ጥበብ በታሪክ ገፅ

ደበበ እሸቱ፣ ስመ ገናና የቴያትር ባለሙያ

መድረኩን ይገዝፍበታል። አስገምጋሚ ድምጹ ከእዝነ ህሊና አይጠፋም። በየተሰለፈበት የቴያትር መስክ፣ በተዋናይነትም በአዘጋጅነትም የተሳካለት፣ ሥራዎቹ የተወደሱለት ነው – አበው ከያኒ ደበበ እሸቱ። በቴሌቪዥን ድራማዎችና በፊልም ሥራዎችም ላይ እንዲሁ። ሥራዎቹ በሃገር ውስጥ የተወሰኑ አይደለም። በተለያዩ የውጭ ፊልሞች ላይ ተጋብዞ ተጫውቷል፤ አቅሙንም በሚገባ አሳይቷል። በሙያ መምህርነትም በአርአያነትም አያሌ ተከታዮችን ያፈራ የጥበብ አባት ነው:: ዛሬ ድረስ ከወጣቶች ጋር በአንድ መድረክ እየተሰለፈ ችሎታና ልምዱን ያጋራል:: በርከት ያሉ የታሪክና የሥነጥበብ ሥራዎችን ወደአማርኛ ቋንቋ ተርጉሞም ለወገኖቹ አበርክቷል። እንግዲህ ዘርፈ ብዙ ከሆነው የከያኒው የጥበብ ሕይወት ውስጥ አለፍ አለፍ እያልን ለማነሳሳት እንሞክራለን።

መነሻ፣

 ሁሉም ነገር መነሻ አለው። የወጣት ደበበ የጥበብ ሕይወትም እንዲሁ። በተፈሪ መኮንን የተማሪነት ዘመኑ እነ ተስፋዬ ገሠሠና መኮንን ዶሪ “ስስታሙ መንጠቆ”ንና የመሳሰሉትን ቴያትሮች ሲሠሩ ተመልክቶ ደስ አለው። የደስታው ምንጭ ውጫዊም ውስጣዊም ነበር። እነሱን ሲያይ እሱን ራሱንም ነበርና ያየው። ስለዚህ ቴያትር የመሥራት ህልሙም፣ ውጥኑም ከዚያው ከተፈሪ መኮንን ጀመረ። ከዚያ ወዲያ እሱም ሆነ ወጋየሁ ከአጠገባቸው ለመራቅ አልፈለጉም:: መጋረጃ የመክፈትና መዝጋትን ሥራም በብቸኝነት ተቆጣጠሩት:: ቴያትሮች ሲሠሩም በነፃ ለማየት ቻሉ:: ስምንተኛ ክፍልን ሲጨርሱ ለቤተሰብ የመሰነባበቻ ዝግጅት የተወሰኑ ተማሪዎች መዝሙር እንዲያቀርቡ፣ ደበበና ወጋየሁ ደግሞ ቴያትር እንዲሠሩ ተነገራቸው::

በወቅቱ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎችን አይቀበልም ነበር:: ስለዚህም ደበበ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደመድረክ በወጣበት ቴያትር የተጫወተው የሴትን ሚና ነበር:: ለዚያውም ሙሽሪትን ሆኖ:: ዘጠነኛ ክፍልን ሲጨርሱ የአየር ኃይል መኮንኖች መጥተው “ሃገራችሁ ትፈልጋችኋለች፣ አብራሪዎች ሆናችሁ፣ ሃገራችሁን እንድታገለግሉ ትጋበዛላችሁ” የሚል ጥሪ ያቀርቡላቸዋል:: ወትሮውንም አለባበሳቸው ይማርከው ነበርና፣ በዚያ ላይ የትምህርት ውጤቱም ጥሩ ስለነበር ደስ ብሎት ሄደ:: እዚያም አንድ ቴያትር ላይ ተጫውቷል:: ሆኖም የአየር ኃይል ዲስፕሊን ከጠበቀው በላይ በጣም ጥብቅ ስለሆነበት ጥሎ ወጣና በደብረብርሃን የመምሕራን ማሰልጠኛ የሁለት ዓመት ሥልጠና ወስዶ መምህር ሆነ:: ከዚያ ወደኢሉባቦር ጎሬ ተልኮ ለአንድ ዓመት ካገለገለ በኋላ ማትሪክ ተፈተነና ወደቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አመራ:: እዚያ ሲደርስ የቀድሞ መምህሩን ጴጥሮስ ወልደማርያምን ያገኛል:: ታዲያ ትምህርቱን ለመቀጠልና ህግ ለማጥናት እንደሚፈልግ ሲያጫውታቸው፣

 “በጭራሽ አንተማ ቴያትር ነው መማር ያለብህ:: በሮክፌለር ፋውንዴሽን ድጋፍ የቴያትር ትምህርት ስለሚሰጥ እዚያ ነው መግባት ያለብህ” ይሉታል:: ደበበም ምክራቸውን ተቀብሎ ወደዩኒቨርሲቲው ኪነጥበባት ወቴያትር (ዛሬ”ተስፋዬ ገሠሠ የባህል ማዕከል”) ይሄዳል:: እዚያ ሲደርስ አንድ አጠር ያለ ሰው ያገኛል:: ፍላጎቱን ገለጸለት:: ሰውየውም በጥሞና አነጋገረው:: በመጨረሻ ፈተነውና አስገባው:: ያ ሰው በስተኋላ በተለይም በቴያትር አዘጋጅነት ታዋቂ የሆነው ከያኒ አባተ መኩሪያ ነበር:: ጋሽ ደበበ ቀሪውን እንዲህ ይነግረናል::

 “ይህን ታሪክ ምሳ ሰዓት ላይ ለወጋየሁ አጫወትኩት:: እሱም ደስ አለው:: አባተንም አነጋገረው:: ከዚያ አባተ ጠራኝና “ደበበ ና ጠዋት የፈተንኩህን ፈትነው” አለኝ:: ፈተንኩት:: “ምን ይመስልሃል?” ሲለኝ “በጣም ጎበዝ ነው” አልኩት:: በቃ እሱም ገባ:: እንግዲህ ጋሽ ፀጋዬንም እዚያው ነው ያገኘሁት:: መምህሮቻችንም እነ ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን፣ ሃሊም ኤልዳብ፣ መንግስቱ ለማ ነበሩ:: በስዕልም በኩል መሰረታዊ እውቀት ለማስጨበጥ፣ ጋሽ ገብረክርስቶስ ደስታ ሰዓሊዎችን ይዞ እየመጣ ሲሠራ እንመለከት ነበር:: ሲነሪ (የመድረክ ትዕይንት) እንዴት እንደሚሠራ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አናጢ እየመጣ ያስተምረን ነበር::”

በዚህ መልኩ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ቴያትር ተምረዋል:: ሆኖም ተማሪዎች እየለቀቁ ወይም ሥራ እየያዙ ሲሄዱ ከመጨረሳቸው በፊት የሮክፌለር ፋውንዴሽን ድጋፍ አለቀና ፕሮግራሙ ተቋረጠ:: ደበበና ወጋየሁ በጣም ተቸገሩ:: ስለዚህ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ካሳ ወ/ማርያም ዘንድ ቀረቡና ሁኔታውን አስረዱ:: ከዚያ በፊት ብዙ ቴያትር ላይ ሲጫወቱ አይተዋቸዋል:: ፕሬዚዳንቱም ወደትምህርት ሚኒስቴር እንዲሄዱ ይመክሯቸዋል:: ከተጠየቁ ምክንያቱን እንደሚያስረዱላቸውም ያሳውቋቸዋል:: በዚሁ መሠረት ደበበና ወጋየሁ ተያይዘው ወደትምህርት ሚኒስቴር ይሄዳሉ:: እዚያም የስኮላርሺፕ ክፍል ኃላፊ ለነበሩት አቶ በቀለ ገይድ የተባሉ ሰው አቤት ይላሉ:: ባለሥልጣኑ ምንም አይነት የትምህርት እድል፣ ለዚያውም በቴያትር፣ እንደማያገኙ ገለጹላቸው:: በራሳቸው ጥረት ካገኙ ግን እንደሚተባበሯቸው ነገሯቸው:: ስለዚህ በየኤምባሲው እየዞሩ ለመጠየቅ ወሰኑ:: በአጋጣሚ መጀመሪያ የሄዱት ወደ ሃንጋሪ ኤምባሲ ነበር:: ሃሳባቸውን ያጋሩት ሰውም የተስፋ ቃል ሰጣቸው::

 “ለእርሻ ትምህርት መጥተው ማንም ያልተጠቀመባቸው ሁለት እድሎች አሉ:: እሱን እድል እንድንሰጣችሁ የድጋፍ ደብዳቤ ካመጣችሁ ልንተባበራችሁ እንችላለን” ይላቸዋል:: ያንኑ ተስፋ ይዘው ቃል ወደገቡላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ሹም ይሄዳሉ:: ይሳካላቸዋል:: ከዚያ ለጫማ፣ ለካፖርትና ለሱፍ ልብስ መግዣ በተሰጣቸው ገንዘብ ቀድመው የአውሮፕላን ትኬታቸውን ቆረጡ:: በተረፈው ልብሳቸውን ገዛዙ፣ ከወዳጆቻቸው ጋርም የመሰነባበቻ ግብዣ አደረጉና ወደአውሮፓ አቀኑ:: በሃንጋሪ የቴያትር ታሪክም የመጀመሪያዎቹ ጥቁሮች ሆነው በመድረክ ላይ ተወኑ:: ከዚያ በፊት ነጮቹ በሜክአፕ ራሳቸውን እያጠቆሩ ነበር የሚሠሩት:: ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደሃገራቸው ሲመለሱ ግን የጠበቃቸው ነገር የሚያበረታታ አልነበረም:: ጋሽ ደበበ ሁኔታውን እንዲህ ያስታውሳል::

 “ከውጭ እንደተመለስን በቴያትር ቤቶች የመቀጠር እድል አላገኘንም። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ በሶሺያሊስት ሃገር ውስጥ መማራችን ነው። ወደቴያትር ቤቶች ቢሄዱ ሌሎች ባለሙያዎችን ሊመርዙ ይችላሉ የሚል ስጋት የነበረ ይመስለኛል። ለዘጠኝ ወራት ያህልም ሥራ አልነበረንም። ስለዚህ ከወጋየሁ ጋር ቁጭ ብለን ተነጋገርንና ሥራ ፈተን ከምንቀመጥ ለምን ጥበብን “ሀ” ብለን የጀመርንበትን የዩኒቨርሲቲውን ኪነጥበባት ወቴያትር ተከራይተን የራሳችንን ቴያትር አንሠራም? ተባባልን። ዩኒቨርሲቲውም ፈቀደልን። ያውም ያለክፍያ። በመጀመሪያ አንድ ሃሳብ ይዘን ያንን ኢምፕሮቫይዝ እያደረግን ለተማሪዎች ማሳየት ጀመርን። ከዚያ ማይም እናቀርባለን፣ ግጥሞች እናነባለን:: ተወደደልን። ቀጠልንበት:: ጉርምስናውም፣ ፍላጎቱም፣ አቅሙም ስለነበረን ደስ እያለን ሠራን:: እንደ አንድ የወር ደመወዝተኛ ራሳችን ችለን ለመኖር የሚያበቃ ገቢም እናገኝበት ጀመር::”

 ሁለቱ ወጣቶች በውጪ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር ለማዋል መንቀሳቀሳቸውን ቀጠሉ:: ውሎ አድሮም ታዋቂነትን እያገኙ መጡ:: ያም ሆኖ፣ ውጪ መማራቸው ስለትወና ጥበብ ብርሃን የፈነጠቀላቸው ቢሆንም እውነተኛውን የመድረክ ጥበብ የተማረው ደራሲ ፀጋዬ ገ/መድኅን “የበጋ ሌሊት ራዕይ”ን በብሔራዊ ቴያትር ሲያዘጋጅ ከታላላቆቹ ተዋንያን ከነአውላቸው ደጀኔ፣ ጌታቸው ደባልቄ፣ ተስፋዬ ሳህሉ፣ አስናቀች ወርቁ፣ አስካለ አመነሸዋና ጠለላ ከበደ ጋር በተጋባዥ ተዋናይነት አብሮ በሠራበት ጊዜ እንደነበር ጋሽ ደበበ ይናገራል:: መድረክ ላይ እንዴት መራመድ፣ እንዴት መናገር እንዳለባቸው፣ መድረክ ላይ ሲቆሙም እንደ አንድ ቤተሰብ መሥራት እንደሚኖርባቸው ከአንጋፋዎቹ ባለሙያዎች መማራቸውን ከአክብሮት ጋር ያስታውሳል:: ጋሽ ደበበ 48 ዓመታትን ባስቆጠረ የቴያትር ታሪኩ በበርካታ ቴያትሮች መሪ ገጸባሪያትን ተጫውቷል:: ከነዚህም መካከል ያላቻ ጋብቻ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ ፍልሚያ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የተሰኙትን መጥቀስ ይቻላል::

አበው ከያኒ ደበበ በፊልም ተዋናይነት፣

 በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ በአሥር ያህል ፊልሞች ላይ ሠርቷል:: የጆን ጊለርመን (John Guillermin) ፊልም በሆነው “ሻፍት በአፍሪካ” (“Shaft in Africa”, እ.አ.አ በ1973) ዋሳ የተሰኘውን ገጸባህሪይ ወክሏል። ዘነበች ታደሰ፣ ወጋየሁ ንጋቱና አልማዝ ደጀኔ (ዛሬ ባለቤቱ) በዚሁ ፊልም ላይ አብረውት ተውነዋል:: ሚሸል ፓፓታኪስ ባዘጋጀው ጉማ (1966 ዓ.ም) ፊልም በመሪነት ተጫውቷል:: ፊልሙ በተመረቀበት ወቅትም አጼ ኃይለሥላሴና ንጉሣውያን ቤተሰቦች እንደተገኙ የጽሑፍ ማስረጃዎች ያሳያሉ:: ጋሽ ደቤ በአልቤርቶ ካቫሎኔ (Alberto Cavallone) “አፍሪቃ” (“Afrika”, 1973) እና “ዜልዳ” (“Zelda”, 1974) ፊልሞች ላይም ሠርቷል:: በ1971 (እ.አ.አ) ደግሞ በኔሎ ሪሲ “A Season in Hell” (“አንድ ወቅት በገሃነም”) የተሰኘ ፊልም ላይ ተጫውቷል:: ፊልሙ ሐረር ውስጥ ይኖር በነበረው ፈረንሳዊ ገጣሚ አርተር ሪምቦ (Arthur Rimbaud) ሕይወትና ሞት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ጋሽ ደበበ እንደ አጼ ምኒልክ ሆኖ ተውኗል:: በቅርቡም በቤተ እሥራኤላዊው ባዚ ጌቴ “ቀያይ ቀምበጦች”፣ (“Red Leaves”, 2014) ምስጋናው ተድላ የተሰኘውን አቢይ ገጸባህርይ አሳምሮ የተጫወተ ተዋናይ ነው:: “ቀያይ ቀምበጦች” እና መሪ ተዋናዩ ጋሽ ደበበ ታላላቅ የሚባሉ ሽልማቶችን አሸንፈዋል:: በሃገር ውስጥም በተለያዩ ፊልሞችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ እየሠራ ልምዱን ለወጣቶች እያካፈለ ነው:: “ስውር ችሎት”፣ “ሰባ ሰላሳ”፣ “ትውልድ”፣ “ደርሶ መልስ”፣ “የልብ ጌጥ”፣ የተሰኙትን ሥራዎች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል::

 ሁለገቧን የመድረክ ባለሙያ ዓለምፀሃይ ወዳጆን “ስለ ጋሽ ደበበ ስታስቢ ቀድሞና ጎልቶ የሚታሰብሽ ምንድነው?” አልኳት:: እንዲህ አጫወተችኝ::

 “ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ናቸው:: በመጀመሪያ ሳውቀው በተዋናይነቱ ነው:: ስሙ የተጠራ፣ በጣም የተከበረ፣ በመድረክ ብትል በፊልም ሥራው የታወቀ ነው:: ከዚያ ብሔራዊ ቴያትር ስመጣ መምህሬ ሆነ::

ጋሼ እያልኩ ነበር የምጠራው:: የማክበርም የፍርሃትም ነገር ነበረበት:: ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባባን:: በግል ሕይወቴ ደግሞ በጣም የቀረበኝ ወንድሜ ነው:: የመጀመሪያ ባለቤቴን የታዴንና የኔን ሠርግ የሽርሽር ወጪ የሸፈነልን ደበበ ነው:: የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ ልጄን ከሆስፒታል ታቅፎ የወጣ እሱ ነው:: የመጀመሪያ መኪናዬን የገዛልኝ እሱው ነው:: የመጀመሪያ የአሜሪካ ጉዞዬን ያደረግኩት ከእሱ ጋር ነው:: አብረንም ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል:: በቃ ምንም ልንለያይ የማንችል ነን:: አሜሪካ ሲመጣም እኔ ጋ ነው የሚያርፈው:: በአጭሩ ደበበ ከትልቁም ከትንሹም ጋር ተግባብቶ የሚሠራ ባለሙያ ነው:: በዚያ ላይ በጣም ለጋስ ነው:: የደበበ እጅ ያልተዘረጋለት ሰው ቢኖር ጥቂት ነው::”

ጋሽ ደበበ ወደቴያትር አዘጋጅነት የገባው በችግር እንደሆነ ይናገራል። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲቲዩት የሚያዘጋጀው አንድ ኮንፈረንስ ነበር:: ያኔ ደራሲ መንግስቱ ለማ “ጠልፎ በኪሴ”ን ሥሩልኝ ሲሏቸው እሳቸው የሚያዘጋጁት መስሏቸው ነበር:: ከዚያ “ደበበ፣ አንተ አዘጋጀው” አሉት:: ከሃገር ፍቅርና ከብሔራዊ ቴያትር ታዋቂና በሳል ተዋንያንን አሰባሰበና የመጀመሪያ የአዘጋጅነት ሥራውን ተወጣ:: አቶ መንግስቱም “ጎበዝ! ደህና አድርገህ አዘጋጅተኸዋል” ብለው አበረታቱት:: በዚህም “ባለውለታዬ ናቸው” ይላል:: ከጠልፎ በኪሴ በኋላ “ኪንግ ሊር (ሊር ነጋሲ)”፣ “ተሃድሶ”፣ “የአዛውንቶች ክበብ”፣ “ዳንዴው ጨቡዴ”፣ “ጠያቂ”፣ “አይጦቹ” (እሱው የተረጎመው)፣ “ጎርፉ” (ራሱ የተረጎመው)፣ ወዘተ. የተሰኙትን ተውኔቶች አዘጋጅቷል:: ስለጋሽ ደበበ የአዘገጃጀት ስልት እንዲነግረኝ ፊት ተማሪው ለጥቆ የሙያ ባልደረባው የሆነውን አንጋፋ ከያኒ ተክሌ ደስታን ጠየቅኩት::

 “የአዘጋጅነት ሥራ የአስተዳደር ሥራ ማለት ነው:: ደበበ በዚህ የተካነ ነው:: ሰዎችን ሲመድብ ያለምንም ይሉኝታ ነው:: ማን የበለጠ ይሠራዋል ነው እንጂ ወዳጄ ምኔ ብሎ ነገር እሱ ዘንድ አይሠራም:: የሰዎችን ጥንካሬና ድክመት ያውቃል:: ሰዎች እንዲያምኑት፣ ሃሳቡን እንዲቀበሉት የማድረግ ኃይልም አለው:: በእሱ ቡድን መሪነት ቴያትር ይዘን ወደ ክፍለሃገር ስንወጣ ከፕሮግራሙ ንቅንቅ የለም:: ደበበ የይቅርታ ሰውም ነው:: ያጠፉትን፣ የበደሉትን ሰዎች ለሥራው ሲል ይቅርታ እየጠየቀ ይመልሳቸዋል:: በተስፋዬ ገሠሠ “ተሃድሶ” ቴያትር ላይ ሲመድበኝ እምቢ ብዬ ነበር:: ምክንያቱም እሱ እኔንና ገጸባህሪውን በተረዳበት መልክ አልተረዳሁትም ነበር:: እሱ ደግሞ “ትሠራዋለህ” ብሎ ሙጭጭ አለ:: ከዚያ ቀስ እያለ፣ በእኔ ውስጥ ሥራውን እየሠራ ነው እንድረዳው ያደረገኝ:: በመጨረሻ በተመኘው መንገድ እንድጫወተው አደረገኝ:: ሥራውም ተወዳጅ ሆነ:: እና ይኼ የደበበ የሥራና የትእግስት ውጤት ነው::”

 ዓለምፀሃይም የምትጨምረው አላት:: “ደበበ አንድን ተውኔት ሲያዘጋጅ አስቦበት፣ በደንብ ተዘጋጅቶበት ነው:: ከዚያ ጽሑፉን በታትኖ ነው የሚሠራው:: እንዳስፈላጊነቱ የፊቱን ወደኋላ የኋላውን ወደፊት ያደርገዋል:: ልክ እንደተክሌ ደስታ:: የአዛውንቶች ክበብን እንደምሣሌ ልጠቅስልህ እችላለሁ:: የጋሽ ተስፋዬ ገሠሠን ድርሰት “ተሃድሶ”ን ሲያዘጋጅ ተዋናይት ሆኜ ሠርቻለሁ:: የተዋንያንን ብቃትና አቅም እያየ ይመድባል:: በዝግጅቱ ሂደትም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል::”

 በዓለማቀፍ ደረጃ የአንድን ጥሩ ተዋናይ ብቃትና ጥንካሬ ያሳያሉ ተብለው የሚታመንባቸው መለኪያዎች አሉ:: እነዚህ መለኪያዎችም ቀጥለው ተዘርዝረዋል::

 1. የሚሰጠውን ሚና አሳምሮ በመጫወት የተመልካቹን ስሜት እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመቆጣጠር የሚችል፣

2. በሙያው ጣራ/ከፍታ ለመድረስ ቆርጦ የሚነሳ፣ በሂደት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጣጥሶ ለማለፍ ሳይታክት የሚሠራ፣

3. በሥራው የሚተማመን፣ ያን መተማመንም በትወናውም ሆነ በግል ኑሮው ማሳየት የሚችል፣

4. የሰዎችን ተፈጥሯዊ ባህርይ በቅጡ የሚገነዘብና ለድርጊቶቻቸው መንስኤ የሚሆኑ ስሜቶቻቸውን በሚገባ ማሳየት የሚችል፣

5. እውቀቱን በማያቋርጥ ንባብ እያሳደገ የሚወክላቸውን ገጸባህሪያት ለመተርጎምና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለመጫወት የሚችል፣

6. በመድረክ ላይ እንቅስቃሴዎች የተካነና የተለያዬ ተፈጥሮና ምግባር/ጠባይ ያላቸውን ገጸባህሪያት በሚገባ ለመጫወት የሚችል፣

7. ለትወናና ሰዎችን ለማዝናናት የሚያስችል የተፈጥሮ ስጦታ ያለው፣

8. የትወና ጥበባትን ከመንፈሱ ጋር ያዋሃደና በሚጫወታቸው ገጸባህርያት ላይ ሕይወት ለመዝራት የሚችል፣

9. ተግባቢ የሆነ፤ ተመልካቾችን፣ አብረውት የሚሠሩ ተዋንያንን፣ አዘጋጆችን፣ ደራስያንን፣ በተለይም የመድረክ ባለሙያዎችን የሚያከብር፣ ለሙያው ልዩ ፍቅር ያለውና ተባብሮ ለመሥራት የሚችል፣

10. ድምጹ፣ በተለይ ለመድረክ ተዋንያን፣ በመጨረሻው ረድፍ ለተቀመጠ ተመልካችም ጭምር የሚሰማ፣ መድረክ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮም ተመልካቹን በንቃትና በሙሉ ስሜት ለማዝናናት የሚችል፣

11. ከልምምድም ሆነ ከትርኢት ሰዓት ቀድሞ የሚገኝና የሥነምግባር አርአያ የሚሆን፣ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ያለምንም መደናገጥ በቅጽበታዊ ፈጠራ (Improvization) ለመሸፈን የሚችል፣

 አበው ከያኒ ደበበ እሸቱ በነዚህ መለኪያዎች ሲመዘን ሁሉንም በብቃት እንደሚያሟላ ያነጋገርኳቸው ባለሙያዎች ሁሉ ይስማማሉ:: ለጋስነቱን፣ ትጋቱን፣ ደፋርነቱን፣ አስፈላጊም ሲሆን ኮስታራነቱን፣ እና ቃሉን የሚጠብቅ ሰው መሆኑንም አብረውት የሠሩ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ:: ገራፊው ገብረየስ (እናት ዓለም ጠኑ)፣ ሻይሎክ (የቬኒሱ ነጋዴ)፣ ናትናኤል (ናትናኤል ጠቢቡ) የተሰኙት ገጸባህሪያት ጋሽ ደቤ የትወና ጫፍ ላይ የደረሰባቸው መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ:: ሌሎችንም እንዲሁ መጥቀስ ይቻላል:: አበው ከያኒ ተክሌ ደስታ ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል::

“ደበበ አንድ ትልቅ ምሰሶ ነው:: በየትኛውም ቴያትር ቢሆን ገኖ መውጣት የሚችል ታላቅ ባለሙያ ነው:: በጥሶ ነው የሚወጣው:: ምን ልበልህ እሱ ያለባቸው ቴያትሮች ብድግ ነው የሚሉት:: ገራፊው ገብረየስን ሲጫወት አንድ አይኑ የጠፋ ገራፊ፣ አስፈሪ፣ ገዳይ ሆኖ ነው:: እርግጥ ነው ገንኖ የወጣበት ትልቅ ሥራው ነው:: ሆኖም ብዙ እኒህን መሰል ሥራዎች አሉት:: በእኔ እምነት “እናት ዓለም ጠኑ” ላይ እሱ ገራፊው ገብረየስን ሲጫወት ሌሎቹን ገጸባህርያት ለምሳሌ ነዳዩ ባዬን (ተስፋዬ ሳህሉ)፣ ጅሉ ሞሮን (ወጋየሁ ንጋቱ)፣ አጼ ኃይለሥላሴን (ሲራክ ታደሰ) ዳምበልን (ሐይማኖት ዓለሙ) በላይ ዘለቀን (ታደሰ ወርቁ) እና ባለቤቱን (አስናቀች ወርቁ)፣ እና ሌሎቹንም የወከሉት ተዋንያን በሙያቸው አንቱ የተባሉ ስለነበሩና ቴያትሩ ልዩ ትኩረት ስለሳበ ነው:: የነዚህ ታላላቅ ተዋንያን በአጠገቡ መኖር በራሱም ደበበን የበለጠ እንዲጫወት እንደሚያደርገው ሳይዘነጋ:: ሻይሎክንም ብንወስድ ከታሪኩ፣ ከገጸባህሪው ተፈጥሮና ከደበበ ችሎታ ባሻገር እንደ ዓለምፀሃይ ወዳጆና አበበ አዲስ ያሉ ምርጥ ተዋንያን አብረውት መሰለፋቸው እሱን የበለጠ ያጫውተዋል::”

 ቫንኮቨር ካናዳ በተዘጋጀ ዓለማቀፍ የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል ላይ “ቀያይ ቀንበጦች” ተካፋይ ሆኖ ነበር:: የዓመቱን የምርጥ መሪ ተዋናይነት ዘርፍ ሽልማትም (“ጎልደን ሊዎፖልድ አዋርድ”) ጋሽ ደበበ አሸንፏል:: የመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት በአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ሊቀመንበርነቱ፣ አፍሪካውያን የራሳቸው ቴያትር ቤት እንዲኖራቸው ላደረገው ጥረት የ”ማላካይድ ስቶን” የሚባል የክብር ድንጋይ በማስታወሻነት ሰጥተውታል:: በቴያትር መስክ ላደረገው አገልግሎት ከጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል “የሕይወት ዘመን ሽልማት” ተቀብሏል:: ኢትዮ የፊልም ማዕከልም የ”ጉማ አዋርድ”ን ሸልሞታል:: በአሜሪካዋ የአትላንታ ከተማም በከንቲባው ውሳኔ ኖቬምበር 24 ቀን “የደበበ ቀን” ተብሎ እንዲከበር በ2004 ተወስኗል::

 አበው ከያኒ ደበበ ከፍ ብለን እንደገለጽነው እጁ የገቡና ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን የትወራ፣ የጥበብና የታሪክ ሥራዎች ወደአማርኛ ቋንቋ እየመለሰ ለወገኖቹ ያደርሳል:: “An Actor Prepares” የተሰኘውንና በታዋቂው ሩሲያዊ የቴያትር አዘጋጅ ኮንስታንቲን ስታንስላቭስኪ የተጻፈውን “የተዋናይ ሀሁ” ብሎ ተርጉሞት የባህል ሚኒስቴር አሳትሞታል:: መጽሐፉም ለብዙ ወጣትና ነባር ባለሙያዎች በማስተማሪያነት አገልግሏል:: በሃገራችን በሠፈራ ምክንያት የተፈጠረውን የቤተሰብ መለያየት ያሳይልኛል ብሎ ያሰበውን የቻይናዊውን የሳዎ ዩ ተውኔት “ድብልቅልቅ” ብሎ ወደአማርኛ መለሰውና በመድረክ ለሕዝብ ቀረበ:: ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “Red Tears” ብሎ የጻፈውንና በደርግ የአገዛዝ ዘመን የተፈጸሙ ግፎችንና የአስተዳደር በደሎችን የሚያሳይ መጽሐፍ “የደም እንባ” ብሎ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ታትሞለታል:: ባሮን ሮማን ፕሮቻስካ “Abyssinia: The Powder Barrel” በሚል ርዕስ ጽፎ ያሳተመውን “ኢትዮጵያ፣ የባሩድ በርሜል” ብሎ ተርጉሞታል:: ለመጀመሪያ ጊዜ በፖለቲካው መድረክ ብቅ ያለበትንና ለሁለት ዓመት ያህል ለእሥር የተዳረገበትን አጋጣሚም “የእምነቴ ፈተና” ብሎ ጽፎ አሳትሞታል::

የአንድ ተዋናይ ታላቅነት የሚለካባቸው መመዘኛዎች

የሚሰጠውን ሚና አሳምሮ በመጫወት የተመልካቹን ስሜት እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመቆጣጠር የሚችል፣

በሙያው ጣራ/ከፍታ ለመድረስ ቆርጦ የሚነሳ፣ በሂደት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጣጥሶ ለማለፍ ሳይታክት የሚሠራ፣

በሥራው የሚተማመን፣ ያን መተማመንም በትወናውም ሆነ በግል ኑሮው ማሳየት የሚችል፣

የሰዎችን ተፈጥሯዊ ባህርይ በቅጡ የሚገነዘብና ለድርጊቶቻቸው መንስኤ የሚሆኑ ስሜቶቻቸውን በሚገባ ማሳየት የሚችል፣

እውቀቱን በማያቋርጥ ንባብ እያሳደገ የሚወክላቸውን ገጸባህሪያት ለመተርጎምና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለመጫወት የሚችል፣

በመድረክ ላይ እንቅስቃሴዎች የተካነና የተለያዬ ተፈጥሮና ምግባር/ጠባይ ያላቸውን ገጸባህሪያት በሚገባ ለመጫወት የሚችል፣

ለትወናና ሰዎችን ለማዝናናት የሚያስችል የተፈጥሮ ስጦታ ያለው፣

የትወና ጥበባትን ከመንፈሱ ጋር ያዋሃደና በሚጫወታቸው ገጸባህርያት ላይ ሕይወት ለመዝራት የሚችል፣

ድምጹ፣ በተለይ ለመድረክ ተዋንያን፣ በመጨረሻው ረድፍ ለተቀመጠ ተመልካችም ጭምር የሚሰማ፣ መድረክ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮም ተመልካቹን በንቃትና በሙሉ ስሜት ለማዝናናት የሚችል፣

ተግባቢ የሆነ፤ ተመልካቾችን፣ አብረውት የሚሠሩ ተዋንያንን፣ አዘጋጆችን፣ ደራስያንን፣ በተለይም የመድረክ ባለሙያዎችን የሚያከብር፣ ለሙያው ልዩ ፍቅር ያለውና ተባብሮ ለመሥራት የሚችል፣

ከልምምድም ሆነ ከትርኢት ሰዓት ቀድሞ የሚገኝና የሥነምግባር አርአያ የሚሆን፣ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ሳይደናገጥ በቅጽበታዊ ፈጠራ (Improvization) ለመሸፈን የሚችል፣

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top