ታዛ ስፖርት

የመጨረሻ ውሳኔ

የመስሪያ ቤታቸው ሰራተኛ ለምን ለሌላ ክለብ እንደሚጫወት ግራ የገባቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ስራ አስኪያጁ አቶ ሰይፉ ማህተመስላሴ ጋር ገብተው ቅሬታቸውን አቀረቡ:: ማክሰኞ እለት አለቃው ሰራተኛቸውን ጠርተው ‹‹ዛሬ የትም እንዳትሄድ›› አሉት::

 ‹‹ምን ማለት ነው?››

‹‹ስራ አለ››

‹‹ለምሳ ቤቴ እሄዳለሁ››

‹‹ምሳህን እዚሁ አካባቢ ብላ››

‹‹ቤቴ ነው የምበላው››

‹‹አትሄድም ብያለሁ››

‹‹መሄድ አለብኝ››

ያላፊው አሁን እያነጋገሩ ያሉት መንግስቱ ወርቁን ነው:: ከስቪል አቪሽን ተመርቆ መብራት ሃይል የተመደበው መንግስቱ የሚጫወተው ለጊዮርጊስ ቡድን ነው:: እሁድ እለት በጥሎ ማለፍ ውድድር ጊዮርጊስና መብራት yይል ተጋጠሙ:: ጊዮርጊስ 5ለ3 ሲያሸንፍ ሶስቱን ግብ መንግስቱ አስቆጠረ :: ሰራተኛው ተናደደ:: ተናደውም ዝም አላሉም:: yላፊያቸውን ተቃወሙ:: አቶ ሰይፉ መብራት yይል ቡድን ተመስርቶ ወደ ውድድር ከመግባቱ በፊት መንግስቱን ለመብራት yይል እንዲጫት አደርጋለሁ ብለው የገቡት ቃል ባለመሳካቱ አበሳጫቸው:: መጀመሪያውኑ ጥያቄው የመጣው ከክለቡ ተጫዋቾች ነበር:: ‹‹መንግስቱ እኛ ጋር ከተጫወተ ቡድኑ ትልቅ ስም ያገኛል›› በሚል ነበር እንዲመጣላቸው የጠየቁት::

መንግስቱ የድርጅቱ ሰራተኛ በመሆኑ ለቡድኑ የመጫወት ግዴታ አለበት ‹‹እኛ ጋር እየሰራ እንዴት እኛን ያጠቃናል›› የሚል ተቃውሞ እየበረከተ መጣ:: መብራት ሀይል የስፖርት ክለቡ እንደተመሰረተ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ ጥር 2 ቀን 1954 ዓ.ም 14 ለ 0 ሲሸነፍ ስምንቱን ያገባው መንግስቱ ነበር:: ከዚያን ወዲህ መብራት ሀይሎች እሱን በጥብቅ ይከታተሉታል:: ከጥሎ ማለፉ ጨዋታ በኋላ ስራ አስኪያጁ ቢሮ የተጠራው መንግስቱ ካባድ ክርክር ገጠመው:: አቶ ሰይፉ ‹‹ማነው ለጊዮርጊስ እንድትጫወት የፈቀደልህ?››አሉ

‹‹ማንም››

‹‹እኛ እያለን እንዴት ለእነርሱ ገባህ››

‹‹እናንተ እኮ የላችሁም ››

‹‹ማለት ››

‹‹መብራት ሳይመሰረት ነው ጊዮርጊስ የገባሁት››

‹‹እና ››

‹‹እኔ የእናንተ ሆኜ አላውቅም››

‹‹አሁን ትሆናለህ››

‹‹አይመስለኝም››

‹‹ጊዮርጊስ ደሞዝ ይሰጥሃል?››

‹‹አይሰጠኝም››

‹‹ከእነርሱ ምን ታገኛለህ?››

‹‹ምንም ››

‹‹ምንም ለማታገኝበት ለምን ትጫወታለህ››

‹‹ክለቡን ስለምወደው››

‹‹እኛን አትወደንም››

‹‹ አወዳችኋለሁ››

‹‹ታዲያ ለምን አትጫወትልንም?››

‹‹እነርሱን ከእናተ የበለጠ እወዳለሁ››

‹‹የመጨረሻውን ልንገርህ››

‹‹እሺ››

‹‹እኛ ጋር አትጫወትም?››

‹‹አልጫወትም››

‹‹ለምን ?››

‹‹አልችልም :: ከጊዮርጊስ ጋር ቃል ኪዳን አለብኝ››

‹‹ከስራህና ከጊዮርጊስ ምረጥ››

‹‹ጊዮርጊስን እመርጣለሁ››

‹‹እርግጠኛ ነህ?››

‹‹አዎ››

‹‹አስብበትና ተመለስ››

‹‹አስቤበታለሁ መልሱ ይሄ ነው››

‹‹በቅርቡ የኛን ውሳኔ ትሰማለህ››

የአሁኑ ንግግር የዛቻ እንደሆነ አውቆታል:: መንግስቱ የጊዮርጊስን ክለብ የተቀላቀለው በ1950 ነው:: መብራት ሀይል ክለቡ የተመሰረተው በ1954 ነው:: ከጊዮርጊስ ጋር የጸና ትስስር አለው:: ‹‹ በቅርቡ የኛንም ውሳኔ ትሰማለህ›› የሚለው ንግግር ምን እንደሆነ መንግስቱ ገበቶታል:: ከስራ ሊያሰናብቱት እንደሆነ አልጠፋውም:: ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ተባረሃል›› የሚል ደብዳቤ አንድ ቀን ወይም በዚህ ሳምንት አለበለዚም ባልታሰበ ቀን እንደሚደርሰው ይገምታል::

 መንግስቱ የሚኖረው ከቅርብ ጓደኛው ከ አቶ ካሳ ገብረጊዮርጊስ ጋር ነው:: ትልቅ ቪላ ቤት ለሁለት ይዘዋል:: በውድ ገንዘብ ነው የተከራዩት:: ስራውን ካጣ የለመደውን ኑሮ ማግኘት አይችልም:: ከጊዮርጊስ ክለብ ምንም የሚያገኘው ነገር የለም:: በክለቡ ቁልፍ ተጫዋች ቢሆንም አምስት ሳንቲም አይከፍሉትም:: የኳስ ጫማውን እንኳን ከደሞዙ ባጠራቀመው ብር ነው የገዛው:: ክለቡ የህዝብ ፍቅር እንጂ ገንዘብ ስለሌለው ጫማ ሲያልቅበት ግዙልኝ ብሎ ማስቸገር አልፈለገም:: በቅርቡ ቤተሰብ የመመስረት እቅድ አለው:: ለጋብቻው ጥሪት መቋጠር አስቧል:: ደግሞም ከጥቂት ግዜ በኋላ ወደ ጎንድር መሄድ አለበት :: ዘንድሮ መቅረት የለበትም:: እናቱን ሄዶ ከጠየቀ ብዙ አመት ሆኖታል:: ለጉዞና ለቤተሰቡ ገንዘብ ያስፈልገዋል:: አሁን እዚህ መስሪያ ቤት ደመወዙን የሚያሳጣ ማስጠንቀቂያ ደርሶታል:: ገንዘብ ከማይሰጠው ጊዮርጊስ እና ደሞዝ ከሚቆርጥለት መብራት ሀይል የመምረጥ ጫፍ ላይ ይገኛል::

መስሪያ ቤቱ ለትምህርት ጣሊያን ሊልከው ቃል ገብቶለታል:: ስሙም ተልኳል :: ከኳሱ ጎን ሙያውንም ማሻሻል ይፈልጋል:: ከድርጅቱና ከጊዮርጊስ ምረጥ በተባለ ሳምንታት ደሞዙን መቀበል ነበረበት:: ወደ ገንዘብ ቤት ገባ:: አንድ ጓደኛው ደሞዝ ሲወስድ ደረሰ:: ልጁ ከመንግስቱ በኋላ ነው የተቀጠረው:: እኩል ነው ደሞዛቸው:: መንግስቱ ደሞዙን ከወሰደ በኋላ ልጁ የተቀበለውን ፖስታ አየ:: አላመነም ‹‹አንተ!!!!››አለ

‹‹አቤት ››

‹‹ይሄ ፖስታ ያንተ ነው?››

‹‹አዎ››

‹‹እንዴት እንዲህ ሆነ?››

‹‹ለሁላችንም እኮ ነው››

መንግስቱ ደነገጠ:: ልጁ የደሞዝ ጭማሪ ተደርጎለታል:: ይሄንንም ገንዘቡ የታሸገበት ፖስታ ላይ ተመልክቶታል:: ድርጊቱ በጣም አናደደው:: በዚህ መልክ እያበሳጩት እንደሆነ አወቀ:: ነገሩ በዚህ ብቻ አላበቃም:: ወደ ጣሊያን እንደሚልኩት ቃል የገቡለትም ለሌላ ሰው መሰጠቱን ሲያረጋግጥ በንዴት ጦፈ:: ተብከነከነ:: በዚህ ብቻ አላበቃም:: እንደጦፈና እየተብከነከነ በጥድፊያ ወደ ስራ አስኪያጁ ቢሮ ገባ:: ‹‹ይሄ ነገር ትክክል ነው?››አለ::

 ‹‹ምኑ ››

‹‹በኔ ላይ የምትጫወቱት?››

‹‹አንተ እኮ የኛ አይደለህም››

‹‹በተመደብኩበት ቦታ ሀላፊነቴን በአግባቡ እወጣለሁ:: የምትለኩኝ በስራ መሆን አለበት››

‹‹እሱን አትነግረንም››

‹‹ምን?››

‹‹የተባልከውን አድርግ››

‹‹እናንተ እኮ ለስራ ነው የቀጠራችሁኝ፤ ለኳስ አይደለም››

‹‹አሁን የመጨረሻውን ልንገርህ?››

‹‹እሺ››

‹‹ ከስራህና ከጊዮርጊስ ምረጥ››

‹‹ነገርኳችሁ››

‹‹አቋምህን አትቅይርም››

‹‹አልቀይርም››

መንግስቱ ተናዶ በሩን በሀይል ዘግቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ግቢውን ተሰናብቶ ወጣ:: ‹‹ቢጠሩትም አልመለስም›› አለ:: ስራ የለውም :: ያጠራቀመውም ገንዘብ የለም:: ደሞዝ ለማይቆርጥለት ክለብ መስእዋትነት መክለፈሉ የሞኝ ስራ እንደሆነ በመስሪያ ቤት የሚያውቁት ነገሩት :: መከሩት:: ወደ ስራው እንዲመለስ ለመኑት:: እሱ ግን አሻፈረን አለ:: ለጊዮርጊስ ወሳኝ ተጨዋች ነው:: ከመብራት ሀይል ስራውን ስለለቀቀ ጊዮርጊስ ምንም ማካካሻ እንደማያደርግለት አውቋል:: ጊዮርጊስ ለማንም ደሞዝ አይከፍልም:: ክለቡን የሚወዱትን ብቻ ነው የሚያጫውተው:: ቤቱ ቁጭ ብሎ ከጓደኛው ከካሳ ጋር መከረ:: ወጪ ተጋርተው ነው የሚኖሩት:: አሁን እጁ ላይ ምንም የለም:: መንግስቱ አንድ ሀሳብ መጣለት የኢንሹራንስ ካምፓኒ ጋር ሄደ:: ናይል ኢንሹራን ነው:: ሀላፊውን ፈልጎ ሊያናግረው ገባ:: ግሪካዊ ነው ‹‹እርስዎን ፈልጌ ነበር የመጣሁት››አለ::

‹‹ምን እንርዳህ?››

‹‹ለጉዳይ ነው››

‹‹ምንድነው ጉዳይህ?››

‹‹ስራ ፈልጌ ነው ››

‹‹ማስታወቂያ እኮ አላወጣንም ››

‹‹ብዙ የኢንሹራንስ ወረቀት እሸጥላችኋለሁ››

‹‹ ለስራው የሚመጥን ትምህርቱ አለህ?››

‹‹የለኝም››

‹‹ልምዱ አለህ››

‹‹የለኝም››

‹‹ ታዲያህ በምን እውቀትህ ትሰራለህ?››

‹‹እናንተ ብቻ እድሉን ስጡኝ››

‹‹ ለመሆኑ ምንድ ነህ አንተ››

‹‹ኳስ ተጨዋች ነኝ››

‹‹ማን ትባለለህ?››

‹‹መንግስቱ ወርቁ››

‹‹ ግን ስራውን እኮ አልችልም ብለኸኛል››

‹‹አዎ››

‹‹ታዲያ እንዴት ትሸጣለህ?››

‹‹ለአንድ ቀን ብቻ አስተምሩኝ››

‹‹እናስተምርሀለን…..ግን››

‹‹ግን ምን››

‹‹ስንት እሸጣለሁ ብለህ ትገምታለህ››

‹‹ ሰሞኑን በቀን እስከ 20 እሸጣለሁ ››

‹‹ትቀልዳለህ››

‹‹አልቀለድኩም››

‹‹የኛ እሳት የላሱት የሽያጭ ሰራተኛ በቀን ለሁለት ሰው እንኳን መሸጥ አልቻሉም››

‹‹እኔን እንደነርሱ አትዩኝ እድሉን ስጡኝ በስራዬ ለኩኝ››

‹‹ስራ እንድንቀጥርህ ነው ይሄን ያህል ሰው አመጣለሁ የምትለው?››

‹‹እድሉን ስጡኝና እዩኝ››

‹‹በቀን ሁለት ሰው ከሸጥክ እንቀጥርሀለን ብዙ ኮሚሽንም እንሰጥሀለን››

መንግስቱ ለስራ ተዘጋጀ:: ከሚሰራበት ድርጅት በእነርሱ የተነሳ ከስራ መባረሩን ደጋፊው ስለሰማ በሚችለው እንደሚረዳው አውቋል:: መርካቶ ገብቶ ብዙ ኢንሹራንስ ሸጠ:: የመጀመሪያ ቀን 15 ሽጦ መጣ :: ስራ አስኪያጁ አላመኑም:: ቆመው ነው የተቀበሉት:: ደሞዙ 150 ብር ነበር:: ወዲያው አሳደጉለት:: ስራውን በሚገባ እንዲያከናውን ፕሮቶኮሉን መጠበቅ ስላለበት ብዙ ሱፍ ልብስ ተገዛለት::

 ስራውን ለማሳደግ ሰዎችን ማስደሰት ስላለበት ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ሜዳ ላይ መጫወት ስላለበት እንዝርት ሆነ :: ጎል የማምረት ስራውን የተቃና አደረገው:: በየቦታው ወደ ኢንሹራን ደንበኞች እየጎተተ ማምጣት ጀመረ:: ወደያውኑ የኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ሰዎች መንግስቱን በእጃቸው ማስገባት ፈለጉ:: ምክኒያቱ ደግሞ መንግስቱ ብዙ ሰው ወስዶ ናይል ኢንሹራንስ ማስገባቱን ሰምተዋል:: እኛ ጋር ከገባህ መኪና እንገዛልሀለን አሉት:: በነገሩ ተደሰተ:: ወደ ናይል ኢንሹራንስ ሄደ:: ባለቤቱ ግሪካዊ ነው:: ወደ እርሱ ቢሮ ሰተት ብሎ ገባ:: ‹‹ ስራዬን ልለቅ ነው››አለ:: ‹‹ለምን?››

‹‹ኢምፔሪያል ብዙ ነገር ሊያደርግልኝ ነው››

‹‹ምን ››

‹‹መኪና ሊገዙልኝ ነው››

‹‹ለአንተ!!!!››

‹‹አዎ››

‹‹አንዴ ቆየኝ››::

ግሪካዊ ባለቤት ስልክ አነሳ ‹‹ሀሎ!!!ፖልሪየስ ነው…ለመንግስቱ ወርቁ የሚሆን ጥሩ መኪና አላችሁ?!!!….. እስኪ ሰርቪስ አድርጉና ዛሬውኑ ይዛችሁ ኑ!!!›› አለ:: አምፔሪያል መኪና ሰጥቶ በየወሩ ከፍሎ 20 በመቶውን ብቻ እነርሱ ሊችሉ ነው:: ናይል ግን ‹‹ግማሹን ካለህ ክፈል ከሌላህም ሌላ ግዜ እንነጋገርበታል ›› አለ:: መንግስቱ መኪና በያዘ ግዜ ስራውን ማቀለጠፍ ጀመረ:: በአጭር ግዜ ሀብት አፈራ:: የተገዛለት ምርጥ መኪና ነበር:: አንድ ነገር ማድረግ አለበት:: ከስራ ወዳባረሩት ሰው ሄዶ ማንነቱንና ወድቆ እንዳልቀረ ማሳየት ፈለገ:: መደ መብራት ሀይል መስሪያ ቤት ሄደ:: መኪናውን እየነዳ ገባ:: አቶ ሰይፉ የሚገቡበትን ሰዓት ስለሚያውቅ ቀድሟቸው ደረሰ:: እሳቸው መኪና የሚያቆሙበት ቦታ ላይ ዘመናዊውን አውቶሞቢል አቆመ::

 ይሄን ያደረገው ሆን ብሎ ነው:: መኪና መያዙን ስራ አስኪያጁ እንዲያዩለት ፈልጓል:: ሌላ ቦታ ካቆመ አያዩለትም:: እሳቸው ቦታ ካቆመ የማነው ብለው ይጠይቃሉ:: መኪናቸውን ለማቆም የዚህ መኪና ባለቤት ተጠርቶ ማየታቸው አይቀርም:: የዚህች ዘመናዊና ምርጥ መኪና ባለቤት መንግስቱ መሆኑን ያያሉ :: ያን ግዜ ማንነቱን ያሳያቸዋል:: መንግስቱ መኪናውን አቆሞ:: ጓደኞቹ ጋር ገብቶ በመስኮት ሁኔታውን ይከታተል ጀመር:: አቶ ሰይፉ መጡ:: ቦታቸው ተይዟል:: ጥበቃውን ጠሩት:: ‹‹ማነው እኔ ቦታ መኪና ያቆመው››አሉ::

‹‹አንድ ሰው ነው ››

‹‹ማን ?

‹‹በፊት እዚህ መስሪያ ቤት ሰራተኛ የነበረ ነው::››

‹‹እዚህ የሚሰራ ሰው ይሄን የመሰለ ዘመናዊ መኪና ሊይዝ አይችልም››

‹‹እዚህ አታቁም ብለነው ነበር››

‹‹እና ››

‹‹ምን አገባችሁ ብሎ አቆመ››

‹‹የታለ››

‹‹እዚያ ቢሮ ገብቷል››

‹‹ጥሩት››

ጥበቃዎቹ መንግስቱን ጠርተውት መጣ:: አቶ ሰይፉ ሲያዩት አላመኑም:: ከስራው ከተባረረ በኋላ ለምኖ ይመለሳል ብለው ጠብቀው ነበር:: ነገር ግን በአቋሙ ጸንቶ በመሄዱና ሄዶም በመቅረቱ ገርሟቸዋል:: ያሰቡት አንዲህ አልነበረም:: ለስራው፤ ለእድገቱና ጣሊያንም የመሄድ እድል ስላዘጋጁለት ደፍሮ ምንም ለማይከፍለው ጊዮርጊስ ጋር ሄዶ አይቀርም ብለው ነው ያሰቡት:: ደግሞም ይሄን የመሰለ ዘመናዊ መኪና መያዙ የእሱ ነው ብለው ሊያምኑ አልቻሉም:: ጊዮርጊስ ደሞዝ አይከፍለውም ከየት ገዛ ብለው ተገረሙ:: ወደ እርሳቸው እንደመጣ ‹‹አንተ ጎረምሳ››አሉት::

‹‹አቤት!!!! ››

‹‹የምን ጥጋብ ነው››

‹‹ምኑ››

መኪና እኔ ማቆያ ስፍራ የገተርከው››

‹‹አላወኩም ››

‹‹ያንተ ነው?››

‹‹አዎ››

‹‹ከየት አመጣህ?››

‹‹ሰርቼ ነው››

‹‹ምን ብትሰራ ነው ይሄን የመሰለ መኪና የገዛኸው?››

‹‹በጊዮርጊስ ተጫዋችነቴ››

አቶ ሰይፉ በድፍረት እሳቸው ቦታ ማቆሙ ቢያናድዳቸውም ሰርቶ ይሄን የመሰለ መኪና መግዛቱን አደነቁለት:: ቁጭ አድርገው መከሩት:: የገንዘቡን ምንጩንና እንዴት እየሰራ እንደሆነ በኩራት ነገራቸው:: በኳሱ ስሙ በጣም እየተነሳ መሆኑንና በሚገባ እንዲጠቀምበት ነገሩት:: በቀየጣዩ አመት እስጢፋኖስ ሼልን ለግለሰብ ለመስጠት ድርጅቱ ጨረታ አወጣ:: አቶ ሰይፉ በጨረታው ተሳተፉ:: እርግጠኛ እንደሚሸንፉና ቦታውን እንደሚወስዱ አውቀዋል:: ነገር ግን ፈረንጁ ጠርቷቸው ‹‹ያለጨረታ ለመንግስቱ ሰጥተነዋል›› አሉዋቸው ነገሩ አበሳጫቸው:: ወደ መንግስቱ ደወሉ ‹‹በየቦታው እየተከታተልከኝ ነው እንዴ?›› አሉ:: ይሄ ከሆነ ከ23 አመት በኋላ መንግስቱ የመብራት አሰልጣኝ ሆነ:: ቡድኑንም አደራጀ:: ሜዳ አሰራ:: አሁን ክለቡ የሚገለገልበት ሜዳ የመንግስቱ ማስታወሻ ነው:: ይህ በአገራችን የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስሙ ጎልቶ የሚጠቀሰው ሰው፤ ለጊዮርጊስ ክለብ እና ለብሔራዊ ቡደን ታላቅ ባለ ውለታ እንደሆነ ይወሳለታል:: ከ2ኛ እስከ 7ኛ የአፍሪካ እግር ኳስ የሀገራችን ብሔራዊ ብድን ውስጥ በመሳተፍ 10 ጎል በማግባት ከፍተኛ የጎል ቁጥር ካስመሰገቡ ተጫዋቾች ተርታ አንዱ ነው፡፡ ታህሳስ 6/2003 ይህችን አለም በስጋ ሞት ቢሰናበትም፤ በስፖርት አፍቃሪዎች ልብ ውሰጥ ግን እንደነገሰ ይኖራል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top