አድባራተ ጥበብ

መገናኛ ብዙሃን እና የውህደተ-ቴክኖሎጂ ጫና

ውህደተ-ቴክኖሎጂ (Convergence) የሚባለው አዲስ የቴክኖሎጂ መር ክስተት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ብቻ ሳይሆን በያንዳንዳችን ህይወት ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አዎንታዊና አሉታዊ ጫና እያሳደረ ይገኛል። እስቲ በአካባቢያችን ስለምናያቸው ለውጦች እናስብ። ከጥቂት አመታት በፊት ጊዜን ለማወቅ በእጃችን ሰአት ማሰር ያስፈልገን ነበር። ሲጨልም የእጅ ባትሪ እንጠቀማለን። የቤት ስልክ፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አይነት ዕቃዎችን ይዘን መንቀሳቀስ አንችልም ነበር። ደብዳቤ የምንልከው በፖስታ ቤት እየተጠቀምንና ሳጥን እየተከራየን ነበር። ዛሬን መለስ ብለን ስናይ በነዚህ ቁሶች ሙሉ በሙሉ መጠቀም አቁመናል ባንልም ይህ ሁሉ አገልግሎት በአንድ ላይ ተዋህዶ በተንቀሳቃሽ የስልክ ቀፎ እየቀረበልን ነው። ይህን እንደ አንዱ ጠቃሚ የውህደተ-ቴክኖሎጂ ውጤት ምሳሌ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

ለመሆኑ ይህ ብዙ የሚወራለት የውህደተ- ቴክኖሎጂ ክስተት ምንድነው በመገኛኛ ብዙሃንስ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ምን ያህል የጎላ ነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ውህደተ-ቴክኖሎጂን በአጭሩ እንግለጸው ካልን ተለያይተው የነበሩ ቁሶች፣ ነገሮች፣ እና ሃሳቦች ወደ አንድ የመምጣት ወይንም የመዋሃድ ሂደት ማለት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚዲያ ውህደተ-ቴክኖሎጂ በመሰረታዊነት በመገናኛ ብዙሃንና በቴሌኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪዎች መካከል በቴክኖሎጂ ምጥቀት ሰበብ እየደበዘዘ በመጣው የድንበር ልዩነት ላይ የሚያተኩር ነው። በውህደተ-ቴክኖሎጂ ሰበብ በአሁኑ ሰአት በሚዲያ ዘውጎች፤ በሚዲያ ባለሙያዎች ክሂሎት እንዲሁም በሚያከናውኑት የስራ ዘርፍ መካከል የነበረው ልዩነት እየጠበበ መምጣቱም በግልጽ ይታያል። ይህ በሚዲያ ዘርፍ የምናገኘው ውህደት በይበልጥ በቴክኖሎጂ ግኝቶች ላይ ተመስርቶ የሚከሰት ለውጥ ሲሆን በመረጃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚመጡ ፈጠራዎች ይህን ሂደት ከኋላ ሆነው የሚነዱ ዋነኛ ኃይሎች መሆናቸውን ማየት ይቻላል።

ውህደተ-ቴክኖሎጂ የሚለው ቃል ከላቲን የተወረሰ ሲሆን ጎርደን እንደሚለው ቃሉን ቢያንስ በጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት ከ1657 እስከ 1735 የኖረው አሜሪካዊው ዊሊያም ዱሪሃም እንደሆነ ይገልጻል። ሲጠቀምበትም ሃይማኖታዊ ይዘት እንደነበረው ጎርደን የታሪክ መዛግብትን ጠቅሶ ያስነብባል። በምሁራን ዘንድ ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ የእውቀት ዘርፎችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው በተፈጥሮ ሳይንስ እንደሆነም ይነገራል። በዚህም እንደ ባዮ-ኬሚስትሪ፣ ፊዚካል-ባዮሎጂ ወዘተ. የመሳሰሉትን የሳይንስ ዘርፎች ውህደት ለማስረዳት ጥቅም ላይ ውሏል። ቀጥሎም በቴክኖሎጂው ዘርፍ የመጡት የናኖ (Nano) የባዮና (Bio) የመረጃ ቴክኖሎጂን (Information Communication Technology) የመሳሰሉ ውህደቶች (NBIC) የውህደተ-ቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው።

በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ቃሉን ቀድሞ በመጠቀም የፖለቲካ ሳይንስ ዘርፉ ተጠቃሽ ነው። ይህም የቀዝቃዛውን ጦርነት መጠናቀቅ ተከትሎ በምእራባውያኑና በሶቪየት መንግስት የፖለቲካ አስተሳሰብ መካከል የመጣውን መቀራረብ (ፐረስትሮይካ) ለማስረዳት አገልግሏል። በኮሙኒኬሽን እና በብዙሃን መገናኛ ዘንድ ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለው በነዚህ ዘርፎች መካከል እየደበዘዘ የመጣውን የድንበር ልዩነትና መዋሃድን ለማሳየት ነው። በተለይም ከ1970ዎቹ የኮምፒዩተር መምጣት ጀምሮ ምሁራን ይህን ቃል በተለያየ መልኩ ማየት ጀምረዋል። የውህደተ-ቴክኖሎጂን እሳቤ ወደ ሚዲያ ምርምር የወሰደው ግን ኒኮላስ ኔግሮፖንቴ እንደሆነ ይነገራል። ቀዳሚ የሆነው የዚህ ሰው የውህደተ-ቴክኖሎጂ ሞዴል እንደሚያሳየው ይህ ውህደት የሚመነጨው በሶስት በተፈጥሯቸው ተለያይተው የነበሩ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎች ጥምረት ላይ ተመስርቶ ነው። ከነዚህም አንደኛው ነባር የሚዲያ ዘውግ የሆነው የህትመት ሚዲያ ኢንዱስትሪ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ዘግየት ብሎ የመጣው የብሮድካስት እና የሲኒማ ኢንዱስትሪ ሲሆን ሶስተኛውና ዋነኛው ደግሞ እጹብ ድንቅ የቴክኖሎጂ በረከት የሆነው የኮምፒዩተር ኢንዱስትሪ መሆኑን ይህ የኔግሮፖንቴ ሞዴል ያስረዳል። የነዚህ ሶስት ኢንዱስትሪዎች ውህደት ነው እንግዲህ የሚዲያ ውህደተ- ቴክኖሎጂን ለማስረዳት በአሁኑ ወቅት እያገለገለ ያለው።

በ1980ዎቹ አካባቢ ብዙ የኮሙኒኬሽን ተመራማሪዎች ይህ የውህደት ባህሪይ ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ጫና በማጥናት ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ ሁኔታዎች አስገድደዋቸዋል። በርካታ የውህደቱን ባህሪና ውጤቶች የሚያሳዩ በቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በባህላዊ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶችን በብዛት እናገኛለን። በ1990ዎቹ ደግሞ ምርምሩ ከዲጂታይዜሽን፣ ከሊበራላይዜሽን እና ከግሎባላይዜሽን ጋር በተጣመረ መልኩ በፖሊሲ አውጪዎችና በፖለቲከኞች በስፋት ተጠንቷል። በተለይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጀባ ያላቸው ባለብዙ ፈርጅ ጠቀሜታዎች ወደ ሚዲያው ዘርፍ ሰርገው መግባታቸው ነገሩን ይበልጥ ያወሳሰበው መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ። ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጥቂቶቹ ዲጂታል ቴሌቪዥን፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ ዌብ 2.0 (Web 2.0) እንዲሁም ተንቀሳቃሽና ገመድ አልባ መገናኛዎች ናቸው።

 ውህደተ-ቴክኖሎጂ ተፅእኖ ፈጣሪና በጣም አሳሳቢ ክስተት መሆኑን የሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በዚህ ክስተት ላይ የሚደረገው ጥናት ዘርፈ ብዙና በሁሉም አቅጣጫ መሆኑ ነው። ውህደተ-ቴክኖሎጂ ብዙ ዘርፎችን ከማሳተፉ የተነሳ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚካሄዱ ጥናቶችም እንዲሁ ከተለያዩ ዘርፎች በተውጣጡ ተመራማሪዎች (interdisciplinary) በጥምረት እንዲካሄዱ ግድ ብሏል። ከዚህም ባለፈ ጥናቱ በምሁራን ብቻ የሚደረግ ሳይሆን በፖሊሲ አውጪዎች፣ በመገናና ብዙሃን ባለቤቶች፣ በህግ ባለሙያዎች እንዲሁም በተለያዩ የንግድና የአገልግሎት ዘርፍ ባለሙያዎች ጭምር ነው። የጥናታቸው አላማ የተለያየ ቢሆንም። ለምሳሌ የሚዲያ ተቋም ባለቤቶች ያተኮሩት ውህደተ-ቴክኖሎጂ ያመጣውን ስር ነቀል የሆነ ለውጥ እንዴት እንደሚቋቋሙና ትርፋማ ሆነው እንደሚቀጥሉ በሚያሳዩ ጥናቶች ላይ ነው። ፖሊሲ አውጪዎች በሌላ በኩል ይህን ፈጣን ለውጥ እንዴት ተቆጣጥሮ በማህበረሰብ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር ማድረግ እንደሚቻል ለማወቅ ይፈልጋሉ። የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምሁራን ደግሞ በዋነኛነት በሚዲያው አካባቢ በውህደተ-ቴክኖሎጂ ሰበብ የሚፈጠረውን ለውጥ ለመረዳትና ለፖሊሲ አውጪዎች ለማስረዳት በሚጠቅሙ ምርምሮች ላይ ተጠምደው እናገኛቸዋለን።

እንደ ፍሌው ትንበያ ገና ሀ ብሎ የጀመረው ውህደተ-ቴክኖሎጂ ወደፊት በህይወታችን ውስጥ የሚጫወተው ሚና በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል። በሱ አባባል ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘ ውህደት በንግዱ፣ በመንግስት አሰራር፣ በጤናና በትምህርት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ዘንድ አያሌ ለውጦችን ያመጣል። ይህንን እኛም በየዕለቱ እያየን ነው። ለምሳሌ እዚሁ ሃገራችን በአሁኑ ወቅት የዚህ አይነት ዲጂታል ቴክኖሎጂ በፈጠረው እድል ተጠቅመን ውሃ፣ መብራትና ስልክን በአንዲት መስኮት መክፈል ችለናል። ይህ ማለት እንደበፊቱ መብራት ሃይል፣ ቴሌኮሙኒኬሽንና ውሃ ልማት መሥሪያ ቤቶች መሄድ አላስፈለገንም ማለት ነው። ይህ ራሱ እንደ አንድ የውህደተ-ቴክኖሎጂ በረከት የሚቆጠር መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ይህም ምን ያህል ልፋታችንን እንዳቀለለልን የተጠቀምንበት እናውቀዋለን።

 እንደ ላፍዘር እምነት ዋነኛው የውህደተ-ቴክኖሎጂ ታሪካዊ አጀማመር በቴሌኮሙኒኬሽንና በመገናኛ ብዙሃን መካከል የተደረገው ጥምረት ነው። በ19ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ለግለሰቦች አገልግሎት ስራ ላይ ሲውሉ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ራሱን ችሎ እንደ ኢንዱስትሪ ተፈጠረ። ከጥቂት አመታት በኋላ የብሮድካስት ኢንዱስትሪ ከነባሩ የህትመት ሚዲያ ጋር በመጣመር አንድ ትልቅ ኢንዱስትሪ ሆኖ ብቅ አለ። እነዚህ ሁለት ዘርፎች ቴሌኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ የቴክኖሎጂና የአስተዳደር ስርአት ይከተሉ ነበር። በተለያዩ ካምፓኒዎችም ይመሩ ነበር። እንዲሁም የተለያዩ የቁጥጥር ስርአትና ህግጋቶች ነበሯቸው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን በሚዲያና በቴሌኮሙኒኬሽን መካከል ያለው የቴክኖሎጂ ልዩነት መፈረካከስ ጀመረ። ነባር ክፍፍሎች፣ የምርምር አካሄዶች፣ የቁጥጥር ሞዴሎች፣ እና የተቆጣጣሪ አካላት ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ፈተና ላይ ወደቁ።

 ይህ የሁለቱ ክፍሎች ውህደት የተከሰተው በሁለት ደረጃዎች ነው። በመጀመሪያ የመረጃ ኮሙኒኬሽንና የቴሌፎን ዲጂታል መደረግ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ የሆነውን የኢንፎርማቲክስ (informatics) መምጣት አበሰረ። ይህም የውህደት ሂደት ቴሌማቲክስ

(Telematics) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህን ተከትሎ ዲጂታላይዝድ በተደረገው የመገናኛ ብዙሃን ይዘትና በዚህ በቴሌማቲክስ መካከል የተከሰተው ጋብቻ በበኩሉ ሚዲያማቲክስ (Mediamatics) ተብሎ የሚጠራውን ውህደት ፈጥሯል። ስለዚህ በሚዲያ ዘርፍ የምናገኘው የውህደት ጥናት ሚዲያማቲክስ በሚባለው ውህደት ዙሪያ የሚያጠነጥን እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

የዚህን ውህደት የማፋጠን ፍላጎት በማሳየት በኩል የቴሌኮም ዘርፍ ቀዳሚ ነበር። የሚዲያ ዘርፉ በመጀመሪያ ሁለት መሰረታዊ ጥርጣሬዎች ነበሩት። አንደኛው በዚህ ውህደት ሰበብ የገበያ ተኮር አካሄዶች ሊንሰራፉና በዚህም ሰበብ ነባር ህግጋቶች ሊላሉ ይችላሉ ብለው የዘርፉ ሰዎች ማሰባቸው ነው። ሁለተኛውና ዋነኛው ስጋት ግን የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ሚዲያውን ሊጠቀልለውና ሊቆጣጠረው ይችላል የሚለው ነበር።

የሆነ ሆኖ ይህ ብዙ እየተወራለት ያለ ውህደተ-ቴክኖሎጂ በሚዲያው ዘርፍ ላይ ምን አይነት ተጽእኖ ያሳድራል የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እያነጋገረ ነው። እንደ ምሁራኑ አመለካከት ይህ የውህደት ሂደት በሚዲያው ዘርፍ ሥራ የሚያሳድራቸው ተጽእኖዎች በአራት መልኩ ይገለጻሉ። የመጀመሪያው የተቀናጀ የሚዲያ ይዘት ዝግጅት (integrated production) እንዲከናወን ማስቻሉ ሲሆን ይህም ማለት ውህደተ-ቴክኖሎጂ በፈጠረው እድል በመጠቀም የተለያዩ የሚዲያ ድርጅቶች የሰበሰቡትን የዜና ዘገባ በጋራ የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል ማለት ነው። ይህ የሚደረገው በመሰረቱ ወጪን መቀነስ ያስችላል በሚል እሳቤ ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ውህደተ- ቴክኖሎጂ ባመጣው እድል በመጠቀም 30 በመቶ የሚሆኑ የጋዜጣ አሳታሚዎች ዜናን የመከፋፈል ስምምነት አላቸው። ይህ ማለት የአንዱ ሚዲያ ጋዜጠኛ የዘገበውን ዜና ሌሎች የስምምነቱ አካል የሆኑት የሚዲያ ድርጅቶች እንዲጋሩት መፍቀድ ማለት ነው።

ሁለተኛው ተጽእኖ ደግሞ በዚህ እየተለወጠ ባለው የሚዲያ አካባቢ የሚሰሩ ባለሙያዎች የተለያየ ክሂሎት እንዲኖራቸው ግድ ማለቱ ነው። ይህም ጋዜጠኛው በመጀመሪያ በተለያዩ ርእሶች (ፖለቲካ፣ ስፖርት፣ ሳይንስ፣ ቢዝነስ ወዘተ.) ላይ ሳይመርጥ እየለዋወጠ እንዲዘግብ ማስፈለጉ፤ ቀጥሎም ጋዜጠኛው የሚዘግባቸውን ዜናዎች ለተለያዩ የሚዲያ አይነቶች (ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን፣ ኢንተርኔት) በሚመች መልኩ መላልሶ በመፃፍ የማቅረብ ችሎታ እንዲኖረው ማስፈለጉ ነው። ሌላኛው ደግሞ ጋዜጠኛው በሁሉም የዜና ዝግጅት ደረጃዎች ላይ ያሉትን ተግባራት (መረጃ መሰብሰብ፣ ዜና መፃፍ፣ የድምጽም ሆነ የምስል አርትኦት

“ውህደተ-ቴክኖሎጂ ብዙ ዘርፎችን ከማሳተፉ የተነሳ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚካሄዱ ጥናቶችም እንዲሁ ከተለያዩ ዘርፎች በተውጣጡ ተመራማሪዎች (interdisciplinary) በጥምረት እንዲካሄዱ ግድ ብሏል”

ማካሄድ) ራሱን ችሎ ያለ ማንም እርዳታ ለማከናወን መቻል ያለበት መሆኑ ነው። ይህ አሰራር የሚዲያ ተቋማትን ትርፋማ ለማድረግ ቢያስችልም የጋዜጠኛውን ስራ ግን በጣም እንደሚያከብደው ብዙዎች ይናገራሉ።

ሶስተኛው ተጽእኖ ደግሞ አንድ የሚዲያ ድርጅት ራሱን በተለያዩ መድረኮች (platforms) እንዲያቀርብ መገደዱ ነው። ይህ ማለት አንድ የጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት እንደ ድሮው ጋዜጣ አሳትሞ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ኢንተርኔትን በመጠቀም የምስልና የድምፅ መረጃዎችንም ይዞ እንዲቀርብ ሁኔታዎች ማስገደዳቸው ነው። እንዲህ ያለ አሰራር የመጣው ብዙ ተደራሽ ለማግኘት የሚደረገውን ውድድር ለማሸነፍ እንደሆነ ይነገራል።

 የመጨረሻውና አራተኛው የውህደተ- ቴክኖሎጂ ተፅዕኖ ደግሞ አዲሱ ጥበብ ባመጣላቸው እድል ምክንያት የተደራሾች የሚዲያ አጠቃቀም መቀየሩ ነው። ሰዎች እንደ ድሮው ጠዋት ጋዜጣ እያነበቡ ከቤት የሚወጡበት ልምድ በኢንተርኔትና በማህበራዊ ሚዲያ መምጣት ምክንያት መለወጡ አንድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ይህ የባህሪ ለውጥ ብዙዎቹን በሚዲያ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ሰዎችን እያሳሰበ በመምጣቱ የመገናኛ ብዙሃን አቀራረባቸውን ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ ለመፈተሽ እየተገደዱ ነው። ይህም አሰራራቸውን በፊት ከነበረው የአቅራቢ ተኮር ሞዴል (offer focused model) ወደ ፍላጎት ተኮር ሞዴል (demand focused model) እንዲቀይሩ እያስገደዳቸው ይገኛል።

ይህም አዲስ ሞዴል የሁሉም የሚዲያ ዘውጎች ይዘት በተደራሹ ፍላጎት ላይ ብቻ ተመስርቶ እንዲቀርብ አስገዳጅ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። የሚዲያ ድርጅቶችም በሁሉም የማቅረቢያ ዘዴዎች (platforms) ተጠቅመው ይዘትን ማቅረብ አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን እየተረዱ መጥተዋል። በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የሚዲያ ቴክኖሎጂ ተመልካቹን ራሱ የዜና ይዘት ፈጣሪ እንዲሆን ማስቻሉ ተደራሹ ተጠቃሚ (consumer) ብቻ ሳይሆን መረጃ አቅራቢ (producer) እንዲሆን ማስቻሉ በጋዜጠኛና በተደራሽ መካከል የነበረውን ልዩነት በማጥበብ ላይ ይገኛል። ምሁራኑ ይህን ሁኔታ፣ የሁለቱን (የጋዜጠኝነትን እና የተደራሹን) ሚና በማጣመር የዛሬውን ተደራሽ ፕሮሲዩመር (prosumer) ብለው ይጠሩታል።

 ይህ የውህደተ-ቴክኖሎጂ ክስተት በኛ ሃገር ተጽእኖው በሰፊው እየታየ ነው። ያመጣው ጫና ወይንም ተፅዕኖ ግን በቅጡ የተጠና አይመስልም። ስለዚህ ውህደተ-ቴክኖሎጂ በሚዲያዎቻችን ላይ በሚያደርሰው ለውጥና ለለውጡ መደረግ ባለበት ዝግጅት ላይ የዘርፉ ምሁራን ወደፊት ከማህበረሰቡ ብዙ ጥያቄዎችን እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top