ማዕደ ስንኝ

ግጥም የማይረባ ብዕር

አደራውን ክዶ ብዕር ከሸፈተ፣

የሀቅ ነቁጡን ስቶ ዘሩን ከጎተተ፣

ከዓላማው ተጣልቶ ሚዛኑን ካደፋ፣

ስልጣኑን ሊያመቻች ቀለሙን ከደፋ፤

ዘረኛ ሊዋጋ ዘረኛ ከሆነ፤

ሚዛኑ ካደፋ ምኑን ብዕር ሆነ?…

ዕውነቱን ለጥቅሙ ደልዞ ከጻፈ፣

ቀስጦ ወስልቶ ክብሩን ከገፈፈ::

መልኩ ያለየለት ባሕሪው ብልጭልጭ፣

ይህን መሳይ ብዕርስ ቢሰብሩትም አይቆጭ::

ተግባሩን ዘንግቶ ብዕር ከዘመመ፣

ድግስ ባየ ቁጥር ሲያኳሽ ከከረመ፣

ኅሊናው ሽጦ ስሙን ከቀየረ፣

ምኑን ብዕር ሆነ ጌታዳር ካደረ፣

ዘረኛን አጋልጦ ከህዝብ ካልወገነ፣

ዲያቢሎስ ነው እንጂ ምኑን ብዕር ሆነ!

ጠበቃ የማይሆን ነገ ተከሳሽ ነው፣

ጽፎ ካላዳነ ሰባብሮ መጣል ነው::

በጨለማው መርፌ ከርቁ ሲታየው፣

በቀን ዝሆን ቆሞ መች በቅጡ ለየው?

ሲደማ ካልታየ በዕውን ለእውነት፣

በእሳት ማጋየት ነው ብዕር ያበለለት::

ትናንት ከፃፈለት ከቃኘው ዕውነታ፣

ዛሬ ባዲስ አቋም ልቡ ካመነታ::

ነገር የቀበሮ ልቡን ከሰረቀው፣

ይዋል ይደርና ታሪክ ይጠይቀው::

ልፋፌ ክታቡ ሀቅ የለውምና፣

ይገረም ይወገዝ “ብዕር” ቀረ መና::

የሀቅ አብነቱ ገጹ ከጠፋበት፣

ብዕር ድንጋይ አይቶ “ዳቦ ነው” ያለ ዕለት::

ወገኑ ሲቃጠል ሲጮህ ከሩቅ አይቶ፣

ካላንገበገበው ጢሱ ባዓይኑ ገብቶ::

ግፍና በደልን ደፍሮ ካልገዘተ፣

ሀቅ ይነቀኝ ብሎ ለእውነት ካልሞተ፣

ከጦር ሰባቂ ጋር ከተጎራበተ፣

መቃ ብዕርም አይደል፣ እሱስ መቃብር ነው -ቀለሙን የደፋ፣

ሥጋ ደሙ ሽቶ በቁም የከረፋ::

በአስማማው ኃይሉ

               /ከብዥታ ስብስብ ግጥሞች/

እኔ እወድሻለሁ

ብዙ ሺህ ዘመናት

 እልፍ አእላፍ ሌሊት

ሚሊዮን መሰለኝ

 ፍቅሬ አንችን ስወድሽ ቀኑ ረዘመብኝ፡፡

እኔ እወድሻለሁ

 የሰማይ መሬቱን

የባህር ስፋቱን

የዓለም ዳርቻ የርቀቱን ያህል

እንደ ፅጌረዳ

እንደ አደይ አበባ

እንደ ሎሚ ሽታ፡፡

እንደ ዕጣን ጢስ እንጨት፤ እንደ ከርቤ ብርጉድ፤

እኔ እወድሻለሁ፤

አበባ እንዳየ ንብ

እንደ ቢራቢሮ ጫካ እንደሚያስሰው

ፍቅርሽ በፍቅሬ በፍቅርሽ ልቅመሰው

ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኳር፤

አማርኛ አይብቃ፤

 ወይ ጉድ!

ባለም ቁዋንቁዋ ቢወራ

እኔ እወድሻለሁ እንደ ማታ ጀንበር፡፡

እንደ ጨረቃ ጌጥ፤

እንደ ንጋት ኮከብ፤

እኔ እማልጠግብሽ

ስወድሽ ስወድሽ ስወድሽ ስወድሽ፡፡

ጡት እንዳየ ህፃን ወተት እንዳማረው

ጠጋ በይ ዘመዴ አፍሽ ህይወቴ ነው፡፡

ጣይ እንዳየ ቅቤ

ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፤

አፈር መሬት ትቢያ ውኃ እንደሚበላው

ፍቅሬ አንችን ስወድሽ

ብዙ ሺህ ዘመናት

እልፍ አእላፍ ሌሊት

እኔ እወድሻለሁ

አይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ

ስወድሽ ስወድሽ

 እኔ እወድሻለሁ፡፡

16/9/1960 የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ

ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top