ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአፍሪካ ዋንጫ- እውነታና ትዝታ

የአፍሪካን ዋንጫ ዘንድሮ በግብጽ ተካሄደ:: ግብጽ አዘጋጅ ሆና ተመርጣ አልነበረም:: ህጋዊ አዘጋጅ የነበረችው ካሜሩን ነበረች:: ካሜሩን ዝግጅቷ ስለተጓተተ ተነጠቀችና ግብጽ ወሰደች:: ግብ የደከመባትን ቱሪዝም ለማንቀሳቀስ ታላቅ እገዛ ስለሚያርግላት በአጭር ግዜ ተቀብላ ባማረ ሁኔታ አስተናግዳለች::

የአፍሪካ ዋንጫ የአፍሪካን ሀገሮች ያቀራረበ ብቸኛው ተቋም ነበር:: የአፍሪካ ህብረት በራሱ የተመሰረተው የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ ከስምንት አመት በኋላ ነው:: የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመር ብዙ ርቀት ተኪዷል:: አንዳንዶቹ ሀሳቦች መንገድ ላይ መክነዋል:: መጀመርያ ጥንስሱ የታየው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የብሪቲሽ ሚለተሪ ሚሽን ተጫዋቾች ያመጡት ሀሳብ ነው:: ጉዳዩ የተጀመረው አዲስ አበባ ላይ ነው:: ግዜውም በ1938 ነው:: የመቻል(አሁን መከላከያ የተባለው) ቡድን ለመጀመርያ ግዜ የኢትዮጵያን ጥሎ ማለፍ አገኘ:: ይሄ ማለት ከኢትዮጵያ የመጀመርያ ዋንጫ ያገኘ ክለብ ነው:: ወታደሩን የሚወክለው አንድ ክለብ ነበር:: እሱም የብሪቲሽ ሚሊተሪ ሚሽን(ቢ.ኤም.ኤም) ነው በሚል የሀበሻ ወታደሮች ቡድን እንዳያቋቁሙና እንዳይሳተፉ ተደረገ:: ሀበሾቹ በቢኤ.ምኤ.ኤም ቡድን ገብተው እንዲጫወቱ ሲጠይቁ የሀገር ሰው አንቀላቅልም አሉ:: የሀበሻ ወታደሮች ንጉሱ ጋር አስፈቅደው ወደ ውድድሩ ገቡ::

መቻል በገባ በአመቱ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና ሆነ:: ይሄ ነገር ቅር ያሰኛቸው የብሪቲሽ ሚሊተሪ ቡድን ከመቻል ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አደረጉ:: መቻል አሸነፈ:: እንግሊዞቹ ድጋሚ ጨዋታ ጠየቁ መቻል እምቢ አለ:: ክርክሩ ቀጠለ:: የመቻል አምበል መቶ አለቃ (በኋላ ጄኔራል)አማን አንዶም እናንተ የውጭ ስለሆናችሁ ኢንተርነሽናል ግጥሚያ ነው መደረግ ያለበት ተባለ:: ይሄም አካሄድ ብዙ ክርክር አስነሳ በመጨረሻም እንግሊዞቹ አዲስ ሀሳብ አመጡ‹‹ናይል ካፕ››በሚል በክለብ ደረጃ የግብጽ ፤ሱዳን የኢትዮጵያ ክለቦች አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው እንዲጫወቱ ሀሳብ ቀረበ:: ይሄ ስያሜ ሲጀመር የአፍሪካ ዋንጫ ነበር :: በኋላ ግን ወደ ናይል ዋንጫነት ተቀየረ:: የአባይ ወንዝ በተለይ ሶስቱን ሀገሮች በዋናነት ስለሚያዝ ነው:: በወቅቱ የዙር ውድድር ስለቆመ ከኢትዮጵያ ወገን የጥሎ ማለፉ አሸናፊ መቻል እንዲካተት ተደረገ:: በጉዳዩ የእንግሊዝ መንግስት ጭምር ገባበት:: ነገሩን ኢትዮጵያውኖች ሲያጠኑት አላማው ሌላ ስለሆነ መቻል በራሱ መሳተፍ እንደማይፈልግ አሳወቀ:: እንግሊዝ ጣሊያንን አስወጥታ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመያዝ ብዙ መንገድ ሄዳለች:: ግብጽና ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ የነበሩ ሀገሮች ናቸው:: ኢትዮጵያ እንግሊዝ ባቋቋመው ናይል ካፕ ብትገባ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዥነቱን እንደተቀበለች የሚያሳይ ነው በሚል ነው:: እንግሊዝ የጠነሰሰው የአፍሪካ ዋንጫ መንገድ ላይ ቀረ:: እንደገና ሌላ ሙከራ ተደረገ::

 በ1942 ዓ.ም ሄሊኒካ የተባለ ቡድን ወደ አዲስ አበባ መጣ:: ለመጀመሪያ ጊዜ በክለብ ደረጃ ለመግጠም አዲስ አበባ የመጣ ቡድን ይሄ ነው:: ይህ ቡድን ነዋሪነቱ በግብፅ ሆኖ አሌክሳንደሪያ ከተማ የሚኖሩ የግሪክ ማህበረሰብ ያቋቋሙት ቡድን ነው:: ይህ ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ያመቻቸውና ወጪውን የሸፈነው ኦሎምፒያ አካባቢ የሚኖሩ የኦሎምፒያኮስ ቡድን አባላት ናቸው:: በዋነኛነት ትልቁን ሚና የተጫወተው ዲሚትሪ ስጎሎምቢስ ነበሩ:: (እኚህ ሰው 26 ዓመት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ከመሆናቸውም ሌላ በ3ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድናችን ዋንጫ ሲያገኝ ቡድን መሪ ነበሩ:: ) ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ መመራት አለበት ስለተባለ ከግብፅ እስማኤል ካሌብ የተባለ ዳኛ እንዲመጣ ተደረገ:: ( ይህ ሰው ለመጀመርያ ግዜ ከውጭ የመጣ አልቢትር ነው:: ) የኛ ሰዎች ውድድሩ ስለጣማቸው ግጥሚያው እንዲቀጥል ተነጋገሩ ድጋሚ ተደረገ:: ሀገር ለሀገር እየተገናኙ መጫወት ፈለጉ:: ከግብጽ ከመጣው ቡድን ጋር በጥልቀት ተወያዩ:: ጥሩ መግባባት ላይ ተደረሰ:: ደብዳቤ እየተለዋወጡ ንግግሩ ቀጠለ:: የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽ ሰዎች ከግብፅ ፌዴሬሽን ጋር መልክት ተለዋወጡና ነገሩ እየዳበረ ሄደ :: ውድድሩን ለመጀመር ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ የራሳቸው ብሔራዊ ቡድን ስለሌላቸው እነሱን መቀላቀል አልተቻለም:: ከኢትዮጵያ ወገን ሀሳቡን የጠነሰሱት ነገሩን ገፉበት:: በ1944 የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ግሪክ ሄደ:: አውሮፓ እየመጣችሁ ከምትጫወቱ ለምን አፍሪካ ውስጥ ቡድኖችን አትጠሩም ተባለ:: በ1948 የሱዳን ቡድን ጥሪ ተደረገለት አሁንም ግብዣ ተደረገና ከግብጽ ጋር የነበረው ውይይት ተነግሯቸውና ተስማሙ:: ከ1 ወር በኋላ በፖርቱጋል ሊዝበን የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የጠነሰሰችውን ሀሳብ ሱዳንና ግብፅ አንስተው ደቡብ አፍሪካ ተቀላቀለች:: ከ8 ወር በኋላ ካርቱም ላይ ተገናኙ:: ደቡብ አፍሪካ ከመጀመሪያውም ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ አልፈለገችም:: በካርቱም ጉባኤው ተካሄደና የአፍሪካ ዋንጫ እንዲጀመር ተስማሙ:: ጉባኤውን ለማካሄድ የተጓዙት ሀገሮች ውድድሩ እዚያው እንዲጀመር ስለፈለጉ ቡድናቸውን ይዘው ነው የሄዱት(በመስራች ጉባኤ ላይ ከኢትዮጵያ ወገን ይድነቃቸው ተሰማና ሻለቃ ገበየሁ ዱቤ ተሳትፈዋል:: የካፍ ሀምሳኛ አመት መጽሔት ግን አማን አንዶምም ከኢትዮጵያ ወገን መሳተፉን ይገልጻል):: ጉባኤው ከተካሄደ ከ2 ቀን በኋላ ውድድሩ እንዲካሄድ ተወሰነ:: ለ4ቱ ቡድኖች እጣ ወጣ:: ግብፅ ከሱዳን ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ይጫወታሉ::

አሸናፊዎቹ ለዋንጫ ያልፋሉ:: ኢትየጵያ ደቡብ አፍሪካን ጥቁርና ነጭን መቀላቀል አለባችሁ ብላ ከሰሰች:: ደቡብ አፍሪካም የሀገሬ ህግ አይፈቅደም አለች:: በዚህ የተነሳ ከውድድሩ ተሰናበተች:: ደቡብ አፍሪካ መጀመሪያም ኢትዮጰያን የፈራችው ለዚህ ነበር::

ካፍን ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት የመሩት የግብፁ አብዱል አዚዝ ሳለሚ ናቸው:: ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የግብፁ ጀነራል አብዱል አዝዝ ሙስጠፋ ሲሆን ለ10 ዓመት መርተዋል:: በ3ተኛነት የሱዳኑ ዶክተር አብድልሀሊም መሐመድ ሲሆኑ ለ4 ዓመት መርተዋል:: በ4ተኛነት ኢትዮጵያዊ ይድነቃቸው ተሰማ ለ16 ዓመት መርተው ነበር :: ለአንድ ዓመት ዶ/ር ሀሊም በጊዜያዊነት ያዙና በምርጫ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ኢሳ ሀያቱ ስልጣን ቆይተው በ2009 አዲስ አበባ የማዳጋስካሩ ተወላጅ አህመድ ተመርጠዋል::

የአፍሪካ ዋንጫ የተጀመረው በካርቱም በ1949 ነው:: ወድድሩን የመሰረቱት ሶስቱ ሀገሮች አዘጋጅነቱን ተከፋፈሉ:: ግብጽ ሁለተኛውን፤ ኢትዮጵ ደግሞ ሶስተኛው ለማዘጋጀት ተስማሙ:: ውድድሩ በየሁለት አመቱ ነው የሚካሄደው:: ሱዳን በ1949፣ ግብጽ በ1951፣ ኢትዮጵያ በ1953 ያዘጋጃሉ:: ሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ ተካሄደና ኢትዮጵያ ሶስተኛውን ለማዘጋጀት ሽር ጉድ አለች ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ በጠሩት መፈንቅለ መንግስት ትልቅ ትርምስ ወስጥ ተገባ :: በየካቲት ሊደረግ የነበረው ውድድር ተቋረጠ:: ከዚያም ብሶ ቱኒዝያ ውድድሩን ለመውሰድ ጠይቃ ነበር:: የፈንጣጣ በሽታ በአዲስ አበባ ስላለ በዚህ አሳባ ለመቀማት ሞክራ ነበር :: እሷን በሚደግፉ ሚዲያዎች ሙከራ አደረገች:: በእነ አቶ ይድነቃቸው ተከራካሪነት ኢትዮጵያ መልሳ ውድድሩን አግኝታ በቀጣዩ አመት በ1954 አዘጋጅታ ዋንጫውን አነሳች::

የሶስተኛው አፍሪካ ዋንጫ መተላለፉ ቁጥሩን አዛበው:: በጎዶሎ ቁጥር ተጀምሮ ሙሉ ቁጥር ሆነ:: በተጀመረበት የጎዶሎ ቁጥር ለመመለስ እንደገና ብዙ አመት አስፈልጓል በፈረንጆች 2012 ተዘጋጀና ወደ ጎዶሎ ቁጥር ለመምጣት አንድ አመት ብቻ አስፈልጓል:: በ2013 ተዘጋጀና እነሆ በተጀመረበት በጎዶሎ ቁጥር ቀጠለ::

የአፍሪካ ዋንጫ ሲጀመር ሶስት ሀገሮች ብቻ ተሳተፉ:: በኋላ ግን ህግ ወጥቶለት አራት ቡድኖች ብቻ እንዲወዳደሩ ተደረገ:: የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት እየወጡ ስለሄዱ ብዙዎቹ በማጣርያው ስለተመዘገቡ ስድስት ቡድኖች ብቻ እንዲሳተፉ ተደረገ:: አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ስድስተኛ አፍሪካ ዋንጫ ስምንት ቡድኖች እንዲወዳደሩ ተደረገ:: ይሄ ቁጥር ለረጅም ግዜ ሄደና ሌሎችም እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥያቄ ስለቀረበ ወደ 16 ከፍ አለ:: ይሄ የ16 ቁጥር እስካለፈው አፍሪካ ዋንጫ ሄዶ ዘንደሮ እሱም ተቀየረና 24 ቡድኖች የሚሳተፉበት ደረጃ ላይ ይገኛል::

ዘንድሮ በግብጽ ላይ የተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመርያ ግዜ ክረምት ላይ እንዲከናወን ተደርጓል:: ከምስረታው ጀምሮ በጥር ወይም በየካቲት ነው የሚደረገው:: አብዛኛው የአፍሪካ ተጫዋቾች በአውሮፓ ሰለሚጫወቱና በጥርና የካቲት ከክለባቸው ፍቃድ ወስደው ለመምጣት ብዙ ስለሚቸገሩና ክለቦችም ለመልቀቅ ስለማይፈልጉ የአውሮፓ ውድድር ሲያልቅ የአፍሪካ ውድድር እንዲደረግ በመወሰኑ ነው:: ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ ለማዘጋጀት ብትጠይቅ ከባድ የክረምት ግዜ በመሆኑ ውድድር ለማከናወን አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው::

 የአፍሪካ ዋንጫ እውነታና ትዝታ

• በአፍሪካ ዋንጫ 3 ጊዜ በተከታታይ ዋንጫ ያመጣ አሰልጣኝ የግብፅ ሐሰን ሸሃት ነው:: ሸሃት ተጨዋች እያለ በ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዲስ አበባ ላይ ከጊኒ ጋር ጎል አስቆጥሯል:: ኢትዮጵያ ከውድድር ስትሰናበት ትልቁን ሚና ያሳየውም እሱ ነው::

 • በዘንድሮ የግብጹ የአፍሪካ ዋንጫ መስራቾች ኢትየጵያና ሱዳን አልተሳተፉም:: ግብጽ ብቻ ተገኛለች::

• በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው የግብፅ ራፋት ነው:: 100ኛውን ጎል ያስቆጠረው ደግሞ የኢትዮጵያ አምበል ሉቻኖ ባሳሎ ነው:: ሁለቱም በሪጎሬ የተገኙ ናቸው:: ለራፋት ሪጎሬውን የሰጠው ኢትዮጵያዊ ዳኛ ነው:: ለሉቻያኖ ደግሞ ሪጎሬውን የሰጠው የግብፅ ዳኛ ነው::

• የአፍሪካን ዋንጫ ብዙ ያዘጋጀቸው ግብጽ ናት:: አምሰት ግዜ አስተናግዳለች:: ከአምሰቱ ሶስቱን ዋንጫ በልታበታለች:: በ1966 በዛየር ፍጻሜ ግማሽ ስትሸነፍ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ዘንድ በ2011 በሩብ ፍጻሜ ወድቃለች::

 • ብዙ ፋይናል ላይ የተገኘ ተጫዋች አራት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው የግብፅ ኢብራሂም ሐሰን ነው::

 • በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ያሸነፈ ሀገር ግብጽ ሲሆን 96 ጨዋታ ረትቷል::

• ብዙ የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳት የቻለችው ግብጽ ናት:: 7 ግዜ ስማለች::

 • -በአፍሪካ ዋንጫ በአጠቃላይ ውድድር ብዙ ያገባው የካሜሩኑ ሳሜኤል ኤቶ ነው በጥቅሉ 18 አግብቷል፣ የአይቮሪኮስቱ ሎረንት ፓኩ ሁለተኛ ሲሆን 14 አስቆጠረ፣ ፓኩ ስድስቱን ያገባው ኢትዮጵያ ላይ ነው፣ ራሽድ ያኪኒ በ13 ግብ ሶስተኛ ነው፣ መንግስቱ ወርቁ በአስር ግብ ስድስተኛ ነው::

 • በአፍሪካ ዋንጫ በሐገሮቻቸው ለዋንጫ ተገናኝተው የተሸናነፉት ናይጄሪያና አልጄሪያ ናቸው:: በ12ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ በሐገሩ አልጄርያን 3ለ0 አሸንፎ ዋንጫ ሲወስድ በ17ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አልጄሪያ ሐገሩ ላይ ናይጄሪያን 1ለ0 አሸንፎ ዋንጫ ወስዷል::

 • በግለሰብ ደረጃ በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ከተጫወቱት ውስጥ አንድም ጨዋታ ሳይቀየር በተከታታይ 26 ጨዋታ ያደረገው የናይጄሪያው አጥቂ ሙዳ ላዋል ነው:: ከ10ኛው እስከ 15ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተጫውቷል:: በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው ድሬዳዋ ላይ ነው:: ጊዜውም በ1968 ዓ.ም ነው:: ናይጄሪያ ከነሞሮኮ ጋር ድሬዳዋ ላይ ነው የተመደበው:: በውድድሩ 3ተኛ ነው የወጣው:: የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል:: አዲስ አበባ ላይ ግብፅን 3 ለ2 ረትተው የነሐስ ሜዳሊያ ሲወስዱ የማሸነፊያውን ግብ ያስቆጠረው እሱ ነበር:: ከጨዋታ በኋላ ማሊያውን አውልቆ ጥላ ፎቅ ላሉት ወርውሮ ሰጥቷቸዋል:: ይህ ማሊያ ያለው ማን እጅ ላይ ይሆን?

• ብዙ? ብዙ አፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ የቻሉት ሶስት ተጫዋቾች ናቸው:: የግብጹ አህመድ ሀሰን፤የካሜሩኑ ሪጎቤርት ሶንግና የጋናው አሳሞ አጃን ናቸው:: 8 አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈዋል:: ሪከርዱ ሁለቱ እጅ ነው:: የነበረው አሳሞ ዘንድሮ ነው የተቀላቀለው::

በአፍሪካ ዋንጫ በተለያዩ ቡድኖችን ዋንጫ ያስገኘው አሰልጣኝ ሄርቬርድ ሬና ነው፡ በ2012 ዛምቢያን፤በ2015 አይቮሪኮስትን፤ዘንድሮ በሞሮኮ አልተሳካለትም::

 በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ሀገሮችን ይዞ የቀረበው ክላውድ ሊሮይ ነው:: ካሜሩን፣ጋና፣ ኮንጎ ኪኒሻሳ፣ ቶጎ፣ ኮንጎ ብራዛቪል:: ስድስት ሀገር ይዞ ተገኝቷል::

 በአፍሪካ ዋንጫ ተጫውተውም አሰለጥነውም ዋንጫ ያገኙት ሁለት ብቻ ናቸው:: የግብጹ መሀመድ ኤልጎሃሪና የናይጀርያው ስቴፈን ኪሺ ናቸው::

 በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ያዘጋጁ ሀገሮች ግብጽ(5)፣ ጋና(4)፣ ኢትዮጵያ (2) ናቸው::

 በአፍሪካ ዋንጫ በሀገር ደረጃ ብዙ የተሳተፈ ግብጽ ነው:: 24 አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተገኝቷል::

 • በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያውን ጨዋታ የመራው ሻለቃ (በኋላ ኮነሬል) ገበየሁ ዱቤ ነው:: ገበየሁ ኢንተርናሽናል ዳኛ አልነበረም:: ይህንን ካጫወተ ከ10 ዓመት በኋላ ነው የፊፋን ባጅ ያገኘው:: ለማንኛውም በአፍሪካ ዋጫ የመጀመሪያውን ፊሽካ የነፋው የኢትዮጵያ ወታደር ነው::

• በአንድ አፍሪካ ዋንጫ 10 ግብ የደረሰ ሰው ጠፍቷል:: ከፍተኛው 9 ጎል ነው:: ይህንንም ያስቆጠረው የዛየሩ ሙላንባ ነው:: ጊዜውም በ9ነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው:: አነስተኛ ግብ የተቆጠረው በ16ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን ኮከብ ግብ አግቢ የተሸለመው በሁለት ግብ ነው:: የካሜሩኑ ሚላ፤ የአልጄሪያው ቤሉሚ ፤የአይቮሪኮስቱ ትራዎሬ እና የግብፁ አብድል ሐሚድ በጋራ ሁለት ጎል በማስቆጠር ኮከብ የሆኑበት ነው::

• በአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ ጋዜጠኞች በአንድ ጊዜ የተገኙበት በ23ተኛው ማሊ ላይ ሲሆን 1100 ጋዜጠኞች ለመዘገብ ገብተዋል::

ዝቅተኛው ደግሞ በ3ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዲስ አበባ ላይ አምስት ጋዜጠኞች ወደ ሐገር ውስጥ የገቡበት ነው:: ግብፅ 3 ቱኒዚያ 2::

 • ከምስራቅ አፍሪካ ሐገሮች በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ በመሳተፍ ኢትዮጵያ የተሻለ ሪከርድ አላት:: 10 ጊዜ ተገኝታለች:: ከአስሩ ማጣሪያውን ያለፈችው በሁለቱ ብቻ ነው:: ሌላውን በአዘጋጅነት፤ በክስ፤ ሌላው ደግሞ ቀደም ሲል ማጣሪያ ያለመደረጉ ነው:: በጠቅላላ 27 ጨዋታ አድርጋ 7ቱን አሸንፋለች:: ከሰባቱ 6ቱን ያሸነፈችው አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ውድድር ነው:: ሶስት ጊዜ አቻ ወጥታለች:: የተቀረውን ተሸንፋለች:: 60 ጎል ተቆጥሯል:: አብዛኛው ጎል የገባው ከ1ኛው እስከ 7ተኛው ባለው የአፍሪካ ዋንጫ ነው::

 • በሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የዋንጫው ክዳን ጠፍቶ 3 ቀን ሙሉ ሲፈለግ ጣይቱ ሆቴል ተገኝቷል:: ግብፆች መጀመሪያ መጥተው ያረፉት እዛ ነበር:: ክዳኑ ተሰረቀ ብለው አመልክተው ነበር:: ባይገኝ ኖሮ የዚያን ቀን ያለክዳን ነበር ለኢትዮጵያ የሚሰጠው::

 • በአፍሪካ ዋንጫ ምንም ግጥሚያ ሳታደርግ ለዋንጫ የደረሰቸው ኢትዮጵያ ብቻ ነች:: የተገኙት 4 ቡድኖች ናቸው:: ግብፅ ከሱዳን ኢትዮጵያ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ተደለደሉ:: ደቡብ አፍሪካ ጥቁርና ነጭ ተጫዋች አልቀላቅልም በማለቷ ከውድድር ተሰናበተች:: ኢትዮጵያ ከማንም ሳትጫወት ለዋንጫ ደረሰች::

• በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በአንድ ጨዋታ 4 ጎል ያገባ ብቸኛ ተጫዋች የግብፁ አዲዳየብ ነው:: እስካሁን ይህ ሪከርድ አልተሰበረም:: ጊዜውም በ1ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን ግቡንም ያስቆጠረው ኢትዮጵያ ላይ ነው::

 • በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ሪኮርድ ያላት ኢትዮጵያ ናት:: በአንድ ጨዋታ 6 ጎል ተቆጥሯል:: አንድ ተጨዋች ለብቻው 5 አግብቷል(ፓኩ) :: በምድብ ጨዋታ 12 ጎል የተቆጠረበት ኢትዮጵያ ናት:: በፋይናል ጨዋታ በ4 ጎል ልዩነት የተሸነፈ ሐገር የለም:: ኢትዮጵያ ብቻ ናት:: እነዚህ ሁሉ ሪከርዶች እስከአሁን አልተሰበሩም:: ይህን ሪከርድ ለቀጣዩ ትውልድ አሰረክበው የሄዱ ተጨዋቾች ‹‹ ፉትቦል በእኛ ጊዜ ቀረ›› ይላሉ::

 • በአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ናይጄሪያ ካሜሩንን አልቻለውም:: 3 ጊዜ ለዋንጫ ተገናኙ:: አቢጃን ላይ 3ለ1 ካዛብላንካ ላይ 1ለ0 ሌጎስ ላይ ደግሞ በመለያ ምት ካሜሩን ዋንጫውን ወስዷል:: ናይጄሪያ መቼ ይሆን በፋይናል ካሜሩንን የሚረታው?

 • በአፍሪካ ዋንጫ በአቻ ውጤት ዋንጫ የተገኘው በ10ኛ ነው:: ሞሮኮና ጊኒ አዲስ አበባ ላይ ለዋንጫ ቀርበው አቻ በመለያየታቸው ሞሮኮ ዋንጫ ወሰደ:: አራቱም ቡድኖች በዙር እንዲጫወቱ መደረጉ ነው::

• በአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀይ የወጣው ነጸረ ወልደስላሴ ነው:: ጊዜው በ1ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው:: ዳኛው ጨዋታው ሊጠናቀቅ አካባቢ ሰዓት በትክክል አልያዝክልንም በሚል ጭቅጭቅ ተጀመረ ተጨዋቾቹ በነጸረ ንግር ስለሳቁ አልቢትሩ ስድብ ባይሆን ኖሮ አይስቁም ብሎ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል::

 • በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ተመልካች የተገኘው በ15ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካይሮ ላይ ነው:: የተገናኙት ግብፅና ካሜሩን ናቸው:: በፋይናል የተገኘው 120ሺ ተመልካች ካይሮ ሲሆን እዚያው ካይሮ ላይ በ9ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አነስተኛው ዛየርና ዛምቢያ ባደረጉት የዋንጫ ጨዋታ 2 ሺ ተመልካች ተገኝቷል:: – የ አ ፍ ሪ ካ ን ዋንጫ ደጋግመው መስጠት የቻሉት ጃንሆይ ናቸው:: 3ተኛውና 6ተኛውን ለአሸናፊዎቹ ሸልመዋል::

 • ከኢትዮጵያ ወገን በአፍሪካ ዋንጫ በብቸኝነት ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎ የተሸለመው መንግሥቱ ወርቁ ብቻ ነው::

• በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ያጫወተ ዳኛ የሞርሸየሱ ሊም ኪ ነው:: 14 ጨዋታ በአምስት የአፍሪካ ዋንጫ መርቷል:: ከእነዚህ ውስጥ አንድ ጊዜ ፋይናሉን ዳኝቷል:: በሁለተኝነት ደረጃ የተቀመጠው ተስፋዬ ገ/የሱስ ሲሆን በ7 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏል:: ሁለት ጊዜ ፋይናል መርቷል:: ተስፋዬ ይህን ጨዋታ ያጫወተው በኢትዮጵያ ስም ነው::

 • በአፍሪካ ዋንጫ በተከታታይ ለዋንጫ መቅረብ የቻለው ጋና ነው:: በአራተኛ፣ በአምስተኛ፣በስድስተኛ እና በሰባተኛው ነው::

 • ጋናና ግብፅ 2 ጊዜ ዋንጫ ወስደው ለሶስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማስቀረት የመጡት ኢትዮጵያ ላይ ነበር:: ግብፅን በ3ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ አስጣለቻት:: ጋናን ደግሞ በ6ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛየር በፍፃሜው አስጣለው:: በመጨረሻ ዋንጫውን ጋና አስቀረው::

 • በአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ እስካሁን ከፍተኛ ጎል የተቀጠረው ኢትዮጵያ ላይ ነው:: በ3ተኛው አፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ግብፅን 4ለ2 ያሸነፈችበት ሲሆን በድምሩ 6 ጎል የተቆጠረበት ነው:: እስካሁን በፍፃሜ ጨዋታ 6 ጎል የተቆጠረበት ጨዋታ የለም::

• በ3ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጫዋታ ጃንሆይ አርፍደው በመምጣታቸው ውድድሩ ዘግይቶ ነው የተጀመረው:: ቡድኖቹ ሁለት ለሁለት ሆነው 90 ደቂቃውን በመጨረሻቸው 30 ደቂቃ ተጨመረ:: መንግስቱ ወርቁ 4ተኛ ጎል ሲያገባ ስለመሻ ለአይን ያዝ አድረጎ ነበር:: በዚን ጊዜ አዲስ አበባ ስታዲየም መብራት ስላልነበረው የግብጹ በረኛ ሰለጨለመ አይታየኝም ብሎ ባነሳው ጥያቄ የግብፅ ተጫዋቾች ስለመሸ አንጫወትም በሚል ባነሱት ጥያቄ ጥቂት ደቀቃ ተቋርጦ ነበር:: ጨዋታውን ለማስደገም የአምስት ቀን ጠቅላላ ወጪውን መቻል አለባቹ ስለተባለ ግብፅም አንገራገረ:: ኬኒያዊው ዳኛ ብሩክስ ኳሱን አስጀመረ ወዲያውኑ ፊሽካ ነፋና አልቋል አለ::

– የዛየር(አሁን ኮንጎ ዲሞክራቲክ) ቡድን ለ10ኛው አፍሪካ ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መጣ:: የተመደበው ድሬዳዋ ላይ ነው:: ዝንጀሮ በሳጥን ሰብስበው ነው የመጡት:: የከተማው ሰው ዝንጀሮ እንደሚበሉ ሰማ:: ከኛ ባህል አንፃር ስለማይሄድ ተቃውሞ ገጠማቸው:: ያረፉበት ሆቴልም በነሱ የተነሳ ገበያ እንዳያጣ የኔን ድስት እንዳትነካ የምሰራበትም ኩሽና እንዳትገባ:: ዛየር ጊቢ ውስጥ ድንኳን ተክሎ ድስት ገዝቶ ኩሽና ሰርቶ ዝንጀሮ ጠብሶ መብላት ጀመረ:: የዛየር ቡድን በዚህ የተነሳ ደጋፊ አልነበረውም:: አንዳንድ ተመልካቾች ከደንገጎ ጋራ ዝንጀሮውን ጨረሰ በማለት ረገመው መሰለኝ ከዚያ በኋላ ዋንጫ አግኝቶ አያውቅም:: ዛየር ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ያገኘው በ6ተኛ አፍሪ ዋንጫ ኢትዮጵያ ላይ ነው::

በገቡበት አመት ዋንጫ ያገኙት ጋናና ደቡብ አፍሪካ ናቸው:: ጋና በአራተኛው ደቡብ አፍሪካ በ20ኛው :: ሁለቱም በሀገራቸው ነው ዋንጫውን ያነሱት::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top