አድባራተ ጥበብ

የክርስቶስ ትንሣኤ ሥዕል በምሥራቃውያን – ኦሬንታል ትውፊት

ሥዕል ቋንቋ ነው ብሎ መጀመር ብቻውን ስሜት አይሰጥም። በርግጥም የመስመሮችን እንቅስቃሴ፣ የቅርጾቹ የመጨረሻ ምስል/ልሕኩኪት (form)፣ የአሣሣል ንድፍና (መሠረት) እና ጠባይ፣ የቀለማት ቀመር፣ የምስል እንቅስቃሴ (ተሐውሶ)፣ የሠዓሊው የድርሰት ችሎታ ዕቅድና የድርሰቱ አጣጣል በአጠቃላይ በዘርፉ ባለሙያዎች በጥልቀት ይገለጻል። የቋንቋ ሊቃውንት በአንድ ልሳነ ሕዝብ ውስጥ የቋንቋው ቃላት ግሥ፣ ባለቤት፣ ቅጽል፣ ተውላጠ ስም፣ አገባብ ስዋሰው የዓረፍተ ነገር ምሥረታ፣ ወዘተ እያሉ እንደሚተነትኑት ዓይነት ሥዕልም ከውበቱ በላይ ትርጉሙ፣ ከዕይታው ይልቅ ንባቡ፣ ጥበቡ ከተገለጸበት ሰሌዳ ወይም ገበታ ይልቅ የሠዓሊው አእምሮ ይነበባል። በተጨማሪም የሥነ ሥዕሉ ዘመን፣ የጥበብ ዓይነት፣ የትምህርት ቤቱ የጥበብ አቋም የሥዕሉ አርዓያ ወይም (ሞዴል) ይዘገባል። በጥበቡ ውስጥ የላቀ ግንዛቤ ያላቸው ሥዕልን አይተው አይጠግቡም። በቀለማት ማዕበል፣ በመስመሮች ሞገድ፣ በምስሎች ተሐውሶ፣ በወርዱ ጥልቀት እና በጥበቡ ስሜት ወላፈን ውስጥ የሥዕሉን ብቻ ሳይሆን የሠዓሊውንም ዕምቅ ጥበብ፣ የእጅ የቡርሽ ክህሎት ለመረዳት የሥዕሉ አካል የሆኑ ያህል በዝምታ ተውጠው በፀጥታ ተመስጠው አፍጥጠው ይውላሉ። ጠቢብ በጥበቡ፣ ከያኒ በኪኑ/በኪነቱ፣ ባለቅኔ በቅኔው፣ ደራሲ በድርሰቱ፣ ሠዓሊም በሥዕሉ እንዲታወቅ በሥዕል ውስጥ ሠዓሊውን መፈለግ፣ ከዚያም ትርጉሙን ከነፍልስፍናው ለመረዳት መጣር ምንጊዜም የማይለያዩ ጉዳዮች ናቸው።

ምሁራን የሰውን ልጅ የጥበብ ታሪክ ሲተርኩ ሰው በማኅበር መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ራሱን ከገለጸባቸው ጥበቦች ሁሉ ሥነ ሥዕልን የሚያክል ጥበብ የለም ይላሉ።

የሥነ ሥዕል ጥበብ ለአሁኑ የዘመናዊ ሥልጣኔ የምስልና የድምጽ ቅንብር፣ የፎቶ ግራፍ ርቀት፣ ቪዲዮ (ተንቀሳቃሽ ምስል)፣ ፊልም (የምስል ወድምጽ ትወና) ጥበባት መሠረት ነው። የሥነ አእምሮና የአንጎል ውስጥ ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ከምንም በላይ በምስል ወይም በሥዕል የመግለጽ ችሎታው የመጨረሻው የብቃት ደረጃ ሲሆን በጣም ድብቅና ረቂቅ የሆነ ሥሜቱን ሳይቀር ከቃላትና ከድምጽ በላይ በምስል የመግለጽ የተሟላ ብቃት አለው ይላሉ። የሰው አእምሮ ድምጽን፣ መዓዛን፣ ጣዕምን፣ ስሜትን፣ ክስተትን፣ በሂደት በቀላሉ ሊረሳ ይችላል፣ ምስልን ግን ለረጅም ጊዜ ሳይረሳ በአእምሮው በማስቀመጥ የማስታወስ ችሎታ እንዳለውም ይናገራሉ። አያይዘውም የሰው ልጅ ከማንኛውም ነገር በላይ በምስል/ሥዕል የሚማረው ትምህርት በፍጥነትና በጥራት የመቀበል ችሎታ እንዳለው ያስረዳሉ።

በዚህ ጽሑፍ ስለ ሥዕል እና ምስል በሰፊው ለመናገር አስቤ ሳይሆን ሥዕል በሰው ልጅ መደበኛ ሕይወት ውስጥ ካለው ጥልቅ አስተዋጽኦ በተጨማሪ በእምነትም ውስጥ እንዲሁ ሰፊ ቦታ እንዳለው ለማሳየት ነው። ይህም የሰውን ተፈጥሯዊ ማንነትና ዝንባሌ መሠረት ያደረገ ሲሆን ሥዕል በእምነት፣ በትምህርትና በአምልኮ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የማይናቅ ቦታ ነበረው። በምሥራቃውያን ኦሬንታል Theology (ነገረ መለኮት) ትምህርት ሰው ራሱ የእግዚአብሔር ተንቀሳቃሽ ሥዕል ነው። ሥነ ፍጥረትም ፈጣሪ በልዩ ዕቅድ፣ (Design) በሕብረ ቀለማትና ሕብረ ገጻት አስውቦ የፈጠረው የአምላክ ሥነ ሥዕል ተደርጎ ይወሰዳል። በምሥራቃውያን ኦርቶዶክሶች ዘንድ ሥዕልን፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን፣ ንዋየ ቅዱሳት ለተገቢው አገልግሎት ይጠቀማሉ። ይህንም ባለማወቅ እንደአምልኮ የሚቆጥሩ ቢኖሩም አማኞች ግን ሥዕላትን ያከብሯቸዋል እንጅ አያመልኳቸውም። አምልከውም አያውቁም። የማክበሩ ሥርዓትም በክርስትና በጣም ጥንት በሐዋርያት የተጀመረ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ትምህርታቸውን ያስፋፉት በዋናነት ዋሻ ፈልፍለው፣ ጉድጓድ ቆፍረው፣ በዋሻ በፍርክታ “ካታኮምብ” (ግበበ ምድር) በተባሉ ቦታዎች ነበር። ይህም የሆነው ክርስቲያኖች እስከ 313 ዓ.ም የሚላን ዐዋጅ (Edict of Milan) ድረስ የአምልኮ ነጻነት ስላልነበራቸው መሠረታዊ ትምህርቶችንና ምሳሌዎችን በሥዕል አስተምረዋል። ተአምራት ነክ እና ክስተቶች ጋር የተገናኙ የቅዱሳት መጻሕፍትን ታሪኮች ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ለማስተማር እና ለማስረዳት ተጠቅመዋል።

 ሥዕላትን መጠቀም በመጽሐፍ ቅዱስም የተጠቀሰ ጉዳይ ሲሆን እግዚአብሔር ሙሴን “ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፣ በታቦቱ መክደኛ ላይ ሣል፤ … በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ሆኜ አነጋግርሃለሁ።” (ዘጸ. 25፡18-22፣ 261-3፣ 36፡8፣ 37፡7) ብሎታል። ጠቢቡ ሰሎሞንም በቤተ መቅደስ ግድግዳዎች፣ በምሰሶዎችና በአንቀጾች ላይ ሥዕላትን ሥሏል (1ኛ ነገ 6፡23-35፣ 2ኛ ዜና 3፡7-14)። በአጠቃላይ ሃይማኖተኞች ሥዕልን፣ ለትምህርት፣ ለሥርዓት፣ ለአክብሮት፣ ለዐፅመ ቅዱሳን ዝክር፣ ለአስተጋብኦ ሕሊና፣ በሥዕሉ የተወከለውን ወደራስ አቅርቦ ሕሊናን ከባለቤቱ ለማገናኘት ይገለገሉበታል። በምሥራቃውያን/ኦሬንታል ክርስቲያኖች ሥዕል መሣል በጣም ትልቅ ክብር አለው፣ ሰፊ መንፈሳዊ ዝግጅትንም ይጠይቃል፣ የሚሣለውን ሥዕል ታሪክና ጥበብም በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ትምህርቶችን ከምሥጢራቸው ሳያፋልሱ መሣል ዋና ትኩረቱ ነው። በዚህም Iconography – writing of Icons, Iconology, Veneration of Icons, አክብሮ ሥዕል፣ Theology of Christian Art (ትርጓሜ ሥዕል (ቴዎሎጅ) History of Christian Art, የሚባሉ የትምህርት፣ የተግባርና የምርምር ዘርፎች ይገኛሉ።

በምሥራቅ ኦሬንታል ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሥዕላት የራሳቸው የሆነ ትርጉምና ምሥጢራዊ መልእክት አላቸው። ሥዕላትን ያከብራሉ በቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹትን መልእክቶችን፣ ነገረ ክርስቶስን፣ ነገረ ማርያምን፣ ክብረ ቅዱስንና ክብረ መላእክትን፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና የሰማዕታትን ገድል ሁሉ በሥዕል ይዘክራሉ። በመሠዊያ መንበር፣ በንዋየ ቅድሳት ላይ እና በመጻሕፍት ውስጥ ገጾች ሁሉ እና በመሳሰሉት ቅዱሳት ሥዕላትን ይሥላሉ። ሥዕላት ልክ ለሥነ ጽሑፍ የሚደረገውን ጥንቃቄ ያህል የሚያስተላልፉት መልእክትና ለሚወክሉት ባለቤት ጥንቃቄ ይደረጋል፣ ምክንያቱም በሥነ ጽሑፍ ውስጥ የተሳሳቱ መረጃዎች አንባቢን የሚያሳስቱት ያህል የተሳሳቱ ሥዕላትም ተመልካችንና አንባቢን ያሳስታሉ። ሥነ ጽሑፍ አንድን ታሪካዊ ክስተትና መሠረተ እምነትን ያለምንም ሥዕላዊ መግለጫ በቋንቋ ሥርዓት በመጠቀም አንባቢ እንዲያስተውለውና በአእምሮው ውስጥ እንዲስለው የማድረግ ኃይል ሲኖረው፣ በሥዕላትም ውስጥ በርካታ ታሪካዊ ክስተቶችና ትምህርቶች ከታሪኩ ጋር ተዛምደውና ተናበው በቀለሞችና በመስመሮች ተዋቅረው ታሪካዊ ክስተቱን በአንድ ሰሌዳ ወይም በተከታታይ ገጾች እየሣሉ እንዲነበቡና እንዲዘከሩ፣ በሠሌዳ አእምሮ እንዲቀረጹ የማድረግ የማይተካ ድንቅ ብቃት አለው።

 በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ አንድ የቬነስ ተወላጅ ሠዓሊ ነበር። ቀደም ሲል የነበረው ስም ብራንካሊዎኒ ሲሆን እዚህ ግን ኢትዮጵያውያን የክርስትና ስም ሰጥተውት መርቆሬዎስ ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህንኑ ሠዓሊ አጼ በዕደ ማርያም የአትሮንስ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን የቤተ መቅደስ ውጫዊ ግድግዳ እንዲሥል አዘዙት። እየሣለ በነበረበት ጊዜም ምስለ ፍቁር ወልዳ የተባለችውን የእመቤታችንንና የልጇን የጌታችንን፣ እንዲሁም የቅዱሳንን ሁሉ ሥዕል ሲሥል የእጃቸውን ሁለት ጣቶች እያሳየ ነበር። ሁኔታው የገረማቸው ሊቃውንትም በተለይ በአካባቢው የታወቁት የደብረ ባህርይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ገዳም ደቀ መዛሙርት ስለ ሁለት ጣት ይጠይቁታል። እሱም ሲመልስ ሁለት ጣት በኦርቶዶክስ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የ “ሁለት ባህርይ” መገለጫ ነው ይላቸዋል። ሊቃውንቱና ደቀ መዛሙርቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ባህርይ እንደማታምን ይገልጹለታል። በዚህም ሰፊ ክርክር ካደረጉ በኋላ ሊቃውንቱ እኛ ግን ሁለት ባህርይን ሳይሆን ሁለት ልደትን እናምናለን አሉ። የሁለት ልደት ትምህርት ከዚያ ቀደም ብሎ በነበሩ የግእዝ ጽሑፎች ላይ በሰፊው ተዘግቦ ነበር። በተለይ መርቆሬዎስ- ብራንካሊዎን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ ጥቂት ዓመታት በፊት በሀገራችን በርካታ ድርሰቶችን በመድረስ የሚታወቁት ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ከድርሰቶቻቸው በአንዱ ስለ ሁለት ልደት አስተምረው ነበር። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ትምሀርት የሠዓሊውን ሐሳብ ረተው ትርጉሙ ኦርቶዶክሳዊ ወይም የኦሬንታል እንዲሆን አደረጉ። የሁለት ጣት ትርጉም በምዕራቡ ትምህርት የሁለት ባህርይን ትምህርተ ሃይማኖት ወይም ዶግማ ማስተማሪያ ሲሆን በኢትዮጵያውን ዘንድ ግን ሁለት ጣት የሁለት ልደት ማስተማሪያ ሆኖ ቀረ።

በአሁኑ ጊዜ በተለይ ከዐሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በመላው የኦርቶዶክስ ክፍለ ዓለም የጥንቱ አሣሣልና የምሳሌዎች ትርጉም እየተረሳና በምዕራባውያን የዐሣሣል ሥርዓት ተጽዕኖ ሥር እየወደቀ ይገኛል። ለዚህ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም ለዛሬ ከትንሣኤ ጋር በተያያዘ የክርስቶስን የትንሣኤ ሥዕል ትርጉምና አሁን ያለበትን ሁኔታ ለማየት እንሞክራለን።

በምሥራቅ ኦርቶዶክስ / ኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ከጥንት ጀምሮ የሚታወቀው የትንሣኤ ሥዕል ጌታችን በክብርና በሥልጣን ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ የሚያሳየው ሥዕል ሲሆን በዚህ ሥዕል ላይ ጌታችን በብርሃን ክበብ ውስጥ ግርማ ባለው ኃይልና ሥልጣን፣ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ምስማሮቹ (ቅንዋት) በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ያረፉበትን ምልክት በሚያሳይ መንገድ በግራ እጁ ሞትን ድል የነሣበትና የአሸናፊነት ምልክት የሆነውን ቅዱስ መስቀል ይዞ የሲዖልን ደጆች ሲሰባብር፣ ቅዱስ ጳውሎስ በዚያን ጊዜ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል፣ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲዖል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ? (፩ኛ ቆሮ ፲፭፡ ፶፭) የሚለውን ትምህርት በሚወክል መንገድ ይሣላል። በቀኝ እጁ ደግሞ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያና ሞት ወደዚህ ዓለም እንዲገባ ምክንያት የሆነውን

የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከመቃብር ሲያወጣ ይታያል። በቀኝ እጁም እንዲሁ በመስቀል ላይ የተቸነከሩት እጆቹ ምልክቱን እንደያዙ ይታያሉ። አዳምንና ትውልዱን ሁሉ ከሞት ማሠሪያና ከሲዖል ግዞት ነፃ ለማውጣት በክብርና በሥልጣን ወደ ሲዖል መውረዱን ለማሳየትም መስቀል ያለበት ሰንደቅ ወደላይ ተቀንፎ ይታያል። በዚሁ ሥዕል ላይ አብረው የሚገለጹት የፍጥረት ሁሉ እናት ሄዋን ከአዳም ጋር እጇን ዘርግታ ትታያለች፣ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢኣተ ዓለም›› ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› በሚል መልክ አብሮ ይሣላል። በቀድሞዎቹ ሥዕሎች ላይ እግዚአብሔር የልቡን ቅንነት አይቶ መሥዋዕቱን የተቀበለለት ጻድቁ አቤል ለጋ እረኛ ወጣት ሆኖ ደስ በተሰኘ ገጽ ይታያል። አቤል በዚህ ሥዕል ላይ የመኖሩ ዋና ምክንያት አቤል ከፍጥረት ሁሉ ቀድሞ የሞትን ፍርድ ከሰሙት ከእናትና አባቱ ከአዳምና ሄዋን በፊት በወንድሙ ተገድሎ ሞትን የቀመሰው እሱ ስለሆነ ነው። በሥዕሉ ግርጌም በጥልቅ ጨለማ በርቀት የሚታይ በሞት ቁልፍ የተቆለፈ የሲዖል አዘቅትና አሮጌ ሰንሠለት አብረው ሲሰባበሩ ይሣላሉ። ከዚሁ ጋር ሁለት መላእክት የሞትን ድል መነሣት የሲዖልን ሥልጣን መሻር ለመላው ዓለም የሚያበሥሩ ሰው የሆነ አምላክ (The- anthropos) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤ መክበሩን ለመላው ዓለም በደስታ ሲያበሥሩ ይታያሉ። ይህ ሥዕል በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ እንደ ጥንታዊ የትንሣኤ ሥዕል ሲቆጠር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከጥንት ጀምሮ ድርሰቱ አጭርም ረጅምም እየሆነ ሲሣል ቆይቷል።

ሜል ጊብሰን “The Passion of Christ” ሕማማተ ክርስቶስ በሚለው ታዋቂ ፊልሙ ላይ በቀጥታ ከተጠቀመባቸው የምሥራቅ/ ኦሬንታል ትምህርቶች ውስጥ አንዱ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በትንሣኤ ስብከቱ የተናገረው ነው። “… እንግዲህ ደጋግመው የወደቁ በሐዘን ሸማ አይኑሩ የይቅርታና የምሕረት ባለቤት ተነሥቷልና፣ እንግዲህ ማንም ሞትን አይፍራ በመድኀኒታችን ትንሣኤ ነፃነትን አግኝተናልና። እሱ ሞትን በትእግስቱ፣ በሕማመ ሞቱ አጥፍቶታልና። ሲዖልንም ካለበት ቦታ ወርዶ ድል ነሥቶታልና፣ ሲዖል በመከራና በጭንቅ ውስጥ ወድቋል፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ሲዖል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች›› ኢሳ 14፡9 ፤ ሲዖል ሥልጣኗ ተወግዷልና በመከራና በጭንቅ ጣዕራ ላይ ነች፣ በጌታችን ድል መንሣት መሳለቂያ ሆናለችና ሲዖል በጣዕር ውስጥ ትገኛለች፣ ሲዖል ተሸንፋ፣ ተፈረካክሳለችና በጣዕር ድምጽ ውስጥ ነች፣ ዛሬ ዕሥር ቤቷ የሲዖል እሥረኛ ሆናለችና ጣዕሯ በዝቷል፣ ..›› ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲዖል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ? (፩ኛ ቆሮ ፲፭፡ ፶፭)፣ “ክርስቶስ ተነሥቷል ስለዚህ ሞት ተሸንፏል፣ ክርስቶስ ተነሥቷል ክፋት ተወግዷል፣ ክርስቶስ ተነሥቷል መላእክት ደስ ብሏቸዋል፣ ክርስቶስ ተነሥቷል ሕይወት (ነፍስ) ነፃነቷ አግኝታለች፣ ክርስቶስ ተነሥቷል መቃብር ከሙታኑ ተራቁቷል፣ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷል አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል“ ብሎ እንደተናገረው በአብዛኛው የጌታችን ትንሣኤ ሞትን ድል ከመንሣቱና ከመቃብር ከመነሣቱ ጋር አብሮ የሚሰበከው የሞት ሥልጣን ሲሻር የሲዖል ቀንበር ሲሰበር፣ ጌታችን ከሙታን ሲነሣ አዳምን ነፃ ሲያወጣ፣ ሲዖል ሲበረበር ዲያብሎስ ሲታሰርና ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶች በሥዕሉ ይገለጻሉ።

 የሥዕለ ትንሣኤ ክርስቶስ ዋና አስፈላጊነት ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው የቆሮንቶስ መልእክቱ “ክርስቶስ ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው፣ እምነታችሁም ከንቱ ናት›› እንዳለ፣ የክርስቶስን ትንሣኤ መስበክና መመስከር፣ በክርስትና ሕይወትም ለትንሣኤ የሚያበቃ ሕይወትን መኖር መሠረታዊ የክርስቲያኖች ሁሉ ተልእኮና ሕይወት ነው። ክርስቲያኖችም ‹‹የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል››። ብሏል። ስለዚህም ነው የክርስቶስ ትንሣኤ ሥዕል ልዩ ትርጉም ያለው። የትንሣኤ ሥዕል ትንሣኤውን እንደሚገልጹት ሥነ ጽሑፎችና የሥርዓተ አምልኮት ንባቦች ሁሉ ትንሣኤው ምስጢራዊና ታሪካዊ መልእክትና ትርጉም ይገልፃል፣ በበርካታ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት በወርሐ ትንሣኤው ወቅት በሚቀደሱ ቅዳሴዎች ‹‹ክርስቶስ ተንሥአ

“ክርስቶስ አዳምንና ትውልዱን ከሲዖል ሲያወጣ የሚያሳየው የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤ መሆኑ በምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ውስጥ ያለውን ዶግማዊ ትርጉም የሚገልጽ፣ ክርስቶስ በኩረ ትንሣኤ መሆኑን በመግለጽ መሣሉ ነው”

እሙታን፣ ሞተ ወኬዶ ለሞት፣ ለእለ ውስተ መቃብር ወኀበ ሕይወተ ዘለዓለም እረፍተ›› እየተባለ፣ ከትንሣኤ እስከ ዕርገት ድረስ በምሥራቃውን ዘንድ በእነሱ አሰያየም በግሪክ ቋንቋ ανάστασις አናስታሲስ በመባል የሚታወቀውን የሲኦልን መታወክ የሚገልጸውን ሥዕለ ትንሣኤ ከፍ አድርገው በመያዝ በመንበሩ ዙሪያ እንዲሁም ከቤተ መቅደስ ውጭ ከትንሣኤ እስከ እርገት ድረስ ዑደትን ያደርጋሉ። በተጨማሪም ሥዕሉ በትንሣኤ ሰሞን ከሚፈጸመው ሥርዓተ ቅዳሴ ጋር ያለውን ትሥሥር በቀላሉ ለማየት እንችላለን። ይህም ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፣ በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን፣ ሐሰሮ ለሠይጣን፣ አግዓዞ ለአዳም፣ ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሓ ወሰላም፣ የሚለው እና ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ሞተ ወኬዶ ለሞት ለእለ ውስተ መቃብር ወሀበ ሕይወት ዘለዓለም እረፍተ የሚለውን ለማለት ነው። ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል በምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ከጥንት ጀምሮ ጥቅም ላይ ከዋለው የትንሣኤ ሥዕል ትንታኔ ጋር ያለውን ዝምድና ለማየት ያስችላል። ከዐሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ክርስቶስ በዘንግ ላይ የባንዲራ ምልክት ይዞ ከመቃብር ፈንቅሎ ልክ እንደ ምዕራባውያን የመቃብር አሠራር ከተሠራ መቃብር ሲወጣ መላእክት የመቃብሩን ድንጋይ ሲያነሡ መቃብሩን ለመጠበቅ የተመደቡት ወታደሮች በድንጋጤ ሲወድቁ ወይም ተኝተው ይታያል። የዚህ ዓይነቱ ሥዕል ቀደም ሲል እንደተናገርነው የምዕራቡ ተጽዕኖ ያለበት የምሥራቁን ትውፊት ያልወከለ ግን የምዕራቡ ክርስትና ቀደም ሲል ጀምሮ ትውፊታዊ የነበረ ሥዕል መሆኑን ነው።

በምሥራቅ ኦሬንታል ኦርቶዶክሳውያን ሥዕለ ትንሣኤ ጥንታዊና ሐዋርያዊ ትውፊት በመጠበቅ በትንሣኤው ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል መነሣቱን፣ መቃብሩም እንደዛሬዎቹ በድንጋይ ተገንብቶ፣ በስሚንቶ ተለስኖ የተሠራ ሳይሆን በዋሻ ውስጥ እንደሆነና በትልቅ ድንጋይ እንደተከደነ ነው። ሌላው ሥዕሉ የተከፈተ መቃብርን በማሳየት ከመቃብሩ መነሣቱን በመግለጽ ብቻ ሳይወሰን ምሥጢራዊ ትርጉሙና በትንሣኤው ከተከናወኑት ዓበይት ክስተቶች ውስጥ የሲዖልን መበርበር፣ የዲያብሎስን መታሠር፣ የነፍሳትን ዓርነት፣ የፍጥረትን ድኅነት በሚገልጽ መንገድ መሣሉ ነው። በተለይ ደግሞ ከዚሁ ጋር ክርስቶስ አዳምንና ትውልዱን ከሲዖል ሲያወጣ የሚያሳየው የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤ መሆኑ በምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ውስጥ ያለውን ዶግማዊ ትርጉም የሚገልጽ፣ ክርስቶስ በኩረ ትንሣኤ መሆኑን በመግለጽ መሣሉ ነው።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ሲሣል በነበረው የትንሣኤው ሥዕል ላይ ጌታችን ግርማ ባለው ኃይል፣ ብርሃንን ለብሶ፣ የድል ባንዲራ መስቀሉን ይዞ፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ የቅንዋት ምልክቶቹን እያሳየ፣ የሲዖልን ደጆች ሲሰብር፣ ዲያብሎስ ሲታሰር፣ መላእክት ቀርነ መለከት ሲነፉ፣ አዳምና ሄዋን ነፃነትን ሲያገኙ ይታያል። ይህን ስናይ ሥዕሉ ስለ በዓለ ትንሣኤ ምን ያህል ሰፊና ጥልቅ ትምህርትን እንደሚያስተላልፍ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጸውን የትንሣኤ ትረካ ብቻ ሳይሆን በሊቃውንት የተተረጎመውን ትምህርት ሁሉ እንዴት እንዳካተተ እንረዳለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top