“ጨፍግጓል ዛሬ ጨልሟል ቀኑ
ብርሃን ጠፍቷል፤ ከፍቷል ዘመኑ…”
እያለ አንዱ እያማረረ፤
ቀንን ከዘመን እያሳበረ፣
ሲነጉድ አየኹት አንገቱን ደፍቶ፤
ባየው በሰማው እጅግ ተከፍቶ፡፡
… ትዕግስት አጥቶ’ጂ -ጥቂት መጠበቅ
መቻልን ችሎ -ተስፋን መሰነቅ…
ያየው ነበረ-
ቀናቶች አልፈው ዘመን ሲተካ፤
ግራሮች ፋፍተው ሲኮስስ ዋርካ፤
ሌቱ ሲወግግ፣ ቀኑ ሲፈካ፡፡
ያውቀው ነበረ-
ሊነጋጋ ሲል እንደሚጨልም፤
የጨፈገገው እንደሚጠፋ-
የጨለመው እንደሚከስም፡፡
ምንጭ- “ሳተናውና ሌሎች…” የአጫጭር
ልቦለዶችና የግጥም መድበል
(ደረጀ ትዕዛዙ)
