ጥበብ በታሪክ ገፅ

የእኛ መልኮች አንዳንድ ገጾች

ሀገራችን በብሔር ብሔረሰቦች የታቀፈችና የተገነባች መሆኑን የካዴ የለም:: ይህ የፈጣሪ ይሁንታ ስለሆነ ሰው ሰራሽ አይደለም:: የሰው ልጅ ይህን መለኮታዊ ጸጋ በአቅሙ ሲያስተናግደው ይኸ የባህል ገጽታ ነውና በዚህ ጽሁፍ ይህንኑ የባህላችንን አይነት በመጠኑ ለመቃኘት ሞከርኩ:: የሀሳቡ አነሳሽ ምክንያት ባለፈው የ‹‹ታዛ›› ህትመት ላይ የወጣው የሐጅ አብደላ ታሪክ ስለሆነ፣ ጽሁፉ በአብደላ ያደረ ትረካ እነሆ ተጀመረ::

 ከቀጠሯችን ቀድሜ ነበር ማለዳ ካፌ የተገኘሁት:: የካፌው አንፊ ‹‹አዳራሽ›› ገና በአራት ሰአት ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሏል:: በዚያ ላይ የሚገባውና የሚወጣው ሰው እንቅስቃሴ ምትሃታዊ ትእይንት ይፈጥራል:: በባህል ልብስ አጊጦ የሚንሸራሸር፣ ጠረንጴዛ ከቦ የሚዝናና ቤተሰብ፤ ጥግ ይዞ ለሽምግልና የተቀመጠ የሚመስል የአዛውንት ስብስብ፣ ሽክ ብላ አጣማጇን የምትጠብቅ ኮረዳ፣ … የባህል አልበም የተገለጠበት አውድ ይመስላል:: በዚህ ምትሃታዊ የጧት ምትሃታዊ ትእይንት ውስጥ እንዳለሁ ሐጅ አብዳላ ዋናውን መንገድ ሲያቋርጥ ታየኝ::

 አይን ለአይን ከተያየን መንፈቅ ሳያልፈን አይቀርም:: ሁልጊዜ እንደሚያዘወትረው ከላይ ጃኬት ከታች ጅንስ ሱሪ ለብሷል:: አለባበሱ ያምርበት ነበር፤ አሁን ግን ሰውነቱ ከልብሱ የሸሸ መሰለኝ:: ሲራመድ ፈጣንና ቆፍጣና ነበር:: ዛሬ ያን አይነት አካላዊ ሰብእናውን አጣሁበት:: የጎበጠ፣ በሶስት እግር የሚሄድ መስሎ ታየኝ:: ምናልባት ከተያየን ስለቆየን ወይም መናፈቄ ይሆን? እየቀረበኝ ሲመጣ የፊቱን ገጽታ አየሁት:: የፊቱ ቀለም ገርጥቷል:: ግንባሩን ከዚህ ቀደም ልብ ያላልኳቸው የመስመር ገመዶች ሸፍነውታል:: የጉንጮቹ ስጋ የተንጠለተለ ነገር ይመስላል:: … ቃሉ ይገልጸው እንደሁም አላውቅም፤ ጉንጭ ለጉንጭ፣ ቀጥሎ መዳፍ ለመዳፍ ተሳሳምን:: … ከፊት ለፊቴ ተቀመጠ::

 ስለ ብዙ ነገሮች ስናነሳ ስንጥል ቀየን:: ስለ ግል ጉዳይ፣ ስለቤተሰብ፣ ስለ አገር፣ ስለ ሙስሊሞች፣ … ያላነሳነው ጉዳይ የነበረ አይመስለኝም:: በመጨረሻ ለዛሬ እንዲንገናኝ ስላደረገን ጉዳይ አመራሁ:: እስከዚህ ጊዜ ሐጅ አብደላ ለምን እንደፈለኩት አልጠየቀኝም ነበር:: ትእግስቱ የሚገርም ነው::

‹‹ያችን ፈረንጅ ሴትዮ ታስታውሳታለህ?›› አልኩት::

 ‹‹ያቺን – ማለት ያንተን አስተማሪ እንዳይሆን?›› አለኝ ከአፍታ ማሰላሰል በኋላ::

ለነገሩ በጋራ የምናውቀው ፈረንጅ አልነበረንም::

‹‹አዎ:: አብረን ኢንተርቪው ያደረግንህ››

‹‹ምን ሆነች?›› አለ ደንገጥ ብሎ:: ‹‹ደግ ሴት ነበረች::››

‹‹ኧረ ምንም አልሆነች እሷ:: እንዲያውም የላከችልህን ደብዳቤ ለማድረስ ነው የቀጠርኩህ›› አልኩት::

‹‹ለኔ ደግሞ የምን ደብዳቤ ነው የምትልከው? ምን አድርጌ?››

‹‹እሱን ያልከው አንተ ነህ:: ለማንኛውም ከፍተህ አንብበው›› አልኩትና የታሸገ ፖስታ ሰጠሁት:: ሐጅ አብደላ ግራ እንደተጋባ ፖስታውን ከፈተው:: ከውስጡ አምሳ ዶላር መዞ አወጣ::

‹‹የምን ዶላር ነው?›› ሲል አፈጠጠብኝ::

‹‹ለሽብር ስራህ ማስፈጸሚያ ቢያግዝህ ብላ የላከችልህ ነው›› አልኩት ኮስተር ብዬ::

‹‹አትቀልድ››:: ለሐጅ አብደላ ባለፈው የታዛ ቅጽ ላይ ያስነበብኩትን ገጠመኝ አጫወትኩት::

‹‹እሷም እንዳንተ የአንድ ቡና/ማኪያቶ ግብዣ ከቤተሰቦቿ አሰባስባ እንዲሰጥህ የላከችው ነው::››

‹‹ምን? በአላህ ምን እያልክ ነው?›› እውነቱን ነገርኩት:: ድንገት ስሜት ውስጥ ገባ:: መሃረብ አወጣና አይኖቹን ጠራረገ:: ግን አልቻለም:: ከአጠገባችን የነበሩ ሰዎች እስኪደናገጡ ድረስ አነባ:: አንዳንዶች መርዶ ያረዳሁት እየመሰላቸው ያፈጠጡብኝም ነበሩ:: ሁለታችንም በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ሆነን ቆየን::

 ‹‹ምን እንደሚያስለቅሰኝ ታውቃለህ?›› ሲል ጠየቀኝ:: አጠያየቁ ከኔ መልስ የሚጠብቅ አልነበረም:: ቀጠለ::

‹‹እድሜዬን በሙሉ በሰብአዊ አገልግሎት ስራ አሳልፌአለሁ ብዬ እገምታለሁ:: ከጡረታም በኋላ የጠለቀ ሃይማኖታዊ እውቀት ባይኖረኝም በነበረኝ የስራ ልምድ ፊቴን ወደ ሙስሊሙ መልሸ ነበር:: … በንጉሱም፣ በደርጉም ዘመን ስለኖርኩ አሁን ህዝበ ሙስሊሙ በብዙ መልኩ ተለውጧል:: ልጆቻችን መስጅድ አዘውታሪዎች፣ በሰላት ቋሚዎች ሆነዋል:: መስጅዶችና መድረሳዎች ተስፋፍተዋል:: ይሁንና ህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያንሰው ይመስለኛል:: የቲሞችን ለመርዳት ስንቀሳቀስ የተረዳሁት እንዲህ አይነቱን ነው:: በዚህ እረገድ ፈረንጆች ያስቀኑኛል:: በብዙ መልኩ ይበልጡናል:: መለኮታዊ አጅር ሳይሆን መንፈሳዊ እርካታ ለማግኘት ሲሉ የሚሰሩት ያስቀናል:: እስላም ክርስቲያን ሳይሉ የተቸገረ ሲረዱ ከማንም ምንም አይጠብቁም:: ከኛ ተምረው በተግባር እኛኑ ሲያስተምሩን ያሳፍራል:: ብዙዎቻችን የተቸገረ ሰውን መርዳት ግደታችን መሆኑን በዘነጋንበት ዘመን እነሱ ብዙ እርቀት ሄደዋል:: … ሐጅ አብደላ ውስጥ በፊት የማውቀው ጥንካሬውን ያጣሁበት መሰለኝ:: የሆነ ጉዳይ ስሜቱን ሳይጎዳው አልቀረም:: የሚናገረውን በጥሞና መከታተሉን መረጥኩ::

‹‹ይቅርታ ብዙ ተናገርኩ መሰለኝ:: የዚያች የማታውቀኝና የማላውቃት ፈረንጅ ሁኔታ ውስጥን እረብሾት ነው:: እዚህ ሙስሊም ሆነህ ችግረኛ ልጆች ለመርዳት ስትሞክር፣ በየቲም ሽፋን ለሽብር ተግባር ገንዘብ ታሰባስባለህ እየተባልክ በገዛ በአገርህ ሰው ትፈረጃለህ:: በገዛ መንግስትህ ቁም ስቅልህን ታያለህ:: … ለማንኛውም የፈረንጇ ድጋፍ የደረሰኝ ደክሞኝና ሰልችቼ ስራውን ለማቆም በወሰንኩበት ጊዜ ላይ በመሆኑ አዝናለሁ፣ አዘኔም አስለቀሰኝ::›› አልዋሽም እኔም አብሬው አልቅሻለሁ:: አላህ ምንዳውን ይጨምርለት:: እኔም ወደሌላኛው መልካችን ልሸጋገር::

ቀጣይቃ ባለ ቃል ታሪካችን ሶፊያ ጠይብ ትባላለች:: ሶፊያ ቁመቷ መካከለኛ፣ የሰውነቷ ቅርጽ እንኳን ሶስት አንድ ልጅ ስለመውለዷ ለማመን የሚያስቸግር አይነት ናት:: ባህሪዋ ደግሞ ከቁመናና ከመልኳ በላይ ነው:: ከአዋቂ ጋር አዋቂ፣ ከልጅ ጋር ልጅ የመኾን ችሎታዋ የሚገርም ነው:: ሰው ታምናለች፣ ለሰው ክብርና አክብሮት አላት:: ይኸ ሁሉ ተደማምሮ የሚያውቋት ሁሉ፣ ትልቅ ትንሹ ‹‹ሶፊ›› እያሉ ይጠሯታል:: ሶፊ በስራ አለም በነበረችበት ጊዜ በርካታ ጓደኞች ነበሯት:: አንዷ ዘላለም ፍስሃ ትባላለች:: ዘላለም አጥባቂ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ስትሆን በተለይ በሰብአዊ ጉዳይ ላይ ታመዝናለች:: የዘላለምና የሶፊ ባህሪ በብዙ መልኩ የሚግባባና የሚመጋገብ መሆኑ አስተሳሰራቸው::

‹‹አንድ ጊዜ፣ ጊዜው የክርስትያኖች የጾም ወቅት ከሰአት በኋላ ነው፤ ዘሌ (‹‹ዘሌ›› የዘላለም የቁልምጫ ስም ነው) ከወትሮዋ ዘግይታ ወደ ቢሮ ትመጣለች:: ፊቷን ሳየው ደስታ አጣሁበት:: የድካም እንዳልሆነም ግልጽ ነበር:: ‹ዘሌ ፊትሽ ጥሩ አይደለም፣ በሰላም ነው?› ስል ጠየኳት:: ‹ሰላምስ ሰላም ነው:: ምናልባት ቤተ ክርስቲያ ሄጄ የተፈጠረብኝ ስሜት ነጸብራቁ ይሆናል› አለችኝ:: ‹ምን ይሆን እሱ?› አልኳት አፌ እንዳመጣብኝ:: ከዘሌ ጋር ሃይማኖታዊ በሆነ ጉዳይ ብዙም አናነሳም:: ካነሳም ስለ ሃይማኖቶቹ የጋራ ሞራላዊ እሴቶች ዙሪያ እንወሰናለን:: ለምሳሌ ዘሌ – የእናንተ ሃይማኖት ለንጽህና የሚሰጠው ቦታ ይገርመኛል:: ጸሎታችሁና ጾማችሁ እድሜና ጾታ ሳይለይ ሁሉም በአንድነት ይሰገዳል፣ በአንድነት ይጾማል:: ከሁሉም በላይ ለድሃና ለተቸገረ ሰው ያላችሁ ስሜት ያስቀናኛል:: ያላችሁን ስትሰጡ ገደብ የላችሁም:: – አይነት ጉዳዮች ደጋግማ ታነሳለች:: ‹ያ መስጠት የሚሉት ያንቺ በሽታ ተጋብቶብኝ የሆኑ ብሮች ለኔ ብጤ ለመስጠት ፈለኩ:: ገና ቦርሳዬን ስነካካ በኔ ብጤ ተወረርኩ:: እንደሌባ ታፈንኩ:: ብሮቹን መስጠት ትቼ እራሴን ለመጠበቅ ተገደድኩ:: አቅም ያለው ከእጄ ላይ መንጥቆ ወሰደ:: ብዙዎች እንደከበቡኝ ቀሩ:: ከዚያ የሆንኩትን አላውቅም:: ሶፊ ምን ብዬ፣ እንዴት ብዬ እንደሚገልጽልሽ አላውቅም:: አለቀስኩ:: እነሱም አብረውኝ ሳያለቅሱ አልቀሩም:: በመጨረሻ እነዚያ የኔ ቢጤዎች አረጋግተው ከቤተክርስቲያኑ አጸድ አስወጡኝ:: ሶፊ አንቺ ብትሆኚ ምን እንደምትሆኒ ማሰብ አልፈልግም::› አለችና ዝም አለች:: ‹ዘሌ አይ እንዲህ መሆን አልነበረብሽም:: የቻልሽውን ያህል ከሰጠሸ ከዚያ በላይ ፈጣሪ የሚጠብቅብሽ አይመስለኝም:: ማዘኑም፣ መስጠቱም የሱ ጸጋ እንደሆነ አትርሺ› ስል ተነፈስኩ:: ‹እሱስ ልክ ነሽ:: ለእኔስ የሰጠኝ ፈጣሪ አይደል:: ስሜቴን የጎዳው ምን መሰለሽ? ጠንከር ያለው የኔ ቢጤ ነው ከእጄ ላይ የነጠቀኝ:: አየሽ ሶፊ መስጠት ለፈለኩት አለመስጠቴ ተሰማኝ› አለችኝ በትካዜ::

ዘሌ ይህን ሀሳብ ስታነሳ ለእኔ ደግሞ ሌላ ሀሳብ መጣልኝ::

አለም ገና ረጲ አካባቢ አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር:: በዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች አብዛኞቹ ችግርተኞች ነበሩ:: የሆነ ነገር በቀን አንድ ጊዜ ቀምሰው ውለው የሚያድሩ፣ ክፍል ውስጥ ፌንት ነቅለው የሚወድቁ የሚበዙባቸው ነበሩ:: ወላጆቻቸው ደግሞ ከልጆቻቸው በባሰ ችጋር ውስጥ የነበሩ ናቸው:: አንዳንዶቹ የቀን ሰራተኛ፣ የቀን ስራ ከጠፋ ጦም የሚያድሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ በበሽታ ያልጋ ቁራኛ ሆነው የሰው እጅ የሚጠብቁ፣ ወዘተ:: ችግሩን ለመቅረፍ መምህራኑ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ካፊቴሪያ ይከፍታሉ:: ከካፊቴሪያው ከሚገኘው አነስተኛ ገቢ፣ ከመምህራኑ የግል ድጎማ የታወቁ ችግርተኞች በቀን አንድ ጊዜ ነጻ የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ የታሰበ ነበር:: በዚህም ችግሩን ብዙም ሊቋቋሙት ሳይችሉ ይቀራሉ:: ሌላ ሃሳብ መጣላቸው፤ ህዝብ እንዲያውቀው በማድረግ የቻለ እንዲረዳቸው መሞከር:: ይህ ሃሳባቸው በአንድ የብዙሃን ድርጅት ለአንድ ጊዜ ተሳካላቸው:: ከዚያ በኋላ ‹‹ከበላይ አካል እንዲህ አይነት ዜና በይፋ ማወጅ ተገቢ አይደለም› ተብሏል ተባለና ዜናው እንዳይሰራጭ ሆነ:: ነገር ግን እንደታሰበው መረጃውን ማፈን አልተቻለም:: ዘገምተኛም ቢሆን ከአንዱ ወደ አንዱ እየተላለፈ ብዙ ሰዎች ጆሮ ደረሰ::

 ‹‹ዘሌ፣ ለምን እዚያ ትምህርት ቤት ሄደሽ የቻልሽውን ያህል አትረጅም›› አልኳት::

 ‹‹ቆይ እንዲህ አይነት ትምህርት ቤት እዚህ አዲስ አለ ነው የምትይኝ?››

 ‹‹ባይኔ አላየሁትም:: ዜናውን የሰሙ፤ ሄደን አየንም የሚሉ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ::››

 ሶፊና ዘላለም ተያይዘው ሄዱ:: የትምህርት ቤቱ አካላዊ ቁመና መመዘኛውን ያሟላ አይነት ነው:: ግቢው ሰፊ፣ አጸዱ የተዋበ ነው:: እዚህ ትምህርት ቤት በቀን አንድ ጊዜ ቀምሰው የሚውሉ ተማሪዎች ይገኙበታል ብሎ ለመቀበል ከበዳቸውና በመገረም ስሜት አይን ለአይን ተያዩ:: ነገር ግን ወደ ውስጥ ዘልቀው፣ የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተር ሲያነጋግሩ እውነታው ከሰሙት በላይ ሀቅ ሆኖ አገኙት:: ርእሰ መምህሩ እዚህ ለመግለጽ የሚከብዱ ችግሮች እንዳሉ ነበራቸው:: ጉዳዩን ህዝብ አውቆት ድጋፍ እንዳይገኝ መደረጉን፣ በዚህም ምክንያት መምህራኑ ከሌለ ደመወዛቸው ያቅማቸውን ያህል ሲረዱ መቆየታቸውን፣ አሁን ላይ በራሳቸው ገንዘብ ካፍቴሪያ አቋቁመው ከሚገኘው ገቢ ልጆቹን እየደጎሙ እንደሚገኙ፣ ወዘተ ተረዱ::

 ‹‹አሁን እኔ ለመርዳት ብፈልግ፣ እንዴት መርዳት እችላለሁ›› አለች ዘላለም::

‹‹ያቋቋምነው ካፍቴሪያ ሌላኛው አገልግሎቱ ለረጅዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው:: አንድ ወይም ሁለት ተማሪ ቁርስ ወይም ምሳ ወይም ቁርስና ምሳ መርዳት ከፈለግሽ የወሩን ወይም የሴሚስተሩን ወጪ ለክበቡ ትከፍያሽ:: በዚህ መልክ ልጆቹ እርዳታ እንዲያገኙ ይደረጋል::››

‹‹እርዳታ የሚፈልጉ ስንት ይሆናሉ››

 ‹‹እርዳታ የማይፈልግ የለም:: ሁሉም አንድ አይነት ነው››

 ‹‹እሺ አሁን እኔ ሶስት ልጆች ለመርዳት ብፈልግ በምን ይታወቃሉ››

 ‹‹እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ልጆች ፋይል አለን:: ማን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ማን እየተረዳ እንደሆነ … ይታወቃል::››

 ‹‹እሺ የሶስት ልጆች የወር ሂሳብ ንገረኝና ልክፈል::››

‹‹ከዚያ በፊት የምትረጃቸውን ልጆች ማየት፣ ጠይቀሽ ማጣራት ይኖርብሻል::›› ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ተማሪዎች ተጠሩ:: ርእሰ መምህሩ ተረጂ ተማሪዎቹን ከነ ዘላለም ጋር አስተዋወቀ:: ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ››

ሲልም ልጆቹን ለማስደሰት ተናገረ:: እነ ዘላለም ከልጆቹ ጋር ሲጨዋወቱ ሁሉም የራሱን ምርጫ አቀረበ:: አንደኛው ደካማ እናቱ በቀን ስራ የምትኖር ስለሆነ እርዳታው ለእናቱ ቢሰጥለት ጠየቀ:: ሁለተኛውም እናቱ ታማ እቤት የቀረች ስለሆነ እርዳታው ለእናቱ ቢሆን ተመኘ:: ሶስተኛዋ ሴት ተረጂ እርዳታው በትምህርት ቤቱ በኩል እንዲሆንላት ገለጸች:: ከገጠር የመጣችና አክስቷ ጋር የምትኖር ነበረች::

 ዘላለም የምታየውንና የምትሰማውን ማመን አልቻለችም:: በተለይም የሁለቱን ወላጆች እናቶች ማየት ፈለገች:: ልጆቹን አሳፍረው መንገድ ገቡ:: የመጀመሪያው ልጅ እናት ቤት ሄዱ:: የልጁን እናት አንዲት ከቆርቆሮ ከተሰራች ጠባብ ክፍል ውስጥ ተኝተው አገኗቸው:: ከሴትዮዋ በቀን ስራ እንደምትተዳደር፣ ለዚያች ክፍል አንድ ሺህ ብር እንደምትከፍል፣ ወዘተ ተረዱ:: ዘላለም ለሴትዮዋ አምስት መቶ ብር ሰጠችና ወደ ሁለተኛው ልጅ እናት ቤት አቀኑ:: የዚህም ልጅ እናት ከቆርቆሮ ከተሰራች ጠባብ ክፍል ተኝታ አገኗት:: ሴትዮዋ የካንሰር ህመምተኛ ነበረች:: ‹‹ቆይ ህክምናው በነጻ ይሰጥ የለ እንዴ፣ ለምን አይታከሙም›› ሰትል ዘላለም ጠየቀች:: ‹‹እውነትሽን ነው ልጄ፣ በነጣ እየታከምኩ ነበር:: ነገር ግን ትራንስፖርቱም ችግር ሆነና አቋረጥኩ›› ስትል መለሰችላት:: ዘላለም ለዚች ሴት ‹‹በሉ ህክምናዎትን ይቀጥሉ›› ብላ አምስት መቶ ብር ሰጠቻት::

 ሶፊና ዘላለም እንደተኮራረፈ ሰው ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ብዙ መንገድ ተጓዙ::

‹‹ሶፊ በፈጣሪ የምን ጉድ አሳየሽኝ ባባትሽ፣ ለመስማት የሚከብድ፣ ይህን ጉድ እያየና እየሰማ የሰላም እንቅልፍ የሚተኛ እግዜር የበደለው መሆን አለበት::››

 ‹‹ዘሌ እኔም ወሬውን ስሰማ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አስቤ አልነበረም::››

 ‹‹በልቤ ምን እያሰብኩ መሰለሽ፣ እኒህን ሶስት ልጆች የቻልኩትን ያህል በቋሚነት መርዳት፣ የሁለቱን ልጆች እናቶች ማቋቋም:: ይህን ባደርግ የህሊና እረፍት የማገኝ ይመስለኛል::››

 ‹‹ጥሩ አስበሻል፣ ባይሆን ከእንግዲህ እኔ የለሁበትም››

ዘላለም ካሰበችው በላይ አደረገች:: ሶስቱን ልጆች የምግብ ብቻ ሳይሆን የልብስና የመማሪያ ቁሳቁስ ወጭ እየሸፈነች እርዳታዋን ቀጠለች:: የሁለቱን ልጆች እናቶችም አልተወቻቸውም:: በሽተኛዋን እናት አሳከማ ጀላቲ እየሸጠች ኑሯቸውን እንዲትደጉም ፍሪጅ ገዛችላት:: ለሌላኛው ልጅ እናት ደግሞ ለጉሊት ስራ የሚሆን ገንዘብ ደጎመቻት:: … ዘላለም ፍስሃ ዛሬ የአሜሪካ ነዋሪ ሆናለች::

ሶፊና ጀምኣዎቿ:: ሶፊ ዝምድናን ለማስቀጠል፣ የእርስበርስ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ መተሳሰብን ለመጨመር፣ ወዘተ በሚል እስላማዊ መርህና ማህበራዊ አስፈልጎት የተቋቋመ የቤተሰብ ጀምኣ ነበራት:: ጀምኣው በየወሩ የሚካሄድ ነው:: በአንድ የረመዳን ወር ዋዜማ ይኸው ጀምኣ ይሰበሰባል:: የተለመደው ዳቦና ቆሎ ከተበላ፣ ሻይ ቡና ከተጠጣ በኋላ ወርሃዊ የዳእዋ/ሰበካ መደረግ ይጀምራል:: የተሰበሰቡበት ጊዜ የረመዳን ጾም ዋዜማ ስለነበር የእለቱ አጀንዳም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይሆናል:: የረመዳን ወር መንፈሳዊ፣ እምሯዊ፣ አካላዊ፣ ማህበራዊ ፋይዳው በሰፊው ተዘረዘረ:: በመጨረሻም በረመዳን ማህበራዊ ፋይዳ ላይ ጊዜ ወሰዱ::

በረመዳን ወር ማህበረ መንፈሳዊ ፋይዳ ካላቸው ክዋኔዎች መካከል ዘካ፣ ዘካተል ፍጡርና ሶደቃ ዋነኞቹ ናቸው:: እነዚህ የረመዳን ወር ክንውኖች ዘካና ዘካተል ፍጡር ግዴታዎች፣ ከሶደቃዎችም የተወሰኑ ግዳታ ያለባቸውንና ሌሎች በፈቃድ የሚፈጸሙ ናቸው:: ሁሉም አይነት ተግባሮች ድሆችን ከመፍቀድ፣ ከማሰብ፣ ከመርዳት፣ ወዘተ ጋር የተገናኙ ናቸው:: የሶፊ ጀምኣዎች በሁሉም ጉዳዮች ዙሪያ ሲተዋወሱ ቆዩ:: ብዙዎቹ ተግባሮች ባለቤቶቻቸው የታወቁና በግል ሊፈጸሙ የሚችሉ ነበሩ:: በዚሁ መካከል ሶፊ ጀምኣውን የሚመለከት አንድ ሃሳብ አነሳች:: ከላይ የረጲ አካባቢን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሁኔታና ከክርስቲያን ጓደኛዋ ከዘላለም ፍስሃ ጋር የነበራትን ተሞክሮ፣ የዘላለምን ፕሮጀክት ሂደት ገለጸች:: ‹‹ ጀምኣችን እንደ ጀምዓ የሆነ ነገር ለምን አናደርግም? ረጲ አካባቢ የሚገኘው ትምህርት ቤት ደግሞ በትክክል በአይን የሚታይ ሶደቃ ተቀባይ የሚገኝበት ትምህርት ቤት ነው›› ስትል ውሳኔ አከል ሃሳብ ሰነዘረች::

‹‹ታሪኩን ስተርክላቸው ከልብ ሳይሰሙኝ አልቀሩም:: ሃሳቤን ስጨርስ ሁሉም ተመስጠው ያዳምጡኝ ነበር:: እንዳልኩትም ሀሳቤ ተቀባይነት አገኘ:: እኔን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሴቶች በቦታው ተገኝተው ያለውን ሁኔታ እንድናሳውቅ ተወሰነ:: ሁለቱን ሴቶች የተባለው ትምህርት ቤት ወሰድኳቸው:: አንድ መምህር አገኘንና የመጣንበትን ጉዳይ አጫወትነው:: ለጓደኞቼ ሙሉ ዝርዝሩን አብራራላቸው:: ድጋፍ ለማድረግ የመጡ ሴቶችን እርዳታ እንድያደርጉ በእናታቸው ስም ተማጸናቸው:: ለገቢ ማሰባሰሚያ የተቋቋመውን ካፍቴሪያ አዩ፣ የሚረዱ ተማሪዎችንም ጎበኙ::

‹‹ ገና ከበሩ ሳንወጣ የእርዳታ እቅድ ተነደፈ:: ለዘንድሮው በብር ድጋፍ እናድርግ:: ለቀጣዩ አመት ግን የተሻለ ገንዘብ አሰባስበን፣ የልጆቹ ወላጆች እራሳቸውን የሚደጉሙበትን ዘዴ መፍጠር አለብን፣ ወዘተ አይነት ሀሳቦች ስናወጣ ስናወርድ ቆይተን በቀጠሯችን ቀን ያየነውን ሁኔታና ያሰብነውን እቅድ ለጀምኣችን አቀረብን:: ሁሉም በሀሳቡ ተስማምቶ ለዚህ አመት አስር ሺህ ብር ድጋፍ እንድደረግ ተወሰነ:: ድጋፉን እንድናደርስ ሃላፊነቱ ተሰጠን::

 ‹‹እኛው የኮሚቴውን ውሳኔ አስር ሺህ ብር ይዘን ወደ ትምህርት ቤቱ ሄድን:: አንድት ጠና ያለ ሰው በቸልተኛ ስሜት ተቀበለን:: የለበስነው ጅልባብ ግራ ሳያጋባው አልቀረም:: የትምግርት ቤቱ ርእሰ መምህር መሆኑን ሲነግረን፣ ከዚህ ቀደም የነበረው እንዳልሆነ ገባኝ:: ከዚህ ቀደም መጥተን ሁኔታውን አይተን እንደተመለስን፣ ዛሬ ደግሞ አቅም በፈቀደ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ መምጣታችንን ነገርነው:: ‹‹የምን ድጋፍ ነው የምታወሩት?›› ሲል ጠየቀን ያልገባው ሆኖ ወይም መስሎ:: ደግመን ነገርነው:: ‹‹ኦ! ይቅርታ:: ተማሪዎቹን ለመርዳት የመጣችሁ ስላልመሰለኝ ነው:: የተቀደሰ ሃሳብ ነው ወገኖቼ:: አሁን የታለ እርዳታው?›› ሲል አስከተለ ከኋላችን የሆነ ነገር እየፈለገ::

‹‹አስር ሺህ ብር ይዘናል፤ ወደፊት ደግሞ ከእናንተ ጋር እየተመካከርን የሚቻለንን ለመርዳት እንሞክራለን›› አልነው:: በዚሁ ተስማማንና ወደ ቢሮ ወሰደን:: ብሩን ቆጥሮ ተረከበና የደረሰኝ ጥራዝ አነሳና ማን ልበል?›› አለ:: ‹‹ሶፊያ ጠይብ›› አልኩት:: ‹‹አይ የድርጅታችሁን ስም››

‹‹እኛ የመጣነው በእድራችን ስም እንጂ የተመዘገበ ድርጅት የለንም›› ስል ለማስረዳት ሞከርኩ:: እጁን ጠረጴዛው መሳቢያ ውስጥ ሰደደና የሰጠነውን የተጠቀለለ ብር አወጣ:: ‹‹አዝናለሁ:: አድራሻው ከየት እንደሆነ የማይታወቅ ገንዘብ እንድቀበል አልታዘዝኩም›› አለና እጁን ዘረጋልኝ::

ሶስታችንም ተደነጋገጥን:: በመገረም አይን ለአይን ተያየን:: ‹‹አልገባንም›› አልኩት::

 ‹‹ይቅርታ እህቶቼ፣ እናንተ በቀና ልብ ልጆቹን ለመርዳት እንደመጣችሁ እገምታለሁ:: ስለዚህ እናንተን ክፉ ነገር ታስባላችሁ ብዬ አልጠረጥርም:: ነገር ግን የአሸባሪ እጅ ውስብስብና ረጅም ነው:: ይቅርታ››

 ‹‹ርእሰ መምህሩ ምን ለማለት እንደፈለገ ገባን:: እኔን በተለይ ገባኝ:: ዘሌ ታወሰችኝ:: ያን ጊዜ አሸባሪ የሚባል ርእስ አልነበረም::››

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top