ጣዕሞት

ቤተ-መጻሕፍቱ ራሱን እያዘመነ ነው

ታዋቂው የታሪክ ፀሐፊና ማህበራዊ ጉዳይ ተንታኝ፤ የኢትዮዽያ ወዳጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ለሀገራችን ካበረከቷቸው መልካም ነገሮች አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያቋቋሙት ይህ ቤተ መፃሕፍት ነው:: የሀገሪቱን ምሁራዊ አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክት የቆየው ይህ የኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ መፃሕፍት፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አዲስ ወደተገነባለት ዘመናዊ ሕንጻ በመዘዋወር ላይ ይገኛል::

 በባለሀብቱ ሼህ አሊ አላሙዲ በለገሱት 117 ሚሊየን ብር ሲገነባ የነበረው ይህ ህንፃ ቤተ መፅሐፍት ሰሞኑን ለምረቃ ሲበቃ፤ የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የሼሁ ተወካይ ዶክተር አረጋ… እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም ደስታቸውንና ቤተ መፅሐፍቱ ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር ጥሩ የእውቀት ተስፋ እንደሚሆን ገልፀዋል::

በቀን ውስጥ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች ከሚሰጠው አገልግሎት በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችለው ቤተ መጽሐፍቱ፤ 250 ሰው የመያዝ አቅም ያለው ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያለው ሲሆን፤ ለንባብ በአንድ ጊዜ 400 ተጠቃሚዎችን ምቾት ባለው ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል መሆኑንም የቤተ መጽሐፍቱ ኃላፊ አቶ እዩብ አለማየሁ በተለይ ለዝግጅት ክፍለችን ተናግረዋል::

በአሁኑ ወቅት ቤተ መጽሐፍቱ በተወሰነ ደረጃ መቀመጫዎች፣ በኮምፒውተሮች፣ እና ሌሎች አስፈላጊ መጠቀሚያዎች የተሟሉ ሲሆን፤ ለመጪው መስከረም ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት:: ቤተ መጽሐፍቱ የሀገርና የህዝብ ሃብት ስለሆነ በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚያደርግ ካለ ተቋሙ በደስታ እንደሚቀበልም ኃላፊው ገልፀዋል::

 ወደፊት ቤተ መጽሐፍቱን ዘመኑን በዋጀ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን እቅድ ያለ ሲሆን በቤተ መጽሐፍቱ ያሉ መጽሐፍቶችንም ሆነ የጥናት ውጤቶች በኢንተርኔት አማካኝነት የትም ቦታ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ከሃላፊው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል::

” ሀገር በሀገር ፍቅር “

አባት አርበኞች ከጣሊያን ጦር ጋር ፍልሚያ በገጠሙ ጊዜ የተቋቋመው የአገር ፍቅር ማህበር ከድሉ ማግስት ጀምሮ በክቡር ፊታውራሪ መኮንን ሀብተወልድ ፊታውራሪነት ተጠናከረ:: የአገር ክብርና አንድነትን ሲያስተጋባ የነበረው ማህበሩ በዘመናት የሂደት ጉዞ ውስጥ ጥበብን እየዋጀ ቴአትር ቤት እስኪሆን ድረስ አያሌ አገልግሎቶችን ሰጥቷል::

በቴአትር እና በሙዚቃ እንዲሁም በፊልም ታዳሚውን ሲያዝናና ዘመናት ተቆጥሯል:: ጥበብን እያቋደሰ ካወጣቸው አንጋፋ የጥበብ ሰዎች መካከል እዩኤል ዮሃንስ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ፍሬው ሃይሉ፣ አሰለፈች አሽኔ፣ መሐሙድ አህሙድ፣ አስቴር አወቀ … ወዘተ መጥቀስ ይቻላል::

ይህ አንጋፋ ቴአትር ቤት እነሆ ዘንድሮ የተመሰረተበትን 84ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ነው:: ” ሀገር በሀገር ፍቅር “ በተሰኘ መሪ ቃል ሰሞኑን የሚከበረው የማህበሩ በዓል፤ በፓናል ውይይት፣ በፎቶግራፍ አውደ ርዕይ፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር እና በሌሎች ጥበባዊ ድግሶች ነው::

 የቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ስለሺ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ ለዚሁ ዝግጅት የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ “ከመጋረጃው ጀርባ” የተሰኘ ቴአትር እየተዘጋጀ ሲሆን፤ ለበአሉ ድምቀት ለተመልካች ይቀርባል:: ሰሙኑን በቴአትር ቤቱ የአገር ሽማግሌዎችና ተደማጭ የሆኑ ታዋቂ ሰዎች ስለ አገር ፍቅር ውይይት አካሂደዋል:: ስለ ሰላም መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ አቅርበዋል:: ዋናው በዓል ግን ፒያሳ ከማዘጋጃ ቤት ጎን በሚገኘው የታክሲ መሳፈሪያ ሰፊ መስክ ላይ ነው የሚከበረው:: እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ::

በቅርቡ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባያገኘው በዚህ ቴአትር ቤት፤ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተጎኝተዋል:: እርሳቸውም በወቅቱ በሰጡት የተስፋ ቃል ቴአትር ቤቱ ተስፋፍቶ፣ አዳዲስና ዘመናዊ ግንባታ ተካሂዶለት ዘመናዊ የጥበብ ማእከል ይሆናል ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top