ከቀንዱም ከሸሆናውም

ስለ ሞትና መረሳት

ይኸን መጣጥፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዘንድሮ 2011 ዓ.ም ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ “አባባ ጃንሆይ” እንድላቸው ይፈቀድልኝና፣ በአፍሪቃ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የቆመላቸው ሃውልት ዜና ትዝ ስላለኝ ነው:: ሰሞኑንም ሐምሌ 16 ቀን የልደታቸው 127 ዓመት ይከበራል:: ለውጭ ሀገር ሰዎች ለነ ክዋሜ ንኩርማህ፣ ካርል ሂንዝ ሃውልት ሲቆም የሳቸው መቅረቱ ቅሬታ ፈጥሮብኝ የነበረውን ለማካካስ ፈልጌ ነው::

 በትምህርት አንፀው ኮትኩተው ለቁምነገር ያበቋቸው አመራሮች ገሸሽ ማድረጋቸው ብዙ ኢትዮጵያውያንን ሲከነክን ቆይቶ፣ ዘንድሮ በ132ኛው የሕብረቱ ጉባኤ፣ መላው የአፍሪቃ መሪዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ እና ሌሎች ታላላቅ ግለሰቦች በተገኙበት ሐውልታቸው መመረቁ “መልካም ሥራ ከመቃብር በላይ ይኖራል” የሚለውን እውነት አስመስክሯል::

 በእርግጥ የኢትዮጵያ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሐወልታቸው እንዲቆም በይፋ ደብዳቤ ጽፈዋል:: ኢህአዴግም አራት ኪሎ የነፃነት ሃውልት ላይ የነበረውን የሳቸውን ምስል ደርግ በጎፈሪያም አርበኛ ተክቶት የነበረውን መልሶ እንደነበር ማስቀረፁ ይታወሳል::

 ይሁንና አሁን በቆመው ሃውልት ላይ አንዳንድ ስሞታዎች መሰማቱ አልቀረም:: ያሁሉ ግርማ ሞገሳቸው ቀርቶ በተራ የሥራ ልብስ መሰራቱ ያልተዋጠላቸው አሉ:: አርቲስቱ በቀለ መኮንን ሲያብራራ ንጉሠ ነገሥቱ የአንድነቷን ድርጅት ለመመስረት ከአገር አገር ተዘዋውረው የለበሱት ልብስ እንደነበር እና የተሰራበትም የንሐስ ብረት በተስማሚነት መመረጡን አስረድተዋል::

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሃውልት

በበኩሌ ወድጄዋለሁ:: ወደ ሀያኛው ክፍለዘመን ያቀራርባቸዋል:: ከአጼ ቴዎድሮስ እና አጼ ዮውሐንስ ቁንዳላ ፣ ከአጼ ምኒልክም ገርዳሳ ለየት ያደርጋቸዋል:: ከሀያኛው ክፍለዘመን ታላላቅ መሪዎች ከነዊኒስተን ቸርችልና ከነ ጆን ኬኔዲ ጋር ያመሳስላቸዋል:: ለወጣቱም ኢትዮጵያዊ የኛ ዘመን ሰው ናቸው ያስብለዋል::

አርቲስቱ በእርግጥም ጃንሆይ የሁለት እጆቻቸውን አውራ ጣቶች እና አመልካች ጣቶቻቸውን አገጣጥመው የሚያሳየው ፎቶ ግራፋቸው መቅረፁ ያስመሰግነዋል:: ምን ይሆን ትርጉሙ? እያልኩ ሳሰላስል ለነበርኩት ሰውዬ ሁሉ ነገር ዜሮ፣ አላፊ እና ጣፊ መሆኑን ያጋለጠልኝ አሁን ነው:: ቋሚ ሆኖ የሚቀር የለም:: የዚች ዓለም አዱኛ እና ሕይወት ጽላሎት ወ-ሕልም ነው:: የሰው ልጅ ግን ምኞቱ ኢ-ሟችነት ነው:: ሞትን አይቀበለውም::

 በተለይ በወጣትነቱ ዘመን የማይሞት ይመስለዋል:: እዚህ ላይ መንዛዛት አይሁንብኝና አንድ የልጅነት ዘመን ገጠመኜን ላውጋ:: አራት አምስት ዓመት ቢሆነኝ ነው:: ሐረርጌ ደደር በሚባል ከተማ አጠገብ በነበረው ርስቴ ላይ ሳድግ ከቤታችን በላይ ባለው ሸንተረር ላይ የሚኖሩ እማማ እንጉዳይ የምንላቸው ዘመዳችን ነበሩ:: በጣም አሮጊት ናቸው:: ዘወትር ፀሐይ ማቆልቆያዋ ሊደርስ ሲል ጭራሮ ለቃቅመው በቤታችን በኩል ያልፋሉ:: ከቤታቸው በታች አንድ “የግራኝ ድንጋይ” የሚባል ጠፍጣፋ ቋጥኝ አለ:: እዚያ ከልጆች ጋር እየሄድኩ ሸርተቴ እጫወትበት ነበር::

አንድ ቀን “እማማ እንጉዳይ ሞቱ” ተባለ:: አሳዳጊ እናቴ ነጠላቸውን አሸርጠው አስከሬኑን ለመሸኘት ብቻዬን ጥለውኝ ይሄዳሉ:: ከቤታችን በታች የተቆለለ የዲኬ (የፍግ) ማጠራቀሚያ ዲብ ላይ ወጥቼ ስጫወት ሸንተረሩን በሚያቋርጥ ቀጭን የእግር መንገድ ላይ ቃሬዛ የተሸከሙ ሰዎች ሲያልፉ አያለሁ:: እናቴን የተከተሉት ሰዎች ውስጥ ለማየት ብፈልግ አጣኋቸው:: ሰዎቹ ከዓይኔ እስኪጠፉ ተመልክቼ ጨዋታዬን ቀጠልኩ:: ጭርር ሲልብኝ ዙሪያ ገቡን ቃኘሁት:: ምንም የተቀየረ ነገር የለም:: ጋራው፣ ጫካው እንዳለ ነው:: አሞሮችም በሰማይ ላይ ይበራሉ:: የግራኝ ድንጋይም ፀሐይዋን ያንፀባርቃል:: ማታ አሳዳጊ እናቴ ከቀብር ሲመለሱ “እማማ እንጉዳይን የት ወሰዳችኋቸው?” ብዬ ጠየቅኋቸው::

 “ደሩ ማርያም ቀበርናቸው” አሉኝ:: “እኔ ግን አልሞትም፤ አልቀበርም ” አልኳቸው::

 ከብዙ ዓመታት በኋላ የደደር ርስቴም ተወርሶ የአሳደጉኝ እናቴም አርፈው፣ ያደግሁበትን ቀዬ ልጎበኘው ሄድኩ:: የቤታችን ደብዛው የለም:: ትልልቅ የገርገራ አጥሩም የለም:: የአካባቢውን ሰዎች ስጠይቅ “ለመንደር ምስረታ ነቃቅለው ወስደውታል” አሉኝ:: የግራኝ ድንጋይንም ከሥፍራው አጣሁት:: እናም አዘንኩ:: ሁሉም ነገር በነበረበት እንደማይቆይ የማውቀውን እውነት በተጨባጭ አየሁት::

ወደ ጀመርኩት ርዕስ ልመለስ:: “መልካም ሥራ ከመቃብር በላይ ነው” የሚባል አባባል አለ:: የማይፈርስ ሃውልት በጎ ሥራ ብቻ ነው:: የሰው ልጅ ከአላፊው ትውልድ የሚቀስመው ትምህርት የተሻለ ነገን ለመፍጠር ሊጥር ይገባዋል:: በብጥብጥ እና በጦርነት የተሞላው ታሪካችን ራሱን እንዳይደግም የሠላም እና የአንድነት አባት የሆኑት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሃውልት ያሳስበናል::

ኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት የውጭ ግድግዳ ላይ አንድ ጽሑፍ አለ:: በፈረንሳይኛ እና በአማርኛ “L” Unite faite la force” ይላል:: ትርጉሙም “አንድት ኃይል ነው” ነው:: ጃንሆይ ለሀገራችንና ለአፍሪቃ የተዉልን ቅርስ ይህ ነው:: ሠላምና አንድነት የአዲሱ ግሎባል ሥልጣኔ ተግዳሮት ብዝሃንነትና አንድነትን ይዞ ማቆየት ነው:: ውጪያዊ ልዩነትን (በባህል፣ በቋንቋ፣ በዘር በሃይማኖት፣ በፆታ) አስወግዶ በውስጣዊ አንድነት (በሰብአዊነትን) መተካት ነው:: ዜኖፎቢያን (የባዕዳንን ፍርሀት እና ጥላቻ) ማስወገድ ነው:: የግርማዊ ጃንሆይ ሃውልት የአፍሪቃ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መቆሙ የሰላምና አብሮ መኖርን ባህል መዳበር የሚረዳ ታላቅ ላንድማርክ ሆኖ እንደሚቆይ እምነት አለኝ:: ሠላም ቆዩልኝ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top