድታደርስለት ይጠይቃታል። አገልጋይ የኔ እመቤት የተከበሩ ሴት ናቸው እንዲህ ያለ ነገር አያደርጉም። የሚል ሐሳብ ብታቀርብም ከብዙ ማግባባት በኋላ እናት ፈቃደኛ ሆኑ። ልጅም ወደቤት ገባ። ማታ ላይ ወደ አልጋ በወጡ ጊዜ እናት ፈቃደ ስጋቸውን አልሸሸጉም፤ ልጅ ደግሞ የሚያውቀውን ያውቃል እና እንዲሁ እያታለለ አደረ። ጧት ላይ ልጃቸው መሆኑን ሲገልጽ እናት በጸጸት አለንጋ ተገረፉ፣ አፈሩ። መጨረሻ ላይም ራሳቸውን አጠፉ። ልጅ እናቱን በዛፍ ላይ ተሰቅለው ራሳቸውን እንዳጠፉ ባየ ጊዜ አዘነ፣ ተጸጸተ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንደበቱን በአርምሞ ቀጣ። ወደ ትምህርት አገሩም ሔደ።

 ይህ የሆነው በንጉስ አንድርያኖስ ዘመን ነበር። ከዚያ በኋላ እንዲናገር እና ከጥበቡ እንዲያካፍላቸው ንጉሡ እና ባለሟሎቹ በማስፈራራትም በማግባባትም ሙከራ ሲያደርጉ እስክንድስ ፍጹም አርምሞን መረጠ። እስክንድስ በሕይወት ዘመኑ ያካበተውን ጥበብ በጽሑፍ እንዲያካፍላቸው ንጉሡ ይለምነዋል። ከዚህ በኋላ ነው የእስክንድስ መርሆዎች (Maxims) የሚጀምሩት። የመጀመሪያ ምልከታው በሰዎች እና በሌሎች እንስሳት መካከል ያለውን ልዩነት በማሳየት ንጉሡ ከእንስሳት ከፍ ያለ የማሰብ እና የምክንያታዊነት ባህርይ ስላለው በሥራው ሁሉ ከሰውነት ክብሩ ዝቅ እንዳይል መምከር ነው። ይህን ብቻ አይደለም በሰዎች መካከል ያለውን እኩልነት ሲገልጽ “ንጉሥ ሆይ ምክሬን ትሰማ ዘንድ ይህች ናት። አንተም እንደኔው ሰው ነህ” ይለዋል። ሰው ልክ እንደ እንስሳት የስሜት ቋት ቢሆንም ከሁሉም ከፍ ያለች ነፍስ እና ነባቢነት ያላት ልሳን ስላለችው ከእንስሳቱ ይለያል። የሰውነት ክብሩም ስሜቱን በተቆጣጠረው ልክ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ንጉሡን ይመክራል። ስለ ሕገ ተፈጥሮ እና የወቅቶች መለዋወጥ፤ መንበረ ሥልጣንም ስለሚለዋወጥ ለዚህ ሕግ ተገዥ መሆን እንዳለበት፣ በዘመነ ንግሥናው ሁሉ ይህንን የማይናወጥ ሕግ እንዲከተል አበክሮ ይመክረዋል። (ገጽ 176-177)

 የሰው ልጆች በሰሩት ስህተት ሰይጣን አስቶኝ ነው እያሉ ኃላፊነትን ለመቀበል ፍቃደኛ ስላለመሆናቸው አንድ ፈላስፋ አስተያየቱን ሲሰጥ “ሰዎች ስለሁለቱም ጥፋታቸው ይቀጣሉ። መጀመሪያ ስለ ጥፋታቸው፣ ሁለተኛ ጥፋታቸውን በሰይጣን ስለማሳበባቸው። ምንም እንኳን ተገደን በደል ብንሰራም ፈቃዱ የራሳችን ነው። የራሳችን ፈቃድ ካልታከለበት በስተቀር ሰይጣን በእኛ ላይ ኃይል የለውም።” (ገጽ 203) ይህ ጉዳይ የነጻ ፈቃድ እና የእጣ ፈንታ ክርክር አንድ አካል ነው። ሰው ለሚያደርገው ነገር የፈጣሪ ትእዛዝ ወይም የሌላ ኃይል አሳሳችነት አለበት በሚሉት እና ሰዎች ሁሉ ነጻ ፈቃድ የተሰጣቸው ስለሆኑ ለሚያደርጉት ነገር ኃላፊነቱን ይወስዳሉ በሚሉት መካከል ያለ ክርክር ነው።

ልክ እንደ ክርስትናው አስተምህሮ እስክንድስም ይህንን ዓለም የኃጢያት ሰንሰለት የሞላበት አድርጎ ይመለከተዋል። የሰው ልጆች ከዚህ የኃጢያት ሰንሰለት ለማምለጥ መጣጣር አለባቸው። ይህም ወይ ከዓለማዊ ነገሮች “ከእንስሳት ፈቃድ” ራሳቸውን ነጻ በማውጣት ወይም ደግሞ ሰላም የሰፈነበትን የተረጋጋ ዓለም በመፍጠር። ይህም መስማማትን (Integrity) በማስፋፋት፣ ቁጣና ጥላቻን በማስወገድ፣ ሰላምን (the daughter of the Most High) በማስፈን (ገጽ 187፣ 192፣ 204) እንደሆነ ይነግረናል። ለኢትዮጵያውያን ዓለም ሰዋዊ ነች ለማለት የሚያስደፍረን የሰው ልጅ ከአካባቢው ጋር ባለው ጥብቅ ቁርኝት የሚንጸባረቀው የመገፋፋት እና የተጽእኖ ኃይል የተገለጸበት መንገድ ነው።

 መ. ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ እና ሐተታ ወልደ ሕይወት Hateta Zär’a Ya’ǝqob Hateta Wäldä Hǝywåt:-

 ስለ ሁለቱ ሐተታዎች ታዛ ቁጥር 19 እና 21 ላይ በሰፊው የተተነተነ ሲሆን አንባቢ ሁለቱን ቅጾች እንዲያነብ እጋብዛለሁ። እዚህ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ከላይ ከገለጽናቸውና ከውጭ ቋንቋ ከተተረጎሙት ጋር ባንድ አቁማዳ ውስጥ በመክተት “ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ፍልስፍና“ ሊባሉ ስለቻሉበት ምክንያት ነው።

ተፈጥሮ በአገር በቀሉ እና “በመጤው”፣ በተጻፈው እና ባልተጻፈው የኢትዮጵያ ፍልስፍና ውስጥ

 የተጻፉት የፍልስፍና ድርሳናት ሁለት ወገን ናቸው። እነርሱም ከውጭ ቋንቋ የተተረጎሙት እና በኢትዮጵያውያን የተጻፉት። እነዚህን በአንድ ላይ ጠቅልሎ ኢትዮጵያዊ ያሰኛቸው ምንድን ነው? ሁሉንስ ኢትዮጵያዊ ያሰኛቸው ልዩ መገለጫ ባሕርይ የቱ ነው? የመጀመሪያው ጥያቄ መልስ አንድም በዘመን ሂደት ውስጥ የአንድ እውቀት ከውርስነት ወደ አገር በቀልነት ስለሚለወጥ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን አግኝተዋል ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ግን ተርጓሚዎቹ ጽሑፎቹን የደረሷቸውን አካላት ባህል እና አስተሳሰብ እንደያዙ አልተረጎሟቸውም። ይልቁን ከኢትዮጵያዊ ወይም ከተደራሲው ማኅበረሰብ ማኅበረ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማሙ ስላደረጓቸው ነው። በተለይም ኢትዮጵያውያን ይህንን የማድረግ ልዩ ተሰጥኦ እንዳላቸው በርካታ አጥኝዎች ይመሰክራሉ። ለምሳሌ ፍትሐ ነገሥት በ15ኛው ክፍለ ዘመን ሲተረጎም ከኢትዮጵያ ባህል እና እምነት ጋር እንዴት እንደሚስማማ ጥንቃቄ ተደርጎበት እንደነበር አበራ ጀንበሬ ይነግረናል (2006፣ ገጽ 160-163)።

 ሳምነርም ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዳ ኢትዮጵያውያን እንደወረደ አይተረጉሙም፣ ይቀንሳሉ፣ ይጨምራሉ፣ ወይም ይቀይራሉ። ይህንን የሚያደርጉት የዋናውን ጽሑፍ ፈትለ ነገር ሳይለቁ ነው ይለናል። መሳይ ከበደም የኢትዮጵያን ባህል እና ወግ ዘመን ተሻጋሪነት ሲያብራራ ኢትዮጵያውያን ባህላቸው እና ወጋቸውን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩት ከውጭ ንክኪ በመጠበቅ ሳይሆን ማንኛውንም ከውጭ የሚመጣን ሐሳብ ወደ ራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ የማዋሃድ ብልሃት እና ልምድ ስላላቸው ነው የሚል መከራከሪያ አለው። ስለዚህ እነዚህ የተተረጎሙ ድርሳናት የኢትዮጵያ ፍልስፍና ያሰኛቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የተወሰነን (ሴሚቲክ) ማህበረሰብ ባህልና ወግ እንዲመስሉ ተደርገው ስለተተረጎሙ ነው። ሌላው እነዚህን አምስት ድርሳናት የሚያስተሳስራቸው ሁሉም የሚያትቱት የኢትዮጵያውያንን ሰዋዊ ፍልስፍና በመሆኑ ነው። ሁሉም በተናጠል መታየት ያለባቸው ሳይሆኑ አንዱ ስር ሌላው ፍሬ ሆነው የኢትዮጵያን ፍልስፍና እድገት ስለሚያሳዩ ነው። የሳምነር መከራከሪያ ያለ ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ እና ወልደ ሕይወት ፊሳልጎስ እርባና ቢስ ሲሆን (ተግባራዊ ፋይዳ፣ ፍልስፍናዊ ፍሬውን ያጣል)፣ ያለ ፊሳልጎስ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሥሩን ያጣል። (“Without the latter developments of Ethiopian philosophy, The Fisalgwos is deprived of its significance; without The Fisalgwos, [the written] Ethiopian philosophy is deprived of roots” (1985, p. 9).)

ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው የማስተሳሰሪያ ሰንሰለት ግን የሚወክሉት ዓለም ሰዋዊ መሆኑ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ሳምነር በቅጽ 2 መጽሐፉ በሰፊው ይጽፋል። ሁሉም ድርሳናት ዓለምን ነፍስ የተዋሃዳት፣ የሰው ልጅ ደግሞ ከዓለም ተነጥሎ ዓለምን የሚመረምር አካል ሳይሆን የተፈጥሮን እንቅስቃሴ እና ሂደት የሚደግፍ የፍሰቱ አካል አድርገው ማስቀመጣቸው ነው (ገጽ 62)። በተለይ የሴሜቲክ ባህል በቋንቋው ሳይቀር ይህን የሰው ልጆች እና የተፈጥሮን ቁርኝት በግልጽ ያሳያል። ከስያሜ ጀምሮ ዓለምን የሚያዩበት መነጽር በሰዋዊነት እንጅ በባእድ ወይም በግኡዝነት፣ መበዝበዝ ወይም መጠናት ያለበት ነው በሚል የተነጠለ ትዝብት አይደለም። ሳምነር ይህንን ሙግት ለማጠናከር የሚያቀርበው ምሳሌ ”ቃል ሥጋ ሆነ” የሚለውን ነው። ቃል ወይም ቋንቋ ሐሳብን ለመግለጽ የሚያገለግል ረቂቅ ሳይሆን የመግዛት፣ የማድረግ ኃይል የተሰጠው፣ ሥጋ የተዋሐደው የግብር እና የለውጥ ኃይል ነው (ገጽ 11)። ለዚህ ማሳያው ለልጆቻችን የምናወጣው ስም ነው። አሸናፊ፣ ደመላሽ፣ ደስታ፣ ሃብታሙ ወዘተ የሚሉት ስያሜዎች የተከሰተን ሁነት ወይም ወደፊት እንዲሆን የምንፈልገውን ምኞት የያዙ የተግባር ቃላት ናቸው። ባለ ሥሙን ማኅበራዊ ቦታውን የመወሰን አቅም አላቸው። ስለዚህ ቋንቋ የመሆን፣ የለውጥ ዓለምን ያዘለ ነው። ሰውም በተፈጥሮ ሂደት ውስጥ ራሱን አዋህዶ ይመለከታል። የተፈጥሮን እና ማኅበራዊውን አካባቢ ፍሰት ያግዛል፣ ይበይናል (ገጽ 12)። ይህ ነው የተጻፉ ድርሳናትን አንድ የሚያደርጋቸው፣ ይህ ሰዋዊ የሆነን ዓለም በማተታቸው።

የኢትዮጵያውያን ዓለም ሰዋዊ ነው ሲባል ሰውን ማዕከል ያደረገ (Anthropocentric) ነው ለማለት አይደለም። በተቃራኒው ሰው የዓለም አንዱ አካል ነው፣ በተፈጥሮ መካከል ራሱን ያገኘ፣ የተፈጥሮን ሂደት የሚያግዝ፣ የሚወስን አካል ነው ለማለት ነው። ለተፈጥሮ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ንቁ አድማጭ ነው።

ያልተጻፉ ተረኮችስ ምን ይነግሩናል? ከሴሜቲክ ማኅበረሰብ ውጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንስ ተፈጥሮን እንዴት ይመለከቷታል? እነዚህ ጥያቄዎች ሰፊ ዳሰሳ ያስፈልጋቸዋል። ራሱን የቻለ ትኩረት የሚጠይቁ ናቸው። ነገር ግን ከተያዘው ርእስ ጋር ትንሽ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል። በደቡብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዓለም ወይም ተፈጥሮ የተቀደሰች የሰው ልጆች ወዳጅ ናት። በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል እና በኦሮምያ ክልሎች የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ማኅበረሰቡ የተፈጥሮ ደኖችን እና እጽዋትን መንፈስ የተዋሃደው፣ መጠበቅ ያለበት ሰዋዊ ክስተት አድርጎ ነው። ለምሳሌ ለአኝዋኩ ደን ወይም ጫካ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ብቻ አይደለም። ይልቁን የአባቶች መንፈስ የረበበበት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የተከበረ ቅርስ፣ ያለ ማኅበረሰቡ ፈቃድ ማንም እንደፈለገ የሚቆርጠው ወይም የሚያረክሰው አይደለም። እጽዋትን፣ እንስሳትን እንደ ገጸ ባህርይ ተጠቅሞ ተረት መተረት፣ በዛፎች ሥር፣ በወንዞች ዳርቻ የሚደረግ አምልኮ ወዘተ ተፈጥሮ ለሰው ልጆች ምላሽ ያላት፣ የሰው ልጆችም የተፈጥሮን ድምጽ ሰምተው ምላሽ የሚሰጡ እንደሆኑ ያሳያል። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ሳምነር “የኢትዮጵያውያን ዓለም ሰዋዊ ዓለም ነው” ሲል የደመደመው። ድምዳሜው እንዲሁ በቀላሉ የሚጣጣል፣ እንደወረደ የምንቀበለውም አይደለም። ክርክሩን ለአንባቢ በመተው እንደዚህ ዓይነት ሰዋዊ ዓለም ውስጥ የሚኖር ማኅበረሰብ እርስ በርሱ እንዴት ሊነታረክ፣ ሊጋጭ እንደቻለ ግን ግራ ያጋባል። ሰዋዊ በሆነው ዓለም ውስጥ፣ ሰዎች በማንነታቸው ሲፈናቀሉ ማየት ትልቁ ተቃርኖ ነው። የተደበቀው የማኅበረሰቡ ፍልስፍና ቢጠና ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ምልከታዎችን ማግኘት ይቻል ይሆናል።

መውጫ

 ሳምነር የውጭ ዜጋ ሲሆን በሙያው ታማኝ በመሆን፣ ባህል እና ቋንቋ፣ የማንነት ማዕቀብ ሳያግደው ከኢትዮጵያውያን ጓዳ ጎድጓዳ ገብቶ ለዘመናት ከተከማቸው የፍልስፍና ድርሳናት በጭልፋ ጨልፎ ከደርዘን በላይ የሆኑ መጻሕፍትን እንካችሁ ብሎናል። ይህም በዘመናችን በማንነት ጠባብ መጋረጃ ተሸብበው የኢትዮጵያውያንን የጋራ ዓለም መመልከት ለማይችሉ “ልኂቃን” አርአያ የሚሆን እና ሊፈጥሩት ለሚዳዱት ጠባብ የብሔሮች ዓለም ማስተባበያ ነው። በኢትዮጵያ ፍልስፍና መነሻ የሚሆኑ የጥናት ግብአቶችን ስላበረከተልን ሊመሰገን ይገባዋል። የርሱን ፈለግ በመከተል ከአባቶቻችን ጥበብ ለዘመናችን የሚሆነውን ዘመን ተሻጋሪ ፍልስፍናቸውን ማስታወስ ለኛ የተተወ ሐላፊነት ነው። በዚህ ጽሑፍ ያየናቸው ትንሽ ድርሳናት ማሳያዎች ናቸው። ከቃላዊ ትውፊቱ፣ ከተረቱ እና ከሌሎች የተጻፉ እና ያልተጻፉ ቅርሶች ውስጥ ለፍልስፍና፣ ለታሪክ፣ ለሃይማኖት፣ ለሕክምና፣ ለባህል ጥናት የሚሆኑ ግብአቶችን ማግኘት ይቻላል። በሌላ ርእሰ ጉዳይ እስክንገናኝ የወር ሰው ይበለን።

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top