ከቀንዱም ከሸሆናውም

ጉዞ መቅደላ፣ ዝክረ ቴዎድሮስ፣ ትንሣኤ አምባ

ሰሞኑን ደመቅ ብለው ከተሰሙ ጉዳዮች አንዱ የታላቁ ንጉሥ የኢትዮጵያ ዳግም አንድነት መሥራች፣ የዘመናዊ ሥልጣኔ በር ከፋች የሆነውን የአጼ ቴዎድሮስን የራስ ጸጉር ቁራጭ (ቁንዳላ) ለማምጣት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ እንግሊዝ አቅንተው የተባለውን ቁንዳላ ይዘው መምጣታቸው ነው::

ይህም በወቅቱ በሰፊው ተሠርቷል:: ይኽ በዚህ እንዳለ የለንደኑ ጉዞ ሳይጠናቀቅ ለምን የራስ ጸጉር መላ አካላቱ ካረፈባት “መቅደላ መቅደላ አንች ኩሩ ጎራ፣ እንደምን ታምሪያለሽ አንቺ ውብ ተራራ፣ ሴቱን ሁሉ ንቆ ሲኮራ ሲኮራ፣ ወንዱ አንችን ወደደ ተኛ ካንች ጋራ” የተባለላት፤ መቅደላ ሲፎክር ይሰማል ግሸን፣ ጀግናው ታምኖብሻል ልትሆኝው ደጀን፤ ተብሎ የተገጠመላት የመቅደላ አምባ ላይ የወደቀውን የጀግናውን አካል ሄደን እንዘክራለን፣

ከተጓዦቹ መካከል ጥቂቶቹ፤

‹‹የመቅደላንም ትንሣኤ እናበስራለን›› ያሉ ወጣቶች ከደብረ ማርቆስ፣ ከደብረ ታቦር፣ ከባህር ዳር፣ በጥንታዊው የበሽሎ መንገድ ሲጓዙ ሌሎች ደግሞ ከአዲስ አበባ በደሴ በኩል ወደ መቅደላ አቅንተዋል:: የአማራ መገናኛ ብዙኀን በኤፕሪል 3/2019 እንደዘገበው፤ ከደብረ ታቦር በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ራስ አገዝ የኢንደስትሪ መንደር ከሆነችው ከ“ጋፋት” የጀመረ ጉዞ መቅደላ ሲጀመር በመቀጠል በነፍ ኮሚኒኬሽን “ዝክረ አጤ ቴዎድሮስ” በሚል መሪ ቃል ከባህር ዳር የተነሣ የእግር ጎዞ መጀመሩ ተዘግቧል:: በዚሁ ሳይቆም ከደብረ ማርቆስ የእግር ጉዞ ተጓዦች ለመጓዝ መነሣታቸውንም ሰምተናል:: ከአዲስ አበባ የተነሣው ተጓዥ “ትንሣኤ መቅደላ-ዝክረ አጼ ቴዎድሮስ” በሚል መሪ ቃል ሲጓዙ ሁሉም በአንድነት ሚያዚያ አምስትና ስድስት መቅደላ አምባ ተገናኝተዋል::

 በመቅደላ አምባ የተንታና አካባቢው እንግዳ ተቀባይ፣ ታሪክ ጠባቂ፣ ጀግኖቹን ዘካሪ የሆነው ነዋሪ ሕዝብና የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት አቀባበል ተደርጎላቸው ተስተናግደዋል:: “መማር እንደ አካልዬ መታገል እንደ ገብርዬ” ተብሎ የተነገረለት፣ ንጉሠ ነገሥቱ የእናቴ ልጅ እያሉ የሚጠሩት የታማኙን ጀግና ፊታውራሪ ገብርየን መቃብር፣ ንጉሠ ነገሥቱ ለሀገር አንድነት ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉበት አምባ፣ በወራሪው ጦር የተቃጠለውን ታላቁን እና ጥንታዊውን የብዙ ቅርሶች ባለቤት ቤተ መዘክርና ቤተ መጻሕፍት የነበረውን የመቅደላ አምባ መድኀኔዓለም ካቴድራል ፍርስራሽ ጎብኝተዋል፣ ሌሎችንም ታሪካውያን መካናት በኪደተ እግራቸው ዳሰዋል::

 “ጊዜ ሲደርስ አምባ ይፈርስ” እንደሚባለው ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ የታላቁን ንጉሥ ታሪክና ቅርስ፣ ሥራና አሻራ ከታሪካዊው ቦታ የወቅቱ የንጉሠ ነገሥቱ ዋና ከተማ መቅደላ አምባ አያይዞ የሚዘክር ትውልድ መነሣቱ የሚመሥጥ ጉዳይ ነው:: ንጉሡ ሀገራቸውን የተባበረች አንድነቷ የፀና፣ እንደማንኛውም ገናና ሀገር የታፈረችና የተከበረች ሀገር እንድትሆን፣ ፍትሕ የሰፈነባት እኩልነት ያለባት፣ ነዋሪዎቿ ሠርተው የሚያድሩባት፣ የሠለጠነው ዓለም ትምህርትና ክሂል በሀገራቸው እንዲስፋፋ፣ ራሷን በጠንካራ ሠራዊት የምትጠብቅ ሀገር ከማድረግ አልፈው በኢየሩሳሌም ያለውን ርስት ለማስከበር ዕቅድ የነበራቸው፣ የዘመናዊ ራስ አገዝ ሥልጣኔ፣ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ትንሣኤ፣ የሉዓላዊነት ግንዛቤ፣ እና የሌሎችም አንኳር ቁምነገሮች ባለቤትነታቸው በጥናት በተደገፈ ምርምር ለትውልድ ቢተላለፍ ጥሩ አርኣያነት እንደሚኖረው ለማንም የተሠወረ አይደለም::

 የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ትክክለኛ ድጋፍ ከተደረገለት፤ የጀግናው ባለውለታ ታሪክ እንዳይጠፋ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን የተወጡ ከአለቃ ዘነብ፣ ሐኪም ወርቅነህ … ጀምሮ፣ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ አባተ መኩሪያ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ፈቃዱ ተክለማርያም፣ የመሳሰሉ በርካታ ሰዎችም አብረው የሚዘከሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም:: ከመቅደላ የተወሰዱት የመድኀኔዓለም ጽላት ባለበት ቦታ ሁሉ ጊዜ በጥቅምት የሚከበሩት የአባ መብዓጽዮን፣ የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ የእመቤታችን እና ሌሎች ጽላቶች፤ በብዙ ሽዋች የሚቆጠሩ የከበሩ ንዋያት፣ ክብረ ነገሥትን ጨምሮ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ የብራና መጻሕፍት፣ ታላቁ የኩርዓተ ርእሱ ሥዕል፣ የነገሥታት የክብር ልብሶች፣ የወግ ዕቃዎች ተመልሰው የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም::

በጎና መልካም ይሁን እንጅ የፈረሰውን ለመሥራት፣ የተወሰደውን ለማስመለስ፣ የጠፋውን ለማግኝት፣ የተረሳውን ለማስታወስ የሚከለክል ምንም ምክንያት የለም:: ስለዚህ በባህልና ቱሪዝም የተጀመረውን የቅርስ ማስመለስ ጥረት እያደነቅን በተመሳሳይ ከየአቅጣጫው የተጀመረው የወጣቶቹ ታሪክን የመጠበቅና የመዘከር የሕሊና እና የአካል ጉዞ ለመቅደላ አምባና በመቅደላ ለተሠራው ታሪክ ትልቅ ትንሣኤ ይኖረዋልና ትኩረት ቢሰጠው፤ ለሀገራችን ሁነኛ የሆነ ፍትሐዊ አንድነትና የሚጠበቀው ሥልጣኔ ለማምጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል:: ጉዞ መቅደላ፣ ዝክረ አፄ ቴዎድሮስ፣ ትንሣኤ አምባ መቅደላ፤ ከታሪክ ዝክርነት በተጨማሪ በቱሪዝም፣ በባህል ልውውጥ፣ በቅርስ ጥበቃ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ተጠናክሮ ይቀጥል!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top