አድባራተ ጥበብ

“ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል”

ብዕሬን ከወረቀቱ ጋር ለማዛመድ ስሞክር በአንድ የገበያ አዳራሽ አንድ ሕፃን ልጅ “እይው እምይ ሸኩላቱ ጋሼ!” በማለት ጣቱን ወደ እኔ ቀስሮ ሲያመለክት እናቱና አብረዋቸው የነበሩት ባለቤታቸው ጭምር ዓይናቸውን በእኔው ላይ ሰክተው መቅረታቸው ነው ትዝ ያለኝ። የልጁ አባባል ግን ከፍተኛ ትርጓሜ ነበረው። ነገሩ እንኳን ሲያስቡት እንደቸኩላት መጣፈጤን የሚመሰክር ሳይሆን በዚያች ጀርመናዊት መንደር እንደኔ የጠየመ ሰው የሌለ በመሆኑ ወላጆቹ ከሚገዙለት የሸኩላት ቀለም ጋር ቆዳዬን ማመሳሰሉ ነበር።

“ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል” እንደሚባል አጠራርም እንዲሁ የአነጋገር ዘርፍ አለውና ከአጠራር ሊፈረድ እንደሚችልም መጠራጠር የለብንም።

ፍቅረኞች በሚነጋገሩበት ቋንቋ ለፍቅራቸው መጠንከርና ለፍቅር ጭውውታቸው ስምረት፣ ለነገሩም መቀዳጀት ከፍ ያለ ድርሻ አለው። “አጠራር የአነጋገር ዘርፍ ነው” ሲባልም ማነጋገር የሚቻለውም በመጀመሪያ ጠርቶ መሆኑን የማናውቅ እንኖር አይመስለኝም።

 የሥነ ልቡናና የሥነ አዕምሮ ሊቃውንት እንደሚያመለክቱት አንድ ሰው የአጠራሩ ሁኔታና መልክ ተጠሪው ለተጠራበት ጉዳይ፣ አመለካከትና ምላሽ አሰጣጥ ዓይነተኛ ትርጓሜ አለው።

ያ ሕፃን ስሜን ባለማወቁ በቸኩላት ቢመስለኝም የቸኩላቱን ማለፊያ ጣዕም በሚገባ ስለማውቅ አጠራሩን በእጅጉ ፈገግ ብዬ ተረክቤዋለሁ። ይሁን እንጂ እንደ እኔው በጠቆረ ብረትና እንጨት፣ ወይም ሬንጅ መስሎ ጣቱን ቢቀስርብኝ ኖሮ ግን ልጁን በሕፃንነቱ ጥቂት ንቄ ባልፈውም ልቤ በደስታ አይሞላም ነበር።

 በአደባባይ የሚደሰኮሩት ኦፊሲዬል ቋንቋዎችንና የአነጋገር ዘዬዎችን በፍቅር ጭውውት በወሲባዊ ግንኙነት ሰዓት ፋይዳ የለሾች እንደሆኑ ስንረዳ የአጠራር ፈሊጥም በዚያው ልክ ባለ ልዩ ትርጓሜ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። “አንቺ አንተ” ብለው ጠርተው ለጭውውት የጋበዙትና “አንቺዬ አንተዬ” ብለው ያማለሉት ለየቅሉ ነው።

ቢሊዮን፣ ፈረንሳይ የሚታተም አንድ የቤተሰብ መጽሔት፣ እንዳመለከተው ከአሜሪካ በቀር ፍቅረኛን አቆላምጦ የመጥራቱ ነገር በአንድ ወቅት በአውሮፓ እየከሰመ መሄዱን አትቶ ነበር። በእነሱ ባህል “ስዊት ኸርት፣ ዳርሊንግ፣ ሐኒ” ብሎ አጣፍጦ ፍቅረኛን መጥራት አሊያም “ጆናታን፣ ጀምስ፣ ሮናልድ” የሚለውን ደግሞ አሳጥሮ “ጆኒ፣ ጂሚ፣ ሬይ” ብሎ ማቆላመጥ ቀስ በቀስ ወደ ታሪክ መዘክርነት እንዳያዘግም በብርቱ መምከር ይዘዋል።

 የሥነ ጋብቻ ጠበብት እንደሚሉት ባልና ሚስት የሚጠቀሙባቸው የቁልምጫ አጠራሮች መልካቸውን ለወጥ ሲያደርጉ በባል ወይም በሚስት ላይ አንድ የሆነ ነገር መኖሩን ይጠቁማል። አቆላምጦ መሳደብ ወይም ደግሞ “ፍቅሬ” ብሎ ወዲያው “የትአባክ” ማለቱ አስቸጋሪ ስለሚሆን የቁልምጫ አጠራር የንትርክ በር ለማጥበብ እንደሚችል በሰሎች ያስረዳሉ፡:

“አቶ” እና “ወይዘሮ” በመባባል አንዱ ሌላውን የትዳር ጓደኛ የሚጠራው በክብር ስሙ ከሆነ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ፍቅር ነው ብለው ሊሟገቱለት ቢቃጡም አንዱ ቅያሜ ቢኖረው ሌላው ፈጥኖ ለማወቅ ያለው ዕድል የተመጠነ ነው። በቁልምጫ የሚጠራሩ ቢሆን ግን ቁልምጫው ሲቀር ኩርፊያው ብቅ ይላል። ያኔ ታወቀ ማለት ነው። አጠራር የኩርፊያ ሲግናል ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በጭውውቱም ወቅት ባለ ሰፊ ድርሻ መሆኑን ሊቃውንት ይናገራሉ።

ከዘመኑ ሥልጣኔ የተነሣ የሰዎችን ንቃተ ሕሊና መዳበር የተመለከተና ራሱን ከውዳሴ ከንቱ ያነፃው ሁሉ ምስጉን ይሁንና በሀገራችን ወደ ኋላ መለስ ብለን የነበረውን የባልና የሚስት ዐጠራር ሁኔታ ብንመረምር “አቶ ጌቶች” ተብለው እርስዎ ተብለው ሚስት ደግሞ (ዕድለኛ ከሆነች) “የማሞ እናት” ነበር። አሁንም ገና አልጠፋም። ይሁንና ይህን መሰሉ አጠራር የማለፊያ ግንኙነት ምስክር እንዳልሆነ እንረዳለን።

 ባልና ሚስት በፍቅር የተዋሀዱ አንድ አካል መሆናቸው አሌ የማይባል ሆኖ ሳለ የፍቅረኛን ፍቅር ከወንድማማችና ከዘመድ ፍቅር ጋር ለማሰተካከል የሚሹ ዘመናይ “የባል ጋሼዎች” አሉ። ቁም ነገሩ “ጋሼ” ማለቱ ላይ አይደለም። ከፍቅረኛ ጋር የሚፈጸመው ጉዳይ ሁሉ ከሌላ ዘመድና ወዳጅ ጋር ከሚወጠነው መርሐ ግብር የተለየ ይዘት ስላለው ሌላው በጅምላ የሚጠራበትን ለፍቅረኛም ደርሶ መስጠቱ አጠራሩ የፍቅረኝነት ዓይነተኛ ማስረጃ ሊሆን መብቃቱ በጣም ያጠራጥራል።

 ወላጆች ያወጡለትን ስም እንዳለ ያለአንዳች ቁልምጫ ወይም ማጣፈጫ በደረቁ ወስዶ ፍቅረኛን መጥራት የባልንጀርነትን መልክ ሲያሳይ የፍቅር ጓደኝነትን ባሕሪይ እጅግም አይዝም። ለፍቅረኞች ብቻ የተፈቀደ ለሌላ የተከለከለ ልዩ አጠራር ይመረጣል።

 ባሕር ማዶኞች “ዳድ፣ ማም” በመባባል የሚሞጋገሱት የማሞ “አባት” ወይም “የማሞ እናት” ከሚለው የአጠራር ፈሊጥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ብሎም ቢሆን ይህን መሰሉ አጠራር የጎጆው ዋስትና ፍቅር ብቻ መሆኑ ቀርቶ የልጅንም በጠለፋ ዋስትና መቅረብ የሚነግር ስለሆነ አጠራሩ በብርቱ አይደገፍም።

እንደ ቋንቋውና እንደ እነዋወሩ ባህል የአጠራር ፈሊጥም ከሀገር ሀገር የተለያየ ነው። የራሳቸውን ቋንቋ ባሕሉን ተከትለው ማደርጀት ተስኗቸው ፍቅረኛቸውን በሰው ሀገር ቋንቋ ለማነጋገር የሚመኙ ከተሜዎች ጥቂት አይደሉም። ይህም በሦስተኛው ዓለም ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በአውሮፓም የሚሰማ ነው። ለምሳሌ ጥቂት ቆርፈድፈድ ከሚለው ጀርመንኛ ይልቅ ለስላሳ በሆነው በወዛሙ ፍራንሣዊኛ ቋንቋ ፍቅረኛቸውን የሚጠሩ አሉ። ቋንቋ አዳቅለው ያለሰለሱም ብዙ ናቸው።

 አማርኛችንን ለምሳሌ ያህል ብንወስድ አዳብሮ መስመር ማስያዝ ብቻ ይቀረን እንደሆነ ነው እንጂ ለዛ ያላቸው ቃላት ሞልተውበታል። የኪነት ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ማለፊያ ቃላት ከመድረኩ ወጥተው ወደ ፍቅረኞች አምባ ሳይዘልቁ በጭራ ግርፍና በመዘምራኑ አንደበት ብቻ ተወስነው የቀሩ ይመስላል። ይህ አሳዛኝ ነው።

 ቀደም ሲል እንዳተትኩት የባህልና የቋንቋ ልዩነት የየሀገሩን የፍቅረኛ አጠራር ፈሊጥ ስለሚገድብ ፈረንጆቹ “ዳርሊንግ፣ ስዊት ኸርት፣ ሐኒ” ያሉትን ተርጉሞ “ማሬ፣ ስኳሬ” ብሎ ለማቆላመጥ መሞከሩ ስሜት ላይሰጥ ይችላል ወይም የአሽዋፊነት ባሕርይ የሰረፀበት ይመስል ይሆናል። የስሜት ነገር ከተነሣ ዘንድ የራሴን አስተሳሰብ ከአማርኛነቱ ጋር አዛምጄ ገለጽኩት እንጂ ምናልባት ሲለመድ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችልም ይሆናል።

 ይሁንና በየወቅቱ በከያንያን አንደበት የሚዜምባቸው እንደ “ሰውነት፣ አካላት፣ ገላ ሰው፣ ፍቅሬ፣ ውዴ—” ያሉት ማለፊያ ቋንቋዎች ለፍቅረኛ መጠሪያነት ቢወሰዱና ቢለመዱ መስተፋቅርነታቸው የሚናቅ አይመስለኝም። “የምወድህ፣ የምወድሽ” መባባሉም ፍቅርን አደርጅቶ የጋብቻውን መዋቅር በእጅጉ ጽኑ እንደሚያደርገው አንድና ሁለት የለውም።

 ግና እነዚህ ወርቃማ ቋንቋዎች ከልብ ለሚናፈቀው፣ ከአንጀት ለሚፈቀረው ሲውሉ ነው እንጂ በየቀኑ ለተለያየ ፍቅረኛ ወይም ድርብ ወዳጅ እየተመጠኑ በመቁነን ሲታደሉ ማየት ክቡሩን ፍቅር ርኩስ፣ ፍቅረኛን ኩንን ያደርጋቸዋል። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top