አድባራተ ጥበብ

ዕድሜያችሁ ሠላሳ ነው

ዕድሜያችሁ ሠላሳ ነው ይለናል አንድ ስሙ የማይታወቅ የሰፈራችን ሰው። ልደት በሚከበርበት ቦታ ሁሉ እየተገኘ። በዚህም ብቻ አያበቃም “የምትሞቱትም ሞትን ስለምትበሉት ነው።“ ይለናል በሰፈራችን የተጣለ የለቅሶ ድንኳን ውስጥ እየተገኘ። አሁንም በዚህ ብቻ አያበቃም ይህ የሰፈራችን ሰው። “ሰው የምትሆኑት ለሰው በተፈጠረው መንገድ ላይ ብቻ በራሳችሁ ፈቃድና ምርጫ ጉዞ ስትጀምሩ ነው።” ይለናል ይኸው ስሙ በግብሩና በንግግሩ የተለወጠለት የሰፈራችን ፈላስፋ።

 ለምንድነው ዕድሜያችሁ ሠላሳ ነው የሚለን? ስል ሁሌ አስባለሁ። ደግሞስ የህጻናት ልጆች ልደት በሚከበርበት ቦታ እየተገኘ እኛ (Happy Birthy day to you) ስንል እሱ “ልጆች ልብ በሉ ዕድሜያችሁ ሠላሳ ነው” የሚለው ለምንድነው እያልኩ ሳስብ አንድ ቀን ይኸው ሰው ይህንንም ሚስጥር ሲተነትን ሰማሁት።

 ዕድሜያችሁ ሠላሳ ነው

 ሰውየው በተለመደው የልደት ቦታ ተገኝቶ ይህንኑ ሚስጥር ሲተነትን ሰማሁት። “ልጆች ተረት ልንገራችሁ…..” ሲል ጀመረ። አስከትሎም “ተረት ተረት የላም በረት” የሚለውን ማስረጃ መጀመሪያ አስከትሎ የልጆችን ምላሽ ሳይጠብቅ እንዲህ ሲል ቀጠለ።

 “….ድሮ ድሮ ፈጣሪ ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ ከጨረሰ በኋላ የእጆቹ ስራዎች ለሆኑት ፍጡራን ሁሉ ዕድሜያቸውን እየሰፈረና እየለካ መስጠት ይጀምራል። በስድስተኛው ቀን የተፈጠረው ሰው ቀድመውት ከተፈጠሩት ፍጥረታት በፊት ቀድሞ የእድሜ መጠኑ ሊነገረው ከፈጣሪው ዙፋን ፊት ይቆማል። ፈጣሪ ሰውን አትኩሮ ከተመለከተው በኋላ አንተ ስምህ ሰው ይባላል፣ ካንተ በፊት የፈጠርኳቸውን ፍጥረታት በሙሉ በሰማይም በምድርም ያሉትን ትገዛለህ፣ ትነዳለህ። የሰማያትን ክዋክብት አፈጣጠራቸውን ሁሉ መርምረህ ትደርስበታለህ። በምድር ያሉትንም ፍጥረታት የሚታየውንም የማይታየውንም ሁሉ ትገዛለህ። ፍጥረት ሁሉ ለአንተ ይሰግዳል። የፍጥረቱ ተወካይ አንተ እድትሆን ሾሜሃለሁ። በባህር ውስጥ ያሉት ታላላቆቹ ፍጥረታት እነ ብሄሞትም ሆነ እነ ሊዋታን የተባሉ ታላላቅ ዘንዶዎች ላንተ ይሰግዳሉ። ከኔ በታች የዚህ ሁሉ ፍጥረት እንደራሴ አድርጌ ሾሜሃለሁ። ዕድሜህ ግን ሠላሳ ዓመት ብቻ ይሁን ይለዋል።

 ሰው ግን ደነገጠ የሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ከተሰጣቸው ክዋክብት ያነሰ ዕድሜ ስለተሰጠው ሰው አኮረፈ። የሰማይና የምድር ገዥ ሁን ተብሎ እየተሸመ ከምድርና ከሰማይ ያነሰ እድሜ ሲሰጠው ሰው ደነገጠ። ደንግጦም ዝም አላለ። እባክህ ጌታዬ ሆይ! ካላጣኸው ስጦታ ትንሽ ዕድሜ ጨምርልኝ” ሲል ይለማመጣል። ”በቃህ አሁን ውጣ !” ይባላል ሰው ከፈጣሪ ዙፋን ፊት አኩርፎና አንገቱን አቀርቅሮ ይወጣና ከዚያው ከዙፋኑ ሰገነት አጠገብ ተክዞ ይቆማል። ቀጥሎ አህያ ዕድሜ ሊቀበል ከፈጣሪው ዙፋን ፊት ገብቶ ይቆማል። ፈጣሪው እንዲህ ይለዋል “አንተ ስምህ አህያ ይባላል። ለሰው አገልጋይ ትሆናለህ። ጀርባህን ጠንካራ አድርጌ ፈጥሬዋለሁ። ሰው የፈለገውን እየጫነብህ በገደሉና በተራራው፣ በቁልቁለቱና በዳገቱ እየወጣህና እየወረድክ ሰውን እያገለገልክ ትኖራለህ። ዕድሜህ ሰባ ዓመት ይሁን ” ይባላል።

 አህያ ከተጫነበት መከራና ከተሰጠው ዕድሜ ርዝመት አንጻር ወደ ፊት የሚጠብቀውን የስቃይና የመከራ ኑሮ አስቦ ዕድሜው እንዲቀነስለት መለመን ጀመረ። “ጌታዬ ሆይ! ይኸንን ያክል መከራ ጭነህብኝ፣ ለሰው ባርነት አሳልፈህ ሰጥተኸኝ፣ ለሰው ከሰጠኸው ዕድሜ በላይ ሰባ ዓመት መኖር ይከብደኛል። እባክህን ዕድሜዬን ቀንስልኝ “ ሲል አቤቱታውን ያቀርባል።

ሰው ከዙፋኑ ጥግ ቆሞ የአህያን አቤቱታ ሲሰማ በጣም ደስ አለው። የመላእክቱን ግልምጫ ሳይፈራ፣ የኪሩቤል ሰይፍ ሳያግደው፣ ዘሎ ገብቶ ከፈጣሪው ዙፋን ፊት ይቆማል። “… ፈጣሪዬ ሆይ እባክህን ከአህያ የምትቀንሰውን ዕድሜ ለኔ ስጠኝ” ሲል ያመለክታል። ፈጣሪም ፈገግ ብሎ ሰውን ከተመለከተው በኋላ ከአህያ ላይ የቀነሰውን ዕድሜ ለሰው ይሰጠዋል። ሁለቱም ደስ ብሏቸው ይወጣሉ። ሰው ዕድሜ ስለተጨመረለት አህያ ደሞ ዕድሜ ስለተቀነሰለት።

ከእነሱ በኋላ ውሻ ዕድሜ ሊቀበል ይገባል። ፈጣሪ ውሻን ትኩር ብሎ ካየ በኋላ አንተ ስምህ ውሻ ይባል። ሰውን እንደተከተልክ ትኖራለህ። ከደጁም ሆነ ከግቢው አትጠፋም። የሚጥልልህን ፍርፋሪ እየበላህ በቀንና በሌሊት እሱንና የሱ የሆኑትን ሁሉ እየጠበቅክ ትኖራለህ። ቀን ቀን ያለ ስጋት ታንቀላፋለህ። ማታ ማታ ደግሞ የራስህን ጥላ እንኳን ስለማታምነው በፍርሃት እየደነበርክና እየጮህክ ሌሊቱን ያለ እንቅልፍ ታሳልፈዋለህ። የሚያስፈራህ ነገር ብዙ ነው። ዕድሜህ ሰባ ዓመት ይሁን ይለዋል። ውሻ ፈጣሪ ከጫነበት መከራ አንጻር የዕድሜው መርዘም እና የተሸከመው ስቃይ አሰቅቆት “አቤቱ ጌታዬ ሆይ! ይህን ሁሉ ስቃይ ጭነህብኝ ሰባ ዓመት መኖር ይከብደኛል። እባክህን ቀንስልኝ“ ይለዋል። ይሄኔ ሰው ይሰማና ደስ ብሎት እንደለመደው ዘሎ ከፈጣሪ ዙፋን ፊት ይገባል።

 “ጌታዬ ሆይ ከውሻ የምትቀንሰውን ዕድሜ ለኔ ስጠኝ” ሲል ይለምናል። ፈጣሪም ፈገግ ብሎ ካየው በኋላ ከውሻ የቀነሰውን ዕድሜ ለሰው ይሰጠዋል። ሁለቱም ደስ ብሏቸው ከዙፋን ችሎት ይወጣሉ። ውሻ ዕድሜ ስለተቀነሰለት ሰው ደሞ ዕድሜ ስለተጨመረለት።

 ቀጥሎ ዝንጀሮ ዕድሜ ሊቀበል ከፈጣሪ ዙፋን ችሎት ይገባል። “አንተ ስምህ ዝንጀሮ ይባላል። ፊትህ እንዲህ እንደተጨማደደ ኑሮህን በገደልና በተራራ ላይ ታደርጋለህ። እንዲሁ እንደጎበጥክ በምድር ላይ ትመላለሳለህ። ራስህ የሰራኸውን ሳይሆን ሌላው የሰራውን እየበላህ ትኖራለህ። ዕድሜህ ሰባ ዓመት ይሁን” ይባላል።

 ዝንጀሮም ይከፋዋል። እባክህ ጌታ ሆይ ቀንስልኝ። በዚህ ሁኔታ ሰባ ዓመት መኖር ከባድ ነው ሲል ያጉረመርማል። አጅሬ ሰው የዝንጀሮን መቃወሚያ ሰምቶ እንደ ለመደው ዘሎ ከዙፋን ፊት ይቆምና “ጌታ ሆይ ከዝንጀሮ የምትቀንሰውን ዕድሜ እባክህ ለኔ ስጠኝ” ሲል ይማጸናል። ፈጣሪም ሰውን ፈገግ ብሎ ካየው በኋላ ከዝንጀሮ የቀነሰውን ዕድሜ ለሰው ይሰጠዋል።

 ሰው ዕድሜ የጠገበ ስለመሰለው ከዙፋኑ ችሎት ወደ ማደሪያው ደስ ብሎት ይመለሳል። የፈጣሪም የዙፋን ችሎት ስራውን ጨርሶ የክብር መንጦላእቱ (መጋረጃው) ይዘጋል። ሰውም የአህያን፣ የውሻን፣ የዝንጀሮንም ዕድሜ ከራሱ ጋር ደምሮ ኑሮውን በምድር ላይ ይጀምራል።

 ሰው እስከ ሰላሳ ዓመቱ ደስተኛ ሆኖ ይኖር ነበር። ቢሮጥ ይቀድማል፣ ቢይዝ ያጠብቃል፣ ቢጠጣ ይረካል፣ ቢጎርስ ይጠግባል፣ ሰው በተሰጠው ሰላሳ ዐመት ውስጥ ለራሱ ኖሮ ለራሱ ሰርቶ ደስ ብሎት ይኖር ነበር። በኋላም ከሚስቱ ከሄዋን ጋር ጋብቻ መስርቶ ልጅ ይወልዳል። ከዚያን ቀን ጀምሮ ለልጆቹ ማሰብ ይጀምራል። ከዋለበትም ሆነ ካደረበት ሲመለስ ልክ እንደ አህያ ለልጆቹ የሚሆን ምግብ ተሸክሞ ወደ ጎጆው ይመጣል። የማረሻውን ሞፈርና ቀንበር ተሸክሞ ወደ እርሻው ሄዶ ሲያርስ ውሎ ማታም እንዲሁ ሞፈርና ቀንበሩን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰው ለራሱ መኖር አቆመ። አንድ ቀን ምርር ብሎት ለምንድነው እንዲህ የሆነው ሲል ሚስቱን ይጠይቃል። ሚስቱ ሄዋንም ”ከአህያ የወሰድከው እድሜ ስለሆነ ነው“ አለችው። “ልክ ነሽ ሄዋን ከአህያ የወሰድከት ዕድሜ ነው ለልጆቼ እንድኖር ያደረገኝ። አህያ እኮ ለራሱ ሳይሆን ለሌላው ተሸክሞ ይኖራል። ለካስ የሰው ዕድሜው ሰላሳ ነው” ሲል ትክዝ ይላል።

ሰው ዕድሜው እየጨመረ መጣ። ለፍቶ ጥሮ የሰበሰባትን ትንሽ ሃብት በያዘ ጊዜ ዕድሜው ሰባ ዓመት ሞላ። አካሉ ደከመ፣ አመጋገቡ ቀነሰ። ይችኑ የሰበሰባትን የሚቀማኝ ሌባ ሌሊት ሌሊት ይመጣል እያለ ትንሻ ኮሽታ እያስደነገጠችው እንቅልፍ አጥቶ ይኖር ጀመር። ቀን ቀን ሰውም ተመልካችም አለ ስለሚል ልክ እንደ ውሻ ይተኛል። ማታ ማታ ደግሞ የተለመደው ጭንቀቱ እንቅልፍ እንደነሳው በመኝታው ላይ ሲገላበጥ ያድራል። አንድ ቀን ብቻውን ሲተክዝ ይህ የሆነበት ሚስጥር ገባው። ለካስ ከውሻ የወሰድኩት ዕድሜ ነው እንዲህ የሚያደርገኝ ሲል ተጸጸተ።

 ሰው ሰባውን ዐመት አልፎ ሰማንያ ውስጥ ገባ። ይህን ጊዜ የፊቱ ቆዳ እንደ ዝንጀሮ ተሸበሸበ። ከወገቡ ጎብጦ ምርኩዝ ይዞ መሄድ ጀመረ። በራሱ ጉልበት ሰርቶ መብላት ስላልቻለ ሌሎች ሰርተው ያመጡለትን ብቻ መብላት ጀመረ። ዝንጀሮ ከገደል ላይ ተንጠልጥሎ እንደሚኖር ሰውም ከሞት አፋፍ ገደል ላይ ተንጠልጥሎ ዕድሜው የማሰለትን መቃብሩን እየተመለከተ ይኖራል። አንድ ቀን እንደ ዝንጀሮ ጎብጦ በከዘራው እየተደገፈ ሲሄድ የመንደሩ ህጻናት አይተው ሳቁበት። ሰው በጣም አዘነ። ወደ ቤቱ ገብቶ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚስቱ ነገራት። ”ህጻናት ሳቁብኝ ለምንድነው?” ብሎም ጠየቃት። ከዝንጀሮ የወሰድከው ዕድሜ ዝንጀሮ ስላስመሰለህ ነው። ዕድሜህ እኮ ሰላሳ ዓመት ብቻ ነበር። ያማረብህ የሞላብህ ያንተ ዘመን ሰላሳ ብቻ ነው አለችው። ሰው የመጨረሻው የዕድሜ ጫፉ ላይ ቆሞ የህይወት ሚስጥር ገባው። ወደ ኋላ ተመልሶ እድሜውን ማምጣት አይችልም። ከሰላሳ በኋላ የአህያውን የውሻውንና የዝንጀሮውን ዕድሜ ሲኖር ይታያል። ካለን በኋላ ስሙ የማይታወቀው የሰፈራችን ፈላስፋ የተለመደችውን መፈክሩን አሰምቶን ዕድሜያችሁ ሰላሳ ነው ብሎን ወጣ።

የምትሞቱት ሞትን ስለምትበሉት ነው።

 ይኸው የሰፈራችን ሰው ስለሞት የነገረን ፍልስፍና ትዝ ይለኛል። ከለቅሶ ቤት ድንኳን ውስጥ ተቀምጠን ሳለ ድንገት ዘው ብሎ ገብቶ “የምትሞቱት እኮ ሞትን ስለምትበሉት ነው” ብሎን ትኩር ብሎ ይመለከተን ጀመር። ትንሽ ቆይቶ ንግግሩን ቀጠለ።

“…ልብ በሉ በጉን ከነህይወቱ እኮ አትበሉትም። አርዳችሁ፣ ገፋችሁ፣ ቆራርጣችሁ፣ ጠብሳችሁ ነው የምትበሉት። ከበላችሁ በኋላ በህይወት እንድትኖሩ ሃይልም እንድታገኙ ያደረጋችሁ አርዳችሁ የበላችሁት ስጋ ነው። ስለዚህ ሞት ምግባችሁ ነው ማለት ነው። እናንተም እኮ ትላላችሁ። ለሞተ እህል ይህን ያክል ስስት ምን ያደርጋል? ማለታችሁ ሞት ምግባችሁ መሆኑን ማመናችሁ አይደል። የተከላችሁትንም ድንች ህይወት እንዲያገኝ ውሃ አጠጥታችሁ፣ አርማችሁ ካሳደጋችሁ በኋላ ልትበሉት ስትፈልጉ ነቅላችሁ ልጣችሁ ከትፋችሁ፣ ቀቅላችሁ እሱንም ከገደላችሁት በኋላ ነው የምትበሉት። ከእናታችሁ ማህጸን ውስጥ ተኝታችሁ በነበረ ጊዜ እንኳን በጊዜው ገፍትሮ ወደዚህ ዓለም የሚያመጣችሁ ሞት ነው። ዘጠኝ ወር ጠብቆና ተሸክሞ የቆየው ማህጸን ጊዜውን ሲጨርስ እሱም ይሞታል። ሞት ገፍትሮ ከዚህ ማህጸን አሁን ወደ ምትገኙበት ዐለም ያመጣችኋል። ማህጸን በጊዜ ሞቶ ስራውን ባያቆም በዚህ ዓለም ማን ተወልዶ ይታይ ነበር? እናም ሞት የህይወት ጓደኛ ነው። ሞት ጓደኛችን ባይሆን ሁላችንም እዚህ አንገኝም ነበር። እሱን ባንመገብ ባላደግን ነበር። ልብ በሉ ሳንገድል የምንበላውና የምንጠጣው ውሃን ብቻ ነው። ውሃን ስትገድለት እናንተም ትሞታላችሁ። ውሃን መግደል ማለት ጌሾና ብቅል ጨምሮ መጠጣት አልኮልን ቀምሞ መጠጣት ማለት ነው። ይህን ጊዜ የማይሞተውን ውሃ ስለገደላችሁት እሱም እያንገዳገደና እያዳፋ በየቦታው ሲያጋጫችሁና ሲያጣላችሁ ይታያል። እና የሚሞተውን ብሉ የማይሞተውን አትግደሉ ይለናል ይህ ስሙ የማይታወቅ የሰፈራችን ፈላስፋ።

 ሰው የምትሆኑት …

 አንድ ቀን ደግሞ ይኸው የሰፈራችን ፈላስፋ እንዲህ አለ። “ሰው የምትሆኑት ለሰው በተፈጠረው መንገድ ላይ በራሳችሁ ፈቃድና ምርጫ ጉዞ ስትጀምሩ ብቻ ነው።” ካለን በኋላ ያቺ የተለመደችውን ተረታዊ ምሳሌ አስከትሎ አንድ ተረት ነገረን። “ድሮ ድሮ ፈጣሪ አስቀድሞ ሁለት የተለያዩ መንገዶችን ሰራ። ሁለት የተለያዩ ነፍሳትን ከፈጠረ በኋላ ስጋ ከማልበሱ በፊት እነዚህን ሁለት ነፍሳት ከሁለቱ መንገዶች መነሻ ጫፍ ላይ አቆማቸውና በመረጣችሁት መንገድ መሄድ ትችላላችሁ ሲል ነጻነት ሰጣቸው። አንደኛው ነፍስ በጣም ቀጥተኛና ለስላሳ ምንም እንቅፋትና ገደል ተራራና ቁልቁለት ያሌለውን መንገድ መርጦ መጓዝ ጀመረ። ይህን ጊዜ ፈጣሪ ስጋ ማልበስ ጀመረ። ምቹ የሆነውን መንገድ መርጦ የተጓዘው ነፍስ እንስሳ ሆነ። ሁለተኛው ነፍስ ደግሞ አስቸጋሪውን መንገድ መርጦ መጓዝ ጀመረ። ይህ መንገድ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ፈጣሪም ስጋ ማልበስ ጀመረ። አስቸጋሪውን መንገድ የመረጠው ነፍስ ሰው ሆነ። ሰውና እንሰሳ በመረጡትና በተጓዙበት መንገድ አይነት ተለያዩ። እናንተም በእውነት ሰው መሆን ከፈለጋችሁ ለሰው በተሰራው መንገድ ላይ ብቻ መጓዝ ምርጫችሁና ፈቃዳችሁ ይሁን። ለስላሳውን መንገድ፣ መውጣትና መውረድ የሌለበትን መንገድ ስትመርጡ እንደእንስሳ መኖራችሁን አስቡ። በመንጋ ትኖራላችሁ፣ በመንጋ ታስባላችሁ፣ እንደሰው ግለሰባዊ ማንነት አይኖራችሁም። ጉልበተኛ ለሆነው ለመንጋው አለቃ ተላልፋችሁ የተሰጣችሁ ባሮች ትሆናላችሁ። ሰው ከእንስሳ የተለየው በማሰቡ ብቻ ሳይሆን በመረጠው እና በፈቀደው የህይወት መንገድ ላይ በሚያደርገው ጉዞውም ጭምር ነው። ሰው መሆን ከፈለጋችሁ በራሳችሁ ፈቃድና ምርጫ በመረጣችሁት መንገድ ደፍራችሁ ተጓዙ። አሁን ስጋ ለብሳችኋል። ፈጣሪ ደግሞ ሰው መሆናችሁን ሲያይ መንፈሱን ያለብሳችኋል። አማራ ነን ከማለታችሁ በፊት ሰው ሆናችሁ ለመሰራት ተዘጋጁ። ኦሮሞ ነን ከማለታችሁ በፊት ሰው የሚያደርጋችሁን መንገድ ፈልጋችሁ አግኙት። ትግሬ ነን ከማለታችሁ በፊት የሰውነትን ስጋ ለመልበስ በመከራና በመሰናክል የተሞላውን የሰውነትን መንገድ ምረጡ። እናም ሰው ሁኑ …. ሰው ሁኑ …. ሰሰሰሰ…..ው! ሰውነት ትግል የበዛበት መንገድ ነው። እንስሳነት ከመንጋው ጋር አብሮ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top