አድባራተ ጥበብ

Modernist Ar t in Ethiopia – ዳሰሳ

የመጽሐፉ ርዕስ፡ Modernist Art in Ethiopia የመጽሐፉ ደራሲ፡ ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) መጽሐፉ የታተመበት ጊዜ፡ 2019 (እ.ኤ.አ.) የመጽሐፉ አሳታሚ፡ ኦሀዮ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ (Ohio University Press) እንደ መንደርደርያ የአደባባይ ምሁር ተብለው ከሚጠሩ ጥቂት የሀገራችን ምሁራን አንዷ ናቸው። በተለይ የሀገራችንን ኪነጥበብ ጉዞ እና የዘመናዊነትን ፅንሰ ሀሳብ ላለፉት አስር ዓመታት ገደማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢያቸው ሆነው በጥናታዊ ኮንፈረሶች፣ በህዝባዊ ውይይቶች፣ በሬድዮ ፐሮግራሞች፣ በቴሌቪዥን አቅርቦቶች በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጠለቅ ያሉ ጥናታዊ ስራዎቻቸውን ሳይታክቱ ሲያቀርቡ ነበር- እያቀረቡም ነው። በተለይ በሸገር 102.1 ሬድዮ ጣብያ የእሁድ ጠዋት “ሸገር ካፌ” ፕሮግራም ለረዥም ጊዜ ቋሚ ደንበኛ ሆነው ጥናታቸውን እና ምሁራዊ ዕይታቸውን አቅርበዋል። ማህበረሰቡን ለውይይት ጋብዘዋል-የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበባት ኮሌጅ መምህርት እና የገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ።

 በዚህጽሑፍበአጭሩ የምዳስሰው አዲሱ መጽሐፋቸው Modernist Art in Ethiopia ሲሰኝ የታተመው ሰሞኑን ነው-ከወጣ ጥቂት ጊዜው!! መጽሐፉ ሁሉን ነገሩን ደምሮ በ 339 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ሀያ አራት ገፅ የፈጀው ወፈር ያለው መግቢያውን ሳይጨምር አምስት ምዕራፎችን ያካተተ ነው። በእነዚህ ምዕራፎች በኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ ታሪክ ዋና ዋና ታሪካዊ ጉዳዮች፣ ባለሞያዎች፣ ፍልስፍናዊ አካሄዶች፣ የትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴዎች እና ደራሲዋ ሊተኮሩባቸው ይገቧቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች አካተው አቅርበዋል። የኦሀዮ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ይህንን መጽሐፍ የ New African Histories Series አካል አድርጎ ያሳተመው ሲሆን በዚህም ዋና ዋና ከሆኑ አዳዲስ የአፍሪካ ማህበረሰባዊ፣ ኪነጥበባዊ እና ፖለቲካዊ ጸሐፊያን እና ጽሑፎች ተርታ መድቦታል። መጽሐፉን አጠር አድርጌ ለመመልከት እሞከራለሁ።

አዲሱ መጽሐፋቸው በጥልቀት ያልተጠናውን የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ታሪክ ከሰፊው የሀገሪቱ የባህል፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ታሪክ ጋር በማያያዝ እጅግ በጠለቀ ሁኔታ የመረመሩበት ነው። በየዘመኑ ዋና ዋና የሆኑ ሰዓሊያንን የስዕል ስራዎች ከወቅቱ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሁኔታ ጋር አዋህዶ በመተንተን በሰዓሊዎቹ ህይወት እና የስዕል ስራዎች ላይ ሰፊ ምልከታ (እንዲያም ሲል አድናቆት!) እንዲኖረን ያስችላል። የመጽሐፉ የጊዜ አከፋፈል ከሀገሪቱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ለውጥ ጋር የተያያዝ ሲሆን የስዕል ስራዎቹ ሲተነተኑ ግን አጠቃላዩን ማህበረ-ፖለቲካዊ ሁናቴ ባጤነ መልክ ነው። በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ ስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበብን ታሪክ በስፋት እና በጥልቀት የተነተነ ለሀገራችንም ሆነ ለዓለም አቀፍ አንባቢ የቀረበ ጥናት ይሄ ትልቁ እና የመጀመርያው ነው። መጽሐፉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መፃፉም ለሀገራችንም ሆነ ለዓለም ዓቀፍ አንባቢ ተደራሽ ለመሆን ትልቅ ድልድይ ሆኖለታል። ከንባቡም በላይ በተለይ ስለ ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ሰዓሊያን እና የስዕል ስራዎች ከሰፊው የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በማዋሃድ መቅረቡ ስለ ኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ሁነኛ መንገድ ነው።

መጽሐፉ

የመጽሐፉ መግቢያ ከላይ እንዳልኩት ወፈር ያለ ነው- በገፅ ብዛቱም፣ በያዘው ሃሳብም። በተለይ የመጽሐፉን ዋና ዋና የመከራከርያ ነጥቦች የተቀመጠበት ነው። በዚህ መግቢያ ደራሲዋ የመጽሐፉ ዋነኛ የማጠንጠኛ ነጥብ ያስቀምጣሉ፡ “የኢትዮጵያ ዝመና እና ዘመናዊነት ከሰፊው የዓለም የዘመናዊነት ርዕዮተ- ዓለም እና ፖለቲካዊ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው።” በማለት። ይሄ ዋነኛ የማጠንጠኛ ሀሳብ በመጽሐፉ የተለያዩ ምዕራፎች ተደጋግሞ በልዩ ልዩ ማስረጃዎች ሲተነትን እናነባለን። በዚህ ክፍል በተለይ በቅኝ ግዛት ትግል ወቅት እና ከነፃነት በኋላ በመጡ ልዩ ልዩ አፍሪካዊ የሀሳብ ክርክሮች እና ውይይቶችን በማንሳት በዚሁ መነፅር የኢትዮጵያን የዝመና እና የዘመናዊነትን ሁኔታ ለመመልከት ይሞክራሉ። አራት መሰረታዊ ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች እንደ ዋና ዋና አምድ በመውሰድም መጽሐፉ የሚኖረውን አጠቃላይ ይዘት ያመለከታሉ።

አንደኛ የኢትዮጵያን የዝመና እና ዘመናዊነትን ጉዞ “በኢትዮጰያ የታሪክ አፃፃፍ የዝመና እና የዘመናዊነት ሁኔታ” በሚል ንኡስ ርዕስ ውስጥ የአራትጸሐፊያንን (ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ እና ዶናልድ ዶንሃም) ስራዎችን በመመርመር የዘመናዊነት እሳቤ በኢትዮጵያ መቼ እንደተጀመረ የየፀሃፊዎቹን የምርምር ውጤት በመጥቀስ ለማብራራት ይሞክራሉ። አጠቃላይ የስነ-ፅሁፎቹ ዳሰሳ በሆነው በዚህ ንዑስ ርዕስ ውስጥ በተለይ የዘመናዊነት ፅንሰ ሀሳብ እና ትግበራን በ1960 ዎቹ ከነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እና አጠቃላይ የሀገራችንን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁናቴ ጋር በማያያዝ የፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴን አቋም ይጋራሉ። በርግጥ በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ጅማሮ ጉዳይ ከብዙ ህሳቦች እና ታሪካዊ ሁነቶች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ አከራካሪ ቢሆንም ዶ/ር ኤልሳቤጥ የ1960 ዎቹ ን እንቅስቃሴ እንደ የዘመናዊነት ሀሳብ እና ትግበራ መጀመርያ አድርገው ወስደው በማስረጃ ይከራከራሉ-“ያለ ጥርጥር 1960ዎቹ በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ ወሳኝ ሁነቶች የተከወኑበት ጊዜ ነው። ይህንን ጊዜ እኔ እንደ ዘመናዊነት ዋና ማጠንጠኛ ዓመታት አድርጌ ወስደዋለሁ።” (14)

በዚሁ የመግቢያ ክፍል ሌላው ከኢትዮጵያ ዝመና እና ዘመናዊነት አንፃር የሚመረምሩት የታሪካዊ ጊዜን ሁኔታ ነው። ከላይ እንደገለፅኩት የዘመናዊነት ህሳብ እና ትግበራ በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ? ብለው ይጠይቁና የ1960ዎቹን አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኪነጥበባዊ ስራዎችን የኢትዮጵያ የዘመናዊነት መጀመርያ ናቸው ይሏቸዋል። በሶሰተኛው የመግቢያቸው ክፍል በዘመናዊ እና ሀገር በቀል በሆነው የኢትዮጵያ ስነ-ጥበባዊ እንቀስቃሴ ላይ አተኩረው በተለይም ይህ (ሀገር በቀሉ-በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የስዕል ስራዎች) የስነ-ጥበብ ስራ በምዕራቡ ዓለም ዕይታ ሁለት መልክ እንደተሰጠው ያትታሉ- ልዩ እና ኋላ ቀር- የሚል። በኋለኛው ምዕራፎች የነዚህን ሀሳቦች ፍርደ ገምድልነት ማስረጃ በመንቀስ ይቃወማሉ፣ይትነትናሉ። እንደውም የኢትዮጵያ ዘመናዊነት አቀንቃኞች ሀሳባቸውንም ሆነ ልምዳቸውን የተዋሱት “በምዕራባውያን ኋላ ቀር ተብሎ ከተፈረጀው ሀገር በቀል ዕውቀት ነው” (19) ይላሉ።

በመግቢያቸው መጨረሻም በተለይ መጽሐፉ በልዩ ሁኔታ ያነሳቸውን ሴት ሰዓሊያንን እና አሳቢያንን እንደሚመለከት አስቀምጠው “በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሴቶች በኢትዮጵያ የዝመና እና ዘምናዊነት ሀሳብ እና ትግበራ የነበራቸው ሚና ተጠንቶ የቀረበበት ነው” ይላሉ። ምንም እንኳ ጥናቱ ከወገንተኝት የፀዳ ለማድረግ እጅጉን የሞከሩ ቢሆንም (እርሳቸውም በመግቢያቸው እንዳመኑት!) አንድ አንድ ጊዜ በጥናታቸው መሀል ስራቸውን ከሚመርመሯቸው መሃል ለአንዳንዶቹ ማድላታቸው አልቀርም።

ምዕራፍ አንድ የመጽሐፉ አጠቃላይ ትወራዊ እይታዎች እና ዋና ዋና የመከራከርያ ሀሳቦች የቀረቡበት ነው። ከአድዋ ድል በኋላ የተፈጠረውን የኢትዮጵያ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ሁናቴ እንደ አንድ መነሻ በመውሰድ በየዘርፉ የተፈጠሩ ሁነቶች የስልጣኔን እና ዘመናዊነትን ሃሳብ እና ትግበራ እንዴት እንዳስፋፉ ያስረዳል። በተለይ ከድሉ በኋላ የተፈጠረውን ሀገራዊ ስሜት በወቅቱ ከነበሩ ሰዓሊያን መሃል በላቸው ይመርን እንደ አስረጅ በመውሰድ ስዕሎቹ ተንትነዋል። በላቸው መሀላ ፒያሳ ላይ በተለይ የአድዋን ድልን የሚዘክሩ ስዕሎችን በመስራት በወቅቱ አዲስ አበባ ለሚኖሩም ሆነ ለተጓዥ ቱሪስቶች ይሸጥ ነበር። ይህንን የበላቸውን ስዕሎች በኢትዮጵያ የስዕል ስራዎች ላይ ምርምር የሚሰሩ የውጪ ሀገር ባለሞያዎች እንደ አውሮፓ የአሳሳል ጥበብ ባለመሳሉ እንደ ሁነኛ የስነ-ጥበብ ስራ ለመቁጠር ይቸገራሉ፣ ይህ ግን ስህተት ነው ሲሉ ይሞግታሉ። የበላቸው እና ዘመነኞቹ ስራዎች (ጸሐፊዋ“የአራዳ አርቲስት” ይሏቸዋል- አራዳ አካባቢ ስዕላቸውን ሰርተው ሰለሚሸጡ!) መጠናት ያለባቸው ስራዎቹ የተሰሩበትን ሰፊ የታሪክ፣ የባህል እና የማህበረስብ አውድ መሰረት በማድረግ ነው።

የእስክንድር ቦጎሲያን – ሥዕል

 በተለይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርትስትያን የአሳሳል ጥበብ ጋር በተያያዝ ቤተ ክርስትያኗ ለዘመናት የቆመችበተን ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ ሁናቴን በጥንቃቄ ከአሳሳል ጥበቦቹ እና የስዕል ስራዎቹ ጋር መጠናት አለባቸው ይላሉ። በተለይ ምዕራባውያን አጥኚዎች የሚስቱት ትልቁ ነጥብ ይሄ መሆኑን ማስረጃ ነቅሰው ይከራከራሉ። ታሪክን ካለማጥናት ባሻገር የሚያጠኑት ሀገር ቋንቋ አለመረዳታቸው የቅኝ ግዛት አስተሳስብ እና አረዳድ ነው ይላሉ። ለዚህም አጥኚዎቹ የሚያጠኑትን ማህበረሰብ ቋንቋ ማወቅ አሊያም ምርምራቸውን በሚያውቁት ላይ ማድረግ ያልተገባ ትርጓሜ ለስራዎቹ ከመስጠት ያድናቸዋል ሲሉ ያስረዳሉ። ገፋ ሲልም በተለይ የኢትዮጵያን ስነ-ጥበብ፣ ታሪክ እና ባህል ለማጥናት ፍላጎት እና አቅሙ አለን ለሚሉ ምዕራባውያን ባለሞያዎች የመጀመርያ ስራቸው የሀገሪቱን ቋንቋ ማወቅ መሆን አለት ሲሉ ጠንከር ያለ ማሳስቢያም ይሰጣሉ።

በዚህ ምዕራፍ የስዕል ስራዎችን ከመተንተን ባሻገር ከሁለተኛው ጣልያን ወረራ በፊት ዝነኛ የነበረውን የብርሀን እና ሰላም ጋዜጣን ጽሑፎች ይቃኛሉ። በተለይ በወቅቱ አከራካሪ የነበረውን የሀገራችን የስልጣኔ ተስፋ እና የዘመናዊነት ጎዳና በወቅቱ የነበሩ ምሁራን እንዴት እንዳሰቡበት እና እንደተወያዩበት በሰፊው ተንትንነዋል። ዋና ዋና የመከራከርያ ሃሳቦቻቸውን በማንሳትም ትንታኔ ሰጥተዋል። ፅሁፎቹ፣ ምንም እንኳ ስለ ኢትዮጵያ ስልጣኔ በመጓጓት የእተፃፉ ቢሆንም በአመለካከታቸው ግን አወሮፓዊ የሆነ ነበር ሲሉም ይትቿቸዋል፦ “የስልጣኔ ሀሳባቸው አውሮፓዊ ስልጣኔን የተመለከት ነው። መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ የአውሮፓዊ ስልጣኔ ታላቅ እንደሆነ እና ኢትዮጵያም ይህንን ጎዳና ልትከትል እንደሚገባትት የሚሰብክ ነው።” (48) ጠለቅ ካለው የጋዜጦቹ ሃሳቦች ትታኔ ባሻገር እነዚህን የጋዜጣ ፅሁፊች ሲተነተኑ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች/ ጥቅሶች አነስተኛነት ሀሳባቸውን አንባቢ በሚገባ እንዳይረዳ እንቅፋት ሲሆኑ እንመለከታለን። የዚህን ምዕራፍ ጥናት በጊዜ ስንመለከተው እ.አ.አ. ከ 1900 እስከ 1957 (የአለ ስነ ጥበባት ትምህርት ቤት ምስረታ) ድረስ ይጓዛል። በዚህ ምዕራፍ ከዋና ዋና የሀሳብ ትንተናዎች ባሻገር የአለ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ምስረታ እና ሂደትም ተቃኝቷል።

1960ዎቹ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኪነ-ጥበባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና የተስተዋለባቸው ዓመታት ነበሩ። በነዚህ ዓመታት አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የታገሉበት፣ የራሳቸውን ባህል እና አመለካከት ለመፍጠር የተፈላሰፉበት፣ የኪነጥበብ ባለሞያዎችም ይህንን እንቅስቃሴ በመደገፍ እስከዛሬም ታላላቅ የሚባሉ ስራዎችን ያስተዋወቁበት ዓመታት ነበሩ። በመላው አፍሪካ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት የተስፋፋበት እና አንዱ ለአንዱ መኖርም በሰፊው የታየበት ነበር። ይህንን ሞቅ ያለ እንስቃሴም በሃገራችንም ተቀጣጥሎ ነበር። የዚህ መፅሀፍ ሁለተኛ ምዕራፍ በተለይ በነዚህ ዓመታት የኢትዮጵያ ስነ-ጥበብ እና ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ይህንን (በተለይ የሀገራችንን) እንቅስቃሴ እንዴት እንደተመለከቱት እና በራሳቸው መንገድ እንደተነተኑት ይመረምራል።

ገብረክርስቶስ ደስታ – ጎሎጎታ

የስነ-ጥበብ ስራዎቹን በወቅቱ ይታተሙ ከነበሩ የጋዜጦች እና መፅሄቶች ጽሑፎች ጋር በማያያዝ ሰፊ ትነተና የተሰጠበት ሲሆን በተለይ የወቅቱ ዝነኛ የነበረው መፅሄት አዲስ ሪፖርተር ጽሑፎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቷቸው እናገኛለን። የአዲስ አበባ እምብርት እና የወቅቱ የኪነጥበብ ባለሞያዎች መሰባሰበያ እና የፈጠራ መነሸጫ የነበረውን ውቤ በረሃን እንደ አንድ የስነ-ጥበብ እንቅስቃሴ መነሻ ቦታ በመቁጥር ትንታኔም ተሰጥቶበታል። ይህም በወቅቱ የተሰሩ ስነ- ጥበባዊ ስራዎችን ከሰፊው አጠቃላይ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁናቴ ጋር አዋህደን እንድንረዳው ያስችለናል። የዚህ መነሻም ፀሃፊዋ ማንኛውም ኪነ-ጥበባዊም ሆነ ስነ-ጥበባዊ ስራ ሲመረመር እና ሲተነተን ስራው በተሰራበት ዘመን የነበረውን ሰፊውን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊው ሁኔታ መጤን አለበት ከሚለው እምነታቸው በመነጨ እንደሆነ በተደጋጋሚ ያስረዳሉ። በርግጥ ይሄ እውነት አለው። የፈጠራ ስራዎች ከተፈጠሩበት ዓውድ ውጪ ለመተንተን እና ለመረዳት መሞከር ለቁንፅል አሊያም ላልተገባ ትርጓሜ የመጋለጥ ዕድልን ያሰፋል። በዚህም ሆነ በቀጣዮቹ ምዕራፎች በሰፊው የሚነሳው ነጥብ በተለይ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጋር በተያያዝ በየጊዜው የነበሩ ዋና ዋና የኪነጥበብ ሰዎች እና የጊዜው አሳቢያን በሰፊው ያልተነተኑት እና ያልተመረመሩት መሆኑን ነው።

 ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ነፃ በመሆኗ የጊዜው ጸሐፊዎች ይህንን ነጻነት ባልተገባ መንገድ ተረድተውታል የሚሉት ዶ/ር ኤልሳቤጥ የኢትዮጵያ የዘመናዊነትም ሆነ የስልጣኔ ታሪክ ከሰፊው የአፍሪካ የቅኝ ግዛት እና ለዚህም ከተደረገ ትግል ጋር መጠናት ይኖርበታል ሲሉ ይሞግታሉ። ቅኝ ግዛትን ከአካላዊ መገዛት ጋር ብቻ አያይዘው በተለይ በባህል እና በአስተሳስብ በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት (ኢትዮጵያንም ጨምሮ) ያሳደረውን ትፅእኖ (ዛሬም ድረስ) በጥንቃቄ ባለመመርመር ራሳቸውን እና ስራቸውን ላልተገባ ትርጓሜ አጋልጠዋል ሲሉ በማስረጃ ይተነትናሉ። በዚህም የአሁኑን እና ቀጣዩን የኪነጥበብ እና የማህበረሰብ አጥኚ እና ተመራማሪ ይህንን መልክ በሚገባ እንዲመለከተው እያሳሰቡ “በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ አርቲስቶች ተግባራት ለቅኝ ግዛት እና ከዚያም መለስ ላለው ድህረ ቅኝ ግዛት አስተሳስብ ጀርባውን የሰጠ ሆኗል።” ሲሉ ይደመድማሉ።

 ይህ ሃሳብ በሀገራችን በልዩ ልዩ ሞያዎች ላይ ጥናትን የሚያደርጉ፣ ተግባርን የሚከውኑ ባለሞያዎች የሚጋሩት ሃሳብ ይመስለኛል። በተለይ ኪነ ጥበባችን አብዛኛውን መልኩን ከአውሮፓ ቀድቶ በአደባባይ በሚታይበት ሁኔታ ላይ ሆነን ራሳችንን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባህላዊ እና ማህበራዊ እውነታ የተለየ መድረክ ላይ ማስቀመጣችን ጊዜ ሳይፈጅ በድጋሚ መፈተሽ የሚገባው ሃሳብ ነው። በርግጥ የዓድዋ ድል እንኳን ለኛ ለሰፊው የጥቁር ህዝብ የነጻነት እና የማንነት መገለጫ ድል ቢሆንም አድዋ ያመጣውን ነጻነት ግን ለማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የመጠቀም ሁኔታችን ግን ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። አንደኛችንን ለአውሮፓውያን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ባናድርም ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችን በተግባር በሚታይ መልኩ ተገንጥለን እንገኛለን። ይህንን ሁኔታ የስነ-ጥበብ እና የኪነ-ጥበበ ሰዎቻⶭን በጥልቀት ሊመረምሩት ይገባል።

 ቀጣዮቹ ሶስት ምዕራፎች በሶስት ዋና ዋና ታሪካዊ ወቅቶች በመክፈል የኢትዮጵያን ስነ- ጥበብ ለመተንተን ሞክረዋል። በምዕራፍ ሶስት “የ1960ዎቹ ዘመነኞች፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ እስኩንድር ቦጎስያን እና ተማሪዎቻቸው”፣ በምዕራፍ አራት “እናት ሀገር ወይም ሞት፡ ስነ-ጥበብ በደርግ” እንዲሁም በመጨረሻው አምስተኛ ምዕራፍ “ዘመነኛ የኢትዮጵያ ስነ- ጥበብ “ በሚሉ ሰፋፊ ምዕራፎች ለሀገራችን ስነ-ጥበብም ሆነ አካዳሚያዊ ንባብ የመጀመርያ  በሆነ ጥልቅ ትንታኔ በየዘመናቱ የተነሱ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ሰዓሊያንን ስራዎች ከሰፊው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ታሪኮች ጋር በማመሳከር ትንተና ተደርጎባቸዋል። በተለይ በሶስተኛው ምዕራፍ የዝነኛውን ሰዓሊ እስኩንድር ቦጎስያን የህይወት ታሪክ እና የስዕል ስራዎች ለመጀመርያ በሆነ ስፊ ትንታኔ ለአንባብያን ቀርቧል። ይሄን ማለቴ በተለይ የእስክንድ ዘመነኛ የሆነው የገብረ ክርስቶስ ደስታ ህይወት እና የሰዕል ስራዎች በሰፊው የሚታወቁ ከመሆናቸው አንፃር እስኩንድር በዚህ መፅሀፋ ያገኘው ሰፊ ሽፋን ይህንን የመረጃ ክፍተት የሚሞላ ይሆናል።

 በየጊዜው እንደ ሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ (በአፄ ሀይለ ስላሴ፣ ደርግ፣ ኢህአዴግ) ከሚፈጠሩ አዳዲስ እና ነባር ሰዓሊያን መሃል ዋና ዋናዎቹ በመምረጥ የስዕል ስራዎችን የሚተነትነው ይህ መጽሐፍ በተለይ ለመጀመርያ ጊዜ የሴት ሰዓሊያንን እና አሳብያንን ስራዎች በሰፊው የመረመረ ነው። ከ1960ዎቹ ዋነኛ የተማሪ ፖለቲካ አቀነቃኞች ጀምሮ እስከ እኛ ዘመን ወጣት ሰዓሊያን እና የኪነጥበብ ሰዎች ድረስ ዋና ዋናዎቹን በመምረጥ በሰፊው የኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ቦታቸውን ለማሳየት ተሞክሯል። የሴቶችን ሚና አጉልቶ ማሳየቱ ያልተዳሰሰውን ጥልቅ የኪነጥበብ ስራ መመርመሩ ብቻ ሳይሆን ፍርደ ገምድል የሆነውን የኢትዮጵያ የማህበረሰብ እና የኪነጥበብ ታሪክ የአፃፃፍ ይትባሃል የፈተነ ነው። የሴት ሰዓሊያን ስራዎች በመጽሐፉ መካተቱ የሰፊውን የኢትዮጵያን ታሪክ እንፅፋለን ብለው ለሚነሱ ጸሐፊዎች ትክክለኛውን ሚዛን በመያዝ ሁሉንም ተዋናዮች እኩል በመመለክት መፃፍ እንደሚገባ ማሳሳበያ እና ትምህርት የሚሰጥም ነው።

መጽሐፉ የኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ ታሪክ ትንታኔ ብቻ አይደለም። ሰፊውን የስነ-ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ እና ስነ-ግጥም በየቦታው በሰፊው ይቃኛል። የአንደኛውን ሰዓሊ ስራ በሚተነትነብት ጊዜ ተመሳሳዩን ርዕሰ ጉዳይ ሌሎች ከያንያን እንዴት እንደገለፁት በየቦታው በሚሰጡ ማስረጃዎች እንመለከታለን። መንግስቱ ለማ፣ አባተ መኩሪያ፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ እና ሌሎችም ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎች ሥራዎች በሰፊው ይተነተናሉ። የመጽሐፉም አንዱ ልዩ ባህርይ አንድን የጥበብ ስራ ለመተንተን የሚመለከታቸው ሌሎች ሰፊ ኪነጥበባዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች መኖራቸው ነው። ይህም የመጽሐፉን የትንታኔ ባህርይ ምሉዕ ያደርገዋል።

 የተመረጡ የስዕል ስራዎችን የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ በሆነ የስዕሎቹ ፎቶግራፍ ኮፒ አስረጅነት መቅረቡ አንባቢው ሰእሎቹን እየተመለከተ ተንታኔንውን እንዲያነብ እድል ይሰጣል። የህትመቱም ጥራት ለመጽሐፉ ተነባቢነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

 ጥልቅ ከሆነው ትንታኔ መልስ መጽሐፉ አንድ አንድ በየቦታው መልስ ያላገኙ ጥያቄዎችን ጥሎም ያልፋል። ለምሳሌ ፀሃፊዋ የዘመናዊ የኢትዮጵያ ስነ-ጥበብ ጀማሪ ብለው ከጠቀሷቸው ሰዎች መሀል በላቸው ይመርን እንደ ዋነኛ ባለሞያ በመውሰድ ትንታኔ አድርገዋል። ነግር ግን በላቸው ይመርን ለምን ከሌሎቹ ለይተው እንደመረጡ ምክንያታቸውን አያስቀምጡም። በተመሳሳይ በምዕራፍ ሶስት የ1960ዎቹን የለውጥ ሀዋርያቶችን ሲተነትኑ የለውጡ ቀዳሚ ጀማሪ ያሏቸውን ምሁራን (በተለይ ከሁለተኛው የጣልያን ወረራ በኋላ የመጡትን) ለምን ትንታኔአቸው ውስጥ እንዳላስገቧቸው ማብራርያ አይሰጡም።

የስነ ጥበብ ባለሞያዎቻችን ሀገራቸውን ከአፍሪካ የቅኝ ግዛትም ሆነ ድህረ ቅኝ ግዛት ታሪክ ጋር አዋህደው አለመመልከታቸውን ሲተቹ፣ ባለሞያዎቹ ሀገራቸውን በዚህ መነፅር ቢመለከቱ ግን ምን አይነት የኪነ ጥበብ ስራ ሊሰሩ እንደሚችሉ እንዲሁም ምን እንደሚያተርፉ ተንትነው አያስረዱም። ከዚህም አንፃር ሁሉም የስነ-ጥበብ ባለሞያዎች ተመሳሳይ የሆነ አቋማ ሊኖራቸው ይግባል ወይ? የሚል ጥያቄም እንድናነሳ የሚያስገድዱ ድምዳሜዎችንም እንመለከታለን። የመረጧቸውን ሰዓሊዎች ስራዎችንም (በርግጥ ካስቀመጡት የትወራዊ ንድፍ ሃሳብ አንጻር ቢሆንም!) ስንመለከት አንዳንድ በሀገራችን የስነ-ጥበብ ታሪክ ታላላቅ ስም ያላቸው ሰዓሊያን “ይገባቸዋል” ብለን ልናነሳ የምንችለውን ያህል ቦታ ሳይሰጣቸው እንመለከታለን- ለምሳሌ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ።

 ከዚህ መለስ፣ እጅም ጥልቅ በሆነ አካዳሚያዊ ትንታኔ፣ ባማረ እና ከፍተኛ ብቃት በሚታይበት የቋንቋ ፍሰት፣ ብዙ ባልታዩ እና አዳዲስ በሆኑ ማስረጃዎቹ እንዲሁም ልዩ ልዩ በሆኑ የስዕል ስራዎቹ መጽሐፉ ሰፊውን የኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ እና ኪነ-ጠበብ ታሪክ በሚገባ ተንተኖ አቅርቧል። ፀሃፊዋ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ እጀግ እንደደከሙበት የሚያስታውቅ ሲሆን ይህንን ምርምር በመፃፋቸው ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች፣ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ሁነኛ ውለታ ውለዋል ለማለት እደፍራለሁ። ሁሉም አግኝቶ እንዲያነበውም እመክራለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top