የጉዞ ማስታወሻ

የፊያሜታ ልጅ

መተማ እንደ ቆላማ የአየር ንብረቷ የነዋሪዎቿ ማህበራዊ ህይወትም የሞቀ ነው። የተጋጋለ። የሱዳናውያንና ኢትዮጵያውያን የእለት ተእለት አብሮነት የሰሀራ በረሃ ጐረቤት የሆነችው መተማ መለያ ነው። ኢትዮጵያውያን የአሜራ ወንዝን በአንድ እርምጃ ተሻግረው የሚያስጐመጀውን የሱዳኖችን የሰርክ ምግብ “ፉል” መመገባቸው የተለመደ ነው። ሱዳኖቹም ከሸሪያ ህግ ነፃ ወደሆነችው መተማ ዮሐንስ ጐራ ብለው በካቲካላ አረቄ ተነቃቅተው ይመለሳሉ ይባላል፤ ሆኖም ይህ ግን ምስጢር ነው።

ለወበቃማው አየር የሚመረጠውን ጀለብያ ለብሰው በድንኳኖቻቸው የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚቸረችሩ ሱዳናውያን ኑሯቸውን በነፃነት ነው የሚመሩት። የሱቆቻቸው መጉደልና መሙላት ካልሆነ ሌላ ነገር ትኩረታቸውን የሚስበው አይመስልም። እርስ በርስ በአረብኛ ተረቶቻቸውና ቀልዶቻቸው መዝናናት ደግሞ የአብሮነታቸው ገመድ ሳይሆን አይቀርም። ሰላምታም በዚህ አካባቢ ስንቅ ነው። “አሰላም አለይኩም” በጋራ “አሊኩም ሰላም” ለሰላምታው ምላሽ ይሰጣሉ።

 ገላባት ፀሀይ ወጥታ እስክትገባ እንደ ፀሀይ ደማቅ ናት። ከፀሀይ ግባት በኋላ ግን ጽሞና ትይዛለች። በምሽት በፀጥታ ትዋጣለች። ገላባት የሱዳን ግዛት ትሁን እንጂ በተለይ ሜድትራኒያን ባህርን አቋርጠው አውሮፓ ለመድረስ ተስፋ ለሚያደርጉ አብዛኞቹ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች መዳረሻ ናት።

 በሥራ ምክንያት እግር ጥሎኝ መተማ ዮሐንስ በነበርኩበት አጋጣሚ ነበር ወደ ገላባት ጐራ ያልኩት። ከወጣቷ አስምረት ጋር የተዋወቅንበት ጊዜ ይኸው ነው። አስምረት ከወበቃማው አየር ጋር ለመስማማት ሰፊ ደማቅ ቀይ ድሪያ ለብሳለች። የበረሃው አየር ቢያጠወልጋትም ውብ የሆነው ዓይኗ ብቻውን ቁንጅናዋን ይመሰክራል። እንደ እርሷ ዓይነት ረዥም ቁመና የታደሉ መለሎ ወጣቶች ድሪያ ያምርባቸዋል። ፈገግታ የተሰጣት ሳይሆን አይቀርም። በአስቸጋሪ የስደት ኑሮ ውስጥ ሆና እንኳ ማራኪው ፈገግታዋ አልተለያትም።

 ከአስምረት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነው ገላባት ነው። ከበርካታ ውብ ወጣት ሴት ስደተኞች ጋር የማውራት አጋጣሚ ነበረኝ። ሴት ስደተኞች ከወንዶች ይልቅ ስለ አውሬው ስደት መተረክ ይችላሉ። አስምረት ኤርትራን ከለቀቀች ስድስት ወር ሆኗታል። የሰሃራ በረሃ ስደተኛ አጓጓዞች አስተጓጉለዋት ላለፉት ስድስት ወራት የስደተኛን መራር ኑሮ እየገፋች ነው። ቢሆንም ማራኪ ፈገግታዋ አልተለያትም፤ አስምረት ተግባቢ ናት። አጥማጅ ውብ ዓይኖቿ፣ ንቁ ወጣትነቷ ከማንም ጋር ያግባባታል።

 አማርኛንና ትግርኛን ደበላልቃ ነው የምትናገረው። በአማርኛው ትግርኛ ጣልቃ ይገባል። ቢሆንም መግባባት ችለናል። ስላጉላሏት ህገ ወጥ የስደተኛ አጓጓዦች እንድትነግረኝ ብገፋፋትም ምንም ፍንጭ ልትነግረኝ አልፈለገችም። በእርግጥም ስለ እነርሱ እንዲሁ ማውራት አደገኛ ነው። አስምረት በአያት ያደገች ቅምጥል ናት። የዛሬን አያድርገውና አያቷ አቅብጠው አቅልጠው ነው ያሳደጓት።

“ባለፈው መጋቢት ሰላሳ ሰባት ዓመት ሆነኝ። ከአያቴ ጋር ነው ያደግኩት። አያቴ አደይ ስላስ ትባላለች። ከሳዋ የውትድርና ስልጠና በኋላ የምወዳትን አያቴንም ትንሿን ሮማን አስመራንም ሳልወድ ተለየኋቸው። እናቴ ጥላኝ ስለሞተች አያቴ እየተረከችልኝ ነው ያደግኩት። እናቴ በአንድ ወቅት አስመራን በአንድ እግሯ ያስቆመች ቆንጆ ወጣት ነበረች። ፊያሜታ ጊላይ ትባላለች። በወጣትነቷ የተቀጨችው እናቴ ታሪክ በእኔ ላይ እንዳይደገም ይመስላል ስለ እናቴ በዝርዝር ነበር የምትተርክልኝ”

“ምን ዓይነት ታሪክ ነው እናትሽን ለማስቀጨት የደረሰ?” የማውቀውን ስም ስለጠራችልኝ ለታሪኩ ጓጓሁ።

 “ልነግርህ እኮ ነው” በመቸኮሌ የሰጠችኝ መልስ ነው። በድርጊቴ እንደማፈር ብዬ፣

 “ይቅርታ!” በማለት ትህትና አሳየኋት።

 “የእናቴ የፊያሜታና የሞቷ ምክንያት እንደሆነ የሚነገረው የጋዜጠኛው ፀጋዬ ታሪክ ምንጊዜም ከውስጤ አለ” አለች በትካዜ።

 በእርግጥም ይህ ታሪክ ከአስምረት ልብ ውስጥ እንደ ድንጋይ ላይ ጽሑፍ የተቀረፀ ይመስላል። አስምረት እየተነገራት ያደገችበትን የእናቷን የወጣትነት ታሪክ ከእርሷ ዘመን ጋር ስታነፃፅረው ይመስላል የምትተክዘው።

 “እናቴ የወጣትነት ትኩሳት ጠብሶ እስኪለበልባት ወጣትነትን እንደ ጀብድ ትቆጥር ነበር። በጊዜዋ ከአስመራ ቆነጃጅት በላይ ነበረች። በአስመራ ከተማ የአስረሽ ምችው ታሪክ ገፀ ባህሪያት ሆናም ትጠቀሳለች። ፊያሜታ ‘ሰሜናዊቷ ጽብቅቲ’ የምትሰኘውም ለዚህ ነበረ። የዱባይና የሚላን የከበሩ ሽቱ ብልቃጦች አሁን ድረስ ከቤታችን እንደቅርስ ተደርድረዋል። እርሷ ያላጌጠችበት የዘመኑ ጌጥ አልነበረም ማለት ይቻላል። የአፍላ ጊዜ ፎቶግራፎቿም ልብ ብዬ የማላውቃትን የእናቴን ዘናጭነት የሚያሳዩ ናቸው።

 “እናቴ በአንድ ጋዜጠኛ ፍቅር ከንፋ ነበር ነው ያልሽኝ?”

 “አዎ ጸጋዬ ይባላል።” አለች በአትኩሮት እየተመለከተችኝ። “እየነገርሁህ እኮ ነው!”

 “በጣም ይቅርታ ታሪክሽ እኮ ስለመሰጠኝ ነው! አትፍረጅብኝ”

 “ፊያማታ ከአንድ መሃል አገር ከመጣ ጋዜጠኛ ጋር ያሰለፈችው ፍቅር አሁን ድረስ በድፍን አስመራ ይወራል። ፀጋዬ ይባላል። ድብን ያለ ፍቅር ይዟት እንደናወዘች። እስከ መቃብር ለፍቅሩ ታማኝ መሆኗን ሁሉ አያቴ ነግራኛለች። የእናቴ ለፍቅር ታማኝ ሆኖ ራስን መሰዋት ያስገርመኛል”

አስምረት እናቷን እንደ ፍቅር ጣኦት ነው የምትቆጥራት። ስለ እናቷ በኩራት ነው የምትናገረው። ከውቧ ወጣት አስምረት ጋር በሶስተኛው ቀን ማለዳ ቁርሳችንን “ፉል” አብረን ከበላን በኋላ በቅመም ያበደ ሻይ እየጠጣን አውርተናል። ናላ የሚያዞረው የመተማ የበጋ የፀሀይ ቃጠሎ ለሚያስከትለው ውሃ ጥማት የመተማ ሻይ ተመራጭ ነው። ሻይ ሌላ ቦታ እንዲህ አልደጋግምም። አስምረትም እንደ እኔ ሻይ ደገመች።

የድንበር ከተማዋ የመተማ ዮሐንስ ከአቅም በላይ ብዙ ሰው ይኖርባታል። አብዛኞቹ

“እንደ ሰሜናዊቷ ጽብቅቲ አስምረት ሁሉ በረዥሙ ፒጃማ ከሙቀቱ ረፍት ያገኙ የሚመስሉት ቆነጃጅት እጅግ ብዙ ናቸው። ፒጃማና ድሪያን የለበሱ ሴቶች ከዚህም ከዚያም ይታያሉ”

ደግሞ እንደ አስምረት ዓይን አልፎ ሂያጅ ስደተኞች ናቸው። ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወጣት ቆነጃጅት ስደተኞች በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ከተጓዙ በኋላ ሜድትራኒያንን በጀልባ ተሻግረው አውሮፓ ይገባሉ። በግብጽ በኩል ደግሞ በጋዛ ሰርጥ ወደ እስራኤል ለሚያደርጉት የሞት ሽረት ጉዞ የሚዘገጃጁት ከዚሁ መሆኑን ሰምቻለሁ።

እንደ ሰሜናዊቷ ጽብቅቲ አስምረት ሁሉ በረዥሙ ፒጃማ ከሙቀቱ ረፍት ያገኙ የሚመስሉት ቆነጃጅት እጅግ ብዙ ናቸው። ፒጃማና ድሪያን የለበሱ ሴቶች ከዚህም ከዚያም ይታያሉ።

“የበዓሉ ግርማዋ ፊያሜታ ጊላይ ልጅ ነኝ እያልሽኝ እኮ ነው!” መደነቄን መደበቅ አልቻልሁም።

“ካላመንህ ድፍን አስመራን ጠይቅ!”

አስምረት በእርግጥም ውብ ዓይኖች አሏት፣ ቆንጆ ናት። “ሰሜናዊት ጽብቅቲ”። ደራሲው “የቀይ ባህር ርግብ” ብሎ እንደሰየማት የማትረሳ ገፀ ባህሪ። “ይህች ውብ ጠይም ሰሜናዊ አበባ ከፊያሜታ አብራክ ነው የተገኘችው?” ራሴን ጠየቅኩ። በእርግጥም ፈገግታዋ እንደ እናቷ ሁሉ እንደጠፍ ጨረቃ ይማርካል።

 አስምረት የፊያሜታ ልጅ ስደትን ተስፋ ካደረጉ በርካታ ኤርትራዊያን ወጣቶች መካከል አንዷናት። አባቷ ስእላይ በርሄ ይባላል። እናትና አባቷ በአፍላ ፍቅር ውስጥ እያሉ ድንገት እንደተወለደች ታውቃለች። ከሁሉም ይልቅ የወላጅ እናቷ የሕይወት መጨረሻ የሆነው የጋዜጠኛው የፀጋዬ እና የእናቷ የፊያሜታ የፍቅር ታሪክ እየተተረከላት ነው ያደገችው። የእናቷ አስደናቂና ለፍቅር መስዋዕት የመሆን መጨረሻን ድፍን የማይተመናይ ሰፈር ሰዎች ሁሉ በአድናቆት እየተረኩላት አድጋለች።

 የቁንጅና ውድድር መድረኮች ላይ የምናያቸውን ውብ ቆነጃጅት የምትተካው አስምረት ከጓደኞቿ ጋር ሜድትራኒያን ተሻግረው አውሮፓ ለመድረስ ተስፋ ሰንቃለች። ስለጉዞው መስመር በቂ መረጃ ነበራት። የሚያርፉባቸውን መዳረሻዎች እርሷም ሆነች ጓደኞቿ በቃላቸው አጥንተዋቸዋል። በችግር ካልተበገረው ውብ ገጽታዋ ሌላ፤ አስተሳሰቧ በህይወትና ኑሮ ተፈትኖ እንዳለፈ ጐልማሳ ነው። ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲሰደድ እንደኖረው ትውልድ እርሷም ስደት መፍትሔ እንደሆነ ታምናለች። ፊት ለፊት ለሚጠብቃት ለአደገኛው የሰሃራ በረሃ ጉዞ መጥፎ ዜና ጆሮ የምትሰጥ አይመስልም። የአስምረት ልብ የቆንጆ ልብ አይመስልም።

“አንች ከተሰደድሽ አሳዳጊ አያትሽን ማን ሊጦራቸው ነው?” አልኳት። አስምረት ለማሰብ በሚመስል ሁኔታ ትካዜ ከተላበሰ ዝምታ በኋላ ቀጠለች።

 “አያቴ አደይ ስላስ ለመከራ የተፈጠረች ሰው ናት። ዕድሜዋ ከ80 አልፏል። በእሳት እንደተለበለበ እንጨት ቁጠራት። ሁለት ልጆቿ በሰሜን ጦርነት ሞተዋል። ብቸኛ ልጇ ፊያሜታ እንዳጋጣሚ እኔን ከወለደች በኋላ ተገድላ ተገኘች። እኔም ኤርትራ መኖር አልቻልኩም። አስመራ ከተማ ማይተመናይ ሰፈር የሚገኘው ቤታችን በሞቱና ድራሻቸው በጠፋ የቤተሰቦቻችን አባላት ፎቶግራፎች ተከብቦ አያቴ አደይ ስላስ ረፍቷን እየጠበቀች ነው።” እንባዋ ከውቡ እና እንደኮከብ ከሚያበራው ዓይኗ የተዝረበረበው ድንገት ነበር። የቻልኩትን ያህል አጽናናኋት።

 “ምናልባት ሁሉም ነገር ፍፃሜ ሲያገኝ እኛ የመጨረሻዎቹ ገፈት ቀማሾች እንደሆን ይሰማኛል” አለችና ጥያቄ በሚመስል ሁኔታ እንደ ውብ አብሪ ኮከብ በደመቁ ዓይኖቿ አተኮረች።

“ልክ ነሽ አስምረት መልካም ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ! ቢሆንም የሰሃራ በረሃን ማቋረጥ ከባድ ነው። ሁሉን ቻይ አምላክ ይከተልሽ” አልኋት ማፅናኛ ቢሆናት ብዬ።

 “ዮሐንስ ሞትን መፍራት ካቆምኩ ቆየሁ። የስደት ጊዜየ ሞትን በየእለቱ አለማምዶኛል። ከማይጨበጥ ተስፋ ጋር መዋል ማደሩን ለመድኩት። ግን እንደገና ተስፋ አደርጋለሁ። ሆኖም አንድ የምነግርህ ሀቅ ሰሃራ በረሃን ማቋረጥ አስመራን ለቆ ከመውጣት የሚከብድ አይመስለኝም። ኦሮማይ!”

 ያን ጊዜ ከአስምረት ጋር ለሶስተኛ ጊዜ ነው ተገናኝተን ያወራነው። አሁን የት እንዳለች አላውቅም። ከአውሮፓ ከተሞች ከአንዳቸው? ወይስ ከሜድትራኒያን አሳ ነባሪዎች መንደር? የፊያሜታ ልጅ ውቧ አስምረት አሁንም ድረስ የውስጤ ጥያቄ ናት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top