አጭር ልብወለድ

“አፋልጉኝ”

ሰማዩ ላይ የተቋጠረው ደመና ዝናብ ከጣለ በኋላ ድራሹ እንደሚጠፋ መገመት ይቻላል። ጥቁሩን ሰማይ ገደላ ገደልና ተራራማ መልክዓ ምድር ያስመሰለው ደመና ህዋውን ሌላ ገፅታ አላብሶታል። ደመናው ሊዘረግፈው የቋጠረው ዝናብ በእርግጥም ህዋውን አክብዶታል፤ በዚህ ላይ በነፋስ የታጀበ ነጐድጓድ እያከታተለ ያጉረመርማል። ጣልኩት የሚለው ደመና ከሚገፋው ሞገደኛ ነፋስ ጋር ይታገላል። ሽቅብ ሲመለከቱት ያረገዘው ደመና፣ የሚያፏጨው ነፋስ ከዝናቡ ጋር የሚያደርገው ትግል በራሱ አስጨናቂ ነው።

 ጀንበር የዕለቱን ተግባሯን አጠናቃ ጠልቃለች። ጀንበርን እንደዚህ ዓይነቱ ደመና እንደ ጋቢ ነው የሚሽፍናት። በእርግጥም ውሽንፍሩ ጀንበርን ጨምሮ ለብዙ ፍጥረታት የበላይ መሆኑን የሚገልፅ ነው የሚመስለው -ዛፎች ያረግዳሉ፣ ጣራዎች ይርገበገባሉ፣ ቅጠሎች ይረግፋሉ። የምድርን አፈር ሳይቀር ይጠርገዋል- ሞገደኛው ነፋስ።

ቀጣዩ ክረምት ከባድ እንደሚሆን ብዙ ሰዎች ከወዲሁ ተንብየዋል። የአየር ጠባዩ መቀየር ምክንያት ሆኖ ይመስላል ክረምቱ ቀድሞ ገብቷል። ወርሃ ሰኔ ላይ አስቀድሞ የሚደርሰው የፎገራ የመስኖ በቆሎ እሸት በዚህ ወቅት በየመንገዱ ዳር እየተጠበሰ ይሸጣል። ቤቱ ወስዶ መጥበስ ለሚፈልግም እንዲሁ በየመንገዱ ዳር የጉልት ገበያ ተከምሮ የገዥ ያለህ ይላል። በቆሎ ሻጮች ለአላፊ አግዳሚው፣

 “አለች እሸት… እሸት እሸት ቅመሱ፤ ጋሸ ጣፋጭ እሸት ነው” በማለት ከማሻሻጣቸው ሌላ፣ የሚጠበሰው በቆሎ እንደ ርችት፣ “ደሽ… ደሽ… ደሽ ደሽ…” እያለ በራሱ ገዥ ይጠራል።

 እንዲህ በሚያስፈራ ዝናብና ወጀብ ታጅቦ “ደረስኩ ደረስኩ” የሚለውን ዝናብ ጋቢዬን ተከናንቤ የተጠበሰ በቆሎ በመብላት ማሳለፍ ያዝናናኛል። እንዲህ ካላደረግኩ ደግሞ ብርዱን የምቋቋመው አይመስለኝም። ሰማዩን በተከታታይ ብልጭታ እያደመቀ ከሚያጉረመርመው ነጐድጓድ ጋር እሽቅድድም የገጠመው የባህርዳር ነዋሪ ወደየቤቱ ይጣደፋል። ወጀብ የቀላቀለው ነፋስ ጃንጥላዎችን ሳይቀር አቅም ነስቷቸዋል። ከነፋሱ ጋር የሚታገለውን ጃንጥላዋን ዘርግታ ወጀቡን እየተከላከለች በቆሎ ወደምትሸጠው ሴት ተጠግቼ፣

 “እቴ በቆሎውን እሸት ስንት ስንት እያልሽው ነው?” አልኳት የተጠቀለለውን የበቆሎ እሸት ለመምረጥ ሸብረክ ብዬ ቁጭ እያልኩ። ከመብራት ምሰሶ ጥግ በቆሎ እሸት የሚሸጡት ሴት በዕድሜ የገፉ አዛውንት መሆናቸውን ልብ አላልሁም ነበር።

 “ይቅርታ የእኔ እናት እንደ ልጅ እግር ቆጥሬ አንጠልጥየ ጠራሁዎት” አልሁ ለድፍረቴ ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ በማሰብ።

 “ግዴለም የኔ ልጅ ከገዛኸኝ ይበቃኛል። ከዚህ ወዲያ ማክበር አለ ብለህ ነው! በዚህ ውሽንፍር ገዝቶኝ ከሚሄድ ሰው ሌላ አክባሪ አይኖረኝም። ደግሞ ጥሩ የባህር እሸት በመስኖ የበቀለ ትኩስ እሸት ነው። ጣፋጭ ነው በኔ ይሁንብህ።”

 የሴትዮዋ “እባክህን ግዛኝ” የሚለው ተማፅኖ በቆሎ እሸቱን ሳልገዛቸው እንዳልሄድ ቀፍድዶ አሰረኝ። የእባክህ ግዛኝ ተማጽኗቸው ብቻ ሳይሆን በቆሎ ሳልገዛ ወደ ቤቴ አልገባም ብዬም ወስኛለሁ።

 “እና ሶስቱን ስንት እያሉት ነው?” “ይኸው ሶስቱ እነዚህ በአንድ ላይ የታሰሩት አስር ብር ነው የሚሸጡት።”

 “ስድስቱ ሃያ ብር ማለት ነው?” “መሆኑ ነው። ስድስት ከገዛኸኝማ ምን ቀረኝ ብለህ ነው። ብዙ ገዛኸኝ ማለት ነው እኮ የኔ ልጅ።”

 “ለነገሩ ለነገም ልግዛ ብዬ ነው እንጅ ለዛሬማ ሶስቱ በቂ ነው፤ ለእኔና ለሚስቴ።”

“ግዴለህም ለነገ ማለት መልካም ነው የኔ ልጅ።” አሉ።

 “ቢሆንም ከሰነበተ ደግሞ ይደርቃል፣ እሸትነቱ ይጠፋል።”

 “ሸለፈቱን አትግለጠው እንጅ አይደርቅም።” “እርስዎ ካሉ መልካም ልግዛዎት የእኔ እናት።”

 “እንዴታ የኔ ልጅ ደግሞ ብዙ ነው የገዛኸኝ። ለእኔ ትልቅ እገዛ ነው። አብዛኛው ሰው እንዲህ በአንድ ጊዜ ደፍሮ ስድስት ፍሬ አይገዛም። በጊዜም ቤቴ እገባለሁ።”

ለአዛውንቷ ሃያ ብሩን ስሰጣቸው በደስታ ነበር የተቀበሉኝ። ቀጠሉና በስሜት ምርቃቱን ደረደሩት።

 “ተባረክ፣ ብርህ እንደዚህ በቆሎ ይንዥርቀቅ። ይኸን ወጀብ የፈጠረ፣ ይኸን ባለግርማ ደመና እንዲህ እንደተራራ የቆለለው አምላክ ይርዳህ። የመጨረሻውን ዕድሜህን የተሻለ ያድርግልህ። የኔ ልጅ ለሰው ልጅ ሀዘኑን የሚያከብደው ልቡ የሚሰበረው እንዲህ እንደ እኔ ጉልበቱ እና ዓይኑ ሲደክም፣ ሆዱን ለመሙላት መውጣት መውረዱ ነው። ቢሆንም ተመስገን ነው፤ ይኸው ከውሽንፍሩ ጋር እየታገልኩ ሰርቼ ማደር ችያለሁ።”

 “ልጆች የሉዎትም? እነርሱ አያግዙዎትም?” አከታትዬ ጠየቅኳቸው።

 “በማን ዕድሌ! ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ በአጠቃላይ ሶስት ልጆች አፍርቼ ነበር። እንደምታየኝ ለፍቼ ማስኜ አሳደግኩ። ሁሉንም በየተራ ጨካኙ ሞት ነጠቀኝ። አንድ በአንድ ጊዜ በላብኝ። ለእንደ እኔ ዓይነት እናት የልጅ ሞት ምን ያህል እንደሚፀና አስበው? ታዲያ በእነርሱ ሞት የተነሳ ሐዘን ክፉኛ ነው እንክትክት አድርጐ የሰበረኝ።” ድምፃቸው ትካዜያቸውን ይገልፅ ነበር።

 “እና ሌላ የሚያስጠጋዎት ዘመድ የለም?”

 “እርሱማ የችግሬን መደራረብ፣ የሐዘኔን መፅናት አይታ አንድ የእህቴ ልጅ አስጠግታኝ ነበር። ጥቂት ጊዜ ከእርሷ ጋር አሳልፌያለሁ። ሆኖም ራሴን ችዬ ለመሥራት በማሰብ ከቤቴ ወጥቸ ከጠፋሁ አንድ ወር ሆነኝ። ስላደረገችልኝ እርዳታና ስላሳየችኝ ፍቅር በእውነቱ መርቄያታለሁ። በዚህ ጭንቅ ጊዜ እርሷ ነበር የደረሰችልኝ። ግን ከእሷው ጋር ተጠግቸ ረጅም ጊዜ መኖር ከበደኝ። ከእርሷ እንድርቅ ደግሞ በፍፁም አትፈልግም። አሁን እዚህ መሆኔን ብታውቅ አስገድዳ ነው የምትወስደኝ። ይኸው አሁን ትንሽ በቋጠርኳት ሳንቲም ሥራ ጀመርኩ። ወቅቱ የእሸት በቆሎ ነው። አሁን በቆሎ እየሸጥኩ ነው ተመስገን እንዳንተ የሚገዙኝ አይጠፉም።”

 ሰማዩ እንደፎቶ ካሜራ የብርሃን ብልጭታ ከበላያችን ላይ እየደጋገመ ያበራል። በዚህ ጊዜ ነበር የአዛውንቷን በቆሎ ሻጭ የተሸበሸበና ባለመስመር ምስኪን ፊታቸውን የመመልከት አጋጣሚ ያገኘሁት።

 በእርግጥም ሴትዮዋ በአፋልጉኝ ማስታወቂያ እየተፈለጉ መሆኑን፣ በየስልክ እንጨቱና ማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ፎቷቸውና ስማቸው መዘራቱን አያውቁም። የሚገርመው በቆሎ እሸት ከሚሸጡበት አጠገብ ከሚገኘው የስልክ እንጨት ምሰሶ ላይም እንዲሁ በጉልህ “አፋልጉኝ” የሚል ጽሑፍና ፎቷቸው ተለጥፏል።

 በእርግጥም የሚፈለጉት ሴት በቆሎ እየሸጡ ያገኘኋቸው ይሆኑ? . . . ብዙ ነገራቸው ያው ተፈላጊዋን ይመስላሉ። ደግ ነገር ልሥራ ላለ ይህ አጋጣሚ መልካም ነው። “አፋልጉኝ” ከሚለው ጽሑፍና ከተፈላጊው ጥቁርና ነጭ ፎቶ በታች በጉልህ በተፃፈው ስልክ ቁጥር “ተፈላጊዋን ወ/ሮ አገሬን ላገኘ ውለታውን እንከፍላለን። እባካችሁ አዛውንቷን ወ/ሮ አገሬን ያያችሁ ደውሉልን!” ይላል።

 በእርግጥ ተፈላጊዋ ወ/ሮ ሀገሬ ራሳቸው መሆናቸውን ላለመጠራጠር ስማቸውን መጠየቅ ይኖርብኛል ብዬ አሰብኩና፣

 “እናቴ ይኸን በቆሎ ነገ ከነገ ወዲያም ተመልሸ መግዛቴ አይቀርም። ስምዎን ማን አሉኝ?”

“ስሜ ያስፈልጋል የኔ ልጅ? ደግሞ የአንዲት በቆሎ ሻጭ ባልቴት ስም ምን ይጠቅም ብለህ? ተጠቀመህስ ሀገሬ ነው።”

 “መልካም እማማ ሀገሬ ነገ ከነገወዲያም እመጣለሁ። እገዛዎታለሁ! አይዞዎት! ደህና ይደሩ! ወደ ቤቴ ልሩጥ ዝናቡ መጣሁ መጣሁ እያለ ነው።”

“ደህና እደር የኔ ልጅ! እኔም ከዚህ በኋላማ ወደ ማደሪያዬ ልጠጋ።”

የበቆሎ እሸቱን አንጠልጥየ በንፋሱ ሃይል አቅጣጫውን እየቀያየረ የሚዘንበውን ስስ ዝናብ ሽሽት ወደ ቤቴ ተጣደፍኩ፣ ነገን እያሰብኩ። ግን አላስቻለኝም። ስልኬን አወጣሁ።

 ወዲያው ደወልኩ። በስልኩ ውስጥ ቀጭን ሰርሳሪ የወንድ ድምፅ “ሄሎ ማን ልበል?” አለ።

“ጤና ይስጥልኝ የኔ ጌታ ስልኩን ያገኘሁት ካፋልጉኝ ማስታወቂያ ላይ ነው። ተፈላጊዋን ወ/ሮ ሀገሬ ያሉበትን ልጠቁማችሁ?”

 “ወ/ሮ ሀገሬ . . . ኧረ የጠፋን ሰው የለም! . . . የኔ ወንድም ቁጥሩን ተሳስተው ይሆን?” አለ ሰውየው በትህትና። በእርግጥም አንድ ቁጥር ተሳስቼ ነበር። በድጋሚ ቁጥሩን አስተካክዬ ደወልኩ። ዝናቡ አሁንም ደረስኩ ደረስኩ እያለ ነው።

 “የደወሉላቸው ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው!” የሚል የመርዶ ድምፅ ተከተለ። ስልኬን ዘጋሁ። ዝናቡ ጊዜ የሚሰጠኝ አይደለም። አዛውንቷን በቀጣዩ ቀን እዚሁ ቦታ ስለማግኘቴ እርግጠኛ አይደለሁም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top