ጥበብ በታሪክ ገፅ

የእሁድ ፕሮግራም ታሪክና ትዝታን አስቀምጦ አልፏል አይመለስም! …” ስለ ኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ታሪክ ሲወሳ አብረው ከሚታወሱ

 ጋዜጠኞች መካከል አባይነሽ ብሩ አንዷ ነች:: 1973 . መጀመሪያ መስከረም ላይ ይህ ፕሮግራም ሲመሰረት ከነ ድምፀ ሸጋው ታደሰ ሙሉነህ ታምራት አሰፋ፣ ንጉሴ አክሊሉና ሌሎች ታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር ሆና የፕሮግራሙን ይዘት የነደፈች፣ ፎርማቱንም የቀረፀች ናት:: ከዘንጋዳ ማሀል እንደበቀለች ጥንቅሽ የሚጣፍጥ ድምፅ ይዛ የአድማጮችን ቀልብ በመግዛት ፕሮግራሙን ያስወደደች ብቸኛ ሴት ሆና ለበርካታ ዘመናት ስትሰራ በፍቅርና በትጋት ነበር:: አባይነሽ በኢትዮጵያ ሬዲዮ 19 ዓመታት ከሪፖርተርነት ጀምራ እስከ ከፍተኛ የፕሮግራም አስተባባሪነት፤ ብሎም የአማርኛ ፕሮግራም ኃላፊነት ሰርታለች:: በዚህ ሁሉ ሂደት እሁድ ፕሮግራምን መስራት አልተወችም ነበር:: ሬዲዮ ጣቢያውን ከለቀቀች በኋላ ግን የለችም፤ የለችም! ለምን? … የዚህ ዕትም እንግዳችን አባይነሽ ለዚህና ለሌሎች ከሙያዋ ጋር በተያያዘ ላነሳንላት ጥያቀዎች እንዲሁም ስለ እሁድ ፕሮግራም ትዝታዋ እንዲህ አውግታናለች :: መልካም ንባብ::

ታዛ፦ ስለምን ጠፋሽ አባይነሽ?

አባይነሽ፦ የሰው ልጅ ኑሮ ሂደት አለው:: በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ወቅት የነበሩበትን ሁኔታ መልቀቅና ሌላ ይዞ፤ እንደገና ሌላ መሻት ያለ ነው:: እኔ የጋዜጠኝነትን ሙያ እየወደድኩት፣ በደንብም እየሰራሁበት ሳለ በአንድ አጋጣሚ ነው የለቀቅኩት:: ወደ ሌላ የስራ መስክ ስገባ ይበልጥ ትኩረትና ጊዜን የሚጠይቅ ማህበረሰባዊ ጉዳይ ላይ ስለተጠመድኩ ጠፋሁ:: ተመልሼ የምመጣበት ሁኔታ አልገጠመኝም:: ታዛ፦ የዛሬ ጎልማሶችና አዛውንቶች ቀደም ስላለው የእሁድ ፕሮግራም የሚያስታውሱት የተለያየ ትዝታ አላቸው፤ አንቺስ?

አባይነሽ፦ ባሳለፍኩት የሕይወት ዘመን ከሰራሁት ሁሉ የማይረሳኝና ስደሰትበት የምኖረው የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሙያዬ ነው:: ብዙ ትዝታ እና ትውስታ አለኝ:: የቱን ይዞ የቱ ይለቀቃል?… እኔ ወደ ጋዜጠኝነቱ የተቀላቀልኩበት ዘመን በጣም ጥብቅ የሆነ የሚዲያ ቁጥጥር የነበረበትና እንደፈለጉ ማውራት የማይቻልበት ዘመን ነበር:: የሙዚቃ ምርጫ እንኳን በገደብ የነበረበት ጊዜ ነው:: በዚያ ዘመን ሾልኮ የወጣ ፕሮግራም ነው ‐ እሁድ ፕሮግራም:: በዚያ ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ብዙ ባለ እውቀቶች ነበሩ፤ ጎልተው የሚታወቁም የማይታወቁም ነበሩበት:: ፕሮግራሙ ሲጀመር ከበስተጀርባው ሆነው ሲደግፉ የነበሩት የወቅቱ የሬዲዮ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ገዳሙ አብርሃ፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በዓሉ ግርማ፣ እና የሁሉም አስተባባሪ ታደሰ ሙሉነህ ግን የነበራቸው ትልቅ ሚና የማይዘነጋ ነው:: ትልቅ ስራ ሰርተዋል:: ያኔ የአብዮት ዘመን ነው:: አዝናኝ ነገር ህዝቡን ማዘናጋት ነው ተብሎ ይታሰባል:: ሰራዊቱን ከትግል ሜዳ ያሸሻል የሚል ጠንካራ አስተሳሰብም ነበር:: የፍቅር ዘፈን መልቀቅና፣ ሌላ አዝናኝ ነገር ማቅረብ ክልክል ነበር:: ያስቀጣል:: የዘፈን ግጥሞቹ የፊውዳልን ስርአት የሚያወድሱ ናቸው፣ ላባደሩን አያተጋም፣ ገበሬውን አያስደስትም፤ ያሰንፋል ይባል ነበር:: እኛ ግን በክላሲካል ጀምረን ቀስ በቀስ እያለማመድን ነው ወደ ሙዚቃው የገባንበት:: ያንን ስናደርግ ፊለፊት የሚቆጡ ቢመስሉም በውስጣቸው ይፈልጉታል:: ከዚያ ጭንቀት ለመላቀቅ ና ለመዝናናት የማይፈልግ ማን አለ? … እንዲያው አብዮታዊ ግዴታና ክልከላ ስለሚባል ነው እንጂ፤ እኔ እስከሚገባኝ ያንን አስተሳሰብ ሰብረን በመውጣታችን ኃላፊዎች በውስጣቸው ደስተኞች ነበሩ :: ሁሉም ካሴቱን ገዝቶ በቤቱ እኮ ሙዚቃን ያዳምጣል፤ እየተፈራራ ካልሆነ በቀር:: ስለዚህ ደፍሮ እርምጃ ለመውሰድ የጠነከረ አልገጠመንም:: ለዚያ ነው የተወደድነው:: በስራ ሂደት የገጠሙኝ፣ ዛሬ በትዝታ ውስጤ የተቀመጡ ብዙ ነገሮች አሉ… በፍቅርም ሰርቼዋለሁ:: ብዙ ነገርም ተምሬበታለሁ::

ታዛ፦ ከአድማጮቻቸሁ ጋር የነበራችሁ ግንኙነት እንዴት ነበር?

አባይነሽ፦ ሬዲዮ በሚደርስበት ቦታ ላይ ሁሉ ነበርን:: በዚያን ጊዜ ሌላ ምንም የሚያዝናና ነገር አልነበረም:: ቴሌቭዝን አብዛኛው የአገሪቱ ክልሎች አይደርስም:: ቢደርስም በቀን የለም:: አዝናኝ አይደለም:: እንደዛሬው ኤፍ. ኤም ሬዲዮ የለም:: ያለው ብቸኛ መዝናኛ የእሁድ ፕሮግራም ነበር:: ስለዚህ ህዝቡ እንደቤተኛ ያየን ነበር:: ይሳተፉ ነበር:: ከሩቅ ይመጡ የነበሩ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች አስገራሚ ነበሩ:: መምህራኖች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ያቺን ቀን ይናፍቁ ነበር:: ያ ከማህበረሰቡ ጋር የነበረን ትስስር ያስደስተናል:: ያተጋናል:: ደብዳቤዎች ይጎርፉ ነበር፣ ስልኩ ሲንጫረር ነው የሚውለው:: ጥያቄ ይጠየቃል፤ ይመለሳል:: እርግጥ በስራችን ሁሉንም ማስደሰት አንችልም:: የተናደደ ይሳደባል:: ደስ ያለው ያመሰግነናል:: እኛም እንደአግባቡ አድማጮቻችንን ሳናስቀይም መልስ እንሰጣለን:: የሚቆጣው ሲበዛ ልትደሰቱ ይገባችኋል ይለን ነበር አለቃችን ታደሰ:: የተቆጡን ስላዳመጡን ነው ይል ነበር:: «እኛ አቅራቢዎች ነን እንጂ የፕሮግራሙ አዘጋጆች የናንተ ናችሁ» ስለምንል ተሳታፊዎቻችን ብዙ ናቸው:: በእውነተኛ ስማቸውና በብዕር ስም የሚጽፉልንም ብዙ ነበሩ:: መጽሐፈ ሲራክ፣ ጠንክር ዘ ካሳንችስ፣ ዳንዴው ሰርቤሎ፣ አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ፣ ተርቡ፣ ዳግላስ ዼጥሮስ፣ መምህር ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ስንቱን ልጥቀስ…:: እኛ አገናኝ ሆነን በእነሱ ብዕር ህዝቡን ለማንቃትና ለማዝናናት ጥረናል:: እኛም አንዳንዴ በብዕር ስም እንጽፋለን:: ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ ግን በስሙ ነበር የሚጽፈው:: የእሱ ጽሑፍ ከነ ስሙ የፕሮግራማችን ግርማ ነበረ:: ታሪኩን፣ ባህሉን፣ ማህበራዊ ጉዳዩቹን ይጽፍልን ነበር:: እንደየ ጽሑፉ ባህሪ እየተቀያየርን እናነብለታለን:: አድማጭም ይደሰታል፤ ይማርበታል::

ታዛ፦ በዚያን ጊዜ በብዕር ስም የሚጽፉላችሁን በአካል ታውቋቸው ነበር?

አባይነሽ፦ አንዳንዶቹን አዎ::

ታዛ፦ ለምሳሌ አሸናፊ ዘ‐ ደቡብ አዲስ አበባን?

 አባይነሽ፦ አላውቃቸውም:: በስልክ ግን በደንብ እንተዋወቅ ነበር:: በዚያን ጊዜ በጽሑፎቻቸውና በአንዳንድ ሃሳቦች እንጨቃጨቅ፣ እንነጋገር ነበር:: ማህበረሰባዊ ህጸጾች ላይ ፣ ትዳር ላይ የተኮሩ ጽሑፎቻቸው ተወዳጅ እንደነበሩ አስታውሳለሁ:: ሃሳባቸውን ማጋራት፣ እውቀታቸውን ማካፈል እንጂ፤ በአካል መታወቅን አይፈልጉም:: ጥሩ ቋሚ ተሳታፊያችን ነበሩ::

 ታዛ፦ ዛሬ የእኛ መጽሔት ቋሚ ዓምደኛ ሆነው መጥተዋል፤ እንግዲህ አንድ ቀን አስተዋውቃችኋለሁ::

 አባይነሽ፦ በደስታ!

ታዛ፦ ጋዜጠኝነት የጋራ ስራ ነው /theme work/ ነው:: ወደ ሬዲዮ ሲመጣ ደግሞ የዚህ ተግባር ዋጋ ከፍ ይላል:: ይህ ሁኔታ በእናንተ ዘመን አሰራር ምን ይመስል ነበር?

አባይነሽ፦ ፕሮግራማችን ያለምክንያት አልተወደደም:: እዚያ ላይ የነበርን ጋዜጠኞች ለፕሮግራሙ ማማር ደስ እያለን እንከፍል የነበረው መስዋዕትነት ተወዳጅ እንድንሆን አድርጎናል:: ትብብር አለን:: በመተራረም፣ በመተሳሰብ፣ በፍቅር ነበር የምንሰራው:: በቂ ዝግጅት እናደርግ ነበር :: ድራማዎች፣ ቃለ ምልልሶች፣ መጣጥፎች የመሳሰሉት ቀድመው ይዘጋጃሉ::ፕሮግራሙን ስናቀርብ ግን ቀጥታ ከስቱዱዮ ነው:: /live/ የምናስተላለፋት አንዲቷ ነገር በጽሑፍ ሳትቀርብ አታልፍም:: አንድ ኮፒ ለቴክኒሺያን፣ አንድ ኮፒ ለፕሮግራም መሪው፣ አንድ ኮፒ ለአንባቢው ይሰጣል:: ስናነብ ከጽሑፉ ዝንፍ ማለት የለም:: «እንደምናደራችሁ» ሳይቀር ይጻፋል:: ከተጻፈው ውጪ ቀጥታ የምናስተላልፈው ከአድማጮች ጋር ባለን የስልክ ግንኙነት መልስ ስንሰጥ ብቻ ነው:: ያም ከፍተኛ ጥንቃቄና ቁጥጥር አለው:: ሁሉም ነገር ግን ጆሮ ገብ ሆኖ ነው የሚዘጋጀው:: ማን ምን ቢያዘጋጅ ወይንም ቢያነብ የተሻለ ነው ተብሎ ድምጹ ይመረጣል:: በዚህ ሁኔታ እሁድ ሰርተን ሰኞ እናርፋለን:: ከማክሰኞ ጀምሮ ለቀጣዩ እሁድ ተፍ ተፍ ማለት ነው:: ቴክኖሎጂውም እንደዛሬ ስራን ያቀለለ አልነበረም:: ኮምፒውተር የለም:: ድምጽ መቅረጫው ክብደቱ አይጣል ነው:: ኡኸር እና ናግራን አንግቦ መሮጥ ነው:: አንዱን ቃል ከአንዱ ለማገናኘት ምላጭ ይዞ ሪል ክሩን መቁረጥ መለጠፍ ነው:: ግን ዛሬ ሳስበው አሰራሩ ቢያደክምም ደስ ይል ነበር:: የህሊና እርካታ ነበረው::

ታዛ፦ በእርግጥ ከስቱዲዮ ቀጥታ /live/ ማስተላለፍ ከባድ ነው:: በተለይ ዘመኑ ሲታሰብ ለቅጣት የሚዳርግ ስህተት ነገር ሾልኮ ሊወጣ ይችላል ብዬ እገምታለሁ…፤

አባይነሽ፦ በጣም! አለ እንጂ:: አንድ ጊዜ ለሰባት ዓመታት ከፈሳሽ በስተቀር እህል ያልበላ ልጅ ቃለ መጠይቅ አድርገን ጠዋት ለቀቅነው:: በዚህ ጊዜ ሀኪሞች ተደናግጠው ከወዲያም ከወዲህ ደወሉልን:: «ይህን ነገር መከታተል እንፈልጋለን» እያሉ:: ከሰዓት በኋላ አንድ ዶክተርን በጉዳዩ ቀጥታ ቃለ መጠይቅ አደረግንላቸው:: ሳይቀረጽ ቀጥታ በአየር ላይ አዋልነው:: ወቅታዊና ማህበረሰቡም ሊያውቀውና ሊማርበት የሚያጓጓ ስለነበረ ኃላፊነቱን ወስደን ሰራነው:: ሳይቀረጽ መተላለፉ ተገቢ ባይሆንም አጋጣሚው ግን ለቅጣት አልዳረገንም:: ከአድማጮች ይልቅ እኛ አብልጠን የምንረዳቸው ሌሎች ስህተቶች ግን ብዙ ጊዜ ይገጥሙናል:: እየተማርንባቸው ዳግመኛ እንዳንደግማቸው በፕሮግራም ግምገማ ላይ እንማማርባቸዋለን:: አለቆቻችንም ይረዱናል:: አሳልፈው አይሰጡንም:: ትልቁ ነገር ይህ ነው:: ሙያውን ወድጄ እንድዘልቅ ያደረገኝ::

 ታዛ፦ ግን እስኪ እንዴት ስሜትሽ ወደ ጋዜጠኝነቱ ተሳበ?

አባይነሽ፦ ልጅ እያለሁ ባለፍኩባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ የማንበብ ፍላጎት ነበረኝ፤ ያ ፍላጎቴን በክፍል ውስጥ እወጣ ነበር:: ቢሾፍቱ አጼ ልብነድንግል እና ተናኜ ወርቅ ትምህርት ቤቶች ስማር መምህራኖቼም እንዳነብ ያበረታቱኝ ነበር:: በቄስ ትምህርት ቤት ዳዊት መድገሙ፣ ወንጌል ማንበቡም ነበር:: በዚህ በዚህ ለስነ ጽሑፉ በተለይም ለንባብ የተመቸሁ ሆንኩ:: መጻፉንም እየተለማመድኩ መጣሁ:: በሂደት ወደ ጋዜጠኝነቱ ዘው አልኳ:: በቃ::

 ታዛ፦ እንዴት? መቼ?

 አባይነሽ፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማርኩ አብዮቱ መጣ:: የተረጋጋ የትምህርት ጊዜ አልነበረም ሦስተኛ ዓመት የተማሪዎች ብሔራዊ አገልግሎት ላይ እያለሁ እድገት በህብረት ዘመቻ ሄድኩ::  ከዚያ መልስ ቤት እንደተቀመጥኩ፤ ስሜቴን የሚያውቁ ወዳጆቼ «አንቺኮ ጥሩ አንባቢ ነሽ፤ ለምን ሬዲዮ ጣቢያ አትቀጠሪም?» አሉኝ:: አላቅማማሁም ወዲያው ሄድኩ:: አንድ እዚያ የሚሰራ የማውቀውን ሰው አማከርኩ:: ያ ሰው አቶ ታደሰ ዘንድ ወሰደኝ:: እሱ ደግሞ ወደ በላይ አለቃው አቶ ከፋለ ማሞ አደረሰኝ:: ከፋለ ለታደሰ «ፈትናት» አለው:: ተፈተንኩ:: አለፍኩ:: አቶ ታደሰ ድምጼን በጣም ወደደው ፡ ግን መገራት አለበት ብሎ የመለማመጃ ጊዜ ሰጠኝ:: ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ለዜናና ለፕሮግራም ስራ እየወጣሁ እሰራ ጀመር:: ወዲያው አየር ላይ መውጣት የለም:: የሬዲዮ መጽሔትን ያዘጋጅ ከነበረው ፀጋዬ ኃይሉ ከሚባል ጎበዝ ጋዜጠኛ ጋር ብዙ ሰርቻለሁ:: ዛሬ በሕይወት የለም፤ ወዲያው ነው የሞተው:: ግን ብዙ ያስተማረኝ ባለውለታዬ ነበር:: ከሬዲዮ ማሽኖች ጋር ያስተዋወቀኝ፤ ከስቱዲዮ ህግና አነባበብ፣ እንዲሁም አዘጋገብ ያስተማረኝ ነበር::ከዚያ እነ አለምሰገድ ህሩይ፣ ወርቁ ተገኝ፣ አሰገደች ይበርታ፣ ታደሰ ሙሉነህ እና ሌሎች አንጋፋ ጋዜጠኞች እዚያው ሬዲዮ ጣቢያ ባለው ጀርመን ሬዲዮ ስቱዲዮ የ3 ወር ስልጠና ሰጡ:: እኔም ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ስልጠናውን ወስጄ ስመረቅ፤ አየር ላይ መውጣት ጀመርኩ:: እናም በ1970 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በፍሪላንሰር ተቀጠርኩ:: በ 420 ብር ደመወዝ:: ስራዬን እየሰራሁ ትምህርቴንም በተጓዳኝ ቀጥዬ ኤጁኬሼን ፋኩልቲ ጨረስኩ:: በባችለር ዲግሪዬን እንደያዝኩ ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ቋሚ ቅጥር እንዲሰጠን ጠየቅን:: ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ቋሚ ሆንኩ ማለት ነው:: በ500 ብር::

ታዛ፦ ከዚያስ?

አባይነሽ፦ ከዚያማ ያው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር የኢትዮጵያ ሬዲዮ አማሪኛ ክፍል ተቀጥሬ አቡነዼጥሮስ ቤቴ ሆነ:: መጀመሪያ ፕሮግራም ክፍል ገባሁ፣ የተለያዩ ፕሮግራሞችን መስራት፣ ሙዚቃዎችን ማቀናበር፣ ማስታወቂያዎችንና ዜናዎችን በየቦታቸው ማደላደልና ሰዓታቸውን ጠብቀው እንዲተላለፉ ማድረግ፣ ሪፖርት ማቀናበር፣ ሐተታ ማንበብ ወዘተ ነበር ስራዬ:: «ከአድማስ ባሻገር» እና «በራስ መተማመን» የተሰኙ ደረቅና ጠንካራ ፕሮግራሞችንም እሰራ ነበር:: ያም ሆኖ በተቻለ መጠን ጆሮ ገብ እንዲሆን የማዋዛት ስራ እሰራ ነበር:: ያው በወቅቱ ከነበረው አገራዊ ሁኔታና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አኳያ የምጠነቀቀው ነገር ነበር:: ያኔ ወንዶች ብቻ ነበር ሐተታ የሚያነቡትና «እኛ ሴቶችስ ለምን አናነብም?» የሚል አብዬት አስነስተን በጉልበታችን ማንበብ እንድንችል ማድረጋችን ይታወሰኛል:: እንግሊዝኛው ላይ ታቦቱ፣ እሌኒ መኩሪያ፣ ማርታ አማረ፣ አማርኛው ላይ አሰገደች ይበርታ፣ አሰለፈች ጌታቸው፣ ሚሊዮን ተረፈን የመሳሰሉ ጎበዝ ጎበዝ ሴት ጋዜጠኞች ነበሩ:: ፈተና ቢኖረውም መልካም ጊዜ ነበር:: ከዚያም በኋላ በጣም ጠንካራ ከሆኑ እንደ ሰሎሜ ደስታና ፀሐይ ተፈረደኝ ካሉ ሴቶች ጋዜጠኞች ጋ ሰርቻለሁ::

ታዛ፦ የእሁድን ፕሮግራም ሲመሰረት የፕሮግራሙ ይዘትና አቀራረብን በመቅረጽ ሚና እንደነበረሽ ይታወቃል፤ ለዚህ እንዴት ተመረጥሽ ግን?

 አባይነሽ፦ ቀደም ብዬ እንዳልኩህ ደረቅ ፕሮግራሞችን እያዋዛሁ ቀለል በማድረግ ጆሮ እንዲይዝልኝ የማድረግ ጥረቴ ነው ያስመረጠኝ:: ያኔ ፕሮግራሙን ለመጀመር ሲታሰብ አቶ ገዳሙ እና ታደሰ በወቅቱ ወዳጅ አገር የነበረችው ቼኮስላቫኪያ ለልምድ ልውውጥ ሄደው ተመልሰዋል:: እኔ ከቡድኑ ጋር ስቀላቀል ታደሰ የሚያመጣው ሃሳብ ከባድና ህልም ይመስል ነበር:: «እንዴት ይሆናል?» እንላለን:: እሱ ግን «ይሆናል እንሰራዋለን!» የሚል ሙሉ መተማመን ነበረው:: እሁድ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ሙዚቃ እና ለሙዚቀኞቹ የሚደረግ ቃለ መጠይቅ ነበር አዝናኝ ፕሮግራም የሚባለው:: ሌላ ከሙዚቃው በተጓዳኝ የሚሄድ አዝናኝና አስተማሪ ነገር አልነበረውም:: ያንንም የሚሰራው ታደሰ ሙሉነህ ነበር:: ቅዳሜ ቅዳሜ ይቀርብ እንደነበር አስታውሳለሁ:: ከዚያ ለየት ያለ አዝናኝ ፕሮግራም ነው ለመስራት የተፈለገው:: ይህ እሁድ ፕሮግራም እንዲጀመር ሃሳቡን ያመነጨው ደግሞ ራሱ ታደሰ ሙሉነህ ነው:: እንዳልኩህ ውጪ የጋዜጠኝነትን ትምህርት ስለተማረ ምን መሰራት እንደሚቻል፣ በምን መልክ መስራት እንደሚገባ፣ ማን ማን ሊሰራው እንደሚችል በደንብ አጥንቶ ነው ያስጀመረው:: እንደጀመርነው ተወደደ::

ታዛ፦ እንዴት ነበር አሰራራችሁ? ለመወደድ ያበቃችሁ?

አባይነሽ፦ አንድ ዝግጅት ከአስር ደቂቃ በላይ እንዲሄድ አይፈለግም ነበር:: ቁም ነገር ቢሆንም ሰዎች የተሰላቸና የተንዛዛ ነገር መስማት አይፈልጉም:: አጠር መጠን ተደርጎ በጣፈጠ ሁኔታ ሲቀርብለት ነው የሚወደው:: ከአንድ ሰዓት ቃለ መጠይቅ ውስጥ አስር ደቂቃ ቁም ነገር ይዞ መቅረብ ምን ያህል ድካምና ትጋት እንደሚጠይቅ ይታይህ:: ለዚያውም በዚያ ዘመን ቴክኖሎጂ:: ምንም የተቆረጠ ሳይመስል ፍሬዋን ጠብ! ነበር የምናደርገው:: ስራችን አድማጭ ልቦና ውስጥ የሚቀረው ለዚያ ነው:: ለኤዲቲንግ የእኔ ጣት ቀጭን ስለነበረች ትመች ነበር:: ከሪል ክር ላይ አንዲትን ፊደል እንቆርጥ ነበር:: ራስን መስዋት ማድረግ ማለት አንዱ እዚያ ላይ በሚጠፋው ጊዜ ነው:: እንደሌሎቹ ባልደረቦቼ ሁሉ ፤ ልጆቼን ትቼ፣ ቤቴን ትቼ ነው ያንን የማደርገው:: ቅዳሜ ምሳዬን በልቼ አላውቅም:: በማግስቱ ድግስ አለና:: እኛ ብቻ ሳንሆን ጸሐፊዎችም፣ ቴክኒሺያኖችም ተራ ይዘው ይገባሉ:: አንዳንዴ የቴክኒሻኑን ቦታ የሚሸፍንልን ነፍሱን ይማረውና ታምራት አሰፋ ነበር:: ቴክኒሻኖቻችቸን ስለሚደክማቸው ስለሚሰለቻቸው እሱ በፍላጎቱ ያግዛቸዋል:: ታምራት የሙዚቃ ሰው፣ የፕሮግራም ሰው፣ የቃለመጠይቅ ሰው፣ ብስል ያለ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ነበር:: ቀላልና ተግባቢ ነው፣ ይታዘዛል፣ መፍትሄ ፈላጊና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር በኩል ንቁ ነው:: በእንዲህ ያለ ተወዳጅ ፕሮግራም ብዙ ከሚያውቁ ጋር መስራቴ ለቀጣይ ህይወቴ ጠቅሞኛል:: ታደሰ ሙሉነህ፣ እኔ፣ ታምራት አሰፋ፣ ንጉሴ አክሊሉ፣ አዲሱ አበበ ነበርን እሁድ ጠዋት ፕሮግራምን የጀመርነው:: እየተወደደ ሲመጣ የአየር ሰዓቱ ሰፍቶ እሁድ ከሰዓት በኋላም ፕሮግራሙ ቀጠለ:: ድራማዎችም መተላለፍ ጀመሩ:: ጥሩ የስራ ዘመን ነበር ብቻ::

ታዛ፦ በደርግ ዘመን የሳንሱር ጉዳይ እንዴት ነበር?

አባይነሽ፦ አለ:: ግን ሁሉም ጋዜጠኛ አልፎ ወደ ሌላው እንዳይሄድ ራሱን ራሱ ሳንሱር ያደርግ ነበር:: ከኤዲቶሪያል ፖሊሲ ውጪ የሆኑ ነገሮችን ቆርጠን እናወጣለን:: በአንዲት ቃል ግድፈት አዘጋጁም፣ ኃላፊውም፣ ጣቢዋውም አንድ ላይ ተያይዘን ነው የምንጠየቀው:: ስለዚህ ሁሉም በየደረጃው አይቶ ነው የሚያልፈው:: አዘጋጁ፣ ኤዲተሩ፣ ከዚያም ከከበደ የፕሮግራም ክፍል ኃላፊው እያለ እስከ ዋና ስራ አስኪያጁ የሚያደርስ የፕሮግራም ፈቃድ ሊኖር ይችላል::

ታዛ፦ ለእሁድ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር የቀደሙ ባልደረቦችሽ ነግረውኛል፤ እስቲ እንዴት ነበር ያ ሁኔታ?

አባይነሽ፦ የሚገርመው ለፕሮግራማችን በተሰጠው ትኩረት የራሳችን ስቱዲዮ ተሰጥቶን ነበር:: ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር የስቱዲዮ ተራ ይዘን ጊዚያችንን ከምናባክን ተብሎ ነው ጀርመን ሰቱዲዮ የነበረውን የተሰጠን:: የራሳችን የግል የድምፅ ላይብረሪም ነበረን:: ከጅምሩ አንስተን ፕሮግራሞቻችንን በአግባቡ አደራጅተን የምናስቀምጥበት:: የድምጽ ላይብረሪያችን ውስጥ የሚቀመጠውን ፕሮግራም ለሌላ አሳልፎ መስጠት የለም:: ሪል ክር ነው፤ ለማስቀመጥ ቦታ ይፈጃል:: ስሱ የሚለጠጠውና በሙቀት ሊበላሽ የሚችለው እስከ አንድ ሰዓት የተቀረጸ ድምጽ ሲኖረው፤ ወፍራሙ ክር ብዙ ዘመናት የሚቆየው ደግሞ 30 ደቂቃ ነው የሚይዘው:: ከነ ጥራቱ በርካታ ዓመታት ሊቆይ ይችላል:: ብዙ ታሪኮች፣ የተለያዩ ታዋቂያን ድምጻች፣ በእነዚህ ክሮች በአርካይቭ ተቀምጠው ነበር::አንዳንዴ ፕሮግራማችንን ስንሰራ፣ ዓመታችንን ስናከብር እንደ አስፈላጊነቱ መለስ ብለን እነዚያን ድምጾች እንጠቀምባቸው ነበር:: አንግዲህ ያ ዶክመንት ዛሬ ይቀመጥ አይቀመጥ፣ ይኑር አይኑር ምንም የማውቀው ነገር የለም::

ታዛ፦ አንቺ በግልሽ ከሰራሻቸው ፕሮግራሞች ውስጥ ለማስታወሻነት ያስቀመጥሽው የለም?

አባይነሽ፦ በፍፁም የለም! አንድም ፕሮግራም ይዤ አልወጣሁም:: አዝናለሁ ያንን ባለማድረጌ::

ታዛ፦ በዚያ ዘመን ፕሮግራሙ በሬዲዮ ሲተላለፍ በቴፕ ክር ከማንኛውም ቤት መቅዳት ይቻል ነበር እኮ፤

አባይነሽ፦ ነበር:: ግን ያኔ አላሰብኩትም:: ለራሳችን አልነበረማ የምንሰራው:: ለራስ የሚባል ስሜት ያኔ የለም:: ሰራን፤ ወጣን:: በቃ:: ዛሬ ቢኖርም በልመናም የማገኝ አይመስለኝም::

ታዛ፦ ባስተላለፍሽው ፕሮግራም ለቅጣት ወይ ለግሳጼ የተዳረግሽበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?

አባይበሽ፦ ቀደም ባለው መንግስት እየተጠነቀቅንም እየፈራንም ስለምንሰራ ብዙም አልተጋለጥንም:: አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶችና ቁጣ ግን አይጠፋም ነበር:: 1980 ዎቹ አጋማሽ ላይ የመጻፍና የማንበብ ነጻነት ለቀቅ ተደርጎ ነበር:: በዚያን ወቅት መጽሔቶች ወሲብ ነክ ጉዳዮችን ይዘው መውጣት ጀመሩ:: ነገሩ ወጣቶችን የሚያበላሽ፣ ማህበረሰቡን የሚበክል ነበርና ሰዉ መጮህ ጀመረ:: እኛም ዝም ማለትን አልፈለግንም፤ ያንን ጉዳይ ተችቶ በብዕር ስም የሚጻፍልንን ማስተላለፍ ጀመርን:: ያኔ ተከሰስን:: ጣቢያው ተከሰሰ:: «እኛ የፕሬስ ነጻነት ስንሰጥ እናንተ እንቅፋት ሆናችሁ» ማለት መጣ:: «አውጡ ማነው የጻፈው?» ብሎ አለቃችን ጠየቀን:: «አናወጣም!» አልን:: ደንበኛችንን አሳልፈን መስጠት አልፈለግንም:: የሚዲያ ህጉም እንደዚያ ለማለት ያግዘናል:: አንገደድም:: « ካስፈለገ ፍርድ ቤት ቀርበን እንመልሳለን» ብለን በአቋም ጸናን:: በእንዲህ ሁኔታ እያለን ፍርድ ቤት ሳንቀርብ እናቶች ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ:: መጽሔቶቹም ታገዱ:: እና አንዳንድ ጊዜ ነጻነታችንን በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን በጣም ችግር ነው:: ሚዲያ የማህበረሰቡን እሴት የመጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነት አለበት:: ያ ክስተት ጥሩ አልነበረም:: የሚዲያ ነጻነት በእንዲያ መልኩ መገለጥ አለበት የሚል እምነት የለኝም:: ጋዜጠኛ በሙያዊ ተግባሩ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን አሴት መጠበቅ አለበት ብዬ አምናለሁ ያ እንደዜጋም ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው:: በህብረተሰቡ ጉዳት የሚያደርስን ነገር ማጋለጥ ደግሞ የሚዲያውም ሆነ የጋዜጠኛው ኃላፊነት ነው:: የሆነ ሆኖ በዚያ ጉዳይ ሳንከሰስ ቀረን እልሃለሁ::

ታዛ፦ በሙያሽ የተመሰገንሽበት ወይ የተሸለምሽበት ሁኔታ ካለ፤

አባይነሽ፦ የሚገርምህ ሬዲዮ ላይ ስትሰራ ትታወቅ ወይም ትመሰገን ይሆናል:: ከዚያ ስትወጣ ግን የሚያስታውስህ የለም:: በአንድ ወቅት አየር ላይ ትገኝ ይሆናል፤ ያ ሲቆም ያንተም መታወስ ይቆማል ማለት ነው:: ምናልባት እኛ በሰራነው ስራ ይሆናል ከህዝብ ልበ ያልወጣነው:: ብዙዎች ምርጥ ምርጥ የሬዲዮ ጋዜጠኞችን ዛሬ የሚያስታውሳቸው የለም:: እንዲያውም ፕሪንት ሚዲያ ላይ የሰሩ ይታወሳሉ መሰለኝ:: ስራቸው ሁሌም ስለሚታይ:: ግን ሬዲዮ ላይ ለመታወስ አወጣጥም ይወስነዋል::

ታዛ፦ ላቋርጥሽና እንዴት ነው ሬዲዮን ልትለቂ የቻልሽው?

 አባይነሽ፦ ምክንያት ነበረኝ:: ልወጣ ስል የአማርኛ ፕሮግራም ኃላፊ ነበርኩ:: የቁጥጥር ኃላፊነቱ ከባድ ነው:: እያንዳንዱ ፕሮግራም በትክከል መተላለፉን ማረጋገጥ አለ:: በየሳምንቱ የሪቪው ስብሰባ ላይ መቀመጥ አለ:: እዚያ ላይ ጥሩ ቢሰራ እንኳ በተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ የሰላ ሂስ የምትሰጥ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል:: ግምገማው ያስፈልጋል፤ መተራረሚያ፣ ማደጊያም ነው:: በእውነታ ላይ ተመስርቶ በተጨባጭ ሲገመገም በቀጣይ ለሚሰሩ ፕሮግራሞች ማማር አቅም ይሆናል:: በዚያ አምናለሁ:: በአንጻሩ ጥሩ ያልሰራ እንዲማርበት ሲነገረው፤ ጣቢያውን የሚያስገምት ነገር እንዳይሰራ ሲነገረው ያለመቀበል አለ:: ጥሩ ሰራሁ የሚለው መበረታታት ሲገበው የሞራል መጎዳት ሲገጥመው በእርግጥም ያሳዝናል:: ኃላፊነቱ ፈታኝ ነው :: ጊዜ ይወስዳል:: በዓል የለም፣ እረፍት የለም:: በዚያ ላይ በራሴ ትራንስፖርት ቅዳሜና እሁድ እየገባሁ ሁሉም በአግባቡ መከወኑን ማየቱ አሰልቺና አታካች ነበር የሆነብኝ:: ሙያውን እየወደድኩት ሰርቶ ማሰራትን እየፈለኩ፤ ኃላፊነቱን ተከትሎ የመጣው ጫና አስጠላኝ:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ፤ አንድ ቀን አለቃዬ የክፍል ኃላፊዎቹን ቢሮው ጠርቶን «ዘነበወርቅ ያለው ዓለም አቀፍ አገልግሎት ሬዲዮ ልንሄድ ነውና ቢሮ ድልድሉ ላይ ተሳተፉ አለን:: «ምን!» አልኩት:: ደነገጥኩ:: የምሆነው አጣሁ::

ታዛ፦ ከዚያስ ?

አባይነሽ፦ ከዚያ እኔም የንዴቴን ተናገርኩ:: «ቀድመን ሳንመካከር፣ በቂ ትራንስፖርት ባልተዘጋጀበት ሁኔታ፣ ባልተስተካከለ መንገድ እንዴት ይሆናል? እንዴት ነው የሚሰራው?…ይህ ጣቢያ እኮ በአብዛኛው በፈቃደኛ ህጻናት፣ ወጣቶችና ተባባሪዎች ነው የሚንቀሳቀሰው፤ እንዴት ይሆናል:: እነሱን ምንድነው የምናደርጋቸው?» ብዬ ጠየኩ:: እሱ ግን ተቆጣ:: በእርግጥ እሱም የታዘዘውን ነው ያለው:: እኔ ግን አልቻልኩም:: «አያገባሽም! አንቺ የታዘዝሽውን ብቻ ነው መስራት ያለብሽ! ቢሮ ትደለድላላችሁ፤ ትደለድላላችሁ በቃ:: እዚህ ላይ ጥያቄ የለም» አለኝ በሀይለቃል:: በቃ ከዚህ በኋላ መነጋገር አላስፈለገኝም:: አዘንኩ:: ቢሮዬ ገባሁና የቅርብ ጓደኞቼን ጠራኋቸው:: «እስከዛሬ ድረስ ከዚህ ከአቡነ ዼጥሮስ ስቱዲዮ ሌላ ሙሉ ጊዜዪን በስራ ተጠምጄ የምኖርበት ቤት የለኝም ነበር:: ከዛሬ ጀምሮ ግን ለባሌ ሚስት እሆናለሁ:: እስከዛሬ ድረስ ለባሌ ሚስት ሆኜ አላውቅም:: ለልጆቼ እናት ሳልሆን ቆይቻለሁ:: ዛሬ ግን በቃኝ:: እናንተ ደግሞ የምትችሉ ከሆነ ቀጥሉ:: ከዛሬ ጀምሮ ለቅቂያለሁ» አልኩና መልቀቂያዬን ጻፍኩ:: «እንዴት ይሆናል?» ብለው ባልደረቦቼ ተንጫጩ:: እኔ ግን ቆርጫለሁ:: ውስጣዊ ህመሜን የማውቀው እኔ ነኛ! ወረቀቴን ያዙት፤ በዚህ ውስጥ እያለሁ የዛኑ ዕለት ጋዜጣ ገልበጥ ገልበጥ ሳደርግ አኮርድ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለአድቮኬሲ ኦፊሰርነት የስራ ማስታወቂያ አየሁ:: ወዲያው ሲቪዬን አያይዤ የቅጠሩኝ ጥያቄዬን መስሪያቤታችን አካባቢ ባለው አራዳ ፖስታ ቤት በኩል ላኩት:: በአራተኛው ቀን ጠሩኝ:: በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ቅጥሩን ጨርሼ ላልመለስ ከአቡነ ዼጥሮስ ሹልክ ብዬ ወጣሁ:: በቃ:: እግዚአብሔር የልቤን ፈቃድ ነው የሞላልኝ::

ታዛ፦ በቃ፤ በቃ? በፈቃዴ ለቅቂያለሁ ብለሽ ነው፤ ግን ምክንያትሽን ገልጸሽ ነበር?

አባይነሽ፦ አልገለጽኩም:: በወቅቱ መግለጽ አልችልም ነበር:: ውስጤ ከነበረው አለመመቸት ጋር በዋናነት ለመልቀቄ ምክንያት የሆነኝ ግን ያ ነው:: በዚያ አግባብ ከአቡነ ዼጥሮስ መልቀቅ የለብንም ነው የእኔ ምክንያት:: ስንትና ስንት ታሪካዊ ቅርሶች የያዘ ነው ሬዲዮ ጣቢያው:: ያለ ምክክር፣ ቅድመ ጥንቃቄ፣ ያለ ሲስተም ዝም ብሎ እንዴት ይደረጋል? … :: ብቻ ቀንቶኝ በጥሩ ደመወዝ ሌላ መስሪያቤት ተቀጠርኩ:: በደርግ ዘመን ማንም ቢሆን ደመወዙ 710 ብር ከደረሰ በኋላ የፈለገ ኃላፊ ቢሆን ጭማሪ የለውም:: እኔ ደርሼ ነበር ኢህአዴግ ሲመጣ እርከን ጭማሪ ሲለቀቅ 835 ብር:: እዚያ ደርሼ ነው በ1989 አጋማሽ ላይ የለቀቅኩት:: ታዛ፦ ኋላ ላይ እሁድ ፕሮግራም ተዳከመ ልበል?

አባይነሽ፦ አዎ:: ከዚያ ቀደም ብሎ ነው የተዳከመው:: ምን ሆነ መሰለህ… በጨለማ ውስጥ ሰማይ ላይ የምታበራ ኮከብ ዙሪያ ሌሎች ኮኮቦች ሲመጡ የመጀመሪያዋ ኮኮብ ብርሃን እየቀነሰ ይመጣ የለ? አዎ… እሁድ ፕሮግራምም መንገዱን ካሳየ በኋላ ያ ነገር ነው የገጠመው:: የትምህርት መገናኛ ብዙሃን ሬዲዮ (ለገዳዲ) በይዘትም ሆነ አቀራረቡ ልክ የእኛን የመሰለ ፎርማት ይዞ ብቅ አለ:: በፕሮግራም፣ በሙዚቃው በኩል ደፋር ሆነ:: በዚያ የአብዮት ወቅት አዳዲስ የፍቅር ዘፈን ሲለቀቅ ተወዳዳሪያችን መሆኑ ገባን:: አድማጮቻችን ተከፋፈሉ:: ያም ሆኖ የእሁድ ፕሮግራም አድማጮችና ተሳታፊዎች ከእለት እለት መጨመራቸው አልቀረም:: ጥሩ ተፎካካሪዎችና አማራጭ ሚዲያ ግን ሆኑ::

ታዛ፦ « እሁድ ን ለአንድ አፍታ» እና «ቅዳሜን ከእኛ ጋራ» ብለው መጡ፤

አባይነሽ፦ እህ! እንደዚያ ነው:: ግን የእነሱ ማሰራጫ አቅም የተወሰነ ስለነበረ በመላው አገሪቱ አይደርሱም፤ ያ ልዩነታችንን አስፍቷል:: በአጭርና መካከለኛ ሞገድ ነበር እኛ የምንደመጠው:: በጥራትም ባይሆን እስከ ውጪ አገር እንሰማለን:: በዚያን ዘመን ለገዳዲ ላይ ይሰሩ የነበሩት እነ አቶ አስረስ፣ ድልነሳው፣ ገበየሁ ደምሴ፣ ከድጃ የስድ የመሳሰሉ በሳልና ታታሪ ጋዜጠኞች አይረሱም:: ወደኛ ልመልስህና ከዚያ ምን ሆነ መሰለህ:: መቼም ቅልጥ ያለ የጦርነት ቀስቀሽ ሙዚቃ አምጥተህ እሁድ ፕሮግራም ላይ ላስኬደው ብትል አይሆንም፤ ከአድማጮች ጋር መቀያየም ነው:: በኋላ ላይ ግን ይህ መምጣቱ አልቀረም:: በጣም ጠንካራ የሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች በእሁድ ፕሮግራም ላይ ይሂዱ እየተባለ በትዕዛዝ መምጣት ጀመሩ:: በዚህ ጊዜ ፕሮግራማችን ወዙን እያጣ መጣ:: «እምቢ» ስንል ደግሞ ችግር ይመጣል:: በዚህ በዚህ ምክንያቶች እንደ አነሳሱ የ እሁድ ፕሮግራም ተወዶ ሊቀጥል አልቻለም:: የፕሮግራሙ አስኳል የሆኑ ጋዜጠኞችም ሲለቁ፣ ሲቀያየሩ የቀድሞ ተደማጭነቱን እያጣ መጣ::

ታዛ፦ የእሁድ ፕሮግራም አይነት አሰራር ተመልሶ ሊመጣ ይችላል ብለሽ ታስቢያለሽ?

አባይነሽ፦ በፍጹም! አይመጣም:: የእሁድ ፕሮግራም ታሪክና ትዝታን አስቀምጦ አልፏል:: አይመለስም:: የአንድ ዘመን ታሪክ ነው:: እንዲመለስ ጊዜውም፣ ቴክኖሎጂውም፣ ሁኔታዎችም አይፈቅዱም:: መሰራት በሚገባው ጊዜ ተሰርቷል:: የዚያ ስራ አንዱ አካል በመሆኔ ግን ሁሌም ተደሳች ነኝ:: ዛሬም አንዳንዶች በድምጼና በስራዬ ሲያስታውሱኝ ደስ ይለኛል::

ታዛ፦ ቅድም የሽልማት ጉዳይ አንስቼልሽ ነበር፤

አባይነሽ፦ አዎ ወደሱ ልምጣልህ:: የሚገርምህ ሬዲዮ እንኳንስ ሽልማትና ምስጋና ሊሰጠኝ «ደህና ሁኚ» እንኳን አልተባልኩም:: በዚያ አዝን ነበር:: ከብዙ ዓመታት በኋላ በፈረንጆች 2010 ሴቶች ማድረግ ይችላሉ የሚባል አገር በቀል ድርጅት «ጣዝሙት» የሚባል ለታታሪ ሴቶች የሚሰጥ አዋርድ ሰጥቶኛል:: ከዚህ ሌላ በጤና ጉዳዮች ላይ በሰራኋቸው ሥራዎች የተነሳ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰርቲፊኬትና በውጭ ሀገር የተለያዩ አለም አቀፍ ስብሰባዎችን የመካፈል ዕድል አግኝቼ አውቃለሁ::

ታዛ፦ የዛሬውን የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ተግባር ከእናንተ ዘመን አሰራር ጋር እንዴት ታነጻጽሪዋለሽ? ምን ጥሩ፤ ምን መጽፎ ነገር ይታይሻል?

 አባይበሽ፦ ጥሩ እድል፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ነው:: ብዙ ድካም የለውም:: የስቱዲዮው፣ የድምጽ መቅረጫው ስራ ሁሉ ዲጂታል ነው:: ሁሉም ነገር የሚያልቀው በኮምፒውተር ነው:: እንደኛ ዘመን ግዙፍ ድምጽ መቅረጫ ይዞ መንቀሳቀስ የለም:: ሞባይል የምታክል ድምጽ መቅረጫ ለስቱዲዮ ትመጥናለች:: ድምጽ ኤዲት ለማድረግ ክሮችን በምላጭ እየቆረጡ በመቀጠል የሚባክን ጊዜ የለም:: የተቀረጹ ድምጾችን ማስቀመጫ መጋዘን አያስፈልግም:: ኮምፒውተር አለ:: ሙዚቃ ችግር የለም:: ብዙ ቴክኖሎጂ ያመጣው ነገር ጋዜጠኛውን አግዞታል:: በዚያው ልክ ደግሞ የጋዜጠኝነት አሰራር ጥራት፣ ጥልቀት፣ ውበት እየቀነሰ የመጣ ይመስለኛል:: እንደ አማራጭ ሚዲያዎች መብዛት ሁሉ የለብለብ ስራ በዝቷል:: ስንፍናው አለ:: ሳያነቡ፣ በጉዳዩ ላይ ሳይዘጋጁ አየር ላይ መውጣት አለ:: ይህ ድፍረት ነው:: እኔ እንደታዘብኩት ዋና ነጥብ የሚባለውን ነገር እንኳን በማስታወሻ ሳይጽፍ በስልክ ከአድማጮች ጋር የሚሆነውንም የማይሆነውንም አውርቶ ፕሮግራሙን በሙዚቃ እያጨናነቁ የሚዘጉ ብዙ ናቸው:: ይህ የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ ምግባር አይደለም:: ሳይንሳዊ ትምህርቱም እንዲህ አይልም:: ቅድም እንዳልኩህ በእኛ አሰራር እያንዳንዷ ነገር ተጽፋ ነው አድማጭ ዘንድ የምትደርሰው:: እንደሱ ይስሩ ማለቴ አይደለም:: ግን ቢያንስ የሚሰራው ፕሮግራም ፈር የያዘ ነገር ቢኖረው ጥሩ ነው:: ሊያወያይ የሚችል፣ የህብረተሰቡን ትኩረት ሊስብ ይችላል ተብሎ የታመነበት አጀንዳ ቢመረጥ መልካም ነው:: እውቀትና አቅም ሳይኖር ድፍረት በብዙ አለ:: ለምሳሌ ከልክ በላይ የሆነ ሳቅ፣ መጯጯህ፣ አንዳንዴ መደበቂያ እስከማጣ የማፍርበት ሁኔታ አለ:: ለአድማጮች ክብር አለመስጠት ነው ይሄ:: አንዳንዴ ሬዲዮ ባልሰማ የምልበት ጊዜ አለ:: ያሳዝናል:: እንግዲህ ይህ የሚሆነው ጣቢያዎቹና ኃላፊዎቹ አምነውበት ነው:: እውነቱን እንዲያውቁት ግን በሂደት አድማጮቻቸውን ያጣሉ:: ከጋዜጠኛው የተሻለ እውቀት ያላቸው ብዙ አዋቂዎች እንዳሉ ማሰብ ይገባል:: አድማጭ ለጆሮው ካልተመቸው ሬዲዮኑን የማጥፋት መብት አለው:: ያ እንዳይመጣ ፕሮፌሽኑ እንዴት መገራት አለበት የሚለው ላይ መምከር ይገባል:: ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶች የቀደመ ኃላፊነት አለባቸው::

ታዛ፦ እዚህ ላይ በቅርቡ የዓለም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ቀንን በማስመልከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የውይይት መርሃግብር ገዳሙ አብርሃ የተባሉ አለቃሽ ሙያውን በተመለከተ አጽንኦት ሰጥተው የሚናገሩትን ጠቅሰሽ ነበር፤ እስኪ…?

አባይነሽ፦ አዎ…አዎ! «ከማይክራፎኑ ጀርባ ስትቀመጡ ከፊታችሁ እናንተን የሚያደምጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጆሮዎች አሉ:: እነዚያ ጆሮዎች ያሏቸው ሰዎች ከእናንተ በጣም የላቁ፣ በኑሮ ብዙ ነገሮችን ያለፉ፣ የታወቁ፣ በጣም የተማሩ ናቸው:: እናንተ ማለት በእነሱ ዘንድ ኢምንት ናችሁ:: ስለዚህ እንደፈለጋችሁ ልትሆኑ በጭራሽ አትችሉም:: አለበለዚያ ማይክራፎኑ ዘንድ አትቅረቡ… » ይሉን ነበር:: አድማጮቻችንን በዚያው ልክ ክብር እንድንሰጥ ያስተምሩን፣ ያስጠነቅቁን ነበር:: ያ አባባላቸው ለብዙዎቻችን ዋና ሙያዊ መመሪያችን ነበር::

ታዛ፦ ግን እስኪ አባይነሽ፤ ዛሬ ሙያው ውስጥ ካሉ የሬደዮ ጋዜጠኞች በንጽጽር ጥሩ ይሰራሉ የምትይው ማንን ነው?

 አባይነሽ፦ መዓዛ ብሩ ላይ የሚደርስ አላገኘሁም:: የሸገር ኤፍ. ኤም ጋዜጠኛዋ:: ስለ እውነት ሮል ሞዴል ነች:: ጥሩ ተዘጋጅታ፣ አጥንታ፣ አንብባ ስለምታቀርበው ጉዳይ በደንብ አውቃ ነው አየር ላይ የምትወጣው:: ቃለ መጠይቋ ይመስጣል:: ሃሳብ አያጥራትም:: ከሰዎች ጋር የምትፈጥረው ግንኙነት ቀለል ያለ ነው:: እንደ ጠያቂና ተጠያቂ አይደለም:: በእሷ ዘመን ከነበሩም ካልነበሩም ጋር እኩል የማውራትና ጥያቄዋን በሰል አድርጋ የማቅረብ ብቃት አላት:: አለሳልሳ፣ ፈልፍላ፣ ኮርኩራ ነው የምታናግረው:: በዚያ ሁነት ውስጥ እንዳለፈ ሆና ነው የምትታየው:: አቀራረቧ እና ድምጿ ጆሮ ገብ ነው:: ይዞ ያቆያል:: በፖለቲከኞቹም፣ በህግ አዋቂዎቹም፣ በታሪክ አዋቂዎቹም፣ በምሁራንም ውስጥ እሷነቷን አስገብታ ነው የምናገኛት:: ይህ ዝግጅቷ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል:: መታደል ነው:: ለሙያው መገዛት:: ለሙያው መታመን ነው:: እኔ በየአጋጣሚው ለአንዳንዶች ሙያው ውስጥ ላሉ ጋዜጠኞች የምመክረው የእሷን ፕሮግራም አቀራረብ ሰምተው እንዲማሩበት ነው:: በዚያው ልክ በስራቸው ሲመዘኑ የሬዲዮ ጋዜጠኞች መሆን የሌለባቸው እንዳሉ ይሰማኛል:: የሚተጉ እና ተስፋ የሚጣልባቸው ጋዜጠኞች እንዳሉም እገነዘባለሁ::

ታዛ፦ ስለ መዓዛ ስናወራ አንድ ነገር ታወሰኝ:: በዚሁ በቀደመው የእሁድ ፕሮግራማችሁ «የአዲሱ ቤተሰብ» የተሰኘ የሬዲዮ ድራማ ላይ እናት ሆና ትተውን እንደነበር ይታወሳል፤ እንዲያው ያ ድራማ በአድማጮች ዘንድ እንዴት ነበር ተቀባይነቱ?

አባይነሽ፦ አዎ ልክ ነው:: ጥሩ አስታውሰሃል:: በጣም ጥሩ ድራማ

“የራሳችን የግል የድምፅ ላይብረሪም ነበረን:: ከጅምሩ አንስተን ፕሮግራሞቻችንን በአግባቡ አደራጅተን የምናስቀምጥበት:: የድምጽ ላይብረሪያችን ውስጥ የሚቀመጠውን ፕሮግራም ለሌላ አሳልፎ መስጠት የለም”

ነበር:: እናትነት ምን እንደነበረ አሳይታበታለች:: ልጅን እንዴት አድርጎ መያዝ እንደሚገባ ጥሩ አድርጋ አስተምራበታለች፣ አድማጮችም እየተማሩ ተዝናነተውበታል:: ድራማው ለበርካታ ጊዜ ሄዷል:: ራሷ ነበረች የምትጽፈው:: ትዝ ይለኛል እሁድ ተላልፎ ማክሰኞ በምናደርገው የፕሮግራሞቻችን ሪቪውና ዕቅድ ስብሰባ ላይ ትገኛለች:: ስለ ድራማው ከአድማጮች የደረሱንን ሃሳቦች ይዘን እንነግራታለን:: ያንን የሃሳብ ግብአት ለቀጣይ ስራዋ በጥሩ ትጠቀምበታለች::

ታዛ፦ ዛሬ ወዳለችበት የጋዜጠኝነት ሙያ ትገባለች ብለሽ ትገምቺ ነበር?

አባይነሽ፦ አዎ! እኔ ዝም ብዬ አስብ ነበር:: ስሜቷን ሳጠናው ወደዚያው ነበረች:: አደረገችው:: ጠንካራ የአላማ ሰው ነች::

ታዛ፦ የሴት ሚዲያ ባለሙያዎች ማህበር አባል ነሽ ልበል አባይነሽ? አባይነሽ፦ አዎ አዎ መስራችም የቦርድ አባልም ነኝ:: ጥሩ ተንቀሳቅሰንበታል፣ አማክረናል አሰልጥነናል:: ጥሩ ጥሩ ልጆችም አፍርተንበት ነበር:: የሲቪል ማህበራት ህግ ከወጣ በኋላ ግን እንደቀድሞ የሚያንቀሳቅሰን አልሆነም:: አሁን ትንሽ ፈተና ይጠብቀናል፤ መቀጠላችን ግን አይቀርም:: ተስፋ የምንጥልባቸው አጋዦች አሉን::

ታዛ፦ ከሙያ አንጻር በአገራዊ ሁኔታ ምን ታዝበሻል::

አባይነሽ፦ የቀደሙ ሰዎችን ያለማክበር ችግር አለ:: በተለያዩ ዘርፎች ሙያዊ እውቀታቸው አገር የሚያቀና ሰዎች አልተያዙም:: አንዱ ይመጣል ጥቂት ዓመታት ይሰራና ይለቃል:: ሙያውን በአግባቡ ሳያሻግር፣ እሱም በአግባቡ ሳይሰራበት ይሰናበታል:: በሙያው ጸንቶ የመቆየት ነገር የለም:: ለዚህ የተለያዩ ምከንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን ሰዋዊ ሃብታችንን እያባከንን ነው:: ልምድ ያላቸው በሙያቸው አይቆዩም:: ይህ እየጎዳን ነው:: የእንግሊዚና አሜሪካን አገር ሚዲያዎች ላይ ያሉ አዛውንት ጋዜጠኞችን ለበርካታ ዓመታት በሙያው የሰሩና የበሰሉ ናቸው:: ልምዳቸው ይኸው ሚዲያቸውን እያሳደገው ነው:: እኔ ከሚቆጨኝ ነገር አንዱ የማልረሳው ሰኔ 22 ቀን/1983 ዓ.ም ከማስታወቂያ ሚኒስቴር 52 የጋዜጠኝነት ዓለም ባለሙያዎች «አትፈለጉም» ተብለው መባረራቸው ነው:: የምናከብራቸው፣ ልምዳቸው የማይገኝ እዚያ መሐል የነበሩ ጋዜጠኞች በግምገማ በአንድ ቀን ሲባረሩ እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት:: ይህ ፖለቲካዊ ለውጡ ያመጣው ቢሆንም፤ ልምዳ ቸውን ግን አገር በሚያቀና መልኩ መጠቀም ይቻል ነበር:: ብዙዎች ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች፣ ልጆች ያሏቸው፣ ሌላ መተዳደሪያ የሌላቸው፣ ነበሩ:: ድንገት ሲሰናበቱ ጭልም ነው ያለባቸው:: መሄጃ የላቸውማ:: ሰባዊ ችግሩ የከፋ ነበረ:: ያኔ እኔ በጣም ነበር አምርሬ ያለቀስኩት:: የቀረነው ባለን አቅም ለመርዳት ተንቀሳቅሰን ነበር፤ ግን መቀጠል አልቻልንም:: እግዚአብሔር ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ እርምጃው ግን አበረታቸው:: አማራጫቸውን አዩ:: የተወሰኑት ተሰባስበው የግል ጋዜጦችና መጽሔት አቋቋሙ:: በሱ አንሰራሩ:: እኛ ስራ ላይ ከቆየነው በተሻለ መኖርን ጀመሩ:: እንዲያውም ለኢትዮጵያ ሚዲያ አዲስ መንገድን አሳዩ:: መንግስትን የሚፈትን ስራ መስራት ቻሉ:: በዚያን ሰው ከስራ ሲባረር «ሞተ» እንደማለት በሚቆጠርበት ወቅት፣ ምንም አማራጭ በማይታይበት ጊዜ፤ እነሱ መለወጥን አሳዩ:: ይገርመኛል ያ ጊዜ …::

ታዛ፦ ዛሬ የአቡነ ዼጥሮስ ሬዲዮ ጣቢያ ፈርሷል:: በስፍራው ላይ አዲስ ግንባታ እየተሰራበት ነው፤ ምን ይሰማሻል?

 አባይነሽ፦ አዲስ ነገር በመሰራቱ ደስ ይለኛል:: ከጊዜ ጋር ለውጥ መኖር አለበት:: ግን ታሪክና ቅርስ አብሮ መፍረስ የለበትም:: አዳዲሶቹም ቢኖሩ ፊተኞቹን መጠበቅ ይገባል:: ቢያንስ ስቱዲዮውን ከተቻለም የድምጽ ላይብረሪውን ለቅርስነት ማስቀመጥ ይገባ ነበር:: ስንትና ስንንት ታሪክ የተሰራበት ነው እኮ ‐ አቡነ ዼጥሮስ:: ስቱዲዮው ጣሊያን ኢትዮጵያዊያን አርበኞችን ሲያስርበት የነበረበት ነው ይባላል:: ለፕሮፓጋንዳነት ሲጠቀምበት እንደነበርም እንሰማ ነበር:: አፈረስነው፤ ያሳዝናል:: እኛ ካላፈረስን መገንባት የምንችል አይመስለንም:: ስለዚህ አዲስ ነገር ስናመጣ እንደፈረንጆቹ የቀድሞውን እየጠበቅን ቢሆን በታሪክ ውስጥ የቀጣዩ ትውልድ ተወቃሽ አንሆንም::

ታዛ፦ ልንጨርስ ነው፤ ዛሬ ስላለሽበት ሁኔታና ቤተሰባዊ ሕይወትሽ ጥቂት በይኝ?

 አባይነሽ፦ ጡረታዬን አስከብሬ ደስ እያለኝ እኖራለሁ:: በግል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በሙያዬ የማማከር ስራ እሰራለሁ:: አነባለሁ፣ ስፖርት እሰራለሁ፣ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ቀን ጂም እገባለሁ:: በጥቂቱ ዮጋ እሰራለሁ:: የእግዚአብሔር ፈቃድ ተጨምሮበት በዚህ በዚህ ጤነኛ ነኝ:: ያባከንኩት ጊዜ እንደሌለ ይሰማኛል:: በስራ ምክንያት ጊዜ ያልሰጠኋቸው ሁለት ልጆቼ ለቁምነገር በቅተውልኝ የልጅ ልጆች አይቻለሁ:: አይበቃህም?

ታዛ፦ ከዓመታት በኋላ «እሁድ እንደገና» በሚል እነ ታደሰ ሙሉነህ እና ንጉሴ አክሊሉ ፕሮግራም ይዘው መጥተው ነበር፤ እዚያ ላይ አንቺ የለሽም ለምን ይሆን?

አባይነሽ፦ እንዳልኩህ ሌላ ውጥረት ያለው ስራ ላይ ስለነበርኩ አልቻልኩም::

ታዛ፦ አንድ ጥያቄ ብቻ ? እንዲያው ዳግመኛ ወደ ሬዲዮ ጋዜጠኝነት የመመለስ ሃሳብ የለሽም?

አባይነሽ፦ አይመስለኝም:: የሚገርምህ አንድ ወቅት ለመመለስ ፈልጌ ነበር:: አንድ ሬዲዮ ጣቢያ ሄድኩና የአየር ሰዓት እንዲሰጠኝ ጠየኩ:: በሴቶችና ህጻናት ላይ መስራት ስለነበረ ፍላጎቴ ፕሮፖዛል አዘጋጅቼ ነው ኃላፊው ዘንድ የቀረብኩት:: ምን እንደሚሰራ ሲጠይቀኝ ነገርኩት:: በጣም ገረመው የቁጣ ያህል ሲመልስልኝ ምን እንዳለ ታውቃለህ ? «ትቀልጃለሽ?! እኛ የምንፈልገው ገንዘብ የሚያመጣ ፕሮግራም ነው:: ይሄ አንቺ የምትይው ሴቶችና ልጆች ማን ያዳምጥልሻል… ባክሽን አትቀልጂ! … ይኸውልሽ እኛ የምንፈልገው እንደ እከሌ ያለ (ስሙን እየጠቀሰ ) የስፖርት ፕሮግራም ነው:: ስፖንሰር ያለው፣ አድማጭ ያለው… ይህ የምትይውን ተይው…» ነው ያለኝ:: በዚህ ጊዜ ምን ልበል? ጭስስ እንዳልኩ ወጣሁ:: ቀረሁ:: ቀረሁ:: ወደ ሬዲዮ ዳግመኛም ሃሳቡ አልመጣልኝም:: በቃ::

ታዛ፦ በመጨረሻ የምትይው ካለ?

 አባይነሽ፦ በአገራችን ሰላም ሰፍኖ ማየትን እመኛለሁ:: የዘር አስተሳሰብ ቀርቶ ሕዝቡ በመፈቃቀር፣ በመተሳሰብ ሲኖር ማየት ያጓጓኛል:: ሰብአዊ መብት ተከብሮ የሚዲያ ነጻነት ሰፍቶ የተሻለ የጋዜጠኝነትን ተግባር ባይ ደስ ይለኛል:: በተረፈ አስታውሰኸኝ በእንግድነት ስለጋበዝከኝ አመሰግናለሁ::

ታዛ፦ እኔም በአንባቢዎች ስም ከልብ አመሰግናለሁ:: ቀሪ ዘመንሽ ሃሳብና ምኞትሽ የሚሳካበት ይሆንልሽ ዘንድ እመኛለሁ::

 አባይነሽ፦ አሜን::

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top