ጣዕሞት

የኢትዮጵያ ወዳጅ ሪታ ፓንክረስት አረፉ

የበጎ ፈቃድ ተግባራትና ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ነሆነው የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር (ሶፊ) የኢትዮጵያ ገሚኒ ትረስትን ጨምሮ ላቅ ያለ አገልግሎት መስጠታቸው በህይወት ታርክ መዝገባቸው ላይ ሰፍሯል:: ከ60 አመታት በላይ የኖሩባት ኢትዮጵያን አብዝተው እንደሚወዱ የሚነገርላቸው ሪታ፤ እንደባለቤታቸው ሪቻርድ ሁሉ፤ ስማቸውን በበጎ የሚያስጠራ ሌሎች በርካታ ተግባራትን ከውነው አልፈዋል::

ወይዘሮ ሪታ ፓንክረስት በተለያዩ ጊዚያት ኢትዮጵያን በተመለከተ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ጥናታዊ ጽሑፎችንና የምርምር ጽሑፎችን ከማዘጋጀታቸው በዘለለ በቀድሞው የአፄ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ እና በብሔራዊ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ በሙያቸው ለበርካታ አመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል::

 በ92 ዓመታቸው ያረፉት ወይዘሮ ሪታ ፓንክረስት ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ያረፉ ሲሆን፤ በቅድስትሥላሴ ካቴድራል የቀብር ስርአታቸው ሲፈጸም፤ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እና የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ ተገኝተዋል::

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ቤተሰብ ለኢትዮጵያ ባላቸው ፍቅርና ለሀገሪቱ ባበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ የክብር ዜግነት እንደተሰጣቸው በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተገኘ መረጃ አመልክቷል::

ወይዘሮ ሪታ ከሶስት አመት በፊት ካረፉት የታሪክ ጸሐፍ እና የማህበረሰባዊ ጥናት ምሁር ባለቤታቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አሉላ እና ሄለን የተባሉ ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል::

ኮመዲያን ደረጀ 3ኛ መጽሐፉን ለንባብ አበቃ

በቀልድ ውበት ቁምነገርን እያዋዛ ለበርካታ ዘመናት ህዝብን በማዝናናት የሚታወቀው ደረጀ ኃይሌ (ኮሜዲያን) “የሚሊዬነሩ ፍዳ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ሰሞኑን አስመርቆ ለንባብ አብቅቷል፡፡

 ግጥሞችን፣ ወጎችን፣ ቁምነገር አዘል ቀልዶችን የከተተበት ይህ መጽሐፍ 81 ገጽ ሲኖረው በብር 59.60 በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

በመጽሐፉ የመግቢያ መልእክት “ያው ሁሌም እንደምንባባለው በህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ የምናስተውላቸውን ነገሮች ወረቀት ላይ አስፍረን ለትውልድ ብናስተላልፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ አንድም እንዝናናባቸዋለን፤ ብሎም ትምህርት እንወስድባቸዋለን፡፡ በተቻለ መጠን አንባቢ ዘንድ በአፍ ብቻ ተወርተው የሚቀሩ ታሪኮችን ወረቀት ላይ ማስፈር ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው” ብሏል ደረጀ፡፡

ይህ መጽሐፍ ሦስተኛው ሲሆን፤ ከአሁን ቀደም በተመሳሳይ መልኩ ትዝታ ሲጨለፍ፣ አንዳንድ ነገሮች እና ሌሎች የተሰኙ መጻሕፍቶችን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ደረጀ በአሁኑ ወቅት ‹‹ጥበብ በፋና›› የተሰኘ የመዝናኛ ፕሮግራም በፋና ቴሌቭዥን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

የአውግቸው ስንብት

አውግቸው ተረፈ የደራሲው የብዕር ስም ሲሆን ህሩይ ሚናስ ትክክለኛ መጠሪያ ስሙ ነበር፡፡ በአጫጭር ልብወለድ፣ በትርጉም፣ እንዲሁም በአርታኢነት የሚታወቀው ኅሩይ ሚናስ/ አውግቸው ተረፈ/ ውልደቱ ከጎጃም ደጀን ነው፤ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አይነ ስውራንን ይመራ ነበር። በዚህ ወቅት ራሱን ለማኖር በረንዳ ላይ አድሯል። ቀስ በቀስ የፀሎት መጻህፍትን ወደ መሸጥ ከዚያም በሂደት የትምህርትና የልብ ወለድ መጻህፍትን በማዘጋጀት ኑሮውን መምራት ቀጠለ።

አውግቸው ተረፈ፤ ወይ አዲስ አበባ፣ እብዱ፣ ያንገት ጌጡ፣ ጩቤው፣ ፅኑ ፍቅር፣የፕሮፍሰሩ ልጆች፣ ደመኛው ሙሽራ (በጋራ)፣ የፍቅር ረመጥ፣ ሚስኪኗ ከበርቴ፣ ጣፋጭ የግሪም ተረቶች፣ የዓለም ምርጥ ተረቶች (1፣ 2 እና 3)፣ የግሪክ እና የሩሲያ ተረቶች እንዲሁም ምስጥራዊቷ እመቤት፣ የትውልድ እልቂት (ትርጉም) እና ሌሎች መጻሕፍትንም ያሳተመ እንደነበር የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በአርታኢነት፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ በተመሳሳይ ሙያ የሰራ ሲሆን፡ በየካቲት መጽሔት ላይ በብእር ሰም በርካታ መጣጥፎችን ሲያወጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡

 ደራሲው የአእምሮ ህመም ችግር ካጋጠመው በኋላ ያንን በመጻፍ የህመም ስሜቱነና የዚያን ወቅት ሕይወቱን አሳይቷል፡ ፡ በዚህም የአማኑኤል ሆስፒታል አንዱን የህክምና ክፍል በእርሱ ስም ሰይሞታል። አውግቸው በስራዎቹ ከፍተኛ እውቅና ያለው ሲሆን፡ በ2008 ዓመተ ምህረት የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚም ነበር።

ይህ በርቱና ታታሪ ሰው፤ በህመም ሲሰቃይ ሰንብቶ በ68 አመቱ ይህችን አለም ተሰናብቷል፡፡ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ አድናቂዎቹ በተገኙበት ሰኔ 12/2011 በአዲስ አበባ ሳለ ቀዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስርአተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ ስሙና ስራዎቹ ግን ህያው ሆነው በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ይቀጥላሉ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top