ጥበብ በታሪክ ገፅ

ባህላዊ የክዋኔ ጥበብ እና የኢትዮጵያ ቴአትር

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ቴአትር ጀማሪ ተብለው የሚጠቀሱት በጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ለሳቸውም ለኢትዮጵያም የመጀመሪያ የሆነውን ድርሰት ለመጻፍ ተረቶችን እና ባህላዊ ዕውቀቶችን መሰረት እንዳደረጉ በታተመው የቴአትር ድርሰታቸው መግቢያ ላይ ቢያትቱም፣ የመሰረቱት እና የጀመሩት ቴአትር ግን አውሮፓዊ ቅርፅ እና መልክ ያለው ነበር። ነገር ግን ባህላዊ የክዋኔ ጥበቦችን በቴአትር ውስጥ አዳብሎ መጠቀምን ከሳቸው በኋላ የመጡ የቴአትር ጸሐፍያን እንደ አንድ መንገድ ለመውሰድ ሙከራ አድርገዋል። እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድረስ በነበሩት ዓመታት በተለይ ዮፍታሄ ንጉሴ እና መላኩ በጎሰው ስነ-ቃልን፣ ተረትን፣ ሙዚቃን እና መሰል ባህላዊ ክዋኔዎችን ከቴአትራቸው ጋር በማዳበል ይጠቀሙ ነበር። ይህም ሲጀመር ጀምሮ አውሮፓዊ ቅርፅ የያዘውን የቴአትራችንን መልክ ሀገራዊ ቀለም ለማስያዝ ሁነኛ መንገድ ነበር። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በቴአትራችን እምብዛም ጥቅም ላይ ስላልዋለው ባህላዊ ክዋኔዎችን የመጠቀም መንገድ ጥቂት የውይይት ሀሳብ ማንሳት ነው።

 የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳዩ የክዋኔ ጥበቦች ከቴአትር ውስጥ መውጣት የመጀመሪያው ምክንያት የሆነው ጀማሪው ጸሐፊ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ለቴአትር የነበራቸው ግንዛቤ ነበር። ተክለሐዋርያት ሩሲያ በመማራቸው እና ፓሪስ እና ሎንዶንን በመጎብኘታቸው፣ በዘመኑ የነበረውን እውናዊ የአውሮፓ ቴአትርን የመመልከት ዕድል አጋጥሟቸዋል። ከዚህም ባለፈ ቴአትሮቹን ከመመልከታቸው በፊት ጽሑፈ ተውኔቶቹን አግኝተው አንብበው ወደ ቴአትር አዳራሽ ይገቡ እንደነበር የህይወት ታሪካቸውን በከተቡበት መጽሐፋቸው ያወሳሉ። እነዚህ የህይወት ልምዶች በኋላ ላይ ለሚጽፉት ቴአትር ጥሩ መነሻ ቢሆናቸውም በአንድ በኩል ግን ትውፊታዊ ቅርፅ ይዞ ሊያድግ ይችል የነበረውን እና በእነ ከንቲባ ኅሩይ “የቴአትር ጨዋታ” ተብሎ የታሰበውን የቴአትር ሃሳብ ያፈረሰ እና የአውሮፓውያንን የቴአትር መንገድ ዛሬ እንደምንመለከተው በሰፊው ተንሰራፍቶ እንዲቀመጥ ምክንያት ለመሆን የበቃ ሆኗል።

የጉዳዩን የጀርባ ታሪክ ለማስተዋወቅ ያህል፣ ተክለሐዋርያት የመጀመርያ ቴአትራቸውን ለመጻፍ ያነሳሳቸውን ጉዳይ ከታተመው የቴአትራቸው መግቢያ እንመልከት፦ ‹‹አንድ ቀን ከአቶ ኅሩይ የአዲስ አበባ ሚኒስፓሊቲ ዲሬክተር የጥሪ ወረቀት መጣልኝ:: ዛሬ ማታ በቴራስ ሆቴል የቴአትር ጨዋታ ለማሳየት ተደራጅተናልና መጥተው እዲያዩልን ፈቃድዎ ይሁን የሚል ነው:: ስለዚህ እኔም አጀማመሩን ለማየት ቸኩዬ ሄድኩ… ግን ክፉኛ ተሳቀቅሁ:: አዝማሪዎች፣ ዘፋኞች /ወንዶችም ሴቶችም/ ተሰብስበው አታሞ፣ መሰንቆና ክራር እየመቱ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ አየሁ… የልጅ ኢያሱ አስተዳደግ በምን ዓይነት እንደተመራ አየሁና የባሰውን አዘንኩ… ወዲያው አንድ የቴአትር ጨዋታ ለምሳሌ ያህል ለማሰናዳት ተመኘሁ::››

የዚህ ሃሳብ ዋና ነጥብ ተክለሐዋርያት ያዩት ነገር ‘ቴአትር አይደለም’ ብለው መወሰናቸው ነው። በወቅቱ ቀርቦ የነበረውን እና በሳቸው ግምገማ ‘አዝማሪዎች፣ ዘፋኞች ተሰብስበው አታሞ፣ መሰንቆና ክራር እየመቱ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ’ መታየቱ ቴአትር ካለመሆኑ ባሻገር እሳቸውን ‘ያሳቀቀ’ ትዕይንት ሆኖ አልፏል። ይህ ሁኔታ ነው እንግዲህ ተክለሐዋርያትን የመጀመርያውን ቴአትር ልጅ እያሱን ለማስተማር ወዲያውም የቴአትር ጥበብንም ለኢትዮጵያውያን ለማስተዋወቅ የፃፉት። እዚህ ላይ አንድ የመከራከሪያ ነጥብ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤ ተክለሐዋርያት የተመለከቱት ‘የቴአትር ጨዋታ’ በዚያው ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም (ወደ ኋላ መለመዱ የማይቀርለት በመሆኑ!) አሁን ካለን የአውሮፓ ቴአትር ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የክዋኔ ጥበብ የሚታይበት መድረክ ይፈጠር ነበር የሚል። ይህ መድረክ በአቀራረቡም ሆን በአሰራሩ ከመደበኛው የቴአትር አጻጻፍ፣ አዘገጃጀት እና አተዋወን ተለይቶ የራሱን ቀለም ይዞ ያድግ ነበር። ይህ ሃሳብ ግን እስከዛሬ በኢትዮጵያ የተሰሩ ሁሉም ቴአትሮች ባህላዊ ክዋኔዎችን እንደ አንድ ግብዓት ተጠቅመው አልሰሩም የሚል አንድምታ የለውም። ሙከራዎች እና ይሁነኝ ተብለው የተሰሩ ቴአትሮች በተለያየ ጊዜ ተመልክተናል።

 እስከ አስራዘጠኝ ሀምሳዎቹ አጋማሽ ድረስ አብዛኞቹ ቴአትር ጸሐፊዎች ልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎችን፣ ስነ ቃሎችን እና ዋና ዋና ህዝባዊ ታሪኮችን በመጠቀም ቴአትሮችን ያቀርቡ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ቴአትሮች በተለይ በአውሮፓ የቴአትር ቅርፅ/አጻጻፍ ስልት ሲገመገሙ ደካማ ጎናቸው የበዛ ሆነው ይገኛሉ። ይህንን የአውሮፓ ስልት የሙጥኝ ብሎ የያዘው ቴአትራችንም እነዚህን መሰል ቴአትሮች ቀስ በቀስ ከመድረክ እያራቃቸው መጣ። በተለይ ከአስራ ዘጠኝ ሃምሳዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጡ ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች መድረኩን ሲቆጣጠሩት እነዚህ ባህላዊ ክዋኔዎች ጨርሶ ከዋናው የቴአትር መድረክ ራቁ።

በደርግ ጊዜ ዝነኛ የነበረው ኪነት፣ (ምንም እንኳ የተቋቋመበት ዓላማ ሌላ ቢሆንም!) በተለይ ባህላዊ ሙዚቃን እና ልዩ ልዩ የክዋኔ ጥበቦችን በመጠቀም ረገድ ከዋናው የቴአትር መድረካችን የተሻለ ነበር። በየተቋቋሙበት ማህበረሰብ ያሉ የክዋኔ እና የሙዚቃ ጥበቦችን በማጥናት ለህዝቡም መልሶ በማቅረብ ከፍተኛ ሚናን ተጫውተዋል። የኪነት ቡድኖች እንቅስቃሴ ከፖለቲካዊ ስራቸው ባሻገር ባህላዊ ሙዚቃ እና ክዋኔ ጥበብን በማስተዋወቅ እና በማስፋፋት ረገድ ሰፊ ሚና ነበራቸው። ምናልባትም ይህ ሚናቸው ሰፊ ጥናት እና ምርምር የሚጠይቅ ይሆናል። በሰፊው ሊያግባባን የሚችለው ግን በመደበኛነት በየቴአትር ቤቶች ከሚቀርቡት ቴአትሮቻችን ይልቅ እነዚህ በየቦታው የተቋቋሙት የኪነጥበብ ቡድኖች በተሻለ ሁኔታ ባህላዊ የክዋኔ ጥበቦቻችንን ለመጠቀም ሞክረዋል።

 ከኪነት ስራዎች ባሻገር በዚህ ጊዜ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ዲፓርትመንት መምህራን እና ተማሪዎች እንዲሁም በአንዳንድ ቴአትር ቤቶች ባህላዊ ክዋኔን ከመደበኛው የቴአትር አቅርቦት ጋር አዋህዶ በአጥጋቢ ደረጃም ባይሆን ሙከራዎች ግን ነበሩ። በዚህ ስራው ከፍ ብሎ የሚጠቀሰው ደግሞ ፍሰሐ በላይ ይማም ነው። ፍሰሐ ዝነኛ በሆኑት አልቃሽ እና ዘፋኝ፣ ስመኝ ስንታየሁ፣ ሆድ ይፍጀው እና ሌሎች ቴአትሮቹ በተለይ ባህላዊ ክዋኔዎችን፣ ስነ ቃሎች እና የአኗኗር ዘይቤዎችን ከአውሮፓዊው የአጻጻፍ ስልት ጋር በማቆራኘት ተወዳጅ የሆኑ ስራዎችን ለማቅረብ ችሏል።

ኢሕአዴግ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ቴአትርን ከባህላዊ ክዋኔዎች ጋር አዳብሎ ማሳየት ከበፊቱ በተሻለ የተለመደ እየሆነ መጣ። በዚህ ረገድ ባህላዊ ክዋኔን ከመጠቀም ባሻገር ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ቴአትር መቅረብ ጀምሯል። በዚህ ዘመን በመደበኛው ቴአትር ቤቶች የታዩ ባህላዊ ክዋኔ እንደ አንድ ግብዓት የተጠቀሙ የቴአትር ስራዎች መታየታቸው ተገቢ ሲሆን ከዚህ በላይ ግን መስፋፋት እና መታየት ይገባቸዋል።

ባህላዊ ክዋኔ መጠቀም ፣ ለምን? ባህላዊ የክዋኔ እንቅስቃሴዎች በቴአትር ውስጥ መካተት ይችላሉ? ወይስ አይችሉም? እንዲሁም የአፍሪካውያን የክዋኔ ጥበባት ቴአትራዊ አላባውያን አሏቸው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች በተለይ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ በኋላ ለተፈጠሩ የአፍሪካ የቴአትር ባለሙያዎች ከፍተኛ የምርምር እና የክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። አሁንም መሆኑን ቀጥሏል። በተለይ ‘ሀገር በቀል የሆነው የክዋኔ ጥበብ አውሮፓዊ ቅርፅ ከያዘው የቴአትር ተግባር በተሻለ ለቴአትር ይቀርባል’ ከሚል ጀምሮ ‘የለም፣ የአፍሪካውያን የክዋኔ ጥበብ ከዘመናዊው አውሮፓዊ ቅርፅ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም፣ የቴአትር ሀሳብም መነሳትም የለበትም’ እስከሚለው ድረስ ልዩ ልዩ ሃሳቦች ይደመጣሉ። ይነበባሉ። አንዳንዶች፣ ለምሳሌ

“ቴአትራችን ለራሱ ተመልካችም ይሁን በሌሎች ሃገራት ለሚያቀርባቸው ስራዎች ተወዳዳሪ እንዲሆን የራሱን ቀለም ይዞ መገኘቱ አዋጭ አካሄድ ነው”

በአፍሪካ ቴአትር ላይ ሰፊ ጥናት በማቅረብ የሚታወቁት ኮንቴህ ሞርጋን (1994) የአፍሪካ የክዋኔ ጥበብ እና የአውሮፓ የቴአትር ጥበብ የሚያመሳስላቸው ነገር ይበዛል ይላሉ። ለምሳሌ ሁለቱም ዳንስን፣ ሙዚቃን፣ እንቅስቃሴን፣ አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ አሻንጉሊትን ሳይቀር መጠቀማቸው የሚያመሳስላቸው ነገር ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

 በሌላ በኩል ኦስቲን አሳግባ (1986) የአውሮፓ ቴአትር ዓለማዊ ገፅታ መያዙ እና የአፍሪካውያን የክዋኔ ጥበብ ደግሞ መንፈሳዊ ይዘታቸው ከፍተኛ መሆንን እንደ አንድ መሰረታዊ የማይታረቅ የዓላማ ልዩነት ያስቀምጣሉ። ነገር ግን ይላሉ፣ ጄን ፕላስቶው African Theater and Politics: the evolution of theater in Ethiopia, Tanzania and Zimbabwe በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ “ብዙዎቹ የመከራከሪያ ሃሳቦች የሚስቱት ዋናው ነጥብ አውሮፓዊውን የቴአትር ፅንሰ ሃሳብ እና ተግባር የመጨረሻው የሃሳብ እና የተግባር ምዕራፍ አድርገው መቁጠራቸው ነው። በመሆኑም ሁሉም የመከራከሪያ ሃሳቦች ይህንን አውሮፓዊ ቴአትር የቴአትር ተግባር ቍንጮ አድርገው ቆጥረው ሌላውን (አፍሪካዊውን) በዚህ መነፅር መመልከታቸው ሰፊውን የቴአትር እና የክዋኔ ጥበብ እንዳንረዳ ያደርጋሉ” ይላሉ። ይህም ሃሳብ ‘የቴአትር  ጨዋታ’ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱት ተከለሐዋርያት ‘የቴአትር ጥበብ ይሄ አይደለም’ እንዲሉ ምክንያት የሆናቸው ሃሳብ ነው። የቴአትርን ፅንሰ ሃሳብ ወይም ጥንተ ተፈጥሮን ከአውሮፓውያን የቴአትር ተግባር ጋር አንድ እና የሚመሳሰል አድርጎ መውሰድ ያስከተለው ውጤት ነው።

 ነገር ግን በጊዜ ሂደት ሁለቱንም ፅንፎች ወደ ጎን በመተው ሁለቱንም ጥበቦች (ማለትም አውሮፓዊውን ቴአትር እና አፍሪካዊውን የክዋኔ ጥበብ) በማዋሃድ አፍሪካዊም፣ ዓለም አቀፋዊም ምስል ያለው ቴአትር መፍጠር ይቻላል የሚል ሀሳብ እየጎላ መጣ። ይህን ሃሳብ በመከተልም በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የቴአትር ባለሙያዎች ሁለቱን ጥበቦች እያዋሃዱ አዲስ አይነት የቴአትር መልክ ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህም ብዙዎቹ ስኬታማ ሆነዋል። የዝነኛውን ናይጄሪያዊ የኖቤል ተሸላሚ የቴአትር ደራሲ ዎሌ ሾይንካ ስራዎችን መመልከት ጥሩ ምሳሌ ለማግኘት ይጠቅማል። በሌላ በኩል የሃገራችንን ጨምሮ በመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የቴአትር ጥበብ ትምህርት ቤቶች ይህንን ዘርፍ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ለተማሪዎቻቸው መስጠታቸው ይህን የአውሮፓ ቴአትርን እና የአፍሪካን ክዋኔ እያዋሃዱ የመጠቀም ጥበብ በየጊዜው እየተስፋፋ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል።

የሃገራችን የቴአትር ጉዞ ይህንን መስመር ለመከተል ሞክሯል። ነገር ግን ከላይ በተመለከትናቸው ምክንያቶች ሳቢያ ይህን ያህልም ሳይሳካለት ቆይቷል። ነገር ግን ጊዜው አሁንም አልረፈደም። የሀገራችን የቴአትር ጥበብ ይህንን መንገድ መከተል አለበት የሚል መከራከሪያ በሁለት ምክንያት አነሳለሁ፦ አንደኛ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ የቴአትር ጸሐፊያን አፍሪካዊም ሆነ ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን በልዩ መንገድ መተረክ የሚቻልበትን የአጻጻፍ ስልት አልፈጠሩም። የቴአትር አጻጻፍ ስልታችን አሁንም ድረስ አውሮፓውያን ባለሙያዎች በግሪክ ጊዜ በተለሙት እና በአሁኑ ዘመን ባሻሻሉት መንገድ እየተጓዝ ይገኛል። ይህንን ስልት ለውጠን ወይም የእኛ የሆኑ ታሪኮችን የምንተርክበት መንገድ እስክናመጣ ድረስ ይህንኑ የአውሮፓ ስልት መጠቀም ግዴታችን ይሆናል። የእኛን ታሪኮች፣ ወጎች፣ ስነ-ቃሎች፣ የአስተሳሰብ መንገዶች፣ እና ፍልስፍናዎችን ሊሸከም የሚችል ነገር ግን ኪነ-ጥበባዊ ውበቱ የተጠበቀ የአጻጻፍ ስልት እስክንፈጥር ድረስ እስከዛሬው በተለመደው ዓለም አቀፋዊ ስልት መጓዝ ተገቢ ይሆናል።

ሁለተኛው ምክንያት፦ ይህንን ስልት ይዘን፣ በይዘት ግን የእኛን የክዋኔ ጥበብ መጠቀም እንችላለን። ይህ ደግሞ የቴአትር ጥንተ- ተፈጥሮን ባግባቡ ከመረዳት እና ከመጠቀም ይመነጫል። የቴአትር መሰረታዊ ምክንያት ይላል ኢዴቢሪ (1978) “በጋራ የመኖር እሳቤ ውስጥ መገኘቱ ነው። የህይወትን ወሳኝ ሁነቶች የሚጠቀምበት መንገድ፣ ውጤቶቹ፣ የተመልካችን ስሜት የሚያሸንፈበት ስልት፣ ይህንን ሁሉ ስንመለከት የቴአትር ጥበብ፣ ከሁሉም ጥበቦች በላቀ ከሰዎች አኗኗር ጋር የተቆራኘ ነው።” ይህ የመቆራኘት ኃይሉ ደግሞ የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ ባህላዊ ክዋኔን፣ ስነ ቃልን እንዲሁም ሌሎች ክዋኔዎችን በቴአትር ስራችን ውስጥ እንድንጠቀም እድሉን ይሰጠናል። ይህን እድል በመጠቀም ኪነ ጥበባዊ ውበቱን በጠበቀ መልኩ ባህላዊ ክዋኔያችንን ከአውሮፓ በወረስነው (አሁን አለም አቀፍ ድንጋጌ ወደመሆን በተሸጋገረው) የአጻጻፍ ስልት አዳብረን መልሰን ለተመልካች እናቀርባለን።

 ይህ መንገድ ሁለት ጠቀሜታ አለው። የቴአትር ስራው በአጻጻፍ እና በአመደራረኩ አሁን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን በያዘው ስልት መሰራቱ በዓለም አቀፍ ተመልካች ዘንድ ቅቡልነት እና ቅርበት የሚኖረው ሲሆን በይዘቱ ደግሞ የሃገሩን ባህል መሰረት ያደረገ መሆኑ ቴአትሩ ለተፈጠረበት ተመልካች ቅርብ ይሆናል። በመሆኑም የቴአትር ስራው በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያለው ይሆናል። በዓለም ዓቀፍ የቴአትር ፌስቲቫሎች እና ውድድሮች እንደሚታየው የራስን ባህል እና የኪነጥበብ ስልት መሰረት ያደረጉ ስራዎች ማቅረብ በዘመናዊው የኪነጥበብ እንቅስቃሴ ጎልቶ ለመታየት ሁነኛ መንገድ ነው።

ሉላዊነት በነገሰበት በዚህ ዘመን የእኔን ብቻ ታሪክ ተመልከቱም ሆነ የእናንተን ብቻ ልስማ የሚል አካሄድ ሁለቱም አዋጭ አይደሉም። ሁለቱም ያከስራሉ። የራስን ብቻ ይዞ መገኘት ራስን ለመሸጥ አዋጭ ቢሆንም ያለው ነባራዊው የዓለም ሁኔታ ግን ይህንን አይፈቅድም። ለሁልጊዜውም ደግሞ የአውሮፓን ቴአትር ብቻ እየሰራን ልንኖር አንችልም። እሱም ቢሆን በዚህ ፈጣን በሆነ የዓለም የኪነጥበብ ዕድገት ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ፈፅሞ የሚቻል አይሆንም። ስለዚህ ሁለቱንም አስታርቆ ሊሄድ የሚችል የኪነጥበብ አካሄድ መከተል በብዙ መንገድ የሚጠቅም ይመስላል።

የሀገራችን የቴአትር አጻጻፍ እና አዘገጃጀት ዓለም አቀፉ የቴአትር ስልት ከዘመነበት እና ከሄደበት ርቀት አንፃር ሲታይ ገና ብዙ ይቀረዋል። ከቴአትር ቤቶች አስተዳደራዊ ችግር ጀምሮ እስከ ጸሐፊ እና አዘጋጆች ለአዲስ ነገር ዝግጁ አለመሆን ድረስ በሚዘልቅ ችግር ተተብትቦ የሚገኘው ቴአትራችን ለራሱ ተመልካችም ይሁን በሌሎች ሃገራት ለሚያቀርባቸው ስራዎች ተወዳዳሪ እንዲሆን የራሱን ቀለም ይዞ መገኘቱ አዋጭ አካሄድ ነው። ይህ አካሄድ፣ ኪነ ጥበባዊ ውበቱ እንደተጠበቀ፣ በሌሎች የአፍሪካም ሆነ ከአውሮፓ የተለየ ባህል እና ክዋኔ ጥበብ ባላቸው ሃገራት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ፣ አሁንም በዓለም አቀፍ መድረክ እየሆነ ያለ ነው። በመሆኑም የቴአትር ባለሙያዎቻችን ተዝቆ ከማያልቀው ባህላዊ የክዋኔ ጥበቦቻችን ባህር በጥቂቱ በመጭለፍ ኪነጥበባዊ ለዛውን የጠበቀ ስራ አብዝቶ ማቅረብ የሚገባቸው ሰዓት አሁን ይመስላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top