አድባራተ ጥበብ

ነገረ ስዕል ወ ጥበባት

የስዕል ጥበብ “በዚህ ቀንና ቦታ፣ በእነ እንትና ተጀመረ” ለማለት ያስቸግራል። ነገር ግን የሰው ልጅ የስዕል ጥበብን ከአኗኗር ዘይቤው ጋር በማያያዝ በሂደት ጥበቡን እያሻሻለው፣ እየረቀቀበትና እየተራቀቀበት ሄደ። የስነ ጽሑፍን ያህል ሰአሊው ሊገልጽ የፈለገውን ነገር እጅግ በረቀቀ መንገድ በአንዲት የሸራ ላይ ስዕል ይናገራል። ስዕል እንደ ስነጽሑፍ ሁሉ ይነበባል። ጥበበኞቹ በስዕል ጥበብ ቅኔን ይቀኙበታል። ከባድና አንገብጋቢ መልእክቶችን ያስተላልፉበታል። ስዕል ፖለቲካ ነው፤ የህዝብ ድምፅና ብሶት ይነገርበታል። ስዕል ሕይወት ነው፤ ብዙዎች ይኖሩበታል። ስዕል ፍስሐ ነው፤ ብዙዎች ይደሰቱበታል፣ ይማረኩበታል፣ ይማርኩበታል። በስዕል ጥበብ መንፈሳዊ ህይወትና መንፈሳዊያን ይገለጡበታል። የመሬት አቀማመጥ፣ የሀገር መልክአ ምድራዊ ውበትና ድንቅ አፈጣጠር ይተረክበታል። የአለማችንና የሰው ልጅ ታሪክ ይተረክበታል። በአጠቃላይ የህይወት ውጣ ውረድና እንቶ ፈንቶ ይተነተንበታል።

የስዕል ቅድመ ታሪክ

የሰው ልጅ የስዕል ጥበብን እንዴት እንደጀመረ ስንመለከት ታሪኩ ወደ 30 ሺ አመተ አለም ያሻግረናል። በነዚህ ዘመናት ውስጥ የሰው ልጅ እንደዛሬው ዘምኖ በህንፃ መኖር ከመጀመሩ በፊት በዋሻ ውስጥ በሚኖርባቸው በነዚያ የጋርዮሽ ጊዜያት ነበር የመጀመሪያዎቹን ጥበበኞች የስዕል ጥበብ የጠራቻቸው። ያ ዘመን የሰው ልጅ በአደን ራሱን ያስተዳድር የነበረበት በመሆኑ እነዚህ የስዕል ጠቢባንም ስለ ዱር አራዊቱ አይነትና ባህሪ፣ ስለአደን ጥበቦችና ስለአዳኞችና ታዳኞች ድራማ ብሎም ስለወቅቱ የሰው ልጅ አለባበስና አኗኗር በሸራ ሳይሆን በየዋሻዎቹ ግርግዳና በየ ድንጋዩ ላይ የየአካባቢያቸውን ግብአት በመጠቀም ይስሉ ነበር። እነዚህ የስዕል አይነቶች ዛሬም ድረስ በደቡብ ፈረንሳይና በምስራቅ ስፔይን በጥሩ ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ። እንዲህ አይነት ጥንታዊ የስዕል አይነቶች በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ይታያሉ። እነዚህ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የዋሻ ስዕሎች በተለይም በስፔኗ አልታሚራ ዛሬም ድረስ ለእይታ ክፍት ናቸው።

የሊዮናርዶ ዳቪንቺ ስዕል “የመጨረሻው እራት”

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከነዚህ ዋሻዎች በአንዱ በአዳኙ ጦር ክፉኛ የተጎዳ ጎሽ ያለአንዳች ማንገራገር እጁን የሰጠ ይመስላል። ስእሉ በቀይና ቡኒ ቀለማት ተዥጎርጉሮ የጎሹ ቅርጽ ግን በጥቁር ቀለም ደምቋል። የዘመኑ ሰአሊያን የቀለም ግብአት የሚያገኙት የተለያየ ቀለም ካላቸው የአፈር አይነቶች ነበር። እነኚህ የአፈር አይነቶች (ቀይ፣ መረሬ፣ ሸክላ፣) በተለያየ ሁኔታ ድንጋይ ላይ ከተፈጩና ቅባትነት ካለው የእንስሳት ስብ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ በአርጩሜ መሳይ ቀጭን እንጨት በመንከር ይሳላል። በአርጩሜ መሳዩ እንጨት እየተሳለ ስእሉ መሀል ላይ ቀለሞቹ ከእንስሳት ፀጉር ወይም ከተክሎች በሚሰሩ ብሩሽ መሳይ ነገሮች ይቀባሉ። እንደሚባለው ከሆነ የዛሬ 30 ሺ አመት ገደማ የሰው ልጅ ለስዕል ጥበብ የሚያገለግሉ መሰረታዊ መሳሪያዎች ፈልስፏል። እነዚህ የስዕል መሳሪያዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየተሻሻሉና እየተራቀቁ እዚህ ዘመን ላይ ደርሰዋል። ይሁንና ለስዕል መሳያ የሚሆኑትን የመጀመሪያዎቹን መሳሪያዎች ተግባራዊ ያደረጉት እነዚያ የጥንቶቹ የዋሻ ውስጥ ሰአሊያን ናቸው።

 የግብፃውያንና ሜሶፖታሚያውያን የስዕል ጥበቦች

 ታሪክ እንደሚነግረን ለአለማችን የመጀመሪያዎቹን የሰው ልጅ ስልጣኔዎች ካስተዋወቁ ህዝቦች መካከል ግብፃውያን ይጠቀሳሉ። ጥንታውያኑ ግብፃውያን ማን እንደነበሩና እንዴት እንደኖሩ ካስቀሩልን መጣጥፎቻቸውና የኪነ ጥበብ ስራዎቻቸው ለመረዳት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች አንድ ታላቅ እምነት ነበራቸው። ሰው ከሞተ በኋላ አካሉ መበስበስና መፈራረስ የለበትም፤ ምክንያቱም ከሞተም በኋላ በህይወት ስለሚኖር። ከዚህ የጠበቀ እምነታቸው የተነሳም በተለይም ንጉሶቻቸው ወይም ፈርኦኖቻቸው (the pharose) ሲሞቱ አስከሬናቸው እንዳይበሰብስና እንዳይፈርስ በሚያደርገው የማሚ ቴክኖሎጂ (mummy) በመጠቀም ከተለያዩ ንብረቶቻቸውና አገልጋዮቻቸው ጋር በነዚያ አስገራሚ ፒራሚዶቻቸው ውስጥ ይቀበሩ ነበር። በዚያን ዘመን የግብፅ የስዕል ጠቢባን ይህን የግብጾች እምነት የሚያንፀባርቁና ሰው ከሞተ በኋላ በህይወት የመኖሩን ጉዳይና የህይወትን ቀጣይነትን የሚያመለክቱ እንዲሁም የሞተ ሰው በድንጋይ መቃብር ውስጥ መኖሩን የሚያሳዩ ስዕሎችን ይስሉ ነበር። እነዚህን ስዕሎች በሰዎች የመቃብር ድንጋዮች ላይና በግድግዳዎች ላይ ይስሉም ነበር። ይህ አይነት የስዕል ጥበብ በግብፅ ለበርካታ ዘመናት ዘልቋል።

ከዚህ በኋላ በአንዳንድ አካባቢዎች በጭቃ የተለሰነን የቤት ግድግዳ በውሀ በተበጠበጠ ቀለም ማሳመር ተጀመረ። እነዚህን በተለያዩ የቀብር ስፍራዎችና ግድግዳዎች ላይ የሚሳሉ ስዕሎችን ከእፅዋትና ከእንስሳት ውጤት በሚገኙ ቀለማትና ማጣበቂያ መሰል ግብአቶች የሚገኙ ናቸው። በነዚህ ግብአቶች የሚሳሉ ስዕሎች ሳይበላሹ ዘመናትን በመሻገር የተሳሉበትን ወቅት ነጋሪ ለመሆን ችለዋል። በ1450 አመተ አለም በግብጽ ቴብስ በምትባል ጥንታዊ የወንዝ ዳርቻ ስፍራ ይኖሩ የነበሩ አዳኞች በመቃብሮቻቸው ግድግዳ ላይ የተሳሉ ስዕሎች ዛሬም ድረስ ተጠብቀውና ለትውልድ ተሻግረው ይገኛሉ። አዳኞቹ ግብፃውያን ታዲያ በስዕሎቻቸው ግዙፍ አሞራዎችን ፈርተው ሲሸሹና አሳን በጦር መሰል ሹል ነገር ሲያድኑ ያሳያሉ።

 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3200 እስከ 332 ዓመተ አለም ድረስ ያለው ጊዜ የሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። ሜሶፖታሚያ በመካከለኛው ምስራቅ በጢግረስና ኤፍራጠስ ወንዞች መሀል ላይ በሚገኝ ሸለቋማ ስፍራ የተከሰተች የስልጣኔ መንደር ናት። ሜሶፖታሚያ በወንዝ ዳር በሸክላ አፈር የተገነባች የአለማችን ሌላኛዋ የሰው ልጆች የስልጣኔ አሻራም ሆና ትወሳለች። የሜሶፖታሚያ ሰዎች በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁና በእሳት የተቃጠሉ የሸክላ ጥበብ ውጤቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለም አበርክተዋል። ይህም የሰው ልጅን የስነ ጥበብ ስልጣኔ አንድ እርምጃ ወደፊት አራምዶታል።

የኤጂያን ስልጣኔ ዘመን

 በአለማችን ሶስት የስልጣኔ እርከኖች ተስተውለዋል። የመጀመሪያው የድንጋይ ዘመን ሲሆን በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ድንጋይን ለተለያዩ የእለት ተእለት ስራዎቹ በመሳሪያነት ተጠቅሞ ኑሮውንና ህይወቱን ይገፋበት ነበር። ሁለተኛው የነሀስ ዘመን ነው። በዚህ ዘመንም ሰዎች መጠነኛ ስልጣኔ አሳይተው ድንጋይን እንደመሳሪያ ከመጠቀም ወጥተው ነሃስን እያቀለጡ ለኑሯቸው መገልገል የጀመሩበት ጊዜ ነው። ሶስተኛው ደግሞ የብረት ዘመን ሲሆን በዚህም ጊዜ ሰዎች ብረትን እያቀለጡ የተለያዩ መሳሪያዎችን ስራ ላይ ማዋል የጀመሩበት ወቅት ነበር።

በመዳብ የስልጣኔ ዘመን ኤጂያን የሚባሉ ህዝቦች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በ1500 ዓመተ አለም ግሪክ ውስጥ ክሬት በምትባል ደሴት ባህር ዳርቻዎች አካባቢ ይኖሩ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። ኤጂያውያኑ በተጓዳኝ የጥንቶቹ ግብጻውያንና ሜሶፖታሚያውያን በኖሩበት ዘመን የኖሩ ህዝቦችም ናቸው። እነዚህ የክሬት ነዋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ምድር ስልጣኔን የጀመሩ ህዝቦች እንደሆኑ ይነገራል። የእደጥበብ ውጤቶች፣ መፃፍና ማንበብ በዚች ደሴት እንደተጀመረና በኋላ ላይ አውሮፓውያን ይህን ስልጣኔ ወስደውና ወደራሳቸው መልሰው እንደሰለጠኑበት ይወራል። የአርኪዎሎጂ ባለሙያዎች የክሬት ደሴት ንጉስ የነበረውን የንጉስ ሚኖስ ቤተመንግስትን በቁፋሮ አግኝተዋል። በቁፋሮውም በዚያ ዘመን የተሳሉ የስዕል ውጤቶችን ለማግኘት ችለዋል። በዚያ ዘመን እነዚህ ህዝቦች ከአሸዋና የተለያየ የቀለም ይዘት ካላቸው የአፈር አይነቶች ድብልቅ በመጠቀም የተለያዩ አይነት ስዕሎችን በግድግዳ ላይ ይስሉ ነበር።

ስዕሎቹ የሚሳሉት ግድግዳዎች ሳይደርቁ በእርጥቡ ነው። በዚህ አይነት ሁኔታ የተሳለው ስዕል ቆይቶ የደረቀው ግድግዳ አካል ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ አይነት ስዕሎች በጣሊያንኛ ፍሬስኮ ይሰኛሉ። ይህም አዲስ ወይም ትኩስ የሚል ትርጉም አለው። የክሬት ሰዎች ስዕሎቻቸውን ለመሳል የፈኩና ደማቅ ቀለማትን ይጠቀሙ ነበር። በተለይም ቢጫ፣ ቀይ፣ ሰማያዊና አረንጓዴ ቀለሞች ምርጫዎቻቸው ናቸው።

 የግሪክና የሮማ የጥንት የአሳሳል ጥበብ

ጥንታውያኑ የግሪክ ሰዎች የቤተመቅደሶቻቸውንና የቤተመንግስቶቻቸውን ግድግዳዎች በተለያዩ ስዕሎች የማስጌጥና የማስዋብ ልምድ ነበራቸው። ግሪካውያን ጠጠሮችን ወይም ቁርጥራጭ ሸክላዎችን በዲዛይን በመስራት ግድግዳ ላይ የማስቀመጥ ልምድ አላቸው። በተለይ ሞዛይክ የሚባለውን የአሳሳል ዘይቤ የጀመሩት ግሪኮች ናቸው። ሞዛይክ ማለት የተለያዩ የቀለም ይዘት ያላቸው የድንጋይ አይነቶችን ወይም የመስታዎት ቅርጾችን አንድ ላይ በመገጣጠም ለየት ያለ ውበት ያለው ምስል መስራት ማለት ነው። በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰአሊያን ስራዎችና የህይወት ዘይቤያቸው በዘመኑ ሰዎች ዘንድ በስፋት ይታወቅ ነበር። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዚያ ዘመን ከተሳሉ ስዕሎች ዛሬ የሚገኙት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወድመዋል። ግሪኮች በመቃብር ቦታዎች ላይ ስዕል የመሳል ባህል አልነበራቸውም። በተለያዩ ቀለማት፣ ዲዛይኖችና ስዕሎች ያሸበረቁና የተዋቡ የአበባ መያዣና ጌጠኛ ዋንጫ መሳይ ነገሮች ከግሪካውያን የተገኙ ጥበቦች ናቸው። እነዚህ የጥበብ እቃዎች ዛሬም ድረስ የዚያን ጊዜ ሰዎችን ጥበብ የሚያሳዩ ህያው ምስክሮች ናቸው። በተለይም የሸክላ ስራ በግሪክ ዘመን በስፋት ይሰራ እንደነበር ይነገራል። እነዚህም በአብዛኛው የሸክላ አፈርን በማርና በዘይት በማሸት ይሰራሉ። የሸክላ ውጤቶቹ ለንግድ ወደ ሌሎች አገራት ከመላካቸው በተጨማሪ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ይመረቱም ነበር። የግሪኮቹ ስዕሎች በሂሳብ ቀመር የተደገፉ፣ ፈፅሞ የማይዛነፉና ይዘታቸውንና መስመራቸውን የጠበቁ ናቸው። በተለይም የአበባ መያዣ የሸክላ ውጤቶች መመረት የጀመሩት ከ1700 እስከ 700 አመተ አለም ባሉት ጊዜያት ነው። የሚሰሩትም በሰው እጅ ሲሆን በደንብ ተቀርፀው በላያቸው ላይ ምስል ይታተምባቸዋል።

79ኛው አመተ አለም የሮማውያን ዘመን ነው። የሮማውያን ስዕሎች በአብዛኛው ግድግዳና ኮርኒስ ላይ የሚሳሉ ናቸው። እነዚህ የግድግዳና ኮርኒስ ስዕሎች የሚገኙት እጅግ ባማሩ ቪላ ቤቶችና ህንፃዎች ውስጥ ነው። በዚያ ዘመን እነዚህ ቤቶች የሚገኙት ፖምፒና ሄርኩላኒዩም በሚባሉ የሮማውያን ከተሞች ውስጥ ነው። እነዚህ ሁለት ከተሞች ኋላ ላይ ቬሶቪውስ ከተባለው ተራራ አናት ላይ በፈነዳው እሳተገሞራ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸው ይነገራል። ሮማውያን የስዕል ጠቢባን መጀመሪያ የተለያዩ ስዕሎች የሚስሉባቸውን ግድግዳዎች በጥንቃቄ ይመርጣሉ። ግድግዳዎቹን በእብነ በረድ፣ በአሸዋና ኖራ ይለብጣሉ። ከዚያም የሚፈልጉትን አይነት ስዕል ይስላሉ። ስዕሎቻቸው በአብዛኛው ከግሪኮቹ ስዕሎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እነዚህ በፖምፒ የሚገኙና ንብረትነታቸው የማን እንደሆኑ ባልታወቁ ቪላዎች ውስጥ የተሳሉ ድንቅና ውብ የግድግዳና የኮርኒስ ላይ ስዕሎች ከተማዋ በ18ኛው መቶ ክፍለዘመን በቁፋሮ ስትገኝ አብረው የተገኙ ሲሆኑ የዘመኑን የስዕል ጠቢባን በእጅጉ አስደንቀዋል። የግሪክና የሮማ ሰአሊያን በተለይም የሰውና የእንስሳትን ምስል ይስሉ እንደነበር ምንጮች ያሳያሉ። የአሳሳል ዘይቤያቸው የግሪኮች ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ስዕሎች እንዳይበሰብሱ ተደርገው በግብፃውያን ሰአሊዎች የተሳሉ ናቸው። አንዳንዶቹም እስከዛሬ ሳይበሰብሱና ሳይበላሹ በአሌክሳንድሪያ ይገኛሉ። ስዕሎቹ በአብዛኛው አንድ ሰው ሲሞት እሱን በማስመሰል በእንጨት ላይ ሰም በማቅለጥ ለግለሰቡ ማስታወሻነት ይሳላሉ። ሰም በማቅለጥ የሚሳሉ የሰም ስዕሎች ሳይበላሹ ለረጅም ዘመናት የመቆየት ብቃት የኤጂያን ስልጣኔ ዘመን ስዕል አላቸው። እንደነዚህ አይነት ስዕሎች በተለይ በ2ኛው አመተ አለም የተሳሉ ቢሆንም ያን ያህል ዘመን ያስቆጠሩ ሳይመስሉ ዛሬም እንደ አዲስ የሚታዩ ናቸው።

 የክርስትና (ቤዛንታይን) ዘመናት ስዕሎች፣

 እንደሚታወቀው የሮማ ገናናነት ዘመን ማብቃት የጀመረው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወቅቱ ደግሞ የክርስትና እምነት እየተስፋፋ የመጣበት ነበር። በ313 አመተ ምህረት የሮማውያን ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን አምኖ ተጠመቀ። እናም ክርስትና የግዛቱ ህጋዊ እምነት ሆኖ ታወጀ። የክርስትና እምነት መስፋፋት ለስዕል ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የዘመኑ የስዕል ጠቢባንም የቤተክርስቲያናትን የውስጥ ግርግዳዎች መንፈሳዊ ይዘት ባላቸው ስዕሎች በማሳመር ስራ ላይ ተጠምደው ነበር። ቤተክርስቲያናትን ከማስዋብ ባለፈ መንፈሳዊ መጻሕፍትንም በተለያዩ ስዕሎች ማድመቅና ማሳመር የተለመደ ነበር። በክርስትና እምነት ጅማሮ ወቅት የነበሩት የስዕል ልሂቃን የአሳሳል ጥበብና ቴክኒክ ከግሪካውያኑ የአሳሳል ጥበብ ጋር ተመሳሳይ ነው። የተለያዩ የቀለምና የምስል ይዘት ያላቸው መስታዎት መሰል ቅርፆች በእርጥብ ኖራ ወይም ሸክላ ግርግዳ ላይ በአግባቡ አምረው እንዲሰኩ ይደረጋሉ። እነዚህ የቤዛንታይን ዘመን ስዕሎች በተለያዩ ቀለማት የደመቁና ያሸበረቁ እንጂ የገሀዱን አለም እውነታ በትክክል የሚያንፀባርቁ አልነበሩም። ቤዛንታይን በዛሬዋ የቱርክ ከተማ ኢስታንቡል አካባቢ የነበረች ጥንታዊ ከተማ ናት። በዚህ ዘመን ድንቅ የሆኑ በቀለማትና በውበታቸው የተሸለሙና ያጌጡ የቤተክርስቲያን ስዕሎች በመንፈሳውያንና ጠቢባን ይሳሉ ነበር። በተለይም በ547 አመተ ምህረት ከተሳሉ የግድግዳ ስዕሎች የቴዎዶራና ጁስቲኒያን ስዕሎች ከፍተኛ ዝናን ያተረፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ

 የመካከለኛው ዘመን ስዕሎች

የመካከለኛው ዘመን ከ6ኛው እስከ 11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ይህ ዘመን የጨለማው ዘመን በመባልም ይታወቃል። በነዚህ ጊዜያት በክርስትናው እምነት አካባቢ በርካታ ክርክሮች የተነሱበትና ያለመረጋጋት የታየበት ነው። በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜንና መካከለኛው አውሮፓ ባርባሪያን የሚባሉ ጎሳዎች አብዛኛውን የአህጉሪቱን አካባቢዎች መቆጣጠር ይጀምራሉ። በዚህም ምእራብ አውሮፓን በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታት ተቆጣጥረው ቆይተዋል። እነዚህ ሰዎች ደግሞ የራሳቸው የአሳሳልና የአነዳደፍ ዘይቤ አላቸው። ባርባሪያን በአብዛኛው ደራጎኖችንና ወፎችን በማነፃፀር የመሳል ባህል ነበራቸው። በዚህ ዘመን ፍሎረንስ በምትባል ጥንታዊት የጣሊያን ከተማ ይኖር የነበረው ሲማቡ የተባለ ጣሊያናዊ ሰአሊ በቤዛንታይን ዘመን ይሳሉ የነበሩ የአሳሳል ዘዴዎችን ዘመናዊ ለማድረግ ሞክሯል። በተለይ ማርያም ልጇን ክርስቶስን አቅፋና በቅዱሳን ታጅባ የሚያሳየውን ስዕል ይበልጥ ውብ አድርጎ ስሏል። በዚህ ዘመን ስዕሎች የሰው ልጅ አቋምና ተክለ ሰውነት እንዲሁም መልክ ይበልጥ ሰው የሚመስልበትን ቅርጽ ይዘዋል። ሲማቡም ስዕሎቹን ተለቅ አድርጎና አሳድጎ ስሏል።

 ሌላው የፍሎረንስ ከተማ ሰአሊ የነበረው ዝነኛው ጊዎቶ የቤዛንታይን ዘመንን የአሳሳል ስልት ሙሉ ለሙሉ በመተውና የራሱን መንገድ በመፍጠር የክርስቶስንና የእናቱን የማርያምን የአኗኗር ዘይቤ ስሎ ለእይታ አብቅቷል። ጊዎቶ ትክክለኛውንና እውነተኛውን የሰው ልጅ ስሜት በስዕል ጥበቡ አንፀባርቋል። በስዕሎቹ የሰው ልጅን መከራ፣ ሀዘን፣ ትካዜ፣ ስቃይና ደስታ አስቀምጧል። ጊዎቶ ለስዕሎቹ ማስዋቢያ የእንቁላል አስኳሎችን ተጠቅሟል። ስዕሎቹ ጥርት ያሉና ቀለማቱ የፈኩ በመሆናቸው የሰውን ቀልብ በቀላሉ መሳብ የሚችሉ ነበሩ። የእንቁላል አስኳል በተለይም ቀኑ ለምሽት ቦታውን ለቆ ፀሐይ ወደ ማደሪያዋ ስትገባና ብርሀን ደንገዝገዝ ሲል ያለውን ገጽታ ለማሳየት አገልግሏል።

አንፀባራቂው የዘይት ቀለም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት የእንቁላል አስኳል ለስዕል መሳያነት እንደቀለም አገልግሏል። በዚህም የተነሳ ጊዎቶ ለስዕል ጥበብ ትንሳኤ መሰረት የጣለ ሰአሊ እንደነበር ይነገራል። የቤልጂየም ዜጋ የሆነው አርቲስት ጃን ቫን ኢይክ ደግሞ ለስዕል መሳያ የሚያገለግለውን የዘይት ቀለም ለመስራት የሚያስችለውን መሰረት ስለመጣሉ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ጣሊያናዊው ማሳኪኦም በህዳሴው ዘመን ብቅ ካሉ የመጀመሪያዎቹ የሰአሊያን ትውልድ መሪዎች ውስጥ እንደ አንዱ የሚጠቀስ ነው። ሰአሊው በሀያዎቹ መጨረሻ እድሜው ከዚህ አለም በሞት ቢለይም በሳላቸው ጥበቦቹ የስዕል አብዮተኛነቱን አረጋግጧል።

 የግድግዳ ላይ ስዕል በህዳሴው ዘመን የታወቀ የአሳሳል ጥበብና ዘዴ ነበር። ይህ የአሳሳል ጥበብ ስእሉ ከተለያየ ማእዘን በቀላሉ እንዲታይ ይረዳል። በዚህ ዘመን በተለይም ፍራ አንጌሊኮ የተባለው ጣሊያናዊ ሰአሊ ማርያም ዘውድ ደፍታ ከነ ልጇ በመላእክት ታጅባ ያለውን ስዕል እጅግ በሚያምር ሁኔታ እንደሳለው ምሁራን ይገልፃሉ። ታዋቂው የስዕል አባት ሊዮናርዶ ዳቪንቺ የስዕል ጥበብን የተማረው በፍሎረንስ ከተማ ነው። ይህ ሰው የሚታወቀው ስዕልን በሳይንሳዊ መንገድ መስራት እንደሚቻል በማሳየቱና በዚህ ዘርፍ የራሱን ጥበባዊ ፈጠራ ለአለም በማስተዋወቁ ነው። ሆኖም ከዚህ ጠቢብ ስዕሎች አሁን ያሉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ከስዕሎቹም “የመጨረሻው እራት” ተጠቃሽ ነው። ይህ ስዕል ከ1495 እስከ 1498 አመተ ምህረት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በዘይት ቀለም እንደተሳለ ይነገራል።

ስፔን ውስጥ ያለው የዋሻ ውስጥ ስዕል

 የስዕል ጥበብ እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። በዚህ ጊዜ የስዕል ጥበብ ማእከል ከጣሊያኗ ፍሎረንስ ወደ ሌላኛዋ የጣሊያን ከተማ ሮም ተሸጋግሯል። በሮማው ጳጳስ ሲክስተስ አራተኛና በእርሳቸው ተተኪ ጁሊየስ ሁለተኛ ዘመን የሮም ከተማ በሚያማምሩ ስዕሎች እንድታሸበርቅ ተደርጓል። አብዛኞቹ የዚህ ስዕል ፕሮጀክቶች የተጀመሩት በሊቀ ጳጳስ ጁሊየስ ሁለተኛ ዘመን ነው። አብዛኛው የሮም ካቴድራል ቤተክርስቲያናት ጣራና ግድግዳ የተሳሉት በታዋቂው ቀራጺና ሰአሊ በሚካኤል አንጀሎ ነው። ሚካኤል አንጀሎ የፍሎረንስ ከተማ ተወላጅ ሲሆን በሀውልቶች ላይ የራሱን አዳዲስ የአሳሳል ዘዴና ጥበብ አስተዋውቋል። የሚስላቸው ስዕሎች ጠንካራና ልክ እንደ ቅርፃ ቅርጽ ሁሉ ከሶስት አቅጣጫ መታየት የሚችሉ ናቸው።

 ራፋኤል ቫቲካንን እንዳስዋባት ሁሉ ሚካኤል ደግሞ የቫቲካንን ቤተክርስቲያናት ጣሪያና ግድግዳ በሚገርም የአሳሳል ጥበብ አስውቧል። ሚካኤል እነዚህን ስዕሎች ስሎ ለመጨረስ አራት አመታትን ወስዶበታል። በስዕሎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅዱሳንና ሰዎች ተካተዋል። በተለይም በመጽሐፍ ቅዱሱ የነቢዩ ኤርሚያስ ፊት ላይ ያለውን የሀዘን ገጽታ የገለጸበት ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ የተደነቀ ነው። ከዚህም ሌላ ጁሊየስ ሁለተኛ በበኩላቸው ራፋኤል ቫቲካንን በስዕል እንዲያስጌጣት ጥረት አድርገዋል። ራፋኤል በዚህ ወቅት ከቫቲካን ሌላ የጳጳሱን ቤተመንግስት በስዕል አስውቧል።

ራፋኤል በልጅነት እድሜው በስዕል ፍቅር ተነድፎ ኡርቢኖ ከምትባለው ከተማ ወደ ፍሎረንስ መጣ። ልጅ እግሩ ራፋኤል የሊዮናርዶ ዳቪንችንና የሚካኤል አንጀሎን የስዕል ጥበቦች በሚገባ ተክኗቸዋል። ራፋኤል እንደ ሚካኤል አንጀሎ እጅግ ማራኪና ውብ ስዕሎችን በመሳሉ በብዙዎች ዘንድ ሊወደድ ችሏል። በተለይም የማርያምንና የክርስቶስን ምስል አስውቦ በመሳል ዝናን አትርፏል።

እነዚህ የራፋኤል ስዕሎች በብዙ ኮፒዎች ተባዝተው በየአገሩ ይገኛሉ።

ከሰሜኗ የጣሊያን ከተማ ቬኒስ የተገኘው ጂዎቫኒ ቤሊኒ ስዕሎችን በዘይት ቀለም በሸራ ላይ በመሳል የመጀመሪያው ሰው ነው። ስዕሎችን ሲስል በርካታ የቀለም አይነቶችንና ብሩሾችን ይጠቀም ነበር። በ16ኛው መቶ ክፍለዘመን ለስዕል ጥበብ ከተፈጠሩ ሰአሊያን መካከል ስፔናዊው ዲያጎ ቬላአዙኩዝ ሌላኛው ነው። ይስ ሰአሊ በስዕሎቹ ተፈጥሯዊውን የሰው ልጅ ቆዳ አስመስሎ በመሳል የመጀመሪያው ነው።

 በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የስዕል ጥበብን የሚያስተምር ትምህርት ቤት የከፈቱት ደግሞ እንግሊዞች ናቸው። 19ኛው መቶ ክፍለዘመን ዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ የተከሰተበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ስዕልን ዘመናዊ እንዲሆን ካደረጉት ክስተቶች አንዱ የካሜራ መፈልሰፍ ነው። ይህ ወቅት የስዕል ህትመትና የማባዣ መሳሪያዎች ብቅ ያሉበትም ነው። ጆን ኮንስታብል እና ዊሊያም ተርነር የተባሉ የእንግሊዝ ሰአሊያን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እነዚህ ሰዎች ሁለቱን የተፈጥሮ ክስተቶች ማለትም ብርሀንንና ነፋሳትን በስዕል ማሳየት እንደሚቻል ያሳዩ ጠቢባን ናቸው። ኮንስታብል በተለይም የማእበልን ገጽታ፣ የባህር ዳርቻን፣ የፀሐይን መግቢያና ትላልቅ ተራሮችን በመሳል ለዘርፉ እድገት የበኩሉን አበርክቷል። ይህ ሰው በተለይም በአንድ ስዕል ላይ የተለያዩ የቀለም አይነቶችን በመጠቀም የመሳል ዘይቤን (divisionism) በመፍጠር ይታወቃል። ለስእሉ መስሪያ የሚያገለግለውን የቀለማት ማደባለቂያ ሰሌዳና ቢላ መሰል እቃ በማዘጋጀት ቀለማቱን በወፍራሙ ይጠቀም ነበር።

የፈረንሳይ አብዮት ተብሎ የሚጠራው ዘመንም ሌላው የስዕል ጥበብ እድገት የታየበት ነበር። በጊዜው ከተነሱ ሰአሊያን መካከል ጃኩስ ሉይስ ዴቪድ አንዱ ሲሆን በወቅቱ በአገሪቱ የነበረውን የአብዮት ሂደትና ታሪክ የሚያሳዩ ስዕሎችን ይስል ነበር።

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተከሰቱ የስዕል ጠቢባን ከዚያ ቀደም ይሳሉ በነበሩ (impressionism) የአሳሳል ዘዴዎች ፈፅሞ ደስተኛ አልነበሩም። በዚህ ዘመን የተፈጠረው ሰአሊ ፓወል ሴዛኔ የቀደመው የአሳሳል ዘዴ የተፈጥሮን ትክክለኛ አቋምና ይዘት አያሳይም የሚል እምነት ነበረው። ይህ ጠቢብ በሱ አጠራር ፀጥ ያለ ህይወትን የመሳል አባዜ ተጠናውቶት እንደነበር ይነገራል። የስዕል ስራው በተለይም በፍራፍሬ ቅርጾችና በሌሎች ቁሶች አቀማመጥና አደራደር ላይ ያተኮረ ነበር። ቪንሴንት ቫን ጎ የተባለው ሌላው የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰአሊ በበኩሉ የገሀዱን አለም (realism) የአሳሳል ስልት ይቃወም ነበር። የዚህ አይነት አሳሳል የዚህችን አለም ገሀዳዊና ቁስአካላዊ ገፅታ ብቻ የሚያሳይ ነው። ስለዚህም ይህንኑ ስልት በማሳደግ የራሱን ግምታዊና ሃሳባዊ ይዘቶች በስዕሎቹ ማንፀባረቅ ችሏል።

 የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታዋቂዎቹ የጥበብ ሰዎች ፓብሎ ፒካሶና ጎርግ ባራኩ የተፈጠሩበትም ነው። ፒካሶና ባራኩ በስዕል ጥበብ አዲስ የአሳሳል ዘዴን አሳይተዋል። ይህ የአሳሳል ጥበብ (cubism) በመባል ይታወቃል። ይህ የአሳሳል ጥበብ ስእሉን በአንድ ጊዜ ከተለያየ አቅጣጫ ማየት የሚያስችል ነው። ከተለያዩ ቁሶች ቅርጽ ያላቸውን ቁርጥራጭ ነገሮች በመውሰድና የስዕል ሸራ ላይ በማጣበቅ አንድ ራሱን የቻለ ቅርፅ ያለው ነገር በማስቀመጥ መልእክት ማስተላለፍ ነው። ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ደግሞ አሜሪካ የአለማችን የስዕል ጥበብ ማእከል ለመሆን በቅታለች። አርሺሌ ጎርኪ እና ጃክሰን ፖሎክ ደግሞ በወቅቱ የታወቁ የስዕል ጠቢባን ነበሩ። እነዚህ ሰአሊያን አዲስ የስዕል አሳሳል ስልትን ፈጥረዋል። የአሳሳል ጥበቡ “ረቂቅ የአሳሳል ጥበብ” (abstract expressionism) በመባል ይታወቃል። እነዚህ የአሳሳል ስልቶች አንድን የተለየ ነገር በስዕል ስራ ከማስቀመጥና ከማሳየት ባለፈ ጠለቅ ያለና ረቀቅ ያለ ሁኔታን፣ የተለያዩ ቀለማትን፣ ዲዛይኖችና የአጣጣል ዘዴዎችን በመጠቀም አዲስ የአሳሳል ጥበብን የማንፀባረቅ ጉዳይ ነው። በ1960ዎቹ አጋማሽ ደግሞ አዲስ የአሳሳል ስልት ብቅ ብሏል። ይህም “Op” በመባል ይታወቃል። “የሚታይ ጥበብ” (optical art) ይባላል። ስእሉ ዝም ብሎ በአንዴ የሚታይና የሚገባ ሳይሆን እይታችንን በማዋዠቅ የማጥበርበር ኃይል ኖሮት በዚህ ውስጥ ጥልቅ ሚስጢራዊ መልእክትን ማስተላለፍ ነው።

 የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ታሪክ

 በኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ከሀይማኖታዊና መንፈሳዊ ይዘት ወደ አለማዊው የአሳሳል ስልት ሽግግር እንዳደረገ ይታመናል። አለማውያኑ ስዕሎች በተለያዩ የቀለም አይነቶች ያሸበረቁና የዘመኑን የህይወት እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ናቸው። በርካቶቹ ሰአሊያን ልማዳዊ ወይንም ባህላዊ የአሳሳል ዘዴዎችን የሚከተሉ ሲሆን በስዕሎቹ ይዘት በርካታ ሀሳቦችን በአንድ የስዕል አይነት ላይ ለመግለጽ የሚሞክሩበት ሁኔታ ታይቷል። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ ጋር በተያያዘ መንፈሳዊ ስዕሎችን መሳል ተጀመረ። የስዕል ጥበቡ በተለይም በቤተክርስቲያናት በብዛት መንጸባረቅ ጀመረ። ስዕሎቹ በአብዛኛው መስቀልንና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ፃድቃንን ህይወት የሚተነትኑ ነበሩ።

በዚያን ወቅት የኢትዮጵያን የስዕል ጥበብ ለየት የሚያደርገው ስዕሎቹ ህብረተሰቡ ከልቡ በሚያምንባቸው ጉዳዮችና እውነታዎች ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ነው። ስዕሎቹ በአብዛኛው ሀሳባዊ ናቸው። ከዚህም ሌላ የስዕሎቹ ምጣኔና ይዘት የተለያየ ነው። ለምሳሌ በአንድ የሰው ምስል ላይ የሰውየው ራስ ቅልና የታችኛው የሰውነቱ ክፍል ተመጣጣኝ አይደሉም። ስለዚህ ይሄንን ሊመስል ይችላል በሚል በግምት ነው የሚሳለው። በኢትዮጵያ ጥንታዊ የአሳሳል ጥበብ ትልቅና ሸውራራ የአይን አሳሳል የተለመደ ነው። ይህ የአሳሳል ጥበብ በኪነጥበብ አዋቂዎች ዘንድ “ተገላቢጦሽ የአይን አሳሳል” በመባል ይታወቃል። በተለይም ቅዱሳኑ የተሳሉት በዚሁ “ተገላቢጦሽ” በሚባለው የአሳሳል ዘይቤ ሲሆን ተመልካቹን የማስደመም ባህሪ ያላቸው ናቸው።

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ መልኩን ቀይሮ ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ጀመረ። በተለይም የአዲስ አበባ የስዕልና የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት መከፈትና የእስክንድር ቦጎሲያን የስነ ጥበብና ዲዛይን ኮሌጅ መከፈት ለአገሪቱ የስዕል ጥበብ የአዲስ ምእራፍ መሰረት ጥሏል። ይህ ወቅት የተለያዩ እምቅ ችሎታ ያላቸው የስነ ስዕል ጠቢባን ብቅ ያሉበት ነው። በዚህም አለ ፈለገ ሰላምና እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን የመሳሰሉ ተጽእኖ ፈጣሪ የስዕል ጥበብ ባለሙያዎች አሻራቸውን በስዕል ጥበብ ማሳረፍ የጀመሩበት ወቅት ነው። በተለይም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተማሪዎች የስዕል ጥበብን እንዲማሩ ያበረታቱና የውጭ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ያደርጉ እንደነበር ይነገራል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top