ፍልስፍና

ጾም እና ፍልስፍና “ንጹም ጾምነ ወናፍቅር ቢጸነ”

መንደርደሪያ

ስለ ጾም ሲነሳ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የጾም ዓላማ ምንድን ነው? መጾም የፈጣሪ ትዕዛዝ ወይስ ለሰው ልጆች የሚበጅ ምድራዊ የሃይማኖት፣ የባህል ወይም የፍልስፍና ምክረ ሐሳብ ውጤት? አሁን እያየናቸው ካለነው የሃይማኖት የጾም ትዕዛዞችና ሥርዓት ውጭ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንድምታ አለው ወይ? ይች ጽሑፍ እነዚህን ጥያቄዎች እንደመነሻ በመያዝ የቀረበች ዲስኩር ናት። ለጽሑፏ መነሻ ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የታወቀው የዓብዪ ጾም ወቅት ላይ መሆናችን ነው። የህዝቡን ቁጥር በወል ባላውቀውም (ሁሉም እኛ ብዙዎች ነን በሚልበት በዚህ ዘመን፣ የሕዝብና የቤት ቆጠራው የተራዘመበትና ወደ መቶ አስር ሚልዮን እንጠጋለን በሚባልበት በዚህ ወቅት እንዴት ላውቀው እችላለሁ?) የተለመደውን አጠቃሏዊነትና ከተጠያቂነት ማምለጫ ዘዴ በመጠቀም “በርካታ ተከታይ” ያላት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የምታውጀው ጾም በሚል ልለፈው። በርካታ ተከታይ የሚጾም ከሆነ የጾሙ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ በግልና በማኅበራዊ ሕይወታችን ዘንድ ከሚገኘው ትሩፋት ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል እንዴት ይጠቀምበታል? የሚል ጥያቄ ተገቢ ነው።

 በዚህ አካሄድ ሁሉም ሃይማኖቶች (የተለያዩ ክርስትናዎችና የእስልምና እንዲሁም ሌሎች የአገር በቀል እምነት ተከታዮች) የራሳቸው የጾምና የአርምሞ (ከምግበ መጠጥ፣ መጥፎ ንግግር፣ እኩይ ምግባር ወዘተ መታቀብ) ትዕዛዛትና ሥርዓቶች አሏቸው። በዓመት ውስጥ እንግዲህ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚጾሙበት ወቅት የሚያመጣው አገራዊ ድምር ውጤት ምን ይመስላል? የሚል የሥራ ፈት ወይም የአገር ጉዳይ የሚያገባው ሰው ምርምር ውስጥ መግባታችን አልቀረምና አብረን እንመራመር በሚል ለማጋራት ፈለግን (እኔና ብዕሬ ተነጋግረን የወሰንነው ነው።) ሐሳቡን እንዲሁ ጠበብ ለማድረግ ሲታሰብ የፈላስፎቹ ነገር ታወሰን እንጅ ጦም (ጾም) በተለምዶ እንደምናውቀው የሃይማኖቶቹ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሳይንስ ተመራማሪዎችን፣ የሥነ ልቡና ባለ ሙያዎችን፣ ፈላስፎችንም ጭምር ያነጋግራል፣ የጥናታቸውም ጉዳይ ሆኗል። የፈላስፎቹ እሳቤዎች ላይ ትኩረት አድርገናል ማለት ሌሎቹን በፍጹም አንመለከታቸው ማለት አይደለም። እንደየ አስፈላጊነቱ ከሁሉም እየጠቃቀስን እንመለከታለን።

 ጾም ምንድን ነው? ቃላዊ ትርጓሜው ጾም ማለት በቀጥታው መከልከል ማለት ነው። ለተወሰነ ጊዜ ከተወሰነ ነገር መራቅ እንደማለት ነው። በልሳነ ግዕዝ መዝገበ ቃላት ፊታውራሪው የቀለም ቀንድ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንዲህ ተርጉመውታል። “መጾም ጥሉላትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከመብል ከመጠጥ ከሌላውም ሁሉ ከክፉ ነገር መከልከል መጠበቅ። ቦኑ ጾመ ዘጾምክሙ ሊተ አኮ ጸዊም እምኅብስት ወማይ ባሕቲቱ። ትጹም ልሳንክሙ እምነገረ ውዴት። ለእመ ኮንከ ዘኢትክል ትጹም እመባልዕት ጹም እንከ እምኅሊናት እኪት።” (ገጽ 746) እነዚህ ቃላት የጾምን አንድ ገጽታ በግልጽ ያሳያሉ። እንደ ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች ከሆነ ጾም ሁለት መሠረታዊ ይዘቶች አሉት። አንደኛው መከልከል ነው። ከተወሰኑ የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች፣ ወይም ከሁሉም ምግበ መጠጥና ግብረ ሥጋ እንደየ ጿሚው አቅም ለተወሰኑ ሥዓታት የሚከለከልበት ሥርዓት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የትሩፋት ሥራ የሚያዘው ነው። በጾም ወራት ምጽዋትና የተቸገሩትን መርዳት አንዱ የጾም አካል ነው። በኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትርጓሜ መሠረት ጾም መከልከል የሚለውን ክፍል ብቻ የያዘ ነው። ከምን መከልከል። የመጀመሪያው ከምግበ መጠጥ ነው። ሁለተኛው የልሳን መጾም ነው። በንግግር ሰዎችን ከማስከፋት መቆጠብ። ሦስተኛው ኅሊና ከእኩይ ሐሳብ መጾም ነው።

 ከተጠቀሱት የግዕዝ ቃላት እንደምንረዳው ከምግብ መጠጥ መከልከል የማይችሉትን እንደ ነፍሰ ጡሮች፣ እመጫት፣ ሕመምተኛ፣ በእድሜ እጅግ የገፉትን ወይም በልዩ ልዩ ምክንያት መጾም የማይችሉትን በሙሉ ከክፉ ሐሳብና ንግግር እንዲጾሙ ያመላክታል።

አለው። ሰው ወደ ሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በሥጋው ጤንነትና በመንፈሱ ሰላም፣ በነፍሱ እርካታ ነው። አንዱ ከተረበሸ ሌላኛው ጤና ሊሆን አይችልም። ይህ የሚሆነው ደግሞ የሁለቱም ፍላጎት ሲሟላ ነው። እንደ አብዝሃኛዎቹ የሃይማኖት አስተምህሮዎች ደግሞ በሁለቱ በመካከል የፍላጎት ተቃርኖ (Conflict of Interest) እንዳለ ነው። ነፍስ ሰማያዊ፣ ዘልዓለማዊነትን ወደሚያረጋግጥላት ወደ ፈጣሪ ልቅረብ ስትል ሥጋ ደግሞ ምድራዊነትን፣ ስሜትን የሚያዳምጥ የፍላጎት ቋት፣ የማይሞላ አቁማዳ ተደርጎ ተስሏል። የነዚህ የሁለቱ አማካኝ ቦታ፣ መገናኛ ደግሞ በሁለቱ ፍላጎቶች የተወጠረው ሰው ነው። የለባዊት ነፍስ (Rational Soul) ባለቤት ተደርጎ ተስሏልና የነፍሱን ዘልዓለማዊነት በመረዳቱ ክፉና በጎ ነገሮችን በመለየቱ የሕይወቱን ጉዞ መንገድ አበጅቷል። ለዚህ ነው የሥጋውንና የነፍሱን ፍላጎቶች ለማርካት ሲባክን የሚኖረው። በሃይማኖቱ ደግሞ በሁለቱ ፍላጎቶች መካከል መመዛዘን ወይም የነፍሱ ፍላጎት ድል እንዲነሳ መላ ተዘይዷል። ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ስግደት። እነዚህ ሁሉ ሥጋን በማዳከም ለነፍስ የማስገበር ሥራዎች ናቸው። የጾም ታሪክ ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር እኩል ነው የሚሉ በርካታ ናቸው። በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ የሕክምና ታሪክ ጾም የህክምና እና የጤና አጠባበቅ አንዱ አካል ተደርጓል። ጤና ደግሞ ነፍስና ሥጋን የሚመለከት ጉዳይ ነው: አካላዊ ጥንካሬና የመንፈስ፣ የነፍስ ሰላምን የሚያካትት ስለሆነ የሁለቱ ጤናማነትና በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት የፍልስፍና አንዱ ጥያቄ ነው።

 ፈላስፎቹ ይህንን የነፍስና የሥጋን ጥያቄ እንዴት አስተናገዱት? ከአስተሳሰባቸውስ ውስጥ የጾምን አንድምታ እንዴት መረዳት እንችላለን? የጥንቱ ፈላስፋ ፓይታጎራስ ዕጸ በልነትን (Vegiterianism) የሚያቀንቀን የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሮለታል። የርሱ ዓላማ ሰማያዊ ክብርን በመሻት የተደረገ የጾም መርህ እንዳልሆነ ግን ግልጽ ነው። በርሱ እሳቤ አንድም የነፍስ ከአንዱ ፍጥረት ወደ ሌላው መተላለፍ እሳቤ ምናልባትም አርደን የምንበላቸው እንስሳት የኛው ወገኖች ናቸው፣ ልንራራላቸው ይገባል ከሚል እሳቤ ነው። በሌላ በኩል መጾም ለኅሊና አስተሳሰብ ጥራትንና የአካል ጥንካሬን ያመጣል የሚሉት የፓይታጎሪያን አስተሳሰብ በጥንታዊ ግሪክና በሌሎች ባህሎችም ቅቡልነት የነበረው ጉዳይ ነው።

 የነፍስና የሥጋ ነገር ቀድሞ ካሳሰባቸው ፈላስፎች መካከል ፕሌቶና አሪስቶትል ይገኛሉ። እንደነርሱ አስተምህሮዎች ነፍስ በሥጋዊ፣ በመንፈሳዊና በሕሊናዊ ጥያቄዎች የተወጠረች ስለሆነች አንድ ግለሰብ የተረጋጋ ሕይወትን ለመኖር ልብላ፣ ልጠጣ፣ ልዘሙት፣ ልግዛ፣ ልቆጣጠር የሚሉትን (የኛዎቹ መምህራን በጥቅሉ የሥጋ ፍላጎቶች ብለው የፈረጇቸውን) እና ልጠበብ፣ ልመሰጥ፣ ልመራመር፣ ልወቅ በሚሉት የነፍስን ሉዓላዊነት፣ የኅሊናን ልኅቀት በሚያረጋግጡት ፍላጎቶች መካከል እርቅ መፈጠር አለበት ይላሉ። ይህ እንግዲህ ተግባራዊነትን ከሥነ ምግባር በጎነት ጋር አስተባብሮ የያዘው የሠናይት (Virtue)  አስተምህሯቸው ዋና ምሰሶ ነው። ቁጡነትን በመቆጣጠርና ያልተገደበ የሥጋን ፍላጎት በመግታት የኅሊናን ምክንያታዊነት ከፍ በማድረግ ጥበብ ላይ መድረስ ይቻላል። ይህ ጥበብን ባለቤት የማድረግ ሥራ መገለጫው ሥነ ምግባራዊ በጎነት ነው። የሥነ ምግባራዊ በጎነት መገለጫው ደግሞ በግለሰቡ የተለያዩ ፍላጎቶች መካከል እርቅ ሲፈጸም ነው። ይህ ማለት በስጋና በነፍስ ፍላጎቶች መካከል ሚዛናዊነት ይኖራል ማለት ነው። ከተስተካከለ ኑሮ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የአሪስቶትል ወርቃማው አማካኝ (The Golden Mean) የሚለው እሳቤ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ነፍስ ከሥጋ እስር ቤት ነጻ ስትወጣ ነው። በምን መልኩ? ባንድም በሌላም መንገድ የጾምን መርሆዎች የሚያሟላ ሕይወት በመኖር ሊሆን ይችላል። የእንደዚህ ዓይነት ምግባረ ሰናይ ግለሰቦች ስብስብ ደግሞ የማኅበራዊ ሰላምን፣ ጠንካራና ፍትሐዊ መንግሥትን ይመሠርታል ይላሉ።

 የአሪስቶትል የቅርብ ርቀት ዘመን የነበሩ ፈላስፎች መካከል የአልተገደበ ደስታን

“አንዳንድ ጾምን በትክክል የሚተገብሩ ሰዎች በጾም ወራት ክርክር፣ አታካራ፣ ጭቅጭቅ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ሁሉ ርግፍ አድርገው ይተዋሉ። ይህም ከምግበ መጠጥ ተዓቅቦ በተጨማሪ ንግግርንና ሰዎችን የሚያስከፉ ተግባራትን ካለማድረግ ለመቆጠብ በማሰብ ነው”

ሕይወት የሚመክሩት ኢፒኩሪያኒስቶች ናቸው። የሰው ልጅ የሕይወት ግቡ የደስታ ሕይወትን መኖር ነው። ዛሬ ትሞት ነገ ትሞት አታውቀውምና በሕይወት ዘመንህ ደስ ብሎህ ኑር የሚል ምክረ ሐሳብ አላቸው። የደስታን ሕይወት የሚመዝኑት በኅሊና ሰላም ነው። ፍጹማዊ የኅሊና ሰላም የሚገኘው ምናልባትም በተመስጦና በአርምሞ ስለመሆኑ፣ የሥጋን ፍላጎት እንዴት ማስተናገድ ቢቻል ነው? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ መሠረታዊ እሳቤያቸው ጦም ከሚያስገኘው የሕሊና ሰላም፣ የነፍስ እርካታ ጋር ምስስሎሽ አለው። ነገር ግን የዚህ ሰላም ዓላማ የነፍስን ዘለዓላማዊት ሕልውና የተሻለ ለማድረግ አይደለም። ምክንያቱም በነሱ እሳቤ ሞት የሕይወት መጨረሻው ምዕራፍ ሲሆን የሚፈራ ፈጣሪም ሆነ የሚጠበቅ ተስፋ የለምና።

 ሃይማኖትና ፍልስፍናን ለማስታረቅ ብዙ የደከሙት የማዕከላዊ ዘመን ፈላስፎች ጉዳይ ወደ ሃይማኖታዊው እሳቤ ስለሚያመዝን የተለየ ነገር የለውም። ምድራዊውን ሕይወት በተወሰነ መልኩ ችላ በማለት ለሰማያዊ ሕይወት የሚሆን ስንቅን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ይህም በተሰበረ ልቡና ወደ ፈጣሪ በሚደረግ መቅረብ ረድኤተ እግዚአብሔርን ያስገኛል ይላሉ። የእውቀትም የምግባረ ሰናይም ምንጩ ይኸው ለፈጣሪ የሚሰጥ ፍጹም ፍቅር እና ለዚያው ማረጋገጫ በሚደረግ ምግባር ነው። ምላሹም ከፈጣሪ የሚገኝ ፀጋ ይሆናል።

ለዘመናዊ ፈላስፎች ራስ ምታት የሆነባቸው ጥያቄ የነፍስና የሥጋ ውሕደት ሥውር ምስጢር ነው። የፈረንሳዩ ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት የነፍስና የሥጋን ውሕደት ችግር ሲያትት ነፍስና ሥጋ ውህደት ወይም አብሮነት ጉዳይ ትልቁ ፈተና ሆኖበት ነበር። በርግጥ ሁለቱ የራሳቸው የተለያዩ ባህርያት አላቸው። የነፍስ ባህርይ ማሰብ ሲሆን የሥጋ ባህርይ ደግሞ መንቀሳቀስ፣ ግዙፍነትና ቦታ መያዝ ነው። ሁለቱ እንዴት አብረው ይኖራሉ? የሚለውን ሲመልስ ነፍስ እንደ ሞተር በግዙፉ አካል ውስጥ ተቀምጣ ማሽኑን ታሽከረክረዋለች የሚል እንድምታ ያለው ድምዳሜ ላይ ይደርሳል። የሁለቱ መገናኛ ቦታ ደግሞ Pineal Gland ነው ይለናል። በዴካርት እሳቤ ነፍስ አሳቢ፣ ተመራማሪና የሰው ልጅ መሠረታዊ የህልውናው መገለጫ ስትሆን ሥጋ ግን ሙያው መንቀሳቀስ ብቻ ነው። ታዲያ ይህች አሳቢት ነፍስ ወደ እውነትና ምግባራዊ በጎነት የምትቀርበው ፈቃድን (Will) ግንዛቤ ወይም በመረዳት (Understanding) ድል ስትነሳው ነው። ነፍስ ከፈቃድ ወደ መረዳት ለመጠጋት አርምሞ፣ ማሰላሰል ሊስፈልጋት ግድ ነው።

ያ የሚሆነው ደግሞ ምናልባትም የሥጋ ፍላጎቶችን (ካሉ) ድል መንሳት ይኖርባት ይሆን? ይህ ነገር ወደ ጾሙ መስመር የሚወስድ ቀዳዳ ይመስላል።

 በርሱው ዘመን የነበረው ዘርዓ ያዕቆብ የተሰኘው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ የጾምን ጉዳይ በግልጽነት እንደጻፈበት ከላይ ተጠቁሟል። የዘርዓ ያዕቆብ ሐተታ በምግበ መጠጥ ዓይነትም ሆነ በመመገቢያ ሥዓት የተገደበው የክርስቲያኖቹም ሆነ የእስላሞቹ ጾም ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ፍላጎቶች ጋርና ከፈጣሪ ቸርነት ጋር የሚሄዱ አይደሉ። ፈጣሪ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የግብረ ሥጋ ፍላጎቶችን ፈጥሮ በዚህ ጊዜ ብላ በዚህ ጊዜ አትብላ፣ በዚህ ጊዜ ተገናኝ በዚህ ጊዜ ተከልከል የሚሉ ትዕዛዛትን ሊያውጅ አይችልም። ባጭሩ ጾም ምድራዊ፣ ሰው ሰራሽ ትዕዛዝ እንጅ ሰማያዊ መለኮታዊ የፈጣሪ ትዕዛዝ ሊሆን አይችልም ይላል። በርግጥ ዘርዓ ያዕቆብ የነፍስን ከሥጋ ባህርያት ነጻ መውጣትና ሥነ ምግባራዊ በጎነትን አበክሮ ያስተማረ ፈላስፋ ነው። እንዲያ የሚሆነው ደግሞ የረሃብ አድማ በሚመስለው የይስሙላ የምግብ ምርጫና መከልከል ሳይሆን ለሰውነት የሚመቸውን ምግበ ሥጋና መጠጥ፣ በተገቢው መጠን በመመገብ እንዲሁም ለመብላትና ለመጠጣት አስፈላጊ በሆነበት ወቅት በመመገብ ነው። ከነፍስ ወይም ከኅሊና ጉዳይ ጋር በተገናኘም ነፍስ በለባዊትነቷ ተመራምራ ለደረሰችበት እውነት ተገዥ የሆነች እንደሆነ ምድራዊ በጎነትና ዘለዓለማዊ ትፍስኅትን ታገኛለች ይለናል። የጾም ደጋፊዎች እንደሚሰብኩን ፈላስፋው የተመጠነ ሕይወትን፣ የነፍስና የሥጋ ፍላጎቶች ሚዛናዊነት የተረጋገጠበትን ሕይወት ይሰብከናል። ከዝሙት፣ ከሥካር ወይም ከቁንጣን ነጻ ሆነን፣ ከሁሉም ሰዎች ጋር በፍቅርና በሰላም ጥበብን በመሻት እንድንኖር የሚያስተምረን ዘርዓ ያዕቆብ ሌላ የጾም መርህ እያስቀመጠ ይሆን?

እንደ ኒቼ ዓይነቶቹ “አፈንጋጭ” ፈላስፎች ደግሞ ሞራሊቲም ሆነ ሃይማኖታዊ ትዕዛዛት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህርይውን እንዳያሳካ ማዕቀብ የሚያኖሩ ማኅበራዊ ልጓሞች ናቸው ሲል ይተቻል። የሰው ልጅ ሲፈጠር ከመሆን ኃይል (The Will to Power) ጋር ስለሆነ ማንኛውም ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ሰው ሰራሽ በሆኑ ህግታት ሊገደብ አይገባውም ይላል። እነ ሳትረም የፈጣሪ ጣልቃ ገብነትን ያገለለ ዓለም በመፍጠር፣ ሰዋዊ የሆኑ የሞራል ሕጎችን ማመንጨት እንችላለን የሚል ሙግት ይዘው መጥተዋል። ሰው ለነጻነቱ የተተወ ነውና ይህን አድርግ ይህንን አታድርግ ሊባል አይገባውም ይላል።

 እንዲህ እንዲህ እያነሳን የፈላስፎቹን እሳቤ ከጾም ትርጓሜ ጋር ለማገናኘት ሞክረናል። አሁን ላይ እየወጡ ያሉ የሳይንስ ግኝቶች የጾምን ወይም ምግብን መርጦ የመመገብን አስፈላጊነት እያረጋገጡ ይገኛሉ። ለምሳሌ “Healthline” በተሰኘ ድረገጽ (https://www. healthline.com/nutrition/fasting-benefits# section2) ያገኘሁት ጽሑፍ ስምንት የጾም የጤና ጥቅሞች በሚል ርእስ ያሰፈረው ሐተታ ጾም የደም ዝውውርን በማፋጠን፣ የልብን ምት በማስተካከል፣ የአእምሮን ሥራ በማቅናት ከደም ግፊት፣ ከውስጣዊና ውጫዊ አካላዊ ቁስለት (inflammation)፣ ካንሰር ወዘተ በመከላከል ጤናማ ሕይወትን እንድንመራ ያደርገናል ይላል።

የምግብ ዓይነት መምረጡ መሠረታዊ ይዘቱ ምንድን ነው? አትክልትና ፍራፍሬ፣ አልኮል የሌላቸውና ከእንስሳት ተዋጽኦ ነጻ የሆኑ መጠጦች የኦርቶዶክሱ ጾም ማጀቢያዎች ናቸው። ይህ ለምን ሆነ? ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት የጠየቅኳቸው አንድ አባት “እግዚአብሔር ቀድሞ ያዘዘው እንስሳትን ሳይሆን እጽዋትን እንድንመገብ ነው። ጾም ደግሞ ወደ መቅድማዊ የንጽሕና፣ የታዛዥነት ሕይወት መመለስ ስለሆነ ነው።” ብለውኛል። በፋሲካ ወቅት ታዲያ ይህንን ብላ ይህንን አትብላ መባሉ ለምንድን ነው? ይህንም ሰፊ የሃይማኖትና የሳይንስ ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በዚህ ጉዳይ ስንወያይ “የሳይንሱ አስተምህሮ ለጤና ተስማሚ፣ ሃይል ሰጭና ንጹሕ ምግብ የሚገኘው ወደ ተፈጥሮ እየቀረብህ በሄድክ ቁጥር ነው።” ብሎኛል። ማብራሪያውን ሲያክልበትም ሥጋ በል እንስሳት ለምሳሌ እንደ ውሻ፣ አንበሳ መከልከላቸው ከሚመገቡት ምግብ የሚያገኙት የተፈጥሮ ጉልበት አናሳ ስለሆነ፣ ብንመገባቸው ትንሽ ጉልበት እናገኛለን፣ ለሰውነታችንም መርዛማ ሊሆንብን ይችላል። እንደ አህያና አሳማ ዓይነቶቹም የሚመገቡት ቆሻሻ ነገር ስለሆነ ሥጋቸው ጥሩ አይሆንም። በግና ፍየል ግን በተቻለ መጠን የተፈጥሮን ቅጠልና ሳር ስለሚመገቡ ቢያንስ በሁለተኛ ደረጃም ቢሆን የተሻለ ጉልበት፣ ንጽሕና ያለው ምግብ ይሰጡናል። ከሁሉም የሚበልጠው ግን ያለ ምንም ኬሚካል የተመረቱ ቅጠላቅጠልና፣ ፍራፍሬ፣ ብንመገብ የተሻለ ጉልበት እንዲሁም የጤና ጥቅም ይሰጡናል ብሎኛል። ሐሳቡ እንዲሁ የሚጣጣል አይደለም።

የጾም አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ

 አሁን ያለንበት ወቅት የዓብዪ ጾም ወቅት ነው። ምናልባትም ከጿሚዎቹ አተገባበር ስህተት፣ ወይም ከአስተማሪዎቹ ስህተት ሊሆን ይችላል አብዝሃኛውን ጊዜ ጾም የረሃብ አድማ እስኪመስል ድረስ ከምግበ መጠጥ መከልከል ብቻ ሆኖ ይተገበራል። ይባስ ብሎ በጾም መግቢያ ዋዜማዎች እና ከጾም በኋላ ወይም ከፋሲካ በኋላ ያለው የአመጋገብ ሥርዓት እንደሚስተዋለው ጾምን ለማካካስ በሚመስል ሁኔታ የምግብ ማግበስበሱና ሥካሩ የግለሰቦችን ሕይወት ለጤና ችግር ሲዳርግ፣ ማኅበራዊ ቀውስም ማስከተሉ የተለመደ እየሆነ ነው። ለመሆኑ ለምን እንጾማለን? አድርጉ ስለተባልን፣ ሌሎች ሰዎች እንዳይወቅሱን በይሉኝታ ወይስ የሚፈለገውን ግላዊና ማኅበራዊ ጸጋ ለማምጣት?

 የጾም ሰባኪ አይደለሁም። መጾምም ሆነ አለመጾም ለግለሰቦቹ ፈቃድ የተተወ ነው። ሃይማኖታዊ ዓላማውም እንደየ ግለሰቦቹ እምነት ለራሳቸው የተተወ ነው። ነገር ግን አብዝሃኛው የአገራችን ህዝብ በተለያየ ወቅትና ይዘት የሚጾመው ጾም ምን ምን ማኅበራዊ ፋይዳዎች ሊኖሩት ይገባል? የሚለውን መነጋገር ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ዘመኑ የዘልማድ አይደለም፤ የጥያቄ፣ የምርምር የምክንያታዊ ዘመን ነው። በጋራም ሆነ በተናጠል የምናደርገው እያንዳንዱ ነገር የሚኖረው መልካም አስተዋጽኦ ወይም ጎጅ ጎን ተፈትሾ መብራራት ይኖርበታል። የጾማችንም ጉዳይ ከዚህ አያመልጥም። የጿሚዎቹን የግል መብት ወይም ሃይማኖታዊ መርህ በማይጋፋ መልኩ ተተግብሮ ትሩፋቱ ለሁላችንም እንዲደርስ አስተያየት መስጠቱ ከሃይማኖት ነጻነት ጋር የሚጋጭ አይመስለኝም።

 ከላይ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ጾም ሁለት ወገን ነው። መከልከልና መታዘዝ። የምንከለከለው የሥጋን ጤንነት ከሚጋፉት፣ የነፍስን ሰላም ከሚረብሹት ምግባሮች ነው። ከኛም አልፎ የሌሎቹን ሰዎች ሰላም ከሚበጠብጡ ንግግሮችም ሆነ ሐሳቦች ልንቆጠብ ነው። የምንታዘዘው የሌሎቹን ሕይወት ምቹ የሚያደርጉ ቁሳዊና ሥነ ልቡናዊ ድጋፎችን፣ ልገሳዎችን እንድናደርግ ነው። አንዳንድ ጾምን በትክክል የሚተገብሩ ሰዎች በጾም ወራት ክርክር፣ አታካራ፣ ጭቅጭቅ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ሁሉ ርግፍ አድርገው ይተዋሉ። ይህም ከምግበ መጠጥ ተዓቅቦ በተጨማሪ ንግግርንና ሰዎችን የሚያስከፉ ተግባራትን ካለማድረግ ለመቆጠብ በማሰብ ነው።

 የዚህ ጽሑፍ መነሻም ጾምን ከዳር ቆመን የነ እከሌ ጾም እያልን በግዴለሽነት ከመመልከት፣ ወይም በተሳታፊነት የእኛ ጾም እያልን ለይስሙላ ከምናደርገው የምግብ መከልከል ባሻገር ጾም ምን ዓይነት ማኅበረ ፖለቲካዊ ፋይዳዎች ይኖሩታል? ጿሚዎቹንስ እንዴት እንቅረባቸው? የሚለውን ጉዳይ ለማንሳት ነው። በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከፍተኛ የሰዎች መፈናቀል፥ የሥርዓት አልበኝነትና የርስ በርስ መናቆር የነገሰበት፣ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መራሹ መነቃቀፍ፣ መሰዳደብ፣ መጨቃጨቅ ጥግ በደረሰበት ወቅት የጾም አስፈላጊነት ጎልቶ ይታየናል። ይህ ሲባል ግን እንደ ነነዌ ሰዎች ታሪክ ሆ ብለን ወጥተን አፈር ለብሰን በጋራ እንተግብረው የሚል የአዋጅ ቃል አይደለም። (በርግጥ እየገጠመን ያለው ማኅበራዊ ቀውስ እንዲህም እንድናስብ ኅሊናችንን ሳይዳብሰው አይቀርም)። እዚህ የተጠቀሰው ጾም ግን ለታይታ ከሚደረገው የምግበ መጠጥ ተዓቅቦ ሳይሆን ሰዎችን በሰውነታቸው ልክ አክብረን፣ የራሳችንንም የነፍስና የሥጋ ፍላጎቶች አጣጥመን፣ ለግልና ለጋራ ሕይወት መሳካት የሚረዳ የጋራ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ መደላድል ለማበጀት የሚደረግ ተዓቅቦተ እም እኩይ (ከክፉ ነገር የመራቅ)፣ እንዲሁም ወደ ጋራ ልዕልና የሚደረግ ዓንቃእድዎ (ወደከፍታው መመልከት) ኅሊና ነው።

 የምግብ ዓይነቱንና የምግብ ወቅቱን መረጣ ለሃይማኖት አስተማሪዎቹና ተከታዮቹ ትተን ጾምን የተስተካከለ የሥጋና የነፍስ ህብረት፣ መልካም ስብዕና ግንባታ ግብአት አድርገን እንመልከተው። ኤዋርድ ኢርል ፑሪንተን የተባለ ሰው ስለ መጽሐፉ ዓላማ ሲነግረን “The Philosophy of Fasting” ርእሱን እየጠቆመ “is a plea for human sincerity and a treatise on human wholeness” ይለናል። የጾም ጉዳይ የሰዎችን የጋራ ደኅንነት ለማረጋገጥ የምናደርገው መሻት ነው ብለን በጥቅሉ እንረዳው። የሃይማኖት አባቶች ስለ ዓሠርቱ ትዕዛዛት ሲያስተምሩ “የመጀመሪያው አንድ ፈጣሪን ብቻ አምልክ” የሚለውና የመጨረሻው “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚሉት ሁለቱ የሌሎቹ ትዕዛዛት ማሰሪያ ወዛምና ልዝብ ለኮዎች (ከለፋ ቆዳ የተሰራ ጠንካራ ጠፍር ወይም መጫኛ) ናቸው ይላሉ። አንድ ፈጣሪን አምልክ እሚለውን ለአማንያን ብቻ የተተወ ቢመስልም ባልንጀራን መውደድ ግን ሁሉም የሚስማማበት መርህ ነው። ባልንጀራ ማለት ወዳጅ ወይም ዘመድ ሳይሆን ሁሉም የሰው ልጆች ናቸው የሚለውን የዘርዓ ያዕቆብን ተማሪ የወልደ ሕይወትን ምክር ልብ ይሏል። ከፑሪንተን ሐሳብ ጋር ስምሙ ይመስላል። የጾም ፍልስፍናዊ መሠረትም ይኸው የሰው ልጆች የጋራ በጎነት፣ አፍቅሮተ ሰብእና አፍቅሮተ እውነት (ፈጣሪ) መሆን ይኖርበታል የሚል ነው የጽሑፋችን ምክረ ሐሳብ። ከፈላስፎቹም፣ ከሳይንቲስቶቹም፣ ከሃይማኖት መምህራኑም ትምህርቶች የሚሻለንን ወስደን ሁላችንም የኅሊናችንን ክፉ አሳብ፣ የአኗኗራችንን ተቃርኖ፣ የአንደበታችንን እንደ ጦር የሚዋጉ ቃላት፣ መርዝ የሚተፉ ብዕሮቻችንን አዳብ በማስገዛት ምክንያታዊነትን ፍቅረ ቢጽንና ሰላምን እናሰፍን ዘንድ ሁላችንም በጋራ መጾም ይኖርብን ይሆን?

 “ንጹም ጾምነ ወናፍቅር ቢጸነ።”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top