አጭር ልብወለድ

የ ፍፃ ሜ መ ጀ መ ሪ ያ በ ዓ ሉ ግ ር ማ

በጋዜጠኝነቱ እና በዘመናዊ ልቦለድ አጻጻፉ የሚታወቀው በዓሉ ግርማ በ1975 ዓ.ም በመንግስት ስር የምትታተመው የካቲት መጽሔት ላይ “የፍፃሜ መጀመሪያ” በሚል ርዕስ የጻፈው ልቦለድ ብዙ አነጋግሮ ነበር:: “የራሱን መጨረሻ የተነበየበት ነው” የተባለለት ይህን ልቦለድ በጻፈ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ራሱ በዓሉ ከቤቱ በሰላም ወጥቶ ሳይመለስ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል:: ዛሬ ድረስ ደብዛው ከመጥፋቱ በቀር እንዴት? ለሚለው መጠይቅ ምላሽ የሚሰጥ አካል አልገኘም:: የመጥፊው ሰበብ የሆነው ኦሮማይን ጨምሮ በስድስት ረጃጅም ልቦለደቹ ሚታወቀው በዓሉ ባልተለመደ ሁኔታ ይህንን አጭር ልቦለድ መጻፉም አስገርሟል:: እነሆ ልቦለዱን ታነቡት ዘንድ እንዳለ አሰፈርነው::

የምስጋና ዓይነት ሰው እንኳ አይደለሁም:: ግን በጣም ሰጋሁ:: ስንታየሁ መስጋት ከጀመርኩ ሰንብቻለሁ:: እንደ ልማዱ ከተሰወረ ቆይቷል:: ሶስት ወር አልፎታል:: መጨረሻ ያየሁት ምሽት የወትሮው ስንታየሁ አልነበረም:: ሳቂታ፣ ተጫዋች፣ ጠጡልኝ ብሉልኝ ማለት የማይታክተው ስንታየሁ አልነበረም:: ሲበዛ ቀልደኛ ነው:: ያለ ሳቅ ህይወት ምንድነው?! ማለት ይወዳል አዘውትሮ:: እና ይቀልዳል፣ ይስቃል ስቆ ያስቃል:: ቀልድ ሲያልቅበት “ያ ቀልድ ትዝ ይልሃል?” ብሎ ይጠይቀኛል::

 “የቱ ልጄ?”

 “ሶስተኛው”

እና ሶስተኛው ቀልድ እያስታወስን መሳቅ እንጀምራለን:: ለምናውቀው ቀልድ ሁሉ ቁጥር፣ ቁጥር አድርገናል:: እኔ አንዳንዴ በቁጥሩ ቀልዱን ማስታወስ ይሳነኛል:: እሱ ግን ምንም አይረሳም:: የሚደንቅ የማስታወስ ችሎታ አለው:: ማስታወሻ አይዝም:: ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማስታወሻ ሲይዝ አይቼው አላውቅም:: ዓመት፣ ሁለት ዓመት ቆይቶ ያን ቀን የተባለውን ወይም የተደረገውን ነገር ቢጠይቁት ግን አንድ በአንድ ዘርዝሮ ያስረዳል:: ማንኛውንም ነገር እንደ ፎቶ ግራፍ ማንሻ ቀርፆ ለማስቀረት የሚችል ጭንቅላት አለው:: ምናልባት ለዚህ ይሆናል ደራሲ የሆነው – አንድን ሰው ደራሲ የሚያደርገው ነገር ምን እንደሆነ በውል ባላውቅም ቅሉ:: እንደ ዕድል ሆኖ ከስንታየሁ ቃለ ሕይወት ሌላ ደራሲ በቅርብ የማውቀው የለኝም:: ሁሉም እንደ ስንታየሁ ከሆኑ ግን ከሩቅ ሊሸሿቸው የሚገባቸው ፍጥሮች ናቸው:: እውነቴን ነው:: ለጓደኝነት አንድ ደራሲ ይበቃል – እሱም በስንት መከራ::

አይ ስንታየሁ! ለሚያደርገው ነገር ሁሉ ልክ የለውም:: ሲጠጣ እንደ አሣ፣ ሲወድ እንደ ጳጉሜ ውሻ፣ ሲቸር እንደ ንጉሥ፣ ሲያጣ እንደ ቤተስኪያን ዓይጥ ነው:: ለነገ የሚለው ነገር ከቶ የለውም:: የሚያደርገው ነገር ሁሉ ከልክ በላይ መሆን አለበት:: ከእሱ ጋር አብረውት እንዲስቁ / ሲስቅ/ ከእሱ ጋር አብረውት እንዲያለቅሱ / ሲያለቅስ/ ይፈልጋል:: ሕይወትን ካልኖርከው እንዴት ልታውቀው ትችላለህ? የሚል ፈሊጥ አለው:: ኃጢያት ነው የሚለው ነገር ያለው አይመስለኝም:: ሕይወት ላይ ኃጥያት ልትሰራ አትችልም:: ከኃጥያት ባሻገር ምንም የለም:: ሕይወቴ በራሷ ፍጻሜ ናት ባሌ ነው:: እና ይኖረዋል:: መጻፍ ሲጀምር እንደዚሁ ያበዛዋል:: እያንዳንዱ ቃላት እና ከያንዳንዱ አረፍተ ነገር ጋር እየተጣላ፣ እየተጨቃጨቀ፣ አማን ሲወርድም እየተዋደደ፣ እህል፣ ውሃ ወይም ዕረፍት ሳይል ልቡ ውስጥ ያለውን አሳብ አውጥቶ በውበት ወረቀት ላይ ካላሰፈረ ቀና አይልም:: ሰው አያነጋግርም፣ ሌላ ደስታ አያምረውም:: ከፈጠራ ሥራ ምትሐት ሥር ይወድቃል:: ለጥበብና ለውበት ፍጹም ተገዥ ይሆናል፤ አንዳንዴ ስመለከተው አንድ የማይታይ ኃይል የሚያመልክ ወይም የሚያነጋግር ይመስለኛል:: የውበት አምላክ ካለ አንዳንዴ በቅጽበታዊ ጨረፍታ የማየው ከስንታየሁ ቆንጆ ገጽታ ላይ ነው:: ቆንጆ ፊቱ አንዳንዴ ዝምብሎ፣ ጸጥ ብሎ ይፈካል – ፈገግ፣ ወከክ፣ ፈካ እያለ፣ ፀዳል ብርሃን እየሆነ ይሄዳል፤ ብዕሩ ይንደረደራል – ቀለሙ ይፈሳል:: የሆነ ነገር ሲሰምርለት ትንፋሽ ያለው መስሎ አይታይም:: ልቡ ቆሞ ይሆን? እላለሁ አንዳንዴ:: ውበት ልብ ያቆማል ልበል እና በውበት አምላክ ፊት ወጣት ይሆናል – ውብ ወጣት:: አጠገቡ መኖሬን ፈጽሞ ይዘነጋል:: አንዴ መጻፍ ከጀመረ ከድርሰቱ ውጭ ለእሱ ምንም ነገር ሕላዊ የለውም:: እኔም ብሆን አላስቸግረውም:: የፈጠራ ውበት፣ ጭንቀት እና ደስታ ስለማይገባኝ ነው መሰለኝ፤ በልቤ ለምን ነው? ይህ ሁሉ ጭንቀት ለምንድነው? እያልኩ ያደረበት ምትሐት እስኪያልፍለት ድረስ ዝም ብዬ እጠብቀዋለሁ:: ምትሐቱ በላዩ ላይ እንዳለ ከቀጠለም ጥዬው እሔዳለሁ:: አንዳንዴ ቀና ብዬ በረጅሙ የደስታ ትንፋሽ ከተነፈሰ በኋላ “አለህ እንዴ?” ይለኛል::

 “አዎ! እንዴት ነው”?

 “ውብ ነበር:: ስንት ሰዓት ነው?” በማለት በደስታ እጆቹን እያሸ፣ “ውብ ነበር:: ሔደን ይህን ቀን እናክብረው:: ጂን ቶኒክ ለዘላለም ይኑር…ታውቃለህ? ዛሬ አንድ ነገር ተረዳሁ ስለ ሰው ልጅ” ይለኛል::

በየጊዜው ስለ ሰው ልጅ አንዳንድ ነገር ይረዳል::

 “ምን ልጄ?”

 “ታውቃለህ ውበትን ከማድነቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው በልቡ ክፉ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም:: አይመስልህም?”

 “እውነት”

“ለማንኛውም ነገር ዛሬ ካንዱ ባህርይ የተረዳሁት ይህን ሐቅ ነው:: ከምትፈጥራቸው ባህርያት ተመልሰህ ትማራለህ… ከሚፈጥራቸው ባህርያት ተመልሶ የማይማር ወይም ስለሰው ልጅ አዲስ ነገር የማይረዳ ደራሲ የሞተ ነው:: አይመስልህም” አሁን እሱን እንተወው እና ሔደን እንጠጣ:: ከሕይወት ጋር ፍቅር ይዞሃል:: እና ለሕይወት ውበት መጠጣት እፈልጋለሁ::

ለምን በጂን ቶኒክ ለመስከር እንደሚፈልግ አይገባኝም:: ዘላለሙን በህይወት አረቄ እንደሰከረ ነው:: ሲደሰት ብቻ አይደለም የሚጠጣው:: ውበት አልታይ ያለው ለትም ይጠጣል:: ከውበት ጋር ያልተሞሸረለት ድንገት ያረጅብኛል:: ውበቱ ከፊቱ ይጠፋል:: ጥርሱ ያገጣል:: ግንባሩ ይቋጠራል:: ሕይወቱ እውስጡ ታፍና ሊፈነዳ ይደርሳል:: እና ይጠጣል:: ለውበት አምላክ ብዙ ጂን ቶኒክ ይሰዋል:: ግን ብዙ የሚጠጣው አንድ መጽሐፍ ደርሶ ጨርሶ ሌላ አሳብ በሚጸንስበት ጊዜ ውስጥ ነው:: ያኔ ዝምታ ያበዛል:: ዝምታው መጨረሻ የለውም:: በዚያን ወቅት ሲኮረኩሩትም አይስቅም:: ዝም ብሎ ይተክዛል:: ዝምታው ግሩም ነው፤ ውብ ነው፤ ድንቅ ነው፤እጭንቅላቱ ውስጥ ግሩም አሳብ ትር ትር ሲል የሚሰማኝ ይመስለኛል:: ባሳቡ ውስጥ የሰው ልጅ ትልቅነት፣ ውበትና ፍቅር ይታየኛል:: ብሩህ ገጽታው ላይ ችግር ምንድነው? የህይወት ውበቷ ከመኖር ላይ ነው የሚል አሳብ ይነበበኛል:: እና ሁልጊዜ እንዲያስብ እና እንዲጽፍ እፈልጋለሁ::

 ላናግረው አልሞክርም:: አንድ ቃል ሳንለዋወጥ ብዙ ቀንና ምሽት አብረን እናሳልፋለን:: አውቀዋለሁ:: ያውቀኛል:: ዝምታችን በቂ ነው:: የግድ መነጋገር የለብንም:: አብረን እስከሆንን ድረስ ዝምታችን ያስደስተናል:: እንደ እውነቱ ከሆነ በዝምታችን ውስጥ ብዙ የምንግባባው ነገር እንዳለ ይሰማኛል:: እኔ ሆንኩ እሱ አንዱ ሌላውን ለማስደሰት የምናደርገው የተለየ ጥረት የለም:: የልብ ጓደኞች ነን በቃ:: እኔ ለእሱ ከዚህ በላይ ነቃ ማለቴ – እኔ ለእሱ ከጓደኛ በላይ መሆኔን ብዙ ግዜ ነግሮኛል:: የሚጽፈው ለኔ ነው:: እኔን ፊቱ ቁጭ አድርጎ ነው የሚጽፈው:: ካለኔ ሌላ ታዛቢም ተመልካችም፤ ሆነ ሃያሲ አያውቅም:: “አሁን የምጽፈው ነገር ህሊናን ያረካው ይሆን?” የሚል ነው የመጀመሪያው ጥያቄ:: በነገራችን ላይ ህሊና እባላለሁ ህሊና ይፍረደኝ:: የሚጽፈው ነገር እኔን የሚያረካኝ መስሎ ካልታየው ወይም ከተሰማው ሀሳቡ ወደፊት አይገፋም፤ እዚያው ይገድለዋል:: በእኔ ምክንያት ስንት ጥሩ አሳብ ገድሎ እንደጣለ አላውቅም:: እርግጠኛ ነኝ ብዙ ናቸው:: ኃላፊነቱ ይሰማኛል፤ ይከብደኛል:: “እኔ ማነኝ” እለዋለሁ:: ምን ርግማን ብሆንበት እና ምን ቢጠላኝ ግን አይተወኝም::

“ምን ማለትህ ነው?”

 “ደርቄአለሁ አልኩት…”

 “አትቀልድ!”

“ቀልዴን አይደለም:: የምለው አዲስ ነገር የለኝም:: ሌሎች ያላሉት፤ ያልዳሰሱት ምን አዲስ ነገር ልል ወይም ልፈጥር እችላለሁ:: ብዙ በፃፍክና ባነበብክ ቁጥር ብልህ ከሆንክ የምትገነዘበው ነገር ቢኖር ዝም ማለት የሚመርጥ መሆኑን ነው:: እውነቴን ነው:: የገደል ማሚቶ ከመሆን ዝምታ ይመረጣል:: በራስህ የዝምታ ጥልቀት ውስጥ መስመጥ ራሱ ውበት ነው” አለኝ::

 “ሶስት ልብወለድ ብቻ ጽፈህ እንዴት እንዲህ ማለት ትችላለህ? እኔ ካንተ ብዙ ነበር የምጠብቀው” አልኩት::

 “ከሶስት ልብወለድ በላይ ልሔድ የማልችል ብሆንስ? ማንም ከልኩ አያልፍም:: አንዳንድ ሰዎች አንድ ልብወለድ ጽፈው ያቆማሉ:: እንደኔ ያሉት ሶስት ጽፈው ያቆማሉ ሌሎች የታደሉ ደራሲያን አሥር አሥራ አምስት ወይም ከዚያም በላይ ይሔዳሉ:: አዲስ ነገር ለማለት ወይም ለመፍጠር እስከቻሉ ድረስ ቢቀጥሉ ጥሩ ነው:: እኔን የሚያሳዝነኝ ምንም አዲስ ነገር ለማለት ወይም ለመፍጠር ሳይችሉ ለመቀጠል የሚፈልጉ ጅሎች ናቸው:: ጥቅሙ ምንድነው? አዲስ ነገር ለማበርከት የማይችሉ መሆናቸውን በወቅቱ ተገንዝበው ዝምታን የሚመርጡ እንዳልኩህ ነኝ – ጉረኛ ባትለኝ” ብሎኝ ዝም አለ::

 በልቤ ዛሬ አልለቅህም አልኩና “እንደ እውነቱ ከሆነ ልጅ ነህ” ብዬ ጮኩበት….

 “እንዴት? እስቲ ንገረኝ” አለኝ:: ነገርኩት:: ታላቅ አብዮት በመካሄድ ላይ ይገኛል:: አሮጌው ስርዓት እየሞተ አዲሱ እያቆጠቆጠ ሲሔድ እናያለን:: ማኅበረሰቡ እንዳለ በእንቅስቃሴ ላይ ነው:: እያንዳንዱ ቀን በእውነት አዲስ ነው – ማለት የተፈጥሮ ህግ ተከትሎ መሽቶ የሚነጋ ተራ ቀን አይደለም፤ ወይም አይመስለኝም:: እኔ… እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ ቀኑ ሰለቸኝ፤ ረዘመብኝ ያልኩበት ቀን ትዝ አይለኝም:: እያንዳንዱ ቀን የራሱ ገደል የራሱ የሆነ ሽንፈት እና ድል፤ የራሱ የሆነ ውበት አለው:: ኢትዮጵያ ላይ በዘልማድ ነግቶ የሚመሽ ቀን የለም:: ታድያ ይህ ሁሉ ምንድነው? ለደራሲያን ከዚህ የበለጠ የወርቅ ማዕድን ከዚህ የላቀ ልምድ፤ ከዚህ የተሻለ ታላቅ ትምህርት ቤት ምን አለ? ሂድ እና ጻፍ! ብትፈልግ ዝፈን:: ቢሻህ አልቅስ:: ግን ጻፍ ሁሉም በመረጠው መስክ መታገል አለበት ትግል የሌለበት ህይወት የለም:: ግን ትግል ሲባል መጀመር ያለበት ከራስ ነው:: ትልቁ የሰው ልጅ ፈተና ትግል ከራስ ሂድና ጻፍ! ቃላት ኮረት ወይም ድንጋይ አልሆኑም:: ውበት ሞታ አልተገነዘችም:: አዲስ ውበት – አዲስ ሐቅ – አዲስ ተስፋ ሞልቷል – በየመንገዱ – በየፋብሪካው – በየማሳው ሂድና ጻፍ! በዚህ ጊዜ ብዕሬን ካፎቱ ልክተት የሚል ደራሲ እኔ እንጃ…” በማለት ነገርኩት ጨቀጨኩት::

 “ደርቄአለሁ አልኩህ! አትሰማኝም:: የውበት አምላክ ፊቱን አዙሮብኛል – በቃ”

 “አላምንም:: ወይስ ሌላ ምክንያት አለህ”? “ምን ሌላ ምክንያት ይኖረኛል”

 “ምናልባት አቤቱ አስጠልቶህ እንደሆን? የፈጠራ ሰዎች ስትባሉ መቼም ስሜታዊ ናችሁ…”

 “አብዮት ላይ እምነት፤ ለሰው ልጅ ፍቅር እንዳለኝ ታውቃለህ…”

 “ታድያ ምንድነው?”

 “ደርቄአለሁ ስልህ ለምን አይገባህም! ”

 “አይገባኝም! ” ብዬው ከፊት ለፊታችን የተደረደሩትን የአረቄ መለኪያዎች ደፍቼ ተነሳሁ:: ዓይኖቹን ለማመን ያቃተው ይመስላል:: አንዴ ወደ ፈሰሰው ጂን አንዴ ወደ እኔ እያፈራረቀ ሲመለከት ቆየ:: እንዲህ ሁኜ አይቶኝ አያውቅም:: “ዛሬ ምን ነካህ?” አለኝ::

 “ምን ሆኛለሁ?” “ተለወጥክብኝ::”

 “ያው የድሮ ሕሊና ነኝ” ግራ እንደተጋባ ከፊቱ ላይ ይነበብ ነበር::

 “ጥሩ ጂን ለምን ታፈሳለህ ጃል” አለኝ ሊያረሳሳኝ::

 “ከእንግዲህ ይበቃል እኔ ያንተ አስታማሚ አይደለሁም:: ከፈለክ ጂን ከተጠመቀበት ጋን ውስጥ ገብተህ ልትሰምጥ ትችላለህ:: በድንገት ምን ፈሪ እንዳደረገህ አላውቅም:: ደፋር ትመስለኝ ነበር:: ገደል ግባ! ” አልኩት የምሬን::

“የት ልትሔድ ነው?”

“ጂን የሚያጣጣ ሌላ ጓደኛ ፍለጋ! ”

“ያልገባህ ነገር አለ…”

“አዎ፤ ከእውነታ አትሸሽ” ብዬው ጥዬው ሔድኩ:: ይህ የሆነው ቆይቷል:: ምናልባት ዘላለሜን እንድሰቃይ ፈልጎ ይሆናል የትም ሔዶ ጠፍቶ የቀረው:: ብቸኛ ተደራሲያኑ አይደለሁ! እየተሰቃየሁ እንድኖር ፈልጎ ነው:: ወደ ሞት ሰደድኩት:: የሞተ ምናለበት? አረፈ ተገላገለ:: ቀሪን ይጭነቀው:: ምነው ባልተናገርኩት፤ ኃጥያቴ ከበደኝ:: ሳይታወቀኝ እምባዬ መጣ:: ባንድ ፊት ደግሞ ንዴት – አደረብኝ:: የምን አትርሱኝ ነው እሱ! ሆነ ብሎ ይሆናል እንዲህ ያደረገው – ዘላለሜን እንዳልረሳው:: ማን ተረስቶ ለመተረት ይፈልጋል – ከሞተም በኋላ በተለይም ደራሲያን? ይሁን:: ግን አሁን ምን አለበት ጠያቂ አድርጎኝ ባይጠፋ! ሰይጣን! የመጣው ዕንባዬ አልወረደም:: አይኔ ላይ ደርቆ ቀረ:: ድንገት የቤቱ በር ሲንኳኳ ሰማሁ::

 “ማነው? ይግቡ”

ስንታየሁ ነበር:: ውበት የተላበሰ ጤናማ ወጣት መስሏል:: “የት ነበርክ አንተ! ”

 “ረጅም ሱባኤ ገብቼ ነበር…”

 “መጥፎ ሥጋት ላይ ጥለኸኝ ነበር:: ምነው ምን አደረግኩህ? ምን በደልኩህ?”

 “አንተም ስለሰው ትጨነቃለህ እንዴ?”

 “ምን ማለትህ ነው? ልቤ ከድንጋይ የተሰራ መሰለህ?”

 “ስለሰው ደንታ ያለህ አይመስለኝም ነበር…”

 “ይህን ሁሉ ዘመን አብረን ስንኖር ስለኔ ያለህ ግምት ይህ ነበር? ይገርማል:: ለምን ልጄ? ምን እንዲህ አሰኘህ?”

 “ግን አሁን ተለውጠሃል” አለኝ::

 “እንዴት? እስቲ ንገረኝ” አልኩት::

 “አሁን ስሜት አለህ:: በፊት ሁሉንም ነገር ከርቀት የምትመለከት ትመስለኝ ነበር:: ደንታ አለህ ለካ! ስሜት እንዳለህ አላውቅም ነበር:: ተደራሲ ሁሉ ደንታ ያለው አይመስለኝም ነበር:: ለማንኛውም ነገር አመሰግናለሁ…”

 “ስለምኑ ልጄ?”

 “የውበት አምላክ ታርቆኛል…”

 “አዲስ ሥራ ጀመርክ?”

 “ስለእሱ ኋላ አጫውትሃለሁ:: ቆንጆ – ውብ አሳብ ነው:: አሁን እንሂድ እና ይህን ምሽት እናክብረው” አለኝ:: ጊዜ አላጠፋሁም ስለ አዲሱ ሥራው ለመስማት በጣም ቸኩዬ ነበር:: ተያይዘን ወጣን:: እንደ ወተት የነጣ የጨረቃ ብርሃን ጭለማው ላይ ነግሷል::

 “ግሩም ናት ውብ ናት:: ዓለም ከእሷ ጋር ይስቃል:: ኮከቦቹን እያቸው:: ሰማይን ተመልከተው:: እና እኔንም” ሁሉንም ተመለከትኩ:: እሱንም ጭምር::

 “መኖር ደግ ነው:: ቆንጆ ነው” አልኩት

 “መኖርና መጻፍ – አዎን ውብ ነው በነገራችን ላይ ፈሪ አይደለሁም” አለኝ:: ፈገግታ ብቻ ሆኖ ነበር…

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top