የታዛ ድምፆች

አበበ ቢቂላ በዘመን ትውስታ ውስጥ

ለመጨረሻ ጊዜ አንድ የማራቶን ውድድር በኦሎምፒክ ለመሳተፍ የፈለገው ሰው ልምምዱን ጠንክሮ እየሰራ ነው። እድሜው 41 ቢሆንም አሁንም ለውድድር ጠንካራና ብስለት ያለው ነው። ‹‹ደክሟል፤ ቀንሷል፤ አቋሙ ወርዷል›› ለሚሉት መልስ ሊሰጥ ፈልጓል። አድናቂዎቹ አሁንም በእርሱ ላይ ተስፋ አላቸው። ደግሞም ‹‹ተአምረኛ ነው›› ይላሉ። ማንም ባልጠበቀው ጊዜ ሮም ላይ በባዶ እግሩ አለምን አስደንቋል። በትርፍ አንጀት በሽታ ኦፕራሲዮን በሆነ በሁለት ሳምንት ቶኪዮ ላይ ማሸነፉ ልዩ ሰው ነው አስብሎታል። አሁንስ ያንን አስደናቂነቱን ለማሳየት ምን ያግደዋል? በእድሜ ተቀራራቢ የሆነው ማሞ በሙኒክ ኦሎምፒክ ስለሚሳተፍ እሱም ከጓደኛው ጋር አብሮ ይሮጣል።

 አበበ ቢቂላ ውስጡ ሀይለኛ እልህ አለ። ይሄ እልሁ ከተንቀሳቀሰ የሚችለው የለም። በቅርቡ ስፔይን ላይ አንድ ውድድር ሊያደርግ እቅድ ይዟል። ዛሬ እሁድ ነው። ነገና ሀሙስ ቀን ጠንካራ ልምምድ ያደርጋል። ከሸኖ ወደ አዲስ አበባ በዚሁ እሁድ ምሽት መኪናውን እየነዳ የሚመጣው አበበ ቢቂላ ወደ ቤቱ በሰላም አልደረሰም። በሚነዳት መኪና አደጋ ደረሰበትና ክፉኛ ተጎድቶ ሆስፒታል ገባ። ወዲያውኑ በአስቸኳይ ወደ እንግሊዝ ተላከ። አደጋው ከፍተኛ በመሆኑ ከወገቡ በታች ሰውነቱ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በጋሪ ለመጠቀም ተገደደ። በአበበ ላይ በደረሰው አደጋ ህዝቡ እጅግ አዘነ። በሙኒክ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ የነበረው ተስፋ እሁድ ምሽት ሸኖ መንገድ ላይ ተሰናከለ።

 አበበ የካሳ ተሰማን ሙዚቃ እጅግ ይወዳል። አንዳንዴ ወደ እሱ ይሄድና ‹‹ካሳ እስኪ ብርቱካኔ የሚለውን ዘፈን ተጫወትልኝ!!!!›› ሲለው ክራሩን ያነሳና ይከረክረዋል። እንደገናም ‹‹እልም አለ ባቡሩ›› በሚለው ዜማ ውስጥ አዲስ ግጥም ይጨምርና ‹‹አበበ ቢቂላ በሮም አደባባይ – ፈረንጁን አሳየው ስቃይ›› እያለ ማዜም ይጀምራል። አበበም ሳቅ ይልና ‹‹እሱን ተውና ብርቱካኔን… ›› ይለዋል። አበበና ካሳ የክብር ዘበኛ ወታደሮች ናቸው። ሁለቱ በደምብ የተዋወቁት በ1949 ዓ.ም አበበ በጦር ኃይሎች ውድድር በ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ ሆኖ በተመለሰበት ጊዜ ነበር። በነሐሴ 1952 ዓ.ም አበበ በሮም ኦሎምፒክ ለመሳተፍ በተዘጋጀበት ጊዜ ከካሳ ጋር ክብር ዘበኛ ግቢ ውስጥ ተገናኙ። አበበ ከጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ቢሮ ገብቶ ሲወጣ አገኘው። ሁለቱ ከተገናኙ የማይቋረጥ ወሬ ይጀምራሉ። ካሳ እየጠየቀው ነው።

‹‹ችግር አለ እንዴ?››

 ‹‹የለም››

‹‹አለቃችን ቢሮ እንዴት መጣህ?››

‹‹መመሪያ ለመቀበል ነው››

‹‹የምን መመሪያ?››

‹‹በኦሎምፒክ ስለማደርገው ውድድር››

‹‹ኦ!!!! ለካ ለእሱ ነው!››

‹‹አዎ››

‹‹እንዴት ነው ታዲያ የምሸኝህ?››

‹‹እንደተለመደው ነዋ!!!››

አበበ የካሳን ክራር ፈልጓል። መንፈሱን ያዝናናለታል። በምሳ ሰዓት ሊያደርጉት ፈልገዋል። ሰፊ ጊዜ ቢኖረው ሁለቱ የሚያውቁበት ቦታ ይሄዱና የልባቸውን እየተጫወቱ በካሳ ክራር ስሜቱን ጥግ ያደርሳል። ወደ ሮም አንድ ሰው ቢፈቀድለት ኖሮ ካሳ እንዲሄድ ይመርጥ ነበር። ካሳ አሁንም እየጠበቀው ነው ‹‹ምን አሰብክ ታዲያ?›› አለው።

‹‹ምኑን?››

‹‹ውድድሩን››

‹‹እግዚያብሄር ያውቃል››

‹‹እሱ ልክ ነህ። አንተ ግን ምን አሰብክ?››

‹‹ለማሸነፍ ነው››

‹‹ይሄን ለሌላ ሰው ነግረሃል?››

‹‹አልነገርኩም››

‹‹ይሄን ስትል ፈረንጆቹ ያምኑሃል?››

‹‹ሰዓቴ ጥሩ እንደሆነ ይድነቃቸው ነግሮኛል››

‹‹ስንት ሰው ነው የሚሮጠው?››

‹‹ብዙ ነው 50 … 60 … 70 ሊሆን ይችላል››

‹‹በኦሎምፒክ ሮጠህ አታውቅም። እንዴት ውጤት አገኛለሁ ብለህ አሰብክ?››

‹‹እኔ እኮ የክብር ዘበኛ ወታደር ነኝ››

‹‹ይሄ አባባልህ ያስማማናል። ለመሆኑ ስትሮጥ አይደክምህም?››

‹‹ይደክመኛል››

‹‹ፈረንጆቹስ ይደክማሉ?››

‹‹እነርሱም እኮ ሰው ናቸው››

‹‹ግን ፈረንጆቹ ይሸነፋሉ?››

‹‹ለምን አይሸነፉም››

‹‹ዘርአይ ደረስ በሮም ጀግንነት ፈጽሟል። አንተም ሌላ ዘርአይ እንደምትሆን ልጠብቅ?››

‹‹ጀግንነት ያለችው በሀበሻ ልብ ወስጥ ነው›› ካሳ በአበበ ቆራጥነት ደስ አለው።

‹‹ፋኖ ፋኖን እጫወትልሃለሁ›› አለው።

አበበ በሮም ውጤት ላያመጣ ቢችልም በልበሙሉነቱ አድንቆታል። ‹‹አበበ እንደሚያሸንፍ ነግሮኛል›› በሚል ካሳ ለጓደኞቹ አወራ። ጓደኞቹ ግን ፈረንጅ እንደማይሸነፍ አስረድተውት የአበበ ፉከራ ሜዳ ላይ እንደሚቀር ያሾፉበት ጀመር። ካሳ አበበን ቢወደውም ጓደኞቹ እርሱን ዝቅ አድርገው መመልከታቸው ደስ አላለውም። በዚህ የተነሳ ‹‹አበበ ያሸንፋል›› በሚል በእሱ ጉዳይ መከራከሩን ሳይገፋበት ቀረ። አበበ በሮም ማሸነፉን ሲሰማ ካሳ ‹‹እንደተናገረው አደረገው … ለካ ፈረንጆቹም ይሸነፋሉ›› አለ። አበበ ከሮም ሲመለስ ካሳ ሁሉንም አጫወተው። ካሳ አበበን አንድ ጥያቄ አነሳለት ‹‹ያን ጊዜ የነገርከኝ እውነትህን ነበር?›› አለ።

 ‹‹የቱ?››

‹‹ስትሄድ ውጤት አመጣለሁ ያልከኝ››

‹‹ሶስተኛ ወይም ሁለተኛ ለማለት…››

‹‹አንደኝነቱንስ?››

‹‹ብዙ ሰዎች ፈረንጆቹ ከባድ መሆናቸውን ስለነገሩኝ እርግጠኛ አልነበርኩም››

‹‹ እኔ ግን አንደኛ ይወጣል ብዬ ተከራከርኩ››

‹‹ከማን ጋር?››

‹‹ከጓደኞቼ››

‹‹አንተ ልክ ነህ፣ እኔ ግን አልነበርኩም››

‹‹እንዴት?››

‹‹እኔ ሮም ደርሼ፣ ሩጫው ከተጀመረ ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው እርግጠኛ የሆንኩት››

አንዳንድ ሰዎች አበበና ካሳ ወንድማማቾች ናቸው ይላሉ። በተለይ ሁለቱም የሀገር ባህል ልብስ ሲለብሱ መልካቸው፤ የቆዳቸው ቀለም፤ ቁመታቸው፤ ጸጉር አበጣጠራቸው ተመሳሳይ በመሆኑ ላያቸው በርግጥም አባባሉን እውነት ሊያስመስለው ይችላል። ነገር ግን ሁለቱም በእድሜ የሚቀራረቡ የክብር ዘበኛ ወታደሮች ናቸው። ሁለቱም በህዝብ ዘንድ ዝነኛ ናቸው። መስከረም 25 ቀን 1966 ዓ.ም የሃምሳ አለቃ ካሳ ታሞ በክብር ዘበኛ ሆስፒታል ገባ። አበበ በጋሪ እየታገዘ የጥንት ጓደኛውን ለመጠየቅ ሄደ። ካሳ ህመሙ በጣም ጸንቶበታል። ክራሩ አጠገቡ የለም። ክራር የሚመታበት እጁም አይታዘዝም። ያን የመሰለ ድምጽ የሚያወጣበት አንደበቱም እንደበፊቱ አይደለም። ካሳ አበበን እንደምንም እያናገረው ነው ‹‹ባለፈው ማሸነፍህን ሰማሁ›› አለው።

 ‹‹የት?››

‹‹ውጭ ሀገር››

‹‹አዎ››

‹‹አንተ ሁሌም ተዓምረኛ ነህ››

‹‹ቀስት እኮ ነው››

አበበ አካል ጉዳተኛም ሆኖ በቀስት ውድድር ውጭ ሄዶ በማሸነፉ ካሳ እያደነቀው ነው። አበበ በሩጫ ውድድር አሸንፎ ሲመጣ ካሳና ጓደኞቹ አቀባበል ያደርጉለታል። ከዚያም ካሳ ለአበበ ውደሳውን እየደረደረ ይዘፍናል። ግጥሙ ውስጥ የክብር ወታደር፤ የጠቅል አሽከር … የሚለው ስንኝ አይጠፋም። ዛሬ አበበ በጉዳት ካሳ በጤና ማጣት ሆስፒታል ውስጥ በሀዘን የትላንቱን እያስታወሱ በትዝታ ብቻ ቀርተዋል። መስከረም 29 አበበ እንደገና ሄዶ ጠየቀው። ጥቅምት አንድ ቀን ተመልሶ እንደሚመጣ ነገረው። አበበ ከቤት ሲወጣ ስልክ ተደወለለት። ወደ ሆስፒታል መሄድም አላስፈለገውም። ካሳ ከሆስፒታል መውጣቱ ተነገረው። አበበ ጋሪው ላይ ሆኖ በድንጋጤ ተክዞ እንባው ዱብ … ዱብ አለ። የሃምሳ አለቃ ከሳ ወደ ቤቱ የተወሰደው አስከሬኑ ነበር።

ካሳ ከተቀበረ ከሳምንት በኋላ ጥቅምት 10 ቀን 1966 ዓ.ም፣ አበበ ‹‹ሆዴን አቃጠለኝ ኧረ ድረሱልኝ!!!›› አለ። ወደ መኝታው ሄዶ ተኛ። ብዙ ጊዜ ረጅም እንቅልፍ ይወስደዋል። ቢያንስ 12 ሰዓት ሳይነሳ ይተኛል። የዚያን ቀንም ለ12 ሰዓት ተኛ ነገር ግን ቶሎ አልተነሳም። በሽታው በጣም ስለጠናበት በነጋታው ጥቅምት 11 ቀን ወደክብር ዘበኛ ሆስፒታል ተወሰደ። የሚገርመው አበበ የተኛው ከሳምንት በፊት ጓደኛው ካሳ ተሰማን በጠየቀበት ቦታ መሆኑ ነበር። አበበ በሽታው በጣም ጸናበት። ሰውነቱ ያተኩሳል። ህክምናው በተጠናከረ መንገድ እንዲሆን ሰባት ዶክተሮች ተመደቡለት። አበበ አይናገርም። በሽታው ምን እንደሆን ማስረዳት አይችልም፤ አይኑን አይገልጥም። የሚተነፍሰው አፍንጫው ላይ በተደረገ የኦክስጅን እቃ ነው። ማክሰኞ ጥቅምት 13 ጃንሆይ አበበን ሊጠይቁ ወደ ሆስፒታል ሄዱ። ያለበትን ሁኔታ ተመለከቱ። ከዶክተሮች ሁኔታውን ተረዱና ነገ በአስቸኳይ ወደ ለንደን ለከፍተኛ ህክምና እንዲሄድ ወሰኑ። ለንደን ላለው ቆንስላ አበበን ተቀብለው እንዲከታተሉ መልዕክት ተሰደደ። ረቡዕ ጥቅምት 14 አበበን ከሆስፒታል አውጥተው ለመውሰድ አልተቻለም። ወደ ለንደን የሚሄደው አውሮፕላን የዛሬ ጉዞውን ሰርዞ ለነገ አስተላለፈ። ዶክተሮቹ የአበበ በሽታ እያዳከመው በመሆኑ የበረራውን መሰረዝ ተቃወሙ። ሀሙስ ጥቅምት 15 ቀን ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ከሩብ አውሮፕላኑ ላይ እንዲገኝ አመቻቹ። ከአበበ ጋር አንድ ድሬሰርና ዩጎዝላቪያዊ ዶክተር አብረው ይጓዛሉ።

 ምሽት ላይ ዶክተሩ አበበን አየውና ወደ ቤቱ ሄደ። ጠዋት የጉዞ እቃውን ሻንጣውን ይዞ ተመለሰ። እግረ መንገዱን ክብር ዘበኛ ማዘዣ ቢሮ ደርሶ ተመለሰ። አለቆች በጊዜ ስላልገቡ አበበን ይዘው ወደ ኤርፖርት ሲሄዱ እግረ መንገዱን በዚህ እንደሚያልፍ አመቻቸ። ከዩጎዝላቪያው ዶክተር ጋር የሚጓዘው ድሬሰር የተመቻቸ ስትሬቸር አዘጋጀ። ገና በጠዋቱ ያለወትሮው ካፊያ እየጣለ ነበር። አንድ ሰዓት ከአስር ሲሆን ዶክተሩ አንዳንድ የህክምና እቃዎችን በቦርሳ ውስጥ ያጭቅ ነበር። 1 ሰዓት ከ30 ቢሮ ውስጥ ሆኖ የጉዞ ዶክመንቶችን አዘጋጀ። ድሬሰሩና ዶክተሩ ቢሮ ውስጥ ሆነው አበበ በኦሎምፒክ ስላመጣቸው ድሎች ይነጋገራሉ። አንድ ሰዓት ከ45 አንድ ጋዜጠኛ ስለ አበበ የለንደን ህክምና ሁኔታ መግለጫ ከዶክተሩ እየተቀበለ ነው።

 አውሮፕላን ማረፊያ ሶስት ሰዓት መድረስ ስላለባቸው አበበን ወደ መኪናው ውስጥ እንዲያስገቡ ዩጎዝላቪያዊው ዶክተሩ ትዕዛዝ ሰጠ። ይሄ ሁሉ ሲሆን ዩጎዝላቪያዊ ዶክተር ስለ ጉዞው ሁኔታ እንጅ ስለአበበ ወቅታዊ የጤንነት ደረጃ መረጃ አልነበረውም። ዶክተሩ ምሽት ላይ ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ አበበ ያለበትን ሁኔታ በሚገባ አያውቅም ነበር። አበበ አንዴ መለስ ይላል። ሌላ ጊዜ አስጊ ነገር ውስጥ ይገባል። ምሽት ላይ የተመደቡት ዶክተሮች ነቅተው እየጠበቁ ነበር። ነርሷ ስምንት ሰዓት ላይ ልቡ እየደከመ እንደሆነ ለሀኪሞቹ አሳወቀች። ተሰባሰቡና ተረባረቡ። ትንፋሹ ወደነበረበት በትንሹ ተመለሰ። 9 ሰዓት ላይ እንደገና ልቡ ደከመ። ከአንድ ሰዓት በኋላ እንደገና መለስ አለለት። በቦታው የነበሩ ዶክተሮች ተስፋቸው ነገ ጠዋት ወደ ለንደን በመሄድ የሚያደርገው ህክምና ነው። ዛሬ ቢሄድ ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር ብለው አሰቡ። ቀኑን ሙሉ በአውሮፕላኑ ጉዞ መሰረዝ ሲማረሩ ነበር። አስር ሰዓት ላይ እንደገና በሽታው አገረሸበት። ስድስት የሚሆኑ ዶክሮች ዙሪያውን ከበው መረባረብ ጀመሩ። ትንሽ መለስ ቢልም ተስፋ ያለው አልነበረም። እየቆየ ህሊናውን እየሳተ ነበር። ዶክተሮቹ የሚችሉትን ነገር እያደረጉ ነው። እንደገና በመሳሪያ እየታገዙ ተረባረቡ። ሆኖም አበበ እንዳመለጣቸው አወቁ። ዶክተሮቹ በሩን ዘጉ ይሄን ነገር ማወቅ ከሚገባቸው ሰዎች በስተቀር ለሌላ ሰው ለጊዜው ላለማሳወቅ ወሰኑ። በሌላኛው ክፍል ሆነው መምከር ጀመሩ። በጠዋት ለክብር ዘበኛ አዛዥ ስልክ ተደወለ። ሀኪሙ ነው።

 ‹‹ደህና አደሩ ጌታዬ!!!›› አለ

‹‹ደህና!! ለመሆኑ እንዴት ነው አበበ››

‹‹ምን አሉኝ?››

‹‹ለጉዞ ተዘጋጀ?››

‹‹የት?››

ዶክተሩ እንዴት አድርጎ እንደሚነግራቸው ግራ ገባው። አበበ የሞተው በእነርሱ የህክምና ብቃት ማነስ የሚል ግምት እንደማይኖራቸው ቢረዳም ይሄን እንዴት መግለጽ እንዳለበት ተቸግሯል። ጉዳዩን መጀመሪያ ለንጉሱ ማሳወቅ ፈልገው ነበር። ሆኖም ከተከራከሩ በኋላ ለንጉሱ ማሳወቅ ያለበት የክብር ዘበኛ ሀላፊ እንደሆነ ተስማሙበት። ሆኖም በስልክ ይሄን ከባድ ነገር እንዴት ነው የሚያስረዳው? አበበ በሮም አሸንፎ ሲመለስ ኤርፖርት በመሄድ ከተቀበሉት፤ ካጨበጨቡለትና ከተደነቁለት ሰዎች አንዱ ነበር። እሱም ቢሆን የአበበን መሞት ሊቀበለው ባይችልም ነገሩ ሆኗል። አለም በድንጋጤ የሚጠብቀው ወሬ የሚገኘው እዚህ ዶክተር እጅ ላይ ነው። እዚህ ክፍል ዝነኛው ካሳ ተሰማ ሞቶ ወሬውን ህዝቡ ሰምቶ አዝኗል። ዛሬ ደግሞ የበለጠ ሀዘን የሚሆነውን ወሬ ለማሰማት እየታገለ ነው። የክብር ዘበኛ ሀላፊ መስመር ላይ ናቸው ‹‹ሀሎ›› አሉ።

‹‹አቤት››

‹‹አበበ አልሄደም?››

‹‹አዎ››

‹‹ዛሬም በረራው ተሰረዘ እንዴ?››

‹‹አልተሰረዘም››

‹‹ታዲያ!!!……ችግርአለ?››

‹‹እንደሱ አይደለም…..››

ዶክተሩ ስለ አበበ ሞት መናገር አልቻለም። አዛዡ ልብሳቸውን አደረጉና ወደ ሆስፒታል መኪናቸው እየበረረ ደረሰ። ሁኔታውን ተረዱ። እዚያው ሆነው ለንጉሱ በስጋትና በፍራቻ ነገሩ። ንጉሱ ቢያዝኑም ለምን ትላንትና ሳይሄድ ቀረ በሚል ወቀሳ አቀረቡ። ጥቅምት 16 ቀን በ46 አመቱ ንጉሱ በተገኙበት ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሰው ባለበት ተቀበረ። ካሳ ተሰማን በ47 አመቱ ከሳምንት በፊት የሸኘው አበበ እሱም ተከትሎት ሄደ። እልም አለ ባቡሩ። ሁለቱም ዘመን የማይረሳቸው የክብር ዘበኛ ወታደሮች ናቸው።

“ቀኑን ሙሉ በአውሮፕላኑ ጉዞ መሰረዝ ሲማረሩ ነበር። አስር ሰዓት ላይ እንደገና በሽታው አገረሸበት። ስድስት የሚሆኑ ዶክሮች ዙሪያውን ከበው መረባረብ ጀመሩ”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top