ስርሆተ ገፅ

ወግ ቡና

በስራ የተወጣጠረ አዕምሮን ፈታ ለማድረግ የተለያዩ ልምዶች እንዳሉ ይታወቃል:: የአፍታ ሸለብታ /Nap/ ሻይ፣ ቡና፣ ማኪያቶ ወዘተ ሊሆን ይችላል:: ቡናን እያጣጣሙ ከንባብ ጋር መጎዳኝት ልምዳቸው ያደረጉ ሰዎችም እንዳሉ ማሰብ ይቻላል:: ሳያነቡ መዋል ወይም ማደር በሕይወታቸው የሆነ ነገር እንደጎደለባቸው የሚሰማቸው እንዳሉም እንገነዘባለን:: ስለ ንባብና ሱስ ስናነሳ አንድ በአይነቱ አዲስ የሆነ አገልግሎት አሰጣጥ ምሳሌነቱ ጎልቶ ታየን:: ከመስቀል አደባባይ ወደ ጎተራ መስመር በሚያስኬደው መንገድ ላይ ከጠመንጃ ያዝ ንግድ ባንክ ወረድ ብሎ ባለ ህንጻ አንደኛ ፎቅ ላይ ነው ይህ አገልግሎት የሚሰጠው:: በስድስት ብር ቡናን እያጣጣሙ ጋዜጣ፣ መጽሔትም ሆነ መጽሐፍ ያለ ገደብ በነጻ የሚያነቡበት የአገልግሎት አሰጣጥ ያለው ነው ቤቱ:: ንጹህ ነች ቤቷ:: ሰፊ በረንዳም አላት:: “ቡና ወግ” ይባላል:: ይህን አገልግሎት የምትሰጠው ወጣት ሰላማዊት ገብረመስቀል፤ የቡናና የንባብ ፍቅር የህይወት መስመሯን ወደ መልካም እየቀየሩት ነው:: እንዴት? ከወጣቷ ጋር ባደረግነው አጭር ቆይታ ይህ ጥያቄ ይብራራል:: ከአነሳሷ እንጀምር::

ሰላማዊት፦ በአንድ ቀን ተነስቼ ያደረኩት አይደለም:: የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ “አዲስ ቤተ መጽሐፍ ቤት ” የሚባል ግሎባል አካባቢ ነበር:: ያንን ቤተ መጽሐፍ በጣም አብዝቼ ነበር የምወደው:: አነብበት ነበር:: አጠናበት ነበር:: እኔነቴን ነው የለወጠው:: ከንባብ ጋር ያስተዋወቀኝ ቤት ነው:: ግን ምክንያቱን ባላወኩት ሁኔታ ቤተ መጽሐፍቱ ተዘጋ:: እኔ ግን ከንባብ ጋር አንዴ ተቆራኝቻለሁና ንባቤን በቤተ መጽሐፍቱ የንባብ ቆይታዬ አነባቸው የነበሩ መጽሐፎች ለመልካም ነገር ያነሳሱኝ፣ ያበረታቱኝ፣ ያጽናኑኝም ነበር:: አንባቢ ስሆን ደግሞ መጻሕፍት መሰብሰብ ጀመርኩ:: በስጦታና በልዩ ልዩ አጋጣማዎች የማገኛቸውን መጻሕፍት በክብር መያዝ ስራዬ ሆነ:: ቀጠልኩ:: ግን ያ ቤተ መጽሓፍት መዘጋቱ ይቆጨኝ ጀመር:: በውስጤ ግን እንደሱ አይነት ቤተ መጽሐፍት በግሌ ቢኖረኝ እያልኩ መመኘቴ አልቀረም:: እና በቤቴ መጽሐፍቶች በበዙ መጠን ያ ሃሳቤ እረፍት ነሳኝ:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ በሱስ ተጠመድኩ::…

ታዛ ፦ የምን ሱስ?

ሰላማዊት ፦ በቡና ሱስ:: ከፍተኛ የሆነ ሱስ፡ ሱሱ የቡና ቅምሻ እንድማር አደረገኝ:: ቡናን በደንብ ማወቅ ስጀምር በሁለት ነገር ፍቅርና ሱስ መውደቄ ታወቀኝ:: በቡና እና በመጻሕፍት:: እነዚህን ሁለት ነገሮች እያጣጣምኩ ሕይወቴን እንዴት መምራት እንዳለብኝ ሳውጠነጥን “ወግ ቡና” መጣልኝ:: ቡና እየሸጡ መጽሐፍትን በነጻ ማቅረብ:: አካባቢን መረጥኩና ስራዬን ቀጠልኩ:: ይኸው እንደምታየው ዛሬ ጥሩ እየተለመደልኝ ነው::

ታዛ ፦ እንደዚህ አይነት አገልግሎት አልተለመደም፤ ስትጀምሪው ስጋት አልነበረብሽም?

ሰላማዊት ፦ ምንም አልሰጋሁም፤ ሰዉ ቡና ባይጠጣ ቢያንስ ያነባል:: በዚያ አልከስርም:: እኔ አላማዬ ብዙ ነው:: አዲስ አበባ ውስጥ ቢያንስ ከተቻለ 10 ቅርንጫፎች ኖረውኝ ሰዉ በንባብ ሲዝናና ማየትን እመኛለሁ:: ባለችው ትንሽ ጊዜ እንኳ ጥቂት ቁም ነገሮችን ከንባብ ቢያገኝ መልካም ነገር አድርጊያለሁ ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል:: ቢያንስ ትንሹ ህልሜ ይህንን ማሳካት ነው:: ሌላው ሌላው ይቀጥላል:: ዓለም ላይ ያሉ ትላልቅ፣ አዳዲስና ሊገኙ አይችሉም ተብለው የሚታሰቡ መጻሕፍትን ይዞ መገኘት ነው ህልሜ::

ታዛ ፦ አገልግሎቱን መስጠት የጀመርሽው መቼ ነው፤ የተገልጋዮችሽ ሁኔታስ?

ሰላማዊት ፦ ካለፈው መስከረም ጀምሮ ነው ስራ የጀመርኩት:: በቅጥር የሚያግዙኝ ሰራተኞችም አሉኝ:: ደንበኞች ከእለት ወደ እለት እየጨመሩ ነው:: የሚሰጠኝን አስተያየት በአግባቡ እጠቀምበታለሁ:: እንደሚታወቀው ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች እና ሌሎች የገንዘብ ዝውውር እና የአገልግሎት አሰጣጥ የሚበዛበት አካባቢ ስለሆነ ሰው አይጠፋም:: በተለይ ዋናው ስራ በምሳ ሰዓት እና ወደ ማታ አካባቢ ነው::

ታዛ ፦ ይህን አገልግሎት ስትጀምሪ አጋዥ ነበረሽ

 ሰላማዊት ፦ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ተመካክሬያለሁ:: ቀጥይበት ነው ያሉኝ:: በነገራችን ላይ ያተርፋል ብዬ የገባሁበት አይደለም:: ለዚያ ነው ሌላ ስራም የምሰራው:: ከትርፍ አኳያ ገና ነው:: እሱ አላጓጓኝም:: ስጀምረው እንዳልኩህ ማንም ቢሆን ቡና እየጠጣ ፈቃዱ ከሆነ በቤቱ ካሉ ሼልፎችና ጠረጴዛዎች አንዱን መጽሐፍ፣ መጽሔት ወይም ጋዜጣ እንዲያነብ መጋበዝ ነው::

ታዛ ፦ ከተጠቃሚዎች የሚደርሱሽ አስተያየቶች አሉ?

ሰላማዊት ፦ አሉ በደንብ:: ምሳ ባዘጋጅ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት እንደምችል የጠቆሙኝ እነሱ ናቸው:: በእርግጥም ትክክል ነበሩ:: ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ያሉ ሰራተኞች ያላቸውን የምሳ ሰዓት ሳያባክኑ መጠቀም የሚችሉት ምሳ የበሉበት አካባቢ ቡና ሲጠጡ ነው:: ያንን ቀለል ባለ ምሳ አቅርቦት ተግባራዊ እያደረኩ በመሆኑ ከወራት በፊት ከነበሩት ደንበኞቼ አንጻር ዛሬ እየበዙ መምጣታቸው እየታየ ነው:: ከቤት ኪራዩ እና ከተለያዩ ወጪዎች አንጻር ኪሳራ ውስጥ ይከተኝ የነበረው ልቤ የፈቀደው ስራ አሁን በጥሩ መንገድ እየሄደ ነው::

ታዛ ፦ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያመጣው አንዱ ነገር አንባቢን ከወረቅት ንባብ ወደ ኮምፒውተር ንባብ መቀየር ነው፤ ይህ ስራሽ ላይ ተጽእኖ የለውም::

ሰላማዊት ፦ የለውም:: በወረቀትም ሆነ በኮምፒውተር ማንበብ ልዩነት የለውም:: ሁለቱም እውቀትና መረጃ ነው የሚሰጡት:: አለፍ ሲልም ያዝናናሉ:: ቴክኖሎጂ ያመጣውን መገደብ አይቻልም:: እንዲያውም ነገሮችን አቅልሏል:: የሚገርመው ግን ሶሻል ሚዲያን ሰው የሚጠቀመው ለንባብ አይደለም፡ ለጥቃቅን መረጃና ለፎቶ ልውውጥ ነው:: ስለዚህ የወረቀት ንባብ በእኔ እምነት የሚገታም፤ የሚቀነስም አይደለም::

 ታዛ ፦ የቡና ሱሰኛ ነኝ ብለሺኛል፤ ምን ያህል ትጠጫለሽ?

ሰላማዊት ፦ ፊት ላይ ብዙ ነበር የምጠጣው አሁን ትንሽ አሞኝ ቀንሻለሁ:: አንደኛ ጠጪ ነበርኩ::

 ታዛ ፦ የህመምሽ ምክንያት ቡና እንዳይሆን?

ሰላማዊት፦ አዎ፤ ጠዋት ጠዋት እንኳ ከእንቅልፌ ስነሳ በባዶ ሆዴ እስከመጠጣት የደረሰ ሱስ ውሰጥ ገብቼ ነበር:: ቀን ላይ አይቆጠርም:: ውሃ እንኳ እንደ ቡና አልጠጣም ነበር:: በጣም በዛና ራሴን ማዞር ሁሉ ጀመረኝ:: እየጎዳኝ ሲመጣ ነው በሀኪም ምክር የቀነስኩት:: አሁንም ግን መጠኑን ብቀንስም እጠጣለሁ::

 ታዛ ፦ ምን ያህል መጻሕፍት አሉሽ?

ሰላማዊት ፦ ውይይ መቁጠር አልችልም:: ግን በቂ ናቸው ብዬ አላስብም:: 123 መጻሕፍት፣ ጥቂት ጋዜጣና መጽሔቶች ይዜ ነው የጀመርኩት:: ከዚያ በኋላ ስጦታ የሚሰጡኝ አሉ:: በተለያየ ሁኔታ የሚጠፉብኝም አሉ:: ዋናው ዓላማዬ ይህንን ስራ ወደ ትልቅ ማሳደግ ስለሆነ፤ ለዚህም ድጋፍ ብጠይቅ የሚተባበሩኝ ብዙ እንደሆኑ ይሰማኛል:: ቤቴ ከሚቀመጥ ብሎ የሚለግስ ብዙ ቀና አሳቢ እንዳለ እረዳለሁ እንደ ሁኔታው ይህንን ለማድረግ አንድ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ሃሳብ አለኝ::

ታዛ ፦ በቡና አገልግሎት መስጪያሽ አንድ አቅጣጫ ግርግዳ ላይ አንድ በጠመኔ የተሞነጫጨረበት ጥቁር ሰሌዳ አየሁ፤ ምንድነው ?

 ሰላማዊት ፦ እሮብና አርብ የውይይት መድረክ አዘጋጃለሁ:: ስራ ሲበዛብኝ የአርቡን ለጊዜው አቆይቼዋለሁ፤ እሮብ እሮብ ግን ቀጥሏል:: የአርቡ “ፓሽን ናይት” ነው የሚባለው፤ በሁለት ሳምንት አንዴ ደራሲያን፣ ጸሐፊዎች ስለ ስራቸው ያወጉናል:: አምስት ጸሐፊዎች በዚህ መልኩ ልምዳቸውን ካካፈሉን በኋላ አልዘለቅኩም:: የእሮቡ ግን ቀጥሏል:: ከማርኬቲንግ ሙያተኞች/ professionals / ጋር በመተባበር ቢዝነስ ላይ ያተኮረ ውይይትና ገለጻ አለ:: “ወግ ቢዝ” ይሰኛል ፕሮግራሙ:: በዚህ በዚህ “ወግ ቡና” ከደንበኞች ጋር ጥሩ ትውውቅ ከማድረግ በዘለለ ሌሎችም የእርስ በእርስ መማማር እንዲፈጥሩ አስችሏል:: የተወሰነ መግቢያ ስላለውም ለጉዳዮች የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እንዲሆን ረድቷል:: ስነ ጽሑፉንም ሁኔታዎች ሲስተካከልልኝ በቅርቡ እመለስበታለሁ ብዬ አስባለሁ:: እንደተለመደው ጃዝ እንዲኖረው ይደረጋል::

ታዛ ፦ አገልግሎትሽን ለማስተዋወቅ የምትጠቀሚባቸው መንገዶች አሉ፤

 ሰላማዊት ፦ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን እጠቀማለሁ:: ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ቲውተር ላይ ወግ ቡና አለ:: ቡናና መጽሐፍ በጥሩ እየተዋወቁ ነው:: የክፍያ አገልግሎት አጠቃቀምን በተመለከተ ማስተዋወቁ ላይ ገና ነኝ::

ታዛ ፦ የተለያዩ ፎቶዎችም በቤቷ ውስጥ ይታያል፤ የታዋቂ ሴቶች ደግሞ በዝቷል፤ ምክንያት አለሽ?

ሰላማዊት ፦ እሱ ብዙ ታሪክ አለው፤ በእኔ እምነት የአገራችን የሴቶች ችሎታና አቅማቸው ገና አልታወቀም፤ አልተገለጸም ይህንን ለማድረግ ደግሞ ገና ብዙ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል፤ እሱ ራሱ ሌላ ታሪክ ስለሆነ ብንዘለውስ…በጥቅሉ ግን እነዚህ ፎቶዎች ደንበኞቼ ጥሩ የዓይን ማረፊያ እንዲኖራቸው ጭምር ያደረኩት መሆኑ ቢታወቅልኝ፤

ታዛ ፦ መልካም፤ ትምህርት እንዴት ነሽ?

ሰላማዊት ፦ በማርኬቲንግ ዲግሪ አለኝ፤ አሁን ማስተርሴን ልቀጥል እያኮበኮብኩ ነው:: በዚሁ ሙያ በግል እየሰራሁ ነው:: ግድ መኖር ስላለብኝ መተዳደሪያ ነው:: ይህንን ስራ ለመጀመር መጀመሪያ ሌላ ስራ መስራት ነበረብኝ ምክንያቱም መነሻ ካፒታል ያስፈልጋል:: ማርኬቲንጉ ብር ያስገኛል፤ ይህ ደግሞ የምወደው ስራ ነው፤ ሁለቱን እያቻቻልኩ ነው:: ከዚያ ይልቅ ወግ ቡና በደንብ ተጠናክሮ መተዳደሪያዬም ቢሆን እመርጥ ነበር፤፤ ያንን ለማድረግም እየጣርኩ ነው:: በጣም የምትወዳቸው ነገሮች ደግሞ ብር አያስገኙም…::

ታዛ ፦ ከአማርኛ መጻሕፍት ለስሜትሽ ቅርብ የሆነው እንዴት ያለ ነው? ከደራሲያንስ እነማንን ታደንቂያለሽ?

ሰላማዊት ፦ የታሪክና የስነ ልቦና መጻሕፍት ይመቹኛል:: የእመጓ ጸሐፊ አለማየሁ ዋሴ እና የታወር ኢን ዘ- ስካይ ጸሐፊ ህይወት ተፈራ ስራዎች ይማርኩኛል:: ከውጪ አብዝቼ የምወደው ፓውሎ ኮሎን ነው:: መንፈሳዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ነው ትኩረቱ::

 ታዛ ፦ ከንባብ ጋር በተገናኘ የምታደንቂው ሰው ይኖር ይሆን?

 ሰላማዊት ፦ መአዛ ብሩን፤ ምክንያቱም ሳታነብ እንደዚያ አይነት ጥያቄ ልትጠይቅ፣ ልታግባባ፣ ነገሮችን ልታብላላና ሌሎች እንዲረዱ ማድረግ አትችልም:: በሕይወቴ የእሷን ያህል የማደንቀው ሰው ያለ አይመስለኝም:: እሷ ለብዙ ነገሮች አነሳስታኛለች:: በፍቅር ነው የምወዳት:: እንደሷ አይነት ሰው መሆን ይቻላል የሚል አስተሳሰብ አለኝ::

 ታዛ ፦ ምን ያህል መጻሕፍት አንብቢያለሁ ብለሽ ትገምቻለሽ?

ሰላማዊት ፦ ዉዉዉ! አላውቀውም:: እንዲያው በደፈኗው ብዙ ቢባል ይሻላል:: ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ አነባለሁ:: ግን ገና ላነባቸው የሚገባ ብዙ ብዙ መጻሕፍት እንዳሉ ይሰማኛል:: በክረምት ወቀቅት በተለይ በየሳምንቱ ቢያንስ አንድ አንድ መጸሕፍት አነባለሁ:: በጣም አንባቢ የምባልም ሰው ግን አይደለሁም::

ታዛ ፦ ከስራሽ ጋር በተገናኘ ወደፊት ብዙ ቅርንጫፎች መክፈት ሃሳብ እንዳለሽ ነግረሽናል፤ በሕይወት ጉዞሽ ሌላ ልታሳኪ የምትፈልጊው ነገር ካለ?

 ሰላማዊት ፦ ይህንን አሳካለሁ ብዬ ግብ ማስቀመጥ፣ ራሴን ማስጨነቅ አልፈልግም፤ ማሰብ እንጂ ካልሆነ ብሎ መሟሟት እኔ ዘንድ የለም:: የሕይወት ግቤ ራሱ ተፈጥሯዊ መንገድ አለው:: ግን እራሴን ማወቅ እፈልጋለሁ:: ሌላ ነገር ለማወቅ በጣርኩ ቁጥር ራሴን እያወኩ ነው የምመጣው:: ለካ ይህንን ማደረግ እችላለሁ የሚል ጥያቄና መልስ ውስጤ ይመጣል:: ከአሁን በኋላ የሚያጓጓኝ ነገር ይበልጥ ራሴን ማወቅ ነው:: ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው መሆን እፈልጋለሁ:: ቢያንስ ምንም ሳልሰራ መሞትን አልፈልግም::

ታዛ ፦ አዲስ አበባ ውስጥ ጨርቆስ ተወልደሽ እንዳደግሽ ሰማሁ፤

ሰላማዊት ፦ አዎ ትክክል:: በጣም የምወደው አካባቢ ነው:: ጥሩ የልጅነት ጊዜን አሳልፊያለሁ:: ልጅ ሲያጠፋ ወላጆች ካላዩ በጎረቤት አባትና እናቶች ይቀጡ ነበር:: እውነተኛ ጉርብትና አለ:: መጥፎ ነገር የለም:: ጨርቆስ ሰፍር አንዳንዶች ሲያጥላሉት ስሰማ ያናድደኛል:: የተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ አሉ፡ በጣም በድህነት የተጎዱ እንዳሉ ሁሉ፤ ሀብታሞችም አሉ:: መከባበርና መፋቀርም አለ:: እኔ እስከማውቀው በልጅነቴ ዱርዬ ተብለው የሚፈሩ እንኳ ትንሽ አምሽቼ ካገኙኝ “ምን ታደርጊያለሽ?” ብለው ቤቴ ይዘውኝ ሲገቡ አውቃለሁ::

ታዛ ፦ ቤተሰባዊ ሕይወትሽስ?

ሰላማዊት ፦ ትዳር አለኝ፤ አንድ ልጅ አለን:: ባለቤቴም በምሰራው ስራ ሁሉ ስለሚያበረታታኝ ውጤታማ እንድሆን ረድቶኛል::

ታዛ ፦ ለወጣቶች መልክት ካለሽ?

 ሰላማዊት ፦ ጥቂት ባነበብን ቁጥር ማንነታችንን እናውቃለን:: ምን እንዳጣን ይገባናል:: ሳናውቀው አስተሳሰባችን ይቀየራል:: ስለዚህ ወጣቶች አንብቡ:: ትጠቀማላችሁ ነው የምለው:: የግድ ቡና ጠጡ አልልም::

 ታዛ ፦ በጣም አመሰግናለሁ፤ በርቺ!

 ሰላማዊት ፦ እኔም አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top