ከቀንዱም ከሸሆናውም

ችቦ አይሞላም

መቼም የሰው ልጅ ፍላጎት እና ባህሪ የተለያየ ነው:: የጀርመኗ ሚቼሌ ኮይቤኬ በጥረቷ የአለማችን ወገበ ቀጭን ተሰኝታለች:: የዚች ሴት ወገብ 16 ኢንች ተለክቷል:: አመጋገቧ በእጅጉ የተመጠነና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው::ሚቼሌ ኮይቤኬ በቀን 10 ጊዜ በጣም ጥቂት ምግብ ላመል ትቀምሳለች:: ምክንያቱም አንጀቷ በዛ ያለ ምግብ በአንድ ጊዜ የመሸከምም ሆነ የመቀበል አቅምም ቦታም ስለሌለው ነው:: ወገቧን የሚደግፍላት ቀበቶ መሳይ ነገር ፈረንጆቹ (corset) ይሉታል፤ ካልተጠቀመች መንቀሳቀስ አትችልም:: ሁለት ወዶ አይሆንምና ሚቼሌ ኮይቤኬ ከጤንነቷ ይልቅ ውበቷን መርጣ ይሄው የአለማችን ቁጥር አንድ ወገበ ቀጭን ተሰኝታለች:: ሚቼሌ የ24 አመት ወጣት ስትሆን፤ ወገቧን ከዚህም ባነሰ ለማቅጠን ቆርጣ ተነስታለች:: ይህች ወጣት ለ3 ተከታታይ አመታት ወገብ ላይ የሚታሰረውን የወገብ ማቅጠኛ ቀበቶ ታጥቃ ኖራለች::ስትተኛም ይህ ቀበቶ ከወገቧ አይለያትም:: “ወገቤን የእንስራ ወይም የጠርሙስ አንገት ሳላሳክል እንቅልፍ አይወስደኝም” ባይ ናት:: ይህ መሆኑ የሆድ እቃዎቿ አቀማመጥና አተነፋፈሷ ላይ ተፅእኖ እያደረሰባት እንዳለ ነው የተገለፀው:: ዶክተሮች ግን አስጠንቅቀዋታል:: “ከዚህ በላይ ወገብሽን ለማቅጠን የምታደርጊው ሩጫ መላ አካልሽን ሽባ (ፓራላይዝ) ያደርዋልና ይቅርብሽ” ብለዋታል:: ማስጠንቀቂያው ለሚቼሌ ምኗም አልሆነም::እናም ወገቧን የማቅጠን ትልሟን ገፍታበታለች:: ሲያጌጡ …. እንዳይሆን ነገሩ::

ፀጉረ ጥምጣሙ

የ25 ዓመት ወጣት ሳለ የቀጣይ ህይወቱን ገፅታ የሚቀይር ክስተት ተፈጠረ::ከዚያ ወዲህ ለ50 ዓመታት ከጓደኞቹና ከዘመድ አዝማዶቹ ደብቆትና ሸሽጎት የቆየው ታሪክ አሁን ላይ ይፋ ሆኗል:: ትራን ቫን አናቱ ላይ ለ50 ዓመታት አንዳች ነገር ተሸክሞ ኖሯል::

 ይህ ሸክሙ በሻሽና በስካርቭ ነገር ይሸፈናል:: ከሻሹና ከስካርቩ በስተጀርባ ምን እንዳለ ግን የሚያውቅ የለም:: “ፀጉር ሊሆን ይችላል” ብለው የገመቱ ግምታቸውን ከንቱ ያደረገው ደግሞ አናቱ ላይ የተቆለለው ነገር ግዙፍነት ነው:: “ፀጉርማ ሊሆን አይችለም” ብለዋል ገማቾቹ ::”እና ምን ሊሆን ይችላል?” የሚያውቁት ሰዎች ሁሉ ጥያቄ ነበር::

ከ50 ዓመት በኋላ እንሆኝ የቬትናማዊዉ ትራን ቫን ሚስጥር ይፋ ሆኗል:: ከአሁን በኋላ ሊሸሽገው አልቻለምና:: ትራን ቫን የ25 ዓመት ወጣት ሳለ እንደማንኛውም ሰው ፀጉሩ በማደጉ የተነሳ ለመቆረጥ ወደ ፀጉር ቆራጮች ዘንድ ያመራል::ተቆርጦና አምሮበት ወደ ጉዳዩ ይሄዳል:: ይሁንና ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ የትራን ቫን ጉዳይ ነብስ ግቢ ነብስ ዉጪ ሆኖ ሆስፒታል ይዘልቃል::እንደምንም ከሞት ይተርፋል::በኋላ ላይ ነገሩ ከፀጉሩ መቆረጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ደርሶበት ዳግመኛ ፀጉሩን ላለመቆረጥ ይወስናል:: በዚህም ፀጉሩን ለ50 ዓመታት ሳይቆረጥ ተሸክሞት ኖሯል:: በወጣ በገባ ቁጥር የሰውን ቀልብና ዕይታን ይስብ የነበረውና እሱም በአደባባይ ብዙም የማይታየው በጎረቤቶቹና በሚያውት ዘንድም “ምንድን ነው የተሸከመው?” እየተባለ ይታማ የነበረው ትራን ቫን በመሞቻው ዋዜማ ላይ 22 ጫማ(7 ሜትር አካባቢ) የሚረዝመውንና 23 ፓውንድ(ከ10 ኪሎግራም በላይ) የሚመዝነውን እንደዘንዶ የተጥመለመለውን ፀጉሩን “እነሆኝ ሸክሜን እዩልኝ፤ ጉዴንም እወቁልን” ብሎ ላይመለስ ወደማይቀረው ሄዷል:: ውድ ባለቤቱም ባሏ ከመሞቱ በፊት የተሸለተውን ፀጉሩን በክብር በመስታወት ሳጥን አስቀምጣዋለች:: በረብጣ ብር እንግዛሽ ያሏትን “አይሆንም የባለቤቴ ማስታወሻ ነው” ብላ ከብር ይልቅ የባሏን ማስታወሻ መርጣለች::ትራን ቫን ከመሞቱ በፊት ለ7 ዓመታት ላለፉት ፀጉሩን ውሀ ነክቶት እንደማያውቅ ባለቤቱ ተናግራለች::

ጥበበኛዋ ባሬስታ

ማንኛውም ሰው በተሰማራበት የሙያ መስክ ውጤታማ ለመሆን ከጣረ በዚያ ሙያ አንቱ መሰኘቱ አይቀሬ ጉዳይ ነው:: ጃፓናዊቷ ኩ ሳን በሙያቷ የታወቀች ባሬስታ ብትሆንም የተለየ ተሰጥኦ ባለቤትም ጭምር ናት:: ይህቺ ወጣት በሚገርም ሁኔታ የወፎች አፍቃሪ ነች::ኩ ሳን ታዲያ በምትሰራበት ካፌ አስገራሚ ነገሮችን እየከወነች የካፌውን ዝና ከፍ አድርጋለች አሁን ላይ ገበያውም ጨምሯል:: ለደንበኞቿ በምትሰራቸው ማኪያቶ ለወፎች ያላትን ፍቅር እየገለፀች ትገኛለች:: የተለያየ ከለር ያለውን የወተት ተዋፅኦ በመጠቀም በምታዘጋጀው ማኪያቶ የምትወዳቸውን የተለያዩየ የወፍ ዓይነቶች በመሳል ወይም ዲዛይን በማድረግ የካፌውን ደንበኞች እያስደመመች ትገኛለች:: በዚህ ውድድር በሞላበት አለም የኩሳን መላ አዋጭ ሳይሆን ይቀራል?

የጎዳናው ጠቢብ

ህንዳዊው ጁዲጊንግ ከራላ በምትባለው የህንድ ግዛት አንዱ ጎዳና ላይ ህይወቱን በልመና የሚገፋው ግሩም ድንቅ አርቲስት ነው:: ይህ ሰው ከልመና የተረፈችውን ጊዜውን የሚያሳልፈው የትላልቅ ህንፃዎችን ግድግዳና ግንብ አጥሮችን በስዕል በማስዋብ ነው:: የሚገርመው ደግሞ እነዚያን የሚገራርሙና የሚያምሩ ስዕሎች የሚስለው በውድ ዋጋ በሚገዙ የስዕል ቀለሞች ሳይሆን በቅርቡ ከሚያገኛቸው የአትክልት ቅጠሎች፣ ከሰልና ጭቃ ነው:: ያየውና የሚያደንቀው ሁሉ ራጁ እያለ ይጠራዋል:: ጁዲጊንግ የሚገርም የስዕል ጥበብ ባለቤት ሆኖ ሳለ ቆሻሻ ልብስ ለብሶና ምላጭ ያላየው ፂሙን አንዠርግጎ በከራላ ግዛት ኮላም ከተማ ጎዳና ላይ መገኘቱ አስገራሚ ክስተት ሆኗል:: ይሁንና ራጁ ላለፉት ስምንት አመታት የከተማዋን ነዋሪዎች በሚገራርሙ የስዕል ስራዎቹ እያስደሰታቸው ይገኛል::

ከዘረፋ ለማምለጥ

 በሜክሲኮ ከተማ የተደራጁና የታጠቁ ዘራፎዎች ነዋሪውን ክፉኛ አስመርረውታል:: በወንበዴዎቹ ንጥቂያ የተማረሩት እነዚሁ ነዋሪዎች አንድ ዘዴ ፈጥረው ከሞትም ከንጥቂያም ራሳቸው እያተረፉ ነው:: እነዚህ ዘራፊዎች በተለይም ስማርት ሞባይሎች ነብሳቸው ነው:: እናም ነዋሪዎቹ የውሸት (ፌክ) ስማርት ሞባይል ቀፎ በከተማዋ ላይ ይዘው እውነተኛውን ደብቀው በመዘዋወር እፎይታን እያገኙ ነው:: ሌቦቹ ስማርት ቀፎውን አገኘን ብለው ከሰው እጅ ላይ እየነጠቁ መሄዳቸውን ቀጥለዋል:: ነዋሪውም ሌቦቹ ሲመጡባቸው የውሸቱን ሞባይል በሰላም እያስረከቡ ይሄዳሉ:: በሜክሲኮ በጎዳና ላይ እንደልብ መራመድም ሆነ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርተ መጠቀም እጅግ አደገኛ እንደሆነ ይነገራል:: ዘረፋው በተለይም በትራፊክ መብራት ማቆሚያ ስፍራ ላይ ሞቅ ያለ ነው:: በዚህ ምክንያት የውሸት ሞባይሎች ግዢ በሜክሲኮ መድራቱ እየተነገረ ነው:: እዚህ እኛምጋ ዘረፋው ከፍቷልና እንደ ሜክሲኮ ነዋሪዎች የሆነ መላ ብንፈጥርስ ምን ይለናል ጎበዝ?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top