ስርሆተ ገፅ

‹‹ዱብ ዱብ!…›› ከጋሽ ግርማ ቸሩ ጋር

ታዳጊ በነበርኩባቸው ጊዜያት ከማይረሱኝ የቴሊቪዥን ፕሮግራሞች አንዱ በጋሽ ግርማ ቸሩ የሚሰናዳው ‹‹ዱብ ዱብ›› የተሰኘው የስፖርት ፐሮግራም ነበር:: የሰፈር ልጆች አንድ ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመመልከት ልምድ ነበረንና አብረን ከጋሸ ግርማ ጋር ዱብ ዱብ እንል የነበረበትን ዘመን አልረሳውም:: ግርማ ቸሩ በሰውነት ግዝፈቱ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሰውነት ቅርጽ በመያዙ ሁላችንንም ይገርመን ነበር:: ይህ ሰው በተለይ ከ1975-1980 ባሉት ጊዜያት በቲቪ ተመልካቾች የሚወደድ ሰው ነበር::

ግርማ ቸሩ ለሰዎች ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ ማንም አንቱ አይለውም:: ግርማ ቸሩ ብሎ ‹‹አንተ›› ይለዋል:: ይህ ሰው በምን መንገድ አልፎ የሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት አሰሪ እንደሆነ ብዙዎች ማወቅ ይፈልጋሉ:: ዛሬ ስለሱ የማውቀውን ጥቂት ልበል::

ግርማ ቸሩ ከሀገር ቤት ከወጣ 29 ዓመት አልፎታል:: መኖሪያውን ካናዳ አድርጎ ለዓመታት ድምጹ ብዙም ሳይሰማ ቆይቷል:: እና ድምጹ መሰማት ሲጀምር ግርማ ቸሩ ሀገሩን የሚወድ ታላቅ ሰው መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ታወቀ:: ግርማ ለዓመታት ያህል ጠፍቶ አንድ ወቅት ለሬድዮ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ስለ ራሱ መረጃዎችን ይፋ አደረገ:: መቼም ይህ ሰው ከልጅነቴ አንስቶ ልዩ ትዝታ የፈጠረብኝ ነውና ስለእርሱ ለማወቅ መጓጓቴ አልቀረም:: እናም የሰጠውን ቃለ-ምልልስ ጥሞና ሰጥቼ አደመጥኩት::

ጋሽ ግርማ ብዙ ያልተወራለት ግን ምናልባትም በሀገሪቱ ስማቸው ከሚነሳ የሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት አባቶች አንዱ ወይም ደግሞ ብቸኛው ነው ልንለው እንችላለን:: በዚሁ በያዝነው ዓመት 2011 ዓ.ም ግርማ ቸሩ ሀገሩ ሲገባ ታላቅ አቀባበል ይደረግለታል ብዬ ስጠብቅ ዱብ ዱብ እያለ ዓመታት በኋላ የሀገሩን ምድር ረገጠ:: ከዚያም ከጋሽ ግርማ ጋር ተደዋውለን መገናኘት ቻልን::

ከ87 ዓመት አስቀድሞ እንደተወለደ ያጫወተኝ ጋሽ ግርማ፤ የትውልድ ቦታውን ሜታ አቦን በፍጹም አይረሳትም:: ጣሊያን ሀገራችንን ከመውረሩ 4 ዓመት ቀደም ብሎ ወደዚህች ምድር የመጣው ጋሽ ግርማ፤ በልጅነቱ ለጨዋታ ልዩ ፍቅር ነበረው:: ስለዛ ዘመን ሲያጫውተኝም ‹‹በቀን 5 ጊዜ እንበላ ነበር›› ሲል ዘመኑን ወርቃማ ሲል ይጠራዋል:: ከአምስት ስድስት በላይ ልብስ ልጆች ሲሰፋላቸው ደግሞ ደስታቸው በጣም ያይል ነበር:: ከየጠቅላይ ግዛቱ የመጡ ልጆች ጋር መማሩ ለጋሽ ግርማ ልዩ ትዝታ ይፈጥርለት ነበር::

ጋሽ ግርማ የዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ቤት ትዝታው ዛሬም ውስጡ አለ:: በተለይ የስፖርት ፍቅሩ የተጠነሰሰው በዚያን ወቅት በመሆኑ ‹‹ያ ዘመን የህይወቴ መሰረት የተጣለበት ነው›› ሲል ይገልጻል:: በጀርመን ሚሲዮን ፣በተፈሪ መኮንን፣ በመድኃኔአለም ተማሪ ቤት የተማረው ግርማ ቸሩ፤ ስፖርተኛ ለመሆን ከውሳኔ ላይ የደረሰው ያኔ ነበር::

ለአንድ ሰው በስፖርት ማደግ የመሳሪያዎች መሟላት ትልቅ ሚና አለው:: በ1930 ዎቹና 40ዎቹ የነበሩት የተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት የበላይ ኃላፊዎች ደግሞ ለተማሪዎች በስፖርት ማደግ የግድ የስፖርት መሳሪያዎች መኖር እንዳለባቸው አምነው ነበር:: ታዳጊው ግርማም ከሌሎች ጓደኞቹ በተለየ መልኩ ለሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ከሌሎች ጓደኞቹ የተሻለ የሰውነት ቅርጽ ያዘ::

ገና በልጅነቱ ክብደት ማንሳት ሲጀምር ደግሞ ሰውነቱ ከቀን ወደ ቀን እየዳበረ መጣ:: የክፍል ጓደኞቹ ታዲያ ጠጋ ብለው ከግርማ ጋር ሲተያዩ ትልቅ ልዩነት ነበራቸው:: ታዳጊው ግርማ በዚያን ዘመን ከሰውነት ማጎልመሻ ባሻገር ለሩጫ እና ለዝላይ ስፖርት ልዩ ፍቅር ስለነበረው በመሮጥና በመዝለልም በተማሪ ቤቱ ዘንድ ታላቅ እውቅና ተቸሮታል::

ጋሽ ግርማ በልጅነቱ ምን መሆን ትሻለህ? ሲባል በልበ-ሙሉነት ‹‹ሀገሬን በሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት አስጠራለሁ›› ሲል ይናገር ነበር:: ታዲያ ይህን ሲል የማያሾፍ ተማሪ አልነበረም:: ጋሽ ግርማ ግን ሙያ በልብ ነው ብሎ ሰውነቱን ማጎልመሱን ተያያዘው::

ስፖርተኛ ግርማ ቸሩ የሰውነት ማጎልመሻ መምህር ከሆነ በኋላ ወደ ህልሙ እየተቃረበ እንደመጣ አሰበ:: በ1950 በአርበኞች ተማሪ ቤት ማስተማር የጀመረው ጋሽ ግርማ፤ ዛሬ ድረስ ትልልቅ ቦታ የደረሱ ሰዎች ከህሊናቸው የማያወጡት መምህራቸው እንደሆነ ቀርቷል:: ስፖርተኛ ለወረት ለጊዜው ዱብ ዱብ ይበል እንጂ አይዘልቀውም እየተባለ በዚያን ጊዜ ይነገር የነበረን ብሂል ውድቅ ለማድረግ ጋሽ ግርማ ቸሩ ሌትና ቀን መስራት ጀመረ::

አንዳንድ ሰዎች ‹‹ስፖርተኞች አንዴ መስራት ይጀምሩና ቆይቶ መጠጥ ሲጀምሩ ይበላሻሉ:: አንተም አንድ ቀን ስፖርቱን ታቆመውና እንደማንኛውም ሰው ትሆናለህ›› ሲሉ፤ ጋሽ ግርማ ግን የሚያየው ህልሙን ብቻ ነበር::

የ1960ዎቹ የከተማችን ወጠምሻዎች በፒያሳ ጎዳናዎች ላይ ሲንጎማለሉ ማነው ያሰለጠናችሁ ሲባሉ የግርማ ቸሩን ስም በኩራት ይጠራሉ:: በዚያን ዘመን ጋሽ ግርማ ስፖርት ቤት ከፍቶ ወጣቶችን ማሰልጠን ሲጀምር ይበልጥ ታዋቂነቱ ጎልቶ ወጣ:: በተለይ ወጣቶች የተለያዩ ሱሶች ውስጥ መዋላቸውን ትተው ግርማ ስፖርት ቤት መዋልን ምርጫቸው አደረጉት:: የጋሽ ግርማም ህልም ይህ ነበር::

ጋሽ ግርማ በየጊዜው እንዴት ስፖርትን በሰው አእምሮ ውስጥ ማስረጽ እችላለሁ ብሎ ያስብ ነበር:: እናም ስፖርት ቤት መምጣት ለማይችሉ በኢትዮጵያ ሬድዮ አማካይነት ስፖርትን እያሰራ ዱብ ዱብ የሚለውን ሀሳብ ማስረጽ ጀመረ:: የማስታወቂያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሰዎችም ግርማ ያመጣውን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ደግፈው ስራው የበለጠ እንዲጠናከር ይረዱት ነበር:: ቆይቶም ዱብ ዱብ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አለ::

ጋሽ ግርማ አስፋወሰን እያስተማረ ነበር ከባለቤቱ ከወይዘሮ ንግስት በለጠ ጋር የተዋወቀው:: ያኔ ወጣት ንግስት የግርማ ቸሩ ተማሪ ነበረች:: ‹‹ከተማሪዎቹ ሁሉ በንቃትና በትጋት ልዩ ስለነበረች ወደድኳት›› ሲል ጋሽ ግርማ ይናገራል:: ወዲያውም ጋብቻን መሰረቱ:: አራት ልጆችንም ወለዱ::

በሀገራችን የፉርኖ ዳቦ በስፋት መመገብ ባልተጀመረበት በዚያን ዘመን፤ የፉርኖ ዳቦ ማስታወቂያን ለቢል ቦርድ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950ዎቹ መስራቱን የሚናገረው ጋሽ ግርማ፤ ማስታወቂያውን ለሰራበት ባይከፈለውም ስለ ፉርኖ ዳቦ በቂ ግንዛቤ እንዲገኝ ማስቻሉን ይናገራል::

ጋሽ ግርማ በ1981 ግድም ነበር ከሀገር የወጣው:: በሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት ላበረከተው ሚና ሽልማት ለመቀበል ካናዳ እንደሄደ በዚያው ቀረ:: ከዚያም መኖሪያውን በካናዳ አደረገ:: ከምንም በላይ ሀገሩን የሚወድ ሰው ነው:: አንድ ቀን ሸገር መናፈሻ ተቀምጠን ስለ ሀገር መውድድ ስናወራ በድንገት የእንባ ዘለላዎች ከጋሽ ግርማ ዓይኖችና ፊት ላይ መንከባለል ጀመረ:: የሀገር ፍቅሩን እንዲህ በእንባ ሲገልÎ የውስጡን ንÎህና አነበብኩ:: አይ ግርማ! በሰው አገር እንዴት እየኖረ ይሆን? ግርማ ወደ ካናዳ ተመልሷል:: ˜ድምና ጤናን ተመገኘሁለት:: መልካም ቀን::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top