የታዛ ድምፆች

መረጃ ዘክዛኪው ጁሊያን አሳንጅ

የ49 አመቱ ጁሊያን ፖል አሳንጅ በታሪኩ የመጀመሪያውን ግዙፍ ሚስጥራዊ መረጃ በማስፈትለክ ይታወቃል። አሳንጅ በተጠመደበት ሚስጥር የመዘክዘክ አባዜ ምክንያት ብዙዎችን አናዷል፣ አሳዝኗል፣ አስቆጥቷል። በዚህም ሰበብ ብዙ ፍዳ እንዳዬ የአለም መገናኛ ብዙሃን ሳይታክቱ ዘግበዋል።

 ሚያዝያ 11 ቀን፣ 2019 (የዘመን አቆጣጠሩ በሙሉ እ.ኤ.አ ነው) በለንደን ኤምባሲዋ ዊሊያም አሳንጅን ለሰባት አመታት ታቅፋ ስትጠብቀው የነበረችው ኢኳዶር ይቺን ቀን አሰፍስፈው ሲጠብቁ ለነበሩት የእንግሊዝ ፖሊሶች “አመሉን አልቻልኩትም፣ በቃኝ፣ እንካችሁ ውሰዱት” አለች። አሳንጅም በሚያስገርም ሁኔታ በእንግሊዝ ፖሊሶች ተይዞ ከኤምባሲው ተጎትቶ ወጣ። እየወጣ ሳለም “ይህ ህገወጥ ነው” እያለ ይጮኽ ነበር። ይህ ጉዳይ ለእንግሊዞቹ ትልቅ እፎይታ ነበር። ምክንያቱም አሳንጅን ለመጠበቅ በኢኳዶር ኤምባሲ ዙሪያ የተመደቡት በኮድ ስማቸው “ኦፕሬሽን ኩዶ” በሚሰኙት የጥበቃና የስለላ ቡድን አባላት ምክንያት ብዙ የእንግሊዝ ግብር ከፋዮች ገንዘብ ያለአግባብ ወጪ ተደርጓል በሚል መንግስት ክስ ተመስርቶበት ነበርና። ሆኖም ክትትሉ በድምሩ እንግሊዝን ከ22 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እንዳስወጣት ይነገራል።

 አሳንጅ ከኤምባሲው በወጣ በሰዓታት ውስጥ ማእከላዊ ለንደን ወደሚገኘው ዌስት ማስተር ሬጅስትራር ፍርድ ቤት ቀረበ። በጥቂት ሰአታት ውስጥ የ34 ሺ ፓውንድ ዋስትና ገደብ በመተላለፍ ተከሶ የ50 ሳምንት ፍርዱን ወደሚፈጽምበት ኤች. ኤም. ቤልማርሽ እስር ቤት ተወሰደ። በተመሳሳይ ቀን አሜሪካውያን አሳንጅን አሳልፋችሁ ስጡን የሚል ጥያቄያቸውን በተጠናከረ መልኩ ለእንግሊዝ መንግስት አቅርበዋል። አሳንጅና በ2006 የመሰረተው ድርጅቱ ዊኪሊክስ ያማረራቸው፣ ያበሳጫቸው፣ ቆሽታቸውን ያሳረራቸው ሀገራትና መንግስታት እጅግ በርካታ ቢሆኑም ይገባዋል ያሉትን ሊፈርዱበትና አንጀታቸውን ሊያርሱ በይፋ የቋመጡት ግን አሜሪካና ስዊድን ናቸው። ከሁለቱ ደግሞ የአሜሪካ ፍላጎት ያይላል። ለመሆኑ ይህ በአለማቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነ ሰው የፈጸማቸው ወንጀሎች ምንድን ናቸው? የሰራውስ ስራ ለዚህ የሚያበቃው ነው ወይ? ብለን ለመፍረድ ያስችለን እንደሆን አንዳንድ ክስተቶችን እንመልከት።

 ጁሊያን አሳንጅ በታውንስቪል፣ ኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ ከእናቱ ከክርስቲን አን ሀውኪን እና ከአባቱ ጆን ሺፕቶን ሐምሌ 3 ቀን፣ 1971 ተወለደ። አባቱ የፀረ ጦርነት አክቲቪስት እንደነበረ ይነገራል። ይህ ቤተሰብ አሳንጅ ሳይወለድ የተለያየ ሲሆን አሳንጅ በህይወቱ የተረጋጋ ኑሮ ያልኖረና በ30 የአውስትራሊያ ከተሞች እንደዘላን እየዞረ እንዳደገ ይነገራል። ገና በጨቅላነቱ በኮምፒዩተር ፍቅር የተያዘው አሳንጅ በ20 አመት እድሜው አካባቢ ሜንዳክስ (በላቲን ትርጉሙ ውሸታም) በሚል ስም የኮምፒዩተር መረጃ ብርበራ (hacking) እንደጀመረ ይነገራል። በዚህም በ1991 ገና በወጣትነቱ 31 የሳይበር ሰበራ ክስ በአውስትራሊያ የቴሌኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ተመስርቶበት ታስሮ የተፈታ ሲሆን ቀጥሎም ከሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን የፊዚክስ ትምህርት አቋርጦ መውጣቱ ተረጋግጧል።

አሳንጅ የመረጃ መልቀቂያ ድርጅቱን ዊኪሊክስን በ2006 ሲያቋቁም በተለያዩ ምክንያቶች ያገኛቸውን በጣም ከባድ የሆኑ የመንግስትና የድርጅት ሚስጥሮችን ፈልፍሎ ለማውጣትና ይፋ ለማድረግ ሆን ብሎ እንደመሰረተው ይናገራል። አሳንጅ የሚሰራውን ስራ ሳይንሳዊ ጋዜጠኝነት (Scientific journalism ) ብሎ ይጠራዋል። ለዚህ ተግባር እንዲረዱት በአለም ላይ ያሉ በተመሳሳይ ተግባር የሚሳተፉ መረጃ በርባሪዎችን በማደራጀት፣ ስብሰባ በመጥራት ካስተባበረ በኋላ ማንኛውንም ሚስጥራዊ መረጃ ቢልኩለት በዌብ ሳይቱ እንደሚለቅ ይፋ አደረገ። በጣም ተፈላጊ የሚል ስያሜ ያላቸውን ሚስጥራዊ መረጃዎች ለይቶ በማውጣት ማንኛውም ሞጭላፊ ፈልጎና በርብሮ ካገኘ እንዲልክለት ጥሪ አደረገ። ከነዚህም ውስጥ የሲ.አይ.ኤ፣ የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ጦርነትና ጓንታናሞ ቤይን የተመለከቱ መረጃዎችን በጣም ተፈላጊ ከሚባሉቱ ዝርዝር ውስጥ አካቶ ነበር። በዚህ ጥሪው አሳንጅ ያገኘው ምላሽ የመረጃ ሱናሚ ቢሆንም አሜሪካዊቷ ቼልሲ ማኒንግ ጥሪውን ተከትላ ከታህሳስ 2009 ጀምሮ ካጎረፈችለት እጅግ የከበዱ የአሜሪካ መንግስት ሚስጥሮች ጋር ግን የሚስተካከል አልተገኘም። ይህች ሴት ኢራቅ ውስጥ ቤዝ ኖሮት ለሚሰራ የአሜሪካ ወታደራዊ መስሪያ ቤት የምትሰራ የነበረች ስትሆን በስራዋም ከባድ ሚስጥሮችን የማግኘት እድል ያላት፣ ለዚህም ስራ ብቁ ሆና ተፈላጊውን የጥንቃቄ መስፈርት ያሟላችና ሚስጥሮቹን ለመጠበቅ ቃለ መሃላ የፈጸመች ሴት ነበረች።

ማኒንግ ከ2010 የካቲት ወር ጀምሮ ሙሉ የዳታ ቤዝ ፋይል ከተለያዩ የአሜሪካ ዲፓርትመንቶች አውርዳለች። ለዚህም ይረዳት ዘንድ አሳንጅ የይለፍ ቃላትን የማለፍ ወይም የመሞጭለፍ ችሎታ እንዲኖራት እንደረዳት እና ሉኒክስ የሚባል ሶፍትዌር (Lunix Operating System) እንድትጠቀም እንዳቀበላት ታውቋል። ይህ የመበርበር ችሎታም ማኒንግ የሌሎች ባልደረቦቿን የይለፍ ቃል በመተላለፍ በነዚህም ሰዎች ዘንድ ያሉ መረጃዎችንም ጭምር ለመሰብሰብ ረድቷታል። ከዚህም አልፋ በሚያዝያ ወር 2010 የብዙ ባልደረቦቿን የይለፍ ቃል (password) በመስረቅ ለአሳንጅ አቀብላለች። በዚህ መሰረት ማኒንግ ከታህሳስ 2009 ጀምሮ ተይዛ እስከ ታሰረችበት ግንቦት 2010 በጣም በርካታ መረጃዎችን ለአሳንጅ በድብቅ ሰጥታለች። ይህም በሃሽ ደረጃ (hash level) የተፈረጁ በከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ብቻ የሚገኙ መረጃዎችን ይጨምራል። በዚህም ጊዜ ውስጥ 90 ሺህ የአፍጋኒስታን ጦርነትንና 40 ሺህ የኢራቅ ጦርነትን የተመለከቱ የወታደራዊ ትግበራ ሪፖርቶችን፤ 800 የጓንታናሞ ቤይ የታሳሪዎች የምርመራ ሂደትና አያያዝ መረጃዎችን የያዘ ሪፖርት፤ 250 ሺህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኬብል ምልልስ መረጃዎችን ለአሳንጅ አሳልፋ ሰጥታለች። አብዛኛዎቹ መረጃዎችም በከፍተኛ ደረጃ በምስጢራዊነት የተፈረጁና በአሜሪካው የበላይ አካላት ትእዛዝ ቁጥር 13526 ይፋ እንዳይወጡ ክልከላ የተደረገባቸው ናቸው።

ለምሳሌ ከነዚህ መረጃዎች ውስጥ ሚያዝያ 2010 የአሜሪካ ሄሊኮፕተር ብዙ የኢራቅ ሰላማዊ ሰዎችን እና ጋዜጠኞችን የገደለበት የ2007 ቪዲዮ ይገኝበታል።

 ይህ ሁሉ መረጃ እንደቀልድ እጁ የገባለት አሳንጅ ከ2010 እስከ 2011 ድረስ በተለያዩ ጊዜያት መረጃዎቹን በዌብሳይቱ በግልፅ አውጥቷቸዋል። ከዚህም አልፎ የበለጡ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አወጣለሁ በማለት የአሜሪካን መንግስት እስከማስፈራራትና ዊኪሊክስን የሚነካ ነገር ከማድረግ ቢቆጠቡ እንደሚሻላቸው እስከማስጠንቀቅ ደርሶ ነበር።

 እስከ 2015 ድረስ ዊኪሊክስ ከ10 ሚሊዮን በላይ መረጃዎችን የለቀቀ ቢሆንም ነገሮች ጠበቅ ያሉበት በ2016 ጀምሮ በለቀቃቸው የአሜሪካ ምርጫ መረጃዎች ምክንያት ነው። በሩሲያ ላይ የከፋ መረጃ ባለመልቀቁ ከሩሲያ ጋር ያብራል ብለው የሚከሱት አያሌ ናቸው። በዚህም ምክንያት በአሳንጅ ላይ የአሜሪካ መንግስት የሚከተሉትን ክሶች ማጠናቀር ጀመረ። የአንድ የብሄራዊ መከላከያ መረጃን ለመቀበል የተደረገ ሸፍጥ (conspiracy)፤ ይህን መረጃ መቀበልና አሳልፎ ለሌሎች መስጠት፤ እንዲሁም የመንግስት ኮምፒዩተርን ያለፈቃድ መበርበር (computer intrusion) በሚል ከሰሰው።

የችግሩ አሳሳቢነት እንግዲህ የሚጀምረው እነዚህ የተለቀቁ መረጃዎች የግለሰቦችን ስም በቀጥታ የያዙ መሆናቸውና ሰዎቹን አደጋ ላይ ሊጥላቸው መቻሉ ነው። ዊኪሊክስ የሚለቃቸው መረጃዎች በሰላማዊ ሰዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአሸባሪዎችም ዘንድ መፈለጉ ብዙ ሃገራትን አሳስቧል። ለምሳሌ ኦሳማ ቢንላደን በተያዘበት ወቅት ከተገኙት መረጃዎች አንዱ ቢንላደን አንዱን ተባባሪውን ዊኪሊክስ ላይ የወጡ የአፍጋኒስታንን ጦርነት የተመለከቱ መረጃዎችን እንዲልክለት የጻፈው ደብዳቤ ነበር። እነዚህ መረጃዎች ለአሜሪካ ድጋፍ የሰጡና በመረጃ ማቀበል የተባበሩ የሀገሪቱ ተወላጆች በስም የተገለጹበት እና ግለሰቦቹን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ። የኢራን መንግስትንም በተመለከተ ብዙ ለአሜሪካ መረጃ የሚያቀብሉ ዜጎች አደጋ ላይ ወድቀዋል። ከዚህም ሌላ ኒው ዮርክ ታይምስ “ታሊባን የመረጃ አቀባዮችን ለማደን ይረዳው ዘንድ ዊኪሊክስን እየመረመረ ነው” ብሎ በዘገበው ዜና ታሊባን ለአሜሪካ መረጃ የሚያቀብሉ ሰላዮችን እየለየ መሆኑን አንድ የቡድኑ ምንጭ እንደገለጸላቸው በጋዜጣው ሠፍሯል።

 ከአሜሪካና ከስዊድን ክስ የበረታበት አሳንጅ በጥር 2010 ለእንግሊዝ መንግስት ባለስልጣናት ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ጥቂት በእስር እንደቆየም በ34 ሺ ፓውንድ ዋስ ተለቀቀ። በዋስ ላይ እያለ ወደ ስዊድን ይላክ አይላክ የሚለውን የፍርድ ሂደት በጠበቆቹ በኩል ሲቃወም ቆይቶ አሳልፎ የመስጠቱ ውሳኔ ጉዳዩን በያዙ ዳኞች ሲወሰንና የይግባኝ ጥያቄዎቹ ሁሉ ውድቅ ሲሆኑበት ሰኔ 19 ቀን 2012 ለንደን ወደሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ገባ። በቪዬና ስምምነት ምክንያት የእንግሊዝ ፖሊሶች ወደ ኤምባሲው መዝለቅ እንደማይችሉ አሳንጅ ያውቅ ነበር። ነሐሴ ወር ላይ የኢኳዶር መንግስት ለአሳንጅ ጥገኝነት መስጠቷን በይፋ ገለጸች። ከኤምባሲ ወጥቶ ይንቀሳቀስ ዘንድ የሃገሪቱን የዲፒሎማቲክ ማእረግ ሰጥታውም ነበር፤ በእንግሊዝ መንግስት ውድቅ ተደረገ እንጂ። በ2015 የስዊድን መንግስት በጊዜ ርዝመት ሰበብ በአሳንጅ ላይ የጀመረውን ክስ ማንሳቱን ገለጸ።

አሳንጅ በኢኳዶር ኤምባሲም እያለ ግን ዊኪሊክስ መረጃዎችን መልቀቁን አላቆመም ነበር። ለምሳሌ በሐምሌ 2016 ወደ 20 ሺህ የሚደርሱ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪዎችን ኢሜይል በመልቀቅ የዲ.ኤን.ሲ (DNC) ኮሚቴ በዲሞክራቲክ ዕጩ ምርጫ ወቅት ከበርኒ ሳንደርስ ይልቅ ለሂላሪ ክሊንተን የወገነ እንደነበር አጋለጠ። በዚህም አመት ብዙ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪዎችንና የምርጫ ዘመቻ መሪውን የጆን ፓዲስታን በርካታ ኢሜይሎች ይፋ አደረገ።

በ2016 ዊኪሊክስ ከሩሲያ የመረጃ ሰራተኞች ጋር በመሆን በአሜሪካ ምርጫ ላይ ጫና በማሳደሩ በኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ለተወሰነ ወቅት የኢንተርኔት አጠቃቀም እገዳ ተደርጎበት ነበር። በ2017 በሌሎች ሃገራት ጣልቃ ገብ የሆነ መረጃ እንዳይለቅ የኢኳዶር ኤምባሲ አስፈርሞት ነበር። ይሁንና ግን በ2018 በማህበራዊ ሚዲያ በሰጠው መግለጫ ይህን ስምምነት ስለተላለፈ ኢንተርኔት እንዳይጠቀም በድጋሚ ታገደ። እንደ ኢኳዶር ፕሬዚዳንት አባባል ሀገሪቷ የአሳንጅ ጥበቃዋን ለማቆም የተገደደችው አሳንጅ ይህን በሃገራት ጣልቃ ያለመግባት ስምምነት ማክበር ባለመቻሉ ነው። በተጨማሪም በኤምባሲ ቆይታው የደህንነት ካሜራዎችን በመከለልና በማሰናከል፤ የነዚህን ካሜራዎች ስራ የሚያስተጓጉሉ መሳሪያዎችን በማሳሳት፣ ጥበቃዎችን በማመናጨቅና የኤምባሲውን ሚስጥራዊ መረጃዎች ሰብሮ እየገባ በመበርበር አስቸጋሪ ጸባይ በማሳየቱ ምክንያት ነው ብለዋል።

 በ2013 የኦባማ መንግስት ኤድዋርድ ስኖውደንና ቸልሲ ማኒንግን ሚስጥራዊ መረጃ በማውጣትና የስለላ ህግን በመተላለፍ ሲከሳቸው፤ አሳንጅን ግን መረጃዎቹን አሳተመ እንጂ ከመረጃ ቋቶቹ አላወጣም በሚል ክስ አልመሰረተበትም ነበር። የሱ ተግባር የጋዜጠኝነት ተግባር ብቻ ነው፤ ስለዚህ እሱን መክሰስ ጋዜጠኝነትን መቃወም ይሆናል ተብሎ ነበር። በ2013 ቸልሲ ማኒንግ በሰራችው ስራ በአሜሪካ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርባ በሰላይነት ወንጀል 35 አመት ተፈርዶባታል። ይሁንና በየካቲት 2017 የኦባማ መንግስት ምህረት አድርጎላት ወጥታለች ሲባል፣ በሌላ ፍርድ ቤት ቀርባ በዚሁ ጉዳይ ላይ የምስክርነት ቃል ላለመስጠት በመወሰኗ በሌላ ዳኛ ተፈርዶባት እስር ቤት ትገኛለች።

 በአሁኑ ሰአት አሳንጅ በአሜሪካ ምድር እስከ 5 አመት የሚደርስ ቅጣት እንደሚጠብቀው እየተነገረ ቢሆንም አንዳንዶች እንደሚሉት ግን አንዴ የአሜሪካን ምድር ይርገጥ እንጂ አሜሪካኖቹ ወደ 17 የሚደርሱ ክሶች ሊከፍቱበት እንደሚችሉ የሚጠረጥሩ አሉ። እስካሁን አብዛኛውን ክስ ያቆዩት የእንግሊዝ ህግ የሞት ፍርድ የሚፈረድባቸውንና በፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተከሰሱትን ሰዎች አሳልፎ መስጠትን ስለሚከለክል ከዚህ ህግ ጋር እንዳይጋጭባቸው በመስጋት ነው።

 አዲሶቹ ክሶች የስለላ ወንጀልን አካተው በጥር 2017 በትራምፕ አስተዳደር የቀረቡና ብዙዎች የሚሉትም በትራምፕ የሚዲያ ንቀት ተበረታተው የወጡ ናቸው ይባላል። በዚህ መንግስት ከምንም በላይ የተፈለገው አሳንጅ እንደ ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ ስለላ ወንጀለኛ፣ ድርጅቱ ዊኪሊክስም እንደ ሚዲያ ተቋም ሳይሆን እንደ ስለላ ድርጅት እንዲታይ ማድረግ ነው። በአሜሪካ ያሉ ብዙ ፖለቲከኞች (እንደ ሴናተር ቤን ሳሴ ያሉ ማለት ነው) “አሳንጅ የፑቲን መሳሪያ ሆኗል፣ ስለዚህ እስር ይገባዋል” የሚሉ ናቸው። አሳንጅ በግራ ዘመም የአሜሪካ ፖለቲከኞች ዘንድ ብዙ ደጋፊ የነበረው ቢሆንም፤ በ2016 የሂላሪን ኢሜሎች ይፋ ካወጣ በኋላ ግን የፑቲን አሻንጉሊትና የትራምፕ ወዳጅ ተደርጎ መወሰድ ስለጀመረ እስር ቤት ገብቶ ብዙ አመታት እንዲማቅቅ የሚመኙ ሰዎች ቁጥር በርክቶ ታይቷል።

የሚገርመው ደግሞ ከሚዲያ ዘርፍ ብዙ ደጋፊዎች የነበሩት ቢሆንም ተቃውሞው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይሎበታል። ለምሳሌ የዋሺንግተን ኤዲቶሪያል ቦርድ በጽሑፉ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ሚስተር አሳንጅ የነጻው ፕሬስ ጀግና አይደለም። እውነት ነው ብዙ የመንግስት ምስጢር አውጥቷል። ብዙዎቹም የዜና መስፈርት ያሟሉ ነበሩ። ሆኖም ግን አሳንጅ እነዚህን መረጃዎች ለማግኘት የሄደባቸው አካሄዶች የጋዜጠኝነትን ስነምግባር የሚፃረሩ ስለሆኑ ተቀባይነት የለውም። አንድን የአሜሪካ ወታደር ኮምፒዬተር ሃክ እንዲያረግ ማድረጉ፤ መረጃዎቹን እንዳሉ ወደ ህዝብ መልቀቁና እውነትነታቸውን ለማረጋጋጥ ምንም ጥረት አለማድረጉ እንዲሁም በመረጃው ውስጥ ስማቸው ለተጠቀሱት ሰዎች ምላሽ የመስጠት እድል መንፈጉ ከዚያም አልፎ ከውጪ ሃገር ሃይሎች ጋር በማበር በአሜሪካን ምርጫ አንዱን ወገን ለመጥቀም እንዲውል በመስራቱ በድምሩ አሳንጅ ጋዜጠኝነትን ያልተከተለ አካሄድ እንደተጠቀመ ይገልጻል”።

የእንግሊዝ መንግስት አሳንጅን ለአሜሪካ አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ብዙ የሀገሪቱን ህጎች የሚመረምር እንጂ ጉዳዩን በቀላሉ የሚወስን እንደማይሆን ይጠበቃል። ለምሳሌ የቆይታ ጊዜው፤ የአሳንጅ ጤናና እድሜ፤ ድርጊቱ ከአውሮፓ ሰብአዊ መብት ህግ ጋር አለመጣረሱን፤ ክሱ ከዘር፣ ጾታና ፖለቲካ አመለከካከት የጸዳ መሆኑን እና አሜሪካ ሲደርስ የሞት ፍርድ እንደማያጋጥመው ማረጋገጥ የፍርድ ሂደቱ ከሚጠበቅበት መስፈርቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። በእንግሊዝ ህግ አሳልፎ የመስጠቱ ሂደት ግለሰቡ በተያዘ በሁለት ወር ውስጥ እንዲፈጸም ያስገድዳል። ለዚህ ነው ይህ ለአሜሪካ አሳልፎ የመስጠቱ የፍርድ ሂደት በዚሁ ሰኔ 12፣ 2019 የህግ ሂደቱ እንዲጀመር የሚፈለገው።

 ወደ አሜሪካ ተላልፎ በመሰጠቱ ጉዳይ ላይ የተከሰስኩት ከፖለቲካ አስተሳሰቤ ጋር ተያይዞ ነው ብሎ አሳንጅ የሚከራከር ከሆነ ተስፋ ሲኖረው ይችላል የሚሉ አሉ። ጠበቆቹም ይህንን መከላከያ እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል። የሞት ፍርድ የሚያስከትል ክስ እንደማይመሰርቱ ግን አሜሪካውያን ቃል ሊገቡ ይችላሉ። በሌላ በኩል በስዊድን በኩል ይህ አሳልፋችሁ ስጡን የሚለው ጥያቄ ሊቀሰቀስ የሚችል ከሆነም ጉዳዩን አወዛጋቢ እንደሚያረገው ይልቁንም የአውሮፓ አካል ስለሆነች ከአሜሪካ ቀድሞ ስዊድን አሳንጅን የማግኘት እድል እንዳላት የሚተነብዩ አሉ። በአውሮፓ ውስጥ ባለው የተቀላጠፈ ህግ ምክንያትም እንግሊዞች የሚቀላቸው ለስዊድን ማስተላለፉ እንደሚሆን የዘርፉ ሰዎች ይገልፃሉ። የሚገርመው ይህ ሰው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ ተግባሩ ብዙ አለማቀፍ ሽልማቶችን ተቀብሏል። ከነዚህም የአውስትራሊያ ታላቁ የጋዜጠኝነት ክብር፤ የወልአለይ ለጋዜጠኝነት የተበረከተ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሽልማት፤ የእንግሊዙ ማርታ ገልሆርን የጋዜጠኝነት ሽልማት፤ እና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ሽልማት ጥቂቶቹ ሲሆኑ፤ ከዚህም አልፎ ለኖቬል ሽልማትም በእጩነት ቀርቦ እንደነበር ይነገራል።

 አሜሪካ በተመሳሳይ ከኮምፒዩተር መረጃ በማስፈትለክ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት የእንግሊዝ ዜጎች ማለትም ሎራ ሎቭ እና ግሪ ማክነን ተላልፈው እንዲሰጧት በተለያየ ጊዜ የጠየቀች ቢሆንም በሁለቱም ሰዎች ጉዳይ አልተሳካላትም። የአሳንጅ ጉዳይ ግን እንግሊዛዊ ካለመሆኑ የተነሳ ምን ውሳኔ እንደሚሰጥ ለመገመት ከባድ ይሆናል። ደግነቱ ሁላችንም የሚሆነውን በጊዜው እናያለን።

ዘመን አይሸሬው “ሳውንድ ትራክ”

ገና በልጅነቴ በሲኒማ አዲስ ከተማ ያየሁት አንድ ፊልም ለረጅም ዓመታት ውስጤ ተቀብሮ ነበር:: ወቅቱ መርካቶ በሚውሉ የሰፈራችን ጎረምሶች ገፋፊነት ከዚህ ፊልም ቤት ጋር ስተዋወቅ በጨለማ ውስጥ ስለሚታየው ጥበብ አንዳችም እውቀት አልነበረኝም:: ጎረምሶቹ የፊልሙን ታሪክ በገባቸው መጠን ሲተርኩልን ግን አፋችንን ከፍተን ነበር የምናዳምጠው::

 በዚያ ጨቅላነት ዘመን አንድ ፊልም ተመልክተን ወጣን:: የጓደኞቼን የአረዳድ ብቃት ባላውቀውም የፊልሙ ሀሳብ ሳይገባኝ በፊልሙ ሥር ሲሰማ የቆየው ክላሲካል ሙዚቃ ግን በውስጤ ነግሶ ቆየ:: በልጅነቴ ያንን የፊልም ሙዚቃ በፉጨት እያስመሰልኩ አንጎራጉር ነበር:: ረጅም ዓመታት አለፉ::

ወደ ሥራው ዓለም በገባሁ ወቅት ያ ሙዚቃ ከተደበቀበት የአእምሮዬ ጓዳ እየወጣ ፊልሙንና የድሮውን አዲስ ከተማ ሁኔታ ያስታውሰኝ ጀመር:: የሶስቱ ኮከቦች የፊት ገፅታ፣ የሽጉጥ አተኳኮስ ቂንጥ፣ እርስ በርስ ለመገዳደል የሚያደርጉት የጭካኔ ተግባር፣ የፈረሶቹ ኮቴ፣ የበረሃው ስቃይ ከዚያ ምርጥ ሙዚቃ ጋር እየተቀናበረ የተሻለ ስዕል ይፈጥርልኝ ገባ:: እንደዛም ሆኖ ግን የፊልሙን ርዕስ እና የአክተሮቹን ገሃዳዊ ማንነት ማወቅ አልቻልኩም::

 ክላሲካሉን ሳስታውስ ለምን በተፈራረቀ ስሜት ውስጥ እንደምበጫረቅ አላውቅም:: ብቻ ደስ ይለኛል… ደግሞ በቦዘዘ ስሜት ርቄ እመነጠቃለሁ:: ርቆ በሄደው ስሜቴ ውስጥ ያለው እውነተኛ ድባብ በምን እንደሚመሳሰል እና በምን እንደሚለካ ማስረዳት ግን አልችልም:: የሆነ ሙዚቀኛ “Music is the answer. I don´t remember the question” ያለው ለእኔ ትክክል ይመስለኛል:: በጊዜው “ይህን ፊልም ፈልገህ እየው” የሚለውን ስሜቴ አደብ ማስገዛት አልቻልኩም:: ቢቸግረኝ ለቅርብ ወዳጄ ደረጄ ጉዳዩን ነገርኩት:: ፊልሙን ድሮ ቢመለከተውም ስያሜውን ማስታወስ አልቻለም::

 እውነቱን ለመናገር በዚህ ፊልም መነሻነት ይሁን በሌላ በማላውቀው ጉዳይ ስጎረምስ ራሴን ከክላሲካል ሙዚቃ ፍቅር ተጣብቆ አግኝቼዋለሁ:: የአራት ኪሎ፣ የፒያሳ፣ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ መዝናኛ ቦታዎች ይመስክሩ:: በተለይ ማዘጋጃ በምሰራበት ወቅት በቡናም ሆነ በምሳ ሠዓቶች ምርጫዎቼ የነበሩት ክላሲካል ሙዚቃን የሚያንቆረቁሩ ሬስቶራንቶች ነበሩ:: ለመስክ ሥራ ክፍለ- ሀገር ስወጣ ክላሲካል ማዳመጥ ተፈጥሮን በአንክሮ ለማስተዋል እና ከሚስጥራቱ ጋር ለመፉተግ የሚያግዝ ሆኖ ይሰማኛል:: ቴአትር እስኪጀመር የሚሰሙ የተቀነባበሩ መሳሪያዎች የሀሳብ እከክን በሻወር አራግፎ የቀለለ ምናብ የማዘጋጀት ያህል የሚታይ ሚና አላቸው:: ቢሮ ቁጭ ብዬ አርቲክል ስቸከችክም ሆነ ቤት አርፌ ከሥነ-ጽሑፍ ጋር ስነጋገር መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎች እንደ ኳስ ያነጥሩኝ… እንደ ፊኛ ያንሳፍፉኝ… እንደ ጀልባ ያስቀዝፉኝ… የፈለጉበት ምናባዊ አለም በፍጥነት ያደርሱኝ ነበር:: ፕሌቶ በተጠጋጋ ቋንቋ ያለው ይሄንኑ አልነበረም:: “music gives a soul to the universe, wings to the minde, flight to the imagination and life to everthing”

ከረጅም ጊዜ በኋላ ደረጀ ትዕዛዙ “ያን ነገር አገኘሁት እኮ! ” ብሎ ሰበር ሃሴት ይዞ ብቅ አለ:: ለዘመናት የተሰወረብንን ፊልም:: “ክሊንት ኢስትውድ የሚሰራበት ፊልም ነው፤ ስያሜው The good, the bad and the ugly ይሰኛል፣ ፈልገህ እየው” አለኝ::

 ደስታዬ ሎተሪ ከወጣለት ሠው ጋር የሚተካከል ነበር:: ጊዜውም በማደጉ ሌላ ዕድለኝነትን አንግቧል:: ምክኒያቱም በሲኒማ አዲስ ከተማ የታዩትን ፊልሞች ቢሮ ቁጭ ብሎ በኮምፒውተር መመልከት ይቻላልና:: ፊልሙ ያልታወሰኝ የረዘመ ስያሜ ስለነበረው ነው አልኩኝ እንደገና:: ነገሩ በኢለመንተሪ ደረጃ ፊልም የምናየው ርዕሱን አብጠርጥረን አልነበረም:: ተሰብስበን እንሄዳለን፤ ሬክላሙ ደስ ካለን ያለው ከሌለው ተበድሮ ልንገባ እንችላለን::

 ይሄን ምትሀተኛ ፊልም ደስ እያለኝ ኮመኮምኩት:: አክተሮቹ እንደናፈቁኝ ዘመዶቼ እንዴት ናችሁ? እያልኩ:: ፊልሙን ካጣጣምኩ በኋላ ከራሴ ጋር በጥያቄዎች ተፋጠጥኩ:: ፊልሙ በውስጤ ተቀርፆ የቀረው በክላሲካሉ ብቻ ነው ወይስ በመላው ታሪኩ? ያኔ ታሪኩን ካልተረዳሁት ይህን ያህል በገዘፈ ደረጃ ለመደሰት በቂ ምክንያት ይፈጥርልኛል?ብቻ ክላሲካሉ ገዝፎ ጠብቆኛል… አሁን የፊልሙ አፅመ-ታሪክ በቅጡ ሲገባኝ በደራሲው ብዕር ተደንቄያለሁ… ብቻም አይደለም በአዘጋጁ ልቀት ተደምሜያለሁ:: ለዚህም ነው ሙዚቃው እና ታሪኩ እኩል ያምታቱኝ::

ለምን ታሪኩ በአጭሩ አላሳያችሁም ?… ፊልሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የበቃው በፈረኘጆቹ አቆጣተር በ1968 ነው:: ታሪኩ የሚያጠነጥነው ደግሞ በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ሶስት የተለያየ ባህርይ ያላቸው (ጥሩ፣ መጥፎና አስቀያሚ) ሠዎች የገንዘብ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት መራራና አስቀያሚ ትግል ላይ ነው:: ገንዘብ እስከተከፈለው ድረስ ማንንም የሚገድለው የወታደር ሹሙ ኤንጅል አይስ (lee van cleef) ከህብረቱ ጦር ሠራዊት ወርቅ የሰረቀውን ቢል ካርሠንን እንዲገድል በቤከር ይቀጠራል:: የህብረቱ ጦር አባል የነበረውን ስቴቨንን ስለ ጉዳዩ ሲጠይቅ ራሡ ቤከርን እንዲገድለው አንድ ሺህ ዶላር በመስጠት ያግባባዋል:: ገንዘቡን ተቀብሎ ስቴቨንን ወዲያው ይገድለዋል::

 ቤከር ጋ ተመልሶ በመሄድ ክፍያውን ከተቀበለ በኋላ እሡንም ይገድለዋል:: በሌላ በኩል ሠዎችን ለመግደል፣ በመዝረፍና ሴቶችን በመድፈር በመንግሥት የሚፈለገው ቱኮ (Eli Wallach) በብሎንዴ ከተያዘ በኋላ አንድ ስምምነት ይገባል:: ሽፍታውን ለያዘ ግለ ሰብ ይሰጣል የተባለውን 25 ሺህ ዶላር ተረክቦ እንደሚያስመልጠውና ገንዘቡን ለሁለት እንደሚካፈሉ:: በእርግጥም ሽፍታው በህዝቡ ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ግፎች ተዘርዝረው በአደባባይ ሊሰቀል ሲል ብሎንዴ (clint east wood) የታሰረበትን ገመድ በጥይት በመበጠስ ተያይዘው ይሰወራሉ:: ይህን መሰል ድርጊትም በሌሎች ከተሞች እየሄዱ በመፈፀም ገንዘቡን ይካፈሉ ነበር:: ሆኖም ቱኮ ይህን መሰል ጀብደኝነት ታክቶኛል ሲል ብሎንዴ በረሃ ውስጥ ትቶት ይሄዳል:: ቱኮ ተበሳጭቶ ቂም ያዘ:: ሊበቀለውም ይፈልገው ጀመር:: ብሎንዴ የወንጀለኞችን ገመድ በመበጠስ ሥራውን እየፈፀመ ሳለ በድንገት በቱኮ ይማረካል:: ያውን የበረሃ ችግር ሲመልስ መቶ ማይል በረሃ አስጉዞ ሊገድለው በፈረስ ጀርባ ላይ ሆኖ ይሳለቅበታል:: የስቃዩ ጫፍ ላይ መድረሱን የተገነዘበው ቱኮ ሊገድለው ሲወስን አንድ ሠረገላ እየቀረበ ሲመጣ ይመለከታል:: ሰረገላው በርካታ የሞቱ ወታደሮች እና በማጣጣር ላይ የሚገኘውን ቢልካርሠንን የጫነ ነበር::

ካርሠን ሁለት መቶ ሺህ ዶላር የሚያወጣው ወርቅ የት መካነ መቃብር እንደሚገኝ መናገር ጀምሮ በውሃ ጥም መቀጠል አልቻለም:: ቱኮ ውሃ ሊያመጣለት ሲጣደፍ ብሎንዴ እንደምንም ተጠግቶ የመቃብሩን ስም ይሰማል:: ቱኮ ውሃ ይዞ ሲደርስ ቢል ካርሠን ሞቶ ነበር:: ጓደኛውን ሊገድለው በረሃ ድረስ ይዞት የመጣው ትኮ አሁን ደግሞ ብሎንዴ እንዳይሞት መንከባከብ ግድ ሆነበት:: ሁለቱ ጓደኞች እና ባላንጦች የተቀበረውን ሀብት ለመፈለግ ጉዞ ሲጀምሩ በህብረቱ ወታደሮች ይማረካሉ:: በምሩኮኞች ቆጠራ ወቅት የሟቹ ቢል ካርሰን ስም ሲጠራ ቱኮ “አቤት እኔ ነኝ” በማለቱ በኤንጄል አይን ትኩረት ትኩረት ውስጥ ይወድቃል:: የራስህ ስም ባልሆነ ስም ምን ፈልገህ ነው ሚስጥር አውጣ ተብሎ አሰቃቂ ድብደባ ከደረሰበት በኋላ የሚያውቀው ብሎንዴ መሆኑን በመናገሩ ኤንጀል አይስ ሁለት ዕቅዶችን ይነድፋል:: ትኮን ወደ መግደያ በባቡር ማሳፈር፣ ከብሎንዴ ጋ ደግሞ ወደ ሃብቱ ሄዶ እኩል ለመከፈል መስማማት::

ቱኮ በሚያስገርም ጥበብ ዝሆን የሚያህለውን ወታደር ገድሎ ይጠፋል:: ብሎንዴ የሹሙን ጠባቂዎች አንድ በአንድ ገድሎ ይሠወራል:: ቱኮ እና ብሎንዴ ከእንደገና ግንኙነት ገጥመው ኤንጅል አይስን ለመግደል ቢያደቡም ታዳኙ ይሰወርባቸዋል:: ወደ ወርቃማዋ ከተማ ሲገሰግሱ ራሳቸውን የርስበርሱ ጦርነት ወደ ተጋጋመበት ቁልፍ ቦታ ያገኙታል:: ጦርነቱ በተአምር ካልቆመ በስተቀር ወደሚያልሙበት የመቃብር ሥፍራ ለመሄድ መንገድ አልነበራቸውም:: ተደብቀው አንድ የጭካኔ ተግባር ይፈፅማሉ:: ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች መሃል የሚገኘውን ትልቅ ድልድይ በተቀጣጣይ ፈንጂ ማውደም:: ይሄኔ ብሎንዴ ቱኮን ለመፈተን በማሰብ የመቃብሩ ስም “አርክሳንተን ነው” ሲል ይነግረዋል:: ቱኮ አላስቻለውም የአንድ ተዋጊ ፈረስ ሠርቆ ወደ ቦታው ብቻውን ይገሠግሳል:: መካነ መቃብሩ ውስጥ ካካሄደው አድካሚ የፍለጋ ሩጫ በኋላ የተባለውን ስም አግኝቶ በእንጨት መቃብሩን ይቆፍራል:: ብሎንዴ በቦታው እንደደረሰ አፈሙዝ ወድሮበት በደምብ እንዲቆፍር አካፋ ይወረውርለታል:: ቆይቶ ኤንጅል አይስ ደርሶ ሌላ አካፋ ይወረውርና ብሎንዴም ጭምር እንዲቆፍር ይጠይቃል:: ብሎንዴ ሁለት ሚስጥራት ስላሉት ለግዴታው ተገዢ አልሆነም::

 አንደኛው ሚስጥር ትኮ እየቆፈረ ያለውን የሰው መቃብር የተሳሳተ መሆኑን ውስጡ ያለውን የሰው አፅም በማሳየት ማረጋገጥ ነበር:: ወርቁ ያለበትን መቃብር ድንጋይ ላይ ይፅፍና በተኩስ የሚያሸንፈው ሰው መውሰድ እንደሚችል በመናገሩ ሶስቱም ትሪያንግል በሆነ ቅርፅ ወደኋላ ለተኩስ ማፈግፈግ ይጀምራሉ:: አንዱ ከአንዱ ጥይት እንዴት መትረፍ እንደሚችል ፍርሃት እና ድንጋጤን የሚያሳብቁ አይኖች ይታያሉ:: ብሎንዴ ግን ሁለተኛውን ሚስጢር በመጠቀሙ የኤንጄል አይስን እጆችና ፊት ብቻ ነበር የሚከታተለው:: በመጨረሻ ኤንጀል አይስ በብሎንዴ ተመትቶ ይወድቃል:: ትኮ ለመተኮስ ጥረት ቢያደርግም ሽጉጡ ውስጥ ጥይቶች አልነበሩም:: ብሎንዴ (ደራሲው ሳይሆን ቱኮ ያወጣለት ስም ነው) ይህን ያደረገው የመቃብሩን ስም ከነገረው አንድ ቀን በፊት ሌሊት ላይ ነበር:: ያልታወቀ (unknown) የተባለው መቃብር ተቆፍሮም ሃፍቱ መውጣት ችሏል:: ቱኮ ወርቁን በደስታ እየበተነ ሲፈነጥዝ ብሎንዴ ለመታነቂያው ገመድ እያዘጋጀለት ነበር:: የገመድ ብጠሳውን ስራ በእሱ እንዲጀመር ሁሉ ለእሱ ሲጨርስ ፊልሙ ያልቃል::

ይሄን ፊልም ባደገ ህሊናዬ ገምግሜ የሁሌም ምርጥ ነው ያልኩት በአምስት መሰረታዊ ጉዳዮች ይመስለኛል:: ከላይ ጨረፍ በደረግኩት ግሩም ውስብስብ ታሪኩ፣ የማይረሳ ገፀ-ባህርያትን በመፍጠሩ፣ የካሜራ አቀራረፁ፣ የመቼት ምርጫው እና ማጀቢያ ሙዚቃው (sound track) ናቸው::

በዚህ ፊልም ባልተለመደ መልኩ ሶስት አክተሮች እኩል የጀግንነት ድርሻ ተላብሰው ይታያሉ:: ፊልሙ ከጅማሬው እስከፍፃሜው ዋና ለሚባል አክተር ከማድላት (The Good) ይልቅ በእኩል ደረጃ የሁሉንም ተግባራት ሲያሳይ ይታያል:: ሶስቱም ሃገሪቱ ለገባችበት የርስ በርስ ጦርነት ደንታ ሳይኖራቸው ሃብት ለማከማቸት ይተጋሉ:: ሶስቱም ባህርያቸውን በአይረሴ መልኩ ተጫውተዋል:: የሚገደለውን በጭካኔ ገድለዋል:: የሚዘረፈውን ያለ ርህራሄ ሰብስበዋል:: በመንግስት፣ በሃይማኖት በህብረተሰቡና በራሳቸው ህሊና ላይ ክህደት ፈፅመዋል:: እርስ በርስ ሊጠፋፉ ጦር ተማዘው መሰሪነታቸው ታድጓቸዋል:: የገፀ-ባህርያቱ ንግግር ታሪኩን በፍጥነት የሚያራምድ ብቻ አይደለም:: ምፆታዊ፣ አላጋጭ የበላይና ባለግዜነትን ጠቋሚ ጭምር ነው:: ለምሳሌ ያህል ቱኮ ብሎንዴን እንዲህ ይለዋል:: “ጓደኛዬ በዚህ ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ:: በአንገታቸው ገመድ የሚያስገቡ እና ይህን ገመድ በመበጠስ ሥራ የሚተዳደሩ” ብሎንዴ በፊልሙ ማብቂያ አከባቢ ትኮን እንዲህ ሲል ይሰማል “ጓደኛዬ በዚህ ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ:: የተቀባበለ ሽጉጥ ያላቸው እና መሬት ቆፋሪዎች፣ እናም መሬቱን ቆፍር!”

ካሜራ በዛ ባለ መልኩ ቀርቦ ሲቀረፅ (close up) ያየሁት በዚህ ፊልም ላይ ነው:: በዚህም ምክኒያት የገፀ-ባህርያቱን ፍርሃት፣ ድፍረት፣ ስቃይ ጭካኔ እና መሰሪ ሀሳብ ሁሉ በቀላሉ እንመለከታለን:: ይህ ልዩ ጥበብ ተመልካቹ ታሪኩን በጉጉት እና በስሜት እንዲመለከት ያስገድደዋል:: በተቃራኒው በሩቅ ቀረፃው (Long shot) ፊልሙ የተሰራበት ውብ መልክዓ ምድራዊ ገፅታ በግድ እንድናደንቅ ያደርገናል::

 ሌላው እና ዋነኛው ነጥብ የሙዚቃው (sound track) ገዳይነት ነው:: በልጅነቴ የመሰጠኝን ይህን ሙዚቃ ባደገው ምናቤ ለማጣጣም ሞክሬያለሁ:: አዘጋጁ ሙዚቃውን ከሶስቱ ዋና ገፀ-ባህርያት ድርጊት አንፃር መጠነኛ በሆነ መልኩ ለመለያየት ጥረት ማድረጉን አንብቤያለሁ:: ደግሞም ትክክል ነው:: ብሎንዴ ከሚፈፅማቸው ተግባራት በኋላ የሚሰማው ክላሲካል ቀጠን ባለ የዋሽንት ድምፅ የታጀበ ነው:: ከኤንጅል አይስ ተግባራት በኋላ በሚከተለው ሙዚቃ ኦካሬና (ocarina) ከተባለው የኢጣሊያ መሳሪያ ጋር የተያያዘ ይመስላል:: ከቱኮ ተግባራት በኋላ የምንሰማው ክላሲካል የሰው ድምፅ አለበት::

 በእኔ እምነት ይህ መሳጭና ያማረ ሙዚቃ ፊልሙን በታላቅነት በማቆም ትልቅ ሚና ተጫውቷል:: የተመልካችን ሙሉ ትኩረት ለመሳብ… ስሜት ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር እንዲሁም የገፀ-ባህርያትን ድርጊት ወይም ውስጣዊ ሃሳብ ለማንፀባረቅ አጋዥ ሆኗል::

ጣሊያናዊው ኢኒዮ ማርኮኒ ያቀነባበረውን ይህን ውብ ክላሲካል ሙዚቃ (sound track) ዛሬም ደጋግሜ እሰማለሁ:: ከወዲያኛው ዓለም ምን እንደምቋጭ አላውቅም:: ሀሴት ከማድረግ ውጪ:: ይህን ዘመን አይሸሬ ክላሲካል ፊልም ዛሬም ደጋግሜ አያለሁ:: ዳይሬክተሩን ሰርጂዮ ሊኦንን እያመሰገንኩ:: ጥሩ፣ መጥፎ እና አስቀያሚ የተባሉ ሶስት ታላላቅ አክተሮችን እያደነቅኩ:: ይህ ድንቅ ፊልም የኦስካር ሽልማትን አለማግኝቱ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው::

 ከዚህ የፊልም አመዶች /ሶስት አክተሮች/ ውስጥ ዛሬ በህይወት ያለው ክሊንትስቱድ ብቻ ነው:: ልሎቹ ምስላቸውንና የፊልሙን ታሪክ ለታሪክ አስቀምጠው አልፈዋል:: በህይወት ለው አዛውንቱ ጎበዝ በዚህ ዓለም ሁለት ዓይነት ዳኞች አሉ:: ለእውነት የቆሙና በእውነት ላይ የቆሙ:: ወደ ሀገራችን ስንተረጉመውም ሁለት ዓይነት የፊልም አፍቃሪዎች፣ ሁለት ዓይነት የፊልም ፀሐፊዎች፣ ሁለት ዓይነት የካሜራ ሙያተኞች እና ሁለት ዓይነት የፊልም አዘጋጆች አሉ:: ይህን ታላቅ ፊልም ያላዩ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top