አድባራተ ጥበብ

የባህልና የማንነት ለውጥ • “ንፁህ” የሰው ልጆች ማንነት ወይም ባህል የለም

በባህል ለውጥና በውህደት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል:: እየቀረቡም ይገኛሉ:: በአንድ በኩል፣ ብዝኀ-ባህል የውጥረት፣ የግጭት፣ ምንጭ አድርገው በማየት የሚቃወሙ ወገኖች ልዩነት የሚል ነገር በመፋቅ ህዝቦችን በሚያመሳስሏቸው የጋራ መገለጫዎች ላይ ብቻ ትኩረት በመስጠት ውህደት አይቀሬና አስፈላጊ በመሆኑ ሂደቱ እንዲፋጠን በሚል ይከራከራሉ:: ከዚህ በተቃራኒ ሌሎች በተለይም ወደ ምዕራቡ ዓለም ከሚፈልሱ ስደተኞች እይታ አንፃር በመከራከር የሰዎች ማንነት ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፤ ልዩ ከሚያደርጋቸው መገለጫ እርቃን እንዳይቀሩ ማንነታቸው እንዲጠበቅ የውህደት ደረጃ በመጠኑ ሊወሰንና ተስማሚነት ባለው መንገድ በሥራ ላይ ማዋል ይገባል በሚል ያምናሉ:: ሌሎች ባህላዊ ልዩነቶችን እንደ ቅመማት  ጣዕም፣ እንደ ቀስተ-ዳመና ኅብረ-ቀለም ፈጥረው እንዲኖሩ ለማስቻል ኅብረ-ባህልን ማክበርና መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው በማለት በተቻለ መጠን በማንኛውም ዘዴ ውህደትን ማስወገድ አስፈላጊ ነው ሲሉ ይከራከራሉ::

ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት በሀገራችን በተፈጠረው የፖለቲካ አውድ ውስጥ ስንመለከት ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ተመሳሳይም የተለያዩም ሆነው እናገኛለን:: በእርግጥም እኛ የምንገኝበት አውድ ሌሎች ከሚገኙበት ዐውድ የተለየ በመሆኑ ልዩነት መታየቱ የሚያስደንቅ አይሆንም:: የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እንደ ማንኛውም የተፈጥሮ ክስተት ባህልም የለውጥ ሕግ ተገዥ ነው:: ባህል ይለወጣል:: ባህል ሲለወጥ ማንነትም የግድ ይለወጣል፤ ለውጡም በባህል/ በማንነት ቅይጥነት እናም በውህደት ሂደት ይከሰታል:: ጥያቄውም ሂደቱ የሚያልፍባቸው ደረጃዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? በዚያውም ዛሬ ከሚታየው የናጠጠ ብሔረሰበኝነት ወይም ጎሰኝነት አንፃር ምን አንድምታ ይኖረዋል?፣ በሚለው ዙሪያ የሚያተኩር ነው::

 ማንኛውም ክስተት በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ የመሆኑ መሠረታዊ ሀሳብ ጥንትም ሆነ ዛሬ በምገኝበት ዘመናዊ ዓለም የታመነበት ጉዳይ ነው:: ለማስታዎስ ያህል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ600ኛው ዓ. ዓ. መጨረሻ ገደማ ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች፣ ለምሳሌ ፓይታጎራስ፡-

 “በዚህ ሁለንተናዊው ዓለም ውስጥ ያለ ለውጥ እንዳለ ቆሞ የሚገኝ ምንም ነገር የለም:: ጊዜ ራሱ ከወንዝ ባልተለየ ሁኔታ ሳያቋርጥ በለውጥ እየፈሰሰ ይከንፋል:: ሁሉም ነገር ይለወጣል፤ ማንኛውም ነገር በተፈጥሮው የበራሪ ምስል የተሰጠው ነው::” ሲል ነበር የተናገረው::

በፈላስፎች ዘንድ ሁል ጊዜ የሚጠቀሰው ሄራክሊተስም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓ.ዓ. ገደማ፡-

“አንድን ተመሳሳይ ወንዝ ሁለት ጊዜ ልትሻገሩት አትችሉም” ሲል ተናግሯል::

ይህ የተፈጥሮ አጠቃላይ የለውጥ ሕግ ተገዥነት ከሁለት ሚሊኒየም በላይ በየዘመኑ በፈላስፎች ወይም በሊቃውንነት ዘንድ የሀሳብ ምንጭነትና መንኮራኩርነት ሲጠቀስ ኖሯል:: ለውጥ በባህልም ይሁን ከባህል ጋር በሚገኙ በከባቢያችን በሚኖሩ ማናቸውም ነገሮች ላይ ይሠራል::

ፕራይሞርዲያሊስቶች እንደሚሉት ባህል ሲፈጠር አንስቶ ባለበት እንደቆመ የሚገኝ፣ ለአንዴም ለሁሌም የተሰጠ፣ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይነካው ዛሬ ከምንገኝበት ዘመን ላይ የደረሰ ወደፊትም መጭው ዘመን በተመሳሳይ ሁኔታ የሚረከበው ነው ይላሉ:: ከዚህ በተቃራኒ ዳንደስ እንዲሁም ናጀል “ባህል/ ማንነት እንደ ማንኛውም ተፈጥሯዊ አካል ለለውጥ ሕግ ተገዥ ነው::” ይልቁንም ጌሪ ፌራሮ እንደሚናገረው “የልዩነት ደረጃው አንድ ህብረተሰብ እንደሚገኝበት ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም እንደ ባህል አስደናቂና ፈጣን ለውጥ የሚያደርግ ነገር የለም::” ለውጥ ደግሞ የሰው ልጅ ዋነኛ ባሕርይ ነው:: ስለዚህ ባህል የግድ ይለወጣል:: የማንነት መሠረቱ ባህል እንደመሆኑ መጠን ባህል ሲለወጥ እሱም በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኝ ክስተት ነው እንጂ ዝንተ-ዓለም ለውጥ ሳይነካው እንደቆመ አይኖርም::

 የባህል ለውጥ የሰዎችን የማንነት ቅይጥነትን ከዚያም ውህደትን ይፈጥራል:: ከዚህ ላይ “ውህደት” የሚለውን እሳቤ በቅድሚያ መግለፅ አስፈላጊ ይሆናል:: በዚህ ጽሑፍ አውድ “ውህደት” በህዝቦች መካከል በተፈጠረ ማንኛውም ዓይነት የግንኙነት መስተጋብር ሂደት ተከትሎ የሚከሰተውን ለውጥ እንጂ ከዚህ ውጭ በኀይል ወይም በግድ የሚከናወነውን አይመለከትም:: የሚመለከተው በታሪክ ህዝቦች በተለያዩ ምክንያቶች የማንነት መለያዎቻቸውን፣ ትውፊታዊ የኑሮ ዘዴያቸውንና ስልቶቻቸውን በሂደት በመለዋወጥ ከሌሎች ጋር የሚቀያየጡባቸውን መንገዶች ነው:: ውህደት አንድ ህዝብ፣ ቡድን ወይም ሰዎች በሚኖራቸው የረጅም ጊዜ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ምክንያት ከብዙ ዓመታት በፊት ይገለፁባቸው የነበሩትን ልዩ የማንነት ባሕርያት በማቀያየጥ የሌላውን ህዝብ ወይም ህብረተሰብ መገለጫ ባሕርያትም እንደ ራሳቸው መገለጫ አድርገው የሚወስዱበት ሂደት ነው:: ይህንም ጎርዶን በዚህ መልክ በህዝቦች መካከል የሚፈጠር አዲስ ቅይጥ ባህል “ውህደት ተብሎ ይጠቀሳል” ይለዋል::

 በዚህ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ በየትኛውም ዓለም የሚገኝ የአንድ ህዝብ የባህል ገጽታዎች፣ የሕይወት ወይም የአኗኗር ስልቶች፣ ትውፊቶች፣ የእምነትና የእሴት ሥርዓቶች፣ አመለካቶች፣ አስተሳሰቦች፣ ወዘተ. ይለወጣሉ:: ይህ ሲሆንም በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ጥልቅና መሠረታዊ ነው:: በሰዎች የሕይወት ዘመን ውስጥ ሥርፀት እንሚያደርግ ሁሉ በዚያው ልክ በግለሰቦችም ሆነ በማህበራዊ ቡድኖች ማንነት፣ አስተሳሰብ፣ ድርጊትና ማህበራዊ ግንኙነት፣ ስለ ከባቢው አለም በሚኖረው ግንዛቤና በሚሰጠው ትርጓሜ ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ከፍተኛ ነው::

 በጉርብትና አብረው በሚኖሩ ህዝቦች መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶች ከጥበብ ጋር የተቆረኙ ናቸው:: በእርግጥ የግንኙነቱ ታሪካዊ ዳራ፣ ደረጃና መጠን ከአውድ አውድ (ከቦታ ቦታ) ሊለያይ ቢችልም እነዚህ ተፅዕኖዎች በህዝቦች በካከል የማህበራዊ፣ የባህላዊና የኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በሚከተሉት ሁኔታዎች በጉልህ ይከሰታሉ:: ለምሳሌ የምርት መሣሪያዎች፣ የአልባሳት፣ የጌጣጌጦች፣ የምግብ አሠራሮችና ዓይነቶች፣ ወዘተ. ከአንዱ ወደ ሌላው ህዝብ የሚኖራቸው ሥርጭት ይኖራል:: በጉርብትና አብረው የሚኖሩ ብሔረሰቦች ተወላጆች በገበያ ወይም በንግድ ልውውጥ ግንኙነት ያደርጋሉ:: በማህበራዊ ግንኙነት በኩልም የጋብቻ ዝምድና የደም ትስስር ሊፈጥሩ ይችላል:: የአንዱ ብሔረሰብ ተወላጅ አባላት በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ሸሽተው፣ በችግር ተሰደው፣ በሙያ አገልግሎት፣ ወዘተ. ከሌላው ህዝብ ጋር አብረው መኖራቸው በታሪክ የተረጋገጠ ነው:: በዚህ መልክ አንዱ ከሌላው ትውፊታዊ እውቀት፣ ጥበብና ዘዴን፣ ሕጎችንና ደንቦችን ይቀስማል:: የአዝርእት አጠቃቀምን፣ ለህማም ፈውስ የሚሆኑ የመድኀኒቶችን ቅመማና የአጠቃቀም ጥበብን፣ የኑሮ ዘዴዎችን፣ የሰላምና የእርቅ መንገዶችን፣ ወዘተ. ይቀስማል:: እየቆየም አንዱ የሌላውን የራሱ ቅርሶችን እሴቶች አድርጎ ይወስዳዋል:: እነዚህና የመሳሰሉት ግንኙነቶች የሚያከናውኑት በቋንቋ አማካይነት ነው:: ስለሆነም በቋንቋዎቹ መካከልም እንደዚሁ ግንኙነት ስለሚፈጠር አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው::

በ“ዘረኝነት” ላይ የተመሠረተ ርዕዮተ- ዓለማዊ ፖለቲካና ፍልስፍና ለረዥም ዘመናት ሲያራምደውና በሰፊው ሲያሠራጨው ቢቆይም በሳይንሳዊ አስተሳሰብ ሲታይ ቅልቅል፣ ቅይጥ ወይም ውህድ እንጂ በዓለማችን ውስጥ “ንፁህ” የሰው ልጆች ማንነት ወይም ባህል የለም:: ይህንም የስነሰብዕ ምሁራን ለምሳሌ ሻውና ስቴዋርት “ንፁህ ባህል የሚባል ነገር ፈፅሞ የለም:: ነንፁህ ማንነትም የለም::” ሲሉ ያሠፈሩት ከዚህ የመነጨ ነው::

 ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ህብረተሰቦች በባህል የውህደት ሂደት ውስጥ ሲያልፉ መካከላቸው ልዩነቶች እየጠበቡ ይመጣሉ:: ጎርዶን እንደሚያስረዳው የባህል የውህደት ሂደት በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ወይም ደረጃዎችም ይከናወናል:: አንዱ ባህላዊ ውህደት (cultural assimilation) ነው:: ይህም የአንድ የህዝብ ቡድን በማንኛውም የአኗኗር ስልት ሁሉ በቋንቋ፣ በሃይማኖታዊ እምነት፣ ልማዳዊ አሠራሮች፣ በትውፊታዊ ሕጎች፣ ደንቦች፣ በእሴቶች፣ ወዘተ. ሁሉ የሚከናወን ውህደት ነው:: ሁለተኛው የማህበራዊ መዋቅር ውህደት ነው:: ይህም በማህበራዊ ግንኙነት መርበቦች፣ በቡድኖች፣ በአደረጃት፣ በማህበራዊ የሙያና የሥራ አከፋፈል ተዋረዶች፣ በአጠቃላይ በሁሉም የማህበረሰብ መዋቅራዊ ክፍሎች የሚደረግ ውህደት ነው:: ሦስተኛው በጋብቻ አማካይነት የሚከናወን ውህደት ነው::

የዚህ የውህደት ደረጃዎች ወይም ሂደቶች ሦስት ናቸው:: አንደኛው ደረጃ በቋንቋ የሚከሰት ለውጥ ነው:: ይህ የአንድ ማህበራዊ ቡድን አባላት የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ የበላይነት ባለው ብሔረሰብ ቡድን ባህልና ቋንቋ የመተካት ደረጃ (ሂደት) ነው:: ቋንቋ ባህል የሚገለጽበትና የሚተላለፍበት ዋና የግንኙነት መንገድ ነው:: የተለያየ ባህላዊ መሠረት ያላቸው ሰዎች በደጉም፣ በክፉም፣ በስደት፣ በጋብቻ፣ በገበያ፣ በንግድ ወይም በጦርነት፣ ወዘተ፣ ምክንያት ከሌሎች ሰዎች ጋር ይገናኛሉ:: ሰዎች በተገናኙ ቁጥር ጠቃሚ ሆኖ ሲያገኙት አንዱ ከሌላው ይወስዳል:: ሁለተኛው የአንድነት ወይም የመዋቅራዊ ውህደት ደረጃ (ሂደት) ነው::

 ይህም ሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ (ሂደት) በሚል ይከፈላል:: ሁለተኛ ደረጃ (ሂደት) የሚባለው የአንድ ማህበረሰቡ አባላት የበላይነት ወደአለው ሰፊ ብሔረሰብ ተቋማትና ድርጅታዊ መዋቅሮች የመካተት ደረጃ (ሂደት) ሲሆን አንደኛ ደረጃ (ሂደት) ደግሞ የማህበረሰቡ አባላት ሰፊ በሆነው ብሔረሰብ በተለይም ኢመደበኛ ማህበራዊ ቡድኖች ውስጥ የሚዋሀዱበት ደረጃ (ሂደት) ነው:: ሦስተኛው የጋብቻ የውህደት ደረጃ (ሂደት) የሚባለው ሲሆን ይህ የማህበረሰቡ አባለት የበላይነት ካለው ማህበረሰብ አባላት ጋር በብዛት በጋብቻ የሚዋሀዱበትን መንገድ የሚጠቅስ ነው:: ጋብቻ የተለያዩ የትውልድ ሐረግ ባላቸው ወላጆች መካከል የሚከናወን ትስስር የልጆቻቸውን፣ በአጠቃላይም የግለሰቦችን፣ ቅይጥ ማንነት ወይም ውህደት ይወስናል::

 እነዚህ የለውጥ መንገዶችና ውጤቶቻቸው ዘመናዊነትን የተከተሉ የኑሮ ስልቶች ማለትም የዘመናዊ አስተዳደርና አሠራር፣ የከተሞች፣ የትምህርት፣ የገበያ ወይም የንግድ ልውውጥ፣ የመጓጓዣ ዘዴዎች፣ የቴክኖሎጂና የኢንዱሰትሪ ውጤቶች፣ የሀገር ግንባታ እርምጃዎች፣ የህዝቦች ከቦታ ቦታ ዝውውሮችና ሠፈራዎች፣ እየተስፋፉና ሥርፀት እያገኙ በመጡ በህዝቦች ትውፊታዊ የአኗኗር ስልቶችና በፆታና በሙያ መስክ በተወሰኑ የሥራ ክፍፍሎች ላይም የሚያስከትሏቸው ለውጦች (የመቀያያጥና የውህድነት ደረጃና ሁኔታዎችን) ፍጥነት ይጨምራሉ::

ዛሬ ስለ እያንዳንዳችን ማህበራዊ ሁኔታ ስንናገር ስለ ዓለማችን አጠቃላይ ሁኔታም እየተነገርን ከምንገኝበት ዘመን ላይ ሆነን ነው:: በተለይም በ21ኛው ምዕተ-ዓመት የምንገኝበት ዘመነ-ሉላዊነት ካፈራቸው የረቀቁ የቶክኖለሎጂ ውጤቶች ማለትም፡ – የሳቴላይት፣ የኮምፒውተር፣ የስልክና የኢንተርኔት ምጥቀት የታገዙ እጅግ ፈጣን ግንኙነቶች፣ የትምህርትና የመረጃ – የዕውቀት፣ የንግድና የዲፕሎማሲ ልውውጦች አንፃር መረዳት ተገቢ ይሆናል:: ዛሬ ብዙዎች እየተናገሩት እንደሚታየው ዓለማችንን ወደ አንድ ጠባብ “መንደር” እየተቀየረች ነው:: ዓለማችን ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረች ነው ማለት የዓለማችን ባህሎችም ወደ አንድ “ማቅለጫ ጋን” እየገቡ መሆኑን ጨምሮ መገንዘብ ያስፈልጋል:: ዘመነ ሉላዊነት የቀለምና የባህል ልዩነት ባላቸው ሰዎች ዘንድ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል:: ቀልጣፋና ቀላል የመጓጓዣ ፍጥነት፣ ዓለም አቀፍ ገበያ፣ የሰው ኃይል (የሙያና የዕውቀት) ፍላጎት ከተለያዩ ሀገሮች የመጠቀም ዕድሎችን ፈጥሯል:: በዚያው መጠን ባህሎችን ይበልጥ እያገናኙ መጥተዋል:: በአጠቃላይ በሉላዊነት አውድ ውስጥ የተፈጠሩትን ዓለማቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስሮችና የቋንቋ ተግዳሮቶች በኅብረ-ባህል/ ማንነት ላይ የሚያስከትሉት አንድምታ ምን እንደሆነ መገመት አያቅትም::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top