በላ ልበልሃ

ደራሲ ደበበ ሠይፉ እና የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ”

መነሻ

ባለፈው ዓመት (2010 ዓ.ም) ቴዎድሮስ ጸጋዬ በኢ.ቢ.ኤስ (EBS) ቴሌቪዥን የርዕዮት ፕሮግራም እንግዳው አድርጎኝ በቀረብኩበት ወቅት ስለጋሽ ደበበ ሠይፉ ጠይቆኝ የማውቀውን ያህል ተናግሬ ነበር:: በዚያን ወቅት የተናገርኩትን አንዳንድ ሰዎች በበጎ ስላነሱልኝ ትንሽ ዳራ (Background) ለመስጠትና በመጠኑም ዘርዘር አድርጌ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ:: በሌላ በኩል ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጀሁ ያወቀው የታዛ መጽሔት ባልደረባዬ መኩሪያ መካሻ “ኦሮማይ በደበበ ሠይፉ እይታ” በሚል ርዕስ ዶ/ር ታዬ አሰፋ በብሌን መጽሔት (ቅጽ 9፣ ቁጥር 2፣ ጥር 2009 ዓ.ም) ያሳተመውን መጣጥፍ ላከልኝ:: ሆኖም የደረሰኝ ጽሑፍ ጥቂት ገጾች የጎደሉት ስለነበር ጸሐፊውን ዶ/ር ታዬን ጠይቄ የተሟላውን ቅጂ አገኘሁ:: ጽሑፉን ካነበብኩና እሱም የእኔን ረቂቅ ከተመለከተ በኋላ ደግሞ ሐሳቡን በኢሜል አጋራኝ:: ዶ/ር ታዬ ከሥነጽሑፍ መምህርነቱና ተመራማሪነቱ በተጨማሪ የኦሮማይ ማኑስክሪፕት ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ለግምገማ በቀረበበት ጊዜ የቦርዱ አባልና ጸሐፊም ስለነበር መረጃዎቹ ክብደት የሚሰጣቸው ናቸው:: ስለዚህ ከጋሽ ደበበ አንደበት የሰማሁትን እንዳለ ሳቀርብ የዶ/ር ታዬን ሃሳብም በተገቢው ቦታ ለማካተት ጥረት አድርጌያለሁ:: ለሰጠኝ አስተያየትም ከልብ አመሰግነዋለሁ::

*    *    *

ጋሽ ደበበ ከምወዳቸው መምህሮቼ አንዱ ነበር:: ብዙዎቻችን እንደምንለው አንድ ቀን ገብቶም እንኳ የሳምንቱን ትምህርት በሚገባ መሸፈን የሚችል ሰው ነበር:: የእሱ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እጅግ የሚናፈቅ ነበር:: አንድ ጊዜ ግማሽ ሰዓት ያህል ዘግይቶ ሲመጣ እኛ ውጪ ተሰብስበን ስንጠብቀው አገኘንና በመገረም አይነት “ምነው ሥራ የላችሁም? ዛሬ ገብርኤል መሆኑንስ አታውቁም?” ብሎ አሳቀን:: የገብርኤል ቀን ታክሲ የማግኘት ችግር እንደነበረበት ከዚያ በፊትም ነግሮን ያውቃል:: ምክንያቱም የግቢ ገብርኤልን መታጠፊያ አልፎ ነበር ወደ ስድስት ኪሎ የሚመጣው:: ተማሪዎቹን እንደ ጓደኛና እንደ ታናሽ ወንድም/እህት ያቀርበንም ነበር:: በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ዘመኔ ቤቱን የማውቀው ብቸኛ መምህሬም ነበር:: እኔ ብቻ ግን አልነበርኩም:: የሆነ ነገር ከፈለገ በቴያትር ትምህርት ክፍል በኩል ስልክ ይደውልና ባካባቢው የተገኘውን ተማሪ አስቀርቦ “እባክህ ይህን ነገር ይዘህልኝ ና” ይላል:: እኔም በዚሁ አጋጣሚ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቱን ያየሁት::

ጋሽ ደበበ ቤቱን ለማመላከት ችግር አልነበረበትም:: “ከላይ ስትመጣ …..ን እንዳለፍክ በግራ በኩል አጠና የሚሸጥበት ቦታ ታያለህ:: እዛ ጋ ትወርድና ወደ ውስጥ በምታስገባዋ መንገድ ይሄን ያህል ሜትር እንደሄድክ የቆርቆሮ በር አለ:: ስትደርስ አንኳኳ” አይነት መመሪያ ነው የሰጠኝ:: ቤቱ እዚያው ከዋናው ጥርጊያ መንገድ አጠገብ ስለሆነ አያሳስትም:: ጠረጴዛው ላይ የረሳውንና ፀሐፊው ወ/ሮ ዓለሚቱ የሰጠችኝን አንድ ጥናት ይዤለት ነው የሄድኩት:: በወቅቱ የቴያትር ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር ነበር:: ወደቤቱ ስገባ የንባብ ክፍሉ ውስጥ አገኘሁት:: በብሎኬት ላይ የተደራረቡ የሞራሌ ጣውላዎች እንደ መጻሕፍት መደርደሪያ ያገለግላሉ:: በርካታ መጻሕፍትም ይዘዋል:: ጥቂት ከተጫወትን በኋላ በምርጫዬ ሻይ ተጋብዤና የታክሲ ተቀብዬ ወደ ግቢ ተመለስኩ:: ከዚያ ወዲያም፣ በተለይም ትምህርቴን አጠናቅቄ በባህል ሚኒስቴር የሥነጥበባትና ቴያትር መምሪያ ከተመደብኩ በኋላ፣ ደጋግሜ ወደቤቱ ሄጃለሁ:: ለዚህም ዋናው ምክንያት እሱ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሊቀመንበር፣ እኔ ደግሞ ተራ አባልና የባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ ስለነበርኩ ነው:: ዋናው ተጠሪ አለቃዬ አቶ በቀለ አበባው ነበር:: ሌላው በአቶ ወንድሙ ነጋሽ ደስታ ይመራ የነበረው የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ቅርንጫፍ እንደነበር አስታውሳለሁ::

 በ1982 ዓ.ም. አካባቢ በባህል ሚኒስትሩ በሻለቃ ግርማ ይልማ የሚመራ “የሕዝብ ግንዛቤ ማዳበሪያ” የሚባል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ነበር:: አባላቱም የአራቱ የሙያ ማኅበራት ሊቃነ መናብርት (አቶ ተ/ዮሐንስ ዝቄ የሙዚቃ፣ አቶ አብዱራህማን ሸሪፍ የሠዓልያን፣ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ የተውኔት ሙያተኞች፣ ጋሽ ደበበ የደራስያን)፣ የሥነጥበባትና ቴያትር መምሪያ ኃላፊ (አቶ ጥላሁን ጉግሳ ዓለሙ)፣ ሁለቱ አማካሪዎች (ባለቅኔና ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድኅንና እጅግ የተከበሩ፣ የዓለም ሎሬት፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ)፣ የሶስቱ ቴያትር ቤቶች ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ (አቶ ጌታቸው አብዲ የብሔራዊ፣ አቶ አማኒ ኢብራሂም የሃገር ፍቅርና አቶ ይገዙ ደስታ የራስ) ምናልባትም የኪነት አገልግሎት ኃላፊዎች፣ እና ፀሐፊዋ ወ/ት ሲሳይ ገ/እግዚአብሔር ነበሩ:: ጋሽ ደበበ በባህል ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ በሚደረገው በዚህ ሳምንታዊ ስብሰባ በቋሚነት ለመሳተፍ ስላልተመቸው እኔን ወከለኝ:: እናም በተወካይነቴ በስብሰባው እየተገኘሁ የውይይቱን ፍሬ ሃሳብ ብዙውን ጊዜ በስልክ አልፎ አልፎ ደግሞ ወደቤቱ እየሄድኩ ሪፖርት አደርግለታለሁ:: ማየት ያለበት ሰነድ ካለም አደርስለታለሁ:: አንድ ጊዜ “መኪና ላኩልኝና እመጣለሁ” ስላለና ሾፌሩ ቤቱን ስለማያውቀው እኔ ይዤው ሄድኩ:: ሆኖም መ/ቤቱ ከነበሩት መኪኖች በወቅቱ የተገኙት ከፍ ከፍ ያሉት (ፒክ አፕ የሚባሉት) ስለነበሩ በአንደኛው ነበር የሄድነው:: መኪናውን ሲያይ ጋሽ ደበበ በጣም ተበሳጨ:: “ምነው ሌላ አነስ ያለ መኪና የላቸውም?” አለኝ:: ሁኔታውን አስረዳሁት:: “በልና እርዳኝ” አለኝና እንደምንም ደግፌ አሳፈርኩት:: ከዚያ በኋላ በተገኘባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ሚኒስትሩን እያስፈቀድን በእሳቸው አውቶሞቢል እንዲመጣ ማድረጋችን ትዝ ይለኛል:: ይህን የማነሳው የሰዎቻችንን ልዩ ተፈጥሮ አጢነን ተገቢውን ዝግጅት አለማድረጋችን ምን ያህል ህሊናን የሚነካ ጉዳይ መሆኑን በእግረ መንገድ ለማስታወስ ነው::

የግብረ ኃይሉ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል ማስተዋወቅና ሃገራዊ አንድነቷንና ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖር ሙያዊ አስተዋፅዎ ማድረግ ነው:: ይህን ዓላማ ሊያሳኩ ይችላሉ የተባሉ የቴያትርና የሙዚቃ ዝግጅቶች፣ የሥዕል ኤግዚቪሺኖች፣ ግጥሞችና አጫጭር ልብወለዶች በመድረክና በመገናኛ ብዙኃን ይቀርቡም ነበር:: ታዲያ ጋሽ ደበበ በስብሰባው ላይ በአካል አይገኝ እንጂ በተለይ ግጥሞችንና አጫጭር ልብወለዶችን በመምረጡ ሂደት ተሳታፊ ነበር:: ሌላው ወደእሱ ቤት የሚወስደኝ ጉዳይም ይኸው ነበር:: አንዳንዴ በቁሜ እመለሳለሁ:: ፋታ ካለው ደግሞ ሾፌሩን ሸኝቼ ቁጭ እላለሁ:: እንደተለመደው ሻይ ያስፈላልኝና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንጫወታለን:: ከእንደዚህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ባንዱ ታዲያ ተደፋፈርኩና ብዙ ጊዜ ይከነክነኝ ስለነበረው የደራሲ በዓሉ ግርማ መጨረሻ አነሳሁበት:: ከዚህ ቀጥሎ የምታነቡት ያልጨመርኩበትን ያልቀነስኩበትን ግን ለማስታወስ የሞከርኩትን ወጋችንን ነው::

 “ጋሽ ደበበ፣ ከበዓሉ ግርማ ጋር ተያይዞ ስምህ የሚነሳው ለምን ይመስልሃል?”

 “አንተ ለምን ይመስልሃል?”

“እኔ ምን አውቃለሁ ብለህ ነው:: እኔ የሰማሁት ተባራሪ ወሬ ነው:: ለዚህም ነው አንተን የጠየቅኩህ::”

“ተባራሪም ይሁን አባራሪ፣ ፊት ያንተን ንገረኝና ቀጥዬ የኔን ወገን ወግ( version) እነግርሃለሁ::”

 “እንግዲህ እኔ የሰማሁት፣ አንተ መጽሐፉን ካነበብክ በኋላ የሆነ ትችት በጋዜጣ መጻፍሕንና ያም ደራሲውን ዒላማ (target) አደረገው ሲባል ነው” አልኩት::

“ለመሆኑ ያልከውን ጽሑፍ አንብበኸዋል?”

“እውነቱን ለመናገር፣ ብርሃንና ሰላም ሄጄ ከ”ኦሮማይ” መታተም በኋላ የተጠረዙትን የአዲስ ዘመንና የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ለመመልከት ሞክሬያለሁ:: ግን የተባለውን ትችት አላገኘሁም:: የጠየቅኩህም ለዚሁ ነው::”

“ያላገኘኸው ቀድሞውኑም ስላልተጻፈ ነው::”

“ታዲያ ለምንድነው ስምህ በክፉ የሚነሳው?”

 “መቼም አቶ አስፋው ዳምጤ አይክደኝም:: እንደኔ እንደኔ ለበዓሉ ግርማ ሞት ተጠያቂ መሆን ያለበት ዳኛቸው ወርቁ ነው::”

 “እንዴት?” (ድንጋጤዬ በግልፅ እየታዬ)::

 “አንዱ የጽሑፉ ገምጋሚ እሱ ነበር:: እና በዓሉ ባለበት ስንወያይ እኔ መሻሻል አለባቸው ያልኳቸውን

ዋና ዋና ነጥቦች እያነሳሁ ነበር::”

“እስኪ የተወሰኑትን ንገረኝ?”

“ለምሳሌ ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይን ትልቅ ጀግና (hero) አድርገህ ፈጥረህ የሴት ፎቶ (የፊያሜታ ጊላይን ማለቱ ነው) ታቅፎ እንዲሞት አድርገኸዋል:: ተምሳሌታዊነት (Symbolism

ነው እንዳይባል ጎልቶ የወጣ ነገር የለም:: እሱ ገፀባህሪይ ላይ ብዙ መሥራት አለብህ:: እንደመከራከሪያ ያቀረብከውን ታሪካዊ ሰነድነትም ቢሆን ከ”አሥመራ ማኒፌስቶ” በስተቀር የሚደግፍልህ ብዙም የለም:: እሱም ቢሆን በጥሬው ተገልብጦ መቅረቡ የልብወለዱን ሥነጽሑፋዊ ለዛ ይቀንሳል እንጂ የሚጨምረው ነገር የለም:: እንደዚህ እያልኩ በትንሽ ወረቀት ላይ የጻፍኳቸውን ማስታወሻዎቼን አንድ ባንድ እያነሳሁ ሳቀርብለት በዓሉ የሚቀበል አይነት አልነበረም::”

 “ጓድ ደበበ፣ አልገባህም ማለት ነው:: እኔ የጻፍኩት እንደ አንድ የታሪክ ሰነድ የሚታይ ሥራ ነው:: አንተ እኮ እንደ ልብወለድ፣ ልክ እንደ “ከአድማስ ባሻገር”፣ እንደ “ደራሲው” አይነት ሥራ አድርገህ ነው ያየኸው:: ይህ በፍፁም ትክክል አይደለም::”

 “ኖኖኖኖ ጓድ በዓሉ፣ ለእኔ ደምበኛ ልብወለድ ነው የጻፍከው:: የሚታየውም በዚያው የልብወለድ መለኪያ ነው’ አልኩት:: እናም በማስታወሻዬ መጨረሻ ላይ (ሰፊ የአርትኦት ሥራ ያስፈልገዋል) (“highly edited) መሆን አለበት” ብዬ ነው የጻፍኩት:: ዳኛቸው ወርቁ ደግሞ፣

 “‘ጓድ በዓሉ ትክክል ነው፣ ይኼ ነገር ፈፅሞ መነካት የለበትም፣ እንዳለ ነው መታተም ያለበት’ ይላል:: ተነጋገርን፣ ግን ልንግባባ አልቻልንም:: እኔ አሻሽሎ ያምጣ በሚለው አቋሜ ፀናሁ:: ከዚያ በኋላ ታተመ ሲባል ነው የሰማሁት:: ቆየት ብሎ ጓድ ሺመልስ ማዘንጊያ ደወለልኝና ‘ማንስክሪፕቱን ላክልኝ’ አለኝ፤ ላክሁለት:: ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ጠራኝና ቢሮው ድረስ ሄድኩ:: ታሪኩንም አስረዳሁ:: ከዚያ ያቺን በብጣሽ ወረቀት ላይ የጻፍኳትን ማስታወሻ አውጥቶ ‘ይህች ጽሑፍ ያንተ ናት?’ አለኝ:: ‘አዎ’ አልኩት:: እንግዲህ እኔን ከተጠያቂነት ያዳነችኝ ያች ማስታወሻ ነች ማለት ትችላለህ::”

ከዶ/ር ታዬ ያገኘሁት መረጃ ከሞላ ጎደል የሚከተለውን ይመስላል:: “ቀድሞ ነገር ዳኛቸው (የቦርዱ ሰብሳቢ) እና ደበበ (የቦርድ አባል) በዓሉን ያነጋገሩት በተናጠልና በተለያየ ጊዜ እንጂ አንድ ላይ ሆነው አልነበረም:: በዓሉን ቀድሞ ያነጋገረው ደበበ ሲሆን ኦሮማይ ከመጻፉ አስቀድሞም ይተዋወቁ ስለነበር ይሆናል በግል ተገናኝተው የተወያዩት:: ዳኛቸው ግን ከበዓሉ ጋር የተነጋገረው በኤዲቶሪያል ቦርዱ የግምገማ አስተያየቶች መነሻነት ነው:: እያንዳንዱ የቦርድ አባል ማኑስክሪፕቱን አንብቦ አስተያየቱን መስጠት ነበረበት:: በአስተያየቶቹ ላይ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ደግሞ እኔ በጸሐፊነቴ ማጠናቀር ነበረብኝ:: ከዚያ ወዲያ አስተያየቶቹ ለበዓሉ እንዲደርሱና ዳኛቸውም ደራሲውን እንዲያነጋግረው ተወሰነ:: ያደረገውም ይህንኑ ነው:: እርግጥ በዓሉ አንዳንዶቹን ነጥቦች ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም:: እኛም ብንሆን ውሳኔውን አክብረናል:: በመሠረቱ የእኛ ቀዳሚ ተግባር ሥራው እንደ አንድ የኪነጥበብ ሥራ ሥነጽሑፋዊ ብቃት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ነበር:: ለፖለቲካውማ እኮ የኢሠፓአኮ የርዕዮተ ዓለም መምሪያ አለ:: ቦርዱ የአንድን ሥራ ጥበባዊ ደረጃ መዝኖ ይታተም ሲል የፖለቲካ ይዘቱን የሚመለከተው የርዕዮተ ዓለም መምሪያው ነው:: …”

ከዚህ ባሻገር ቀደም ብዬ በጠቀስኩትና በብሌን መጽሔት በታተመው የዶ/ር ታዬ ጽሑፍ ውስጥ በራሱ የእጅ ጽሑፍ የቀረቡት የጋሽ ደበበ ዝርዝር አስተያየቶች ለእኔ ከነገረኝ ጋር ተመሳሳይ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ:: ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን እንመልከት:: “በቋንቋ ረገድ መጽሐፉ ተነባቢ ነው:: ሁኖም እንደ “ከጥቁር ብሩህ ፊቱ ላይ ሁልጊዜ የማይጠፋው ልባዊ ፈገግታው እንደተላላፊ በሽታ ባንድ ጊዜ ሰው ይወራል” … እና “…እንደገሀነም አፋቸውን በከፈቱ፣ እንደ ሲዖል በሚያዛጉ ተረተሮች…” … ያሉ አያሌ አባባሎች መታረም አለባቸው:: ዋናው ገፀባህርይ ምንም እንኳን ጋዜጠኛ መሆኑን ብናውቅ፤ ቃለጉባዔ ዐይነት መዘርዝሮች (details) ቢቀሩና በሥነጽሑፋዊ ቋንቋ እንደገና ቢጻፉ ጥሩ ነው:: – የአስመራ ማኒፌስቶም እንዲሁ::

“በመጨረሻ ላይ ቀደም ብለን ነካ ወዳረግነው ነጥብ እንመለስና፣ ብዙዎቹ ጉልህ ገፀባህርያት ፍቅር በቁሙ፣ እምነት ፣መግባባት በቁሙ ጥሩ ነው እሚሉ እንደመሆናቸው ሀልዮታዊ አተያይ ያጠቃቸዋል:: በዚህም ምክንያት ከመጽሐፉ ይዘን የምንወጣው ቁምነገር እማያጠግብ እንደሆነም ቀደም ብለን ጠቅሰናል:: ደራሲው በእነዚህ ባህርያት አንፃር አንድ ጠንካራ ባህርይ ቢቀርጽ በመጽሐፉ ጠቅላላ ይዘትና ቅርጽ ላይ መልካም ለውጥ ሊያመጣ ይችላል:: ለዚህም አዲስ ባህርይ መፍጠርም አያሻው:: ኮ/ታሪኩን በበለጠና በደመቀ ሁኔታ እንደገና ቢስለው በቂ ይሆናል::”

 ጋሽ ደበበን ከዚህ በላይ ልጠይቀው ባለመቻሌና ተጨማሪ መረጃዎችን ባለማግኜቴ አዝናለሁ:: በጣምም ይቆጨኛል:: ታላላቅ ሰዎቻችንን በህይወት ስናያቸው አላፊ መሆናቸውን እንዘነጋለን:: እርግጥ ጋሽ ደበበ ገና ብዙ ሊሠራ በሚችልበት እድሜ ነው የተለየን:: የሆነ ሆኖ ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማዘጋጀት የፈለግኩበት ምክንያት ከደራሲ በዓሉ ግርማ አሳዛኝ መጨረሻ ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚነሱ ሰዎች አንዱ እሱ በመሆኑና ራሱን በሚከላከልበት ሁኔታ ስላልነበረና ስላልሆነም የማውቃትን ያህል ለማካፈል ነው:: እንደ ጋሽ ደበበ ሁሉ ለእኔ በማያሳምነኝ መንገድ ስማቸው የሚጠራ ሰዎች እንዳሉም አነባለሁ:: የደርግ ባለስልጣናት፣ በተለይም በመጽሐፉ ተሳልቆብናል ብለው ያኮረፉት ሰዎች፣ የአንድ በዓሉን ህይወት ለማጥፋት የማንንም ድጋፍ ይፈልጋሉ ብዬ አላምንም:: የሚያሳዝነው ጉዳዩን የሚያውቁትና እዚህም ይሁን በሌሎች ጽሑፎች በስም የተጠቀሱት የነዚሁ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት ሁኔታ ነው:: የእስር ጊዜያቸውን፣ ምህረትም ታክሎበት ቢሆን፣ ጨርሰው ወጥተዋል:: ለምን እውነቱን ተናግረው ለቤተሰቦቹም ይሁን ለአድናቂዎቹ አንድ መቋጫ አያበጁም?

በሌላ በኩል ጋሽ ደበበን ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ያሳየው በኢሠፓ አባልነቱና በደራስያን ማህበር ሊቀመንበርነቱ የኢሠፓ የርዕዮተ ዓለም መምሪያ ሃላፊ ከነበሩት ከአቶ ሺመልስ ማዘንጊያ ጋር የነበረው ቅርበት እንደሆነ የሚያምኑ አሉ:: እርሱ ግን የራሱን ሥራዎች እንኳ እንዴት ሳንሱር አድርጎ ያስቀር እንደነበር ሁለት ምሳሌዎችን ጠቅሼ ላጠቃልል::

 የመጀመሪያው “እናትና ልጆች” ከተሰኘው የተውኔት ድርሰቱ ጋር የተያያዘ ነው:: የአራተኛ ዓመት ተማሪዎች ሆነን ተውኔቱን Production II ለተባለ ኮርስ በመድረክ ሠራነው:: መምህራችን አቶ አቦነህ አሻግሬ (ዛሬ ተባባሪ ፕሮፌሰር) ነበር:: በቋንቋው ውበትም ሆነ (በአብዛኛው ግጥማዊ ነበር) በታሪኩ ይዘት በጣም ኃይለኛ የሆነ፣ ተመልካቹን የመያዝ ብቃት ያለው ሥራ ነበር:: ታሪኩ ወደኋላ ሄዶ ድርቅን፣ የህዝቡን ስቃይና ጉስቁልና የሚያነሳም

ነበር:: መድረኩ ራሱ ሃዘንና ብካይ የሰፈነበት ነበር ማለት ይቻላል:: በዩኒቨርሲቲው ይትባህል መሠረት አንድ ቀን ለተጋባዥ እንግዶች ካሳየን በኋላ በአምስት ኪሎው የቴያትር አዳራሽ ለህዝብ ለማቅረብ ስንዘጋጅ “አይታይም” ተባልን:: ምክንያቱን ስንጠይቅ ጋሽ ደበበ አልተስማማም ተብሎ ተነገረን:: አንደኛ ድርሰቱ የእሱ ነው፣ ሁለተኛ የትምህርት ክፍሉም ሊቀመንበር ነበር:: በሁለት ገጽ ሊያስጠይቀው እንደሚችል ገምቷል፣ ሰግቷልም:: ብንለምነውም በጅ የሚል አልሆነም:: የያኔው የክፍል ጓደኛዬና የስከዛሬ ወዳጄ አሰፋ ወርቁ በቅርቡ እንዳስታወሰኝም “ይኸ ቴያትር ቢታይ ሁላችንም ተጠራርገን እስር ቤት እንገባ ነበር” ያለው::

“የብርሃን ፍቅር፣ ቅጽ ፩” ከመታተሙ በፊት ከሁለት መቶ ቅጠሎች (ለማንስክሪፕት ገጽ አይባልም) በላይ የሚሆኑ በስቴንስል የተጻፉ ግጥሞቹን አንብበን እርማት እንድናደርግለት ለእኔና ካልተሳሳትኩ ለሌላው የክፍል ጓደኛዬ ለኤፍሬም በቀለ ሰጥቶን ነበር:: ስንጨርስ የተጠረዘውን አንዳንድ ቅጂ በማስታወሻ መልክ ሰጠን:: ከዓመታት በኋላ “የብርሃን ፍቅር፣ ቅጽ አንድ” በ1980 ዓ.ም ታትሞ ሲወጣ አንዳንዶቹ በጣም የወደድኳቸው ግጥሞቹ እንዳልወጡ ተገነዘብኩ:: እናም እንኳን ደስ ያለህ ልለው ወደቢሮው በሄድኩበት አጋጣሚ “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ”ን ለምን ሳታሳትመው ቀረህ? It was my favorite” አልኩት በወዳጅነት መንፈስ:: እሱ ግን እንደወትሮው የቀኝ እጅ አመልካች ጣቱን ከንፈሩ ላይ አድርጎ በከፊል ሳቅና በከፊል ስላቅ “አሁን ይኼ ዘመን “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” የሚታተምበት ነው?” አለኝ:: ደነገጥኩ:: ከደራስያን ማኅበር ሊቀመንበርነቱ በተጨማሪ በምረቃ ወቅት በኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ ማርያም ፊት የሚነበበውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ንግግር የሚጽፈው እሱ እንደነበር ስለምናውቅ ለመንግስት ቅርብ የሆነ ሰው እንጂ እንደ ማንኛችንም ስለሳንሱር ጣጣ የሚጨነቅ ሰው ነው ብዬ አስቤ አላውቅም:: እንዳለውም “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ (የብርሃን ፍቅር ቅጽ ፪)” የታተመው የደርግ መንግስት ከወደቀና እሱም ሕይወቱ ካለፈ በኋላ፣ በ1992 ዓ.ም ነበር:: ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር ጋሽ ደበበ ሌሎች የሥራ ጫናዎች እንደነበሩበትም ግልጽ ነው:: አንድ ቀን፣ እጅግ ውጥርጥር ያለበት ጊዜ ነበር ይመስለኛል፣ በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ “ለመሆኑ መቼ ነው ይቺ አገር Leave (እረፍት) የምትወጣው?” ብሎ ፈገግ እንዳስደረገን አስታውሳለሁ:: ጋሽ ደበበ እላይ ከጠቀስኳቸው ሁለት የግጥም መድበሎቹና ሳይታይ ከቀረው ተውኔቱ በተጨማሪ ከባሕር የወጣ አሳ፣ እነሱ እነሷ፣ ሳይቋጠር ሲተረተር፣ የህፃን ሽማግሌ፣ ጋሊሊዮ ጋሊሊ፣ እና ክፍተት (አዛማጅ ትርጉም)፣ የተሰኙ ተውኔቶችን ጽፏል:: “የቴያትር ጥበብ -ከፀሐፌ ተውኔቱ አንፃር” የተባለ ንድፈ ሃሳባዊ መጽሐፍም አሳትሟል::

ወደፊት እንደ እንዳለጌታ ከበደ ያሉ ትጉህ አጥኚዎች ተጨማሪ መረጃዎችን በማምጣት ስለሰማዕቱ ደራሲ በዓሉ ግርማ ሕይወትና በክፉም ይሁን በበጎ አብረውት ስለሚነሱ ሰዎች ያለውን ክፍተት ይሞሉልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: ለመሰናበቻ ከፍ ብዬ ከጠቀስኩት የጋሽ ደበበ ግጥም (ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፣ ገጽ 44) ጥቂት ስንኞችን ተጋበዙልን::

 ጋሼ፣ ዛሬ ይህን ወረቀት፣ ስጽፍልህ ታግዬ

 እንዳይመስልህ የተፋታሁ፣ ከአያሌ ወራት ዝምታዬ

 በእግዜሬ፣ በወገኔና በራሴ፣ ካወጅኩት ኩርፊያዬ

ካደበተኝ ስቃዬ፣ ካነበዘኝ ምንዳቤዬ

እንዳይመስልህ ያመለጥኩኝ፣ ከብቸኝነት ጉዞ ዋሻዬ::

 አሁንማ መች ዝምታ ብቻ

 አሁንማ መች ኩርፊያ ብቻ

አሁንማ መች ብቸኝነት ብቻ

ፍርሃትም አሳጥቶኛል፣ እምቆምበት ዳርቻ፣

 እምገባበት ሥርቻ::

 አንድ ወንድሜን አንተን፣ ጠልቼ አይደል አለመጻፌ

 ምን ሊበጅህ ብዬ እንጂ፣ ደህና ነኝ ብልህ ባፌ

 አሁን ግን ፍርሃቴ ነው፣ ይህን ደብዳቤ የላከው

 በዚህ መካነ ደይን፣ ተቀብሬ እንዳልቀረው

የዚህን ምድረ – ፋይድ ታሪክ፣ ሳላወጋ ሳልናገረው::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top