ጥበብ በታሪክ ገፅ

ስለቱሪዝም ልማት አንዳንድ ነጥቦች

በስፋት ተቀባይነትን ባገኘው ድንጋጌ መሰረት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሆቴልና የማረፊያ አገልግሎቶችን፣ የጉዞ ውክልናና ተዛማጅ ሙያዎችን፣ አስጐብኚ ድርጅቶችን፣ የቅድሚያ ወረፋ ይዞታ ስርዓትን (reservation systems) ፣ የመዝናኛ ፓርኮችን፣ መካነ ፈውሶችንና የፍልውሃ ስፍራዎችን ያጠቃልላል።

 በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ግድም አዝጋሚ የነበረው የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ዕድገት ወደ ክፍለ ዘመኑ አጋማሽ ላይ ፈጠን በማለት ከ1970ዎቹ በኋላ ጉልህ እመርታን እያሳየ የመጣ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል በ1950 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር 25 ሚሊዮን እንደነበርና ከዚህ የጉብኝት እንቅስቃሴ 2.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር (ከዚህ በኋላ አ.ዶ) ገቢ ተገኝቶ እንደነበር ተገምቷል። ከ1960 እስከ 1970 ዓ.ም በነበሩት አስር ወይንም አስራ አንድ ዓመታት ውስጥ የቱሪስቶች ቁጥር በ2.5 እጅ ሲጨምር ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት በየአስር ዓመቱ በእጥፍ እያደገ ነበር። የገቢው እድገት ከጐብኚዎች ቁጥር እድገት ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ብልጫ ነበረው። በ1970 ዓ.ም 18 ቢሊዮን አ.ዶ የነበረው ገቢ በ1980 ዓ.ም ወደ 105 ቢሊዮን አ.ዶ አድጓል። በአሁኑ ጊዜ ቱሪዝም ለዓለም ኢኮኖሚ ያለው ሁነኛ ድርሻ በውል በመታወቁ የ21ኛው ምዕተ ዓመት ግዙፍ ኢንዱስትሪ ተብሎ ተሰይሟል። ሁኔታውን የበለጠ አጉልቶ ለማሳየት ከፍ ሲል ከተጠቀሱት አሃዞች በተጨማሪ የዓለም ቱሪዝምና የጉዞ ካውንስል (WTTC) እንዲሁም ጆን ኔይስቢት የተባለ ጸሐፊ ‹‹ግሎባል ፓራዶክስ›› በተሰኘ መጽሃፉ የጠቀሳቸውን አንዳንድ መግለጫዎች መመልከቱ ጠቃሚ ነው። በኔስቢት መረጃ መሰረት፡-

• ከዓለም የሰራተኛ ሃይል 10.6 ከመቶ የሚሆነው በቱሪዝም መስክ የተሰማራ ነው፣

• ሀገሮች ከሚያመርቱት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ) ቱሪዝም 10.2 ከመቶውን ይሸፍናል፣

• ከታክስ ከሚገኝ ገቢ የቱሪዝም ዘርፍ 655 ቢሊዮን አ.ዶ ድርሻ አለው፣

• የ3.4 ትሪሊዮን አ.ዶ ጥቅል የምርት ውጤት በመሸፈን ቱሪዝም እጅግ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሆኗል፣

 • የቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ከሸማቾች 10.9 ከመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል፣

• ከዓለም የካፒታል መዋዕለ ነዋይ 10.7 ከመቶ የሚሆነው ቱሪዝም ላይ ይውላል፣

 • ከመንግስታት አጠቃላይ ወጪ የቱሪዝም ድርሻ 6.9 ከመቶ ይሆናል፣

ይሁን እንጂ ከፍ ሲል የተጠቀሱት ጠቋሚ መረጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ተዘዋውሮ የመስህብ ስፍራዎችን ሊጐበኝ ይችላል ተብሎ ከሚታሰበው የዓለም ህዝብ ቁጥር (potential and capable travelers) ውስጥ የቱሪስቱ ቁጥር ከሰባት በመቶ አይበልጥም። ስለሆነም ከዘርፉ የሚጠበቁት እጅግ ግዙፍና እምቅ የእድገት ውጤቶች እውን የሚሆኑት ወደፊት ነው። በዚህ ምክንያት ይመስላል ቀደም ሲል የጠቀስነው ፀሀፊ ‹‹በወደፊቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ወሳኝ የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው የመረጃ አብዮት ነው›› ያለው። የማይክሮሶፍቱ ቱጃር፣ ቢል ጌትስም፣ ወደፊት ቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጣቸው የንግድ ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ይሆናል በማለት አጽንዖቱን አጠናክሮታል።

 ከዓመታት በፊት የቱሪዝም ልማት ዘርፍ መፃዒ ዕድልን በሚመለከት የዓለም ቱሪዝም ድርጅትና የዓለም ቱሪዝምና የጉዞ ካውንስል የሚከተሉትን አራት በብሩህ ተስፋ የተሞሉ ትንበያዎች አስቀምጠው ነበር።

 • በ2020 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር 1.6 ቢሊዮን ይደርሳል፡

• በ2020 ዓ.ም የቱሪስቶች ወጪ ወይንም በተለያየ መልክ ከቱሪስቶች የሚገኘው ገቢ 2000 ቢሊዮን አ.ዶ ግድም ይሆናል፤ (በቀን 5 ቢሊዮን አ.ዶ እንደማለት ነው)፣

 • በ2020 ዓ.ም የቱሪስቶች ቁጥር በዘላቂነት በየዓመቱ በ4.3 በመቶ፣ ከመስኩ የሚገኘው ገቢ ደግሞ በ6.7 በመቶ ከፍ ይላል። ይህም ምናልባት የዓለም ሃብት በየዓመቱ ያድጋል ከሚባልበት የ3 በመቶ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍ ያለ ነው፣

 • ከ1995 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ በቱሪዝም ዘርፍ 144 ሚሊዮን ተጨማሪ የስራ ዕድል እንደሚኖርና ከዚህም ውስጥ 77.7 ከመቶ የሚሆነው በእስያ ፓሲፊክ ሀገሮች እንደሚሆን ተገምቷል።

 የቱሪዝም ሃብት ልማትን በአዲስ አስተሳሰብ መቃኘት ከተጀመረ ዓመታት አልፈዋል። በቱሪዝም ዘርፍ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ የትኩረት አቅጣጫን ከውሱን መርሃ ግብር ወደ ስትራቴጂ፣ ከውጭ ምንዛሪ ማካበት ወደ ሰፋፊ የኢኮኖሚ ልማት ውጥኖች ማዞርን ይጠይቃል። እዚህ ላይ ውሱን የሆኑ መርሃ ግብሮችን እየቀረጹ ማስፈጸምና የውጭ ምንዛሬን ማሰባሰብ እርግፍ ተደርገው ይተዋሉ ማለት ሳይሆን የዘርፉ ልማት ዋነኛ ግብ ወይንም የረዥም ዘመን ራዕይ ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም ለማለት ነው።

 ቱሪዝምና ተዛማጅ የስራ ዕድሎች

 ከተጨማሪ የስራ እድል ባሻገር ከቱሪዝም ልማት ጋር ከፊትም ከኋላም የተሳሰሩ (backward & forward linkages) ተዛማጅ መስኮች በርካታ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ሰራተኞች በደሞዝና ምንዳዕ መልክ 17 ትሪሊዮን አ.ዶ የሚያገኙ ሲሆን በታክስ መልክ ደግሞ 230 ቢሊዮን አ.ዶ እንደሚከፍሉ ይገመታል። ተዛማጅ የሆኑ የስራ መስኮችን በሚመለከት፣ የቱሪዝም ልማት ከእርሻ፣ ከዕደጥበብ፣ ከወተትና የወተት ተዋጽዖ ምርት፣ ከዶሮ እርባታ፣ ከምግብ ዝግጅት፣ ከግንባታ፣ ከምህንድስና እና ከቤት ውስጥ ሽብርቅ፣ ወዘተ ጋር በየደረጃው በተለያየ መጠን ይዛመዳል።

 ቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪ

ሆቴሎች ከሌሉ ቱሪዝም የለም። ይህ በብዙ ሀገሮች እንደ መፈክር የሚቆጠር አባባል ነው። በእርግጥም የሆቴል ኢንዱስትሪ ከቱሪዝም ጋር በጽኑ የተሳሰረ ነው። በአብዛኞቹ ሀገሮች በቱሪዝም አማካይነት ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ከግማሽ የማያንሰው የሚሰበሰበው በሆቴሎች በኩል ነው። በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሆቴል ስራ በገጠር ልማት እንቅስቃሴ በተለይም ከእርሻ ስራ ወጣ ያለ ተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው። የሆቴሎችን የመኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባና የምግብ አዳራሾች፣ ቢሮዎችና የመዝናኛ ሰገነቶች ለማስዋብ የተለያዩ ምንጣፎች፣ መጋረጃዎች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ወዘተ ስለሚያስፈልጉ የሆቴል ኢንዱስትሪ መስፋፋት እነኚህን ዕቃዎች ለሚያመርቱ ሰዎች ወይንም ለሚያቀርቡ ሱቆች መልካም የኢንቨስትመንት አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

 በገጠርና ገጠር-ቀመስ ከተሞች የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን በአግባቡ በማልማትና ተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ በእርሻ መሬት ላይ ያለውን የሰው ሃይል ጫና እና የአካባቢ ጉዳት በመቀነስ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን ለመቆጣጠር ይቻላል። ከጐብኚዎች ቁጥርና ፍላጐት ማደግ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ግዙፍ የኢኮኖሚ ልማት ውጥኖች የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የአየር ትራንስፖርት መስመሮችንና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን የማስፋፋት ስራን የሚያካትቱ ናቸው።

 ከፍ ሲል ከተጠቀሱት የቱሪዝም ዘርፍ ልማት ትንበያዎች ተጠቃሚ ለመሆን ከተፈለገ አስቀድሞ ዝግጁ ሆኖ መገኘት ተገቢ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቁ ሆኖ በመገኘትና ከተጠቀሱት ዕድሎች አብዛኞቹን በመጠቀም ጉልህ ውጤት ለማስመዝገብ እጅግ አዳጋች ቢሆንም፣ የሀገራችንን ባህላዊና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶች በተቻለ መጠን በአግባቡ በማልማት ከቀድሞው የተሻለ ስራ መስራት ይቻላል።

 ስልትና ስትራቴጂ

 ለቱሪዝም ዘርፍ ልማት አስቸኳይና አስፈላጊ የሆኑት የስትራቴጂ እርምጃዎች የተቀናጁ፣ በአግባቡ የተቀናበሩና በጊዜ ገደብ የተወሰኑ የድርጊት ፕሮግራሞችን የያዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ገና ካልለማው የሀገራችን ሰፊ የመስህብ ሃብት አንፃር ሲታይ የሚያዋጣው የልማት ስልት በተወሰኑና በተመረጡ ስፍራዎች ላይ ማተኮር ነው። ሜክሲኮን፣ ኢንዶኔዥያንና ታይላንድን የመሳሰሉ ሀገሮች በመስህብ ሃብት ልማት ጐልቶ የሚታይ ውጤት ሊያስመዘግቡ የቻሉት ምርጥ የሚሏቸውን ጥቂት ስፍራዎች በተገቢው መንገድ በጥራት ለማልማት በመቻላቸው ነው።

በተጨማሪም የተመረጡ የመስህብ ሃብት ስፍራዎችን ለማልማትና ለማስተዳደር ፍሬያማ ነው ተብሎ የሚቀርበው ዘዴ የቱሪዝምን ዘርፍ ወሳኝ ከሆኑት የመሰረተ ልማት አውታሮች የልማት መርሃ ግብር ጋር የማቆራኘቱ ስልት ነው። ይህም የመንግስትንና የግል ባለሃብቶችን የጋራ ጥረት እውን ለማድረግ የሚያስችል ሁነኛ መንገድ እንደሆነ በአንዳንድ ሀገሮች የሚገኙ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች አበክረው ያስረዳሉ። ለንስሃ ወይንም ለስዕለት የሚደረጉ በርካታ ሃይማኖታዊ ጉዞዎችና የንግስ ክብረ-በዓላት ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

 ቱሪዝምና የአካባቢ እንክብካቤ

ከቱሪዝም ዘርፍ ልማት አበይት ተግባራት አንዱ የተፈጥሮና ባህላዊ የመስህብ ሃብት አካባቢዎችን በአግባቡ የመጠበቅ ሃላፊነት ነው። ለቱሪስቶች (በተለይም ለውጭ ዜጎች) ውብ የሆኑና ያልተመሰቃቀሉ የተፈጥሮ አካባቢዎችን መመልከት ከፍላጐቶቻቸው ሁሉ ዋነኛው ነው። የተለያዩ የተፈጥሮ መስህብ ሃብቶች ያሏቸውን ልዩ ልዩ ባህርያት ጠብቆና ተንከባክቦ በማቆየት ለተፈጥሮ ቱሪዝም (ኤኮቱሪዝም) ልዩ ዝንባሌ ያላቸውን ጐብኚዎች በገፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል። የቱሪዝም ዘርፍ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ይህን የጐብኚዎች ፍላጐት ለማርካት የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቁጥር በርካታ ነው። ለተሻለ ውጤት ደግሞ የእነኚህ ድርጅቶች የተቀናጀ ጥረት እጅግ ወሳኝ ነው።

በሌላ አነጋገር ማራኪ በሆኑ የተፈጥሮ አካባቢዎች ውስጥ ወይንም ዙሪያ የሚደረግ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የአካባቢን ስነምህዳር በማያዛባ መንገድ መሆን ይኖርበታል። ‹‹ለማንኛውም ሃይል/ድርጊት ሌላ እኩልና ተቃራኒ የሆነ አፀፋ-ሃይል/ድርጊት አለ›› የሚለው ሳይንሳዊ አባባል በቱሪዝም ላይም ይሰራል። ክፍለ ኢኮኖሚውን ለማጐልበት የሚረዱ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከመዘርጋታቸው በፊት በተፈጥሮ ሃብት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት ጉዳት በውል ሊጤን ይገባል። ወደ ተራራማና በደን የተሸፈኑ ማራኪ የተፈጥሮ መስህብ ሃብቶች አካባቢ የሚመጡት ቱሪስቶች ቁጥር ሲጨምር በአንድ ወይንም በሌላ ምክንያት አደገኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፉክክር ሊከሰት ይችላል። ይህ በሚሆን ጊዜ ለአካባቢው ውበት ተጨማሪ አስተዋጽዖ ሊኖራቸው የሚችሉ የደን ተከላ ፕሮጀክቶች ሊዘነጉ፣ አካባቢ ሊራቆት፣ ብካይና ቁሻሻ ሊከማች፣ በአጠቃላይ ስነምህዳር ሊዛባ ይችላል። ይህ እንዳይሆን መንግስት አስቀድሞ ጠንከር ያሉ የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል። በመገናኛ ብዙሃንና በሌሎች አመቺ ህዝባዊ መድረኮች አማካይነት ሰፊ የግንዛቤ ማዳበሪያ ስራዎችን መስራት እጅግ ጠቃሚ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ደንቦችን በሚተላለፉ ሰዎች ወይንም ተቋማት ላይ ያለማመንታት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የመስህብ ሃብት አካባቢዎች ንፁህ ሊሆኑ ይገባል። ንፁህ አካባቢ ጐብኚዎችን የመሳብ ዓይነተኛ ድርሻ አለው።

ቱሪዝምና ማህበራዊ አተያዩ (ፐርስፔክቲቭ)

 ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መዳበር ማህበራዊ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከሚገመቱት ውስጥ አንዱ ለጉዞ፣ ለሽርሽርና ለእረፍት-ጊዜ ይሰጥ የነበረው ትርጉምና አስተያየት መቀየር ነው። በተለምዶ ቱሪስት ማለት አንድ ከአገር አገር የሚንሸራሸር ገንዘብ የተረፈው ቅንጡ ቱጃር ተደርጐ ይቆጠር ነበር። በሀገራችን ይህ አስተሳሰብ ጨርሶ ተለውጧል ለማለት ባያስደፍርም በርከት ባሉ የውጭ ሀገሮች ዘንድ ቱሪዝም የቅንጦት ሽርሽር (ወይንም መቀናጣት የበዛበት ጉዞ) ነው የሚለው አስተሳሰብ በአመዛኙ ተለውጧል። በአሁኑ ጊዜ የቱሪስቱ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወዘተ ዳራ እጅግ የተለያየና ፍላጐቱም የዚያኑ ያህል የተራራቀ ነው። የማይናቅ ቁጥር ያላቸው፣ ነገር ግን እጅግ ሃብታም የማይባሉ፣ ሀገር ጐብኚዎች በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የሚገኙ ሀገሮችንና ህዝቦችን ለመጐብኘት ረዥም ርቀት በመጓዝ ዘለግ ያሉ ቀናትን ያሳልፋሉ።

ልክ እንደ ሌሎች መስኮች ሁሉ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ለቱሪዝም መዳበር ከፍተኛ ድርሻ አለው። የመገናኛ ዘዴዎች መሻሻልና የአውታሮች መስፋፋት፣ የሆቴልና መሰል የማረፊያ ስፍራዎች መኖር የቱሪስቶችን ጉብኝት ቀልጣፋና ምቹ እንዲሆን በእጅጉ ይረዳል። ቀድሞም ቢሆን ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር መጓዝ በሀገሮች መካከል ለሚደረግ ማህበራዊ ግንኙነት ዋነኛው ምክንያት እንደነበር በታሪክ ተደጋግሞ የተመሰከረ ነው።

ባህላዊ ቱሪዝም

የቱሪስት መስህብ ሃብት ያላቸው ሀገራት ብዙ ጐብኚዎችን ወደ ሀገራቸው ለመሳብ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ። በመሆኑም ከፉክክሩ የሚገኘውን ድርሻ በየጊዜው ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ዝቅ ሳይል ጠብቆ ለማቆየት እንኳ የማስተዋወቅና የገበያ ጥረቶችን በዘለቄታው አጠንክሮ መገኘት የግድ ነው።

 ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው የቱሪዝም እንቅስቃሴ አንዱ ባህላዊ ቱሪዝም ነው። የሀገራችን የባህልና የአርኪዮሎጂ ቅርሶች አለም አቀፍ እውቅናን ያገኙ በመሆናቸው በብዙ ቱሪስቶች እንደሚጐበኙ ይታወቃል። እነኚህ የመስህብ ስፍራዎች ጥንታዊ ታሪክንና ባህልን ለማጥናት ከመርዳታቸው ባሻገር፣ ብሄራዊና ዓለም አቀፋዊ መግባባትን ብሎም ወዳጅነትን የሚያጐለብቱ ናቸው። በዚህ ረገድ ቱሪዝም ለማህበራዊና ባህላዊ ልማት መረጋገጥ ሁነኛ ድርሻ አለው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ እንዲሁ ቢተዉ ጥቅም ሊሰጡ ከማይችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች፣ የማይናቅ ገቢ ማግኘት የሚቻለው ከቱሪዝም ዘርፍ ልማት ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ ከቱሪዝም መስፋፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ አሉታዊ ማህበራዊ ውጤቶች መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም። በዘመነ ኢንፎርሜሽን፣ ቱሪዝምን ለባህል ወረራ እንደ ዋነኛ መንስዔ አድርጐ መውሰድ አጓጉል ግነት ቢሆንም ንቆ መተው ግን አይቻልም። ይህን በሚመለከት በጥቅምት ወር 2001 ዓ.ም ታትሞ በወጣው የናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት ላይ ሁሴን ዳውድ ኤል ማዉይ የተባሉ የስዋሂሊ አረጋዊ ሮበርት ካፑታ ከተባለ የመጽሔቱ ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ውይይት የሚከተለውን ብለው ነበር።

ቱሪዝም ሁለት ስለት እንዳለው ጐራዴ ነው። ጐብኚዎች ሀገራችንንና አኗኗራችንን ለመመልከት ይመጣሉ፤ ሲመጡም ባዶ እጃቸውን ሳይሆን ገንዘብ ይዘው ነው። ገንዘቡን ደግሞ እንፈልገዋለን። ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር የሚመጡትና ትተዋቸው የሚሄዱት የባህርይና የባህል ተጽዕኖዎች ወጣቶቻችንን በቀላሉ የሚስቡና በጽኑ የሚፈታተኑ ናቸው። ከቱሪዝም የሚገኘው ገንዘብ ኑሯችንን የሚደጉም ቢሆንም ገቢው ቱሪስቶቹ ሊያዩት የሚፈልጉትን (ማለትም ባህላችንን) የሚያጠፋ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ምራቃችንን ዋጥ ያደረግነው አንጋፋ የማህበረሰብ መሪዎች ቱሪስቶችን በማስተናገድና ባህላችንን በመጠበቅ መካከል ባለች ቀጭን ገመድ ላይ እንደሚረማመዱ ሰዎች ነን።

አዳዲስ የቱሪዝም ልማት መስኮችን መፈለግ

 ተፈጥሮ በሚስጥርና በተዓምር የተሞላች ናት። የተፈጥሮን ሚስጥርና ተዓምር በውል ለመረዳት የሰው ልጅ ዝንተ-ዓለም እንደጣረ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክና ስልጣኔ ካላቸው ሀገሮች አንዷ ናት። ተራሮቿ፣

“ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መዳበር ማህበራዊ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከሚገመቱት ውስጥ አንዱ ለጉዞ፣ ለሽርሽርና ለእረፍት-ጊዜ ይሰጥ የነበረው ትርጉምና አስተያየት መቀየር ነው”

ቆላዎቿ፣ ወንዝ ሸንተረሮቿ፣ ደኖቿና አራዊቱ፣ አዕዋፋቱና ዕጽዋቱ የተፈጥሮ ፍስሃ ናቸው። ይህን የተፈጥሮ መስህብ ሃብት አይቶ ለመደሰት የሚመጡት ጐብኚዎች ቁጥር ብዙ ነው ባይባልም የሚናቅ አይደለም። በመሆኑም የቱሪስቱን ፍላጐት ለማርካት አዳዲስ የጉብኝት መስመሮችን ወይንም አማራጭ የጉብኝት ፕሮግራሞችን መዘርጋት ያስፈልጋል። ይህን ባለማድረግ ከኢንዱስትሪው የሚታጣው ጥቅም እጅግ ግዙፍ ነው። ስለዚህ የሀገሪቱን የመስህብ ሃብቶች በማስተዋወቅ ስራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ብቁ ስልት በመንደፍ በስፋት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

 በዚህ ረገድ፣ ፈተና የበዛበት፤ ነገር ግን እርካታ የተመላበት፣ ምናልባትም ዝና የሚገኝበት ‹‹አድቬንቸር ቱሪዝም›› በመባል የሚታወቀው የጉብኝት ፕሮግራም ከፍ ሲል ለጠቀስነው አማራጭ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥሩ አስተዎጽዖ ሊኖረው ይችላል። የሀገራችን መልክዓ ምድር ለእንዲህ ዓይነቱ የቱሪዝም መስክ የማያመች አይደለም። ‹‹አድቬንቸር ቱሪዝም›› የእግር ጉዞን፣ በጋማ ከብት ተቀምጦ ጋራና ሸለቆ መጐብኘትን፣ ተራራ መውጣትን፣ በወራጅ ወንዝ ላይ የታንኳ ቀዘፋን (ሪቨር ራፍቲንግ)፣ ወዘተ ያጠቃልላል። በዚህ መልክ ሊለሙ የሚችሉ አካባቢዎች በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ይገኛሉ።

 በቱሪዝም ኢንዱስትሪ በስፋት ለመጠቀምና ደህና ገቢ ለማካበት፣ ለእንዲህ ዓይነት አማራጭ የኢንዱስትሪው መስኮች መንግስት ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት። ለምሳሌ የጉዞ መስመሮችን ተከትለው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ሊሰጡ የሚችሉ የመንገደኞች ማረፊያ ቤቶች (ጐጆዎች) መዘጋጀት አለባቸው። ጐብኚዎች እንዳይደናገሩ የጉዞው መስመሮች በጫካ ውስጥ የሚያልፉ ከሆኑ የአቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች መኖር የግድ ነው። በጉዞ መስመሮች አካባቢ ስለሚገኙ አራዊትና እንስሳት በሚገባ የሚገልጽ ዝርዝር ጽሑፍ፣ በዋና በዋና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች፣ ማዘጋጀት የብዙ ጐብኚዎችን ጥያቄ ከመመለሱ ባሻገር በመስኩ ልዩ ዝንባሌ ላላቸው ቱሪስቶች ከፍተኛ እርካታን ይሰጣል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top