አጭር ልብወለድ

ጄ ኔ ራ ሎ ቹ


/ይህ ጽሑፍ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ በልቦለዳዊ በሥነ ጽሑፍ ቅርስ የቀረበ ነው/

ወደ እስረኞቹ ግቢ የመጣው ሰው ‹‹ኮሎኔል አምሳሉ!!!›› ብሎ ተጣራ። እስረኛው ወደተጠራበት ቦታ ሄደና ‹‹ማነው የፈለገኝ?›› አለ። ‹‹እኔ ነኝ››

‹‹ለምን አስጠራኸኝ?››

‹‹መልእክት አለህ››

‹‹ምንድነው?››

‹‹እቃ ነው የተላከልህ››

‹‹ምንድነው እሱ?››

‹‹ለጥርስህ ነው››

‹‹ምን አልክ?››

‹‹ኮልጌት ተልኮልሃል››

‹‹ማነው የላከው?››

‹‹ጄኔራል አብዱላሂ ናቸው››

‹‹ሌላ እቃ አልተላከልኝም?››

‹‹ምን አልክ?››

‹‹ሌላ ሰው…ማለት…››

ኮሎኔሉ ግራ ተጋባ። የተቀበለውን ኮልጌት ይዞ በድንጋጤ ወደ ክፍሉ ሄደ። ኮልጌት እንዲያመጡለት ማንንም አላከም። ወይም አልጠየቀም። የሚበቃውን ያህል ኮልጌት አለው። ግን ሌሎች ሰዎች ለእርሱ እቃ መላክ አለባቸው። አሁን ያስደነገጠውም ከነዚህ ጄኔራሎች ምንም ነገር ባለማግኘቱ ነው። የጠዋቱን ፊልም ማጠንጠን ጀመረ። አንደኛው ጄኔራል የተናገሩትን ነገር አስታወሰ። ነገሩን ሲያስበው ‹‹አይደረግም!!!!!›› እያለ ለብቻው ማውራት ጀመረ። ስለዚህ ኮድ እቃና ስለተፈጠረው ነገር ለማንም ሰው መንገር የለበትም። የሰውየው አባባል ትክክል ከሆነ ሞት ፊቱን ወደ እርሱና ጓደኞቹ እንዳዞረ አሰበ። የጠዋቱን ጨዋታ በድጋሚ ማሰላሰል ጀመረ። ነገሩ ሲጀመር እንደዚህ ነበር።

 ገና በማለዳው በቆርቆሮ በታጠረው ግቢ ውስጥ የሚያወሩት ሁለት ወታደሮች ዛሬ በእስረኝነት እዚህ ግቢ ውስጥ በከባድ ሁኔታ የሚጠበቁ ናቸው። በውትድርና ትምህርት በጣም የሚታወቁት ጄኔራል ተስፋዬ ትርፌ ለኮሎኔል አምሳሉ እያወሩለት ነበር። ጄኔራሉ እየተጫወቱ ቢሆንም ውስጣቸው ግን ደስተኛ አልነበረም። ገና በጠዋቱ ፊታችው ጭፍግግ ብሏል። ጄኔራሉ ዛሬ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት እለት በመሆኑም የምትወስዳቸውን መኪና እየጠበቁ ነው። መኪናዋ መምጣት ከሚገባት ጊዜ ዘግይታለች። ዛሬ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን እንደሆነ ገምተዋል። ግን ምን ይወሰንብን ይሆን? የሚለው ጉዳይ የሌሎች እስረኛ ጄኔራሎችም ጥያቄ ነበር። በዚህ ጉዳይ ጄኔራሎቹ ሰሞኑን እየተወያዩበት ነበር።

ጉዳያቸው የሚታየው በጦር ፍርድ ቤት ሲሆን ዋናው ዳኛ ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ ስጋት አድሮባቸዋል። እስረኞቹ የሚገኙት ቤተመንግስት ሲሆን ፍርድ ቤቱ እነርሱ ካሉበት 200 ሜትር ያህል ቢርቅ ነው። ጄኔራል ተስፋዬ ትርፌ ከኮሎኔል አምሳሉ ጋር እያወሩ ባለበት ጊዜ የፖሊስ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ወርቁ ዘውዴ ተቀላቀሉና ሶስት ሆነው ማውጋት ጀመሩ። በወሬያቸው መሀል ገልመጥ እያሉ ወደዋናው በር ይመለከታሉ። አሁንም የመኪናዋን መምጣት ቢጠባበቁም በሰዓቱ በር ላይ አልተገኘችም። እነዚህ ሶስት ሰዎች የጀመሩትን ወሬ ሳይጨርሱ አንድ ትልቅ መኪና እስረኞቹን ለመውሰድ ግቢው በር ላይ ቆመ። ቀጥሎም እስረኞች ወደ መኪናው እንዲገቡ ተነገራቸው። መኪናው ትልቅ ብቻ ሳይሆን መስታወት የሌለው ድፍን ያለ ነገርም ነው።

ከመኪናው ጋር ወታደሮች አብረው መጥተዋል። እስረኞቹ በተለያየ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄዱ ወታደሮች አብረዋቸው ይጓዛሉ። አሁን ግን የመጡት ወታደሮች ብዛት አላቸው። መሳሪያ አያያዛቸውም የተለየ ነበር። ለዚህ ሁሉ ነገር ትኩረት የሰጠው እስረኛ አልነበረም። አንድ ሰው ግን ጥርጣሪያቸው የተለየ ነበር። ሶስቱ ሰዎች አሁንም እያወሩ ቢሆንም ጄኔራል ወርቁ ሊወስዳቸው የመጣውን መኪና በደምብ ተመለከቱትና በድንጋጤ መንፈስ ‹‹አምሳሉ!!!!›› አሉ።

‹‹አቤት››

‹‹በቃ!!! ይሄ ሰውዬ ሊገለን ነው››

‹‹ማን?››

‹‹መንግስቱ››

‹‹በምን አወቁ?››

‹‹መኪናው››

‹‹የቱ መኪና?››

‹‹በር ላይ የቆመው››

‹‹ምን የተለየ ነገር አለ?››

‹‹እኔ እኮ ፖሊስ ነኝ››

‹‹እና››

‹‹ይሄ እኮ የሚገደሉ ሰዎች የሚሄዱበት መኪና ነው››

ይህ ቀን ግንቦት 11 ነው። እለቱ ደግሞ ቅዳሜ ነው። የጄኔራል ወርቁ ንግግር ሁለቱን ሰዎች አነቃቸው። ጄኔራሉ አሁንም እልህ በተቀላቀለበት ሁኔታ ማውራት ጀመሩ። መኪናውን እያዩ ‹‹አብቅቶልናል›› በሚል ስሜት እየተናገሩ ነው። ጄኔራል ወርቁ አሁንም ስጋት ገብቷቸው እያወሩ ነው። ‹‹… በፊት ኢሕአፓ ተብለው የታሰሩት በሞት እንዲቀጡ ሲወሰን ይሄ መኪና ነበር የሚወስዳቸው። በመኪናው የሚሄዱትን እስረኞች መሞታቸውን ለማረጋገጥ ከኮሚቴው ሁለት ሰዎች ተመድበው ያረጋግጡና ሪፖርት ያደርጉ ነበር። ዛሬ እኛንም ሊጨርሱን ነው ይሄን መኪና ያመጡት። የፍርድ ቤቱ ነገር አብቅቶለታል።›› በማለት ተናገሩ። አጠገባቸው ያሉት ሰዎች ግምታቸውና ጥርጣሬያቸው የተጨበጠ እንዳልሆነ ቢነግሯቸውም በእነርሱም ዘንድ ትልቅ ስጋት ነበረ። እነጄኔራል አብዱላሂን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሰዎች ተቀላቅለዋቸው ጄኔራል ወርቁ ባነሱት ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ማጋራት ጀመሩ። ጉዳዩ የራሳቸው በመሆኑ ሞት እንደሌለበት ራስ በራስ የማጽናናት አይነት ማውራት ጀመሩ። ቢሆንም መኪናውን እያዩ እውነት ይሆን እንዴ? በሚል ስጋት ላይ መውደቃቸው አልቀረም።

 እነዚህ ሰዎች ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ላይ መፈንቅለ መንግስት አድርገው የታሰሩ ናቸው። ለአመት ያህል ጉዳያቸው በጦር ፍርድ ቤት እየታየ የቆየ ሲሆን ዛሬ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣቸዋል። መፈንቅለ መንግስቱ በተደረገበት ጊዜ የተወሰኑ ጄኔራሎች ተገድለዋል። እነዚህ ግን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ በመሆኑና አመት ስላለፈው ቢከፋ ቢከፋ እድሜ ልክ እስር እንጂ ግድያ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። በዚህ የተነሳ ጄኔራል ወርቁ አሁን የተናገሩት እውነትነት የሌለውና የተሳሳተ ግምት መሆኑን በመንገር ፖሊሳዊ ጥርጣሬያቸውን ውድቅ አደረጉት። ያም ሆኖ የመኪናው ጉዳይ ማሳሰቡ አልቀረም። ምክንያቱም እነዚህ ጄኔራሎች ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የነበረው በሚኒባስ መኪና ነው። ዛሬ ለምን ቀየሩት?

ጄኔራል ወርቁ ፖሊስ ናቸው። ፖሊስ ደግሞ በጥርጣሬ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ ፖሊስነታቸው እንጂ እውነታ ላይ ሆነው አይደለም የተናገሩት የሚለውን ጉዳይ መቀበል ፈለጉ። መቀበል የፈለጉት ደግሞ እውነታው ይሄ አይደለም ብቻ ለማለት ሳይሆን ክፉ ነገር እንዳይመጣ ከመፍራትም ጭምር ነበር። ከመጀመሪያዎቹ ሌላ አሁን በዚህ ወሬ መሀል እየተሳተፉ የሚገኙት ሌሎች ጄኔራሎችን ጨምሮ የሰውየውን ሀሳብ እያጣጣሉ ሳለ ወደመኪና እንዲገቡ ተጠየቁ። ለወሬው ከተሰባሰቡት ስድስት ሰዎች ለፍርድ የሚሄዱት አምስቱ ብቻ ናቸው። ኮሎኔል አምሳሉ ግን እዚህ ግቢ የሚቀሩ ናቸው። የእነርሱ ተራ ሌላ ቀን ነው። እየቀፈፋቸው ወደ መኪናው የሚገቡት ሰዎች ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ኮሎኔል አምሳሉ ቅድም ጄኔራል ወርቁ ባወሩት ነገር ግራ ስለተጋባ ‹‹ታዲያ እንዴት ነው ማወቅ የሚቻለው?›› አለ።

‹‹ምኑን››

‹‹መትረፋችሁን?››

‹‹እቃ እንልክልሃለን››

‹‹ምን ማለት ነው?››

‹‹እቃ ከላክንልህ በህይወት አለን ማለት

ነው››

‹‹እዚህ አትመለሱም ማለት ነው?››

‹‹ካልተመለስን ወይም ካልተገደልን እቃው ይነግርሃል››

ከአስር በላይ የሚሆኑ የሀገሪቱ ታላላቅ ጄኔራሎች ድፍኑ መኪና ውስጥ ገቡ። እነዚህ ሰዎች በወታደራዊ እውቀታቸው የደረጁና የኢትዮጵያን ጦር ወደዘመናዊነት ያሸጋገሩ ትልቅ ክብር ያላቸው ቢሆንም በእንደዚህ አይነት መኪና ተከርችሞባቸው መሄዳቸው በግቢ ውስጥ ያሉትን ሌሎች እስረኛ ወታሮች ቅር ያሰኘ ነበር። ጄኔራሎቹ ከዚህ ቀደም ለፍርድ ሲሄዱ ሶስት ሰዓት ወይም አምስት ሰዓት ግፋ ቢል ስድስት ሰዓት ነበር የሚያቆያቸው። ዛሬ ግን በጊዜ አልተመለሱም። ሰዓቱ እየገፋ ሄደ። አሁንም አልመጡም። ምሽት ላይ እስረኞች ወደ ቤታቻው እስኪገቡ አለመምጣታቸው ስጋት አሳደረ። በኋላ ግን አንድ ወሬ ተሰማ። እስረኞቹ ሌላ ቦታ እንዳሉ ተነገረ። ይሄንን ጉዳይ ሁሉም ተቀበለው።

እነዚህ ጄኔራሎች ወደዚህ እስር ቤት ከመጡ አንድ ወራቸው ነው። ከዚያ በፊት ሌላ ቦታ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ፍርድ ቤት ሄደው ከጨረሱ በኋላ ወደ ሌላ እስር ቤት ይወስዷቸዋል። ስለዚህ የሰዎቹ መቅረት ተገድለው ሳይሆን ተዛውረው ነው የሚለውን ነገር ሁሉም ተቀበለው። የጄኔራል ወርቁ ፖሊሳዊ ጥርጣሬ ትክክል አልነበረም ተብሎ ተደመደመ። በነጋታው ለኮሎኔል አምሳሉ የመጣው መልእክት ደግሞ ግራ የሚያጋባ ነበር። ጄኔራሎቹ ‹‹ከተረፍን እቃ እንልክልሃለን›› ብለውታል። የላኩት ጄኔራል አብዱላሂ ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ተገድለው እሳቸው ተርፈዋል ማለት ነው? ወይስ ምንድነው? ምናልባት በደምብ መልእክቱን አልተቀበለም ማለት ነው? ከተረፍን እቃ እንልካለን ማለት አንድ ሰው ከላከ ሁላችንም አለን ማለት ነው ብለውት ይሆናል። ደግሞም አምስት ሰው ለአንድ ሰው የተለያየ እቃ መላኩ ሌላ ነገር ሊያስጠረጥር ስለሚችል አንድ ሰው ብቻ እንዲልክ ተስማምተውበት ይሆናል። ላለመገደላቸው ይሄ መልእክት በቂ ማስረጃ ነው።

ግን ታዲያ ለምን ወደዚህ እስር ቤት አልተመለሱም? ሌላ ቦታ ቢዛወሩ እቃቸውን መውሰድ አላባቸው። ነገር ግን ባለመምጣታቸው ሌላ ጥርጣሬ ፈጠረ። ቢሆንም ጄኔራል አብዱላሂ መልእክት መላካቸው ሌላ እስር ቤት ተዛውረዋል፤ እቃቸውንም ነገ ከነገ ወዲያ ሊወስዱ ይችላሉ። በቃ ይሄን ያህል መተማመኛ ከተገኘ ጥሩ ነው። ግቢ ውስጥ የነበሩት አብላጫዎቹ እስረኞች ጄኔራል ወርቁ ጠዋት የተናገሩትን ሰምተዋል። በዚህ የተነሳ የሰውየው አጉል ጥርጣሬ ሌሎችንም ማስገረሙ አልቀረም። የዚያን እለትም መነጋገሪያ ይሄ ጉዳይ ነበር። ከሶስት ቀን በኋላ የሁለተኛው ቡድን አባላት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

 እስረኞቹ ወታደሮች ወደፍርድ ቤቱ ሲገቡ ቤተሰቦቻቸው ከሌላው ቀን በተለየ ሁኔታ በብዛት መጥተዋል። ነገር ግን ሚስቶታቸው ሁሉም ጥቁር ለብሰዋል። ሁኔታው እስረኞችን ግራ አጋባቸው። እናም አስደነገጣቸው። ጥቁር የለበሱበትን ምክንያት ለማወቅ ተጣደፉ። ምንድነው ብለው ቀስ ብለው ሲጠይቁ ጄኔራሎቹ መገደላቸውን ነገሯቸው። ፖሊስ አጠገባቸው ስላለ ጉዳዩን በደምብ ለማወቅ ባይችሉም የጄኔራል ወርቁ ፖሊሳዊ ጥርጣሬ ሁሉንም አሳመነ። ማሳመን ብቻ ሳይሆን ነገሩ ወደ እነርሱ እንደመጣ አውቀዋል። የሀዘን ልብስ የለበሱት የነዚህ እስረኞች ሚስቶች ናቸው። የሟቾቹ ጄኔራሎች ሚስቶች ከጓደኝነት አልፈው እንደቤተሰብ የሚተያዩ በመሆኑ ሀዘናቸውን ለመጋራት ነው። ደግሞም የነርሱ ባሎች ሞት በር ላይ ስለሆኑ ጉዳዩ እጅግ አሳስቧቸዋል። ቅዳሜ እለት ወደ ፍርድ ቤት በትልቁ መኪና የተጫኑት ጄኔራሎች ተገድለዋል። የሁለተኛው ቡድን አባላት እንደነርሱ ቀጠሮ እየተሰጣቸው ሲከራከሩ ቢቆዩም ለፍርድ በሄዱ ቁጥር ይገሉናል እያሉ ትልቅ ስጋት ነበረባቸው። ለመጨረሻ ጊዜ ጉዳያቸውን ለማየትና ለመወሰን ለግንቦት 15 ቀን 1983 ዓ.ም ተቀጠሩ።

ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን ምሳ ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ሬድዮ የቀረበው ሰበር ዜና የኢትዮጵያን ህዝብ ያስገረመና ያስደነገጠ ቢሆንም በቤተመንግስት እስር ቤት የነበሩትን የመፈንቅለ መንግስት አድራጊ እስረኞች እጅግ ያስደሰተ ነበር። እነዚህ እስረኞች ለመሞት ሁለት ቀን ነበር የሚጠብቁት። እንደሚገደሉ አውቀዋል። ተአምር ካልመጣ በስተቀር ባለፈው ጊዜ የተገደሉት ጓደኞቻቸውን እንደሚቀላቀሉ አልጠፋቸውም። ከእነርሱ በፊት በሞት የተሸኙት ጄኔራሎች ሊያሳስር እንጂ ሊያስገድል የሚችል ጥፋት ባይሰሩም ውሳኔው የአንድ ሰው በመሆኑ እጣ ፈንታቸው ሞት ሆኗል። አሁን ለመጨረሻ ውሳኔ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ሀሙስን የሚጠብቁት ሰዎች ማክሰኞ እለት በሬድዮ የተሰማው ወሬ ቢያንስ ለመኖር እንደሚችሉ የሚያበስር ዜና እንደሆነ አምነዋል።

 ዛሬ ግንቦት 15 ነው። መፈንቅ መንግስት አድራጊ ወታደሮች የመጨረሻውን ፍርድ የሚቀበሉበት ጊዜ ነው። እስረኞቹ እስከዛሬ ፍርድ ቤት ባደረጉት ምልልስ ጥፋተኛ መሆናቸው ታውቆ ውሳኔውን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥረዋል። ጓደኞቻቸው ጥፋተኛ መሆናቸው ስለተረጋገጠ ሞት ተፈርዶባቸው ተሸኝተዋል። አሁን ፍርድ ቤቱ በነርሱ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ ነው። አሁን ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። የኢሕአዴግ ጦር እየገሰገሰ አዲስ አበባ በር ላይ ደርሷል። በጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን የሚመራው የሃገሪቱ ሰራዊት አዲስ አበባ ላይ ተደራጅቶ እየጠበቀ መሆኑ እየተነገረ ነው።

የመፈንቅለ መንግስት አድራጊ እስረኞች በሁለቱም ወገን ተፈላጊ ናቸው። በስልጣን ላይ ያለው አመራር እስረኞቹ መፈንቅለ መንግስት በማድረጋቸው በሃገሪቱ ህግ መሰረት ሞት ባይኖርም ፍርዳቸውን መቀበላቸው አይቀሬ ነው። ታጣቂዎቹ ገፍተው ሃገሪቱን ከተቆጣጠሩ ደግሞ በጦር ሜዳ የተዋጓቸው በመሆናቸው በነርሱም መፈለጋቸው አይቀሬ ነው። ለጊዜው የትኛውንም ቢሆን መምረጥ የሚቸገሩበት ሁኔታ ላይ ነበር የሚገኙት። ከነዚህ ባለትልቅ ማእረግ ወታደር እስረኞች መካከል በጥበቃው መላላት የተነሳ ከታሰሩበት ለማምለጥ የፈለጉም ነበሩ። ካሁኑ በግርግሩ ማምለጥና ከከተማው ሆነ ከሃገር መውጣት ምናልባት የተሻለ እንደሚሆን ያመኑም ነበሩ፡:

 አብላጫው ወገን ደግሞ የሚመጣውን ሁኔታ ለመጋፈጥ እዚሁ ሆኖ መጠበቁን የመረጡ ይመስላሉ። ከዚህ ማምለጥ የፈለጉት በጊዜ ወጥተው ወደ ኬንያ እየተጓዘ ያለውን ተማሪና ወታደር ተቀላቅለው መገስገስ ነው።

እስረኞቹ ሐሙስ ግንቦት 15 የመጨረሻ ፍርዳቸውን ለመስማት የሚወስዳቸውን መኪና እየጠበቁ ነበር። በዚህን ጊዜ ነበር መኪናዋ ሰተት ብላ ወደ ግቢ የገባችው። ከማዕከላዊ የመጡ ሰዎች አብረዋት ደርሰዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊስት የያዘ ሰው መጥቶ የመፈንቅለ መንግስት አድራጊ ወታደሮችን ስም እየጠራ መኪናው ላይ እንዲወጡ ነገራቸው። ግራ በመጋባት ሁኔታ እንደተባሉት መኪና ላይ ተሳፍረው እነርሱ ወደሚወስዷቸው ቦታ ተጓዙ ። ዛሬ ፍርድ ቤት ቀጠሮ አላቸው። ለዚህ ነው በመኪና የሚሄዱት።

 የሚሄዱበትን መንገድ በቀዳዳ ተመለከቱ። አሁን እየተጓዙ ያሉት ወደ ፍርድ ቤት አይደለም። መኪናዋ ከተማውን እየለቀቀች ወደ ጉለሌ እየተጓዘች ነው። ቤተሰቦቻቸው ፍርድ ቤት እየጠበቋቸው እነርሱ ወደማይታወቅ ቦታ በመሄዳቸው አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አስጊም ነበር። የነበሩበት እስር ቤት ጥበቃው የላላ በመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር ወደሚደረግበት እስር ቤት ሊወስዷቸው ይሆናል። የሚሄዱበትን መንገድ ሲመለከቱ ጥርጣሬ አደረባቸው። የሚሄዱበት ቦታ የሚታወቅ እስር ቤት የለውም። ሊገሏቸው ይሆን እንዴ? ጓደኞቻቸውን እንዲሁ እንደዋዛ ወስደው ነበር የገደሏቸው። ዛሬ ደግሞ በቀጠሮው መሰረት ፍርድ ማግኘት ነበረባቸው። ግን እዛ እንኳን አልቀረቡም።

 ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛነት ውሳኔ አሳል ፎባቸዋል። ጥፋተኛነታቸው የጓደኞቻቸው አይነት ውሳኔ የሚያሰጣቸው እንደሆነ ያውቃሉ። ጓደኞቻቸው የፍርድ ቀን ነው ተወስደው የተገደሉት። እነዚህም የፍርድ ቀን ወደማያውቁት ቦታ እየተወሰዱ ነው። መኪናዋ እስረኞቹን ይዛ ጉለሌ ራስ እምሩ ቤት አስገባቻቸው። ቤቱ ትልቅ ጥበቃ የሚደረግበት ቦታ ነው። ምናልባትም አሳቻ ስፍራ ስለሆነ ሁሉንም ረሽኖ ደብዛቸውን ለማጥፋት የታሰበ ይመስላል። ጓደኞቻቸውም የት እንደተገደሉ እንኳን አያውቁም። ብዙ ጊዜ እስረኞች አሳቻ ቦታ ይገደሉና ደብዛቸው ይጠፋል። እነዚህ እስረኞችም እንዲህ ያለውን ታሪክ ያውቃሉ። ዛሬ እነርሱም ማንም ያልጠረጠረው ቦታ ሲወስዷቸው የእነርሱ ግብአተ መሬት እዚህ እንደሚፈጸም ያምናሉ ወይም እዚህ በጥብቅ ቁጥጥር ስር እንደሚሆኑ ይገመታል። በመጪው የሚሆነውን ነገር ከአሳሪዎቹ በሰተቀር ማንም የሚያውቅ ሰው የለም። ወደ ግቢው እንደገቡ እንዲቀመጡ ተነገራቸው። አንድ ባለስልጣን መጣ። ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ነጻ ናችሁ›› አላቸው። የሰሙትን በፍጹም አላመኑም፣ ግን ሆነ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top