አድባራተ ጥበብ

የለውጥ አማጪዎች መሰረታዊ ባህርያት

ለውጥ በተፈጥሮም በኑሮም ያለና የማይቀር ነገር ነው። ሁሉም ነገር በለውጥ ውስጥ የሚያልፍ ነው። የማይለወጡ ነገሮች ቢኖሩ እንኳ እጅግ በጣም ውስን መሆን አለባቸው። በተለይ ደግሞ በሀገር ደረጃ የሚከናወኑ ለውጦች ዘርፈ-ብዙ ናቸው። ሀገራዊ ለውጦች ሽቅብ ወደ ብልጽግና አሊያም ቁልቁል ወደ ኋላቀርነት ሊያመሩ ይችላሉ። ለውጥና ቁሞቀርነት አብረው አይሄዱም።

 አስተያየቱ ይለያይ እንጂ ሀገራችን በብርቱ የለውጥ ሂደት ውስጥ ናት። ምንም ለውጥ የለም ከሚሉ ጀምሮ የለውጡን መኖር ተቀብለው የሂደቱን ፍጥነትና ዝግመት፣ የባህርዩን መሰረታዊነት ወይንም አሻሻይነት (ሪፎርሚስት) እና የውጤቶቹን ግዝፈትና ውስንነት በምክንያትም በስሜትም የሚተቹ ብዙ ክርክሮችን መስማት የተለመደ ሆኗል። ከክርክሮቹ መልካም ሃሳብ ማጥለል ይቻል ይሆናልና መኖራቸው ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ለውጡን ወደማይፈለግ አቅጣጫ እንዳይገፉት መጠንቀቅም ይገባል። በዚህ ጽሁፍ የለውጥ አማጪዎች (ኤጀንትስ) መሰረታዊ ባህርያት ምን እንደሆኑ በግርድፉ ለመዘርዘር እሞክራለሁ። ዓላማዬ ‹‹እነዚህን ባህርያት በመሪዎቻችን ላይ እናስተውላለን ወይ? በተለይም ደግሞ ለህብረተሰቡ በጣም ቅርብ በሆኑት የተለያዩ መሪዎች ላይ እንመለከታለን ወይ?›› የሚል የውይይት ሃሳብ ለመቀስቀስና በተለያየ ጊዜ ለፖለቲካና ማህበራዊ አመራር የምንመርጣቸው ሰዎች ምን ዓይነት ሰብዕና ያላቸው መሆን እንደሚገባቸው ለማስታወስ ነው። ነገር ግን የሚፈለጉትን መልካም ባህርያት ሁሉ አሟልቶ የሚገኝ ሰው ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ሆኖም የግለሰቡ ተነሳሽነት፣ ትጋትና ቁርጠኝነት ከታከለበት ባህርያቱ በሂደት እየዳበሩና እየበለጸጉ የሚሄዱ ናቸው። መሪዎቻችን እነኚህን ባህርያት እንዲላበሱ እንሻለን።

 ከለውጥ ሂደት መልካም ውጤትን መጠበቅ የማንም ጤነኛ ሰው ፍላጐት ነው። ትልቁ ችግር ግን ለውጡን የተሳካ ማድረግ ነው። የለውጥ ሂደትን የተሳካ ለማድረግ አንዱ ዘዴ ቀደም ሲል ይከናወኑ የነበሩ ነገሮችን በተለወጠ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ፣ እንዲሁም አዳዲስ ሃሳቦችን ወጥኖ በጥንቃቄ መፈጸም ነው። ይሁን እንጂ በለውጥ አመራር ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በተቋማት ውስጥ ከሚከናወኑ የለውጥ ተግባራት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የተሳኩ አይሆኑም። ለሀገራዊ የለውጥ ሂደት ይህ የምንቀበለው ስታቲስቲክ አይደለም።

የለውጥ ሂደት አልጋ ባልጋ ባለመሆኑ የለውጥ አማጪዎች ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። ዳተኝነትን፣ መዋቅራዊ ጋሬጣዎችን፣ የደባ ተግባራትን፣ መጨበጫ የሌላቸው ትችቶችን፣ ወዘተ መጋፈጥ የግድና የማይቀር ነው። ለውጥ ሆን ተብሎ የሚከናወን ተግባር በመሆኑ በሂደት እምነት የያዙ ደጋፊዎችን እያስገኘ መቀጠሉ አይቀርም። ነገር ግን እንደ ብዙ ተግባራት ሁሉ የለውጥ አማጭ መሆን የሚጀምረው ከራስ ነው። የለውጥ አማጪዎች ለለውጥ ስኬት ምን ምን ጉዳዮች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ፣ ምን ዓይነት ተጋድሎ ተገቢ እንደሚሆን፣ ትግሉም ትክክልና ውጤታማ እንደሆነ አስቀድመው መለየትና መወሰን ይጠበቅባቸዋል። የለውጥ መሪዎች ብዙውን ጊዜ ተገማች (ፕሪዲክቴብል) ናቸው። በሌላ አገላለጽ፣ እርምጃን በሚሻ የተጫጫነ ሁኔታ ውስጥ የለውጡን ሂደት በንቃት የሚከታተሉ ሰዎች ስለ ለውጥ አማጪዎቹ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ኋላ ላይ የለውጥ መሪዎቹ ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ጋር ተቀራራቢነት ይኖራቸዋል እንደ ማለት ነው። የተከታታይ ትውልዶችን ያልረካ ፍላጐት፣ የዘመኑን ትውልድ ጥያቄዎችና ሉላዊ ሁኔታውን አገናዝቦ መረዳት የለውጥ አማጪዎች ክህሎት ነው።

 ፒተር ፉዳ የተባለ የለውጥ አመራር አጥኚ ‹‹የውልጠታዊ [ትራንስፎርሜሽናል] ለውጥ አማጪዎች ባህርያት›› በሚለው አጭር የድረገጽ ጽሑፉ 15 ባህርያትን ይዘረዝርና ባህርያቱን በሦስት ማዕቀፎች ስር ጠቅለል አድርጐ ያስቀምጣቸዋል። ማዕቀፎቹ የድርጊት/የተግባር፣ የግንዛቤና የሰብዕና ናቸው። ተግባር የለውጥ ሃሳብን በድርጊት ለመተርጐም የሚረዱ ክሂሎትና ዘዴዎችን፣ ግንዛቤ እውነታን የመረዳትና ትርጉም የመስጠት አቅምን፣ ሰብዕና ደግሞ የግል ጠባይን ወይንም ባህርያትን ያመለክታሉ። በፉዳ አስተያየት የለውጥ አማጪዎች ትልቁ ወጥመድ ለድርጊት የሚሰጡት ለየትና ከበድ ያለ ትኩረት ነው። በእርግጥ ድርጊት ከምንም በላይ ጐልቶ ይታያል፤ በገሃድም ይመሰክራል። ይሁን እንጂ ፉዳ እንደሚለው ከድርጊት ግንዛቤ፤ ከግንዛቤም ሰብዕና መቅደም አለበት።

 ከሰብዕና አንፃር የለውጥ አማጪዎች በቅድሚያ አርአያነት (ፈረንጆቹ ሮል ሞዴል የሚሉት) ሊኖራቸው ይገባል። ከዚያ በኋላ ነው ስለለውጡ ሊሰብኩና ሊደሰኩሩ የሚችሉት። ተስፋን ሰንቀው መልሰው ተስፋን የሚያሳዩ መሆን አለባቸው። የለውጥ መሪዎች ፍርሃትን አይነዙም። ደፋር ናቸው። ለእኔ የሚሉት ነገር የላቸውም። ተአማኒ ናቸው፤ የመታመንንም ፋይዳ ከፍ አድርገው ያሳያሉ። አገልጋይ እንጂ ክብር ፈላጊ አይደሉም። በብዙ ጉዳዮች ቀድመው ምሳሌ ለመሆን ፍላጐቱ ስላላቸው ወደኋላ አይሉም። ለለውጡ ስኬት ሲባል ከእያንዳንዱ ሰው የሚፈለገውን ባህርይና አመለካከት በራሳቸው አማካይነት ለማሳየት ይሞክራሉ። ዜጎችም ለውጡ በእርግጥ እውን መሆኑ የማይቀር እንደሆነ ለማመን የመሪዎቹን ቃልና ተግባር በጥንቃቄ መመዘናቸው አይቀርም።

 የለውጥ መሪዎች እውነታን የሚገነዘቡበትና የሚተረጉሙበት መንገድ ከተለመደው ለየት ያለ ነው። በማስረጃና በእውነት (ፋክት ኤንድ ትሩዝ) መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀው ይገነዘባሉ። ሌሎች መሪዎችን የሚመለከቱት በነግበኔ አተያይ (ሲምፓቴቲክ ሆነው) ነው። የሚወስዷቸው እርምጃዎች የዘፈቀደ ሳይሆኑ ስትራቴጂካዊ አውድ እንዲኖሯቸው ይሻሉ። ከተርታ የወረደ ሳይሆን ከፍ ያለ ማንነትን አሻግረው ያያሉ።

 ድርጊትን በሚመለከት የለውጥ አማጪዎች ክሂሎት ሂደትን ጭምድድ አድርጐ ይዞ በመቆጣጠር ላይ የተመሰረተ አይደለም። ሂደትን አጥብቆ ከመቆጣጠር ይልቅ ለስኬት የመነሻ ስፍራና ድባብ ይፈጥራሉ። የተግባር ማዕቀፎችን፣ ሞዴሎችንና መሳሪያዎችን

“ውጤታማ የለውጥ መሪ ሁሉን አውቃለሁ ባይ አይደለም። ለሁሉም ጥያቄ መልስ አለኝ ከሚል ተዓብዮ የራቀ ነው። ብዙ ጥያቄዎችን የሚጠይቅና በመደበኛውም ይሁን በሌላ መንገድ መልስም ግብረ-መልስም የሚሻ ነው”

በጥበብ ለመጠቀም ይመርጣሉ። በበላይ ሃላፊዎች ዘንድ ቅሬታን ሳይፈጥሩ እርምትን ለመስጠት ፈቃደኝነቱ አላቸው። ንግግራቸው አስቀድሞ ለልብ ከዚያ በኋላ ለአዕምሮ ነው። ሆኖም ጥሪያቸው ለተግባር ነው።

 በበለጸጉት ሀገራት (በተለይም በዩኤስ አሜሪካ) በተካሄደ አንድ ጥናት 275 የሚሆኑ የትላልቅ ኩባንያዎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በስራ ዘመናቸው ስላጋጠሟቸው የተሳኩና ያልተሳኩ የለውጥ አመራር ጥረቶች አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር። የጥናቱ ተሳታፊዎች ከ15 ዓመት በላይ የስራ አመራር ልምድ ያላቸው፣ ከ500 በላይ የሆኑ ሰራተኞችን ያስተዳድሩ የነበሩና በከፍተኛ ሃላፊነት ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ሲወስኑ የነበሩ ናቸው። የጥናቱ ዋና ዓላማ ለውጥን ለመምራት የሚችል አመራር ባህርያት ምን ምን እንደሆኑና ለውጥን የሚያደናቅፉ የአመራር ዘይቤዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለመረዳት ነበር። የጥናቱ ውጤት ዘጠኝ ባህርያትን ለይቶ ያመለክትና እነኚህን ባህርያት መልሶ በሦስት ዋና ዋና ጐራዎች ውስጥ ያስቀምጣቸዋል።

 በመጀመሪያው ጐራ ለተሳካ የለውጥ አመራር በጣም መሰረታዊና በስፋትም የሚታወቁ ሦስት ባህርያት ተመልክተዋል። እነርሱም ተግባቦት፣ ትብብርና ቁርጠኝነት ወይንም ሆኖ መገኘት ናቸው። በእንግሊዝኛው አጠራር communicate, collaborate, and commit የሚባሉት ሲሆኑ በጥቅል አገላለጽ “The three C’s of change leadership” ተብለውም ይታወቃሉ። ከተግባቦት አንፃር ከለውጡ ጀርባ ምን ምን ነገሮች እንዳሉ በማብራራት ላይ የተጠመዱ የለውጥ መሪዎች የተሳካላቸው አይደሉም። የተሳካላቸው የለውጥ መሪዎች ከለውጡ ጀርባ ስላሉት ነገሮች ብቻ ሳይሆን ለውጥ ለምን እንደሚያስፈልግ ማብራራትና ማስረዳት የቻሉ ናቸው። የለውጡ ዓላማ ከሀገራዊ እሴቶች ጋር ያለውን ትስስር ወይንም ያስገኛቸውን ትሩፋቶች መግለጽ የቻሉ መሪዎች ጠንካራ ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ። በመሆኑም ዜጎች ወይንም ተከታዮቻቸው የጉዳዩን አጣዳፊነትና የአፈጻጸሙን አስቸኳይነት በቀላሉ ይረዱላቸዋል። በለውጥ ሂደት ሰዎችን አስተባብሮና ለውጥን በጋራ አቅዶ መተግበር እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። በአስተሳሰብ ድንበር አለመታጠርን፣ ሰዎችም ከአስተሳሰብ ጉሮኖ እንዲወጡ ማበረታታትን፣ ጤናማ ያልሆነን ፉክክር መቆጣጠርንና በማናቸውም ውሳኔን በሚሹ ጉዳዮች ላይ አግባብነት ያላቸውን ሰዎች ማሳተፍን ይጠይቃል። ያልተሳካላቸው የለውጥ መሪዎች እነኚህን ተግባራት ለመፈጸም ያልቻሉ ናቸው። ቁርጠኝነት ወይንም ሆኖ መገኘት በለውጥ ሂደት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ባህርይ ነው። ለውጥ በጣም አስቸጋሪ ተግባር ቢሆንም ሂደቱን በስኬት የሚወጡ መሪዎች በቀላሉ አቋማቸውን የማይለዋውጡ፣ ወድቆ መነሳትን የሚያውቁና ከለመዱት የምቾት ቀጠና ወጣ ብለው ተግባራትን የሚከውኑ ናቸው። በትልቁ ሀገራዊ ስዕል ላይ አተኩረው ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚያ ያውላሉ። ለውጥን ማሳካት ያልቻሉ መሪዎች ተግዳሮትን ለመለማመድ/ለመጋፈጥ የተሳናቸው፣ አሉታን የሚያበዙና በውጤት መጥፋት ትዕግስት ያጡ ሆነው ይታያሉ።

በሁለተኛው ጐራ ውስጥ የተፈረጁት የለውጡን ሂደት ለመምራት የሚያስችሉ የለውጥ አማጪዎች ባህርያት ናቸው። በመሰረቱ ስትራቴጂያዊ ለውጥ በራሱ እውን አይሆንም። ስኬታማ የለውጥ መሪዎች የለውጡን ሂደት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ መምራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ ከፍ ሲል በጠቀስነው የጥናት ውጤት ውስጥ የተመለከቱት አስፈላጊ ባህርያት ሦስት ናቸው። አንደኛው፣ የለውጡን ሃሳብ የማፍለቅና የማስጨበጥ፤ ሁለተኛው፣ ለተግባራዊነቱ ስትራቴጂውን የመንደፍና ሦስተኛው፣ ስትራቴጂውን በተግባር የማዋል ናቸው።

የተሳካላቸው የለውጥ መሪዎች በቅድሚያ የለውጡን አበይት ጉዳዮች የሚያመለክት የዳሰሳ ዘገባ ሊኖራቸው ይገባል። ይህም ሀገራዊውን ነባራዊ ሁኔታ፣ የለውጡን አስፈላጊነት፣ ርዕይ፣ የሚፈለጉትን ውጤቶችና በጋራ ሊያዝ የሚገባውን ሀገራዊ ግብ ያካተተ መሆን አለበት። በእነኚህ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የለውጡን የወል ግብ ለማስጨበጥ ያልቻሉ መሪዎች የለውጥ ሂደትን በአግባቡ ሊመሩ አይችሉም።

 በመሰረቱ የለውጥን ሂደት ለመምራት ስትራቴጂ መንደፍና ግልጽ የሆነ የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። ይህም የተግባራትን ቅደም ተከተል፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ ተቋማዊ መዋቅር፣ የሰው ሃይልና ሌሎች አስፈላጊ ሃብቶችን ማደራጀት ያካትታል። በዚህ ሂደት መሪዎች መለወጥ ያለበትንና እንደነበረ መቀጠል የሚገባውን መለየትና ይህንኑ መግለጽ አለባቸው። በየጊዜው የሚቀርቡ ጥያቄዎችንና አሳሳቢ ጉዳዮችን በአንክሮ ለመስማት ያልቻሉ የለውጥ መሪዎች የተጀመረውን ለውጥ ዳር ማድረስ አይችሉም።

 የተነደፈውን ስትራቴጂ ወደ ተግባር መለወጥ መሪዎች ማድረግ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል ዋነኛው ነው፤ ብቸኛው ግን አይደለም። በተግባር ምዕራፍ ስኬታማ የሆኑ የለውጥ መሪዎች ቁልፍ የተባሉ ሰዎችን ቁልፍ በተባሉ የሃላፊነት ስፍራዎች ይመድባሉ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ከሃላፊነት ያነሳሉ። አላልቅ ያሉ ትላልቅ ኘሮጀክቶችን ወደ ትናንሽ ተግባራት በመመንዘርና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታዩ ውጤቶችን በማስገኘት የለውጡን ግለት ጠብቆ ለማዝለቅ ጥረት ያደርጋሉ። ሂደቱን ለመከታተል የክትትል ስርዓት ይዘረጋሉ፤ ለምዘናም የሚረዱ አመልካቾችን ያዘጋጃሉ። ያልተሳካላቸው የለውጥ መሪዎች በጥቃቅንና ዝርዝር ተግባራት ላይ በመጠመድ የለውጡን ዋና ግብ ወይንም ትልቁን ስዕል ይዘነጋሉ። በዚህም የለውጡ ሂደት ይሰናከላል።

ቀደም ሲል በጠቀስነው ጥናት ውስጥ በሦስተኛው ጐራ የተጠቀሰውና የለውጥ ሂደትን ከመምራት ችሎታ ቀጥሎ የተሳካላቸው ለውጥ አማጪዎች ሊኖራቸው የሚገባው ባህርይ ሰዎችን የመምራት ችሎታ ነው። ብዙ ጊዜ ይዘነጋ ይሆናል እንጂ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት የለውጥ ሂደት ጠባዮች ውስጥ አንዱ ሰብዓዊ ገጽታው ነው። ለለውጡ ስኬት አስፈላጊውን አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ ሰዎችን አፈላልጐ ወደ ሂደቱ ለማስገባት የለውጥ መሪዎች ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው። በዚህ ረገድ የተዋጣላቸው የለውጥ መሪዎች ሊኖሯቸው የሚገቡ ሦስት ባህርያት ሰዎችን መደገፍ፣ መማረክና ሳያስተጓጉሉ ከለውጡ ሂደት ትምህርት/ተሞክሮ መቅሰም ናቸው። እነኚህ ባህርያት ከፍ ሲል በፒተር ፉዳ አጭር ጥናት ውስጥ “የመሪዎች ሰብዕና” በሚለው ስር ከተመለከቱት ጋር ይመሳሰላሉ።

 የተሳካላቸው የለውጥ ፕሮግራሞች ሰራተኞች የሚያጋጥሟቸውን ወይንም ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጋሬጣዎችና አሽክላዎችን የሚከሉ ሃላፊዎች ያሏቸው ናቸው። ለውጥ አማጪዎች የደጋፊዎቻቸውን ሰብዕና ከሚጎዳ ተግባር የተቆጠቡና የለውጡ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው በማድረግ የሰራተኞቻቸውን እድገትና መሻሻል ያሳልጣሉ። የለውጡን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የጊዜና ሌሎች ግብዓቶች እጥረት እንዳይፈጠር ይጠነቀቃሉ። ለስኬት ያልታደሉት መሪዎች ግን ትኩረታቸው ውጤት ላይ ብቻ በመሆኑ ውጤቱን የሚያስገኙት ሰዎች ሊያገኙት የሚገባውን ድጋፍ ይዘነጉታል።

 ጥሩ የለውጥ መሪ ቀትረ-ቀላል አይደለም፤ “ትከሻው ከባድ” እና ግርማ ሞገስ ያለው ነው። ሰውን የመማረክና ቀልብን የመሳብ ችሎታ ሊኖረው ይገባል። ለለውጡ የሚረዱ አስፈላጊና ተገቢ ሰዎችን መምረጥና የለውጡን ርዕይ ማጋራት መደበኛ ስራው ነው። ለውጥን ያደናቀፉ መሪዎች የተወሰኑ አካላትን (በተለይም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን) አግባብቶ የለውጡ አጋዥ ከማድረግ ይልቅ በማራከስ፣ በማዋረድ፣ በማዋከብና በማሳደድ ባህርያቸው የታወቁ ናቸው።

 ውጤታማ የለውጥ መሪ ሁሉን አውቃለሁ ባይ አይደለም። ለሁሉም ጥያቄ መልስ አለኝ ከሚል ተዓብዮ የራቀ ነው። ብዙ ጥያቄዎችን የሚጠይቅና በመደበኛውም ይሁን በሌላ መንገድ መልስም ግብረ-መልስም የሚሻ ነው። በዚህ መልክ የተገኙት ግብዓቶች ለውጡን በመምራት ሂደት ተከታታይ የሆኑ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ይረዳሉ። ለውጥን በአግባቡ የማይመሩ ሰዎች ይህን ከማድረግ የተቆጠቡና ካጋጣሚው ለመጠቀም ያልቻሉ ናቸው።

 በአጠቃላይ በለውጥ አመራር ከፍ ሲል ከተዘረዘሩት ዋና ዋና ባህርያት ባሻገር የአመራር አሽክላዎችና መስመር-አሳች ደንቃራዎች በመባል የሚታወቁ ሌሎች ባህርያት አሉ። የሆነው ሆኖ የለውጥ አማጪዎች ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ ከፈለጉ በየደረጃው በሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የየድርሻቸውን መፈጸም እንዳለባቸው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በየደረጃው የሚከናወኑ ተግባራትም መለየት አለባቸው። በሀገራችን የሚከናወነው የለውጥ ሂደት በላይኛው እርከን ላይ ብቻ የተወሰነ ነው የሚል ሰፊ ትችት አለ። ትችቱ እውነት ቢሆንም ለውጡን ወደታችኛው እርከን የማዝለቁ ተግባር ጊዜን ይፈልጋል። ሂደቱን ማገዝ ተገቢ ነው። ትዕግስትም አስፈላጊ ነው፣ ግን ትዕግስቱና ትችቱ ልኩ የት ድረስ ይሆን?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top