የጉዞ ማስታወሻ

ከኖርዌይ ወዳጆቼ ትዝታ

ኖርዌይ ውስጥ ባሳለፍኳቸው ሁለት አሠርትን የዘለሉ ዓመታት ውስጥ፤ ከሕጻናት እስከ ጎምቱ አዛውንቶች ድረስ፤ ብዙ ወዳጆችን አፍርቻለሁ። የሰው ልጅ ባሕሪይና ተፈጥሮ የተለያየ እንደመሆኑም፤ የተለያዩ ባሕሪያትና ተፈጥሮ ያላቸው ኖርዌጂያን የሥራ ባልደረቦች፣ ወዳጆችና ጎረቤቶች ገጥመውኛል። አንዳንዶች ቀኑን ሙሉ ከሰው ጋር ምንም ዓይነት ንግግር ሳያደርጉ ሥራቸውን አከናውነው የማታ ማታ ወደ ቤታቸው የሚሄዱ ናቸው። ከጸጥታቸው ውስጥ የሚወጣው ውስጥን ሰርስሮ ገብቶ የሚመረምር የሚመስል እይታቸው ዘወትር ከሕሊናችሁ አይጠፋም። አንዳንዶች ደግሞ ሥራቸውን በመሰልቸትና በግዴለሽነት አስሬ ቡና እያፈሉ የሚጠጡ፣ ሲጋራ የሚያጨሱ፣ ከቢሮ በረህ ውጣ ውጣ የሚላቸውና ወግ መጠረቅ የሚቀናቸው ናቸው። ለሥራው ትኩረት ለሚሰጥ ሰውም በጎ አመለካከት የላቸውም። ‹‹በምሳ እረፍት ጊዜ ማረፍ ሲገባው፣ ሥራ ይሠራል›› ብለው የሚከሱም ገጥመውኛል።

ሌሎች በኮንስትራክሽን መስክ የተሰማሩ የሥራ ጀግኖች ደግሞ፣ በክፉው የኖርዌጂያን ቀዝቃዛ ክረምት ውስጥ፣ የእጆቻቸውን ጣቶች ጫፎች የማይሸፍኑ የሥራ ጓንቶች ብቻ አጥልቀው፣ ስምንት ሰዓት ሙሉ ከጅምር ሕንጻ ላይ ተንጠልጥለው ሲሠሩ ታገኟቸዋላችሁ። ባንጻሩ ደግሞ እዚሁ እኛ አገር ውስጥ ባዲስ አበባ መንገዶች ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች አካፋና ዶማቸው ላይ ተቀምጠውና ተደግፈው፣ ወሬ ሲጠርቁና ፀሀይ ሲሞቁ እያስተዋላችሁ ታዝናላችሁ። በበጋው መጠናቀቅ የነበረበት የመንገድ ሥራ ክረምቱ ገብቶ ግንባታው ሲቆም፤ እንኳን ተሽከርካሪና እግረኛም መሄጃ አጥቶ ሲሰቃይ የመንገድ ሠራተኞቹ ይስቃሉ። አቅም የለም እንጂ እኒህን አይነት ዋልጌዎች ወደ ምእራቡ ዓለም ወስዶ፣ ሥራ እንደምን በትጋት እንደሚሠራ አሳይቶ መመለስ ነበር።

 ከኖርዌጂያን በጎ ባሕል አንዱ የራስን መኖሪያ ቤት በራስ እጅ መሥራት፣ መጠገን፣ መንከባከብና ግቢን ማሳመር ነው። አንድ ጎበዝ ወዳጄና ጎረቤቴ የነበረ ሰው፣ በሰፊ ግቢው ውስጥ አንድ ተጨማሪ ቪላ ቤት እንደዋዛ ሠርቶ የጨረሰው በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር። ለማስመረቂያው አባቱ ያደነውን ኤልግ የተሰኘ ግማሽ ያውሬነት ግማሽ የቀንድ ከብትነት ተፈጥሮ ያለውን እንስሳ ሥጋ ጠብሶና ቀቅሎ እኔና ቤተሰቤን በክብር ጋብዞ እንዳበላንም አስታውሳለሁ። እዚህ እኛ አገር ውስጥ ግን ብዙዎቻችን የዘመመ አጥራችንን ለማቃናት አናጺ ፍለጋ እንሮጣለን። ይህ መቀየር ያለበት ባህል ነው።

 አንዳንድ ኖርዌጂያን ወዳጆቼ ደግሞ ሁለት ዓይነት ተፈጥሮ ያላቸው ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ሰናይና እኩይ ባሕሪያትን የተላበሱ ማለቴ ነው። ባንድ በኩል እቤታቸው ድረስ ጋብዘው አብልተው አጠጥተው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ይሄንን የመሰለ ቪላ ቤት፣ መኪና ወዘተ… ለምን ትገዛለህ? አንተኮ ስደተኛ ስለሆንክ ነገ ወደ አገርህ ተመላሽ ነህና ቋሚ ንብረት አታፍራ›› ብለው ፍጥጥ ያለ አተካሮ ውስጥ የሚገቡ ገጥመውኛል። በዚሁ አንጻር ደግሞ ሌሎች ብርታቴና ጥንካሬዬ እንደሚያኮራቸው፣ ጉርብትናዬም ከሌሎች ያገራቸው ልጆች ይልቅ እንደሚያስደስታቸው፤ አልፎ ተርፎም ሕጻናት ልጆቻቸው ከልጆቼ ጋር ተመሳስለው እንዲያድጉላቸው አዘውትረው ወደ ቤቴ የሚልኩ መልካም ሰዎች ገጥመውኛል።

ኡለ ማርቲን ይባል የነበረው ህጻንማ ከሦስት ዓመት እድሜው ጀምሮ እኔን እንደ አጎቱ እያየኝ የበላነውን እየበላ፣ የጠጣነውን እየጠጣ በቤታችን ያደገ ነው። የ12 ዓመቱ ልጄ ናትናዔል ከእህቶቹ በተማረው የእንጀራ መጋገር ጥበብ ሲራቀቅበት ኡለ ማርቲን ቆሞ በደስታ ያስተውለዋል። መጨረሻ ላይም ባገራችን ወግ መሠረት በቀረው እንጥፍጣፊ ሊጥ እንጎቻ ሲጋግር የኡለ ማርቲንን የፊት ቅርጽ አስመሰሎ በመጋገር እያስደሰተው አብረን ኑረናል። ኡለ ማርቲን እንጎቻው ላይ በርበሬ ተነስንሶለት እየተደሰተ ሲበላ፣ የሌሎችን ወስፋት ይከፍታል። ባንጻሩ ደግሞ እንኳን ቤታችን መጥተው ሊጋበዙና ሊቀላቀሉ ቀርቶ፤ በዘረኝነት ሰይጣናዊ መንፈስ ተለክፈው የእግዜር ሰላምታም ነፍገውን ካንድ አሠርት በላይ በጉርብትና የኖሩም ነበር። በነገራችን ላይ ኖርዌጂያኖች የሰው ልጅ የበላውን ማናቸውንም ዓይነት ምግብ ሁሉ ደፍረው በመብላት ጋባዦቻቸውን የሚያስደስቱ ሰዎች ናቸው። ለዚህም ነው በመኖሪያ ቤቴ በተደረገ የልጄ የዩኒቨርሲቲ ምረቃ ግብዣ ላይ ለዓይነት ቀርቦ የነበረውን የጥሬ ሥጋ ግብዣ፣ ባዋዜና በሚጥሚጣ እየለወሱ፤ ከእኛ ከሃበሾች እኩል እንክት አድርገው የበሉት።

 ወደ ሌላው ዓይነት ወዳጄ ደግሞ ልውሰዳችሁ። አባት አርበኛ ኢዩጂን ጉንደርሰን ይባላሉ። የ80 ዓመት የእድሜ ባለጸጋና የሻምበልነት ማእረግ ያላቸው ናቸው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጸረ ናዚ ጎራ ተሰልፈው ላገራቸው ለኖርዌይ የተዋጉ ናቸው። በጦር ግምባሮች ለአሥር ዓመታት የቆዩ ሲሆኑ፣ ቀኝ እግራቸው ላይ በደረሰባቸው የመቁሰል አደጋ እስከ ዛሬ ድረስ ያነክሳሉ። ለመንቀሳቀስ ይረዳቸው ዘንድ ባለ አራት እግር ተሸከርካሪ ምርኩዝ ይጠቀማሉ።

 አርበኛው ኢዩጂን በነዚያ መራራ የጦርነት ዘመናት ካውሮፓ አልፈው፤ በጃፓን ሂሮሺማ፣ ቶኪዮና ዮኮሃማ ከናዚ አጋሮቹ ጃፓኖች ጋር ተፋልመዋል። ብዙ ጓደኞቻቸውን እንዳጡና ጦርነቱም የሰው ልጅ እንደቅጠል የረገፈበት ክፉ ወቅት እንደነበር በሃዘን ያስታውሱታል። እኚህ ሰው አገራቸውን በቁርጠኝነት በማገልገላቸው፣ ከጦርነቱ በኋላ ተገቢው እንክብካቤና ክብር ይደረግላቸዋል። በየክብረ በዓላቱና በየሸንጎው ይጋበዛሉ።

አባት አርበኛው ሁለቴ አግብተው፣ ከሁለተኛዪቱ ሟች ባለቤታቸው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል። ዛሬ ሕይወትን በብቸኝነት የሚመሩ ናቸው። ማንግለ ሩድ በሚባለው የኦስሎ ከተማ ክፍል በጉርብትና አብረን ነው የምንኖረው። ታዲያ እሳቸውን ከሌሎቹ ለየት የሚያደርጋቸው ጸባያቸው እጅግ ሲበዛ ሰላምተኛ መሆናቸው ነው። ወደ ማንግለ ሩድ የገበያ ማእከል ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ብቅ ያለ ሰው ኢዩጂንን አያጣቸውም። ጠዋት ከቤታቸው እንደወጡ የሚያመሩት ወደዚያው ነው። ልክ የጋሼ ስብሃት ገብረ እግዚአብሄር ፍጡር የሆኑት አጋፋሪ እንደሻው በማለዳ ተነስተው፣ በቅሏቸውን እያሰገሩና በየመንደሩ እየዞሩ የታመመና የሞተ እንዳለ እንደሚጠይቁት ሁሉ፣ አባት አርበኛውም ተመሳሳይ ተግባር ይፈጽማሉ። በዚያ በማንግለ ሩድ የገበያ ማእከል ውስጥ የሚገኙትን ከሃምሳ በላይ ባለመደብሮች እየዞሩ፤ ‹‹እንደምን ውላችሁ አድራችኋል? እከሊት ተሸላት? እከሌ እንደምን ሆነ?›› እያሉ እየዞሩ ይጠይቃሉ። ሁሉንም ካዳረሱ በኋላ፣ በቀጥታ ወደለመዱትና ጓደኞቻቸውን ወደሚያገኙበት ካፌ ያመራሉ። እኔንም እዚያ ነው የሚያገኙኝ። ወዲያው እንዳዩኝም፤ ‹‹የቄሳር ልጅ እንደምነህ?… እንዴት አደርክ?…›› ማለታቸውን አይረሱም። እኔም በሞቀ የወዳጅነት ስሜት ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ አጸፋውን እመልሳለሁ። በኖርዌጂያንኛ ቋንቋ ‹‹KEISER – ቄሳር›› ማለት ‹‹ጃንሆይ ወይም ንጉሥ›› ማለት ነው።

 ኢትዮጵያዊ መሆኔን ካወቁበት ቀን ጀምሮ፤ ባዩኝ ቁጥር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ያስታውሷቸዋል። ‹‹ የቄሳር ልጅ›› እያሉ እኔን መጥራታቸውም ሰበቡ ይሄው ነው። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እ.አ.አ. በ1952 ዓ.ም. ኖርዌይን ሲጎበኙ ያስታውሷቸዋል። በተጨማሪም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የኖርዌዩ ንጉስ ኡላቭ በስደት እንግሊዝ አገር በሚኖሩበት ጊዜ በጣም የሚቀራረቡ ጓደኛሞች እንደነበሩ እውቀቱ አላቸው። ሁለቱም አገሮቻቸውን የያዙት ወራሪ ኃይላት (ኢትዮጵያን ኢጣሊያ ኖርዌይን ጀርመን) ከተባረሩላቸው በኋላ፤ የሚጠያየቁ የክፉ ቀን ጓደኛሞች ሆነዋል። ጃንሆይ ኖርዌይን በጎበኙበት ሰዓት፣ አገሪቱ በጦርነትና በእጦት ኢኮኖሚዋ የደቀቀበት ሰዓት ስለነበር፤ ኢትጵያ ለኖርዌይ 50 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እርዳታ አድርጋላታለች። ዛሬ ግን ኖርዌይ የነዳጅ ድፍድፍ ከሚያመርቱ ቱጃር አገሮች መካከል በመጀመሪያው መስመር ተርታ ላይ ትገኛለች። ጃንሆይ የኦስሎ ማዘጋጃ ቤትን በጎበኙበት እለት ለከንቲባው ያበረከቱት የወርቅ ጋሻና ጦር እስከ ዛሬ ድረስ ለጎብኝዎች በግልጽ ቦታ ተቀምጦ በመታየት ላይ ይገኛል።

 ንጉሥ ኡላቭም እ.አ.አ. በ1966 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በመጎብኘት አጸፋዊ ምላሽ ሰጥተዋል። የንጉሥ ኡላቭ የኢትዮጵያ ጉብኝት እጅግ የደመቀና የሁለቱን ሕዝቦች ወዳጅነት ያበረታ እንደነበር፣ ኖርዌጂያዊው የታሪክ ጸሐፊ ኮሬ ፔተርሰን፣ “ETIOPIA Dronningen av Sabas Land… (ኢትዮጵያ – የንግሥት ሣባ አገር)” በሚል ርእስ እ.አ.አ. በ1967 ዓ.ም. ባሳተመው መጽሐፉ ላይ ገልጾታል። ደራሲ ኮሬ ከንጉስ ኡላቭ ጋር ተከትሎ የመጣ ስለነበር፤ እያንዳንዱን የንጉሱን ጉብኝትና የኢትየጵያ ቆይታ በ171 ገጽ መፅሐፉ ላይ ገልጾታል። በዚህ በፎቶግራፍ የተደገፈ መጽሐፉ፤ የመጡበት አውሮፕላን የኢትዮጵያን መሬት ከመርገጡ በፊት ስምንት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች ልዩ ልዩ ያየር ላይ ትርኢቶች እያሳዩ እንዳጀቧቸው ኮሬ ባድናቆት ጽፏል።

 ወደ አባት አርበኛው ጉዳይ ልመለስና ጉዳዬን ልቋጭ። ጡረተኛው ኢዩጂን በካፌው ውስጥ የሚቀመጡበት የተለመደ ስፍራ አላቸው። በስተቀኝ በኩል እጫፍ ላይ ሁሉንም ጓደኞቻቸውን አጥርተው የሚያዩበት ወንበር ላይ ይቀመጣሉ። ልባዊ ሰላምታቸውን ለሁሉም ካርከፈከፉ በኋላ ቡና ያዛሉ። ሁሉም ቡና ጠጪዎች ናቸው። እንደኛ አገር ገሚሱ ቡና፣ ገሚሱ ሻይ፣ ገሚሱ ቢራ ወይ አልኮል ባዘቦት የሥራ ቀናት በኖርዌጂያን ዘንድ አይጠጣም። ነውር ነው። ቢራና አልኮል መጠጣት የፈለገ ሰው አምስቱ የሥራ ቀናት አልቀው አርብ ማታና ቅዳሜ ማታ ነው ድብን እስኪሉ ድረስ የሚጠጡት። እና ኢዩጂን ጓደኞቻቸው ዘንድ በተቀላቀሉበት ሰዓት፤ ሁሉም ጓደኞቻቸውና የኔ ቢጤ ወዳጆቻቸው ሁሉ በእለቱ ጋዜጦች ንባብ ላይ ስለሚመሰጡ፤ እሳቸውም አንዱን ጋዜጣ ሳብ አድርገው፤ ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› እያሉ የተገዘጠውን መኮምኮም ይጀምራሉ። አንዱን ጋዜጣ ሲጨርሱ ወደ ሌላው መሸጋገርና የወሬ ቋቱን ሁሉ አራግፈው ማወቅ የኖርዌጂያኖች የየእለቱ ሱስ ነው። ዩኔስኮ በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት ከዓለማችን ሕዝቦች እጅግ አንባቢዎች እያለ የሚያመላክታቸው እነሱን ነው። ይህም በተሟላ የኑሮ ደረጃ ምቾትም ብዙ ጊዜ አንደኞች እየተባሉ እንደሚመረጡት ሁሉ ማለት ነው።

 የጋዜጣና የመጽሔት ንባቡ ቆይታ ከተገባደደ በኋላ ባነበቡት ጭብጥ ዙሪያ መወያየትና መተቸት ይቀጥላል። ክርክር አይቀሬ ነው። ጸብ ግን የለም። አንዱ ያንዱን አስተያየት አልቀበል ካለ የራሱን አቋም ገልጾ አደብ ይገዛል እንጂ ጸብ የለም። መደማመጥና መቻቻልን እንደ ጥሩ ባሕላቸው አድርገው አሳድገውታል።

አባት አርበኛው ወዳጄ ኢዩጂን ሁሌም ወደ ገበያ ማእከሉ ብቅ ሲሉ በፊልድ ጃኬታቸው ላይ በደረደሯቸው ሜዳሊያዎች፣ ምልክቶችና አርማዎች አሸብርቀው ነው። ይህ ያለባበስ ልማዳችው ከአራት አሠርት በላይ የዘለቀ ነው። ፊልድ ጃኬቱ አርጅቶ ሲነትብ ብቻ ነው ባዲስ የሚተካው። የ12 የጦር ሜዳ ሜዳሊያና የስምንት ኒሻን ተሸላሚ ጀግና ናቸው። ‹‹ሜዳሊያና ኒሻን ከደረት ላይ አርፎ ዘወትር መታየት አለበት እንጂ፤ እሳጥን ውስጥ ተቀምጦ መሻገት የለበትም›› ይላሉ ሌሎችን ሲመክሩ። ሁሌም የሚያነሷቸው የጫወታ ርእሶችና ቁም ነገሮች መሬት ጠብ የሚሉ አይደሉም። ኢዩጂን ከካፌው ውስጥ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን አንብበው፣ ቡናቸውን ደጋግመው ጠጥተው ከተጨዋወቱ በኋላ ወደ ምግብ መደብር ያቀናሉ። ዳቦ፣ ዓሣ፣ ሥጋ፣ አትክልቶች፣ ቢራና የመሳሰሉትን ከገዛዙና ከዚያች ባለ አራት እግር ምርኩዛቸው የሸራ ሳጥን ውስጥ ከቀረቀቡ በኋላ፣ እሷን እየገፉ ወደ ቤታቸው ያቀናሉ። እግረ መንገዳቸውንም ለሚያገኙት ሰው ሰላምታ መስጠታቸው አይቀሬ ነው። በኖርዌጂያኖች ዘንድ ያልተለመደውን ይህን የማያውቁትን ሰው ሰላም ማለት ብዙዎችን ፈገግ እያስደረጋቸው አጸፋውን እየሰጧቸው ያልፋሉ።

x ያርበኛው ኢዩጂን የየቀን ሕይወት ከዓመት እስካመት እንዲህ ሆኖ ይቀጥላል። አንዴም ሰለቸኝ ሲሉ አይደመጡም። ሁሌም አዲሱ ቀን አዲስ ሕይወት፣ ሰላምና ደስታን ይዞላቸው እንደሚመጣ በብርቱ የሚያምኑ ቅንና ደግ ሰው ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top