ሌሎች አምዶች

የሐተታ ወልደ ሕይወት ተግባራዊ ፍልስፍና እና ማኅበራዊ ትችት

መንደርደሪያ

ባለፈው በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብን ሐተታ ፈትለ ነገር አይተን ነበር። በአንባቢ ኅሊና ውስጥ ለመሆኑ የዘርዓ ያዕቆብ አስተምህሮ ወደ ቀጣዩ ትውልድ አልተላለፈም ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የተጻፈ የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ስሙ በቅድምና የሚነሳው ዘርዓ ያዕቆብ ዘመኑን በሙሉ ምን ሲያደርግ እንደነበር ማሳያ ከሚሆኑን አንዱን የትምህርት ልጁ የሆነውን የወልደ ሕይወትን ሐተታ ስናነብ እናገኛለን። ዘርዓ ያዕቆብን አንስቶ ወልደ ሕይወትን፣ ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብን ተመልክቶ ሐተታ ወልደ ሕይወትን ማለፍ አይቻልም። በግልባጩም እንዲሁ፣ የወልደ ሕይወትን ታሪክና ሥራ ለመተንተን መቅድሙ የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ሊሆን ግድ ነው። የወልደ ሕይወት ሐተታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፍልስፍና ጥናት ውስጥ በርካታ ሚናዎች አሉት። አንደኛው በትውልዶች መካከል የፍልስፍናን ቅብብሎሽ ለማጥናት ይረዳል። ሁለተኛው የዘርዓ ያዕቆብን እና ወልደ ሕይወትን ኢትዮጵያውያንነት ለማስረገጥ በሁለቱ ሐተታዎች መካከል ያለውን ልዩነት፣ የዘርዓ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊ መሆን ለሚጠራጠሩ ሰዎች ሁለቱ ሐተታዎች የአንድ ኅሊና ፈጠራዎች ላለመሆናቸው ማሳያ ይሆናል። ሦስተኛ ዘርዓ ያዕቆብ በሕይወት ዘመኑ በርካቶችን ፍልስፍና ያስተምር እንደነበር የወልደ ሕይወት ምስለኔነት ትልቅ ቦታ አለው። አራተኛ ዘርዓ ያዕቆብ ራሱ ያልነገረንን የሕይወት ገጽታዎች ወልደ ሕይወት ዘግቦልናል። አምስተኛውና ዋናው ደግሞ ረቂቁ (Abstract) የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ማኅበራዊና ተግባራዊ ፋይዳው ጎልቶ እንዲታይ የደቀ መዝሙሩ አስተዋጽኦ የጎላ ነው። በዚህ አጭር ጽሑፍ የምመለከተውም ይህንን ተግባራዊ ፍልስፍና ነው። ወልደ ሕይወት ዘርዓ ያዕቆብ “የጸጋ አባቴ” እያለ የሚጠራው የባለ ውለታው የሀብቱ ልጅ ነው። እንደ ወልደ ሕይወት ምስክርነት ከሆነ በዘርዓ ያዕቆብ ሥር የተማሩት በርካቶች ነበሩ። ግን ብዙዎቹ ፈርተው ፍልስፍናቸውን አልገለጡም። እኔ ግን ለ59 ዓመታት የተማርሁትን፣ በዘርዓ ያዕቆብ መጽሐፍ ላይ ይህችን ጨመርሁ ይለናል።

 ከዘርዓ ያዕቆብ ሐተታ በገጽ ብዛቱና በተግባራዊ ፋይዳው የወልደ ሕይወት ጎላ ያለ ነው። በመሠረታዊ የነገረ ሕልውና፣ የሥነ እውቀትና የሥነ ምግባር አስተምህሮዎች ከዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና የሚለይ አይደለም። ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ነፍስ ሐተታ፣ ስለ ሃይማኖት ጉዳዮች፣ ስለ ምርምር ወዘተ ያነሳቸው ሙግቶች ከመምህሩ ፍልስፍና የተወረሱ ናቸው። የወልደ ሕይወት ሐተታ ባብዛኛው በማኅበራዊ ትችትና ተግባራዊ ፍልስፍና ላይ ያተኩራል። በዚህም ወደ መሬት ወርዶ በዘመኑ ከነበረው ማኅበረ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማኅበረሰቡ ይላቀቅ ዘንድ በተደጋጋሚ ይመክራል። ለመሆኑ ወልደ ሕይወት ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች ምን ምን ነበሩ? ከተግባራዊ ፍልስፍና እና ማኅበራዊ ትችት ጋር የተገናኙትን እንደሚከተለው እንመልከት። የተጠቀምኩበት መጽሐፍ አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ የተረጎሙትንና በ2007 ዓ.ም የታተመውን ነው።

ተግባራዊ ፍልስፍና

 ተግባራዊ ፍልስፍና የሚባለው የፍልስፍና ዘርፍ የቅርብ ጊዜ እድገት ነው። ለምሳሌ የጾታ እኩልነት፣ የአካባቢ ደህንነት፣ የቴክኖሎጅ እድገትና ማኅበራዊ መስተጋብር፣ እንደ ጽንስ ማስወረድ ያሉ አከራካሪ ጉዳዮች ወዘተ በፍልስፍናዊ ሙግት ይሁንታ የሚያቀርብ ነው ተግባራዊ ፍልስፍና። የወልደ ሕይወት ፍልስፍናም ከልጆች አስተዳደግ፣ ከትዳርና ከሴቶች እኩልነት፣ ከመልካም የሥራ ባህል እና መረዳዳት፣ ስለ ሕግና ፍትህ፣ ስለ ማኅበራዊ ሕይወትና መልካም ተግባቦት፣ ስለ ትምህርት ፍልስፍና፣ እናትና አባትን ስለማክበር፣ ስለ መልካም አስተዳደር ወዘተ በሰፊው ጽፎልን አንብበናል። በዚህም በወቅቱ የነበረውን እውነታ በፍልስፍናዊ ትዝብቱ ቁልጭ አድርጎ ከማሳየቱም በላይ ዘመን ተሻጋሪነቱ ለዘመናችን ችግሮች መፍትሔነት ዓይነተኛ ምክረ ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል።

 ለምሳሌ

 ከትዳር ጋር በተያያዘ የሴቶች በትዳር እኩልነት ከንብረት እና በቤተሰብ ጉዳይ ከመወሰንም አልፎ በግብረ ሥጋ ግንኙነት እኩል የድርሻቸውን እርካታ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይሞግታል። “አንተ ግን ጠቃሚ በሆነ ጊዜ ሚስትን አግባ። ለአካለ መጠን በደረስህም ጊዜ ሥጋህ የጋብቻ የባህርይ ፈቃድን ያሳይሃልና። ተፈጥሮህ ባልሆነ መንገድ ኃጢያት ሰርተህ ፈጣሪህ በጋብቻ ያዘጋጀልህ ዋጋ እንዳይጠፋ ፈጥነህ አግባ እንጂ አትዘግይ። በረከቱንም ካንተ እንዳታርቅ ከአመንዝራነት ራቅ። ከአንዲት ሴት ወደ ሌላይቱ አትሂድ። ሴትም በባልዋ ላይ ወንድ አትመኝ። ይህ የማይጠቅም ሴሰኝነት ነውና። ፈጣሪ ለሰው ልጆች ከሰራው ሥርዓት የወጣ ነውና።” (ምዕ.24፣ ገጽ 84)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ተፈጥሮ ባልሆነ መንገድ” የሚለው ሀረግ ምናልባትም ግብረ ሰዶም፣ ሌዝቢያኒዝም እንዲሁም ምንኩስናን ለመተቸት የተጠቀመበት ይመስላል። የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ የዘመናችን አንዱ አከራካሪ ርእሰ ጉዳይ ነው። ወረድ ብሎ “ከዝሙት፣ ተፈጥሮህ ባልሆነ መንገድም ዘርህን ከማፍሰስ፣ ምውት ከሆነውም ምንኩስና ራቅ።” ሲል ያጸናዋል (ገጽ 85)። ስለ ግብረ ሥጋ ግንኙነት መጣጣም ሲመክርም “ወደ እርሷ በተጠጋህ ጊዜም የሩካቤውን ጣዕም ለብቻህ አትሻ። ለሚስትህም የጣዕሙን ሥሜት እንዲኖራት አድርግ እንጂ። እግዚአብሔር የሰጣትን ድርሻዋን አታሳጣት።” ይላል። ይህም በዘመናችን ለጋብቻ መፍረስ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አለመጣጣም እንደሆነ ግልጽ ነው። ፈላስፋው ስለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ አትቷል።

የዘመናችን አንዱ ችግር የህጻናት አስተዳደግ ነው። የጋብቻ ፍሬ ስለሆኑት ህጻናት አስተዳደግ ያለን ሥነ ሥርዓት ከተዛባ ማኅበራዊ መስተጋብራችን በሙሉ የተዛባ ይሆናል። ይህንን ችግር ቀድሞ የተገነዘበው ወልደ ሕይወት የዘመኑን የህጻናት አስተዳደግ ችግር ሲተች እንዲሁ ልቅ የሆነ ወይም በኃይል ላይ የተመሠረተ የህጻናት ቅጣት የሚያሳድረው ሥነ ልቡናዊ ተጽእኖ በወደፊት ባህርያቸው ላይ እንዴት እንደሚንጸባረቅ ይሞግታል። በህጻንነታቸው ሳንሰለች በመልካም ትዕግስት ልናሳድጋቸው እንደሚገባ፤ እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ግን እንደየ ጥፋታቸው ዓይነትና ልክ ቅጣቱም እንደሚለያይ በዝርዝር ይተነትናል። “ዝም ከማለታችሁ የተነሣ ክፋት እንዳይለምዱ ጠቃሚ በሆነ ጊዜም ምትዋቸው። በትንሽነታቸው ጊዜ ባትገሥጽዋቸው ግን በክፋታቸው ያድጋሉ። ካደጉ በኋላ ተግሳፃችሁን አይሰሙም።” በምን መልኩ ጠባያቸውን ማስተካከል እንደሚቻል ሲመክርም እንዲህ ይለናል:- “ልጆችህን በምትገሥጻቸው ጊዜም፣ የምትገሥጻቸውም ስለ ራሳቸውና ስለ ጥቅማቸው እንደሆነ በሚያውቁበት በጥበብና በምክር ቃል እንጅ በቁጣና በስድብ ቃል፣ በርግማንም አትገሥጻቸው። በማስተማር፣ ምሳሌን በመመሰል ታሪክና የሌሎችን ሰዎች አርአያነት በመጥቀስ ዘወትር እያስተማርህ እንዲያስተውሉ አድርጋቸው።” (ገጽ 92)

ስለ መልካም አስተዳደር ባተተበት ምዕራፍ “በሰዎች ላይ ብትሾምም አገዛዝህን በነርሱ ላይ አታክብድ፣ በኃይልም አትታገላቸው። ከትልቁም ከትንሹም፣ ከባለጸጋውም ከድሀውም፣ ከሁሉም ጋር ቅን ሐሳብ ይኑርህ እንጅ። የሰውን ፊት አትፍራ። ለሁሉም ያለ አድልዎ ፍረድ።” በማለት ያስረዋል። (ገጽ 99)

የሥነ ምግባርና የማኅበራዊ መስተጋብር መሠረቱ ኢመዋቲት የሆነች ነፍስ እንዳለችን ማወቅ ነው። ለዚህም ምክንያታዊ አድርጎ ፈጥሮናል። መልካም ምግባሮችም ከዚህ ይመነጫሉ። ከሁሉም ጋር በሰላም ኑር የሚለው ወልደ ሕይወት በሃይማኖት ወይም በማንኛውም መለኪያ ሰዎችን አይተህ አታዳላ። ሁሉም የሰው ልጆች አንድ ዘር እንደመሆናቸው እኩል ናቸው። በመሆኑም ማንንም በሰው ሰራሽ ማንነቱ ምክንያት ልታሳንስ ወይም ልታስበልጥ አይገባም። እያለ ስለ ሰላም፣ ስለ እኩልነት ይመክራል። “ስለዚህ እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ እግዚአብሔር በልባችን ሰሌዳ የጻፋት ይህችን የዘላለም ህግ እንጠብቅ ዘንድ ይገባናል። እርሷም ‘ባልንጀሮችህን እንደራስህ ውደዳቸው፣ እነርሱ ሊያደርጉልህ የምትሻውን አንተም አድርግላቸው፣ ሊያደርጉብህ የማትሻውን አንተም አታድርግባቸው’ የምትል ናት። ይህችን ቀዳሚት ህግ በመጠበቅም የምግባራችንና የጽድቅ ሁሉ ፍጻሜ ይገኛል። … ደጎችም ቢሆኑ ክፉዎች፣ ክርስቲያንም ቢሆኑ እስላም፣ አይሁድም ቢሆኑ አረማውያን ሁሉም ከእኛ ጋር እኩል ናቸው (ምዕ. ፲፫፣ ገጽ 64)። ይህ ሐሳብ ለዘመናችን “ብሔር ተኮር” የአስተሳሰብ ዝንፈቶች ሁነኛ ምክር ነው።

ከትምህርትና ለማወቅ ከመጣጣር ጋር በተያያዘ ለዘመናችን የሚመጥን ምክረ ሐሳብ ይሰጣል። ትምህርትንና ጥበብን መውደድ ለልቡና ብርሃን ለኅሊና ሐሳብ የእውቀትና የምግባረ ሰናይ መሠረት እንደሆነ ይመክራል። በማርና በሰም መስሎ ማሩ ልቡናን ደስ የሚያሰኝ ቀናነት ሲሆን ሰሙ ደግሞ እውቀት ለተጠሙ የሚያበራ ብርሃን ነው ይለናል። (ምዕራፍ 17)

ማኅበራዊ ትችት

 ማኅበራዊ ትችቱ ከላይ የተጠቀሱት ምክረ ሐሳቦችና ሙግቶች መንስኤ የሆኑትን የባህል፣ የሃይማኖት፣ የአስተዳደር፣ የማኅበራዊ መስተጋብር ወዘተ ተቃርኖዎችን የተቸበት ፍልስፍናው ነው። ማኅበራዊ ትችት (Social Critic) አንዱ የፍልስፍና ሚና ነው። በማንኛውም ማኅበረ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ባህላዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ውስጥ ጨቋኝ ተቃርኖዎችን እና ለሰው ልጆች የተስተካከለ ሕይወት የማይበጁትን ተግባሮች በመንቀስ ትችት የሚያቀርብ የፍልስፍና ክፍል ነው። በ17ኛው ክፍለ ዘመን ወልደ ሕይወት በኖረበት ማኅበረሰብ ውስጥ ያያቸውን፣ የሰማቸውን፣ እንዲሁም የታዘባቸውን ስህተቶች ለመተቸት ወደ ኋላ አላለም። በዚህም የሰላ ትችቱ ሰዎችን ወደ መልካም ጎዳና ለመምራት ይበጃሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች ጽፎልናል።

 አጽንኦት ሰጥቶ ከተቻቸው ነገሮች ውስጥ በዋናነት ሰዎች ራሳቸው ሳይመረምሩ በተቀበሉት ሃይማኖት ምክንያት መጣላት እንደሌለባቸው፤ በትምህርትና በእውቀት ጉዳይ ላይ ትንሽ አውቀው ብዙ ያወቁ የሚመስላቸውን (ገጽ 71) ይገስጻል። ሥራን ስለ መናቅና በሥራ ባህል ምክንያት ስለ መሰዳደብ “የእጅ ሥራን መሥራት ግን ለድሆችና ለገበሬዎች፣ ለአንጥረኞችና ለግንበኞች፣ ለገባርም ልጆች ይገባቸዋል። ለታላቆችና ለከበርቴዎች ልጆች ግን አይገባቸውም” አትበል። (ገጽ 72) እያለ የዘመኑንና እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀውን ቀጥቃጭ፣ አዝማሪ፣ ሸማኔ፣ እየተባለ መሰዳደብና ማኅበራዊ መገለልን አውግዟል። ስለዚህ ጉዳይ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝም በአጽንኦት ጽፏል። ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ያስቀራትም ይኸው ሥራ ተኮር የሆነው ማንቋሸሽና መሰዳደብ ነው። የወልደ ሕይወት ብዕር ከ300 ዓመታት በፊት ትዝብቱን አልደበቀንም። የሰዎችን ባህል ስለማክበር፣ ባህላቸውን መናቅ እንደሌለብንና እነርሱንም መስሎ ስለመኖር እንዲሁም ስለ ብዝሃነት ከላይ ከጠቀስነው በተጨማሪ በምዕራፍ 15 በሰፊው ያብራራል። (ገጽ 68)

ትዕቢትንና ቁጣን ሲያወግዝ “ቁጣ ጥበብን ያጠፋልና … ቁጡዎች በሰላም አብረው መኖርን አይችሉም።” (ገጽ 97) ሲል በምዕራፍ 23 ደግሞ ስካርን፣ ሐሜትን፣ ዝሙትና ሌብነትን ያወግዛል (ገጽ 81-82)። ጤናንና ንጽሕናን ስለመጠበቅ በዘመኑ የታዘበውን ለቆዳህ በሽታን በሚያመጣ ሳር ላይ አትተኛ፣ ከመሬት ከፍ ያለ አልጋን ሥራ፤ ልብስህንም በውሃ እጠብ (ገጽ 78) እያለ ይመክራል። ጾምን እና ምንኩስናን፣ የትዳርን ሥነ ሥርዓት በተመለከተ ያለው አቋም ከዘርዓ ያዕቆብ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ማጠቃለያ

 ዘርዓ ያዕቆብ ሲታሰብ ወልደ ሕይወት፣ ወልደ ሕይወት ሲነሳ ዘርዓ ያዕቆብን አለማሰብ አይቻልም ብያለሁ። ለዚህም የመምህሩ ረቀቅ ያሉ ፍልስፍናዊ ሙግቶች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ሲሆን የደቀ መዝሙሩ ረጅም እጆች ደግሞ ወደ ማኅበረሰቡ የአኗኗር ይትበሃል ዘልቀው በመግባት የሚጠቅሙ ተግባራዊ ምክረ ሐሳቦችና መቀረፍ አለባቸው ያላቸውን ተቃርኖዎች በመተቸት የመምህሩን ረቂቅ ፍልስፍና ነፍስ ይዘራበታል። በተማሪው ድርሳን ረቂቅ ሐተታ የለም፤ በመምህሩ ሐተታም ተግባራዊ ፍልስፍና አልተንጸባረቀም ማለት ግን አይደለም። የሁለቱም ሐተታዎች በራሳቸው መንገድ ፍልስፍናዊ ጉዳዮችን ተንትነዋል። ልዩነቱ የትኩረት ምህዋራቸው ላይ ነው። ዘርዓ ያዕቆብ በዋሻ ውስጥ ያስተነተናቸውን ጉዳዮች በማስተማርና በመጨረሻም በገጽ ብዛቷ ትንሽ በይዘቷ ሐብታም የሆነች ሐተታን በመጻፍ እንካችሁ ሲለን ወልደ ሕይወት ደግሞ ከመምህሩ ከተማረው ፍልስፍና ቀድቶ፣ ከማኅበረሰቡ ተረትና ይትበሃል ጨልፎ በዘመኑ ለነበረው ማኅበረሰባዊ ተዛንፎዎች ማስተካከያ፣ ማረቂያ ይበጃል ያላቸውን ሙግቶቹን አቅርቦልናል።

 ይህ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የፍልስፍና ባህል ወደ ቀጣዩ ትውልድ ተሸጋግሯል ወይስ በዚያው የውሃ ሽታ ሆነ? የዘርዓ ያዕቆብና የወልደ ሕይወት ፍልስፍናዊ ሐተታ መሠረቱ ከየት ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ማንሳታችን አይቀርም። አንባቢና ተመራማሪን ከጥያቄዎቹ ጋር በመተው ለወደፊቱ በሌላ ጽሑፍ ለመገናኘት የዚያ ሰው ይበለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top