የታዛ ድምፆች

“ልጄ ቆማ ቀረች”

“ሴቷ ልጄ ዕድሜዋ ሃያ ስድስት ነው:: በመምህርነት ሙያዋ ምስጉን ለመባል በቅታለች። ግና ዳሩ እስከ አሁን ድረስ ፍቅረኛ የሌላት በመሆኗ ታሳዝነኝ ጀመር:: ሳታገባ የማርጀቷ ነገርም አስግቶኛል። ታዲያ ምን ትሉኛላችሁ?” ሲሉ አንዲት እናት ችግራቸውን በጋዜጣ አውጥተው ያስነበቡት ይታወሳል።

 “ልጄ ቆማ ቀረችብኝ” የሚሉትን ጀርመናዊት ወይዘሮ ፍሬ ቢስ ጥያቄ እንዳቀረቡ የተመለከቱ አንባብያን አልተገኙም። ስለምን? ጋብቻ ኮሰመነ፣ ትዳር ምሥረታ መነመነ ሲባል የተድላ ብሥራት አይደለምና “ፍቅር መሰከነ” ተብሎ ሲነገርም በሐሴት አያስፈነድቅምና!

በሌላ በኩል ግን ጥያቄው መቅረብ ከነበረበት ቦታ ሳይነሣ የመጠየቅ መብት ባልተሰጠው ግለሰብ (እናት ቢሆኑም) በመሰንዘሩ ፈጥኖ ፈዋሽ የሆነ የመማክርት ረድኤት ሊታደል አልበቃም። በሊቃውንቱ አስተሳሰብ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት በራሷ በልጅቷ ብቻ ነው።

“እርስዎ ወልደው ከብደው ሊታዩ እንደቻሉት ልጅዎም ይህን የሕይወት በረከት ታገኝ ዘንድ ልባዊ ምኞትዎ መሆኑ መልካም ነው። ይሁንና የዘመኑ ወጣቶች የትኛውን፣ የትኛዋን እንደሚያፈቅሩ ከማንና ከምን ጋር እንደሚተሳሰሩ፣ መቼ እንደሚያገቡ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ውሳኔውን ለልጅዎ ብቻ መተው እንጂ በጣልቃ ገብነት ማስቸገር አይኖርብዎትም።” እናትዬዋ ያገኙት ይህን መሰል ምላሽ ነው። ዛሬ ወልዶ እናት ለመሰኘት ብቻ የሚጥሩ ኮረዶች የሉም። ተምረው፣ ከወንዱ እኩል ተመራምረው ላቅ ወዳለ ደረጃ ለመድረስ ሴቶች ይፈልጋሉና ከራስዎ ነባር ሕይወት ጋር አዛምደው አይመለከቱትም? ሲሉም በማከል ለጥያቄው ምላሽ ሰንዝረዋል።

ጉዳዩን ጠለቅ ብለው ሲመረምሩት እናት ለልጇ ወይም አባት ለልጁ እንዴት ክፉ ሊያስብ ይችላል? የወላጆች ምክርስ ለልጆች አይጠቅምምን? የተሰኙትን ጥያቄዎች ይደቅናል። በመሠረቱ የልጁን ውድቀት፣ ጉዳት የሚመኝ ወላጅ አለ ለማለት ያዳግታል። ብሎም ቢሆን ሴት ልጆቻቸውን ለባለጸጋ ለመዳር ማለፊያ አማች ለማግኘት ሲሉ ሸፍነው የሰጡ (የሸጡ ማለት ያስደፍራል) ወላጆች በእኛ ኅብረተሰብ የነበሩ መሆኑን ዛሬም አልፎ አልፎ መታየታቸውን እናውቃለን። እነዚህ ዓይነቶቹ እናትና አባት በቅን አሳቢነት ደረጃ ሊመደቡ ይችላሉ አይባልም።

 “ልጄ አደራሽን እንዳታዋርጂኝ” እያሉ የመውጫዋን፣ የመግቢያዋን ደቂቃና ሴኮንድ እየተቆጣጠሩ ለወደፊት አማች ለብር አምባር ቀረርቶኛ የድንግል ዘበኝነታቸውን ያሳመሩ ወላጆች እንደነበሩ፣ ዛሬም እንዳሉ እንረዳለን። የቅድመ ጋብቻ ወሊድ በማኅበራዊው ኑሮ ላይ የሚቆልለውን አንዳች የሚያህል ጫና ሳንገነዘብ ቀርተን አይደለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደታዘበው ግን የወላጆቹ ጭንቀት “ሳታገባ ወለደች” ከተባለ ስማቸው በየመንደሩ፣ በየሠፈሩ ስለሚጠፋና ላሰቡት ለመዳር ቢፈልጉም የድንግል ዋስትና መስጠት ስለሚኖርባቸው በዚህ ያፈጀ ወግና ሥርዓት ተተብትበው እንጂ አብዛኞቹ ስለማህበራዊ የኑሮ ውጥንቅር ተረድተው አይደለም። ለመረዳት የማይሹም አሉ።

 ይህ ጉዳይ በየወቅቱ የተጻፈበት ነውና በዚህ ላይ ሰፊ ትንታኔ ለማቅረብ አልሞክርም። ይሁንና ጀርመናዊው የሥነ ልቡና ተጠባቢ ሐንስ ኒገንናበር ማን ከየትኛው (ከየትኛዋ) ጋር እንደሚፋቀር፣ መቼ በጋብቻ እንደሚተሳሰር፣ መቼ ጋብቻ እንደሚያዋቅር የራሱ የባለጉዳዩ ግላዊ ውሳኔ እንጂ የወላጆች ብያኔ ሊሆን እንደማይገባው የጻፉት ለጥቅስ የሚበቃ ነው። ምናልባት (በእኔ አስተሳሰብ) ራሱን ከዘመኑ ሕይወት ጋር ያስተዋወቀ፣ በባህል ዕድገት፣ በሥልጣኔ የተራመደ አንዳንድ ወላጅ ሊመክር ይችል ይሆናል። ያም ቢሆን ግን በውሳኔው ላይ አንዳች ተጽዕኖ ማድረግ አይኖርበትም። ከዚህ ባሻገር ደግሞ እንደ ጀርመናዊቷ ወይዘሮ “ልጄ ቆማ ቀረች” ማለትና አያገባው ገብቶ መጨነቅ የለበትም። በሀገራችንም “ከባለቤቱ ያወቀ……….. ነው።” የተሰኘ ብሂል አለና!

 መቼም የየግለሰቡ ችግር እንደየ ሁኔታው የተለያየ መልክ ያለው መሆኑ አይካድምና አንድ ጉብል ያሠፈረውም ጥያቄ ይጠቀሳል። እንዲህም ይነበባል፡–

 “እወዳታለሁ፣ ታፈቅረኛለች፡ ከወላጆቼ ጋር ብኖርም ወደ እኔ ቤት ለመምጣት አትከለከልም። ወደእርሷ ቤት ለመግባት ግን ወላጆቿ አይፈቅዱልኝም። አንዳንዴ በድፍረት አስገብታኝ በክፍሏ ውስጥ ተቀምጠን በምንገኝበት ጊዜም እናትዬዋ አስሬ ሲያልፉና ሲያገድሙ በዓይናቸው ሲቃኙን ይውላሉ። ምን ማድረግ ይበጅ ይሆን?”

እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ ለባሕር ማዶኞች እንደ ሐሳብ ወለድ ተረት መምሰሉና መሳቂያና መሳለቂያ መሆኑ ባይጠረጠርም በእኛ ኅብረተሰብ ዘንድ ግን በቁጥር የሠፈረ ችግር መሆኑን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በውል ያረጋግጣል።

እንኳን እቤት የማስገባት ጥያቄ ሊያቀርብና ከወላጆቹ ጋር ሆኖ የሚወዳትን ኮረዳ በጎዳና ስታልፍ ቢመለከት አይቶ እንዳላየ የሚሆን ጉብል ሞልቷል። በትምህርት ቤት ሲያጫውታት ወይም እንደ ነገሩ በኳስ ሜዳ ሲያዛልላት የሚውለውን ከዚያም አልፎ የሚወዳትን፣ ያበደላትን፣ እርሷም “ሞትኩልህ” ያለችውን ከእናት ከአባቷ ጋር ሆና ፒያሳ፣ መርካቶ፣ እስታዲዮም ብታገኘው ፊቷን ታዞርበታለች። አባባና እማማ እንዳይቆጡ!

 አንድ አያውቄ አባት “ምነው ይኸ ልጅ አንቺን እያየ ይስቃል?” ብለው ቢጠይቁ “ምን አውቄ ሊመነትፍ ይሆናላ፣ የዛሬ ሌባ አሳስቆ አይደል!” በማለት ወዳጇን ኪስ አውላቂ ያደረገች ነበረች። ሳትወድ በግድ፣ በጎታች ባህል ተጽዕኖ!! በኋላ ግን ተጋብተው፣ ወልደው ከብደው የትዝታቸውን ቁራሽ ሊያድሉን በቅተዋል።

 “ለመሆኑ ወላጆች የልጆቻቸውን ፍቅረኞች ለመተዋወቅ የማይሹበት ምክንያት ምን ይሆን? ልጆችስ የሚያፍሩበት?” ለእነዚህ ጥያቄዎች አርኪ ምላሽ ለመስጠት አሁን፣ አሁን የሚቻል አይመስለኝም። የባህል ዕድገትን፣ የአስተሳሰብ ለውጥን የሚፈልግ ነውና! በጥቅሉ ግን ኋላ ቀርነት ከማለት ሌላ የምናወድስበት ልዩ ቋንቋ አይኖረንም።

 በእርግጥ ቆነጃጅቱም ሆኑ ጎበዛዝቱ በስሜታዊ ብስለት ሳይደነድኑ በግብታዊ መውደድ ታውረው “ዛሬ እገሌን፣ ነገ እገሊትን በተራ እናስተዋውቃችሁ” ሊሉና ወላጆቻቸውን ሊያስቸግሩ አይገባም። “ልንጋባ በመወሰናችን…..” ብሎ የቅድመ ውሳኔ ምስክርነት መስጠቱ፣ በቃል መፈጣጠሙ ቢያዳግትም ረዘም ላለ ጊዜ አብረው መሆናቸው ከታወቀ ግን ወላጆችም ቢተዋወቁላቸው ቤተሰባዊውን ፍቅር የጸና ያደርጋል የሚለው የብዙዎች እምነት ነው። “መጀመሪያ፣ እኛን ጠይቁ እንጂ…..” የሚባለውና በአማላጅ ግትልትል የሚካሄደው ትውውቅ ግን በዘመኑ ሥልጣኔ እዚህ ግባ የሚሰኝ አይደለም። ያረጀ ወግ ነው። ከማርጀትም አልፎ ያፈጀ ነው። “ቆማ ቀረች” ማለትም ሆነ የወደደችውን እንድታፍርበት መጫን ጊዜ ሊሽረው የተገባ ጎታች ባህል መሆኑን ብዙዎች የሀገራችን ሰዎች ይገነዘቡ ዘንድ የተገባ ሳይሆን አይቀርም።

ይህ ያረጀ፣ ያፈጀ ወግና ባህል ግን ሊቀር የሚችለው በማስተማር፣ በመማር፣ በመማማር ነው። በትግል ነው። በጋዜጦች በመወያየት ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥ ነው። እንዲያውም የቤተሰብ ጉዳይ እያነሱ መተረኩ ፋይዳ አለው ወይ? ብለው የሚጠይቁም ይኖራሉ።

ማለፊያ ብዕራቸው ሞገስ ይሁንላቸውና ፔርል በክ የማናቸውም ባህል ጥራቱ የሚመዘነው በሚያፈራው ዜጋ ልክ ነው። ያሉት ምላሽ የሚሰጥ ይመስለኛል። ግለሰብ፣ ብሎ ቤተሰብ፣ ከዚያም “ኅብረተሰብ” መሰኘቱንና እንዲያ ሲልም የሀገር ጉዳይ መሆኑን ለማወቅ አይሳነንምና!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top