በላ ልበልሃ

ንባብ አዕምሮን በማደስ እንጂ በማቃወስ አይታማም

“ሰው እጅና እግር እያለው፣ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር አእምሮ ተፈጥሮለት እንዴት ጥቂት ተንኮል ሳያክልበት ቀና ሆኖ ይኖራል?” ሲል በድፍረት የተናገረ አንድ የጊዜው ሰው የኔንም ቀናነት ጭምር እንድጠራጠር አድርጎኛል። በአሳዛኝ መልኩ!!

ወጣም ወረደ ኅብረት፣ አንድነት፣ የጋራ ስምምነት ለድል አድራጊነት እንደሚያበቃ፣ መለያየት፣ መነጣጠልና መገነጣጠል በሽንፈት እንደሚያስጠቃ ሳይታለም የተፈታ ነው። ቀደም ካለው ታሪካችን እንዲያው የአድዋውን ድል እንኳ ብናይ ለዚህ አኩሪ ታሪክ በምስክርነት አይቆምምን? ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እኮ “አንተ የወዲህ ሰው ነህ፣ አንተ የወዲያ ሰው ነህ” ሲሉ ለያይተው በዘር፣ በጎሣ፣ በኃይማኖት ነጣጥለው አልዘመቱም። “ክተት” ብለው የሄዱትም ወደ አድዋ ነው። ይህን ልብ ማለት ያሻል። በዚህም ሳቢያ ድል ተገኝቷል። ሀገርም ሕዝብም በአንድነት ቆሞ አቅራርቷል። ከዚያ በኋላ ያሉትንም የኅብረት፣ የአንድነት፣ ታሪኮችን ብናይ ደስ የምንሰኝበት በእኛነታችን የምንኮራበት መሆኑን ለመገንዘብ ዳገት አይሆንብንም።

 ለምሳሌ “ነገር ከጀማሪው ውሃ ከመሻገሪያው” የሚል የቀደምት አበው ዘይቤ አለ። ለአብነት ያህል የአንድን መጽሐፍ ጥቅል ይዘት ለመገንዘብ የሚቻለው በመጀመሪያ የጽሑፉን ቃለ መቅድም ወይም መግቢያ በትክክል ከመረመሩ በኋላ ነው። ይሁንና የአንድን የጽሑፍ ምንነት ለማወቅና ለመረዳት የሚፈልጉ ብዙዎች የዘመናችን አንባብያን በመጀመሪያ ወደ መሐል ገብተው፣ ሆድ ዕቃውን ጎትተው ለመፈተሽ ሲፈልጉ የመታየታቸው ነገር ሳያስገርም የሚቀር አይደለም። እኔ እንዲያው ሌላ ቃል ላገኝላቸው ባለመቻሌ “አንባብያን” ለማለት ተገደድኩ እንጂ በዛሬ ጊዜ መጽሐፍ ማንበብ የሚወድ ከስንት አንድ ቢሆን ነው። ፊልሙ፣ ሞባይሉ፣ ኢንተርኔቱና መሰል የቴክኖሎጂ ተወላድያን እነ ቃና የት ሄደው ሰው በወረቀት ላይ በሰፈረ ሆሄ ዓይኑን ሲያፈዝ፣ ሐሳቡን እያንጎላጀጀ ሲያናውዝ ይስተዋላል? “ለምን በፊደል ጥርቅምና በሆሄ ገበታ ግሳንግስ አንጎሌን አዞራለሁ?” ያለኝ አንድ የዘመኑ ጉብል ዘወትር አይዘነጋኝም። ይህን መሰል ስንኩል አመለካከት የሚጋሩት ጥቂት እንዳልሆኑ በኩራት ሲናገር እንኳ አላፈረም።

 ንባብ ዕውቀት የሚገበይበት፣ ጥበብ የሚካበትበት መሆኑ ቀርቶ ሰው የሚቀውስበት፣ በወፈፌነት ጨርቅ የሚቀድበት መሆኑ የተነገረበት ጊዜ ላይ መድረሳችን እጅግ የሚያሳዝን ነው። ወደ ተነሣሁበት ጉዳይ ልመለስና የአንድ መጽሐፍ ቃለ መቅድም የተለየ ትርጓሜ ያለው መሆኑን ለአፍታ እንኳ መጠራጠር አያሻንም። ለዚህም ነው ቃለ መቅደም በመግቢያነቱ እንደጸደቀ፣ ምስጢራዊ ይዘቱ እንደረቀቀ፣ ለዘመናት ቆይቶ ለጊዜ አዛውንትነት ምስክር ይሆን ዘንድ የበቃው።

 ስለምን? የአንድ ነገር መነሻ ከሌለ መድረሻውም የሚታወቅ ሊሆን የሚችልበት ብልኃት የለምና!! የብዕር አለቃውንም ሆነ የብዕሩን ማንነትና ምንነት ለመረዳት የሚቻለው በቃለ መቅድሙ ነው። እንዲያውም በቁጥር ያላነሱ ደራስያን የልባቸውን አውጥተው የሚገልጹት በመጽሐፉ የመጀመሪያ ገጾች በሚሰፍሩት ቃለ መቅድም አማካይነት መሆኑን የተረዳን ሆነን አልተገኘንም። ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸውን በዚህ ረገድ ለአብነት ያህል ብንወስድ “አርሙኝ” በተሰኘው የድርሰት ስብስብ ጥራዛቸው እንዲህ ሲሉ ያስነብቡናል።

Reading book while drinking coffee on balcony

“በ1928 ከኦጋዴን ተመልሼ ከግርማዊነታቸው ጋር ተሰደድኩ። የስደት ቦታውም ኢየሩሳሌም ይሆን ዘንድ ተቆረጠ። አንድ ዓመት ከተቀመጥን በኋላ ኢያሪኮ ላይ ቦታ ገዛን። በዚያችም ርስታችን ውስጥ ከበኩረ ሎሚና፣ ከመንደሪን፣ ከሙዝ ዛፎች መሐከል የተሠራች አራት ክፍል ያላት፣ ለእኛም ትዳር የምትበቃ ልከኛ ቤት ነበረችባት። እኔና ባለቤቴ ልዕልት የሻሸ ወርቅ ይልማ በዚያች ጎዦአችን ውስጥ ደስ ብሎን ሥራችንን ተከፋፍለን እንኖር ነበር። — እኔ ውሃ ማጠጣትና አትክልት መኮትኮት፣ ከዚህ በኋላ የበሰለውን በኩረ ሎሚና ሙዝ ሌላውንም አትክልት አንድ መንኮራኩር ብቻ ባላት በአንዲት ትንሽ ጋሪ እየገፋሁ በከተማው ውስጥ እያዞርኩ እሸጥ ነበር። በተረፈም ሥዕል እየሣልኩ ለልባሳችን ያህል ገንዘብ እናገኝ ነበር። —

ባለቤቴም በማለዳ ተነስታ ሥራዋ ቤት መጥረግና መስተዋት መወልወል፣ ወጥ መቀቀል፣

   “እነሆ እኔም ይህን ልበ ወለድ ታሪክ ትንሹ ዕውቀቴ በሚፈቅድልኝ መጠን ጽፌ ለማሳተም ያሰብሁት ምናልባት ከብዙው ገለባ አንዲት ፍሬ ትገኝበት እንደሆነ ነው”

እንጀራ መጋገር፣ ሹራብ መሥራት ነበር”ካሉ በኋላ በውድቅት ሌሊት የውሃ አከፋፋይ ሹሙ በር መትቶ እንደሚያስነሣቸው፣ እርሳቸውም የሚደርሳቸው ውሃ ሳያመልጣቸው፣ በከንቱም ፈሶ እንዳይቀር የላስቲክ ቦት ጫማ አጥልቀው፣ ዶማና አካፋም ይዘው ያን ውሃ ብቻቸውን     አጠጥተው፣ ለመጠጥ የሚሆነውንም በገንዳ እንዲጠራቀም አድርገው፣ ወፍ ጭጭ እስኪል ድረስ በጉልበት ተግባር የተሠማሩበትን ዕለታዊ ኑሮ ያስታውሳሉ። እኒያ በዚያ ዘመን የኮሩ፣ የተከበሩ ታላቅ ሰው ያን ዝቅተኛ ሥራ ይሠሩ ነበር ማለት ነው።

 “— ይህንንም ሁሉ ሳደርግ ያ በላያችን ላይ ደርበነው የነበረው የጸጋ ሀብትና ክብር እጅጉን የከንቱ ከንቱ መሆኑን ያሳስበኝ ነበር” በማለት ለዚህ ነባር ትዝታ አጽንዖት ይሰጣሉ። ያ ጊዜአዊ ሀብት በጊዜያዊነት ብቻ እንዳስከበረ ያስተምራሉ። በዚህም ሳቢያ “ኢትዮጵያ ስለምንድን ነው ድል የሆነችው?” የሚለውንና ሌሎችንም መጻሕፍት እንደደረሱ ይነግሩናል። “አትፍሩ ሥጋን ከሚገድሉ” የተሰኘውንና እንዲሁም “ዓለም ወረተኛ” እና “የደም ድምፅ” ሌሎችም እንደ “ቃየል ድንጋይ፣ የድሆች ከተማ፣ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የተባሉት መጻሕፍትም በከፊል የዚያው የስደት ዘመን ቅርሶች መሆናቸውን ይገልጻሉ።

 “በዓለም ወረተኛ” ድርሰት ወረቀት ባስያዙት ቃለ መቅድም ላይ ደግሞ “– — ዓይኑን የታመመ ሰው ፀሐይን ትኩር ብሎ ለማየት እንደማይችል — በክፋትና በኃጢአት የታመመ የሰው ዓይንም የአምላክን ብርሃነ ዕውቀት ለማየት አይችልም፣ — ስለዚህ የፈጣሪን ብርሃነ ዕውቀት እናይ ዘንድ መጻሕፍትን በጥልቅ ባለመሰልቸት እንድንመለከት ያስፈልጋል — አንባቢ ዕውቀት ያገኛል — ብዙ የሚያነብም ዐዋቂ ይሆናል ተብሏልና” ሲሉ ንባብ ፈለገ ጥበብ መሆኑን በሚገባ ያስረዱናል። እንደ አሁን ዘመን አመዛኝ ጎበዛዝትና ቆነጃጅት ከንቱ አስተሳሰብ “ንባብ ለድንቁርና ቀኖና” በር የሚከፍት ሳይሆን ይልቁንም በዕውቀት ምንጭነት ለሕይወት ልምላሜ በምስክርነት የሚቆም መሆኑን በማያወላውል ሁናቴ ያረጋገጡበት አባባል በዚያ ቃለ መቅድም ተሰምሮበታል። በተለይ ያን መከረኛ የስደት ዘመን ባሳለፉበት ወቅት ያ ሁሉ የነበረ የድሮ ክብርና ሀብት የከንቱ ከንቱ መሆኑን በ“ዓለም ወረተኛ” መጽሐፋቸውም አልዘነጉትም። መነሻው ግን ቃለ መቅድሙ ነው። እንዲህም ሲሆን ቃለ መቅድም የቱን ያህል የተለየ ትርጓሜ እንዳለው ያስገነዝበናል።

አንዳንድ ደራሲዎች ደግሞ ምንም ዕውቀቱና ችሎታው ባያንሳቸው በቃለ መቅድማቸው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚገኙበት፣ አንባቢን በመንበረ ዙፋን አስቀምጠው ያከበሩበትን አድራጎት እናያለን። ለምሳሌ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው የጻፉትን “አርአያ” የተሰኘ ዝነኛ የልብ ወለድ ድርሰት መቅድም ብንመለከት ደራሲው እንዲህ ሲሉ ይነግሩናል፡- “—ስለ ሀገር ጥቅምና ስለ ምግባር ለእያንዳንዳችን የመሰለንንና ያመንበትን፣ ከሊቃውንትም የቀዳነውንና የተረዳነውን ሐሳብ እውነት መሆኑና ጠቃሚነቱን ከተቀበልነው ዘንድ ለሕዝብ ማስገንዘብ ይገባኛል” በማለት “እነሆ እኔም ይህን ልበ ወለድ ታሪክ ትንሹ ዕውቀቴ በሚፈቅድልኝ መጠን ጽፌ ለማሳተም ያሰብሁት ምናልባት ከብዙው ገለባ አንዲት ፍሬ ትገኝበት እንደሆነ ነው—” ሲሉ የቱን ያህል ስለ ትሕትና ራሳቸውን ዝቅ እንዳደረጉ የሚመሰክርልን አባባል ነው።

 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን “አርአያ” እንደ ስሙ ለሁላችንም በምሳሌነት የሚወደስ፣ በአብነት የሚጠቀስ እንጂ እርሳቸው ለአትሕቶ ርዕስ፣ ሲሉ እንዳመለከቱት በብዙ ገለባ የታጀለ፣ ከፍሬው የቀለለ ድርሰት ሆኖ አይደለም። እንዲያውም በወቅቱ ወደ ባሕር ማዶ ቋንቋ የተተረጎመ ዝነኛ መጽሐፍ ነበር። ነገር ግን እኔም ሆንኩ አመዛኙ ኢትዮጵያዊ ወገን የተባለ ሁሉ በዕድሜያችን ስናዝን የምንኖርባቸው ዓበይት ድርጊቶች ውስጥ አንድ ታላቅ ነገር አለ። ይኸውም ደርግ የእነዚህን መሰሎች የአገር ቅርስ መጻሕፍት ባለቤቶች ሁሉ፣ እነርሱንም የመሳሰሉትን እየመረጠ በሕይወት የሌሉትን ታሪካቸው እንዳይነገር፣ በጸሐፍያን እንዳይመሰከር ብርቱ ማዕቀብ የማድረጉ፣ በሕይወት የነበሩትን ደግሞ ከነቤተሰባቸው ጭምር በእሥር እያሠቃየ የማማቀቁ፣ የመረሸኑ ጉዳይና ድርሰቶቻቸውም እንዳይነበቡ የማገዱ፣ እንዲያውም እንዲቃጠሉ በጭካኔ ፈርዶባቸው በሰው እጅ ተደብቀው የተረፉት እጅግ ጥቂት ጥራዞች የመሆናቸው ነገር ነው።

 ይህ አድራጎት እጅግ ሲያሳዝነን ይኖራል። ደርግ በመፈክርና በመዝሙር እንደለፈፈው ለሰፊው ሕዝብ የሕይወት ፋና ይዞ፣ ሳይሆን ለብዙኃን ድንቁርና፣ ለብዙኃን ሰቆቃወ ሕሊና ጦር መዞ የመጣ፣ ለድፍን ኢትዮጵያ የጭንቀት ሕልውና መትረየስ ያነገበ፣ ፈጣሪ አምላክ በቸርነቱ በሰጠው አዕምሮ የተጠቀመ ሳይሆን በጠመንጃ አፈ ሙዝ ያሰበ፣ በሰው ልጅ ደም የታጠበ ማን ዘራሽ ሀገር በቀል ፋሺስት በመሆኑ ለ17 ዓመታት ምድሪቱን በደም አጨቀየ። ታሪኳንም እንዳልነበር ያደርግ ዘንድ በርዕዮተ አጋንንት ራዕየ ዲያብሎስ ተነበየ። ታሪክ ግን አልሞትም ብሎ ዛሬም ምስክርነቱን በነፃነት አሳየ። ይህ ለሁላችንም፣ ለአለነውም ሆነ ለመጪውም ትውልድ በሚገባ ሲዘከር መኖር ያለበት ነው።

ስለዚህ ዛሬ በሰላም አንዳችም ማዕቀብ ሳይኖርብን የፈቀድነውን ለማንበብ፣ ሲሻንም ለመተቸት እና ለትችትም ተገቢ መልስ ለመስጠት በተለይም አሁን በተያያዝነው የለውጥ ወቅት መብቱ የተረጋገጠልን ነው። ይሁንና አንዳንዴ በሰላም እንዲህ እንደ ልባችን በመሆናችን፣ በነጻነት ወዲያ ወዲህ በመንቀሳቀሳችን የነበረውን ረስተን፣ ያልሆነ ነገር ውስጥ ገብተን መገኘታችን አልቀረም። ይህ እጅግ ሊያሳዝነን የሚበቃ መሆኑን መካድ ከእውነቱ መራቅ ይሆናል። በመሆኑም በፈጣሪ አምላክ ቸርነት፣ በብዙዎች መሥዋዕትነት ያገኘነውን ይህን መሰል ሰላም እንደገና እንዳናጣ በጥንቃቄ ሁሉን ነገር ልንይዘው ይገባል ባይ ነኝ። በለውጡ የተገኘ ሰላም በተንኮል ሊታጣ አይገባምና!!   

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top