ጥበብ በታሪክ ገፅ

ዘመን አይሸሬው “ሳውንድ ትራክ”

ገና በልጅነቴ በሲኒማ አዲስ ከተማ ያየሁት አንድ ፊልም ለረጅም ዓመታት ውስጤ ተቀብሮ ነበር:: ወቅቱ መርካቶ በሚውሉ የሰፈራችን ጎረምሶች ገፋፊነት ከዚህ ፊልም ቤት ጋር ስተዋወቅ በጨለማ ውስጥ ስለሚታየው ጥበብ አንዳችም እውቀት አልነበረኝም:: ጎረምሶቹ የፊልሙን ታሪክ በገባቸው መጠን ሲተርኩልን ግን አፋችንን ከፍተን ነበር የምናዳምጠው::

 በዚያ ጨቅላነት ዘመን አንድ ፊልም ተመልክተን ወጣን:: የጓደኞቼን የአረዳድ ብቃት ባላውቀውም የፊልሙ ሀሳብ ሳይገባኝ በፊልሙ ሥር ሲሰማ የቆየው ክላሲካል ሙዚቃ ግን በውስጤ ነግሶ ቆየ:: በልጅነቴ ያንን የፊልም ሙዚቃ በፉጨት እያስመሰልኩ አንጎራጉር ነበር:: ረጅም ዓመታት አለፉ::

ወደ ሥራው ዓለም በገባሁ ወቅት ያ ሙዚቃ ከተደበቀበት የአእምሮዬ ጓዳ እየወጣ ፊልሙንና የድሮውን አዲስ ከተማ ሁኔታ ያስታውሰኝ ጀመር:: የሶስቱ ኮከቦች የፊት ገፅታ፣ የሽጉጥ አተኳኮስ ቂንጥ፣ እርስ በርስ ለመገዳደል የሚያደርጉት የጭካኔ ተግባር፣ የፈረሶቹ ኮቴ፣ የበረሃው ስቃይ ከዚያ ምርጥ ሙዚቃ ጋር እየተቀናበረ የተሻለ ስዕል ይፈጥርልኝ ገባ:: እንደዛም ሆኖ ግን የፊልሙን ርዕስ እና የአክተሮቹን ገሃዳዊ ማንነት ማወቅ አልቻልኩም::

ክላሲካሉን ሳስታውስ ለምን በተፈራረቀ ስሜት ውስጥ እንደምበጫረቅ አላውቅም:: ብቻ ደስ ይለኛል… ደግሞ በቦዘዘ ስሜት ርቄ እመነጠቃለሁ:: ርቆ በሄደው ስሜቴ ውስጥ ያለው እውነተኛ ድባብ በምን እንደሚመሳሰል እና በምን እንደሚለካ ማስረዳት ግን አልችልም:: የሆነ ሙዚቀኛ “Music is the answer. I don´t remember the question” ያለው ለእኔ ትክክል ይመስለኛል:: በጊዜው “ይህን ፊልም ፈልገህ እየው” የሚለውን ስሜቴ አደብ ማስገዛት አልቻልኩም:: ቢቸግረኝ ለቅርብ ወዳጄ ደረጄ ጉዳዩን ነገርኩት:: ፊልሙን ድሮ ቢመለከተውም ስያሜውን ማስታወስ አልቻለም::

እውነቱን ለመናገር በዚህ ፊልም መነሻነት ይሁን በሌላ በማላውቀው ጉዳይ ስጎረምስ ራሴን ከክላሲካል ሙዚቃ ፍቅር ተጣብቆ አግኝቼዋለሁ:: የአራት ኪሎ፣ የፒያሳ፣ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ መዝናኛ ቦታዎች ይመስክሩ:: በተለይ ማዘጋጃ በምሰራበት ወቅት በቡናም ሆነ በምሳ ሠዓቶች ምርጫዎቼ የነበሩት ክላሲካል ሙዚቃን የሚያንቆረቁሩ ሬስቶራንቶች ነበሩ:: ለመስክ ሥራ ክፍለ- ሀገር ስወጣ ክላሲካል ማዳመጥ ተፈጥሮን በአንክሮ ለማስተዋል እና ከሚስጥራቱ ጋር ለመፉተግ የሚያግዝ ሆኖ ይሰማኛል:: ቴአትር እስኪጀመር የሚሰሙ የተቀነባበሩ መሳሪያዎች የሀሳብ እከክን በሻወር አራግፎ የቀለለ ምናብ የማዘጋጀት ያህል የሚታይ ሚና አላቸው:: ቢሮ ቁጭ ብዬ አርቲክል ስቸከችክም ሆነ ቤት አርፌ ከሥነ-ጽሑፍ ጋር ስነጋገር መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎች እንደ ኳስ ያነጥሩኝ… እንደ ፊኛ ያንሳፍፉኝ… እንደ ጀልባ ያስቀዝፉኝ… የፈለጉበት ምናባዊ አለም በፍጥነት ያደርሱኝ ነበር:: ፕሌቶ በተጠጋጋ ቋንቋ ያለው ይሄንኑ አልነበረም:: “music gives a soul to the universe, wings to the minde, flight to the imagination and life to everthing”

 ከረጅም ጊዜ በኋላ ደረጀ ትዕዛዙ “ያን ነገር አገኘሁት እኮ! ” ብሎ ሰበር ሃሴት ይዞ ብቅ አለ:: ለዘመናት የተሰወረብንን ፊልም:: “ክሊንት ኢስትውድ የሚሰራበት ፊልም ነው፤ ስያሜው The good, the bad and the ugly ይሰኛል፣ ፈልገህ እየው” አለኝ::

 ደስታዬ ሎተሪ ከወጣለት ሠው ጋር የሚተካከል ነበር:: ጊዜውም በማደጉ ሌላ ዕድለኝነትን አንግቧል:: ምክኒያቱም በሲኒማ አዲስ ከተማ የታዩትን ፊልሞች ቢሮ ቁጭ ብሎ በኮምፒውተር መመልከት ይቻላልና:: ፊልሙ ያልታወሰኝ የረዘመ ስያሜ ስለነበረው ነው አልኩኝ እንደገና:: ነገሩ በኢለመንተሪ ደረጃ ፊልም የምናየው ርዕሱን አብጠርጥረን አልነበረም:: ተሰብስበን እንሄዳለን፤ ሬክላሙ ደስ ካለን ያለው ከሌለው ተበድሮ ልንገባ እንችላለን::

ይሄን ምትሀተኛ ፊልም ደስ እያለኝ ኮመኮምኩት:: አክተሮቹ እንደናፈቁኝ ዘመዶቼ እንዴት ናችሁ? እያልኩ:: ፊልሙን ካጣጣምኩ በኋላ ከራሴ ጋር በጥያቄዎች ተፋጠጥኩ:: ፊልሙ በውስጤ ተቀርፆ የቀረው በክላሲካሉ ብቻ ነው ወይስ በመላው ታሪኩ? ያኔ ታሪኩን ካልተረዳሁት ይህን ያህል በገዘፈ ደረጃ ለመደሰት በቂ ምክንያት ይፈጥርልኛል?ብቻ ክላሲካሉ ገዝፎ ጠብቆኛል… አሁን የፊልሙ አፅመ-ታሪክ በቅጡ ሲገባኝ በደራሲው ብዕር ተደንቄያለሁ… ብቻም አይደለም በአዘጋጁ ልቀት ተደምሜያለሁ:: ለዚህም ነው ሙዚቃው እና ታሪኩ እኩል ያምታቱኝ::

 ለምን ታሪኩ በአጭሩ አላሳያችሁም ?…

 ፊልሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የበቃው በፈረኘጆቹ አቆጣተር በ1968 ነው:: ታሪኩ የሚያጠነጥነው ደግሞ በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ሶስት የተለያየ ባህርይ ያላቸው (ጥሩ፣ መጥፎና አስቀያሚ) ሠዎች የገንዘብ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት መራራና አስቀያሚ ትግል ላይ ነው:: ገንዘብ እስከተከፈለው ድረስ ማንንም የሚገድለው የወታደር ሹሙ ኤንጅል አይስ (lee van cleef) ከህብረቱ ጦር ሠራዊት ወርቅ የሰረቀውን ቢል ካርሠንን እንዲገድል በቤከር ይቀጠራል:: የህብረቱ ጦር አባል የነበረውን ስቴቨንን ስለ ጉዳዩ ሲጠይቅ ራሡ ቤከርን እንዲገድለው አንድ ሺህ ዶላር በመስጠት ያግባባዋል:: ገንዘቡን ተቀብሎ ስቴቨንን ወዲያው ይገድለዋል:: ቤከር ጋ ተመልሶ በመሄድ ክፍያውን ከተቀበለ በኋላ እሡንም ይገድለዋል::

በሌላ በኩል ሠዎችን ለመግደል፣ በመዝረፍና ሴቶችን በመድፈር በመንግሥት የሚፈለገው ቱኮ (Eli Wallach) በብሎንዴ ከተያዘ በኋላ አንድ ስምምነት ይገባል:: ሽፍታውን ለያዘ ግለ ሰብ ይሰጣል የተባለውን 25 ሺህ ዶላር ተረክቦ እንደሚያስመልጠውና ገንዘቡን ለሁለት እንደሚካፈሉ:: በእርግጥም ሽፍታው በህዝቡ ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ግፎች ተዘርዝረው በአደባባይ ሊሰቀል ሲል ብሎንዴ (clint east wood) የታሰረበትን ገመድ በጥይት በመበጠስ ተያይዘው ይሰወራሉ:: ይህን መሰል ድርጊትም በሌሎች ከተሞች እየሄዱ በመፈፀም ገንዘቡን ይካፈሉ ነበር:: ሆኖም ቱኮ ይህን መሰል ጀብደኝነት ታክቶኛል ሲል ብሎንዴ በረሃ ውስጥ ትቶት ይሄዳል:: ቱኮ ተበሳጭቶ ቂም ያዘ:: ሊበቀለውም ይፈልገው ጀመር:: ብሎንዴ የወንጀለኞችን ገመድ በመበጠስ ሥራውን እየፈፀመ ሳለ በድንገት በቱኮ ይማረካል:: ያውን የበረሃ ችግር ሲመልስ መቶ ማይል በረሃ አስጉዞ ሊገድለው በፈረስ ጀርባ ላይ ሆኖ ይሳለቅበታል:: የስቃዩ ጫፍ ላይ መድረሱን የተገነዘበው ቱኮ ሊገድለው ሲወስን አንድ ሠረገላ እየቀረበ ሲመጣ ይመለከታል:: ሰረገላው በርካታ የሞቱ ወታደሮች እና በማጣጣር ላይ የሚገኘውን ቢልካርሠንን የጫነ ነበር::

 ካርሠን ሁለት መቶ ሺህ ዶላር የሚያወጣው ወርቅ የት መካነ መቃብር እንደሚገኝ መናገር ጀምሮ በውሃ ጥም መቀጠል አልቻለም:: ቱኮ ውሃ ሊያመጣለት ሲጣደፍ ብሎንዴ እንደምንም ተጠግቶ የመቃብሩን ስም ይሰማል:: ቱኮ ውሃ ይዞ ሲደርስ ቢል ካርሠን ሞቶ ነበር:: ጓደኛውን ሊገድለው በረሃ ድረስ ይዞት የመጣው ትኮ አሁን ደግሞ ብሎንዴ እንዳይሞት መንከባከብ ግድ ሆነበት:: ሁለቱ ጓደኞች እና ባላንጦች የተቀበረውን ሀብት ለመፈለግ ጉዞ ሲጀምሩ በህብረቱ ወታደሮች ይማረካሉ:: በምሩኮኞች ቆጠራ ወቅት የሟቹ ቢል ካርሰን ስም ሲጠራ ቱኮ “አቤት እኔ ነኝ” በማለቱ በኤንጄል አይን ትኩረት ትኩረት ውስጥ ይወድቃል:: የራስህ ስም ባልሆነ ስም ምን ፈልገህ ነው ሚስጥር አውጣ ተብሎ አሰቃቂ ድብደባ ከደረሰበት በኋላ የሚያውቀው ብሎንዴ መሆኑን በመናገሩ ኤንጀል አይስ ሁለት ዕቅዶችን ይነድፋል:: ትኮን ወደ መግደያ በባቡር ማሳፈር፣ ከብሎንዴ ጋ ደግሞ ወደ ሃብቱ ሄዶ እኩል ለመከፈል መስማማት::

ቱኮ በሚያስገርም ጥበብ ዝሆን የሚያህለውን ወታደር ገድሎ ይጠፋል:: ብሎንዴ የሹሙን ጠባቂዎች አንድ በአንድ ገድሎ ይሠወራል:: ቱኮ እና ብሎንዴ ከእንደገና ግንኙነት ገጥመው ኤንጅል አይስን ለመግደል ቢያደቡም ታዳኙ ይሰወርባቸዋል:: ወደ ወርቃማዋ ከተማ ሲገሰግሱ ራሳቸውን የርስበርሱ ጦርነት ወደ ተጋጋመበት ቁልፍ ቦታ ያገኙታል:: ጦርነቱ በተአምር ካልቆመ በስተቀር ወደሚያልሙበት የመቃብር ሥፍራ ለመሄድ መንገድ አልነበራቸውም:: ተደብቀው አንድ የጭካኔ ተግባር ይፈፅማሉ:: ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች መሃል የሚገኘውን ትልቅ ድልድይ በተቀጣጣይ ፈንጂ ማውደም:: ይሄኔ ብሎንዴ ቱኮን ለመፈተን በማሰብ የመቃብሩ ስም “አርክሳንተን ነው” ሲል ይነግረዋል:: ቱኮ አላስቻለውም የአንድ ተዋጊ ፈረስ ሠርቆ ወደ ቦታው ብቻውን ይገሠግሳል:: መካነ መቃብሩ ውስጥ ካካሄደው አድካሚ የፍለጋ ሩጫ በኋላ የተባለውን ስም አግኝቶ በእንጨት መቃብሩን ይቆፍራል:: ብሎንዴ በቦታው እንደደረሰ አፈሙዝ ወድሮበት በደምብ እንዲቆፍር አካፋ ይወረውርለታል:: ቆይቶ ኤንጅል አይስ ደርሶ ሌላ አካፋ ይወረውርና ብሎንዴም ጭምር እንዲቆፍር ይጠይቃል:: ብሎንዴ ሁለት ሚስጥራት ስላሉት ለግዴታው ተገዢ አልሆነም::

 አንደኛው ሚስጥር ትኮ እየቆፈረ ያለውን የሰው መቃብር የተሳሳተ መሆኑን ውስጡ ያለውን የሰው አፅም በማሳየት ማረጋገጥ ነበር:: ወርቁ ያለበትን መቃብር ድንጋይ ላይ ይፅፍና በተኩስ የሚያሸንፈው ሰው መውሰድ እንደሚችል በመናገሩ ሶስቱም ትሪያንግል በሆነ ቅርፅ ወደኋላ ለተኩስ ማፈግፈግ ይጀምራሉ:: አንዱ ከአንዱ ጥይት እንዴት መትረፍ እንደሚችል ፍርሃት እና ድንጋጤን የሚያሳብቁ አይኖች ይታያሉ:: ብሎንዴ ግን ሁለተኛውን ሚስጢር በመጠቀሙ የኤንጄል አይስን እጆችና ፊት ብቻ ነበር የሚከታተለው:: በመጨረሻ ኤንጀል አይስ በብሎንዴ ተመትቶ ይወድቃል:: ትኮ ለመተኮስ ጥረት ቢያደርግም ሽጉጡ ውስጥ ጥይቶች አልነበሩም:: ብሎንዴ (ደራሲው ሳይሆን ቱኮ ያወጣለት ስም ነው) ይህን ያደረገው የመቃብሩን ስም ከነገረው አንድ ቀን በፊት ሌሊት ላይ ነበር:: ያልታወቀ (unknown) የተባለው መቃብር ተቆፍሮም ሃፍቱ መውጣት ችሏል:: ቱኮ ወርቁን በደስታ እየበተነ ሲፈነጥዝ ብሎንዴ ለመታነቂያው ገመድ እያዘጋጀለት ነበር:: የገመድ ብጠሳውን ስራ በእሱ እንዲጀመር ሁሉ ለእሱ ሲጨርስ ፊልሙ ያልቃል::

 ይሄን ፊልም ባደገ ህሊናዬ ገምግሜ የሁሌም ምርጥ ነው ያልኩት በአምስት መሰረታዊ ጉዳዮች ይመስለኛል:: ከላይ ጨረፍ በደረግኩት ግሩም ውስብስብ ታሪኩ፣ የማይረሳ ገፀ-ባህርያትን በመፍጠሩ፣ የካሜራ አቀራረፁ፣ የመቼት ምርጫው እና ማጀቢያ ሙዚቃው (sound track) ናቸው::

 በዚህ ፊልም ባልተለመደ መልኩ ሶስት አክተሮች እኩል የጀግንነት ድርሻ ተላብሰው ይታያሉ:: ፊልሙ ከጅማሬው እስከፍፃሜው ዋና ለሚባል አክተር ከማድላት (The Good) ይልቅ በእኩል ደረጃ የሁሉንም ተግባራት ሲያሳይ ይታያል:: ሶስቱም ሃገሪቱ ለገባችበት የርስ በርስ ጦርነት ደንታ ሳይኖራቸው ሃብት ለማከማቸት ይተጋሉ:: ሶስቱም ባህርያቸውን በአይረሴ መልኩ ተጫውተዋል:: የሚገደለውን በጭካኔ ገድለዋል:: የሚዘረፈውን ያለ ርህራሄ ሰብስበዋል:: በመንግስት፣ በሃይማኖት በህብረተሰቡና በራሳቸው ህሊና ላይ ክህደት ፈፅመዋል:: እርስ በርስ ሊጠፋፉ ጦር ተማዘው መሰሪነታቸው ታድጓቸዋል:: የገፀ-ባህርያቱ ንግግር ታሪኩን በፍጥነት የሚያራምድ ብቻ አይደለም:: ምፆታዊ፣ አላጋጭ የበላይና ባለግዜነትን ጠቋሚ ጭምር ነው:: ለምሳሌ ያህል ቱኮ ብሎንዴን እንዲህ ይለዋል:: “ጓደኛዬ በዚህ ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ:: በአንገታቸው ገመድ የሚያስገቡ እና ይህን ገመድ በመበጠስ ሥራ የሚተዳደሩ” ብሎንዴ በፊልሙ ማብቂያ አከባቢ ትኮን እንዲህ ሲል ይሰማል “ጓደኛዬ በዚህ ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ:: የተቀባበለ ሽጉጥ ያላቸው እና መሬት ቆፋሪዎች፣ እናም መሬቱን ቆፍር!”

ካሜራ በዛ ባለ መልኩ ቀርቦ ሲቀረፅ (close up) ያየሁት በዚህ ፊልም ላይ ነው:: በዚህም ምክኒያት የገፀ-ባህርያቱን ፍርሃት፣ ድፍረት፣ ስቃይ ጭካኔ እና መሰሪ ሀሳብ ሁሉ በቀላሉ እንመለከታለን:: ይህ ልዩ ጥበብ ተመልካቹ ታሪኩን በጉጉት እና በስሜት እንዲመለከት ያስገድደዋል:: በተቃራኒው በሩቅ ቀረፃው (Long shot) ፊልሙ የተሰራበት ውብ መልክዓ ምድራዊ ገፅታ በግድ እንድናደንቅ ያደርገናል::

ሌላው እና ዋነኛው ነጥብ የሙዚቃው (sound track) ገዳይነት ነው:: በልጅነቴ የመሰጠኝን ይህን ሙዚቃ ባደገው ምናቤ ለማጣጣም ሞክሬያለሁ:: አዘጋጁ ሙዚቃውን ከሶስቱ ዋና ገፀ-ባህርያት ድርጊት አንፃር መጠነኛ በሆነ መልኩ ለመለያየት ጥረት ማድረጉን አንብቤያለሁ:: ደግሞም ትክክል ነው:: ብሎንዴ ከሚፈፅማቸው ተግባራት በኋላ የሚሰማው ክላሲካል ቀጠን ባለ የዋሽንት ድምፅ የታጀበ ነው:: ከኤንጅል አይስ ተግባራት በኋላ በሚከተለው ሙዚቃ ኦካሬና (ocarina) ከተባለው የኢጣሊያ መሳሪያ ጋር የተያያዘ ይመስላል:: ከቱኮ ተግባራት በኋላ የምንሰማው ክላሲካል የሰው ድምፅ አለበት::

በእኔ እምነት ይህ መሳጭና ያማረ ሙዚቃ ፊልሙን በታላቅነት በማቆም ትልቅ ሚና ተጫውቷል:: የተመልካችን ሙሉ ትኩረት ለመሳብ… ስሜት ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር እንዲሁም የገፀ-ባህርያትን ድርጊት ወይም ውስጣዊ ሃሳብ ለማንፀባረቅ አጋዥ ሆኗል::

ጣሊያናዊው ኢኒዮ ማርኮኒ ያቀነባበረውን ይህን ውብ ክላሲካል ሙዚቃ (sound track) ዛሬም ደጋግሜ እሰማለሁ:: ከወዲያኛው ዓለም ምን እንደምቋጭ አላውቅም:: ሀሴት ከማድረግ ውጪ:: ይህን ዘመን አይሸሬ ክላሲካል ፊልም ዛሬም ደጋግሜ አያለሁ:: ዳይሬክተሩን ሰርጂዮ ሊኦንን እያመሰገንኩ:: ጥሩ፣ መጥፎ እና አስቀያሚ የተባሉ ሶስት ታላላቅ አክተሮችን እያደነቅኩ:: ይህ ድንቅ ፊልም የኦስካር ሽልማትን አለማግኝቱ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው::

ከዚህ የፊልም አመዶች /ሶስት አክተሮች/ ውስጥ ዛሬ በህይወት ያለው ክሊንትስቱድ ብቻ ነው:: ልሎቹ ምስላቸውንና የፊልሙን ታሪክ ለታሪክ አስቀምጠው አልፈዋል:: በህይወት ለው አዛውንቱ ጎበዝ በዚህ ዓለም ሁለት ዓይነት ዳኞች አሉ:: ለእውነት የቆሙና በእውነት ላይ የቆሙ:: ወደ ሀገራችን ስንተረጉመውም ሁለት ዓይነት የፊልም አፍቃሪዎች፣ ሁለት ዓይነት የፊልም ፀሐፊዎች፣ ሁለት ዓይነት የካሜራ ሙያተኞች እና ሁለት ዓይነት የፊልም አዘጋጆች አሉ:: ይህን ታላቅ ፊልም ያላዩ::

1 Comment

1 Comment

  1. አ. ገ

    April 26, 2020 at 4:56 pm

    የመጨረሻው ሀሳብ ስለተቆረጠ አጨራረሱን ስሜት አልባ አድርጋችሁታል ። መሆን የነበረበት ‹ ይህን ታላቅ ፊልም ያዩ እና ይህን ፊልም ያላዩ › በሚል ነበር ። ይህ ብቻ አይደለም ፣ ስራው ውስጥ ብዙ የተቆረጡ ሀረጎች አሉ ። የቃላት ስህተቶች በርካታ ናቸው ። ታይፕ ከተደረገ በኋላ ዞር ብላችሁ እንደማታዩት በሌሎችም አርቲክሎቼ መረዳት ችያለሁ ። እባካችሁ ፕሩፍ ሪዲንግ መሰረታዊ ሙያ መሆኑን ተረዱ ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top