የጉዞ ማስታወሻ

ትዝታ ሲጨለፍ

ብዙ ነገር ሳትፈልጉ የምታዳምጡበት ቦታ በእርግጠኝነት ልንገራችሁ? ፀጉር ቤት ነው- የወንድ:: የሴቶቹን ስላልገባሁበት አላውቀውም::

ፖለቲካ የሚተነተንበት፣ ስፖርት የሚተችበት፣ ኪነ-ጥበብ የሚብጠለጠልበት፣ ትዳር የሚገመገምበት፣ ፋሽን የሚታይበት፣ ሚስጢር የሚዘከዘክበት፣ ቀልድ የሚፈረክበት… ብቻ ሌላኛው ፌስቡክ ነው ቢባል ተቃዋሚ አይኖርም::

አንድ ደምበኛ አለኝ:: በሳምንት አሊያም በ15 ቀን ብቅ ብዬ ፀጉሬንም ቀልቤንም ተሸልቼ እሄዳለሁ:: እመለሳለሁ:: በሚያዝናናው ተዝናንቼ፣ በሚያሳዝነው አዝኜ፣ በሚደንቀው ተገርሜ፣ በሚያሳስበው ደንግጬ መውጣቴ የዘወትር ተግባሬ ነው::

አንድ እሁድ ቀን ተራዬ ደርሶ ወንበሩ ላይ ፌጥ አልኩ:: ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ቆራጩ ሥራ ጀመረ:: ዝምታ ሰፍኗል:: ሬድዮ ብቻ ዘፈን ይዘፍናል::

 “ዛሬ ወሬ የለም እንዴ?” አልኩት:: “እንዴት ሆኖ” ብሎ ስዓቱ እስኪደርስ ጠብቅ አለኝ:: ሰው ይገባል:: ይወጣል:: ሰላምታ ልውውጡ ቀጥሏል:: ከግማሽ ሰዓት ቆይታ በኋላ አንድ ወጣት ፊቱ ፍክት ብሎ መጣ:: ቆራጩም ፈገግ ብሎ ተቀበለው:: ሰላምታ ተለዋወጡ::

“እሺ… እንዴት ሆነ ተሳካ” ቆራጩ

 “እንዴታ!” ወጣቱ መልሰ

 “ተፈተንክ?” ቆራጩ ጥያቄ ደገመ::

 “ገንዘብ ውሎ ይግባ …” ብሎ ደረቱን ነፋ አድርጎ መለሰ::

 “ኦ! ኮንግራ…” ቆራጩ ወጣቱን በትክሻው መታ አደረገው:: ሁለቱም ከዚያ በኋላ የሚያወሩት ብዙ አልገባህ አለኝ:: ኮድ አዘል ወሬ ነው:: ይሳሳቃሉ:: ወጣቱ ልጅ ፀሐይ ልሙቅ ብሎ ወንበር ይዞ ውጪ ወጣ:: መጥቶ ሰላም የማይለው ሰው የለም:: ደስታው ጥግ ድረስ ነው:: ሁሉም ይጨብጠዋል::

ይሄን ጊዜ ነገሩን ከነከነኝ:: ምን ያህል ትልቅ ጉዳይ ቢሆን ነው ሀበሻ ሁሉ ‹‹congra!›› የሚለው ስል አሰብኩ:: “ምኑ ነው የተሳካለት?” ጠየቅሁ::

 “መንጃ ፍቃድ አልፎ ነው”

 “ምን ይደንቃል?” ደገምኩ:: ቆራጩ ሳቀ::

“ምን አሳቀህ?”

“ሰባት ጊዜ ወድቋል”

“እና”

 “ቢያቅተው ገንዘብ ከፍሎ አለፈ”

 “ምን መኪና ሊነዳ?”

“ሲኖ ትራክ”

“እንዴት አለፈ?”

“ገንዘብ በደምብ ሰጠ:: የፈተናው ቀን ካሜራው እንዲበላሽ ተደረገ:: ከዚያ ሞተር አስነሳ… ሳይነዳ አለፈ” አለኝ ፀጉር ቆራጩ:: ግርም አለኝ:: ደነቀኝ:: ምን እየተደረገ ነው ስልም አሰብኩ:: በገንዘብ መንጃ ፈቃድ ወጣ:: አሁን ሲኖ ትራክ ሊነዳ ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅኩ::

“እስኪ ጠይቀው” አልኩት ቆራጩን::

“ምን ብዬ?” አለኝ::

“ሲኖትራኩን አሁን ትነዳለህ በለው…” አልኩት::

ፀጉር ቆራጩ ጉሮሮው ሳለ:: ወደ ውጪ ተመልክቶ ወጣቱን ጠራው:: ወጣቱ ደስታው አልለቀቀውም ፈገግ ብሎ መጣ::

 “ምነው?” አለ ወጣቱ

“አሁን ሲኖትራኩን መንዳት ትጀምራለህ?” ብሎ ጠየቀ ቆራጭ::

“አይ… በሚኒባስ ነው የምጀምረው” አለ ኮራ ብሎ::

“አሃ! ሰው መፍጀቱን!” ተሳቀ::

የትራፊክ መብራት ላይ ቆም እንዳሉ ብዙ ነገር ያያሉ:: መስኮትዎ ክፍት ከሆነ ፍዳዎትን መብላትዎ ነው:: ማስቲካ፣ ካሴት፣ ሲዲ፣ ጋዜጣ፣ ባርኔጣ፣ ቻርጀር… ልመና ይሄን ሁሉ ያስተናግዳሉ:: አንዱ ድንገት የቆምኩበት ከተፍ አለ:: በእጁ ያልያዘው የለም:: መብራት ስለሌለ ትራፊክ ነው የሚያስተናግደን::

“ቻርጀር ይፈልጋሉ?” ጠየቀ::

“አይ”

“እሺ.. ኮፍያ..”

“አይ”

“ማስቲካስ?”

“አልፈልግም!!” ቁጣ::

“እሺ የጀኒን ሲዲ..”

“አይ”

“እሺ ሪፖርተር ጋዜጣ”

“ኡፍፍ…”

“እሺ.. ፍላሽ..”

“አይይይ …” የባስ ተናደድኩ::

“እሺ ፓወር ባንክ …”

“ኡይይ … ትራፊክ እንዳልጠራ”

“በምንዎ?”

“ጮኬ!!”

“ፊሽካ አለኝ ግዙኝና ንፉለት”

ትራፊኩ ለቀቀን ሄድኩ:: ኡፍፍፍ …

ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ. ም

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top