አድባራተ ጥበብ

“በአርቲስትነቴ የሚያውቁኝ ሁሉ፤ የማየት አቅሜ እየጠነከረ የሄደ እስኪመስለኝ ድረስ ብርታት፣ ምርኩዝ፣ ዓይን ሆነውኛል”

አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ

በተለያዩ የሙያ አስተዋጽኦዎቹ ይታወቃል። ቁጥራቸው በርከት ባሉ የመድረክ ቴአትሮች ላይ ተውኗል። የፊልም ባለሙያ ነው። በበርካታ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ድራማዎች በመሪ ተዋናይነት ተጫውቷል። የማስታወቂያ ባለሙያም ነው። የተለያዩ አገራዊና ጥበባዊ መድረኮችን ሲመራ ጎርናና ድምፁ ቀልብ ይገዛል። ይህ ሰው አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ ይባላል። ኪሮስ ዛሬ በደረሰበት የዓይን ዕይታ ችግር ከጥበባዊ ስራዎች ራሱን ቢያገልም፤ በሁኔታው አለመደናገጡና የመጣውን አሜን ብሎ መቀበሉ፣ መንፈሰ ጠንካራነቱና በተስፋ መኖሩ ሌሎችን የሚያስገርም ሆኗል። ኪሮስ ዛሬ ስላለበት የጤና ችግርና በስራዎቹ ዙሪያ እንዲህ አውግቶናል።

ታዛ፦ ዓይንህን የታመምክ ሰሞን አድናቂዎችህና አክባሪዎችህ ተደናግጠው ነበር፤ አሁን ጤንነትህ ምን ይመስላል?

 ኪሮስ፦ እርግጥ በደንብ አላይም፣ የሰው ቅርፅ ይታየኛል እንጂ ማንነትን አልለይም። ብርሃን ይታየኛል። የመኪና መንገድ ማቋረጥ አልችልም። ቅርብና ሩቅን መገመት ያዳግተኛል። ራቅ ያለ ቦታ ለመሄድ ስፈልግ በሰው እገዛ ነው። በተረፈ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግቢን እና መኖሪያ ቤቴን ራሴን ችዬ ነው የምንቀሳቀሰው። አንድ ጋዜጠኛ ልክ እንዳንተ ልጄን “ጋሽ ኪሮስ እንዴት ነው?” ሲል ይጠይቃታል፤ በዚህ ጊዜ የመለሰችው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?

ታዛ፦ ምን አለች?

ኪሮስ፦ “ዓይን ማለት ዓለምን የምናይበት መስኮት ነው አይደል? ለጊዜው የአባቴ ዓይን መስኮት ገርበብ ብሏል፤ አሁን ወደ ውጪ ሳይሆን ወደ ውስጡ ነው የሚያየው” ነው ያለችው። ይህ የእሷ መልስ የእኔም መልስ ነው።

 ታዛ፦ ምን ማለት ነው? እንዴት ተረዳሃት?

ኪሮስ፦ ከእንግዲህ የውጪውን ዓለም አያይም ማለቷ ነው የሚመስለኝ። የህንጻውም ውበት፣ የተፈጥሮም ውበት፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ መጻፍ፣ እንደ ልብ ሮጦ መራመድ፣ ከልክ ያለፈ መዝናናት፣ የፈለጉትን ለማድረግ መጣር … የለም ማለቷ ነው። የውጪውም ቢሆን ወደ ውስጥ የሚገባ ነው። ስለሱ ታስባለህ፣ ታደንቃለህ ስለሱ ትዘምራለህ። ወደ ውስጥ መመልከት ደግሞ ስላለፈው ነገር ብቻ ነው የምታስበው። ምን መልካም፣ ምን መጥፎ ሰራሁ፣ ምን ይቆጫል፣ እነዚህንስ ከአሁን በኋላ እንዴት ነው ከራስ ጋር ማስታመም፤ ማስታረቅ የሚቻለው። በሚለው መንፈስ የተረጎመችው ይመስለኛል። በሌላም መንገድ ወደ ውስጥ ማየት ጀምሯል ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ጀምሯል ማለቷም ነው። በፆም፣ በፀሎት፣ በልመና፣ በምስጋና፣ በአጠቃላይ ውስጥን ማድመጥ ላይ ነው ማለቷ ነው። ትክክልም ነው። ሳይኮሎጂስት ናት። ሰመሃል ትባላለች፤ ትልቋ ልጄ ነች። በነገራችን ላይ በጥሩ ትዳር ውስጥ ነኝ። በአሁኑ ወቅት አምስት ልጆች አሉኝ። የልጅ ልጆችም አይቻለሁ። ቤተሰቦቼ ሌላው ዓይኔ ናቸው።

 ታዛ፦ በጣም ደስ ይላል። እስኪ የህመምህ መነሻው ምንድነው? መቼ እና እንዴት እንደነበርስ ታስታውሳለህ?

ኪሮስ፦ የዛሬ ሁለት ዓመት አሜሪካን አገር ለሠርግ ስሄድ አውሮፕላን ውስጥ ነው ድንገት ዓይኔ የጨለመብኝ። ድንገት። የቀኝ ዓይኔ አላውቀውም እንጂ ከልጅነቴ ጀምሮ የማየት ኃይሏ ደካማ ነበር። የግራዋ ጥሩ ዕይታ ስለነበራት በሁለቱ የማይ ነበር የሚመስለኝ። የግራዋ ስትጨልም በቃ አበቃ። አውሮፕላን ውስጥ ለመውረድ ስንቃረብ የኢምግሬሽን ፎርም እንድንሞላ ወረቀት ይሰጠናል፤ ያኔ ልሞላ ስል ጉም ነገር ጋረደኝና አልታይ አለኝ። ቀላል ነገር መስሎኝ ደጋግሜ አይኔን ባሽ ምንም የሚለወጥ ነገር አልመጣም። ትንሽ ደነገጥኩ፤ ወዲያው ግን ተረጋጋሁና ሆስቴሷ እያነበበችልኝ ፎርሙ እንዲሞላ ሆነ። በዚያው የሚቀር አልመሰለኝም ነበር። እግዚአብሔር ግን የፈቀደውን አደረገ፣ ያንን ተቀብያለሁ። እኔ በተፈጥሮዬ /positive thinker/ መልካምን ከሚያስቡ ሰዎች ውስጥ ነኝ ብዬአምናለሁ። እግዚአብሄር አምላክ ያንን ያደረገበት ምክንያት አለው። ስለዚህ እራሴን ከሁኔታው ጋር አለማምጃለሁ።

 ታዛ፦ ህክምናውስ?

 ኪሮስ፦ ሁለት ወር ቆይቼ ወደ አገሬ ስመለስ ባሰ። ቤተ አማን የሚባል የዓይን ህክምና ሆስፒታል ውስጥ ዶክተር ሳምሶን ዘንድ ቀርቤ ታየሁ። አቫስት የሚባል መርፌ ዓይኔ ላይ ተወጋሁ። የዓይን ግፊት መሆኑ ታወቀ። በየ ስድስት ሳምንቱ መርፌ መወጋቱን ቀጠልኩ። አንዱ መርፌ ሶስት ሺ ብር ነው። ያም ሆኖ እየባሰ ሄደ። ምኒልክ ሆስፒታልም ዶክተር ትልቅሰው ዘንድ ቀርቤ ታከምኩ፣ ያም ሆኖ መሻሻል የለም። ግን ዶክተሮቹ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። በጥሩ ክትትል 47 ደርሶ የነበረው ግፊት ኋላ ላይ ወደ 20 ወረደ። እዚያው ባለበት እንዲቆም ሆነ። ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች አንድ ሰው ብቻ ነው የዓይን ግፊቱ ወርዶ ባለበት የሚቆመው። እድለኛ ነኝ። ከዚያ በኋላ ሞራም ተገፈፍኩ። የዓይን ጤና መጠበቂያ ሌዘር አደረኩ። ላለፉት ስድስት ወራት ግፊቱም አልጨመረም። እግዚአብሔር ይመስገን በዚያ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት። በእግዚአብሔር እርዳታ ሙሉ ለሙሉ እንዳልታወር ረድተውኛል። ተመስገን ነው። በእግዚአብሔር የምናምን ከሆነ ያንን ነው ማለት። እሱ ነው ሰጪ፤ እሱ ነው ነሺ። ደህና ነኝ።

 ታዛ፦ ውጪ የተሻለ ህክምና ይኖር ይሆን?

 ኪሮስ፦ ብዙ ሰው እንደዚያ ነው የሚለኝ። ለምን ውጪ ሄደህ አትታከምም?… እዚያ ያሉ ወዳጆቼም ሞክረዋል። በታሰበው ሁኔታ አልተሳካም። አሁንም መሄድ እችል ነበር። ግን ሃኪሜን አማክሬ እዚያም ብሄድ አቫስት እንደሚወጉኝ ነው የነገረኝ። የተሻለ ህክምና ቢኖር ለመሄድ የምችልበትን ሁኔታ እሞካክር ነበር። የሆነው ሆኖ አሁንም አማራጮችን እያየሁ ነው።

ታዛ፦ ከዓይንህ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር በስራህ ላይ የመጣ ተፅእኖ አለ?

ኪሮስ፦ ዳና የተሰኘውን የቴሌቪዥን ድራማ ዓይኔን እያመመኝና ማንበብ እያቃተኝ ልጆቼ እያነበቡልኝ አጥንቼ ነበር ሰርቼ የጨረስኩት። በጣም ተቸግሬ ነው የተወጣሁት። ሆኖም በስኬታማነት ነው ያለቀው። ከዚያ ባለፈ ግን የእኔ ትልቁ ስራ የነበረው ከመንግስት ስራ በ2002 ዓ.ም በፈቃዴ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ሁነቶችን ማሰናዳት /Event organize ማድረግ/፣ መድረክ መምራት ነበር። ያንን መስራት አልችልም። የቤተሰብ መደጎሚያ የሚያስገኙት እነሱ ነበሩ። ፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ከጥበቡ፣ ከህብረተሰቡ ላለመራቅ ነው። ከዚህ በኋላ ያንንም ለማድረግ ሳያስቸግረኝ አይቀርም። ዛሬ ቁጭ ብሎ የጡረታ ገንዘብ መቀበል ነው እንግዲህ። እና ጉዳቱ ቀላል አይደለም። ዕድሜዬ ከ60 በላይ ነው ግን ውስጤ ገና ነበር። ገና ብዙ እሰራለሁ ብዬ ነበር የማስበው። ግን የእኔ ሃሳብ ሌላ ነው፤ የእግዚአብሔር መንገድ ደግሞ ሌላ ነው። ይህ መንገድ ተሰናከለ ብዬ ደግሞ እግዚአብሔርን አላማርርም። “እሱ የከፈተውን ጉሮሮ እሱ ይዘጋዋል” አይደል የሚባለው። ያ ነው።

ታዛ፦ ግን ይህ ሁኔታ ባይከሰት ምን ለመስራት ነበር እቅድህ ?

ኪሮስ፦ የመጻፍ ምኞት ነበረኝ። በዕድሜ እና በስራ ያካበትኩትን ልምድ የመጻፍ፣ የማንበብ ብርቱ ፍላጎት ነበረኝ። ከሌሎችሊቃውንቶች ጋር ሲነጻጸር ቢራራቅም የአቅሜን ያህል አንብቢያለሁ። የዚያ ሁሉ ጥርቅም አንድ ውጤት እንዲያመጣ እጽፋለሁ ብዬ ነበር። አልሆነም። ድራማውንም፣ ሌሎች የጥበብ ስራዎችንም እያሰብኩ ነበር። እንግዲህ አሁን አረፍ ብዬ ላስታመውና ካልሆነ ብሬል እማራለሁ የሚል ሃሳብ አለኝ። ተስፋ አልቆርጥም።

 ታዛ፦ በህመምህ ወቅት በልዩ ሁኔታ ፈጥነው ደረሱልኝ የምትላቸው ይኖሩ ይሆን?

ኪሮስ፦ በጣም ይገርምሃል በጣም በጠና በታመምኩ ጊዜ ሰይፉ ፋንታሁን በሬዲዮ ቃለ መጠይቅ አድርጎልኝ በዩቲዩብ ለቀቀውና በመላው አለም ተሰራጨ። ይሄን ያህል ሰው ያውቀኛል፤ ይህን ያህል ሰው ይወደኛል፣ ሀዘኑን በለቅሶ ይገልፅልኛል ብዬ አላስብም ነበር። በወቅቱ ከበርካታ የውጪ አገራት ነው የስልክ ጥሪ ያስተናገደኩት። እድለኛነቴን በዚያ አየሁት። የጥበብ ሰዎች ህዝብ ነው ሃብታችን የሚሉት ያለ ምክንያት አይደለም። ያንን ነው የተገነዘብኩት። ጭብጨባ፣ አድናቆት፣ ፍቅር ነው የምናተርፈው እንጂ ገንዘብ አይደለም። እኛ አርቲስቶች በጭብጨባ ተወልደን፣ በጭብጨባ አድገን በጭብጨባ የምናረጅ ነን። እና ከሚያውቁኝም ከማያውቁኝም ለአንድ ወር ያህል ያለ እረፍት ሲደወልለኝ አንዱ በምን መልኩ እንርዳ፣ ጎ ፈንድ እናቋቁም፣ መጥተህ ታከም፣ እያሉ ነበር ሃሳብ የሚሰጡኝ። የሚያጽናኑኝ። ገንዘብም የላኩልኝ አሉ። ከዚህ ሌላ ምን ሃብት አለ። ምን ፍቅር አለ። እጅግ በጣም ነው አክባሪዎቼን እና አድናቂዎቼን የማመሰግነው። እዚህ አገር ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆኑ በአርቲስትኔቴ የሚያውቁኝ ሁሉ። የማየት አቅሜ እየጠነከረ የሄደ እስኪመስለኝ ድረስ ብርታት፣ ምርኩዝ ዓይን ሆነውኛል። ብዙ ጓደኞቼ ስለ እኔ ሲጠየቁ እንባቸው ይቀድማል። በጣም የሚያውቁኝ ከመሆናቸው የተነሳ ነው ያ የሆነው። እኔ ግን ብዙ አላስቸግርም እንዲያውም እቀልዳለሁ። የሰለሞን አስመላሽ ውለታ የሚከፈል አይደለም። በተለይ ይህን መልእክት አስተላልፍልኝ፡ እናንት በልግስናችሁ ስማችሁ እንዲጠቀስ የማትፈልጉ ሁለት የልብ ወዳጆቼ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋችሁልኛልና ሳመሰግናችሁ እኖራለሁ በልልኝ።

 ታዛ፦ አደርሳለሁ፤ እስኪ ወደ ሙያህ እንምጣና እንዲያው በጥበቡ ዘርፍ ምን ያህል ዘመን አገለገልክ?

 ኪሮስ፦ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዳና ማብቂያ ድረስ 35 ዓመት ሰርቻለሁ። 1975 ዓ.ም. ነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት የባችለር ዲግሪዬን ይዤ ስራ የጀመርኩት። በዩኒቨርሲቲው በቴአትር ዘርፍ ትምህርቱ ሲሰጥ ሦስተኛው ባች ነኝ። በስራ ዓለም ከጥበብ ስራ በተጓዳኝ በሃላፊነት በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም፣ የባህል መምሪያ ሀላፊ፣ የሚሊኒየም በዓል አከባበር ጽቤት ዋና ዳይሬክተር፣ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት አርቲስቲክ ማኔጀር ሆኜ ሰርቻለሁ።

ታዛ፦ ህዝብ ከጥበብ ስራዎችህ ውስጥ በይበልጥ በምን ያውቀኛል ብለህ ታስባለህ?

 ኪሮስ፦ አጠቃላይ አርቲስቱ በማኔጅመንት ያውቀኛል።ነገሮችን ወደ ጥሩ ነገር በመምራት በማደርገው ጥረት ያውቀኛል ብዬ አስባለሁ። ወጣቶች ወደ አርቱ እንዲመጡ በማደርገው ጥረት ያውቀኛል። ብዙዎቹ ወጣቶች ዛሬ ፕሮፌሽናል የሆኑ የኛ ተከታዮች አርቲስቲክ አባት እንደሆንኩ ያስቡኛል ብዬ እገምታለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ነገር ነው የሚያውቀኝ። በፊልም ገንኜ የወጣሁባቸው ሰማያዊ ፈረስ እና ስላንቺ በተሰኙት ነው። በመሪ ገጸ ባህሪያት ህዝቡ ውስጥ እንድቀር ሆኛለሁ። በቴሌቭዥን ድራማ ገመና ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ፣ ቀጥሎ ለስድስት ዓመት በሄደው ዳና ድራማ ላይ በተጫወትኳቸው ገጸ ባህሪያት በደንብ ታውቄበታለሁ።

ታዛ፦ ገመና ቁጥር አንድ ላይ ዓይንህ ታውሮ እንደ አባት የሰራህበት ገጸ ባህሪ እንዳለ አውቃለሁ። ይህ ሁኔታ አሁን ካለብህ የዓይንህ ችግር ጋር ተገጣጠመ ልበል ኪሮስ?

 ኪሮስ፦ ይገርምሃል፤ እንደዚያ ነው የሆነው። በፊልሙ ላይ አይኔ የማያይ ሆኖ ቤት ውያለሁ። ያኔ በእውኑ ማንነቴ ዓይኔ ጤነኛ ነበር። እንደዚያ በመሆኔ እቤት ውስጥ ቤተሰቦቼ የሚያደርጉት ነገር ተመልካችን ያናድደዋል። ሃብታም ስለሆንኩ ንብረት ላይ የነበረው ሽኩቻ በእርግጥም የሚያናድድ ነበር። ድንገት ወድቄ ነርቬ ሲነቃነቅ ደግሞ ዓይኔ ይበራል። ሳይንሳዊ ጥናትን ተከትሎ ነው ድርሰቱ የተዘጋጀው። እና ይህን ፊልም የተመለከቱ አንዳንዶች “አይይ ኪሮስ የተመኘውን ነው ያገኘው” ነው ያሉት። ማየት የተሳናቸው የሚያደርጉትን በደንብ ተውኜዋለሁ መሰለኝ። ግን ግጥምጥሞሽ ነው። ደራሲው የእኔን የወደፊት ሁኔታ አስቦ ያዘጋጀው ነገር አይደለም። ሊሆንም አይችልም። የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው።

 ታዛ፦ በቴአትር ዘርፍስ?

 ኪሮስ፦ የተለያዩ የመድረክ ቴአትሮች ላይ ስተውንም ህዝቡ ያውቀኛል። የዊሊያም ሼክስፔር የትርጉም ስራ የሆነው የቬኑሱ ነጋዴ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ጣውንቶቹ፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ሳልሳዊ ባልንጀራ፣ አሉ፣ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። በአንጻሩ እኔ መሆኔን ህዝቡ ጠንቅቆ የማይረዳቸው የጥበብና የጋዜጠኝነት ስራዎችም አሉኝ። ከትምህርት ቤት እንደወጣሁ ሬዲዮ ላይ ወደ አራት ዓመት በፍሪላንስነት ሰርቻለሁ። በድራማ፣ በጽሑፍ አንባቢነትና የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀትም ተሳትፎ ነበረኝ። በሬዲዮ ምናልባትም ከ25 ዓመታት በላይ የኢትዮዽያ ሬዲዮ ለፕሮግራም መክፈቻነት የተጠቀመበት “ኢትዮዽያን እንቃኛት” የሚለው ድምጽ የእኔ መሆኑን ብዙ ሰው አያውቀውም። በተመሳሳይ የፖሊስና የጦር ኃይሎች ፕሮግራም መክፈቻም ነበረኝ።

ታዛ፦ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ባልደረቦች ከሙያዊ ወዳጅነት ባለፈ በማህበራዊ መስተጋብራቸውም የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ይታያል፤ ይህ ከምን የመጣ ነው?

ኪሮስ፦ እኔን ያገኘኸኝም ሆነ አሁን እያወራኸኝ ያለኸው እዚሁ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግቢ ውስጥ ነው። አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም በቤቱ ፍቅር አለ። በአመት በዓልም ሆነ እሁድ ግቢው ውስጥ መጥፋትን አንሻም። ሰው አይጠፋበትም። ታሪካዊ ቤት ነው። የቀደሙ የጥበቡ ሰዎችም የሚመቻቸው ግቢ ነው። የቴአትር ቤቱን መጥፎነት ማንም አይፈልግም። ከቤቱ ስርቅ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም፤ የሆነ ነገር ሆኖ የሚጠብቀኝ ነው የሚመስለኝ። የሆነ ነገር የሚጎድልብኝ አይነት ስሜትነው የሚያድርብኝ። የብዙዎቻችን ስሜት ነው ይሄ። ማህበራዊ ትስስሩ ራስ ምታት ታሞ ለቀረ እንኳን መዋጮ ይደረግ የሚባልበት ቤት ነው። በቃ ቤቱ እንደዚያ ነው። ዛሬ ዛሬ ግን የቀድሞዎቹ ግማሹ በሞት፣ ግማሹ በህመም ከቤቱ እግራቸውን ሲያርቁ ያ ሁኔታ ደብዘዝ እያለ መጥቷል። ወጣቱ ትውልድ ያንን ጠብቆ ቢዘልቅ ምኞቴ ነው።

ታዛ፦ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ፈርሶ ዘመናዊ ግንባታ ሊደረግበት እንደሆነ ይሰማል፤ አንዳንዶች ደግሞ ታሪካዊ ቤት ስለሆነ በቅርስነት ሊቀመጥ ይገባል ባይ ናቸው፤ አንተስ?

ኪሮስ፦ ይህ ነገር በተለያዩ ጊዚያት ሲባል ነበር። በኔ እምነት በብሔራዊ ደረጃ ቴአትር ቤት መሆን የሚገባው አገር ፍቅር ነበር። በጥቁር አፍሪካውያን ዘንድ የመጀመሪያው ቴአትር ቤት ነው አገር ፍቅር። ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ ቴአትር ቤት ነበራቸው ግን የራሳቸው አልነበረም። የነጮቹ ነው። የገዥዎቻቸው። ጥቁር አፍሪካውያን ቀድሞ ነገር ሊዝናኑ ማን ፈቀደላቸው? …ኢትዮዽያ ብቻ ነች ይህን ነፃነት በራሷ ያገኘችው። ጣሊያንን ለመከላከል ተብሎ የተቋቋመ የኪነጥበብ ተቋም ነው አገር ፍቅር። ለዚህ ነው ቀዳሚ ቦታ ሊሰጠው ይገባል የምለው። እንደ አገልግሎቱ እና እንደሰራው ስራ ማንኛውም የተፈራረቀው መንግስት ምንም ያደረገለት ነገር የለም። አሁንም ቢሆን ከቃል ያለፈ ነገር ላይ አልደረስንም። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ በቅርቡ መጥተው ከጎበኙት በኋላ ይህን ተናገሩ። መፍረስ ያለበት ፈርሶ ታሪካዊውን አቆይተን የሚጨማመሩ ቦታዎችን ጨማምረን ዲዛይኑ ወጥቶ በአስቸኳይ በሚቀጥለው አመት ይጀመር ነው ያሉት። የወጣቶችና ህፃናት ቴአትር ቤት ህንፃ ተጀምሮ ማለቅ በሚገባበት ጊዜና በጀት አላለቀም፤ ራስ ቴአትር ፈርሶ ግንባታው ሳይጀመር አመታት እየተቆጠረ ነው፤ ይህን ይህን ስንመለከት መቼም ስጋት ሳያድርብን አይቀርም። ከሆነ ይህ ትልቅ ነገር ነው። ከዘመኑ ጋር መዘመን መልካም ነው። ሲሆን ነው እንግዲህ የምንደሰተው።

ታዛ፦ በመጨረሻ ህዝብ ስላንተ ምን ቢያውቅ ደስ ይልሃል፤ ከዚህ ቀደም ስላንተ ከተነገረው ውስጥ ይስተካከልልኝ የምትለው ካለ እድሉን ልስጥ ?

ኪሮስ፦ አንዳንዴ ሰዎች አንተ ባልሆንከው መንገድ ሊረዱህ ይችላሉ። በእነሱ አእምሮ ዘርህ፣ ብሔረሰብህ፣ ቋንቋህ አንተ ባላሰብከውና ባልሆንከው ቦታ ላይ ሊያስመድብህ ይችላል። በአንዳንዶች ዘንድ እኔ ባለ ብዙ ፎቅ ባለቤት ነኝ፣ ብዙ ሃብትና ንብረት ያለኝ ነኝ። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልኝ የምፈልገው ግን እንደማንኛውም አርቲስት መንግስት በሚሰጠኝ ደመወዝ የምተዳደር፤ ከዚያ ውጪ ከልጆቼ በቀር ምንም የሌለኝ ሰው ነኝ። አንዳንድ የተዛባ አስተሳሰብና መንገድ የሚከተሉ ሰዎች በምክንያት፣ በተጠየቅ፣ በሎጂክ እንዲመሩና ልቦና እንዲሰጣቸው ነው የምመኘው።

ታዛ፦ አመሰግናለሁ፤ በአንባብያን ስም ቀሪ ዘመንህ የጤናና የሰላም እንዲሆንልህ እመኛለሁ።

ኪሮስ፦ አሜን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top