ለሬዲዮ ፕሮግራም እንግዳ ሲኮን ምንም እንኳ ጠጉር ቤት ገብቶ ውበት ተላብሶ ለመምጣት ባይቃጣም አእምሮን አዘጋጅቶ መምጣት ግድ ይላል:: ምን እጠየቃለሁ፣ ምን እመልሳለሁ፣ ምን አስታውሳለሁ፣ ምንስ እዘነጋለሁ በሚል ሀሳብ ተወጥሮ ጎራ ማለት የተጠያቂው (የእንግዳው) የቤት ሥራ ይሆናል:: አንድ ጊዜ መሰለ መንግሥቱ (ጋዜጠኛ) ዘንድ እንግዳ ሆንኩ:: የእንግሊዝ የእግር ኳስ ጨዋታን አስተያየት መስጠት ነው – ጉዳዩ::
ሰዓቱ ደርሶ ስቱዲዮ ገባሁ:: እግሬ ሥር ቡትሌ ቢራ አስቀምጦ የጨዋታውን መጀመር ይጠብቃል – እሱ:: እኔ ደግሞ የማወራውን እመርጣለሁ::
ብዙውን ሰዓት ጨዋታው ስለሚይዘው በእረፍት ሰዓት ላወራ የምችለውን ሃሳብ ወረቀት ላይ አሰፈርኩ::
ጨዋታውን ተመልክቼ የምሰጠውን አስተያየት በጥሩ ቃላት ለመግለፅ ተሰናዳሁ:: ጉሮሮዬን ጠረግሁ:: አቀማመጤን አስተካከልኩ:: በቃ ሩኒ የሚያየኝ ይመስል ኮሌታዬን አጣጠፍኩ:: ወዜን ጠራረግሁ:: ብዕሬን አሾልኩ::
ጨዋታው መሀል መሀል ላይ የምጥለውን አዝናኝ ነገር በአዕምሮዬ አጠናሁ:: አውጠነጠንኩ::
ጨዋታው ተጀመረ:: መሰለም ጀመረ:: ኳሷ እንደተጀመረ ልፋቷን ቀጠለች:: የመሰለም ምላስ እንደ ኳሷ ሥራዋን አሀዱ አለች::
በስህተት የእጅ ፎሪ .. አሊያም የማዕዘን ምት አልገኝ አለ:: መሰለ ቀጥሏል – እኔ ዝም ብያለሁ:: ሳያየኝ ወደ ቤት ብሔድም የሚያውቅ አይመስለኝም:: ቢራዬን ጨርሼ ሁለተኛ ከፈትኩ:: መሰለ አልሰማም:: ጉሮሮዬን አርጥቤ ማስታወሻ እይዛለሁ:: ለብቻዬም እንዲህ አስባለሁ “የእንግሊዝ ፕሪሚየም ሊግ ጨዋታን እይ ነው ያለኝ ወይስ እኔን ነው ተመልከት ያለኝ” እያልኩ እራሴን እጠይቃለሁ::
በመሀል ጎል ገባ:: እንግሊዝ ውስጥ ያሉት ተመልካቾች እንደሱ አልጮሁም:: ደነገጥኩ:: ፊት ለፊቴ ያለውን ቴክኒሺያን ጠበል ነገር አምጣ ለማለት በእጄ ምልክት አሳየሁት:: ሳቀ::
ጨዋታው ቀጥሏል:: ለመናገር ጉሮሮዬን ጠረግ ሳደርግ በቀኝ እጁ አፌን አፍኖ የስፖንሰሮችን ድርጅቶች ስም ይጠራ ጀመር::
ሶስተኛ ቢራዬን ስከፍት አይቶ በግራ እጁ አውራ ጣት Congra አለኝ እና ወሬውን ቀጠለ::
ጨዋታው ጦፏል:: መሰለም በላብ ቀልጧል:: አዘንኩ:: ቢያንስ ለአድማጮች ስሜን እንኳ ሳልናገር ቁጭ በማለቴ ተበሳጨሁ::
ሁለተኛ ጎል ተቆጠረ:: አሁን ዝላዩን አብሬ ዘለልኩ:: ማን ያግባ .. ማን ያቀብል የማቀው ነገር የለም:: ስቱዲዮውን ስታዲዮም አስመሰልነው:: ተረጋጋንና ተቀመጥን:: ሃሳብ ልሰጥ ስንጠራራ ስሜን እንድናገር ጋብዞኝ ካወራሁ በኋላ ጨዋታውን ማስተላለፍ ጀመረ::
አራተኛ ቢራዬን ከፍቼ ጠጣሁ:: ላብና ሞቅታ ተደራረቡ:: ዝም ብዬ ሳቅ ሳቅ ይለኝ ጀመር::
“ለምን መጣሁ?” ብዬ ራሴን ጠየቅኩኝ:: አሃ .. ቢራ ልጠጣ አልኩና ለብቻዬ ዘና አልኩኝ::
ነገር ዓለሙን ትቼ ቲቪውን .. ቴክኒሻኑን .. መሰለን .. ግድግዳውን.. ጠረጴዛውን .. እያየሁ ተፍነከነኩ:: ጨዋታው ተጠናቀቀ:: መሰለም በረዥሙ ተንፍሶ የዕለቱን የክብር እንግዳ አመስግኖኝ ፕሮግራሙ ተገባደደ:: ከስቱዲዮ ወጣሁ:: ጨበጥኩት:: ሌላ ጊዜ በሰፊው ላወራ እንደምችል ተስፋ እና ቀጠሮ ሰጥቶኝ ተለያየን::
በሳምንቱ ጓደኛዬ ኮሜዲያን አስረስ በቀለ ደወለልኝ:: “ደሬ” አለኝ “አቤት” “መሰለ መንግስቱ ደወለልኝ”
“ለምን” “እንግዳ ሊያረገኝ ፈልጎ”
“ምን ችግር አለው ሂዳ”
“እኔ እኮ ብዙም ስለ ኳስ አላውቅም:: ቢያፋጥጠኝስ?”
“መጀመሪያ ሲያስወራህ ነው .. ስምህን ብቻ ተናግረህ ቁጭ ነው … እሱ ነው 90 ደቂቃ የሚያወራው” አልኩት
“ጥሩ .. እንደዛ ከሆነ እሺ” ብሎኝ ስልኩን ዘጋ::
አስረስ በቀጠሮው ስቱድዮ ተገኝቶ የሆነውን ከስቱድዮ ከወጣ በኋላ እየረገመኝ አወራኝ:: “ገና እንደገባሁ ስሜን ተናገርኩ ከዚያ ስለ ሁለቱ ቡድኖች ጠየቀኝ:: በኋላ ስለ ዳኛው .. ስለ አራጋቢው .. ስለ ቡድን መሪው.. ስለ ኦጌሻው .. ስለ አሰልጣኙ .. ስለ ሾፌሩ .. ስለ ኮሜንታተሩ .. እንዲሁም ስለ ተመልካቹ … እያለ .. እያለ .. እያለ … ስለ እኔ .. ስለ ቤተ ሰቤ .. ስለ ጓደኞቼ .. ስለ ቀበሌዬ ወዲያው ስለ ቅርጫ .. ስለ ዕድር .. ብሎ ብሎ .. ሲደክመኝ ለምኜው አሁን ገና ወጣሁ… ደረጀ ምንም አታወራም ብለኸኝ … የስራህን ይስጥህ … ኡፍፍ …” አለ::
መሰለን ደውዬ ጠየቅኩት:: “የዛሬው ጨዋታ በመጥፎ አየር ምክኒያት ተሰርዟል ታዲያ ሰዓቱን በምን ልሙላው” ብሎኝ ዘጋው::
