ጣዕሞት

‹‹ ፍካሬ ሞት ወ-ሕይወት ›› መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ

በቃኘው ወልዱ የተዘጋጀው ‹‹ፍካሬ ሞት ወ-ሕይወት›› የተሰገኘ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ የበቃው ሰሞኑን ነው:: መጽሐፉ በ410 ገጽ እና 8 ምዕራፎች ውስጥ ጥልቅ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን እያነሳ ከእምነት፣ ከማንነት ከሞራልና ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር ቁምነገሮችን ያስጨብጣል:: በእነዚህ ጉዳዮች የሚነሱ ፍልስፍናዎችን እያጣቀሰ ግንዛቤን የሚፈጥረው ይህ መጽሐፍ፤ አዕምሮን ሰቅዞ የመያዝ ብርታት እንዳለው ተነግሮለታል::

 በመጽሐፉ መቅድም ላይ እንደተገለጸው፤ መጽሐፉ በእግዚአብሔር ፍፁም ፍቅርና ምህረት ላይ የተመሰረቱ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሳት ይጠይቃል፤ ይሞግታል፤ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፤ ፍጥረት ራሱን በራስ ያስገኘ አለመሆኑን ያትታል:: ይልቁንም በሰው አፈጣጠርና ክብር ፣ በሕይወትና ሞት ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ ይሰጣል:: ሰው ፈጣሪውን የሚወደው፣ የሚያመሰግነውና የሚያመልከው በግድ ሳይሆን፤ በፍቅርና በነፃነት መሆኑን ከበቂ ማጣቀሻ ጋር ማብራሪያ ይሰጣል::

145 ብር ዋጋ ያለው ይህ መጽሐፍ ሰሞኑን በመሸጥ ላይ ይገኛል::

“ኩሳ” የተሰኘ የኦሮምኛ መጽሐፍ ተመረቀ

በዮናታን ኢቢሳ ስዳ የተዘጋጀውና ‹‹ኩሳ›› የተሰኘ የኦሮምኛ መጽሐፍ በኦሮሞ ባህል አዳራሽ የተመረቀው ሰሞኑን ነው:: ርዕሱ ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹‹ድልብ›› የሚል ትርጓሜ የሚሰጠው ይህ መጽሐፍ፤ ግጥሞችን፣ ኦሮምኛ ባህላዊ አባባሎችና ተረቶችን አካቷል::

 ለ18 ዓመታት በውጭ አገር ቆይተው በቅርቡ ወደ አገራቸው የተመለሱት ጸሐፊው፤ ስለ አገራቸው የነበራቸውን አስተውሎት ጠብቀው ለአንባቢያን ያደረሱት፤ በማህበራው፣ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚዊ፣ ባህላዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የሚያውቁትንና ለአንባቢያን ቢደርስ ጠቃሚ ይሆናል ያሉትን ነው::

183 ገጽ ያለው መጽሐፉ፤ በ90 ብር በመሸጥ ላይ ነው::

‹‹ የንስሐ አባት እና የንስሐ ልጅ ድርሻ ››

መጽሐፍ ተመረቀ

በመምህር ቀሲስ አንድነት አሸናፊ እና በመምህር ዲ/ን ፋሲል አስቻለው ‹‹ የንስሐ አባት እና የንስሐ ልጅ ድርሻ ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው አዲስ መንፈሳዊ መጽሐፍም የተመረቀው በቅርቡ ነው::

አባቶች ካህናት፣ ምሁራንና ጥሪ የተደረገለ፤ቸው እንግዶች በተገኙበት ሰሞኑን በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርሲቲ ኮልጅ ውስጥ በተከናወነው ምረቃ መርሃግብር፤ ባለንበት ዘመን የሰው ልጅን ከመጥፎ ምግባር የሚገራ አስተማሪ መጽሐፍ በብዙ ያስፈልጋል ተብሏል::

 በመጽሐፉ ዙሪያ አጭር ዳሰሳ የቀረቡት መምህር ግርማ ባቱ እና መምህር አካለወልድ ተሰማ፤ መጽሐፉ ከሃማኖታዊው ዋጋው ባለፈ፤ ላነበበው የጥሩ ስነ ምግባር ባለቤት የሚያደርግ ምክርና አስተምሮ አለበት ብለዋል::

 በሦስት ምዕራፍ ስር በርካታ ንዑስ ክፍሎች ያሉት ይህ መጽሐፍ፤ 350 ገፆች ያሉት ሲሆን፤ በ150 ብር በመሸጥ ላይ ነው::

ሲያምሽ ያመኛል በኮንሰርት

በቅርቡ ‹‹ሲያምሽ ያመኛል›› የተሰኘ አልበም ለገበያ ያቀረበው ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ በጊዮን ሆቴል ሙዚቃ ኮንሰርት ሊያቀረብ መሆኑ ተሰምቷል::

በተለያየ ደረጃ መግቢያው ከ300 እስከ 900 በሆነበት በዚሁ ኮንሰርት ከ 10 ሺ በላይ የሙዚቃ አፍቃሪዎች ሊታደሙ እንደሚችሉ ኮንሰረቱ አዘጋጅ የሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃ/የተ/የግ/ማ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዶኒክ ወርቁ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል::

ይህ መጀመሪያው ኮንሰርት የዳግማተነሳይ ዕለት ዋዜማ ሚያዚያ 26/2011 ዓ.ም ምሽት የሚካሄድ ሲሆን፤ በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ከዚያም አልፎ በውጪ አገራት እንደሚካሄድ ተናግረዋል::

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሹም ሽር ተደረገ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መምህር ዶ/ር ሙሉጌታ ፍስሃ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል::

 ባለስልጣኑን ለስምንት አመታት የመሩትን አቶ ዮናስ ደስታን የተኩት እኚሁ ምሁር፤ በዶክተር አብይ አህመድ ደብዳቤ ሹመቱን እንዳገኙ ነው የተሰማው::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ- ጥበብና ታሪክ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መምህር የሆኑት አበባው አያሌው ደጎሞ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውም ተሰምቷል::

‹‹ ክብረ ጊዜ – ክብረ ሰው ›› ለምረቃ በቃ

በአምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ተዘጋጅቶ በቅርቡ ለንባብ የበቃው ‹‹ ክብረ ጊዜ – ክብረ ሰው ›› የተሰኘ መጽሐፍም በስካይ ላይት ሆቴል ባለፈው መጋቢት 29/2011 ዓ.ም ለምረቃ በቅቷል::

በርካታ የጥበብ አፍቃሪዎች፣ የሃይማኖት፣ አባቶች ደራሲዎችና ከፍተኛ መንግስት ስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመረቀው ይህ መጽሐፍ፤ ሰውና ጊዜ ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት ተንትኖ የሚያሳይ ነው:: የሰው ልጅ ጊዜን በአግባቡ ሲጠቀምበት ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም ያስገነዝባል::

አምባሳደር ሙሉ፤ ከአሁን ቀደም ‹‹ግዜና ሌሎች››፣ ‹‹ሲንቢሮ››፣ ‹‹ስንክፍሬ››፣ እና ‹‹እጣ›› የተሰኙ የወግ፣ የልቦለድና ግጥም መጻሕፍትን ለንባብ ማብቃታቸው የታወቃል::

የ ‹‹ሂፓፕ›› አቀንቃኙ አለፈ

የ2018 ግራሚ አዋርድ ዕጩ የነበረው ከኤርትራዊ አባት የተወለደው የ33 ዓመቱ ወጣት ኤርሚያስ አስገዶም ሰሞኑን ህልፈቱ ከወደ አሜሪካ ተሰምቷል::

 ‹‹ኒፕስይ ሃሰል›› በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ይህ ‹‹የሂፕ ሀፕ›› የሙዚቃ ስልት አቀንቃኝ፤ በልብስ መሸጫ ሱቁ /Marathon Closing/ አጠገብ እንዳለ ድንገት በተተከሰ ጥይት ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል:: ኤርሚያስ ባለፈው ዓመት ‹‹ቪክትሪ ላቭ›› የተሰኘው አልበሙ በተለያዩ መድረኮች ላይ ምርጥ አልበም ተብሎ ይጠራ እንደነበር ይታወቃል:: በዓለም የሙዚቃ ተርታም የ4ኛ ደረጃነትን ሊይዝም ችሏል:: አርሚያስ ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበር::

ኤርሚያስ አሜሪካ በሚገኙ የኤርትራን ማህበረ-ሰብ ጨምሮ በተለያዩ ኮሚኒቲዎች ላይ በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ ይሳተፍ እንደነበር ይታወቃል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top