ስርሆተ ገፅ

” የሠርግ ዝግጅት በራሱ ጥበባዊ ሥራ ነው … “ -ግዛቸው አርጋው በዳሶ

ትውልዱ አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ከተማ፤ እድገቱ ደግሞ ኮልፌ ነው:: አርቲስት እና ኢንስፔክተርም መለያ ማዕረጎቹ ናቸው:: ይህ የታዋቂው የጉራጌ ባህል ዘፋኝ አርጋው በዳሶ ልጅ፤ ዛሬ ደግሞ የሠርግ ፕሮ ግራም አማካሪና ፕሮቶኮል (wedding planner) ነው:: ግዛቸው ይባላል:: ዛሬ የዚህ አምድ እንግዳ ያደረግነው ከሙያው፣ ከቤተሰቡ የኪነ ጥበብ ወዳጅነት እና ከሕይወት ጉዞው የሚያካፍለን ቁምነገር በመኖሩ ነው:: መልካም ንባብ::

ታዛ፦ ኢንስፔክተር የሚለው ማዕረግ ከየት መጣ?

ግዛቸው፦ ፖሊስ ነበርኳ:: ፖሊስ ውስጥ ከ27 ዓመት በላይ አገልግያለሁ:: ጅማሪዬ ሙዚቃ ክፍል ነው:: አገር ፍቅር እና ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል በተወዛዋዥነት አገልግያለሁ:: ከለውጡ በፊት (1983) በአስመራ የውዝዋዜ አሰልጣኝ ነበርኩ:: እዚያ አንደኛ ዲቪዚዮን ጠረጴዛ ቴኒስ እጫወትም ነበር:: ከዚያ ተፈናቅዬ ከመጣሁ በኋላ፣ ፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ገብቼ ከአርቱ ውጪ ደወሌ፣ አዋሽ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ውስጥ በሀላፊነት ሰርቻለሁ:: ፖሊስ ውስጥ የገባሁት ግን በልጅነቴ ነው::

ታዛ፦ የትኛው ክፍል? መቼና በምን ሁኔታ ነው ለመቀጠር የቻልከው?

ግዛቸው፦ በ1975 ዓ.ም ነው ፖሊስ ሰራዊት የተቀጠርኩት:: በስልጠና ላይ ስሜቴ ወደ ጥበቡ ስላደላ ከሁለት ዓመት በኋላ በውድድር ወደ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ተዛወርኩ:: ያኔ አባቴ እዚያው ሙዚቃ ክፍል ባልደረባ ነበረ:: ተገጣጠምን:: ይመስለኛል የአባቴ የሙዚቃ ሙያ ሳይታወቀኝ እንድሳብ አድርጎኛል::

 ታዛ፦ እህትህም እዚያው ክፍል ተወዛዋዥ ነበረች አሉ::

ግዛቸው፦ ምን አሉ ብቻ:: ነው እንጂ! የሚገርመው እህቴ ኢንስፔክተር አበራሽም እዚያው የሙዚቃ ክፍል ከኔ ቀድማ በተወዛዋዥነት ተቀጥራ ነበር:: ከአባታችን ጋር በአንድ መስሪያ ቤት በአንድ መድረክ ላይ ብዙ ጊዜ ተጫውተናል:: እንዲያውም አባታችንን መሃል አድርገን ስንወዛወዝ የሚያሳይ ፊልም በቴሌቭዥን ደጋግሞ ይቀርብ ነበር:: ይህ ታሪክ ዛሬም አለ:: በዚህ ሁኔታ ግን ስንጀምረው አባታችን ደስተኛ አልነበረም:: ብንማርና በሌላ ሙያ ብናድግ ነበር ምኞቱ:: የሆነው ሆኖ ያንን ያህል ዓመት በአርቱና በቢሮ ስራ አገልገዬ የዛሬ 5 ዓመት ገደማ ነው ጡረታ የወጣሁት:: ተመስገን አይደል?

ታዛ፦ በዚያ ዘመን አብረውህ ከሠሩ ታዋቂ ሙዚቀኞች የተወሰኑትን ልትጠቅስልን ትችላለህ?

ግዛቸው፦ ብዙ ናቸው:: ለምሳሌ የዛሬው ተወዳጅ የሙዚቃ ሰው ቴዲ አፍሮ አባት የመድረክ አስተዋዋቂው ካሳሁን ገርማሞ እና እናቱ ተወዛዋዥ ጥላዬ አብረውን ነበሩ:: ሂሩት በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ሻምበል መስፍን ኃይሌ፣ አያሌው መስፍን፣ ጌታቸው መኩሪያ (ሳክስፎኒስት)፣ መኮንን መርሻ (ትራምፔት ተጫዋች)፣ እና ዋለለኝ አዘነ ነበሩ:: ዛሬ ግን ሌላ ስራ ላይ ነኝ:: የሠርግ ስራ::

ታዛ፦ ሁልጊዜ ደስታ ላይ ነሃ? እንዴት ነው የሠርግ ስራና ገበያው?

ግዛቸው፦ ተመስገን ነው:: እግዚአብሔር ይመስገን:: ሁልጊዜም የደስታ ቦታ እንድውል አድርጎኛል:: ገበያ ሞልቷል:: ሠርግን ማሳመር የመሰለ ደስ የሚል ነገር ምን አለ? ዓለማቸውን ለሚያዩ ሙሽሮች የደስታን መንገድ ስትመራቸው ደስ ይላል:: በስራዬ ተደሳች ነኝ:: እዚህ ላይ ለመድረስ ግን ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችንና ችግሮችን አሳልፌያለሁ:: “ሁሉም ያልፋል” አይደል የሚባለው::

 ታዛ፦ ምን ምን አገልግሎት ነው የምትሰጠው?

ግዛቸው፦ ዛሬ ባለኝ ሙያ በሠርግ ዙርያ የማማከር ስራ እሰራለሁ:: ይህንንም ስል ከሽምግልና ጀምሮ ያሉ ሂደቶች ምን መሆን እንዳለባቸው፣ የድግሱ ወጪ ከጋብቻ በኋላ ኑሮን መጉዳት እንደሌለበት፣ የተጋቢዎቹ ማንነትና የመጠናናት ሁኔታ እስከ ምን ድረስ መሆን እንዳለበት፣ ከጋብቻ በፊትና በኋላ ስለሚኖራቸው ህይወት እና የሚገጥማቸውን ፈተናና መልካም አጋጣሚ እንዴት ማስተናገድ እንደሚኖርባቸው፣ ሌላ ሌላውንም እናማክራቸዋለን:: ከዚህ በተጓዳኝ ከአጋሮቼ ጋር በመሆን ሠርግን ማሰናዳት ማለትም ፕሮግራሙን መምራት፣ ፕሮቶኮሉን፣ የሙዚቃውን፣ የአልባሳቱን፣ አጠቃላይ ባህሉን፣ ወጉን፣ ሃይማኖቱን በጠበቀ መልኩ ጋብቻ እንዲፈፀም አድርጋለሁ:: በዚህም ብዙዎች ተጋብተዋል:: ታዋቂዎችን ጨምሮ::

ታዛ፦ ለምሳሌ?

ግዛቸው፦ ለምሳሌ ከጥበብ ሰዎች የፊልም ባለሙያዋ ሰላም ተስፋዬ፣ የሙዚቃ ሰው ታደለ ሮባ፣ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፣ ቤዝ ጊታር ተጫዋቹ ሚኪ:: 25 የሚሆኑ ታዋቂ ዘፋኞች ቆመው ”ሙሽራዬ“ ብለው የተቀበሉበት ሠርግ ነው፣ ሌሎችም አሉ:: በማማከርም ሠርጋቸውን በማሰናዳትም::

ታዛ፦ በአገልግሎትህ ባንድ አለህ?

ግዛቸው፡- ለጊዜው የራሴ ባንድ የለኝም:: ባንድ ያላቸውን እከራይላቸዋለሁ:: በአቅማቸው:: ማንኛውንም ነገር ነው የማቀርበው:: የባህልም፣ የዘመናዊም፣ ከፈለጉም ዲጄ፣ አልያም አሙቁልኝ የሚባሉትን አጫፋሪዎች ሳይቀር የማቅረብ ልምዱም ሆነ ግንኙነቱ አለኝ:: እንደ ሙሽሮቹ እና ቤተሰቦቻቸው ፍላጎት ነው ይህ የሚሆነው:: ካሜራም፣ ሆነ ሌላ ሌላውን የማቅረብ ኃላፊነት አለብኝ:: አሁን በለኝ አቅሜ ሁሉንም በግሌ ጠቅልዬ ልያዝ ካልኩኝ ይከብደኛል:: ለዚህ ነው አጋር አለኝ የምለው:: እኔ ሁሉም በየሙያ ባለቤቱ ሲሰራ ነው የተሳካና ያማረ ሠርግ የሚሆነው:: ያንን ማመቻቸት ነው የኔ ዋና ተግባር::

 ታዛ፦ ምን አይነት ሠርጎችን ነው የምትመራው?

ግዛቸው፦ ሆቴልም፣ ቤትም፣ አዳራሽም፣ ድንኳንም፣ መናፈሻም ሠርግ ይደገሳል:: ሁሉም ስፍራ እንደተጋቢዎች አቅም ሠርጉን አመቻቻለሁ:: ዋጋዬ የተመጠነ ነው፤ ደንበኞቼ ያውቁታል:: ሙሽሮች በዘመናዊ ሊሙዚን የሚንፈላሰሱበት፣ ታዳሚው ውስኪ እንዲራጩ የሚያደርጉበት እንደ ሸራተን ባሉ ትላልቅ ሆቴሎች እና አዳራሾች የሚዘጋጁ ሠርጎችን መርቻለሁ:: የደጋሾች አቅም ይለያያል:: እጅግ በጣም የናጠጡ ሃብታሞች እንዳሉ ሁሉ፤ መለስተኛና አነስተኛ ደጋሾችም አሉ:: ሁሉንም እንደየ አቅማቸውና እቅዳቸው የድርጊት መርሃግብር ነድፌ ስርአቱን አመቻቻለሁ::

 ታዛ፦ የአገራችን የሠርግ አይነቶች ስንት ናቸው?

ግዛቸው፦ በዋናነት አምስት ናቸው:: አንደኛው ዓለማዊ ይባላል:: በዘመናዊ ሠርግ የሚከወን ነው:: ሁለተኛው በባህላዊ ደንብ የሚከወን ነው:: በዓለም ላይ ያሉ ሠርጎች በእነዚህ ሁለቱ ይጠቃለላሉ:: በእምነቱ ስንሄድ ደግሞ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህገ ደንብ የሚካሄድ ነው:: በስርአተ ተክሊል እና በቁርባን የሚፈፀም ነው:: እሱ ራሱ ሁለት አይነት ነው:: አንደኛው እዚያው ቤተክርስቲያን ሁሉም ነገር የሚያልቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የቤተክርስቲያኑ ህግና ደንብ ጋብቻው ከተፈጸመ ከሳምንት በኋላ ዓለማዊ ልብስ ተለብሶ (ቬሎ ተደርጎ) የሚፈፀም ነው:: የቤተክርስቲያኑን ህግና ደንብ ተከትለው:: በባንድ ዓለማዊ ሙዚቃ የሚያከናውኑም አሉ:: ይህ እንደ ተጋቢዎቹ ፍላጎትና ምርጫ ነው:: ትክክል ነው አይደለም ለሚለው ምላሽ መስጠት አልችልም:: ወደ ሙስሊሙ ስንመጣም ሁለት አይነት ጋብቻ ነው የምናየው:: አንዳንዱ ሙሉ ለሙሉ በነሺዳ የሚያልቅ ሠርግ አለ:: አላህን በማክበርና በማመስገን:: አንዳንዶች ደግሞ ነሺዳንም ዓለማዊ ሙዚቃንም ቀላቅለው የሚፈፅሙ አሉ:: ሌላው አምስተኛው አይነት ሠርግ ወንጌላዊ አማኞች የሚፈጽሙት ነው:: እነሱም በመንፈሳዊ መዝሙር፣ ዓለማዊውንም ሆነ መንፈሳዊውን ስርአት እንደየተጋቢዎቹ ምርጫ ይፈጽሙታል:: እነዚህን ሁሉ አይነት ስርአቶች ተከትለን እኔና የእኔን አይነት ስራ የሚሰሩ ሁሉ ስርአቱን እናስፈጽማለን::

 ታዛ፦ በዚህ ሁኔታ ምን ያህሉን ሠርግ አሰናድቻለሁ ብለህ ታስባለህ?

ግዛቸው፦ በቁጥር መግለፅ ይከብዳል:: ቤቴ ግን መረጃው በደንብ ተቀምጧል:: ያንን ማየት ሊያስፈልግ ነው:: በግምት ግን ቢያንስ በሠርግ ወቅት በወር ስምንት ዘጠኝ ሠርግ እንሰራለን:: ቅዳሜና እሁድ ሁል ጊዜ ሠርግ ላይ ነኝ:: አንዳንድ ጊዜ ማክሰኞም ሃሙስም እንሰራለን:: በዓመት ከ60 በላይ ሊሆን ይችላል::

ታዛ፦ ከሌሎች መሰል የሠርግ አመቻቾች አንተን የሚለይህ ነገር አለ?

ግዛቸው፦ አዎ! ቀብድ አለመቀበሌ:: በዚህ በአገራችን የመጀመሪያው ሰው ልሆን እችላለሁ ብዬ አስባለሁ:: ይህንን ሁሉ ሠርግ ስሰራ አንድም ጊዜ ቀብድ የተቀበልኩበት ሁኔታ የለም:: መጀመሪያ እንዋዋላለን፣ ስራውን ሳጠናቅቅ ክፍያዬ ይፈፀማል::

 ታዛ፦ ለምን?

 ግዛቸው፦ የደንበኞቼ ቃላቸውና ውላችን ቀብዴ ነው:: ሰው ተደስቶ ነው እንጂ አዝኖ እንዲከፍለኝ አልፈልግም:: ካዘነ ባይከፍለኝ እመርጣለሁ:: ደስ ብሎት ሲከፍለኝ በረከቱ ይበዛልኛል:: ያኔ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ:: ለቀደመው ውልና ቃሌ እታመናለሁ:: ባለፈው ጥር የእህቴ ሠርግ ነበረ:: እኔ ግን ቀድሜ የያዝኩት ውል ስለነበረ የእህቴን ሠርግ ሳላሰናዳ ቀርቻለሁ:: ልጄ ታሞ ሆስፒታል አስገብቼ የሰራሁት ስራ አለ:: እግዚአብሔር ግን ቃሌን በመጠበቄ ልጄን አትርፎልኛል:: በዚህ በዚህ ሙሉ እምነት አለኝ::

ታዛ፦ ብዙውን ጊዜ ሠርግ ላይ ከመዝናናቱ፣ ከመደሰቱ፣ ከመጨፈሩ በዘለለ ጠብ ቢጤም አይጠፋም:: በታዳሚውም ሆነ በሙሽሮቹ አካባቢ ይህ ሊከሰት ይችላል፤ ምናልባት በዚህ ረገድ ለየት ያለ ገጠመኝ ካለህ?

ግዛቸው፦ በጣም ብዙ አለኝ እንጂ:: ብዙ! ሠርግ በደስታ የተሸፈነ ቢመስልም ብዙ ችግሮች አሉት:: ሠርግ በራሱ ውድድርና ፉክክር ስላለበት የሚከተለው መዘዝ ብዙ ነው:: ፊት ለፊት የሚታየው ወጪ ያበሳጫል:: በዚህ በኩል ሙሽሮች ዘንድ የተፈጠረው ፀብ ወደ እኔም ሆነ ታዳሚው ዘንድ ይመጣል:: አላስፈላጊ ንግግሮች፣ ቁጣዎች፣ ኩርፊያዎች፣ ከዚያም ሲያልፍ ጉሸማዎች አሉ:: “እነዚህ ሰዎች ሳይወስኑ ነው እንዴ ወደ ሠርግ የመጡት” እስከሚያስብል ድረስ ትዝብት ውስጥ የሚወድቁ ጥቂት አይደሉም:: የሚገርምህ ቀን ተጨፍሮላቸው ማታ የተለያዩ አሉ:: ከ800 ሰው በላይ የታደመበት፣ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት፣ በሀመር እና በሌሎች ዘመናዊ መኪናዎች የታጀበ፣ በታዋቂ ባንድ የታጀበ ሠርግ ነው:: ሙሽሮቹ በማያስታውቅ ሁኔታ ቀን ሲናቆሩ ነበር የዋሉት፤ እኔና ሚዜዎች ለማስማማት ሞክረን የተሳካ መስሎን ነበር፤ ማታ ግን ቤተዘመድን ያሳፈረ ነገር ተፈጸመ:: 300 የሚሆኑ ሰዎች ወንዱ ቤት ሙሽሮችን ሊቀበሉና ራት ሊጋብዙ በተሰናዳው ድግስ ላይ ሙሽሪት አልተገኘችም:: ወንዱ ቤት መኪና እስክናዞር አዘናግታ በኮንትራት ታክሲ ጠፋች:: እንደ ወጉ የዳቦ ስም ሊወጣ፣ ሊጨፈር ነበር:: ባንድ ሁሉ አለ:: ግን ማፈሪያ ሆንን::

ታዛ፦ እና መጨረሻው ምን ሆነ?

ግዛቸው፦ ምን ይሆናል በብልሃት አለፍነው:: ሙሽራው በጣም አዝኖ ተቆጥቶ ነበር:: አልቅሶ ሲያበቃ ከነ ሚዜው አጅበን ይዘነው ገባን:: ሙሽራዋን ባለማየቱ ህዝቡ ሲደነግጥ ”ይቅርታ አድርጉልን ቀን የበላችው ምግብ ስላልተስማማት ሆስፒታል ገብታለች:: ሃኪም ትረፍ ስላለን ሙሽራውን ይዘን መጥተናል” ብለን ቅጥፍ አደረግን:: ከዚያ በቀዘቀዘ መንፈስ ህዝቡን እራት አስበልተን አለፍነው::

ታዛ፦ ከዚያስ?

ግዛቸው፦ ከብዙ ሙግትና ውዝግብ በኋላ ከሁለቱም ቤተሰቦች የሚፈሩና የሚከበሩ ሰዎችን ይዤ ቤተ ክርስቲያን ወስጄ እንዲታረቁ አደረኩ:: መልስ ተደርጎ ጉዳዩ ተደመደመ:: ዛሬ ሁለቱም አሜሪካን አገር ናቸው:: እንዲህና እንዲህ መሰል ገጠመኞቼ ብዙ ናቸው:: ከምንም በላይ ግን ፍቺ ውጉዝ ነው:: እግዚአብሔር አይወደውም:: ሰው እንዴት አድርጎ የግራ ጎኑን ነቅሎ ይጥላል? ከባድ ነው:: ጋብቻ ከመመስረት በፊት ሊገጥሙ የሚችሉ እክሎችን እንዴት በጋራ ማስወገድ እንደሚገባ ማወቅ ያሻል:: ልብ ለልብ መግባባት፣ መተማመን፣ መፋቀር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆን አለባቸው:: ቁሳዊ ነገሮች አላፊ ጠፊ ናቸው:: ያንን ነው ማሰብ የሚገባው:: ሌላው ሰርግ ላይ የታዘብኩት የብሔር ጉዳይ የፀብ መነሻ መሆኑን ነው…

ታዛ፦ እንዴት?

ግዛቸው፦ አንዳንድ ሠርግ ላይ ሙሽሪትና ሙሽራው የተለያየ ብሔረሰብ አባል ይሆኑና ጭፈራ ላይ በሚመረጠው የዘፈን ምርጫ ሰበብ በታዳሚው ወይም በቤተዘመድ መካከል ግጭት ይፈጠራል:: ምናልባት ዘፈኑ ወደ አንድ ብሔር አድልቶ ሊሆን ይችላል:: ወይም ”የእኔ ሊጎላ ይገባል“ በሚል ግብዝነትም ሊፈጠር ይችላል:: በዚህ ምክንያት ዛሬ ዛሬ ጠብና ጭቅጭቅ እየበረከተ ነው:: አንድ ጊዜ በአንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ በተዘጋጀ ሠርግ ላይ ሁለት ዲጄ ግራና ቀኝ ቆሞ የሁለቱንም ብሔረሰቦች ዘፈኖች በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በአንድ ላይ እንዲያስጨፍሩ የተደረገበትን ሠርግ መርቻለሁ:: ይህ መጯጯህ ነው እንጂ መደሰት አይደለም:: ፈተና ነው:: የፈተና ዘመን:: የሠርግ ዋና ዓላማ ሙሽሮች እወቁልን ተጋብተናል፣ ተጣምረናል የሚሉበት፣ በወላጆቻቸው የሚመረቁበት ነው:: መብላት መጠጣቱ፣ መጨፈሩ ሁለተኛ ነገር ነው:: ስለምን ነው እንዲህ መሆናችን? ስለምን የተወደደ ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ ፍቅራችንን እናጣለን? ኧረ ቆም ብለን እናስብ:: ይህ ነገር ወዴት እየወሰደን መሆኑን እንገንዘብ:: አንድነታችን፣ መከባበራችን፣ መፋቀራችን ነው የሚበጀን:: እኔ በዚህ ሁኔታ እየተበሳጨሁ ነው…::

ታዛ፦ በአመዛኙ ሰርግ ላይ መጠጥ አለ፤ መጠጥ ባለበት ደግሞ አንዳንድ አላስፈላጊ ነገሮች መከሰታቸው አይቀርም:: በዚህ በኩል ያስተዋልከው ወይም የታዘብከው ነገር አለ?

ግዛቸው፦ በዚህ በኩል ሊነገር የሚችል ገጠመኝ የለኝም:: ግን እንዳልከው አንዳንድ ነገሮች አይጠፉም::

ታዛ፦ አንተስ ትጠጣለህ? ምናልባት ለስራ ቅልጥፍና ያግዛል በሚል ትንሽ ትቀምስ እንደሆን?

ግዛቸው፦ በፍፁም! አይደለም መጠጥ ምግብ እንኳን አልበላም:: ከቤቴ ነው ተጠናቅቄ የምወጣው:: መጠጥ ትንሽ ያደርጋል:: ይህንን ስል ይቅርታ እየጠየኩ ነው:: እየጠጣህ ከሚያይህ ሰው ጋር የፈለገ ቁም ነገር ብታናግረው እንኳን ያንተ እውነት አይታመንም:: መጠጥ አዕምሮ እንደሚቀይር ይታወቃል:: ጠጪ አዳማጭ የለውም:: ስለዚህ በእኔ ስራ ውስጥ መጠጥ ቦታ የለውም:: እኔ ቁጭ ብዬ ስበላ የሆነ ነገር የሚበላሽ ሆኖ ነው የሚታየኝ:: ደሞም እውነት ነው:: ስራ ያበላሻል:: በእኔ እምነት መጠጥ ከስራ ውጪ ነው ተገቢነቱ:: አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በተገቢው ቦታ ከመሰሎቼ ጋር እየጠጣሁ እዝናናለሁ:: በኃላፊነት ስሜት:: ግን ለዚያ የሚተርፍ ጊዜ የለኝም:: ሁለት ሴት ልጆቼን ያለ እናት ነው የማሳድጋቸው:: የ17 እና የ19 ዓመት:: እናታቸው ካለፈች 16 ዓመት መሆኑ ነው:: ስለዚህ ያ ኃላፊነቴን ጠንቃቃ ያደርገዋል:: ለልጆቼ እናት የምትሆናቸውን ሌላ ጥሩ የትዳር አጋር አግኝቻለሁ:: በበፊቷ ስሜቴ ቢጎዳም በአሁኗ እየተጽናናሁ እኖራለሁ ማለት ነው:: ብዙ አናገርከኝ…::

ታዛ፦ ደሃ በበዛበት አገር፣ ችግረኞች በተበራከቱበት አገር ሠርግ መደገስ ተገቢ ነው?

ግዛቸው፦ በእኔ እምነትና አስተያየት በአንጻራዊነት ተገቢም የሚሆንበት የማይሆንበትም ሁኔታ አለ:: ሰው ለፍቶ ደክሞ ያገኘውን ሃብት ለመደሰቻ ቢያውለው ክፋት የለውም:: አንዱ መደሰቻ ደግሞ ሠርግ ነው:: ለሙሽሮች እኮ ይህ ቀን ዓለማቸው ነው:: ተመልሰው አያገኙትም:: እንዳልከው ደግሞ የሚበላው ያጣ በሚታይበት ደሃ አገር ላይ አላስፈላጊ ወጪ ማውጣቱ አይታየኝም:: ሌሎችን ለመርዳት፣ ለመደገፍ እያሰቡ ደግሞ ቢያስደርጉት መታደል ነው:: ድል ያለ ሠርግ ከመደገሳቸው በፊት መቄዶኒያ ሄደው ችግረኞችን አብልተው፣ አጠጥተውና አልብሰው የሚደሰቱ መልካሞች እንዳሉ አውቃለሁ:: ሙሽሮች ሌሎችን ከማሰብ ባለፈ የወደፊት ኑሯቸውን በማይጎዳ መልኩ ቢያዘጋጁ እኔ መጥፎነቱ አይታየኝም:: መግለፅ ስላላስፈለገ ነው እንጂ ታይታ የማይወዱ መልካምና በጎ አድራጊዎች እንዳሉ አውቃለሁ:: እነዚህ ለነፍስና ለስጋቸው እንደሚጠቅም የተረዱ ናቸው:: ስለዚህ በዚህ እሳቤ ድሃ ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን፣ ወገኖቻቸውን መደገፍ ሲገባቸው በግብዝነት ስላላቸው ብቻ ብራቸውን የሚያፈሱ በየትኛውም መመዘኛ ተጎጂዎች ናቸው:: በአጠቃላይ ግን ሠርግ አስፈላጊ ነው? አይደለም? የሚለው ጉዳይ አከራካሪ አይሆንም:: በደንብ ያስፈልጋል:: ክዋኔው ነው አካራካሪ የሚያደርገው::

 ታዛ፦ ለመሆኑ ሠርግ የማማከሩና የፕሮቶኮሉ ወይንም መርሃግብሩን የመምራቱ ሃሳብ እንዴት መጣልህ? መቼ እና እንዴት ጀመርከው?

ግዛቸው፦ በአንድ ጊዜ የሆነ አይደለም፣ ሂደቶች አሉት:: እንደሚታወቀው አባቴ በሠርግ ሙዚቃ ስራ የታወቀ ነው:: እንዲያውም ”አለም ብሬ“ ነው የሚባለው፤ በቅፅል ስሙ:: ነፍሱን በገነት ያኑርልንና ዛሬ በህይወት የለም:: እና አባቴ በእድሜ እየገፋ ሲመጣ እኔ ነበርኩ በየሰርጉ በመኪና የማመላልሰው:: ታዲያ በዚህ ምክንያት በየሰርጉ ስታደም የማያቸው ብዙ የስነ ስርአት ስህተቶች ነበሩ:: ባለቤት የሌላቸው ጉዳዮች ይገጥሙኛል:: በቀላሉ የሚሰሩ ግን በቸልታና በመዘናጋት ሊያምሩ የሚገባቸው ሰርጎች ሲበላሹ ይገጥሙኛል:: ይህን ትዝብቴን በማስታወሻዪ መመዝገብ ያዝኩ:: ነገሩን ሳብላላው ለዚህ ባለቤት ብሆንስ የሚል ስሜት አደረብኝ:: በሠርግ ላይ የሚወጣው ወጪ ቀላል አይደለም:: ገንዘብን፣ ጊዜን፣ አዕምሮን ይጠይቃል:: የአንድ ሰው ስራ ብቻ አይደለም:: ሙሽራ፣ ሚዜ፣ ቤተዘመድ፣ አጃቢ፣ አዝማሪ (ባንድ)፣ አለባበስ፣ መኪና፣ የምግብ ዝግጅት፣ የዝግጅት አዳራሽ (ድንኳን) ወዘተ የሚያቀናጅ በመጥፋቱ ብዙ የተደከመበትና ወጪ የፈሰሰበት ሠርግ ሲበላሽ፣ ታዳሚው ትዝብት ውስጥ ሲወድቅ ስለማይ ለምን እኔ የዚህ ባለቤት አልሆንም? የሚል ጠንካራ ወኔ ይዤ ገባሁበት:: የዛሬ 9 ዓመት ገደማ:: ፖሊስ ቤት ያሳለፍኩት ሕይወቴ እና አርት ውስጥ መቆየቴ ለዚህ ስራ ጠቅሞኛል:: ሠርግ በራሱ አርት ነው:: ሁለቱንም በማቀናጀት ወደ ስራው ስገባ ውጤታማ ሆንኩ:: እግዚአብሔር ይመስገን ዛሬ ተፈላጊ ነኝ:: ሙያው ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከገባሁበት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ስራ ሲደራረብብኝ የምመልሰው ይበልጣል እንጂ ስራው ሞልቷል:: ህይወቴን የምመራው በሱ ነው:: ሁለት ልጆቼን የማስተዳድርበት በቂ ገቢ አለኝ::

ታዛ፦ አባትህ አርጋው በዳሶ ታዋቂ የጉራጊኛ ባህል ዘፋኝ እንደሆኑ ይታወቃል፤ በጭንቅላታቸው ሁሉ ቆመው መጨፈራቸው ልዩ ያደርጋቸው ነበር:: ከዚያ ነጋዴም፣ የብዙ ቤተሰብ አስተዳዳሪም እንደሆኑ ይነገራልና እስኪ ስለሱ አጫውተን?

 ግዛቸው፦ ትክክል ነህ አባቴ ከተለያዩ የትዳር አጋሮቹ 18 ልጆችን አፍርቷል:: ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ አሥራ አምስታችን በህይወት አለን:: ሃያ ስምንት የልጅ ልጆችና ስድስት የልጅ ልጅ ልጆች አሉ:: ልጅ በልጅነት እና ልጅ በእድሉ ያድጋል የሚለውን ብሄል በአግባቡ የተገበረ ነው አባቴ …(ሳቅ):: ይህ ሲሆን ምክንያት ነበረው:: አባቴ ጉራጌ ነው:: ገጠር ውስጥ ቤት መሬት ነበረው:: ከቦታ ወደ ቦታ ለስራና ለኑሮ መዘዋወር ሲመጣ ንብረት ለማስተዳደር ሲባል ከአንድ በላይ ማግባት ይቻል ነበር:: በዚህ ሰበብ ነው ዘሩን ያበዛው:: እንዲያውም አንዷ ባለቤቱ ቶሎ ልጅ አልመጣ ቢላት እናቴ ልጅ እንዲሰጣት የተሳለችበትና ስለቷ የሰመረላት ሁኔታ አለ:: ልጇ ብርቅነህ ይባላል:: በዘፈን ዓለም አባታችንን ይተካል ብለን ተስፋ አድርገንበታል:: በዚያው መስመር እየሄደ ነው::

ታዛ፦ ይህንን ሁሉ ቤተሰብ መምራትና ማስተዳደርኮ ቀላል አይደለም፤ የገቢ አቅማቸው ደግሞ…

ግዛቸው፦ የሚገርመው አባቴ ህይወቱን የኖረው እንደ አርቲስት ብቻ ሳይሆን እንደ ነጋዴም ነው:: ልጆቹንም ሆነ የልጅ ልጆቹን ሲያስተዳድርና ሲደግፍ በመንግስት ስራ በሚያገኘው ደመወዙ ብቻ አይደለም:: ጥሩ ነጋዴም ነበር:: በተለያዩ ዘመናት ጠጅ ቤት፣ ቡና ቤት፣ ላውንደሪ ቤት ነበረው::

ታዛ፦ ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ እንዴት ነው?

ግዛቸው፦ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳት እንኖራለን:: ውጪም ያሉ አሉ:: ለአመት በዓል ጊዜ ሁላችንም እንደተለምዷችን አባታችን ቤት ተሰባስበን ነው የምናሳልፈው:: የልጅ ልጆቻችን ጭምር የሚሳተፉበት የቤተዘመድ ማህበርም አለን:: እቁብም እንጥላለን:: የቸገረው ወይንም ገንዘብ ለሚያስፈልገው ቅድሚያ እንሰጣለን:: በተቻለን መጠን ዛሬ በሕይወት የሌሉት የአባት እናቶቻችንን ፍላጎትና ምኞት ለማሳካት በምርቃቶቻቸው ተከልለን እንኖራለን::

ታዛ፦ ጋብቻን ለሚፈሩ ወይም እንዲሁም እቅድ ላይ ላሉ ከተሞክሮህ ተነስተህ የምትመክረው አለ?

ግዛቸው፦ እንደ እግዚአብሔር ቃል ጋብቻ ቅዱስ ነው:: ቅዱስነቱ በየትኛውም ሃይማኖት ነው:: ማንም ቢሆን ዘር እንዲተካ ይፈለጋል:: ከዝሙት ለመዳንም ሆነ ተጋግዞ ለመኖር እጅግ አስፈላጊ ነው:: የትውልድ ሰንሰለት የሚቀጥለው በጋብቻ በተሳሰሩ ጥንዶች ነው:: ስለዚህ ማንም ቢሆን በንፁህ ልብ አምሳያውን ፈልጎ ቢያገባ ደስ ይላል:: ንፁህ ልብ ከያዝን ደግሞ እግዚአብሔር ይደግፈናል፤ ያሰብነውን ያሳካልናል:: ትዳርን አንፍራው:: ለማግባት የሚያስቡ ደግሞ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ሠርጋችሁን ደግሱ ነው የምለው::

ታዛ፦ በመጨረሻ የሕይወት ጉዞህ ምን መልክ ቢኖረው ደስ ይልሃል?

ግዛቸው፦ እሱን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው:: እኔ ግን ይህን ሙያዬን በማሳደግና በማስፋፋት መቀጠል እመኛለሁ:: እጥራለሁም:: የሰርግ ፕሮግራሞችን ከማስተባበርና ከመምራት ባሻገር ቁሳዊ አቅርቦቶችን ሁሉ እራሴን ችዬ ማሰናዳት እፈልጋለሁ:: ለመንግስት የሚከፈለውን ግብር እየከፈልኩ አገሬንና ሕዝቤን በሙያዬ ማገልገል ነው እቅዴ:: ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ አገር ሰላም ስትሆን ነው:: ሠርጉ፣ ጭፈራው፣ ድግሱ፣ መዝናናቱ የሚኖረው አገር ሠላም ስትሆን ነው:: ያንን አያርቅብን ነው የምለው::

ታዛ፦ መልካም ግዛቸው:: ሃሳብህና ምኞትህ እንዲሳካልህ እንመኛለን፤ እናመሰግናለን::

ግዛቸው፦ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እኔም አመሰግናለሁ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top