ቀዳሚ ቃል

በአስተውሎት እንራመድ

የታዛ መጽሔት ለሃያ ሁለተኛ ጊዜ ገበያ ላይ ውላለች። በዚህ ዕትም እንደተለመደው የተለያዩ ባህላዊና ሥነ-ጥበባዊ ጉዳዮችን ጀባ ብለናል:: በመጽሔት ይዘታችን ላይ የአንባቢዎቻችን አስተያየቶችና ምክሮች ወሳኝ ናቸው:: ምክራችሁ፣ ጥቆማችሁ፣ እንዲሁም ትችታችሁ ለመፅሄታችን ዕድገት ጠቃሚያችን ነውና ፃፉልን:: የሀገራችንን በህላዊና ሥነ-ጥበባዊ ዕድገት ለማራመድ ጠንክራችሁ ሥሩ:: ምክንያታዊ ሁኑ፤ምክንያታዊ እንሁን::ታዛን በክርክር መድረክነት ተጠቀሙ::

ምክንያት እና ምክንያታዊነት በአብዛኛው ህዝባችን ዘንድ ቢሰርፅ ወይንም እንደ ባህል ቢያዝ አሁን ላሉብን ችግሮች መፍትሔ ይሆናል ብለን እናምናለን::

በሃያኛው ዕትማችን “ማንነት፣ ዘርና ዘረኝነት” በሚል ርዕስ በቀረበው ጽሑፍ በተለይም “ዘር” የሚለው ፅንሰ ሀሳብ የተሳሳተ እንደሆነ በሳይንሳዊ ትንተና መቅረቡን እንረዳለን። በዚህ ጽሑፍ ብዙዎቻችን በስሜት እንጂ በምክንያታዊ መንገድ ነገሮችን ልብ ብለን እንደማናያቸው ተገንዝበናል።

ይህ የተዛባ አመለካከት በአንድ ጽሑፍ ብቻ መፍትሔ ያገኛል ብለን አናስብም። በእኛ በኩል ሌሎችም እንዲጽፉ፣ በእኛ መጽሔትም ሆነ በሌሎች ሚድያዎች እንዲወያዩበት እንሻለን። በዚህ በሃያሁለተኛ ዕትማችን ጸሐፊው ባሕልና የማንነት ለውጥ ተፈጥሯዊ ባሕሪ ያለው መሆኑን በሳይንሳዊ ዕይታ በመተንተን በአሁኑ ወቅት ያለንበትን ሁኔታ ያሳዩናል:: በአስተውሎት ከተራመድን ያቀድነው ግብ ላይ እንደርሳለን። ዘመናዊነት እና አርቆ አስተዋይነትን በሰከነ እና በግልጽ መወያየት ብንጀምር መልካም ነው እንላለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top