ፍልስፍና

ፍ ል ስ ፍና የኢትዮጵያ ፍልስፍና በሳምነር መነጽር

መነሻ

የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሲነሳ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ሰዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ፕሮፌሰር ክላውድ ሳምነር ነው ። ሳምነር በኢትዮጵያ በኖረባቸው ወደ ግማሽ ክፍለ ዘመን ከሚጠጉ ዓመታት እና በምድር ላይ በቆየባቸው 92 ዓመታት ውስጥ ምናልባትም ብዙውን ጊዜውን የፈጀው የኢትዮጵያን ፍልስፍና በማጥናት ላይ ነው። የአንድን ማኅበረሰብ የአስተሳሰብ ታሪክ እና ፍልስፍና መሰነድ እጅግ አድካሚና ትዕግስትን የሚጠይቅ ሥራ ነው። በተለይ ደግሞ ፍልስፍና ከሞላ ጎደል በሚወገዝበት፣ የተጻፉ የፍልስፍና ድርሳናት እንደ ልብ በማይገኙበት እና ባለብዝሃ ባህል በሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ወስጥ ሥራው እጅግ ውስብስብ እና ከባድ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ አብዝሃኛው የተጻፉ ቀደምት ድርሳናት በግዕዝ ወይም በአረብኛ የብራና መጻሕፍት ስለሚገኙ የማንኛውም ማኅበረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ባልሆኑት በነዚህ ቋንቋዎች የተጻፉ ድርሳናትን በቀላሉ መረዳት አይቻልም። የቋንቋዎቹ ባላቤቶች (ካህናቱ፣ ሊቃውንቱ፣ አሊሞች፣ ወይም መምህራኑ) ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ፤ የትርጉም ሥራዎችን ፍልስፍናዊ ይዘት ለመረዳት ወይም በዋናነት ሃይማኖታዊ ከሆኑ ድርሳናት ውስጥ ፍልስፍናን ፈልፍሎ ለማውጣት ቀላል አይሆንም። ሳምነር ይህንን ችግር ለመወጣት መጀመሪያ ግእዝን ማወቅ ነበረበት። በዚህም በቀጥታ ከግእዝ ወደ እንግሊዝኛ እየመለሰ፣ በነዚህም ላይ ማብራሪያ እየጨመረ አመስት የተጻፉ የኢትዮጵያ መጻህፍትን ለዓለም አስተዋውቋል። በእያንዳንዳቸው ላይ የጻፋቸው ትንታኔዎች ባለ 5 ቅጽ መጻህፍት ሲወጣቸው የትርጉም ሥራዎቹን (ፊሳልጎስ፣ አንጋረ ፈላስፋ፣ የእስክንድስ ሕይወትና መርሆዎች) እና Original የፍልስፍና መጻሕፍቱን (ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ፣ እና ሐተታ ወልደ ሕይወት) ባንድ ላይ ሰብስቦ እ.አ.አ በ1985 Classical Ethiopian Philosophy በሚል ርእስ አሳትሞታል።

የኢትዮጵያን ፍልስፍና በምልዓት ለመረዳት የተጻፈውን እና በቃል የሚተላለፈውን የማህበረሰቡን አስተሳሰብ በቅርበት መተንተን ያስፈልጋል፣ ነገር ግን “ለጥናት ምቾትና በዘዴም ቀላሉ ከተጻፈው መጀመሩ ጥሩ ነው” የሚለው ሳምነር በተጻፉት ላይ ብቻ ሳይወሰን “The Oromo Wisdom Literature” በሚል ባለ ሦስት ቅጽ መጻሕፍት ቃላዊ ጽሑፎች እና አባባሎች ላይ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ማግኘት እንደሚቻል ለማሳየት ጥረት አድርጓል። በዚህ ሙግቱም ፍልስፍና የተጻፈ ብቻ ሳይሆን በቃል የሚተላለፍም ጭምር ነው፤ ለማሰብ መጻፍ ቅድመ ሁኔታው ሊሆን አችልም፤ ሐሳብን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍም ጽሑፍ ብቸኛው መንገድ አይደለም የሚል የኢትዮጵያን ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ፍልስፍና ህልውና የሚገዳደረውን የአውሮፓውያንን መስፈርት ውድቅ ማድረግ ችሏል። ከቀደምት ተማሪዎቹ አንዱ ቴዎድሮስ ኪሮስ እንዲህ ይለናል::

 Recent philosophical thinking has changed this view [the view that philosophy proper is what is in a written form and the result of individual’s critical reflection]. African philosophers and non-African philosophers such as the late Claude Sumner who considered himself “Canadian by birth and Ethiopian by choice” – and many of his fellow students, of whom I am one, have originated a new narrative, in which it is argued that philosophy is not exclusively textual, but also significantly and creatively oral, and that the content of philosophy can be transmitted both in written and oral forms, and that the two forms are not mutually exclusive. African philosophical forms therefore are importantly oral and written (2015).

 የሳምነር በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ያለው አስተዋጽኦ ልክ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለውን ያክል ነው። ሳምነር በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ብቻ ሳይገደብ በአፍሪካ ፍልስፍና ላይም ትልቅ አሻራውን አስቀምጧል። ከላይ የጠቀስነው የቴዎድሮስን አባባል የፕረስበይ እና ማክሊን የጽሑፍ ያጠናክርልን::

 His collection Classical Ethiopian Philosophy (published by Adey in California in 1994, with a five volume set published by Commercial Printing Press in Addis Ababa), filled as it was with texts originally in Ge’ez, translated into English, debunked the stereotypes of Africa as a land without a history of written philosophical texts (p. viii).

በግጥም ለመሆኑ ይህንን የሚያደርገው ክላውድ ሳምነር ማን ነበር? ይህንን ለማድረግስ ያነሳሳው ምንድን ነው? የጥናቱ ውጤት ያስገኛቸው ትሩፋቶችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉ ጥያቆችን መነሻ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ፍልስፍና የምናደርገውን ጉዞ አሃዱ እንበል። ስለ ሳምነር ግድ የሚለን የኢትዮጵያ ፍልስፍና አንድ ቀዳም ተራምዶ እንዲገኝ ስላደረገ ነው።

በትውልድ ካናዳዊ፣ በምርጫ ኢትዮጵያዊ ነኝ” (ሳምነር)

 አንድ ሰው የሚወለድበትን ማኅበረሰብና ቦታ የመምረጥ እድል አልተሰጠውም። በዚህ ረገድ እስካሁን የተወለድሁበትን ቦታና ማኅበረሰብ፣ ዘመን እና ባህል መርጫለሁ የሚል አካል አልገጠመኝም። በሌላ በኩልም ስለሰው ከተደረጉ የሥነ ሕይወት፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና ወይም የሥነ ሰብ ጥናቶች የሰው ልጅ የሚወለድበትን ቀንና ሰዓት፣ ቦታና ሁኔታ መምረጥ ይችላል የሚል ሙግት አላየሁም። እንዲሁ ሰው በፈጣሪው ፈቃድ የተወረወረ ነው የሚለው ድምዳሜ ሁሉንም የሚያስማማ ይመስላል። በዚህ ረገድ ሰው የተወለደበት ዘር፣ ያደገበት ባህል፣ የኖረበት የትምህርት ወይም የባህል ጫና ወዘተ አስተሳሰቡን እንደሚወስነው፣ በኖረበት የማኅበረሰባዊ ቀረቤታ ወይም የደም ትስስት የፍቅር ስሜት ነዝሮት ራሱን የአንድ አካባቢ አፍቃሪና ተቆርቋሪ ሊያደርግ ግን ይችላል። በዚያው ልክ የታሪክ ትርክት ወይም ነባራዊ መስተጋብር እና ሁኔታዎች ገፋፍተውት “ለሌላ” ማኅበረሰብ ክፍል የጥላቻ ወይም የፍቅር ስሜቶች ሊያዳብር ይችላል። ይኸ ሁኔታ የሚነቀፍ ወይም የሚሞገስ ላይሆን ይችላል። ተገቢው ነገር ግን፣ አንድ የሰው ልጅ የቋንቋ፣ የባህል፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የመልክዓ ምድር ወዘተ ቅያዶችን፣ መሰናክሎችን እና ዘባተሎዎችን ሻገር ብሎ ማሰብ፣ ሰውን በሰውነት ክብሩ መረዳት፣ ከ“ሌላው” የማኅበረሰብ ክፍል እምነት፣ ባህልና እና የኑሮ ዘዴም የምማረው ነገር ይኖራል ብሎ የህሊናውን እና የልቡናውን በሮች በርግዶ በጥበብ እና በአእምሮ፣ በፍቅረ ሰብ እንዲበለጽግ ይመከራል።

 ካናዳዊው ፈላስፋ እና የሃይማኖት ሰው (በጥቅል ቋንቋ Humanist) ክላውድ ሳምነር ያደረገው ይኸንን ነው። እ.አ.አ ሐምሌ 10, 1919, በSaskatoon, Canada የተወለደው ሳምነር፣ በ92 ዓመት እድሜው እ.አ.አ በሰኔ 24፣ 2012 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከግማሽ በላይ የእድሜ ዘመኑን በኢትዮጵያ ያሳለፈው ሳምነር በ1950ዎቹ የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጥ ልቡ በፍቅር እንደተነደፈ ይነግረናል። አጋጣሚውን ልክ ከመጀመሪያ የዓይን ፍቅር ጋር ያመሳስለዋል። ቴዎድሮስ ኪሮስ የሳምነርን የትውስታ ቃላት ወደኛ አስተላልፎልናል::

There is such a phenomenon as love at first sight. I remember when I alighted from an Ethiopian Airlines plane on 15 September 1953 at 4.00 p.m. I immediately felt at home amongst the people I met and the bit of country I entered into: the cool weather, the green fields, the mountains, the exquisite politeness of the Ethiopian people.

 ፍቅር ወገን፣ ድንበር፣ የጊዜና የቦታ ገደብ የለውም ይባላልና ሳምነርም የነደፈው ፍቅር ምንም እንኳ በትውልድ ካናዳዊ ቢሆንም “በምርጫ ኢትዮጵያዊ” እንዲሆን አስገድዶታል። ሳምነር በ1960ዎቹ “የነገረ ሰው ፍልስፍና” (The Philosophy of Man) በሚል ርእስ ኋላ ላይ (1989 እ.አ.አ) በተከታታይ ሦስት ቅጽ የታተሙትን መጻህፍት በማዘጋጀት ላይ ነበር። እናም በዚያ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መጻህፍት ወመዘክር ጎራ ይላል። በዚያ ቅጽበት “መጸሐፈ ፈላስፋ/አንጋረ ፈላስፋ?” (The Book of the Philosophers) በሚል ርእስ በእንጨት የተለበደ (“hard cover”) የብራና መጽሐፍ ላይ ዓይኑ ያርፋል። በህዝቡ ትህትና፣ በአየሯ ጸባይ፣ በመስኳ ልምላሜ የተሳበውና የተደመመው ፈላስፋ አሁን ደግሞ በአፍሪካ ምድር ይገኝ ዘንድ ዘበት ነው ስለሚባለው የተጻፈ ፍልስፍና ድርሳን ፍንጭ የሚሰጥ ድርሳን ልቡን አስደነገጠው። “ሰውን በመፈለግ ላይ ነበርሁ፣ አፍሪካዊውን አገኘሁት!” በማለት ወደ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ጥናት የገባበትን አጋጣሚ “The Source of African Philosophy: The Ethiopian Philosophy of Man” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ አስነብቦናል።

 ማንም ሳያስገድደው በፈቃዱ ኢትዮጵያዊነትን መርጧል። ኢትዮጵያዊነትን ሲመርጥ ደግሞ በሙያው ህዝቧን ማገልገል ነበረበት። የJesus Societies አባል የነበረ ሲሆን ከኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር ለ30 ዓመታት ሰርቷል። እንዲሁም የሰንበት ህጻናትን ያስተምር እንደነበር ፕረስበይ እና ማክሊን ይነግሩናል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር በመሆን ያገለገለው ሳምነር ጎልቶ የሚታወቀው በኢትዮጵያ ፍልስፍና ዙሪያ ባሳተማቸው ትልልቅ ከደርዘን በላይ መጻሕፍቱ ነው። በርግጥም ለግማሽ በላይ እድሜውን (እንደ ምሁር ደግሞ ብዙ ሊሰራበት የሚችለውን የሙያውን የከፍታ ዘመናት) በኢትዮጵያ እንደማሳለፉ ይህንን ያክል ቢሰራ ላይደንቀን ይችላል። ነገር ግን ካለው የቋንቋ ገደብ እና ከአከናወነው ሥራ ክብደት አንጻር ካየነው አንድ ግለሰብ በእድሚው ሊያከናውነው ከሚችለው በላይ ነው ለማለት ያስደፍራል። ስለዚህ የሥራ ቁርጠኝነቱ ቴዎድሮስ ሲመሰክር Classical Ethiopian Philosophy የተሰኘውን መጽሐፉን በማስታወስ እንዲህ ይለናል: “This book is a rare example of an extraordinary synthetic power bearing the deep marks of scholarly seriousness, patience, hard work, honesty and respect for its subject matter.” የሳምነር ቁርጠኝነት እና ቀናነት ከየትም የመነጨ አይደለም። የሚሰራለትን ማኅበረሰብ ከመውደድ እንጅ።

ስለ ኢትዮጵያ የፍልስፍና ሐብታምነት ሲመሰክር ኢትዮጵያውያን በጽሑፎቻቸው እና በቃላዊ ይትበሃላቸው ውስጥ ጥልቅ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችን ማግኘት እንችላለን ብሎ በልበ ሙሉነት ይደመድማል። እንዲያውም በአፍሪካ ምድር ጥበብም ሆነ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ የለም ለሚሉት ሰዎች የማያወላዳ መልስ ከሰጡት ውስጥ ሳምነር ተጠቃሽ ነው። ይህንን ያደረገው ደግሞ አገሬ፣ ታሪኬ፣ ማንነቴ ኩራቴ በሚል የቃላት ኩፈሳ አይደለም። በተቃራኒውም የሌላውን በመዝለፍ ላይ አይደለም። ይልቁን በተግባር፣ ሰርቶ በማሳየት ነው። ስለ ሥራው ባንድ ወቅት ኮንፈረንስ ላይ “Modern Science and the Ethiopian Wisdom” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቦ ሲጨርስ “ይህ የአንተ ሥራ የEthnophilosophy አካል ነውን?” ተብሎ መጠየቁን በማስታወስ ማብራሪያውን በ Classical Ethiopian Philosophy መግቢያ ላይ ሲገልጽ እንዲህ ይላል። የEthnophilosophy በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ በእጅጉ ከተተቹ ጉዳዮች አንዱ ነው። ምክንያቱም ባህላዊ ክዋኔ እና ማኅበረሰባዊ የጋራ አስተሳሰብ ፍልስፍና ሊሆኑ አይችሉም፤ እንዲህ ዓይነቶቹ opinions እና pupular wisdom የፍልስፍና ይዘት የላቸውም የሚል ነው። የኔ ሥራ ግን ከዚህ ይለያል። እንደ የፍልስፍና ታሪክ ስነዳ አድርጌ ነው የምወስደው። ማንም ሰው ተነስቶ እውቀቱ ካለው ያንድን ፈላስፍፋ ሥራዎች በማሞገስም በመንቀፍም ታሪኩን ሊሰንድ ይችላል። እንዲሁም የአውሮፓን የፍልስፍና ታሪክ የጻፉ በርካቶች ናቸው። እኔም እያደረግሁ ያለሁት የኢትዮጵያን የፍልስፍና ታሪክ በማጥናት ለአድማጭ ማቅረብ ነው።

በርግጥ እዚህ ላይ ስለ ፍልስፍና ትርጓሜ መስማማት አለብን የሚለው ሳምነር ፍልስፍና ወይ በግለሰብ የምርምርና የተመስጦ ሥራ እጤት ናት አልያም በሰፊው ትርጓሜው በማኅበረሰባዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሊገለጥ ይችላል። እንደ የኢትዮጵያ ፍልስፍና አጥኝ እና ለኢትዮጵያ ፍልስፍና ቅርብ የሆነ ሰው እያደረግሁ ያለሁት በሁለቱም የፍልስፍና ትርጓሜ (በቀጥተኛውና በአንድምታዊው) መሠረት በኢትዮጵያ ያገኘሁትን የሐሳብ ታሪክ ለአንባቢ ማቅረብ ነው። ያንን አለማድረግ ደግሞ ባንድ በኩል አንድ ሊቅ ስላጋጠመው አስደማሚ እውቀት ለአድማጩ ያለማካፈል ንፉግነት ሲሆን በሌላ በኩል ራስን ኢትዮጵያውያን ካሳዩት የምክንያታዊነት መንገድ መከልከል ነው።

 On the basis of the enthusiastic reaction to the totality of the Ethiopian “philosophical” experience I believe it would be as unfair to deprive the modern audience from the richness of Ethiopia’s wisdom as it would be to limit oneself to the expression of Ethiopia’s original approach to rationalism (1985, p. 10).

 ለሩቅ ተመልካች እነዚህ መስመሮች በርግጥም የተጋነኑ ይመስላሉ። ባንድ በኩል በሥልጣኔ ወደ ኋላ የቀሩ ህዝቦች ይህንን ያክል የተጋነነ የፍልስፍና ውርስ አላቸው ወይ? በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሪጅናሌ የምክንያታዊነት መንገድ የተባለው እንደምን ያለ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭራሉ። ወደ ማብራሪያው ከማምራታችን በፊት የዶናልድ ሌቪንን ተመሳሳይ ምስክርነት መጥቀሱ አስፈላጊ ይሆናል። ሌቪን ኢትዮጵያ ላይ በጻፋቸው “ታላቋ ኢትዮጵያ” እና “ሰምና ወርቅ” በተሰኙ ሁለት መጻሕፍቱ የሚታወቅ ተመራማሪ ነው። እ.አ.አ በ 2006 “Powers of the Mind: The Reinvention of Liberal Learning in America” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፉ በዓለም ላይ ታላቅ ባህል እና ታናሽ ባህል (“Great Tradition” and a “Little Tradition”) የሚባል ነገር አለ። ታናሽ የሚባለው ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚያውቀውና በቃል የሚማረው ሲሆን በትምህርት ወይም በልዩ አጋጣሚ የተለዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች የሚያውቁት ደግሞ ታላቅ ባህል ነው። ይህ ታላቅ ባህል ካላቸው አምስት ስልጣኔዎች (ቻይና፣ ህንድ፣ አይሁድ፣ እስላማዊ እና የክርስትና ሥልጣኔዎች) ውስጥ ኢትዮጵያ አንዱን ይዛለች። ይኸውም የመጽሀፍ ቅዱስ እና ሌሎች ቅዱሳም መጻሕፍት እንዲሁም የቅኔ ባህል ነው። “in the Christian tradition, the Old and New Testaments and other sacred literature, with variants such as Ethiopian Orthodox Christian texts and an esoteric type of poetry” (ገጽ፣ 12)። የእነዚህ ታላላቅ ባህላዊ ቅርሶች ትልቁ ፋይዳቸው ሰውን ለምድራዊ ሕይወት ማመቻቸት ላይ ብቻ ሳይወሰኑ ወደ ሌላ ከፍ ያለ ልዕልና የሚያመሩ መሆናቸው ነው በማለት ያክልበታል። “Notable in all these traditions is a shift from using cultural forms solely for purposes of adjustment to natural and social worlds to ways of honoring them as guides to transcending worldly habits and thereby producing a higher, “civilized” type of humanity”.

እዚህ ላይ ነው የኢትዮጵያ ፍልስፍና ነገር ብቅ የሚለው። ሳምነር የደረሰበት ድምዳሜም ኢትዮጵያውያን በረጅም ዘመን የጽሑፍ ታሪካቸውና በሰምና ወርቅ ቅኔያቸው፣ በተረትና ምሳሌ፣ በታሪክ ነገራ፣ በግእዝ ቅኔ፣ ወዘተ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ አድማስ የሚያሰፋ፣ መኅበራዊና ተፈጥሯዊ ችግሮችን የሚፈታ፣ የተፈጥሮን ምስጢር፣ ጓዳ ጎድጓዳ ወዘተ የሚፈትሹበት የፍልስፍና ታሪክ አላቸው የሚል ነው።

ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሃንስም የዚህ ድምዳሜ ተጋሪ ናቸው። የከፍተኛ ትምህር ዘይቤ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 63 ላይ እንዲህ ይላሉ “በአፍሪካ ምስራቃዊ ዳርቻ የታወቀውን ሥልጣኔ ለማስገኘት ብዙ ሊቃውንት ጥረዋል። ሰማዩ ወይም ጠፈሩ ልሙጥ ነበር። የነዚህ ሰዎች ጥረት የሚያበሩ ከዋክብት በዚህ ጠፈር ላይ አስገኝቷል። ምን ይሆናል። ብዙ ደመና ሸፍኗቸዋል። እነሱን ለመረዳት ክንፍ [-] ብርቱ የሕሊና ክንፍ ያሻል። እንዳቅማችን እንሞክራለን። ስለዚህ መኅበረ ሊቃውንት በመላ ለመናገር በጠቀስነው ምክንያት አይቻልም። አብነት ወይም ምስለኔነት ያለውን እንመርጣለን። ይህም […] ያሬድ [-] ቅዱስ ያሬድ ነው። ቅዱስ ያሬድ በዘመናት መካከል ለነበሩት ሁሉ የሀገራችን ሊቃውንት እንደራሴነት ያለው ጥልቅ መንፈስ ነው ብለን እናምናለን።” ይህ የእጓለ አነጋገር አንድ ነገር ያስታውሰናል። ይኸውም ከህዝባዊ ጥበብ ባሻገር በየዘመኑ የዘመኑን መንፈስ የሚገልጡ ታላላቅ ሊቃውንት በምስራቃዊ የአፍሪካ ዳርቻ ሰማይ ስር እንደነበሩ። ያንን ደግሞ ብርቱ ጥረት፣ ጠንካራ ክንፍ፣ ትእግስትና የቋንቋና የባህልን ወሰን አጠር ሻገር ማለትን፣ ሰብአዊነትና ቀናነትን ይጠይቃል። ሳምነርም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያደረገው ይህንን ነው።

የሳምነር ፍለጋ በአንድ በኩል እነዚህን የዘመን ዋልታና ማገር፤ ዓምድና ግድግዳ ሆነው የኢትዮጵያን የሐሳብ ታሪክ ጉዞ ፊታውራሪ ሆነው የመሩትን የሐሳብ መሃንዲሶች ነው። በሌላ በኩል ረብ የለሽ በሚመስለው፣ የላይ የላይ ወይም ያልተመረመረ ጭፍን እምነት ተብሎ በተፈረጀው የማኅበረሰቡ የእለት ተዕለት መስተጋብር ውስጥ በሚንጸባረቀው የጋራ አስተሳሰብ ውስጥ መሠረትና ጣሪያ የሆነው ፈትለ ነገር ምን እንደሆነ በቃላዊና በጽሑፍ ድርሳናት ውስጥ ያለውን ድር መፈተሽ ነው። ለመሆኑ የፈላስፋው መነጽር ምን አግኝቶ ይሆን? በሚቀጥከው ጽሑፍ ዋና ዋና የፍልስፍና ድርሳናት አጭር ዳሰሳ እና በኢትዮጵያ ፍልስፍና ውስጥ ማዕከላዊውን ስፍራ የያዘውን ርእሰ ጉዳይ እናያለን። የወር ሰው ይበለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top