ሌሎች አምዶች

የ2018 ምርጥ መጽሐፍ

በፈረንጆቹ 2018 ከተጻፉ ምርጥ መጻሕፍት የጆን ቦይኔ “ወደ ሰማይ መውጫ መሰላል” (A Ladder to the Sky) ምርጥ ተሰኝቷል። ጆን ቦይኔ አየርላንዳዊ ደራሲ ሲሆን ዛሬም በደብሊን ይኖራል። ከዚህ ቀደም አስራ አንድ ልብ ወለድ መጻሕፍት ለአንባቢያን ጀባ ብሏል። አብዛኞቹ መጽሐፎቹ በ50 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። “ወደ ሰማይ መውጫ መሰላል” መጽሐፍ የሌብነት፣ የመዳራትና የክፉ ምኞት አስከፊ ገጽታ በጣፋጭና አገርኛ ወጎች ተዋዝቶ የቀረበበት ነው። መጽሐፉ ባጭሩ “በልብህ ያለውና የሚመላለሰው ሚስጥርና ምኞት ምንድን ነው?” ሲል ይጠይቃል። ደራሲው ከዚህ ቀደም በሁለት መጻሕፍቱ የአየርላንድን የመጽሐፍ ሽልማት አሸንፏል።

ሁለተኛው ምርጥ መጽሐፍ የሊንደሲ ሂልሰም “የጦርነት ዘጋቢዋ ማሪ ኮልቪን ህይወትና አሟሟት” (The Life and Death of the War Correspondent Marie Colvin) የሚለው ነው።

 ሊንደሲ ሂልሰም የእንግሊዙ ቻናል 4 ቴሌቪዥን ዜና አርታኢ ናት። ይህቺ ጋዜጠኛ ላለፉት 25 ዓመታት በትላልቅ አለማቀፍ የጦርነት አውድማዎችና ቀውሶች ዘገባ ተሳትፋለች። ለምሳሌም የሶርያ፣ የዩክሬን፣ የኢራቅ፣ የኮሶቮ፣ የአረብ አብዮትና የሩዋንዳ የዘር እልቂትን መጥቀስ ይቻላል።

 ሊንደሲ ሂልሰም በዚህ መጽሐፏ ለእንግሊዙ ጋዜጣ The Sunday Times ትዘግብ የነበረችው አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ማሪ ኮልቪንን በፈተና የተሞላ የጋዜጠኝነት ህይወትና በተለይም በጦርነት ዘገባዎቿ የደረሰባትን ፈተና እንዲሁም በመጨረሻ የሶሪያውን የጦርነት ቀውስ ስትዘግብ ህይወቷ ማለፉን በጥኡም አገላለጽ ተርካለች።

የ2018 ምርጥ ሙዚቃ

በ2018 አለም ጆሮ ከሰጣቸው ምርጥ ሙዚቃዎች የካናዳዊዉ ራፐር አውብሬይ ድሬክ ግራሃም “ጊንጥ” (Scorpion) እና “የአምላክ እቅድ” (God’s Plan) የተሰኙት አልበሞች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። አርቲስቱ ከዚህ ቀደም በየተጫወታቸው ሙዚቃዎቹ የምርጦች ምርጥ ተሰኝቶ በተለይም በ2015 እና 2016 ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል። “ጊንጥ” (Scorpion) የተሰኘው አልበሙ 8.2 ሚሊየን ሰዎች ዘንድ ደርሷል። “የአምላክ እቅድ” (God’s Plan) ደግሞ ከ1 ቢሊዮን አድማጮች ጆሮ ደርሷል። በነገራችን ላይ አውብሬይ ድሬክ ግራሃም ራፐር፣ ዘፋኝ፣ የሙዚቃ ድርሰት ጸሐፊ፣ ሙዚቃ አዘጋጅና የፊልም ተዋናይ ጭምር ነው።

የ2018 ምርጥ ፊልም

“12 Strong” የተሰኘው ፊልም የ2018 ምርጥ ፊልም ተሰኝቷል። የፊልሙ ጭብጥ በአሜሪካ ከተከሰተው ናይን ኢለቨን (9/11) አደጋ በኋላ የመጀመሪያው የአሜሪካ ልዩ ኃይል ወደ አፍጋኒስታን መላኩን ያሳያል። ይህ በአዲስና ቆራጥ አዛዥ የተመራው ልዩ ኃይል ተልእኮ ደግሞ በአፍጋን ያስቸገረውን ታሊባን የተሰኘ ቡድን በዚያው ካሉ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች ጋር በመምከርና በመተባበር መድረሻ ማሳጣት ነው።

አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ “Jumanji: Welcome to the Jungle “ የ2018 ምርጥ ፊልም ነው ይላሉ። ይህ በታወቁ የአሜሪካ ፊልም ተዋንያን የተሰራ ፊልም ዘውግ ጀብዱ የተሞላበትና አዝናኝ (ኮሜዲ) የሚባለው አይነት ነው። ፊልሙ የተዘጋጀው በጃክ ካሳዳን ሲሆን የተጻፈው ደግሞ በክሪስ ማክኬና ነው። በፊልሙ ላይ ድዋይኔ ጆንሰን፣ ኬቪን ሀርት፣ ካሬን ጊላንና ኒክ ዮናስን የመሳሰሉ ምርጥ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

የ2018 ምርጥ ቲያትር

“መላእክት በአሜሪካ” (angels in america) የተሰኘው ቲያትር የ2018 ምርጥ ቲያትር ተሰኝቷል:: ቶኒ ኩሽነር በፃፈው ቲያትሩ ባለልፉት ዘመናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ተከስቶ ብዙ ጉዳት ያደረሰው ኤች አይ ቪ ኤድስ አሁን ላይ ማንሰራራቱን በዋናነት ጭብጡ ያደርጋል::በአሜሪካ ብሄራዊ ቲያትር ቤት የታየው ይህ ቲያትር አንድሬው ጋሪፊልድና ናታንላኔ በኮከብ ተዋናይነት ተሳትፈውበታል:: በትያትሩ ጊዜው አስከፊ መሆኑንና ጥንቃቄ እንደሚያሻው ያመለክታል:: በትወናው የሀይማኖት ተቋማት፣ ፖለቲከኞች፣ ሴት ወንዱ በአጠቃላይ ትውልዱና ጉዳዩ የሚመለከታቸውም የማይመለከታቸውም ተቋማት በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጣቸውና መቀዛቀዛቸው ተንፀባርቋል::ዝምታው በብዙ ተኮንኗል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top