ጥበብ በታሪክ ገፅ

አክሮፖሊስ ለአቴንስ፣ ካፒታሊዩም ለሮም፣ “ፊንፊኔ” ለአዲስ አበባ

“አዲስ አበባ

የምትሀታዊ ንጽጽር ከተማ፣

ባንድፊት

የሥነ ህንፃ ብርቅዬዎች

ጣሪያዎችና ግድገዳዎች፣

በሌላ ፊት

ደሳሳ ጎጆዎች፣

ባንድፊት

በጭነት የደለቡ ትሬንታ ኳትሮዎች፣

በሌላ ፊት

ጦማጋ አህዮችና ጭሰኞች

ያለጫማ የሚሄዱ ሳዱላ ቆንጆዎች

ዘባተሌ የለበሱ ኩታራዎች፣

በሌላ ፊት

ባለ ነጭ ሸሚዝ ሕሳዊ ዘመነኞች

አዲስ አበባ

የጉዳጉድ ከተማ…”

(ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን)

ከአዲስ አበባ ምስረታ ጋር በተያያዘ ይታመንም አይታመን የዋና ከተማነቷን ‘ንግርት’ አንስቶ ማለፍ ያስፈልጋል:: የሮም፣ የአቴንስ፣ የሞስኮ፣ ወዘተ… ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም:: ይህንን በተመለከተ ያሬድ ገ/ሚካኤል እንደሚከተለው ይገልፃል:: “ሣህለ ሥላሴ ንጉሠ ሸዋ በጉራጌ አገር ይገኝ የነበረውን አሰን (አንጃቦ) የሚባለውን ባላባት ለማስገበር ዘምተው አስገብረው ሲመለሱ ‘ቱሉ ፊንፊኔ’ ላይ ሠፈር አድርገው ለሠራዊታቸው ግብር አብልተው ሲያበቁ፤ የዚች ከተማ ትልቅነት መንፈስ ተገልጾላቸው ‘በዚች ስፍራ የልጅ ልጄ ይነግሥባታል፤ ነጋሪት ይጎሰምባታል’ ብለው ትንቢት ተናግረው ነበርና የትንቢቱ ፍጻሜ በመድረሱ ይህች ስፍራ ለከተማነት ተመርጣ አዲስ አበባ ተባለች” ይሉናል:: በዛሬ ጊዜም ንግርት አልቀረም:: ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚንስትሩ ባደረጉት የበዓለ ሲመታችው ንግግር እናታቸው “ንጉሥ ትሆናለህ” ያሏአቸውን የልጅነት ትውስታ መናገራቸው እዚህ ላይ ያስታውሷል::

ከቱሉ ፊንፊኔ ጋር በጉልህ የሚነሳው ሌላው ስፍራ “ቢርቢርሳ” ነው:: ይህ ስፍራ ቢርቢርሳ ብቻ ሳይሆን “ማሪያም ጊፍቲ” ተብሎም ይታወቃል:: ቢርቢርሳ በኦሮሚኛ ዝግባ ማለት ነው:: ይህ ሥፍራ በአሁኑ ጊዜ ፒያሳ እንብርቱ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ይዞ ያለው አካባቢ እንደሆነ አባ ኤሚል ፋውቼ ፅፈውታል:: ሥፍራው የግራኝ አህመድ ጦር ወደ ሰሜን በሚዘምትበት ወቅት በቦታው የነበረውን ጥንታዊ ቤተክርስቲያን በማፍረስ ወደፊት ገሰገሰ:: ሁኔታው የሚያመለክተው በግራኝ ዘመን (በንጉሥ ኃይለመለኮት የግዛት ዘመን መሆኑ ነው)በአሁኑ ጊዜ አራዳ(ፒያሳ) ብለን በምንጠራው ሥፍራ ቤተክርስቲያንና ክርስቲያን አማኞች ይኖሩ እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል::

በወቅቱ የካቶሊክ እምነት ለማስፋፋት አባ ያዕቆብ የተባሉ አባት ምንም እንኳ ወደ ደቡብ የሃገሪቱ ክፍል ሄደው ክርስትናን ለማስፋፋት የፈለጉ ቢሆንም በፊንፊኔ ቆይታ አደረጉ:: ንጉሱ ወደ ነበሩበት ሊጨ በመጓዝም ለአጼ ምኒልክ ብርቢርሳ ለመቆየት መወሰናቸውን ነገሩአቸው:: ፍቃድም ጠየቁ፤ “እዚህ ስፍራ ለመቆየት ያነሳሳኝ ምክንያት በቦታው የሚገኙት ቆንጆ ዛፎች ብቻ ሳይሆኑ ከሁሉም በላይ የሳበኝ በግራኝ የወደመው የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ነው” ሲሉ መግለጻቸውን አስፍረዋል:: ምኒልክም ጥያቄውን በመቀበል በስፍራው ቤት እንዲሰሩና አነስተኛ ቤተ ክርስቲያን እንዲያቆሙ ፈቀዱላቸው:: አባ ያዕቆብ ብርቢርሳ የደረሱት ኦክቶበር 11 1868(እ. ኤ. አ) ነበር:: ለተወሰነ ጊዜም ፍልውሃ አካባቢ ወዳለው በአባ ኦቦ ጊቢ እንደኖሩ ታሪክ ያረጋግጣል:: በኦክቶበር መጨረሻ በ1868 አባ ፊርዲናድ የተባሉ ቄስ (አባ አትናቲዩስ ተብለውም ይታወቃሉ) ስፍራው ከደረሱ በኋላ የመጀመሪያው የቢርቢርሳ ቤተ ክርስቲያን የፍለጋ ቁፋሮ ተጀመረ:: ከብዙ ልፋትና ቁፋሮ በኋላ የጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን አቋም መታየት ጀመረ:: በሦስት ማዕከል የተከፋፈለ የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ህንፃ በጉልህ ተዋቅሮ ወጣ:: በወቅቱ እንደተመለከተው ያን መሰል የግንባታ ሁኔታ በአብሲኒያ እምብዛም የሚታወቅ አልነበረም:: የራሳቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የ“ቢርቢርሳዋን ማሪያም” ተክለው የአካባቢውን ሕዝብ ማስተማር በመጀመራቸው ባለውለታችን ናቸው::

ፊንፊኔ (ፍል ውሃ) ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአብዛኛው የቱለማ ጎሳ ንዑስ ክፍል የሆኑ የአቢቹና ገላን ጎሳዎች የሚኖሩበት ስፍራ ነበር:: አቢቹና ገላን እስከ 19ኛው ክ/ዘመን ድረሰ እርስ በርስ ይጋጩ ስለነበር የሸዋው ንጉስ ሳህለ ስላሴ ወደ ደቡብ ባደረገው መስፋፋት የአቢቹ ጎሳን በመደገፍ የፍልወሃን (ፊንፊኔ) አካባቢን በግዛቱ ሥር እንዳዋለ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢቶፒካ (አርታኢው Uhlig) ይገልፃል:: ለመጀመሪያ ጊዜ ፊንፈኔ የሚለውን ቃል በታሪክ ምንነት የተጠቀመው ተጓዡ ሌፌብሬ (Lefebvre) እንደነበር ይታወቃል::

 ለመጀመሪያ ጊዜ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ መጋቢት 1843(እ.ኤ.አ) ወደ ፊንፈኔ በመጓዝ በግራኝ አህመድ ጦር በፈረሰችው የጥንት ቤተክርስቲያን ሥፍራ(ታሪካዊ የክርስቲያን ግዛት በነበረችው) አዲስ ቤተክርሰቲያን ለማነፅ አቅዶ እንደነበር ሌፌብሬ (Lefebvre) ፅፏል:: ፊነፊኔ በሸዋ ሥር ከወደቀች በኋላ የቱለማ ንዑስ ጎሳ የሆነው የጉለሌ ኦሮሞ ብዙዎቹን ነባር ነዋሪ የሆኑትን የገላንና የአቢቹን ጎሳዎች ወደ ምስራቅና ወደ ደቡብ እንደገፈተሯቸው ዲ አብዲ በ1890 ፅፏል:: በዚያን ወቅት የታወቁት መንደሮች ጉለሌና መሪ ብቻ ነበሩ::

ቀደም ሲል በ1879(እ.ኤ.አ) አፄ ዮሐንስ ሚሲዮናውያን ከሥፍራው እነዲነሱ በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት “ቢርቢርሳ ማሪያም” አገልግሎትዋን አቋረጠች:: በኋላም በ1897(እ.ኤ.አ) ምኒልክ በሰጡት ትእዛዝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሆነው ገነተ-ፅጌ ቤተክርስቲያን በራስ መኮንን ገበዝነት ተገነባ:: በኋላም ዛሬ የምናየው ቤተክርስቲያን በዘመናዊ መልክ ከ1906-11(እ.ኤ.አ) እንደገና ቆመ::

 በርካታ በአገራችን ታሪክ ላይ የተጻፉ ድርሳናት በኢትዮዽያ የዘመናዊ ሥልጣኔ ጅማሬን ከዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጋር ያያይዙታል:: ምንም እንኳን የአገር ውስጥ ቅራኔዎች የነበሩና ከዛም የአድዋ ጦርነት የተከሰተ ቢሆንም በዚህ መሀል ንጉሠ ነገሥቱ የማይናቁ መሰረቶችን ጥለው አልፈዋል::

 የአዲስ አበባ ምስረታ በበርካታ ድርሳናት ውስጥ እንደተተነተነው የራሱ ልዩ የሆኑ ምክንያቶች አሉት:: ሆኖም መጀመሪያ ሀሳቡን የጠነሰሱት እቴጌ ጣይቱ መሆናቸው ተደጋግሞ የሚጠቀስ ጉዳይ ነው:: በተለይ ደግሞ የፍልውሀው መኖርና ውሀውም ፈዋሽነት አለው ተብሎ መታመኑ የእቴጌ ጣይቱን ቀልብ ስቧል:: እቴጌዋ ለቁርጥማት ህመማቸው ማስታገሻ ወደ ፊንፊኔ ይመላለሱ እንደነበር ይታወቃል:: እቴጌይቱ ቦታውን በመውደዳቸውና ለፈውስም ሲሉ አዲስ አበባን ሰይመው ከተሙባት::

 አክሮፖሊስ ለአቴንስ፣ ካፒታሊዩም ለሮም ከተማ የሆኑትን ያህል “ፊንፊኔ” ወይም “ፍልውሃ” ደግሞ ለአዲስ አበባ መቆርቆር መሰረትነት ትወሳለች። ፊንፊኔ የአዲስ አበባ ምስረታ እምብርት ነች። በወቅቱ ጋሪትሰን እንደጻፈው በነዋሪ ኦሮሞዎች ዘንድ “ቱሉ ፊንፊኔ” በሚል መጠሪያ የምትታወቀው ስፍራ ለምኒልክ ቤተ- መንግሥትነት ተመረጠች። ከዚያ ሥፈራ ነው ዛሬም ዶ/ር ዓብይ ኢትዮዽያን የሚዘውሯት:: አዲስ አበባን ተጭኖና ገዝፎ ከሚታየው የእንጦጦ ተራራ ቤተ-መንግሥት ይልቅ እቴጌ ጣይቱ ብጡል በፍልውሀ ተማረኩ። ይህም ለአዲስ አበባ መመስረት ፈር ቀዳጅ እርምጃ ሆነ። አዲስ አበባም የዘመናዊቷ ኢትዮዽያ እምብርት ሆነች።

አዲስ አበባ ከተመሰረተች በኋላ የአድዋው ድል ከአንድ አስርተ- ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመከናወኑ ለከተማዋ እድገት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። የተማረኩ የኢጣሊያ ወታደሮች በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በመንገድ ሥራዎች እንዲሰማሩ ተደረገ። ኤ.ቢ. ዋይልድ ከአድዋ ድል በኋላ አዲሰ አበባን ጎብኝቶ እንዳረጋገጠው በከተማዋ እድገት መታየቱን ገልጿል። መራብ ደግሞ ከ1889 እስከ1901 ዓ.ም ባለው የ12 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከተማዋ “እንደ እንጉዳይ ብቅ ብቅ” ብላ ነበር ሲል ገልጿል። ከዚያ በፊት የነበረውን የከተማዋን ገፅታ የኤርትራ አስተዳዳሪ የነበረው ማርቲኒ በፃፈው ማስታወሻ “አዲስ አበባ ከተማ አይደለችም፣ እንዲሁ የመንደሮች ስብስብ ናት” ማለቱን ጋርትሰን አስፍሯል።

በከተማዋ እድገት ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን መገንባትና ከቤተክርስቲያኑ በስተደቡብ በኩል የከተማው ገበያ እድገት መታየት ከቤተ-መንግሥቱ በተጨማሪም ከተማዋ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ መስፋቷን ያመለክታል። ከዚሁ ጋር የንጉሡ ታማኝ አሽከሮችና ባላባቶች ንጉሥ ተክለ ኃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ራስ ተሰማ፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ውቤ፣ ራስ አባተ፣ አፈ-ንጉስ ነሲቡ፣ ደጃዝማች ብሩ፣ ደጃዝማች ወሰን ሰገድ፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስና ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ የጦር ካምፓቸውን በመመስረታቸው ለከተማዋ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸው አልቀረም:: ከአድዋው ጦርነት በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመጡ አውሮፓውያን፣ አርመኖችና ሕንዶች (በአብዛኛው ነጋዴዎች) በከተማዋ የገበያ ሥፍራ ንግዳቸውን አቋቋሙ:: ይህ የንግድ እንቅስቃሴም የመሬት ዋጋና የቦታ ኪራይ እንዲጨምር ሲያደርግ በከተማዋ ሰሜን – ምሥራቅ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣሊያ፣ ሩሲያና ጀርመን ሌጋሲዮኖቻቸውን በማቋቋማቸው ከተማዋ እየደመቀች ሄደች:: ከተበታተኑ የጐጆ ቤቶች ስብስብነትና መንደርነት ተቀይራ የከተማን መልክ የሚያስይዙ ቤቶች ተሠሩባት:: መራብ ስለ አዲስ አበባ ስፋት ሁኔታ ሲገልጽ በ1910 (እ.ኤ.አ) በአንድ አቅጣጫ 7 ኪሎ ሜትር በሌላ ወገን ደግሞ 8 ኪሎ ሜትር ያህል በመስፋቱ የፓሪስን ከተማ እሩብ ትሆናለች ሲል አረጋግጡአል:: ሦስት ሚሊዮን ህዝብ ካላት ከፈረንሳይ ዋና ከተማ አንፃር ነዋሪዎቿ 100‚000 ቢደርሱ ነውም ብሏል::

 ንጉሡን የሚከተሉ አሽከሮች፣ ወታደሮች፣ ባለ እጆችና ሥራ ቤቶች ወደ 15‚000 የሚጠጉ ከመሆናቸውም በላይ ከተማዋ ይበልጥ በሰዎች የምትጨናነቀው ከተለያዩ ክፍለ – ሀገራት ባላባቶች ከነተከታዮቻቸው ስለሚመጡ ነበር:: ዱቸስኒ – ፎርኔት “ሚሽን ኢን ኢትኦፒ” በሚል ማስታወሻው እንዳሰፈረውና በኋላም በመቶ አለቃ ካላት በ1905 (እ.ኤ.አ) እንደተረጋገጠው እነዚህ ከየሀገሩ የሚመጡ ገዢዎች ወደ ከተማዋ ሲመጡ የሕዝቡ ብዛት ከ40‚000 ወይም ከ50‚000 አልፎ 100‚000 ወይም 150‚000 እንደሚያሻቅብ ገልጿል::

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ የተጀመሩ የግንባታ ሥራዎችና የመንገድ ጽዳት የጉልበት ሠራተኞችን በመፍጠራቸው ብዙ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ጐረፉ:: አብዛኛዎቹ የጉልበት ሠራተኞች ደግሞ የሚመጡት በምኒልክ ጦር ከተያዙት የደቡብ ክፍለሀገራት ነበር:: በአብዛኛው ከከተማዋ በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚኖሩ የጉራጌ ብሔረሰብ አባላት ለሥራ ወደ አዲስ አበባ ይገቡ ጀመር:: “በጉልበት ሥራና በአምራችነት” የሚታወቁት እነዚህ ዜጐች “በከተማዋ በጊዜያዊ ቤት ይጠለሉ ነበር” ሲል መራብ ይገልፃል::

በተጨማሪም ምኒልክ ወደ ደቡብ ባደረጉት የመስፋፋት ጦርነት ተይዘው የነበሩ የጦር ምርኮኞች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ተደርገዋል:: ቬንድርሄም እንደገለፀው በ1894 (እ.ኤ.አ) በተደረገው በወላይታ ዘመቻ ወቅት 96‚000 ምርኮኞች ተይዘው እንደመጡ ቢጠቅስም 20‚000 ምርኮኞች የሚለው አሀዝ ግን የበለጠ ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል:: እነዚህ ወደ ከተማዋ የመጡት የወላይታ ብሔረሰብ አባላት በአብዛኛው በከተማዋ የፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጓድና ምሽግ ሥራዎች ተሠማርተው አገልግለዋል:: በወቅቱ ወደ ከተማዋ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው በግለሰቦች ቤት ውስጥ ሲያገለግሉ ከነበሩት ውስጥ ከቤኒሻንጉል መጥተው የከተሙት 15‚000 ይደርሱ ነበር:: የቤንሻንጉል ነገር አንድ ነገር አስታወሰኝ፣ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምን:: ተክለማርያም መንግሥቱ እንደፃፈው ከሆነ “አዲስ አለም ስትተከል በአክሱም ፅዮን ማርያም ደረጃ ንቡረ ዕድ የሚሾምባት እንድትሆን አፄ ምኒልክ ባቀዱት መሠረት ሰፊ ድርጅት (ብዙ ጋሻ መሬቶች) ያላት እንድትሆን አድርገዋል:: ዳሩ ግን ቤተክርስቲያኒቷ የነበራትን ሰፊ ድርጅት የሚያስተዳድርና የሚጠብቅ የሰው ኃይል ይጠይቃል:: ንብረ ዕድ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት ቢያደርጉም በቂ የሰው ኃይል ሳይገኝ ይቀራል:: ስለሆነም በየዓመቱ ግብር ለማስገባት አፄ ምኒልክ ዘንድ ይመላለሱ የነበሩትን ሼህ ሁሴን ሆጄሌን (ሸጎሌ) ለጥበቃ ሥራ ከሠራዊታቸው እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ:: አምስት መቶ ያህል ሰው ይሰጧቸዋል:: የመንግሥቱ ኃ/ማርያም (የቀድሞው ኘሬዚደንት) ቅድመ አያትም በሼህ ሆጄሌ ለአዲስዓለም ማርያም ከተሰጡት አንዱ እንደነበሩ ነው” ሲል ያስታውሳል:: ወድጄ አይለም፣ ነገርን ነገር ያነሳዋል ብዬ ነው ይህን የጠቆምኩት:: ለኢትዮጵያዊ ማን ከማን እንደተዳቀለና ከዬት እንደመጣ ማወቅ ያስቸግራል፤ ሳፊ ሰው የለምና::

 እንቀጥል:: ከአዲስ አበባ ዙሪያ ደግሞ ምርታቸውን ለመሸጥ ሲሉ ወደ ከተማዋ ብዙ ዜጐች ጎረፉ:: ለከተማዋ ማኅበረሰብ የሚሆን የምግብ ሸቀጦችን የሚሸጡት ጉራጌዎችና ኦሮሞዎች መሆናቸውን መራብ ይጠቅሳል:: ኦሮሞዎች የገበያውን ግማሽ ያህል ህዝብ ብዛት ያላቸው ሲሆን ጉራጌዎች ደግሞ ከኦሮሞ ገበሬዎች የተለያዩ ምርቶችን እየገዙ መልሰው በመሸጥና በጠንካራ ሠራተኛነታቸው ይታወቃሉ:: በአጠቃላይ የገበያውን የሕዝብ ብዛት የሚወክሉት ከኦሮሞዎችና ከጉራጌዎች በተጨማሪ አማሮች፣ አረቦች፣ ሕንዶች፣ አርመኖችና ግሪኮች ነበሩ ሲል መራብ ያረጋግጣል::

 የተለያዩ ፀሐፊት ማለትም እነ ኮላት፣ ማርሴል ኮኸን፤ ሲኪነር ሮዘንና ሲፓላ ስለ ከተማዋ ነዋሪ መጠን የተለያዩ የሕዝብ ብዛት ግምቶችን በወቅቱ ቢሰጡም ተአማኒነቱ ይበልጥ ያጋደለው መራብ (Impressions d’Ethiopie በሚለው መጽሐፍ) እንደሚከተለው ዘርዝሮ ያቀርባል ፡-

ኦጋሪትሰን እንደሚለው፣ በወቅቱ አማሮችና ትግሬዎች ከእርሻ ውጭ የጉልበት ሥራ መሥራትን እንደ አዋራጅ ሥራ ስለሚቆጥሩት በከተማዋ የጉልበት ሥራ ይበልጡኑ ተካፋይ የነበሩት ጉራጌዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሻንቅላዎች፣ ቤኒ – ሻንጉሎችና ወላይታዎች ናቸው:: ስለዚህ በከተማዋ ዋነኛ ዕድገት ላይ አሻራቸውን የጣሉት እነዚህ ሠራተኛ ብሔር – ብሔረሰቦች መሆናቸውን ዛሬ በኩራት መናገር ይቻላል::

ኦሮሞዎች                         20‚000

ሻንቅላዎች፣ ቤኒሻንጉሎች ወዘተ.      15‚500

ሽዋዎች                           15‚000

ወላይታዎች                         5‚000

አማሮች                            3‚500

ጉራጌዎች                           2‚500

ትግሬዎች                           1‚000

ጐጃሞች                             1‚500

ሌሎች (ሶማሌዎች፣ አፋሮች፣ ከፋዎች

ወዘተ.)                               3‚000

በጠቅላላ                             65‚000

በዕምነት አንፃር ደግሞ የከተማዋ ጥንቅር ሲታይ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማሮች አብላጫውን ቁጥር የያዙ ሲሆን በአነስተኛ ቁጥር ደረጃ እስላሞች፣ ዕምነት የለሾችና ካቶሊክ ክርስቲያኖች አዲስ አበባን መኖሪያቸውና መጠጊያቸው አድርገዋል::

በከተማዋ ውስጥ ሕዝቡ የሚገለገልበት ዋነኛው የአማርኛ ቋንቋ መሆኑን በጊዜው ስለነበረው የከተማ ሁኔታ የተለያዩ የታሪክ ሰዎች ያረጋግጣሉ:: ከአማርኛ ቀጥሎ ግን “አፋን ኦሮሞ” በሰፊው በከተማዋ የሚነገር ሲሆን የኦሮሞ ብሔር ባልሆኑ ነዋሪዎች ዘንድም ቋንቋው ለመግባቢያነት ይውል ነበር:: የተለያዩ ብሔረሰቦችም በኦፊሴል ባይሆንም በየማህበረሰባቸው ቋንቋቸውን ይጠቀማሉ:: በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ግን ዋናው የገበያ ቋንቋ አረቢኛ ሲሆን የተማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጐች ደግሞ በዋነኛነት ፈረንሳይኛ ቋንቋን ይጠቀማሉ:: ከፈረንሳይኛ ቀጥሎ ጣልያኖች ኤርትራን ይገዙ ስለነበረና በጣልያን ሚሲዮን አማካይነት ቋንቋው በመስፋፋቱ ጣልያንኛ ቋንቋም በከተማዋ ይዘወተራል:: በተጨማሪም በአውሮፓውያን የውጭ ዜጐች መካከል ደግሞ እንግሊዝኛ፣ ግሪክ፣ ጀርመንኛና የሩሲያ ቋንቋዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ጋርትሰን መራብን ጠቅሶ ጽፏል:: ዛሬም በአኗኗራችንና በመቀያየጣችን(በዘመኑ ቋንቋ በመጋመዳችን) የተለወጠ ነገር ያለ አይመስለኝም:: አዲስ አበባ የሁላችንም ናት:: መጠጊያችን ናት:: አንዱ ልዩ ጥቅም ፈላጊ፣ ሌላው ልዩ ጥቅም ሰጪ የሚሆን ማንም የለም:: የጋራ ጥቅም ነው ያለው:: ሞስኮ የሞስከቫይቶች እንደሆነችው ሁሉ፣ አዱ ገነትም የአዲስ አበቤዎች ናት:: አዲስ አበባን ቆርቁረው ያስረከቡን ተስማምተው ኖረውባታል:: ታሪክ ሰርተውባታል፤ የእነሱን ፈለግ ተከትለን ዓለማቀፍ የከተማ ደረጃ እንድትይዝ ከማድረግ ይልቅ አዲስ አበባ የማናት? እያልን እንደ ጀብራሬው የነገር ፋንዲያ አንፀዳዳ:: የዕውቁን የፖለቲካ ተንታኝና ፀሀፊ የዩሱፍ ያሲንን ቃል ልበደርና “አብረን ለመኖር የተፈረደብን ህዝቦች ነን” ያለውን አንርሳ:: አራት ነጥብ:: ስለዚህ፣ “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር የደናቁርት ጩኸት ከመሆን አያልፍም::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top