የጉዞ ማስታወሻ

ከኖርዌይ ደራስያን ማኅበር ትውልደ ሶማሊያዊቷ ተሸላሚ ደራሲ ሶማያ ይርዴ አሊ ማስታወሻዬ

የኖርዌይ ደራስያን ማኅበር በቅርቡ እ.አ.አ. ከማርች 25 – 26 ዓመታዊ ጉባዔውን አካሂዷል። ይህ በኦስሎ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በዝነኛው ብሪስቶል ሆቴል ውስጥ የተካሄደው ዓመታዊ ጉባዔ ለ125ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ማኅበሩ እ.አ.አ. በ1894 መቋቋሙን ታሪኩ ያስረዳል።

ለዚህ ጉባዔ የወጣውን ጠቅላላውን ወጪ የሸፈነው ማህበሩ ነው። ወጪው የ140 ተሳታፊዎችንና የተጋባዥ እንግዶችን መኝታ፣ ቁርስ፣ ምሳና እራት ያጠቃልላል። ማህበሩ ባጠቃላይ 647 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከዋናው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሌላ አምስት ንኡሳን ኮሚቴዎች አሉት። እነሱም የሥነ ጽሑፍ፣ የኢኮኖሚ፣ የአስተዳደር፣ የዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማትና የምርጫ አስፈጻሚ ምክር ቤቶች ናቸው።

 እንደወትሮው ሁሉ፣ በዘንድሮውም ጉባዔ የተለያዩ አጀንዳዎች ቀርበው ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆን፤ በሞት የተለዩ አባላትን በሕሊና ጸሎት ማሰብ፣ አዳዲስ አባላትን ተቀብሎ በጉባዔው ማጽደቅ፣ አባላት የጡረታና የህመምተኝነትን ደመወዝ በደራሲነታቸው የሚያገኙበትን ዝርዝር ጥናት ተወያይቶ ማጽደቅ፣ የገንዘብ ድጎማ (ክፍያ) ለደራሲው ሥራ ወሳኝ በመሆኑ የባሕል ሚኒስቴር ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥበት ውሳኔ ማስተላለፍ፣ የዓመቱን ምርጥ ደራሲ መሸለም፣ የዓመቱን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት መስጠት፣ የ2019 ዓ.ም.ን በጀት ማጽደቅና የሥራ ጊዜያቸውን በጨረሱ አመራሮች ምትክ አዳዲሶችን መርጦ መተካት ነበሩ።

በዚህ ዓመት አንድ ወጣት ደራሲ በምርጥ ሥራው የ‹‹ቴሪዬ ቬሳስ‹‹ን ሽልማት ሲያገኝ፤ ወጣቷ ሶማሊያዊት ደራሲ ሶማያ ይርዴ አሊ ደግሞ የ2019 ዓ.ም.ን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት ተቀብላለች። ሶማያ እ.አ.አ. በ2005 ዓ.ም. ወደ ኖርዌይ የመጣች ሲሆን፤ በአጭር ዓመታት ውስጥ የኖርዌይን ቋንቋ ተምራ ሦስት መጻሕፍት ጽፋበታለች። ሶማያ የ25 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ በግጥሞቿና ወጎቿ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሂስ በማቅረብ ተቃዋሚና ደጋፊም ያፈራች ጠንካራ ብእርተኛ ነች። ይህን ዘንድሮ ሶማያ ያሸነፈችውን ሽልማት፣ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንና (እ.አ.አ. በ2005) ኤርትራዊ- እስዊዲሹ ዳዊት ይስሃቅ (እ.አ.አ. በ2009) ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ሶማያ የተዘጋጀላትን ያሸናፊነት ዲፕሎማና የ200 ሺህ ክሮነር ቼክ ከማህበሩ መሪ ከወ/ሮ ሃይዲ ማሬ ክሪዚንክ እጅ ተቀብላለች። ጉባዔተኛውም ከመቀመጫው በመነሳት፣ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ይሁንታውን ገልጾላታል። ይህ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት ማህበሩ ከ25 ዓመታት በፊት የተመሰረተበትን አንድ መቶኛ ዓመት ሲያከብር፣ የባህል ሚኒስቴር በያመቱ እንደ ሽልማት ሲሰጠው የቆየ ነው። በ100 ሺህ ክሮነር ተጀምሮ የነበረው ሽልማት፣ ዛሬ 200 ሺህ ደርሷል። ማህበሩ በዓለም አቀፍ ኮሚቴው አማካኝነት በዓለም ዙሪያ ለብእር ነጻነት የታገሉ ደራስያንን እያፈላለገ አወዳድሮ ፣ ላሸናፊው ገንዘብና ዲፕሎማ ያበረክታል።

ማኅበሩ ለዘንድሮው የ2019 ዓ.ም. በጀቱ 27,817,000 ክሮነር (ሃያ ሰባት ሚሊዮን ስምንት መቶ አሥራ ሰባት ሺህ ክሮነር በገቢነት የታሰበ ሲሆን፤ በወጪ ደግሞ የ30,727,500 ክሮነር (ሰላሣ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሃያ ሰባት ሺህ ክሮነር) ግምት ተይዟል። የማህበሩ ገቢ ካባላት መዋጮ፣ ከተቋማት የድጎማ ገንዘብ፣ ከግል የቅጂ ተጠቃሚዎች ማካካሻ፣ ከመጻሕፍት ክለቦች ገቢ፣ ከይፋዊ የመንግሥት ድጎማ፣ ከግል ድርጅቶች ድጎማ፣ ከቤት ኪራይና ከመሳሰሉት ገቢዎች የሚገኝ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top