ሰላምና ጤና ለናንተ ይሁን:: እነሆ ታዛ እጃችሁ ገባች:: የጥበብ ባህላችን እንዲያድግ፣ ዘመናዊ አስተሳሰብ እንዲበለጽግ ሃሳቦች ይንሸራሸሩባት ዘንድ የተመቻቸችው ታዛ መጽሔት አንደኛ ዓመት ቁጥር 23 እነሆ እጃችሁ ገባች::
በባለፉት ዕትሞቻችን በስነ ጽሑፍ፣ በፍልስፍና፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በባህል፣ በማህበራዊ ጉዳዮች እና የጥበብ ዘርፎች የተስተናገዱት ጽሑፎች በአንባቢያን ዘንድ እውቀትን እንዳስጨበጡ ጥሩ ግንዛቤን እንደፈጠሩ፣ መረጃም እንደሰጡ እንገነዘባለን:: ይህንን የምንለው በተለያዩ መንገዶች ከሚደርሱን አስተያየቶች በመነሳት ነው::
ከጊዜ ወደ ጊዜ ያበዛነው አንባቢዎቻችንን ብቻ ሳይሆን፤ ቋሚ አምደኞቻችንንም ጭምር ነው:: ዛሬ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከውጪ አገርም ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ የሚጽፉልን የመሔታችን ወዳጆች የተለያዩ ሃሳቦች ከተለያዩ ወገኖች እንዲደርስ አስችሏል:: አልፎ አልፎ የልዩነት ሃሳቦችን ማስተናገዳችንም አንባቢያን ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቃኝተው የራሳቸውን ግንዛቤ እንዲወስዱ ያስችላል ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው::
መጽሔታችን በኢንተርኔት አማካኝነት በተለያዩ አገራትና አካባቢዎች እንድትደርስ በምናደርገው ጥረትም ለተወሰነ ጊዜ አንድ ቦታ ቆሞ የነበረው ዌብ ሳይታችንን እንዲያንሰራራ አድርገነዋል:: በሱ ተከተሉን:: በተረፈ ይዘን የተነሳነውን ዓላማ ለማሳካት የእናንተ አስተያየትና የተሳትፎ ጽሑፍ አስፈላጊያችን ነው:: ይህንን ማድረጋችሁ ያተጋናልና አብራችሁን ወደ አዲሱ አመት እንሻገር::
ውድ አንባቢያን! በቀጣዩ መስከረም ሁለተኛ ዓመታችንን ጨርሰን ወደ ሦስተኛ እንዘልቃለን:: እንደተለመደው አዳዲስ ሀሳቦች የምናመነጭበት፣ ታሪካችንን የምናስታውስበትና ጥበብን በጋራ የምናሳድግበት እንዲሆን እምነት አለን:: መልካም ቀን!
